የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ መርሃግብር
ሀገራችን ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ሀገረመንግስትነት ታሪኳ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት የሆነች፣ በአመዛኙ አኩሪ የታሪክ ውርስ ያላት፣ በሀገር በቀል እውቀት፣ በነጻነት ቀንዲልነት የተሽለመለመች ሀገር ናት፡፡ ይሁን እና ሀገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታ በከፍታ ከነበረችበት ማማ ጋር የማይሰናሰል ክፍተት መኖሩን ሚያመለክት ነው፡፡ የክፍተቱ ዋና ተጠያቂ ደግሞ የፖለቲካ ሥርዓታችን አለመስልጠን ነው፡፡ የፖለቲካ ሥርዓታችን የወቅቱን አስተሳሰብ ከሚመጥን የኃይል አገዛዝ ተላቆ ወደ ሰለጠነ ሥርዓት መሸጋገር ይገባው ከነበረ ብዙ አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ይሁን እና ከንጉሳዊው ሥርዓት ማብቃት በኋላ የፖለቲካ ሥርዓታችን ሁለንተናዊ ህዝባዊ ፍሬ እንዲያፈራ ተደጋጋሚ የሽግግር አጋጣሚዎችን የከሰተ ትግል ቢደረግም፣ ተፈላጊውን ፍሬ ማፍራት እንደተሳነው ቀጥሏል፡፡ ይባስ ብሎም፣ በአሁን ወቅት እንደ ሀገር የመቀጠል የህልውና ተግዳሮት፣ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ገጽታ ባለው ሁለንተናዊ አዘቅት ውስጥ ተዘፍቀን እንገኛለን፡፡
አዲስ አበባችንም የኢትዮጵያችን ልብ እንደመሆኗ፣ የሀገሪቱ ሁለንተናዊ ልእልናም ሆነ ህመም በዋናነት ነጸብራቁን የሚያሳርፍባት ናት፡፡
ሀገራችን በዋናነት በመንታ ስለት የፖለቲካ ሰንኮፍ እየተመተረች ትገኛለች፡፡ በአንድ በኩል ለዘመናት የታሪክ ፍሰት ንዑስ ማንነቶች የተዛነቁባት፣ የሀውርታዊ ንጥር መሆኗን ያላገናዘበ፣ ግለሰባዊነትን እና ዜግነትን የሻረ አገዛዝ ስር መውደቋ ነው፡፡አገዛዙ ኢትዮጵያ የተቀመረችበትን ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚዊ እና ማህበራዊ ውቅር ያላገናዘበ እውቅና እና የፖለቲካ ውክልና የነፈገ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ምንም እንኳን አገዛዙ ከግለሰባዊው ልዕልና ይልቅ ለቡድናዊው ማንነት ቅድሚያ እሰጣለሁ ቢልም፣ ለአዲስ አበባዊ ልዩ ውቅር እና ማንነት እውቅና የሚሰጥ የፖለቲካ አስተዳደር መዋቅር እና ውክልና የነፈገም ነው፡፡
በዚህ መሰረታዊ ሰንኮፍ ምክንያትም ሀገራችን ተሰናሳይ ለሆኑ ዘርፈ ብዙ ምስቅልቅሎሽ ተዳርጋለች፤ የኢትዮጵያዊነት እሴት ተሸርሽሯል፤ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍትህ ተዛንፏል፣ የህዝቡ የሞራል እና ስነ ምግባር ሚዛን ተዛንፍል፣ ድህነት ሀገራዊ መገለጫ ሆኗል፣ ዜጎች ለስደት፣ ለመፈናቀል፣ ለሰብዓዊ እና ዴሞክራሲዊ መብት ጥሰት ተዳርገዋል፡፡
በመሆኑም፣ የሀገራችን መሰረታዊ የጥያቄ ትኩረት አቅጣጭ ሶስትዮሽ ሆነዋል፤ እነዚህም፡-
1.1. እንደ ሀገር መቀጠልና አለመቀጠል የሚወሰንበት የህልውና ጥያቄ
1.2. ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የወለደው የህዝባዊ አስተዳደር መመስረት እና
1.3. ሁለንተናዊ ልማት የሚያረጋግጥ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት መስፈን ናቸው፡፡
በመሆኑም፣ የድርጅታችን መርሀ ግብር የአጭር ግዜ እና የረዥም ግዜ ሁለንተናዊ (ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ) መሻቶችንና ጥቅሞችን አንጥሮ በመለየት፤ እንዲሁም ያሉትን ሁለንተናዊና መሰረታዊ ችግሮችን አንጥሮ በመለየት፤ ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችሉ እምቅ አቅም አንጥሮ በመለየት፤ ያለውን እምቅ አቅም ላለው ችግር መፍትሄ ሊሆን የሚችልበትን የአጭር እና የረዥም ግዜ የፖለቲካ አደረጃጀትና አመራር በመገንባት፣ የርእዮት ዓለም አቅጣጫ፣ ራእይ፣ ተልእኮ፣ ዓላማ፣ እሴት፣ መርህ፣ የፖሊሲ እና የስልት አቅጣጫ በመንደፍ ተግባራዊነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል የሂደት ትልምም ግብም አውጥቷል፡፡
2.1. ራዕይ
ኢትዮጵያ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት፣ የዜጎች እኩልነት፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የሰፈነባት፣ እራሷን የሆነች እና ባለቤትነቷ የህዝቧ ሆና ማየት ነው
2.2. ተልዕኮ
ራዕዩን እውን ለማድረግ ሀገር በቀል እውቀት ከውጩ ዓለም እውቀትና ተሞክሮ ያዛነቀ፣ ርእዮት-ዓለማዊ
አቅጣጫን ከተግባራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ ያዋደደ፣ የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ፣ በኢትዮጵዊነትና በሰው ልጆች ሁሉ የጋራ እሴቶች ላይ የተመሰረተ፣ አሳታፊ እና ተመንዳጊ የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ በመገንባት ኢትዮጵያን ከሕዝብ፣ በሕዝብ፣ ለሕዝብ ለቆመ የፖለቲካ ሥርዓት እንድትበቃ ማስቻል ነው
2.3. ዓላማዎች
ፓርቲያችን ከላይ የተገለፁትን ራዕይ እና ተልዕኮ እውን ለማድረግ የሚከተሉት ዓላማዎች ይኖሩታል፤
እንደ ሀገር የተጋረጡትን የፖለቲካ ተቃርኖዎች እና ተግዳሮቶች በሰላማዊ፣ በሰለጠነ እና በህዝብ ለህዝብ የሚፈቱበትን ትልም በማመቻቸት የህልውና ሰንኮፎችን ለማስወገድ መስራት
በጽኑ ሀገራዊ ህልውና ላይ ዘላቂ ተቋማዊ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን የበኩሉን ሚና መወጣት
ሀገራዊ ህልውናን፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን፣ ህዝባዊ ህገመንግስትን እና ህገመንግ ስታዊነትን ሊያጸኑ የሚችሉ፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዱ ሀገራዊ ተቋማት እንዲታነጹ የበኩሉን ድርሻ መወጣት
ህዝብ ሉዓላዊ ባለቤት የሆነበት አዲስ ህገ መንግሥት እንዲኖር መታገል፣ ህገ መንግስታዊ ለውጥ እስከሚደረግ ባለው ህገመንግስት የህግ የበላይነትን አክብሮ በነጻ፣ፍትሀዊና ተዓማኒ ምርጫ ህዝባዊ የፖለቲካ ስልጣን ለመጨበጥ መትጋት
በመሰረታዊነት የግለሰብ/የዜጎች ነጻ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ሆኖ ሲያበቃ የግለሰብ እና የወል ማንነት መብቶች ተጣጥመው የሚተገበርበትን ትልም መንደፍ
ከነባራዊው የሀገራችን ፖለቲካ ሁኔታ አኳያ የህዝቡን ማህበራዊ መሰረት ያጣጣመ ፖሊሲ/ፍኖተ ግብር እና መርሃግብር መተግበር
በኢትዮጵያዊነት እሴቶች የታነጸ፣ ሰብዓዊ ክብርን የሚያስቀድም፣ የቀደምት አበውን አርዓያነት የሚስቀጥል፣ ለዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት የበቃ ውቅረ-አእምሮ ያለው፣ ምክንያታዊ እና በስነምግባር የታነጸ ትውልድ ለመገንባት መትጋት
በነፃና ፍትኃዊ ምርጫ በህዝብ ድምፅ የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ፤ በስልጣን ላይ ባልሆንበት ጊዜ ሁሉ
በሰላማዊ መንገድ ለፓርቲያችን ተልእኮ መሳካት ግብዓት የሚሆኑ ስራዎችን መስራት
በማነኛውም ወቅት ሀገሪቷ ከህዝቧ የምትጠብቀውን ተግባር ሁሉ በንቃት ማድረግ፣ ሌሎች እንዲያደርጉ ማበረታታት
ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያመጡ የፖሊሲ አማራጮችን ማቅረብ፣ ከሚገኘው ዕድገትም ህዝቡ
ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል
የህዝቡ ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና ተፈፃሚም ኢንዲሆኑ በጽናት መቆምለህዝቡ አስተማማኝ የማሕበራዊ ደህንነት ዋስትና አገልግሎት ለማቅረብ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ እንዲሳተፍ ማመቻቸትና ማበረታታት
ሀቀኛ፣ ብቃትና ተጠያቂነት ባለው አመራር አማካኝነት ታታሪና የፈጠራ ችሎታ ያለው የሰለጠነ ሀገራዊ የሰው ኃይል መፍጠር፤ በነፃነት የሚያስብ ሕብረተሰብ መመስረት፤ ወጣቱ ትውልድ በራሱና በወረሰው መልካም ነገር እንዲኮራ ማደፋፈር፡፡
3.1. ከድርጅቱ ራዕይ፣ ተልእኮ፣ ዓላማ፣ ርዕዮት ዓለም እና ፖሊሲ አኳያ ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራትን በሂደት፣ በውጤት እና በፈጠሩት ተጽእኖ የሚመዝን እና ተገቢውን የእርምትና የእድሳት ቅጣጫ ሚያስቀምጥ የክትትል እና ምዘና ሥርዓት እንዲዘረጋ ይደረጋል
3.2. የክትትል እና ምዘና ስርዓቱ ወጪና ግዜ ቆጣቢነትን፣ውጤታማነትን፣ የክንውኑን አስፈላጊነት፣ ዘላቂነት፣ ተጽእኖአዊ ውጤት ታሳቢ ደረገ ይሆናል
3.3. የክትትል እና ምዘና ስርዓቱ የሚኖረው ስነ አመክኖአዊ ፍሰት ዓላማውን ለማሳካት የሚያገለግሉ
ግብአቶችን፣ግብአቶችን ተመስርቶ የሚደረጉ የሰራ ክንውኖችን፣ የሚጠበቁ ውጤቶችን እና ጽኗዊ ለውጦችን የሚቃኝ ይሆናል 3.4 የክትትል እና ምዘና ስርዓቱ ዋና ዓላማ ፓርቲውን ሁለንተናዊ መዳረሻ ለማሳካት የሚያስችል፣ ውስጠ ድርጅታዊ አቅም መፈጠሩን እና ውጫዊ ውጤቶችን መዝኖ ስህተቶችን በማረም ከሁኔታዎች ጋር የሚራመድ አቅጣጫን የሚከተል ይሆናል3.5. በውስጠ ድርጅታዊ አሰራሩ ምክንያታዊነትንና ወጥነትን ሚዛን መሰረት አድርጎ፣ የሰው ኃይል ብቃትን እና የአፈጻጸም ትሩፋትን የሚለካ የራሱ መለያ ያለው ድርጅታዊ መዋቅር የሚፈጥር ይሆናል
3.6. ድርጅቱ በሴራ እና በመጠላለፍ ተቃኝቶ ከቆየው የሀገራችን የፖለቲካ ባህል ተገቢውን ትምህርት በመውሰድ ለቀጣይ እርምቶች ክፍት ይሆናል3.7. ለፓርቲያችን ብቸኛው የስልጣን መያዣ መንገድ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ይሆናል
3.8. ድርጅቱ በመሰረታዊ የመዳረሻ፣ የአደረጃጀት እና የትግል ስልት ተቀራራቢነትን መሰረት አድርጎ ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በአብሮነት በመታገል በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ ማህበረሰባዊ መሰረት ያለው ተገዳዳሪ የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ እንዲፈጠር አበክሮ ይሰራል፤ በዚህ ረገድ ከህብረ ብሄራዊም ሆነ ከብሄር ድርጅቶች ጋር በአብሮነት ይሰራል
3.9. የሀገራችን ፖለቲካ በሃሳብ ልዕልና እንዲመራ እና ዴሞክራሲያው የፖለቲካ ባህል እንዲዳብር የበኩሉን ሚና ለመወጣት ይሰራል
3.10. ድርጅቱ የሚታገልላቸው ዓላማዎች ለማሳካት ምርምር እና ጥናት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ይሰራል
3.11. ታሪክን ለከፋፋይ ፖለቲካ ዓላማ መሳሪያነት ከማዋል ይልቅ፣ ተገቢውን ትምህርት ቀስሞ መጪውን ግዜ ብሩህ እንዲያደርግ ይሰራል
3.12. የፖለቲካ ልዮነቶች ለቀጣይ ውይይት እንጂ ለግጭት መንስዔ እንዳይሆኑ አበክሮ ይስራል
3.13. ሀገርበቀል፣ባህላዊ እና ኃይማኖታዊ ግጭት አፈታት ስርዓቶች እና እሴቶች የሀገሪቱን የፖለቲካ ባህል በሚጠቅሙበት ሁኔታ እንደግብአት እንዲያገለግሉ ይሰራል
3.14. የሲቪል እና የሙያ ማህበራት በሀገሪቱ ፖለቲካ ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው ይሰራል፤
3.15. የአዲስ አበባን ሁለንተናዊ ጥቅም ከቀሪው የሀገራችን ክፍል ጥቅም ጋር ተሳስሮ እንዲታይ ይሰራል፡፡
4.1. መንግስትና ኃይማኖት የተለያዩ ናቸው በሚለው መርህ ስር ሆኖ፣ ለኃይማኖት ነፃነትና ለሁሉም ኃይማኖቶች የላቀ ክብር መጎናፀፍ መትጋት፤ በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ የሚገባ የመንግስት ባለስልጣን በከባድ ወንጀል ደረጃ እንዲጠየቅ የሚያደርግ ህግ እንዲወጣ መትጋት
4.2. በአጠቃላይ የሰው ልጆችንና የኢትዮጵያዊነት እሴቶችን ማክበር፤ ለሀገር ሉዓላዊነት፣ ለመንፈሳዊና ቁሳዊ ቅርሶች፣ ለአኩሪ ታሪኮች፣ ለጀግኖች አርበኞቻችን ቀናኢ በመሆን ውርሳቸውን ለማክበር እና ለማስቀጠል መትጋት4.3. ለስነምግባር መርሆዎች እና ለህሊና ተገዢ መሆን፣ ለሰብዓዊ ክብር ቅድሚያ መስጠት
4.4. በውይይት፣ በሃሳብ ልእልና የሚመራ አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ባህልን ማዳበር፣ከራስ ስህተትም ሆነ ከሌላው ጥንካሬ ለመማር ክፍት የሆነ የአሰራር ሥርዓትን ማዳበር
4.5. ከአለፈው ታሪክ ጥንካሬ እና ድክመት ተምሮ የአሁኑን በመተንተን፣የወደፊቱን የሚተልም ተሰናሳይ ራእይ ማንገብ፤
4.6. ለህግ የበላይነት፣ ለአኩልነት ለፍትህ ተገዥ መሆን
4.7. ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ለህግ የበላይነት ተገዢ እንዲሆኑ መትጋት፤ በተለይ የመንግስት ባለስልጣናት ለህግ ተገዢ እንዲሆኑ የሚያስችል የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት መዘርጋት
4.8. የህግ የበላይነትን ለማስከበር እንዲቻል ሁሉንም ዜጋ ያለ አድልኦ የሚያስተናግድ የፍትህ ስርዓት እንዲፈጠር ማድረግ፤ ሁሉም ዜጋ በስርዓቱ ተጠቃሚ እንዲሆንም አስፈላጊውን ፖሊሲና አደረጃጀት መዘርጋት
4.9. ለፓርቲው እሴቶች፣ ሁለንተናዊ ግቦች (ራእይ፣ ተልእኮ፣ ዓላማ፣ መርሀግብር፣ ፖሊሲ እና እስትራቴጂ) ተገዢ መሆን፤ ማስፋፋት እና ማስረጽ4.10. በድርጅቱ ሁለንተናዊ ግቦች እና ርእዮት ዓለም ጽኑ እምነት ማሳደር፤ ሆኖም የተፎካካሪም ሆነ የሌላ ውጫዊ ኃይል አስተሳሰብ እና የፖለቲካ መስመር ክብር በመስጠት የመቻቻል እሴቶችን ማዳበር፤ ከተቀናቃኝም ቢሆን ለመማር መዘጋጀት
4.11. የፓርቲው ዓላማ ከአዳዲስ እውቀቶች፣ ከጥናት እና ምርምር ግኝቶች፣ ከህዝብ አስተያየቶች፣ ከውይይቶች፣ ከግዜና ከቦታዎች እንፃር ከሚለዋወጡ የፖለቲካ ሁኔታዎች ጋር ተናቦ እንዲራመድ በሩን ክፍት ማድረግ
4.12. በሃሳብ ልዕልና የተቃኘ የውይይት ባህል በማዳበር፣ ከራስ ሃሳብ ምርኮኝነት ተላቆ አለመግባባቶችን በውይይት እና በመቻቻል ለመፍታት መጣር
4.13. አምባገነንነትን፣ ግለኝነትን፣ አድሎአዊነትን፣ ዘረኝነትን፣ አሉባልተኝነትን፣ ጽንፈኝነትን፣ ቂመኝነትን እና ቡድነኝነትን መዋጋት እና መጠየፍ
4.14. በህብረተሰቡ መካከል የሚፈጠሩ ጎጂ መከፋፈሎችን ሁሉ አጥብቆ መቃወም፤ ይህ እንዳይፈጠርም መጣር፤ የተፈጠሩትንም ለማስተካከልና ለማጥፋት መስራት
4.15. ሁሌም ለምሉእነት እና ለታላላቅ ስኬቶች መስራት4.16. የፓርቲው ጠቅላላ እንቅስቃሴና ፕሮጀክቶችን በሚያግባባ መልኩ ሊመዘኑ በሚችሉበት መልኩ እንዲቀረፁ ማድረግ፡፡
5.1. በኢትዮጵያ ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ባለሙሉ የሥልጣን ባለቤት ነው፡፡ ሀገሪቱን የማስተዳደር ሥልጣን ከሕዝብ ይመነጫል
5.2. የኢትዮጵያ ህዝብ በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ የሚገኘው የመሬት፣ ውሃና የአየር ክልል፣ እንዲሁም በከርሰ ምድርና በከርሰ ውኃ የሚገኘው ሃብት፣ በአየር ክልሉ ያለው የድምፅና የምስል ሞገድ ባለቤት ነው፡፡ ይህን የምላዓተ ህዝብ መብት በብሄር፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በጎጥ ወይም በማንኛቸውም በሌላ መንገድ መሸራረፍ ወይም ቅድመ ሁኔታ ሊቀመጠብት የማይችል ነው
5.3. የኢትዮጵያ አንድነትም ሆነ ሉዓላዊነት አይነጣጠሉም፤ለሌላም አይለቀቁም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛውና ህጋዊ የሉዓላዊነት ባለቤት ኢትዮጵያዊያን በፌድራል ደረጃ የሚያስተዳድረው መንግስት ነው፡፡ ክልሎች/ክፍለ ሀገራት ከፌድራል መንግስቱ የተለየ ወይም የሚስተካከል ሉዓላዊነት የላቸውም
5.4. የኢትዮጵያ ሀገረመንግስት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት እውቅና ያገኘ፣ በሀገሪቱ መንግስት ግዛት ስር የሚገኘውን የምድር፣ የአየር፣ የባህር ሉአላዊ የግዛት ወሰን እና በውስጡ የሚኖረውን አንድ ህዝብ የሚያካትት ነው፡፡ በአንድ ህዝብነቱ ውስጥ ለረጅም ዘመን በአመዛኙ በባህል፣ በቋንቋ፣ በትውፊት፣ በእሴት ተሳስሮ እና ተቻችሎ የኖረ የንዑስ ማንነት ብዝሀነት እና በሀውርታዊነት የሚኖር ነው፡፡ ብዝሃነቱ ተዛንቆ፣ እንደ አንድም እንደብዙም ሆኖ የተቋጨበት የጋራ ማንነት ኢትዮጵዊነት ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነት የታሪክ፣ የኢኮኖሚ የባህል የማህበራዊ እና የፖለቲካ ጭማቂ እምብርት ደግሞ፣ የእምዬ ኢትዮጵያ ክፋይ የሆነችው አዲስ አበባ ናት
5.5. ኢትዮጵያ ሀገራችን የረጅም ዘመን ሀገረ-መንግስትነት ታሪክ፣ የቀደምት ብርቅዬ ስልጣኔ (የስነ ህንጻ፣ የዜማ፣ የፊደል፣ የስነ-ስእል፣ የስነ-ጽሁፍ፣ የስነ-መለኮት፣ የሰነ ምህዋር፣ የበሀር-ሃሳብ፣ የባህላዊ መድኃኒት፣ የፍልስፍና፣ የቅኔ ወዘተ) ባለቤት የሆነች፣ ታላላቅ እምነቶችን (የተዋህዶ ክርስትናን እና እስልምናን) ከዓለም ቀድማ የተቀበለች እና አግባብታ የማኖር እጹብ ድንቅ እሴት ያዳበረች፣ የዘርፈብዙ ሀገር በቀል እውቀቶች፣ እሴቶች፣ትውፊቶች እና ባህሎች ባለቤት የሆነች፣ በቅኝ ሳትገዛ ነጻነቷን በማስጠበቅ ከራሷ ጋር ታርቃ የኖረች አኩሪ ገድሎችን እና ጀግንነቶችን ያስመዘገበች የጥቁር ህዝብ ኩራት የሆነች ብርቅዬ ሀገር ናት
5.6. ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ የተፈጥሮ ነዳጅ እምቅ ወረት መገኛ ከሆነው የገልፍ ሀገራት የተቆራኘ፣ የዓለም የነዳጅ ንግድ ዋና መተላለፊያ ከሆነው ቀይ ባህር እና ባብል መንደብ የተሳሰረ፣ በብዝሀ ህይወት እና በተፈጥሮ ሀብት በታደለው እና በሀያላን ሀገራት የፖለቲካ መሻት የትኩረት መአከል በሆነው ምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ውስጥ ነው፡፡ ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብት እና በህዝብ ብዛት ከቀጠናው ሀገሮች ግዙፍ ብትሆንም፣ የራሷ ወደብ የሌላት ከመሆኗም በላይ፣ ወደብ ባላቸው እና የአካባቢውን ሰላም በማይፈልጉ ኃይሎች ሊጠለፉ በሚችሉ ትናንሽ ሀገራት የተከበበች ናት፡፡ የዚያኑ ያክል ቀጠናው በበርሃነት መስፋፋት፣ በተፈጥሮ ሀብት መመናመን፣ በስደት፣ በህዝብ መፈናቀል፣ በፖለቲካ አለመረጋገት እና በሀገራት መሰነጣጣቅ እየታመሰ የሚገኝ እና ለወደፊት የመተራመስ እጣፈንታም የተጋረጠበት ነው፡፡ይህ የቀጠናው ገጽታም በሀገራችን ላይ የራሱን አዎንታዊ እና አሉታዊ ትሩፋት የሚያሳድር በመሆኑ፣ የቀጠናውን ጂኦ ፖለቲካ በማገናዘብ የሀገሪቱን ዘላቂ ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችል አካሄድ መከተል ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ረገድ ኢትዮጵያ ቀዳሚውን ሚና መጫወት ይጠበቅባታል
5.7. ሀገራችን የአኩሪ ታሪክ፣ የሀገር በቀል እውቀት ባለቤት እና የነጻነት ቀንዲል የመሆኗን ያክል፣ ጭቆናን የሚጠየፍ፣ፈላጭ ቆራጭነትን የሚገራ የሰለጠነ ስርዓተ መንግስት ማንበር እና ሀገር በቀል እውቀቷን ወደላቀ ምእራፍ ማሸጋገር ተስኗት፣ ለገናናው ክብሯ እና ታሪኳ የማይመጥን አስከፊ በሆነ ኢኮኖሚዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ አዘቅት ውስጥ ተደፍቃ ትገኛለች፡፡ ከኢህአዴግ መከሰት ወዲህ ደግሞ፣ ከሁለንተናዊ ማሽቆልቆል ባለፈ የህልውና ተግዳሮት ውስጥ በመዳከር ላይ በመሆኗ፣ ለኢትዮጵያውያን የሚያስቆጭ፣ ለጠላቶቿ ደግሞ የዘሩትን አረም መሰብሰቢያ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡
5.8. የሀገራችን ብሎም የአዲስ አበባ የፖለቲካ ሁኔታ ሶስት ተሰናሳይ የትግል ምእራፎችን የሚጠይቅ ነው
1ኛ የሀገሪቱንም ሆነ የአዲስ አበባን የህልውና ሰንኮፍ በመንቀል ሀገሪቱን በጽኑ መሰረት ላይ ማሰቀጠል
2ተኛ በህዝባዊ ህገመንግስት መሰረት ላይ ዴሞክራሲዊ ሥርዓትን እና ህገመንግስታዊነትን ማንበር
3ተኛ በሰፈነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሰረት ላይ አማራጭ የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ መስርቶ የመንግስት ስልጣንን በመያዝ የሀገሪቱን ብሎም የአዲስ አበባን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ በማበጀት፣ ለትውልድ የሚተላለፍ ኢትዮጵያዊ ሆኖ የመኖር ዋስትና እና የልማት መሰረት መዘርጋት ያስፈልጋል
5.9. የአዲስ አበባ መሰረታዊ ችግር የሚመነጨው እንደሀገሪቱ ሁሉ ከተዛባ የታሪክ ትርክት፣ በሃሳዊው የዘውግ ጨቋኝ-ተጨቋኝ ትርክት ላይ ከተመሰረተው የግራዘመም ርእዮት ዓለም እና ይህንኑ እውቅና ከሰጠው የህወሓት ህገ መንግስት ነው፡፡ የዚህ ውጤት የሆነው የፖለቲካ ሥርዓት አዲስ አበባንም ሆነ ነዋሪዎቿን እውቅና እና የፖለቲካ ውክልና የነፈገ ነው፡፡ ስለሆነም፣ የትግሉ አቅጣጫ ህገ መንግስቱን እና ፖለቲካ ስርዓቱ እንዲቀየር በማድረግ ከተማዋ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ክፋይነቷን ማረጋገጥ (የአዲስ አበባ ክልል እንድትሆን ማድረግ) ይሆናል፡፡
6.1. የቀኝ ዘመም የፖለቲካ አመለካከለትና ፖሊሲዎች ለሀገራችን ሁለተንተናዊ ችግሮች ተመራጭ መፍትሄ ያስገኛሉ
6.2. የሀገራችን መሰረታዊ የፖለቲካ ቀውስ ፈውስ እንዲያገኝ ለማስቻል፣ተቋማዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት እና ህገመንግስታዊነት መሰረት እንዲይዝ፣ አሁን በስራ ላይ የሚገኘው የህወሓት ህገ መንግስት በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ተወግዶ፣ ሙሉ በሙሉ አዲስ በሆነ ህገ መንግስት መተካት ይገባዋል
6.3. ኢትዮጵያ በራሷ ሉዓላዊ ሀገር እንጂ በብሄሮች የሉዓላዊነት መዋጮ የተመሰረተች አይደለችም፤ የሀገሪቱ የሉአላዊ ሰልጣን ምንጭ አጠቃላዩ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው
6.4. የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ ወደታች አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው6.5. የግለሰብ እና የቡድን መብቶች የሚጻረሩ ሳይሆኑ በግለሰብ ነጻነት እና በኢትዮጵዊነት መሰረት ላይ ተዛንቀው የሚተገበሩ ናቸው
6.6. በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ንዑስ ማንነቶች የራሳቸውን ባህል፣ ቋንቋ እና እምነት የሚያሳድጉበትና ብዝሃነት የሚስተናገድበት ምህዳር መፈጠር ተገቢ ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ የንዑስ ማንነቶች መብት በተለጠጠ ሁኔታ በመተርጎም የአንድ ንዑስ ማንነት የራሱ የግዛት ወሰን፣ የመሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት፣ የንዑስ ማንነት የፖለቲካ ማህበር መመስረት፣ ሉአላዊ ስላጣን ባለቤት መሆን፣ የዜጎችን በሁሉም የሀገሪቱ የግዛት ወሰኖች በእኩሉነት ሃሳብን የማራመድና ንብረት አፍርቶ የመኖር መብትንና እሴትን የሚያቆረቁዝና ለሀገር ህልውና አደጋን የሚያስከትል መሆን የለበትም
6.7. የሀገሪቱን ህዝብ ብሎም የአዲስ አበባን ህዝብ ታሪካዊ ትስስር፣ባህላዊ ቁርኝት፣መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ አስተዳደራዊ አመቺነትን፣ብዝሃነትን ከግምት ያስገባ ፌደራል አወቃቀር ሊኖር ይገባል
6.8. ሁሉም የፌድራሉ ክልሎች/ ክፍለ ሀገራት አስቀድመው በህዝበ ውሳኔ የሚፀድቁ መሆን ይገባቸዋል6.9. የሀገሪቱ ርዕሰ ብሄርም ሆነ ርዕሰ መንግስት በህዝብ በቀጥታ በሚመረጥ ፕሬዚዳንት መሆን ይገባዋል
6.10. የአዲስ አበባና የትላልቅ ከተሞች ርዕሰ መስተዳድር/ከንቲባ በህዝብ በቀጥታ መመረጥ ይገባዋል
6.11. የመሬት ይዞታ ባለቤትነት መብት እንደሁኔታው ተገቢነት የግል፣ የወል እና የመንግስት ሊሆን ይገባዋል፤ በግል ይዞታ ስር ያለ መሬት እንደማንኛቸውም ንብረት የሚሸጥና የሚገዛ መሆን ይገባዋል6.12. የቡድኖች ሰብዓዊ መብት መጠበቅና ተግባር ላይ መዋል የዴሞክራሲ መሠረት በመሆናቸው የህግ ከለላ ሊሰጣቸው ይገባል
6.13. መንግሥት በግለሰብም ሆነ በቡድን ነፃ ኢኮኖሚ ግንባታ ጣልቃ ሊገባ አይገባም6.14. በማህበረሰብ ውስጥ ሰዎች የጋራ መብት ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆኑ፣ የጋራ መብት ተጠቃሚነት
የሚያሳርፍባቸውን ግዴታዎች በመቀበል ተከባብረው መኖር አለባቸው፤ ለዚህም ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡
7.1. ኢትዮጵያ በአዲስ ህገ መንግስት አዲስ የመንግስት አደረጃጀት ሊኖራት ይገባል፤ በአዲሱ የመንግስት አደረጃጀት ኢትዮጵያ ህገ መንግስታዊ የፌድራል አደረጃጀት ሊኖራት ይገባል፤ የፌድራል አደረጃጀቱ የአሜሪካን ፌድራሊዝምን ተሞክሮ መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባል፡፡
7.1.1. የፌድራል መንግስት
ሀ.1. በኢትዮጵያ የፌድራል የስልጣን ክፍፍል አብዛኛው ስልጣን ለፌድራል መንግስቱ የተሰጠ ሊሆን ይገባዋል፤ በህገ መንግስቱም የፌድራል መንግስቱ በክልል/ ክፍለ ሀገር መስተዳድሮች ላይ ግልፅ የሆነና በህግ የተደነገገ የበላይነት እንዳለው ሊገለፅ ይገባል፤ በሀገሪቱ ብቸኛው የሉዓላዊነት ባለቤት የፌድራል መንግስቱ መሆኑ በህገ መንግስቱ በግልፅ መቀመጥ ይገባዋል
7.1.2. የክልል/ የክፍለ ሀገር መስተዳድር
ለ.1. የክልል/ክፍለ ሀገር መስተዳድሮች በህገ መንግስት የተደነገገ መብትና ስልጣን ይኖራቸዋል፤ ይህንን በህገ መንግስት የተደነገገ መብትና ስልጣን የፌድራል መንግስቱ ሊቀማቸው አይችልም፤ ሆኖም፣ የመስተዳድሮቹ ስልጣን የመንግስትነት ወይም የሉዓላዊነት ደረጃ እንዳልሆነና የአስተዳደር ስልጣን ብቻ እንደሆነ በግልፅ ቋንቋ መቀመጥ ይገባዋል፡፡
8.1. የመንግስት ሥልጣን በሕግ አውጪው፣ በሕግ ተርጓሚውና በሕግ አስፈፃሚው አካላት መካከል የሚከፋፈል ሊሆን ይገባል፤ አንዱ በሌላው የሥራ ድርሻ ጣልቃ ሳይገባ በእኩልነትና በነፃነት መስራት የሚያስችላቸው ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ሊኖር ይገባል፤ የሀገሪቱ መሪ ይህንን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ጥሰው ከተገኙ በወንጀለኛ መቅጫው እንዲጠየቁ የሚያደርጉ ንዑስ ህጎች ሊኖሩ ይገባል
8.2 የዳኞች፣ የዐቃቤ ህጎች፣ የፖሊስ፣ የመከላከያና የደህንነት ከፍተኛ ኃላፊዎች ምልመላ እና ሹመት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ፀድቶ በሕግ እውቀት፤ ልምድና ብቃታቸው ብቻ እንዲሆን የሚያስችል ሥርዓት ሊኖር ይገባል፡፡
9.1. የአዲስ አበባ ባለቤት መላ ኢትዮጵያዊያን ናቸው
9.2. በአዲስ አበባ ማንም የተለየ ጥቅምም ሆነ መብት ሊኖረው አይገባም
9.3. በአዲስ አበባ የተወለዱና በሌሎች ክልሎች ተወልደው በከተማዋ የሚኖሩ እኩል ባለመብቶች ናቸው
9.4. ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም እንዳላት የሚደነግገው ህገ መንግስት በህዝብ ፈቃድ ያልወጣ፤ በኃይል በሀገር ላይ የተጫነ ነው፤ ድርጅታችንም ሆነ የአዲስ አበባ ህዝብ ፈፅመው ሊቀበሉት አይገባም
9.5. አዲስ አበባ የፌደራል መንግስት መቀመጫ ከመሆንዋ ጎን በአስተዳደር ቁመናዋ የክልል/ክፍለ ሀገር ደረጃ ሊኖራት ይገባል፤ የክልል/ ክፍለ ሀገር ደረጃዋ በነዋሪዎቿ ነፃ ፈቃድ በህዝበ ውሳኔ የሚወሰን ሊሆን ይገባል
9.6. የአዲስ አበባ የአስተዳደር ወሰን ህወሓት/ኢህአዴግ በ1983 ስልጣን ሲይዝ የነበረው ሊሆን ይገባል
9.7. አዲስ አበባ በዙሪያዋ ካሉ አካባቢዎች ጋር በማስተር ፕላን ልትተሳሰር ይገባል፤ የከተማዋ ነዋሪዎች በዙሪያዋ ባሉቦታዎች ያለምንም መሸማቀቅ ቤት የመስራት፣ የንግድ ተቋማትን የማቋቋም የዜግነት መብታቸው ምንም ሳይሸራረፍ ሊጠበቅላቸው ይገባል9.8. የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የቤትና የከተማ ቦታ ባለቤት የመሆን መብታቸው ሊረጋገጥ ይገባል፤ ይዞታቸውንም ማልማት፣ መሸጥ፣ መለወጥና ለሌሎች በውርስ ወይም በስጦታ የማስተላለፍ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል
9.9. የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የመኖሪያ ችግር ለመቅረፍና የከተማዋን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማሳለጥ፣
የከተማዋ መስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን በብዛትም በጥራትም በከፍተኛ ደረጃ ሊያሳድገው ይገባል፤ ለዚህም ከባንኮች፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በትብብርና በሽርክና ሊሰራ ይገባል
9.10. የትራንስፖርት አገልግሎት ለነዋሪዎች በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብ በዘርፉ ለሚሰማሩ ዜጎች ማበረታቻ ሊቀርብላቸው ይገባል፡፡
የድርጅታችን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሀብትን ከማከፋፈል ይልቅ ሀብትን በመፍጠር ላይ ያተኮረና ለዜጎች ሥራ መፍጠርን ዋነኛው ዓላማው ማድረግ ይገባዋል ብሎ የሚያምን ይህንንም እውን ለማድረግ የግሉ ክፍለ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዋና አንቀሳቃሽ ነው ብሎ የሚያምን የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ወደ ፈጣን እድገት ለማሸጋገር የውጭ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት ( የውጭ ኢንቨስትመንት) ወሳኝ ነው ብሎ የሚያምን ስለዚህም፣ የውጭ መዋዕለ ንዋይን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሀገራችንን የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትን በፍጥነት እውን ከማድረግ አንስቶ የተለያዩ አዳዲስ ፖሊሲዎችን የሚተገብር፤ ሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ከኢትዮጵያ ገበያ ይልቅ የዓለም ገቢያን ኢላማ አድርገው ማደግ ይገባቸዋል ብሎ የሚያምን ለሁሉም ክፍላተ ኢኮኖሚ ተቀናጀ እድገት ትኩረት የሚሰጥ ከፍተኛ የሥራ አጥነት ሲከሰት፣ የኢኮኖሚ መቆርቆዝ ሲያጋጥም፣ የዋጋ ግሽበት ሲመጣ፣ የመንግስት የበጀት ጉድለት ሲጨምር እና መሰል ችግሮች ሲከሰቱ መንግስት በእውቀትና በጥናት የተመሰረተ ጊዜያዊ የማረጋጋት እርምጃ የሚወስድ በግል ባለሀብቶች ሊመሩ የሚችሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ግሉ ይዞታ ወይም አስተዳደር እንዲዛወሩ አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብሎ የሚያምን ለዘላቂ ልማት ወሳኝ በሆኑ የተፈጠሮ ሀብቶች አጠቃቀም ዙሪያ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚና የሀገር ሉዓላዊነትን ባስጠበቀ መልኩ መከናወን ይገባቸዋል ብሎ የሚያምን ነው፡፡
10.1 አጠቃላይ
10.1.2. የእያንዳንዱ ዜጋ እድገት የሀገራችን ሕዝብ እድገት መሠረት ሲሆን፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት መሰረትም የሀገራችን ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህም፣ ማንኛቸውም ዜጋ በፈለገው ሙያና የሥራ መስክ
የመሰማራት፣ ሃብት የማፍራት፣ የንብረት ባለቤት የመሆን፣ የመያዝ፣ የመሸጥ፣ የመጠቀምና በህጋዊ
መንገድ ለሌላ ወገን የማውረስ ወይም የማስተላለፍ መብቱ ይከበርለታል
10.1.3. ፖሊሲያችን የሀገራችንንና የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ገበያ-መር የኢኮኖሚ
ሥርዓት ይዘረጋል10.1.4. የውጭ ኩባንያዎችና የግል ባለሃብቶች ኢኮኖሚው ውስጥ ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ ይበረታታሉ፤ ሀገር ውስጥ ካለ ባለሀብት እኩል የህግ ከለላና ጥበቃ ይደረግላቸዋል
10.1.5. የአሰሪና ሰራተኛ መብቶችና ግዴታዎች ኢትዮጵያ ብዙ ተፎካካሪ ሀገራት እንዳሉባት ያገናዘቡ፣ ነፃና ፍትሃዊ ውድድርን የሚያዳብሩ፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን የንብረት ባለቤትነት መብትን
የሚያረጋግጡ፣ የተበላሸ አስተዳደርና ሙስናን የሚከላከሉና ሌሎች ለኢኮኖሚው አስተዳደር አስፈላጊ የሆኑ ህጎችንና መመሪያዎችን ያካተቱ ሊሆኑ ይገባቸዋል
10.1.6. የፖለቲካ መረጋጋት፣ ሰላምና ደህንነት ለኢኮኖሚው ጤናማ እድገት አማራጭ የሌላቸው ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው ብሎ የሚያምን ነው፡፡
10.2. ስለ ግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚና መሬት አቅጣጫዎች
10.2.1. የመሬት ባለቤትነት መብት የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ የመንግስት እና የማህበረሰብ የወል ሃብት ሊሆን ይገባል
10.2.2 እያንዳንዱ የመሬት ባለቤት መሬቱን የማልማት፣ የመንከባከብ፣ የማከራየት፣ የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ በውርስ ወይም በስጦታ ለሌሎች የማስተላለፍ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ሊሆን ይገባል
10.2.3 ማንኛውም ሰው በግል የያዘው መሬት ለመንግሥት አገልግሎት ቢፈለግ በወቅቱ የገበያ ዋጋ ተገቢው ካሳ ሊከፈለው ይገባል፤ የመሬቱ የገበያ ዋጋ የተለያዩ ባለድርሻዎች በሚሳተፉበት ገለልተኛ ቦርድ የሚወሰን ሊሆን ይገባል
10.2.4. በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በማዳበሪያ ሳቢያ ከሚደርስባቸው እንግልትና ተፅዕኖ እንዲላቀቁ ሊደረግ ይገባል፤ በዚህም ረገድ በኢህአዴግ የእጅ አዙር ቁጥጥር ስር ሆነው የማዳበሪያ አቅርቦት የሚሰጡ የንግድና የብድር ተቋማት በግል ባለሀብቶች እንዲተኩ ሊደረግ ይገባል
10.2.5. በጫት የሚተዳደረው ገበሬ ተመጣጣኝ ገቢ በሚያስገኝለት ሌላ ምርት እንዲተካው የምክር፣ የስልጠና፣ የብድር አገልግሎት ሊሰጠው ይገባል
10.2.6. በመስኖ ለሚደገፍ ግብርና ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል
10.2.7. በነጠላ የሚያርሰውን ገበሬ ለማዘመን ዝርዝር ፖሊሲዎች ሊወጡ ይገባል
10.2.8. ሰፋፊ እርሻዎችን ለማስፋፋት ዝርዝር ፖሊሲዎች ሊወጡ ይገባል
10.2.9. በግብርና ያለው ህዝብ የኤሌክትሪክ፣ የንፁህ ውሃ፣ ጥራት ያለው ትምህርትና የጤና አገልግሎት የሚያገኝበት ዝርዝር ፖሊሲ ሊወጣ ይገባል
10.2.10. በግብርና ያለውን ህዝብ በፍጥነት ወደ ከተማ ለማስገባት ያለመ መንግስታዊ ፖሊሲ ሊወጣ ይገባል፡፡10.3. ስለ ኢንዱስትሪ አቅጣጫዎች
የኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ለፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ወሳኙ ዘርፍ ነው፡፡ ይህ ክፍለ ኢኮኖሚ የኢትዮጵያን ገበያ ብቻ ተገን አድርጎ ነፍስ መዝራት የሚችል አይደለም፡፡ ስለዚህም፣ በዋነኛነት ለዓለም ገበያ የሚያመርት ዘርፍ ሆኖ የሚገነባ መሆን አለበት፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ፣ በቀዳሚነት በዓለም ላይ ያሉ ስመ ጥር ኩባንያዎች በሀገራችን ውስጥ አምርተው ምርቶቻቸውን ለዓለም ገበያ እንዲያቀርቡ የሚያስችላቸውን ዝርዝር ፖሊሲዎች መንደፍና መተግበር ያስፈልጋል፡፡ ወደ ሀገር ውስጥም እንዲገቡ አመች ኢኮኖሚያዊ ድባብ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡በዚህ ረገድ፣ ድጋፍ የሚሰጧቸው አነስተኛ ሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎችና እደጥበባት ስለሚያስፈልጉ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
በዚህም መሠረት፡-
10.3.1. የኢንዳስትሪዎችን የቴክኖሎጂ ይዞታና ምርታማነት ለማሳለጥ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል
10.3.2. የኢንዱስትሪው ዘርፍ በሁሉም የኢኮኖሚ ክፍሎች ትስስር እንዲፈጥር ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል
10.3.3. አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገት ሀገራዊ መሰረት ሊኖረው የሚችለው የአነስተኛ ኢንዳስትሪዎችና የሀገር በቀል ዕደ ጥበባት እድገት ሲዳብር በመሆኑ፣ ለእነዚህ ዘርፎች እድገት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መጠነ ሰፊ የብድርና የስልጠና ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል
10.3.4. ከፍተኛና ተነፃፃሪ ጥቅም ላይ የተመሰረቱ ኢንዳስትሪዎች እንዲኖሩ ለማድረግና የቴክኖሎጅ አቅም እንዲጎለብት፣ በየጊዜው የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲኖር ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምርምር ማዕከሎች ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
10.4. ስለ ንግድና አገልግሎት አቅጣጫዎች
የንግድና የአገልግሎት መርሃችን በአምራቹና በሸማቹ፣ በአገልግሎት ሰጭውና ተጠቃሚው መካከል ያለውን ግንኙነት ምቹና ቀልጣፋ ማድረግና በገቢና ወጪ ንግዳችን መካከል የተጋነነ ልዩነት እንዳይኖር የሚጠነቀቅ መሆን ይገባዋል በዚሁም መሰረት፡-
10.4.1. በንግድ ወይም በአገልግሎት ሰጭዎችና በተጠቃሚዎች መካከል በአቅርቦትና በፍላጎት መስተጋብር ላይ ብቻ የተመረኮዘ ስርዓት ሊኖር ይገባል፤ መንግስት በጣም በልዩ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር የዋጋ ቁጥጥር አያደርግም፤ የዋጋ ቁጥጥር ካደረገም በፍርድ ቤት የሚጠየቅበት የህግ ማዕቀፍ ሊኖር ይገባል
10.4.2. ለንግድና አገልግሎት ሰጭዎች ፈቃድ አሰጣጥ ቀልጣፋ እንዲሆን ተጨማሪ ማሻሻያዎች ሊኖሩ ይገባል፤ ማህበረሰቡ ደግሞ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት ማግኘቱን የሚቆጣጠር ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል
10.4.3. የንግድ ማዕከላት እንዲስፋፉ፤ የንግድና አገልግሎት ሰጭዎች መረጃ ትስስር ዘመናዊ እንዲሆን
የሚያስፈልጉ ድጋፎች ያስፈልጋሉ
10.4.4. በአገልግሎት ዘርፉ የቱሪዝም መስኩ ከፍተኛና ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤ በዚህ ዘርፍም የውጭ ባለሀብቶች በብዛት እንዲሳተፉበት ሊበረታቱ ይገባል፡፡
10.5. ስለ ግብር አቅጣጫዎች
10.5.1. የግብር አወሳሰን ሥርዓት በጥናትና በትክክለኛ ገቢ እና ወጭ ላይ የተመሰረተ፣ ከአድልዎ የፀዳ፣ ግልፅነት እና ተጠያቂነት ያለው ሊሆን ይገባል10.5.2. የግብር እና ቀረጥ ሥርዓቱ የውጭ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ ሊሆን ይገባል
10.5.3. በበጎ አድራጎት ተግባራት ለተሰማሩ ግለሰቦችና ተቋማት፣ ለዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድል ለሚፈጥሩ ድርጅቶች ግለሰቦችና ተቋማት የግብር ቅነሳ ወይም የመክፈያ ጊዜ እፎይታ ሊያገኙ ይገባል
10.5.4. በደምወዝ ላይ ያለው የግብር መጠን የዋጋ ግሽበቱን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ሊሻሻል ይገባዋል
10.5.5. በትርፍ ላይ ያለው ግብር ኢንቨስትመንትን በሚያበረታታ መልኩ ሊሻሻል ይገባዋል፡፡
10.6. ስለ መሠረተ ልማት አቅጣጫዎች
10.6.1. የባቡር፣ የተሸከርካሪ መንገድና የአዉሮፕላን ማረፊያዎች በመንግስት ወጭ እንዲሰሩና ያሉትም
እንዲስፋፉና እንዲጠገኑ ልዩ ትኩረት ሊያገኙ ይገባል፤ እንዲሁም የግል የሀገር ውስጥም የውጭ ባለሀብቶች በመስኩ እንዲሰማሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይገባል፤ በተለይ በዚህ ዘርፍ ከለጋሽ ሀገራትና ከዓለም የገንዘብ ተቋማት ጋር በቅርበት ሊሰራ ይገባል
10.6.2. የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ትኩርት ከብዛት ወደ ጥራት ተሸጋግሮ፣ የዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቁ ሊሆኑ ይገባቸዋል፤ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ልዩና የማይቆራረጥ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውሃ አቅርቦት ሊቀርብላቸው ይገባል፤ ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ አገልግሎት እንዲያገኙ ድጋፍ ሊደረግ ይገባል
10.6.3. በዓለም አቀፍ ህግ ጥላ ስር የሆኑ የኒውክሊየር የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እንዲገነቡ ሊደረግ ይገባል፤
10.6.4. ለብዙሃኑ ህዝብ የሚዳረስ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
በማህበራዊው በኩል ያለን መርህ በቀዳሚነት የሰው ልጆች በሙሉ አንድ መሆናቸውን የሚያምን፣ ከዚያም በቀዳሚነት በኢትዮጵያዊነቱ፣ ብሎም በሁሉም ማንነቶቹ የሚኮራ ዜጋን ከፍ የሚያደርግ ሀገራዊ ድባብ መፍጠር ነው፡፡ ለዚህም የኃይማኖት፣ የቤተሰብ፣ የትምህርት፣የጤና፣ የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የባህል፣ የኪነ ጥበብ፣ የአካባቢ ጥበቃና የስፖርት ዝርዝር ፖሊሲዎች እንዲወጡ ሊደረግ ይገባል፡፡
11.1. ስለ ኃይማኖት አቅጣጫዎች
11.1.1. ማንኛውም ዜጋ የፈለገውን ኃይማኖት የመከተል የማራመድና የማስፋፋት መብቱ የተጠበቀ ሊሆን ይገባል
11.1.2. መንግስታዊ ኃይማኖት አይኖርም፤ መንግስት በኃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ ሊገባ አይገባም
11.1.3. የኃይማኖት ተቋማት መንግስትን የመተቸትና የመገሰፅ ህጋዊ መብት ሊኖራቸው ይገባል፤ ሆኖም፣ የመንግስትን ስልጣን በቀጥታ ለመቆጣጠር የሚንቀሳቀስ የኃይማኖት ተቋም ሊኖር አይገባም
11.1.4. በሀገራችን ኢትዮጵያ በኃይማኖቶች መካከል መቻቻል እና መከባበር እንዲኖር ድርጅታችንና አባላቱ በሙሉ ተግተው ሊሰሩ ይገባል፡፡11.2. ስለ ትምህርት አቅጣጫዎች
11.2.1. የትምህርት ፖሊሲ ዋነኛ ትኩረት ከብዛት ወደ ጥራት ሊዞር ይገባል
11.2.2. የትምህርትን ጥራት የመጠበቅና የመከታተል ኃላፊነት የመንግስት ሊሆን ይገባል
11.2.3. ሁሉም ወላጆች ከስድስት ዓመት አንስቶ ልጆቻቸውን የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የማስገባት ግዴታ ሊጣልባቸው ይገባል
11.2.4. ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከ1 – 12ኛ ክፍል በነፃ የመማር መብትና ግዴታ ሊኖረው ይገባል፤ ለከፍተኛ ትምህርት የወጪ መጋራት አሰራር ተግባራዊ ሊሆን ይገባል
11.2.5. ሥርዓተ ትምህርትን ለመቅረፅ መምህራን፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣ ወላጆችና ተማሪዎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል
11.2.6. መደበኛ ትምህርት ከአንደኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍሎች የተከፋፈለ ሊሆን ይገባል፤ በዚህም መሰረት አንደኛ ደረጃ ከአንደኛ እስከ ስድተኛ ክፍል መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ከሰባተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ሆኖ ሊዋቀር ይገባል
11.2.7. የዓለም የሳይንስና ቴክኖለጂ ቋንቋ ለሆነው እንግሊዘኛ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ የትምህርት ፖሊሲ ሊቀረፅ ይገባል፤ ትምህርቱን የሚሰጡት መምህራን በቂ እውቅት እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ፖሊሲም መሆን ይገባዋል11.2.8. የኢትዮጵያዊያን መግባቢያ የሆነው ዐማርኛ ቋንቋ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአግባቡ እንዲሰጥ የሚያደርግ የትምህርት ፖሊሲ ሊኖር ይገባል
11.2.9. በዋናነት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ያነጣጠረ የትምህርት ፖሊሲ ሊኖር ይገባል
11.2.10. ሁሉም ተማሪ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ የቀለም ትምህርት ሊከታተል ይገባል፤ ከአስራ ሁለተኛ ክፍል በኋላ የሙያ ትምህርት መከታተል ለሚፈልጉ ተጨማሪ ስልጠና እንዲያገኙ ሊደረግ ይገባል፤ በቀለም ትምህርት ለመቀጠል የፈለጉ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲገቡ ሊደረግ ይገባል
11.2.11. በመንግስት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሕፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ወይም ወላጆች
በሚመርጡላቸው ቋንቋ እንዲማሩ ሊደረግ ይገባል
11.2.12. መለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች (ከሰባተኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል) ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሊያስተምሩ ይገባል
11.2.13. ሀገር አቀፍ የትምህርት ደረጃን በጠበቀ መልኩ የግል ት/ቤቶች በመረጡት ቋንቋ እንዲያስተምሩ ሊፈቀድላቸው ይገባል
11.2.14. ልዩ ትምህርት ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ችግሮቻቸውን ግምት ውስጥ የሚያስገባ የትምህርት ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል11.2.15. በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎችን የሚያበረታታ ዝርዝር ፖሊሲ ሊቀረፅ ይገባል
11.2.16. በትምህርት ዘርፉ የግል ባለሃብቶችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በስፋት እንዲሳተፉ የሚያበረታታ ፖሊሲ ሊቀረፅ ይገባል
11.2.17. መምህራንና የትምህርት ባላሙያዎች(የግል የመንግሰት ሳይባል) እንዲከበሩ፣ የሙያ ብቃታቸውን እንዲያዳብሩ፣ የተሻለ ጥቅምና ማበረታቻዎች እንዲያገኙ ሊደረግ ይገባል፡፡11.3. ስለ ጤና አቅጣጫዎች
11.3.1. ከጤና ተቋማት ግንባታ ባልተናነሰ በጥራት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ፖሊሲ ሊቀረፅ ይገባል
11.3.2. በሽታን አስቀድሞ ለመከላከልና ለህፃናት ክትባት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ ፖሊሲ ሊኖር ይገባል
11.3.3. የጤና ባለሙያዎች ብቃት ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ ፖሊሲ ሊቀረፅ ይገባል
11.3.4. ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች፣ አቅመ ደካሞችና የተለየ ትኩረት የሚስፈልጋቸው ነፃ ህክምና ሊያገኙ ይገባል
11.3.5. መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በመንግስት የጤና ተቋማት ሲገለገሉ ተመጣጣኝ ክፍያ እንዲከፍሉ ሊደረግ ይገባል፤ ይህንንም ተፈፃሚ ለማድረግ ደምወዝተኞች ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው የጤና መድን (ኢንሹራንስ) እንዲያገኙ የሚያስችል ሀገራዊ አሰራር ሊዘረጋ ይገባል
11.3.6. በወረርሽኝ መልክ የሚሰራጩ በሽታዎችን የሚከታተልና የሚቆጣጠር መንግስታዊ ተቋም ማቋቋም ያስፈልጋል
11.3.7. የጤና ባለሙያዎች ወደ ሌሎች ሀገራት እንዳይሰደዱ የሚከላከል ፖሊሲ ሊቀረፅ ይገባል
11.3.8. በጤናው ዘርፍ መንግስት ወሳኝ ድርሻ እንዲኖረው የሚያስገድድ ነባራዊ ሁኔታ ቢኖርም፣ የግልና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም በዘርፉ እንዲሳተፉ የሚያበረታታ ፖሊሲ ሊኖር ይገባል፡፡
11.4. ስለ ማህበራዊ ዋስትና አቅጣጫዎች
11.4.1. በመንግስትም በግል ድርጅቶችም ያሉ ሠራተኞች የማህበራዊ ዋስትና ሽፋን ሊያገኙ ይገባል
11.4.2. ሰራተኞች በጡረታ ወይም በፕሮቪደንት ፈንድ የመጠቀም መብታቸው ሊጠበቅላቸው ይገባል፤
ጡረተኞች በዋጋ ግሽበት እንዳይጎዱ አስፈላጊው የህግ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል
11.4.3. መንግስት በጦርነት፣ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ግዴታ ሊጣልበት ይገባል
11.4.4. የአካልና የአእምሮ ጉዳተኞች፣ ረዳት የሌላቸው ህፃናትና አረጋውያን እንክብካቤና ጥበቃ
እንዲደረግላቸው ህገ መንግስታዊ ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
11.5. ስለ ሴቶች አቅጣጫዎች
11.5.1. ሴቶችን ያገለለ ማንኛውም ዓይነት ፖሊሲ ውጤታማ እንደማይሆን ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ሊሰራ ይገባል11.5.2. ሴቶች በፖለቲካው መስክ በስፋት እንዲሳተፉ የሚያበረታታቸው ፖሊሲዎችን በድርጅትም በመንግስትም ደረጃ ሊቀረፅ ይገባዋል
11.5.3. የሴት ባለሀብቶችን በብዛት ለመፍጠር የሚያስችል ፖሊሲዎች መቅረፅ ያስፈልጋል
11.5.4. ሴቶች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያላቸውን ተሳትፎ የሚያሳድጉ ፖሊሲዎች ሊቀረፁ ይገባዋል
11.5.5. ሴቶችን ከጥቃትና ከአድልኦ የሚከላከሉ ጠንካራ ህጎች ማውጣት ያስፈልጋል፡፡
11.6. ስለ ወጣቶች አቅጣጫዎች
11.6.1. ወጣቶች በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችላቸውን ድርጅታዊና መንግስታዊ ፖሊሲ ሊቀረፅ ይገባዋል
11.6.2. ወጣቱን ደረጃ በደረጃ ከጫት፣ ከሺሻና ከተለያዩ ሱሶች ለመታደግ የሚያስችሉ የህግ ድንጋጌዎች መውጣት ይገባቸዋል፤
11.6.3. ወጣቱን በተለይ ከጫት የሚያላቅቀው ሀገራዊ ንቅናቄ መፍጠር ያስፈልጋል
11.6.4. ወጣቱ ተቀጣሪ ከመሆን ስራ ፈጣሪ እንዲሆን የሚያስችል መጠነ ሰፊ የብድር፣ የስልጠና፣ የምክርና የክትትል ስርዓት መፍጠር የሚያስችል ፖሊሲ ሊቀረፅ ይገባል፡፡
11.7. ስለ ባህል አቅጣጫዎች
11.7.1. ባህሎቻችን ዓለም አቀፋዊ እውቅና እንዲያገኙ፣ እንዲሁም ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲሰጡ የሚያስችል ፖሊሲ ሊቀረፅ ይገባል 11.7.2. ጎጂ ባህሎችን የሚከላከሉ ህጎች ማውጣት ያስፈልጋል
11.7.3. ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በኢትዮጵያ ያሉ ባህሎችን እንዲያውቁ እና ብሄራዊ ስሜታቸውን እንዲያጎለለብቱ የሚያስችል ፖሊሲ በትምህርት ፍኖተ ካርታ ውስጥ ሊካተት ይገባል፡፡11.8. ስለ ኪነ -ጥበብ አቅጣጫዎች
11.8.1. ኪነ-ጥበብ እንዲያድግና እንዲጠናከር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል
11.8.2. የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በነፃነት እንዲሰሩ የህግ ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል
11.8.3. ለኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የአእምሮ ፈጠራና የባለቤትነት መብት የሚያስከብር ጥብቅ ህግ ሊወጣ ገባል፤ ህጉንም ለማስከበር የሚያስችል ቁርጠኛ የመንግስት አመራር ሊኖር ይገባል
11.8.4. የኪነ-ጥበብ ሙያን ለማዳበር የማሰልጠኛ ተቋማት እንዲያስፋፉ ሁሉን አቀፍ ጥረትና ድጋፍ ሊደረግ ይገባል፤11.9. ስለ አካባቢ ጥበቃ አቅጣጫዎች
11.9.1. የተፈጥሮ ሀብትን ከብክለት ለመታደግ የሚያስችል ጠንካራና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ፖሊሲ ሊኖር ይገባል11.9.2. የአካባቢ ጥበቃ ህጎች ኢንቨስትመንትን እንዳይጎዱ ተደርገው መቀረፅ ይገባቸዋል
11.9.3. በአካባቢ ጥበቃ ላይ የተሰማሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ግለሰቦች ሊበረታቱ ይገባል
11.9.4. የቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራዎች ከቆሻሻ ማጠራቀሚያነት አልፈው ለመልሶ መጠቀም፣ ለማዳበሪያነት፣ ለኃይል ምንጭነት እንዲውሉ የሚያስል ፖሊሲ ሊቀረፅ ይገባል
11.9.5. ኢንዱስትሪዎች አካባቢን ሊበክሉ የሚችሉ ተረፈ ምርታቶችን በተለየ መልኩ እንዲያስወግዱ
የሚያስገድድ ህግ ሊወጣ ይገባል፡፡
11.10. ስለ ስፖርት አቅጣጫዎች
11.10.1. ሀገራቸውንና ራሳቸውን የሚያስጠሩ ምርጥ ስፖርተኞችንና ብድኖችን ለማፍራት የሚያስችል ዝርዝር የስፖርት ፖሊሲ መቅረፅ ያስፈልጋል
11.10.2. የተለያዩ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው ሊንቀሳቀሱ ይገባል11.10.3. ለስፖርትና ለመዝናኛ የተመደቡ ቦታዎች ሊስፋፉ ይገባል
11.10.4. የግል ባለሀብቶች የስፖርት ተቋማትን እንዲያስፋፉ ሊበረታቱ ይገባል፡፡11.11. ስለ ማህበራት አቅጣጫዎች
11.11.1. ዜጎች የጋራ ጥቅምና መብቶቻቸውን ለማስከበር መንግስታዊ ባልሆኑ ማህበራት ተደራጅተው
የመንቀሣቀስ መብታቸው የተከበረ ሊሆን ይገባል
11.11.2. ሀገራዊ የሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የገንዘብ ምንጫቸውን ካለምንም ገደብ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ እንዳያገኙ የሚገድባቸው ህግ ሊኖር አይገባም
11.11.3. መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በቀጥታ ለመንግስት ስልጣን የማይወዳደሩ ቢሆኑም፣ ለመረጡት የፖለቲካ አመለካከትም ሆነ ድርጅት ድጋፍ የመስጠት መብታቸው ሊጠበቅላቸው ይገባል
11.11.4. ዓለም አቀፋዊ የሆኑ የሰብዓዊ መብትና ግብረ ሰናይ ማህበራትና ድርጅቶች በህግ አግባብ እንዲንቀሳቀሱ ሊፈቀድላቸው ይገባል፤ በፖለቲካ ውሳኔም እንዳይዘጉ የህግ ጥበቃ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
+