ሁለቱም የግፍ እስረኞች ለ ታህሳስ 19 ተቀጠሩ
የባልደራስ ፓርቲ አባል የሆኑት የግፍ እስረኞች አቶ ካሱ ደስታና አቶ ናትናኤል ያለምዘውድ ዛሬ በአራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል። በዚህም መሰረት:-
በትናንትናው ዕለት (13/04/2015ዓ.ም) አቶ ካሳሁን ደስታ በአራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት መቅረባቸው ይታወሳል። ችሎቱም የፖሊስን መዝገብ ለመመርመር ለአዳር ቀጥሮ ነበር። ፖሊስ ባቀረበው መዝገብ የሶስት ሰዎች ቃል የተቀበለ መሆኑን ገልጿል።
ችሎቱ በትላንትናው እለት ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀናት የምርመራ ጊዜን እና የተከሳሽ ጠበቃን መቃወሚያ ከሰማ በኋላ ከትናንት ጀምሮ የሚቆጠሩ 6 ተጨማሪ ቀናትን ፈቅዷል። በዚህን መሰረት የግፍ እስረኛው አቶ ካሳሁን በታህሳስ 19/2015ዓ.ም ለ 8 ሰዐት ላይ ፍ/ቤት ይቀርባሉ።
በተያያዘ የሌላኛው የግፍ እስረኛ አቶ ናትናኤል የአለምዘውድን ክስ ፍርድ ቤቱ መልክቷል። ፖሊስ አቶ ናትናኤል ያለምዘውድ ከ10 እስከ15 የሚደርሱ ዩኒፎርም የለበሱ የአምሐ ደስታ ተማሪዎችን በትምህርት ቤቱ ደጃፍ ላይ በማነጋገር “የኦሮሚያ ባንዲራ ሲሰቀል ጩሁ እኛ ከእናንተ ጀርባ አለን ምንም የሚመጣ ነገር የለም” በማለት ተማሪዎችን ለፀብ ሲያነሳሳ እንደነበረ የምስክሮች ቃል ተቀብያለሁ ብሏል። በማከልም የተጨማሪ የሌሎች ምስክሮችን ቃል ለመቀበል እንዲሁም ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት መረጃዎችን እየጠበቅን ስለሆነ ተጠርጣሪው የባልደራስ ፓርቲ አባል በመሆናቸው መረጃዎችን የማጥፋት አቅም ስላላቸው ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድቤቱን ጠይቋል።
የተከሳሽ ጠበቃ አቶ ሔኖክ አክሊሉ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ለፖሊስ የተሰጠው 12 ቀን ለምርመራ ጊዜ ከበቂ በላይ እንደሆነ ለፍርድቤቱ ገልፀው የተከራከሩ ሲሆን በተጨማሪም ፖሊስ “ተከሳሽ የዋስ መብት ቢሰጣቸው የባልደራስ ፓርቲ አባል ስለሆኑ መረጃዎችን የማጥፋትና ምስክሮችን የማባበል አቅም አለው” ያለውን አንስተው ፥ባልደራስ ህጋዊ ፓርቲና በህግ ማእቀፍ ውስጥ የሚሰራ በመሆኑ ደንበኛዬ እንደውም የባልደራስ ፓርቲ አባል መሆናቸው ህግ አክባሪ ለመሆናቸው ምስክር ነው በማለት ለፍርድቤቱ ገልፀዋል ።
ፍርድቤቱም ግራ ቀኙን ከሰማ በኋላ ተጨማሪ አምስት ቀናት የምርመራ ጊዜ ሰጥቷል። በዚህም መሰረት የግፍ እስረኛው አቶ ናትናኤል በታህሳስ 19/2015 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዐት ላይ ከሌላው የግፍ እስረኛ ከአቶ ካሳሁን ደስታ ጋር እንዲቀርቡ ሲል አዟል።
ፍትህ ለግፍ እስረኞች!
ድል ለዲሞክራሲ!