የሞራል ግዴታችንን እንወጣ !
ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ላሉት ለሀገርና ሕዝብ ተቆርቋሪ፣ የሰላም ታጋዮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም፣ አስካለ ደምሌ ጎን መቆማችንን በተግባር እናሳይ።
ነገ ማክሰኞ ጥቅምት 9, 2014 ዓ. ከጠዋቱ 3:00 ሰአት ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንገናኝ።
ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ላሉት ለሀገርና ሕዝብ ተቆርቋሪ፣ የሰላም ታጋዮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም፣ አስካለ ደምሌ ጎን መቆማችንን በተግባር እናሳይ።
ነገ ማክሰኞ ጥቅምት 9, 2014 ዓ. ከጠዋቱ 3:00 ሰአት ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንገናኝ።
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ነገ ማክሰኞ ጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጧት 3 ሰዓት ላይ ችሎት ይቀርባሉ።
በመሆኑም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ላይ በመገኘት ክርክሩን እንድትዘግቡ ባልደራስ ጥሪ ያቀርባል።
ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ላሉት ለሀገርና ሕዝብ ተቆርቋሪ፣ የሰላም ታጋዮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም፣ አስካለ ደምሌ ጎን መቆማችንን በተግባር እናሳይ።
የሞራል ግዴታችንን እንወጣ!
ነገ ማክሰኞ ጥቅምት 9, 2014 ዓ. ከጠዋቱ 3:00 ሰአት ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንገናኝ።
እስክንድር ነጋ! የህሊና እስረኛ፣
ቂልንጦ አዲስ አበባ !!
1.1 —ረሃብ ወደ መሥራቱ መሸጋገር
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ያለው ጦርነት ያለ ምክንያት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት አልሳበም፡፡ ሶስትና አራት ከባድ ከበድ ከበድ ያሉ ምክንያቶች አሉ ።ግን አንዳቸውም ከአንዣበበው ረሃብ በላይ አይደሉም፡፡ ልብ እንበል፡፡ ያንዣበበው አደጋ ድርቅ አይደለም፡፡ ዘንድሮ የዝናብ ችግር የለም፡፡ ድርቅ የሌለበት ረሃብ ነው ያንዣበበው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ረሃብ፣ “ሰው ሰራሽ ረሃብ” ይባላል፡፡ ድሮ የምናውቀው ረሃብ፣ ተፈጥሮ (ማለትም፣ ድርቅ) የሚያመጣብንን ነበር፡ አሁን እኛ ራሳችን ረሃብ ወደ መሥራቱ ተሸጋግረናል፡፡
ያለንበትን አውድ እናስቀምጠው፡፡ የአው ዱ እውነታ፣ ፈረንጆቹ “Subjective truth – ሃሳባዊ እውነት” የሚሉት ዓይነት አይደለም፡፡ መሬት ላይ የተደረገ ውጊያ ውጤት ነው፡፡ በዚያ ውጊያ፣ ሕወሓት የሰሜን እዝን አስቀድሞ በማጥቃት ጦርነት ጭሯል፡፡ የፌድራል መንግሥቱ የተከፈተበትን ጦርነት ከመከላከል ውጭ አመራጭ አልነበረውም፡፡
ሻዕቢያ ጣልቃ ባይገባ ኖሮ፣ በዐቢይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ይወድቅ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ሁሉም ሀገራት የውጭ ጦርን
ወደየግዛታቸው የማስገባት ሉዓላዊ መብት እንዳላቸው ባያከራክርም፣ የውጭ ጦር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ የመፍቀድ ሥልጣን ያለው ሥራ አስፈፃሚው ነው? ወይስ ህግ አውጪው? ለሚለው ጥያቄ ያለው መልስ ግልፅ አይደለም፡፡ ወደፊት ማከራከሩ አይቀርም፡፡
1.2—የአሸናፊዎች ፍትህ
ጦርነቱ ከተቀጣጠለበት ጊዜ አንስቶ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍሎች- ትግራይ፣ዐማራና አፋር – የወጡ ዜናዎች የጅምላ ግድያዎችና አስገድዶ መድፈሮች፣ መጠነ ሰፊ የንብረት ውድመቶች መድረሳቸውና እየደረሱ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል። እነዚህ ዜናዎች በስመ- ጥር የሰብዓዊ መብት ተቋማት በከፊል ተረጋግጠዋል፡፡ ሙሉ ስዕሉ ጦርነቱ ካለቀ በኋላ የሚወጣ ይሆናል፡፡
ለሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ግኝቶች የተሰጠው ምላሽ ጉራማይሌ ሆኗል፡፡ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኩል፣ አብዛኞቹ ሀገራት ዝምታን ቢመርጡም፣ ምዕራባዊያንን በከፊል በድንጋጤ፣ በከፊል “በቀጣይነት ምን ሊመጣ ይችላል?” በሚል ስጋት ተቀብለውታል፡፡ በአሜሪካ በኩል (ሌሎችን ምዕራብያዊያንን ሳይጨምር)፣ በአባይ ጉዳይ የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ እንደ አንድ ተጨማሪ ግብዓት ልትጠቀምበት አትፈልግም ማለት አይቻልም፡፡
የትራምፕ አስተዳደር በአባይ ጉዳይ ገለልተኛ አልነበረም፡፡ በተለይ በመጨረሻዎቹ የሥልጣኑ ወራት፣ ግብፅ ወታደራዊ እርምጃ እንድትወስድ እስከማደፋፈር ደርሷል፡፡ የባይደን አስተዳደር የትራምፕን ያህል ፅንፍ ይሄዳል ተብሎ ባይገመትም፣ በጂኦ ፖለቲካው ሂሳብ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለግብፅ የላቀ ዋጋ እንደሚሰጣት ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥትም የተሰጠው ምላሽ የተደበላለቀ ነው፡፡ በአብዛኛው፣ ይጠቅሙኛል ያላቸውን እያጎላ፣ ይጎዱኛል ያላቸውን ደግሞ፣ “የምዕራብያዊያን ሴራ ነው” በማለት አጣጥሏቸዋል፡፡ በሌላ በኩልም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን በማመን፣ ወታደሮችን አስሮ ክስ እንደመሰረተባቸፈው ገልጿል፡፡ በተጨማሪ፣ የተባበሩት መንግሥታት የምርመራ ቡድን ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ እንዲያጣራ አድርጓል፡፡ ከምር ይሁንም አይሁንም፣ ተጠያቂነት መኖር እንዳለበት ተቀብሏል፡፡
በአንፃሩ ሕወሓት፣ ተዋጊዎቹ ፈፀሟቸው የሚባሉትን የመብት ጥሰቶች ካለመቀበሉም ባሻገር፣ ለይስሙላ እንኳን ጉዳዩን ለማጣራት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አላደረገም፡፡ ሆኖም፣ ገለልተኛ አካላት ቢያጣሩ ተቃውሞ እንደማይኖረው ተናግሯል፡፡ ወደደም ጠላም፣ በዚህ ጉዳይ በእነ ዐቢይ ተበልጧል፡፡
ግን፣ በሕወሓትም በኩል ሆነ በቀሪዎቹ ተተላሚዎች ዘንድ፣የተሟላ ተጠያቂነት ለማስፈን ልባዊ የሆነ ፍላጎት የለም፡፡ አሁን እንዳለው አካሄድ ከሆነ፣ በመጨረሻ “የአሸናፊ ፍትህ- victor’s justice” የሚሉት ነው እውን የሚሆነው፡፡ ይህ ማለት፣ ተሸናፊው ተጠያቂ ይሆናል፡፡ የአሸናፊው ግፎች ግን ተሸፋፍነው እንዲታለፍ ይደረጋል፡፡ ይህ እንዳይሆን፣ለፍትህ የቆሙ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ብርቱ ትግል ይጠብቃቸዋል፡፡
1.3 —-የእጅ አዙር ጦርነት (Proxy war) አደጋ
በዚህ አውድ፣ ቻይናና ሩሲያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር፣ አብዛኞቹ ምዕራብያዊያን ደግሞ ከሕወሓት ጋር ተሰልፈዋል፡፡ ቻይናና ሩሲያ ጦርነቱ በድርድር እንዲያልቅ ቢፈልጉም፣ እነሱንም ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ ከምትጨቃጨቃቸው አሜሪካ ጎን ተሰልፈው መገኘት አልፈለጉም፡፡ እነ ዐቢይ ምንም አሉ ምንም፣ ምዕራብያዊያን ሕወሓት ወደ ሥልጣን እንዲመለስ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ቀደም ብለን ያነሳናቸው ነጥቦች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዋናው ጉዳያቸው ኢትዮጵያም እንደ ሶሪያ የታራዘመ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ልትገባ ትችላለች የሚለው ስጋታቸው ነው፡፡ እነ ዐቢይም ሆነ ሕወሓት፣ጦርነቱን የማሸነፍ ብቃትና አቅም አላቸው ብለው አያምኑም፡፡ ትክክል ይሁኑ አይሁኑ፣ በሂደት ይታያል፡፡
ኃይማኖትን፣ ታሪክን፣ ባህልን፣ ቋንቋን እንደ መለኪያ የምንወስዳቸው ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ከጥቁር አፍሪካ ይልቅ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ታጋድላለች፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓዊያን እስከሚተኳቸው ድረስ፣ አረቦችና ኦቶማኖች( ቱርኮች) በአፍሪቃ ቀንድ ያሉትን የባህር በሮች (ወደቦች) በሙሉ ለአንድ ሺህ ዓመታት በእጃቸው አስገብተው፣ አካባቢውን በበላይነት ተቆጣጥረው ኖረዋል፡፡
በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ድጋፍ ኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል መቻሏ፣ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ከአፍሪቃ ቀንድ መልቀቅ በጀመሩበት አውሮፓዊያን እግር፣ የአረብ ሀገራት እየተተኩ መሆናቸው አመላክቷል፡፡ በአሁኑ ግዜ፣ ቱርክ፣ ሳውዲ አረቢያና የተባበሩት ኤመሪትስ በአፍሪቃ ቀንድ ያሏቸው የጦር ቤዞች ስድስት ደርሰዋል፡፡ የሰሜኑ ጦርነት በፍጥነት ካልተቋጨ፣እነዚህ ኃይሎች በተዘዋዋሪም ቢሆን ጣልቃ መግባታቸው አይቀርም፡፡ ይህ ከሆነ፣ ጦርነቱ በቀላሉ የሚቋጭ አይሆንም፡፡ አደጋው ከፍ ያለ ነው፡፡
እውነት ለመናገር፣ ከእኛ ይልቅ ምዕራብያዊያ አደጋውን በተሻለ ደረጃ ተረድተውታል፡፡ በየመን፣ በሶሪያና በሊቢያ የሆነው ይታወቃል፡፡ በየመን አላልቅ ባለው ጦርነት፣ በአንድ በኩል ሳውዲና ኤመሬትስ፣ በሌላ በኩል ኢራን ተሰልፈው ቅልጥ ያለ የእጅ አዙር ጦርነት (Proxy war) ላይ ይገኛሉ፡፡ የሊቢያው ጦርነት፣ ቱርክና ግብፅ በተዘዋዋሪ የሚፋለሙበት መድረክ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ይባስ ብሎ፣ ምዕራብያዊያና ሩሲያም ተደርበውበታል፡፡ በሶሪው ጦርነት እጃቸውን ያስገቡ ብዙ በመሆናቸው፣ ሶሪያዊያን ሀገራቸውን በቀላሉ አያስመልሱም፡፡
በእኔ ዕይታ፣ ምዕራብያዊያኑ፣ “የሰሜኑ ጦርነት ወታደራዊ መፍትሄ የለውም” የሚሉት ከፖለቲካዊ ይልቅ ወታደራዊ ግምገማ አድርገው የደረሱበት ድምዳሜ ነው፡፡ ግምገማቸው ትክክል ነው፡፡ ያልተረዱት ስሜታችንን፣ ሥነ ልቦናችንን፣ ባህላችንን ነው፡፡ ፖለቲካችንንም አልተረዱትም፡፡ በእኛ በኢትዮጵያዊያን በኩል – በፌድራልም ሆነ በሕወሓት – ወታደራዊ መፍትሄ እንደሌለ በተግባር መሬት ላይ እስካልተረጋገጠ ድረስ፣ ስሜታችን፣ ሥነ ልቦናችን፣ ባህላችንና ፖለቲካችን እውነታውን ቀድም ብለን እንድናምን አይፈቅዱልንም፡፡ ተዋግተን ሳንደክም አንገላገልም።
1.3 — ያልተሰወረ እውነታ
መሬት ላይ ያለውን እውነታ እንቃኘው፡፡ ሕወሓት ጦርነቱን በወታደራዊ ኃይል የማሸነፍ አቅም የለውም፡፡ ወደ አዲስ አበባ ቢገፋ፣ ሻዕቢያ ከበስተጀርባ ውጊያ ይከፍትበታል፡፡ ወደ አሥመራ ቢገፋ፣ መከላከያ ከበሰተጀርባ ውጊያ ይከፍትበታል፡፡ መከላከያና ሻዕቢያ ተጣምረው ጥቃት ከሰነዘሩበት ደግሞ፣ ወይ ይደመሰሳል፣ ወይ ከተሞችን ለቆ ወደ በረሃ ለመሸሽ ይገደዳል፡፡ጥቃቱን በመሥመራዊ ውጊያ የመመከት ዕድሉ የጠበበ ነው። በደቡብ ጎንደር የደረሰበት ሽንፈት፣ የማጥቃት አቅሙ (offensive capability) ጦርነቱን ለማሽነፍ በቂ እንዳልሆነ አሳይቷል፡፡ የጥይት፣ የከባድ መሣሪያ፣ የነዳጅና የመድኃኒት እጥረት አለበት፡፡ ከሱዳን ጋር የሚያገናኘው ኮሪደር እስካልተከፈተ ድረስ፣ ከማጥቃት ይልቅ የመከላከል አቅም ነው የሚኖረው፡፡
እነ ዐቢይ ላስተላለፉት የተናጠል የተኩስ ማቆም ውሳኔ አዎንታዊ ምላሽ ባልሰጠበት ሁኔታ መጠነ – ሰፊ ረሃብ ከተከሰተ ደግሞ፣ ከትግራይ ህዝብ ጋር የመቃቃር እድሉ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ በቀኝም በግራም አጣብቂኝ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ሁለቱም ወገኖች የሚያከብሩት የተኩስ ማቆም ስምምነት ቢኖር፣ ከእነ ዐቢይ ይልቅ ሕወሓት ይበልጥ ይጠቀማል፡፡
በእነ ዐቢይ በኩል፣ ትግራይን በሁለት መንገድ ዳግም መያዝ ይችላሉ፡፡ ከውጊያ አኳያ ብቻ የሚታይ ከሆነ፣ መከላከያና ሻዕቢያ ተቀናጅተው ትግራይን መያዝ ይችላሉ፡፡ ግን ከሻዕቢያ አኳያ፣ ጦርነቱ የሚያስከፍለው የሰውና የቁስ ዋጋ ስለሚኖር፣ በአንድ በኩል፣ የኤርትራ ህዝብ ጦርቱን ይደግፈዋል ወይ? የሚለው ጥያቄ ከምር መታየት አለበት፡፡ ወደ ትግራይ ገባ ብሎ መውጣት አይቻልም፡፡ መሬትን ቆንጥጦ መያዝና መቆየት ይጠይቃል፡፡ በሌላ በኩል፣ የኤርትራ የተዳከመ ኢኮኖሚ ለጦርነቱ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ስለሚቸገር፣ የጉዳዩ ዋና ባለቤት ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋር ወጪን ለመጋራት ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡
ስለዚህም፣ በቀላሉ የማይፈቱ ጥያቄዎች ባሉበት አውድ ከሻዕቢያ ጋር ተቀናጅቶ ትግራይን ከመያዝ ይልቅ፣ በመከላከያ ብቻ የሚፈፀም ተግባር ቢሆን ለእነ ዐቢይ ተመራጩ መንገድ ይሆናል፡፡ የሁለትና ሶስት ወራት ሥልጠና ብቻ በተሰጠው ጦር ይህን ማድረግ እንደሚቻል በኢትዮ–ሱማሊያ ጦርነት ታይቷል፡፡ ግን ይህን ታሪክ መድገም ቢቻል እንኳን፣ ሕወሓትን ከእያንዳንዱ ዋሻ ማጽዳት አይቻልም፡፡ ይህን ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ ደግሞ፣ ከህዝብ ካለው ድጋፍ አንፃር፣ ቀስ እያለ ማደጉ አይቀርም፡፡ ብቃት ያላቸው የጦር አዛዦች፣ ታማኝና ዲሲፕሊንድ የሆኑ ተዋጊዎች አሉት፡፡ በረዥም የግዜ ሂደት፣ ከእነ ግብፅ ጋር መቀናጀቱም አይቀርም፡፡ ይህ እውነታ ከእነ ዐቢይ የተሰወረ አይደለም፡፡
1.4—የኃያላኑ ትብብር
እውነት ለመናገር፣ እነ ዐቢይ የተናጠል የተኩስ ማቆም ውሳኔ በማስተላለፍ ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ቀደም ብለው በተግባር አሳይተዋል፡፡ የትግራይ ህዝብ በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ መሆኑን የሚናገረው ሕወሓት፣ ለህዝቡ ሲል ተመሳሳይ እርምጃ አለመውሰዱ፣በታሪኩ ከፈፀማቸው መሰረታዊ ስህተቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በሕወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አቅም መካከል ክፍተት እንዳለ አመላክቷል፡፡
የጦርነቱ መልክ በትንሽ ሳምንታት ውስጥ ይለያል፡፡ እነ ዐቢይ ለረዥም ጊዜ የተጠበቀውን የማጥቃት ዘመቻቸውን በቅርቡ ይጀምራሉ፡፡ ያኔ፣ ወይ ህወሓት ተንዶ ወደ ዋሻዎቹ ይመለሳል፣ ወይ በተዓምር መክቶ ይዞታዎቹን እንደያዘ ይቆማል፡፡ ጦርነቱ በዚህም ሄደ በዚያ፣ ከማጥቃት ዘመቻው በኋላ ቢያንስ አንዱ ወገን ለድርድር ዝግጁ ይሆናል፡፡ ሁለቱንም ወገኖች የድርድር ጠረጴዛ ላይ ለማስቀመጥ ግን፣ መሬት ላይ ካለው እውነታ ይልቅ፣ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጫና ይበልጥ ውጤታማ የመሆን ዕድል አለው፡፡
በዛላይ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በኩል የሚኖረው ግፊት፣ አሜሪካ፣ቻይና፣ሩሲያና የአውሮፓ ህብረት ካልተባበሩ ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ አይሆንም፡፡ በእነዚህ ኃይሎች መካከል ከባድ ፉክክር ያለ ቢሆንም፣ ፈፅመው ሊተባበሩ የሚችሉ አይደሉም የሚባሉ አይደሉም፡፡ አሁን እንዲተባበሩ የሚያስችላቸው ጉዳይ አለ። ረሃብ በሞት ከሚቀጥፋቸው ሰዎች መካከል፤ ከአራቱ ሶስቱ ከአምስት ዓመታት በታች የሆኑ ህፃናት ናቸው፡፡ አራቱ ኃይሎች (አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ የአውሮፓ ህብረት) የእነዚህን ህፃናት ህይወት ለመታደግ መተባበር ካልቻሉ፣ በምን ጉዳይ ሊተባበሩ እንደሚችሉ ማሰብ ይከብዳል፡፡
አራቱ ኃይሎች ጦርነቱን ለማስቆም መተባበር እንደማይችሉ ተቀብለው፣ ቢያንስ ቢያንስ ግን፣ ጦርነቱ ኖረም አልኖረም፣ ለተራቡት እህል ለማድረስ እንዲተባበሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊማፀናቸው ይገባል፡፡ የተራቡ ወገኖቻችን ከፖለቲካ ይበልጣሉ፡፡ ይህን ታሳቢ ያላደረገው የአሁኑ ሀገራዊ አካሄዳችን፣ በምድርም በሰማይም የሚያስጠይቀን ነው፡፡ የተራቡ ወገኖቻችን ከፖለቲካችን ይበልጣሉ።ይህን ታሳቢ ያላደረገ የአሁኑ ሀገራዊአካሄዳችን፣ በምድርም፣ በሰማይም የሚያስጠይቀን ነው።
በእነ እክንድር ነጋ መዝገብ ላይ ከዚህ በፊት የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እና ሰበር ሰሚ ችሎት “ዳኞች ተሟልተው አልቀረቡም”፣ “መዝገቡን አልመረመርንም”፣ “ፕላዝማ ተበላሽቷል” በሚሉ ሰበቦት እስከ አንድ ወር ድረስ የረዘሙ ተለዋጭ ቀጠሮዎች ይሰጡ ነበር። በዚህም ምክንያት ምስክሮች በግልፅ ችሎት ይቅረቡ?፣ ከመጋረጃ ጀርባ ይቅረቡ?፣ በዝግ ችሎት ይቅረቡ በሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ሲሟገቱ ከአንድ አመት በላይ ሆነ።
ይኸው ጉዳይ ዘንድሮም ቀጥሏል። ከበላይ ፍርድ ቤቱ የተማረው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ዛሬ ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጧት በዋለው ችሎት ቀጣዩን ችሎት በዚሁ ቀን ከቀትር በኋላ ለማድረግ ቀጥሮ ነበር፤ ነገር ግን ከሦስቱ ዳኞች መካከል አንዱ ማለትም የቀኝ ዳኛው ባለመገኘታቸው በቀጠሮው መሰረት ክርክሩን ሳያስቀጥል ቀርቷል። ሁለቱ ዳኞች ብቻ ቢሰየሙም ክርክሩን እንደ ታዳሚ ከማዳመጥ ውጭ ብቻቸውን መፍረድ እንደማይችሉ ለችሎቱ ተናግረዋል። የቀኝ ዳኛው ቤተሰብ ታሞባቸው ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንደሄዱ ሰብሳቢ ዳኛው ተናዘዋል።
ይህንን ሲሉ ከጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት የማውቃት ዝነኛ አባባል ትዝ አለችኝ። “ጋዜጠኛ አይሞትም! አይታመም!” አባባሉ ምንም አይነት ችግር ቢደርስብህ ለጊዜው የተመደብህበትን የጋዜጠኝነት ሚና በጊዜው መወጣት አለብህ የሚል ነው። በዚህ መርህ የእናታቸውን አስክሬን እቤታቸው አጋድመው እንባቸውን እያዘሩ ዜና ለማንበብ ወደ ስቱዲዮ የሚገቡ ጋዜጠኞች ዓለም ላይ በርካታ ናቸው። ወታደር እንኳን በሚያፈገፍግበት ጦር ሜዳ መሀል ገብተው የጥይት ብልጭታ በካሜራቸው የሚቀርፁ ዘጋቢዎች የትየለሌ ናቸው። በርግጥ “የታክሲ ሰልፍ ረዘመ፤ መንገድ ተዘጋጋ” ብለው በዜና ሰዓት ሙዚቃ የሚያስጮሁ ምንግዴ ጋዜጠኞችም ሩቅ ሳንሄድ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ሞልተዋል።
ሰው ጤፉ ዳኛም ታዝዘው ይሁን ወይም ፈቅደው ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት ችሎቱን አጉላልተዋል። እውን ቤተሰባቸው ታመው ከሆነ ፈጣሪ ይማርላቸው። ብዙ ልወቅሳቸው አልፈልግም። የሙያ ስነ ምግባራቸውን ለራሳቸው እተወዋለሁ። ምክንያቱም እንኳን የሙያ ስነ ምግባራቸው ምለው የተሾሙበት፤ የሚያሽቃብጡት ሕገ መንግሥትም ተከብሮ አያውቅም። ግን ግን ድርጊታቸው ችሎት መድፈር አይደለም ወይ? አያስቀጣም ወይ?
ችሎቱ ከጧቱ የቀጠለ በመሆኑ በአጭር ደቂቃ ሊጠናቀቅ የሚችል ነበር። ከልደታ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለመድረስም ከ10 ደቂቃ የሚበዛ ጊዜ የሚወስድ አይመስለኝም። በመሆኑም አንድ አፍታ ከሆስፒታል ተመልሰው ዳኝተው መሄድ የሚችሉበት ዕድል ሙሉ በሙሉ ዝግ አልነበረም። በተጨማሪም ሌላ ዳኛ መተካት ይቻል ነበር። ይህ እንዳይሆን ግን ሁሉም ዳኞች ለስልጠና መውጣታቸውን ሰብሳቢ ዳኛው ተናግረዋል። ቤተሰብ ታመመባቸው የተባሉት ዳኛም ችሎቱ በተሰየመበት ሰዓት የስልጠና አዳራሹ ውስጥ ታይተዋል የሚል ጭምጭምታ ደርሶኛል።
በዛሬው ቀጠሮ ችሎቱ የሁለት ምስክሮችን እማኝነት ሊሰማ የነበረ ቢሆንም ለቀጣዩ ሳምንት ተሸጋግሯል። በዚህም ዳኛው የእነ እስክንድር ነጋ የእስር ቤት እድሜ ላይ የአንድ ችሎት የቀጠሮ ጊዜ ጨምረዋል ማለት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለዐቃቤ ሕግ ሌላ የቅጥፈት ጊዜ ይሰጠዋል።
በጧቱ ችሎት ዐቃቤ ሕግ የምስክሮችን ስም ዝርዝር እና የዳኝነት ጭብጦቻቸውን ይዞ እንደሚቀርብ ቢታዘዝም ተግባራዊ አላደረገም። ይልቁንም በግልፅ ችሎት እንዲመሰክሩ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የታዘዙ ምስክሮች ስም ለመገናኛ ብዙሃን እንዳይጠቀስበት ጠይቋል። ለዚህም ሲባል ስማቸውን ለዳኞች ብቻ በምስጢር ያሳወቀ ሲሆን ለተከሳሾችና ለጠበቆች ግን እንዳይሰጥበት ጠይቋል። ይህ ዝግ እንጂ ግልፅ ችሎት እንዳልሆነ በመጥቀስ እነ እስክንድር ነጋ ተቃውመውታል። “ጧት የተወሰነው አሁን መከበር አለበት። ቢያንስ ይቀርባሉ የተባሉት ሁለት ምስክሮች ማንነት በትዕዛዙ መሰረት አሁን ይነገረን። ስማቸውም በሚዲያ ይፋ ቢደረግ ሕጋዊ ይሆናል። የምስክሮች በሚዲያ ይፋ መሆን ተጠያቂነት (Acountablity) እንዲኖር እንጂ ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ለማስፈራራት አይደለም” ብሏል እስክንድር ነጋ።
በተጨማሪም “ዐቃቤ ሕግ ሐሰተኛ ምስክሮች የማቅረብ ልምድ ያለው ነው” ብሎ ንግግሩን ሲቀጥል ሰብሳቢ ዳኛው ጣልቃ ገብተው እስክንድር ነጋን ለማስቆም ሞክረዋል። እንደዚህ አይነት ድምዳሜ መስጠት ተገቢ እንዳልሆነም አብራሩ።
እስክንድር እንደገና በመቀጠል “እኛ አስር አመት እስር ቤት ስንኖር ይህንን ዐቃቤ ሕግ እናውቀዋለን። በሀሰት ሲከሰን፤ በሀሰት ሲያስመሰክርብን ኖሯል። አሁንም አልተቀየረም። ይሄ መንግሥት ያመነው ጉዳይ ነው። ይሄ ችሎት ሊክደው አይገባም። የሁለቱ ምስክሮች ስም አሁን ይነገረን” አለ።
“ግልፅ ችሎት ማለት ምን ማለት ነው? መስፈርት የለውም ወይ? ከመገናኛ ብዙሃን ከተደበቀ ምኑ ነው ግልፅነቱ? ከዚህ በፊት ተከራክረንበት አይደለም ወይ? ችሎቱ ለምን አቋም አይኖረውም?” በማለት አስቴር ስዩም ጨመረች። ሆኖም ለእነዚህ ጥያቄዎች ሁሉ መልስ መስጠት የሚቻለው ዳኞች ተሟልተው ሲቀርቡ በመሆኑ ውሳኔዎች ወደ ቀጣዩ ችሎት ተገፍተዋል።
“470 ቀን እስር ቤት ውስጥ ነው ያለነው። ልጆቻችን 470 ቀን እያለቀሱ ነው። ዐቃቤ ሕግ ለምስክሮቹ እንደሚጨነቀው ለእኛ ልጆችም ማሰብ ያስፈልጋል” ያለው ስንታየሁ ቸኮል በበኩሉ የኩላሊትና የጉበት ህመም ያለበት በመሆኑ ከእስር ቤት ውጭ ባለ የህክምና ተቋም በግሉ እንዲታከም ጠይቋል። ለዚህም በቀጣዩ ችሎት ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ምላሽ እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱ ጠርቷል።
ዐቃቤ ሕግ ከዚህ በፊት 21 ምስክሮችን እንዲያሰማ የተጠየቀ ሲሆን ከዘጠኝ በላይ ምስክሮችን ማግኘት እንዳልቻለ አስታውቋል። የዘጠኙን ስም ዝርዝር ለዳኞች ብቻ በምስጢር ሰጥቷል። በማነኛቸው ተከሳሾች ላይ እና በምን ውስን ድርጊት ላይ እንደማመሰክሩ የዳኝነት ጭብጥ እንዲያቀርብ ቢታዘዝም ትዕዛዙን ጥሷል። ማንን በምን ጉዳይ ላይ እንደሚያስመሰክር ዝርዝር መግለጫ አለማዘጋጀቱንም ተናግሯል።
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ዛሬ ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በአካል ቀርበዋል። ዐቃቤ ሕግ ሁለት ምስክሮችን በግለፅ ችሎት እንዲያሰማም ለዛሬ ከቀትር በኋላ ማለትም ከቀኑ ከ7:30 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል። የምስክሮችን ስም ዝርዝር እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት ቢያዝዝም ከሳሽ ማቅረብ እንደማይችል ተናግሯል።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ነሐሴ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ምስክሮች በግልፅ ችሎት እንዲሰሙ ማዘዙን አስታውሶ ትዕዛዙን እንዲያከብር አስጠንቅቋል። “የሕግ ልዩ ሁኔታ (exception) አለ። የትዕዛዝ ልዩ ሁኔታ ግን የለም። ይሄ አዲስ እውቀት አይደለም፤ ነባር ነው። በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕጉ አንቀፅ 136 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት ተከሳሾች የሚመሰክሩባቸውን ሰዎች ማንነት የማወቅ መብት አላቸው። ቀድማችሁ ማቅረብ ቢኖርባችሁም የሁለቱን ዝርዝር አሁን አቅርቡ፤ የሌሎችን ደግሞ ከሰዓት በኋላ ይዛችሁ ቅረቡ” በማለት ችሎቱ አዝዟል። ሆኖም ዐቃቤ ሕግ ዛሬ የሚመሰክሩትን ሁለት ሰዎች ስም ዝርዝር በፅሁፍ እንዳልያዘ ገልጿል። ከቀትር በኋላ በሚኖረው ችሎት እማኝነታቸውን ሲሰጡ የሁለቱን ስም እንዲያቀርብ ተስማምተዋል። የሌሎች 19 ምስክሮችን ስም ዝርዝርም በታዘዘው መሰረት እንደማያቀርብ ዐቃቤ ሕግ ተናግሯል። “ገና ከማህበረሰቡ ስላላገለልኳቸው ለደህንነታቸው እሰጋለሁ” ሲልም ገልጿል። ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ዐቃቤ ሕግ የታዘዘውን የማይፈፅም ከሆነ የራሱን አማራጭ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል። ዛሬ ይመሰክራሉ የተባሉ እማኞች በነፃነት ታጋዩ አንደኛ ተከሳሽ እስክንድር ነጋ ላይ ብቻ የሚመሰክሩ ናቸው። የሚመሰክሩበትን የድርጊት ጭብጥ እንዲገልፅ ቢታዘዝም ከሳሽ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ትዕዛዙን እንደማይፈፅ ደመላሽ ኢጄታ በተባለ ዐቃቤ ሕግ አማካኝነት አሳውቋል። በተለይም ከማክሰኞ ጀምሮ የሚሰሙ ምስክሮችን የምስክርነት ጭብጥ ቢገልፅ ማንነታቸውን ማጋለጥ እንደሚሆንበት ጠቅሷል።
ከፊታችን ማክሰኞ ጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ 19ኙ ምስክሮች መሰማታቸውን እንዲቀጥሉ ታዝዟል። በአንድ ችሎት ስንት ምስክሮች መቅረብ እንዳለባቸውም ችሎቱ ዛሬ ከቀትር በኋላ ይወስናል።
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ከአለፈው ዓመት ሐምሌ 14 ቀን በኋላ ዛሬ ጥቅምት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በአካል ቀርበዋል። በዓቃቤ ሕግ ጠያቂነት በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ታግዶ የቆየው የምስክሮች አሰማም ሂደትም ነገ ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ክርክር ተደርጎበት እንደሚቀጥል አዲስ የተሰየሙት ሦስት ዳኞች ተናግረዋል።
ዐቃቤ ሕግ በዛሬው ችሎት ሁለት ምስክሮችን በግልፅ ችሎት እንዲመሰክሩ ይዞ መቅረቡን ተናግሯል። ሆኖም “አሉ፤ መጥተዋል” ከማለቱ ውጭ የችሎቱ አዳራሽ ውስጥ ገብተው አላየናቸውም።
የእነ እስክንድር ጠበቆች የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በፈረደው መሰረት ምስክሮች በግልፅ ችሎት የሚቀርቡ ከሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት የምስክሮች ስም ዝርዝር ቀድሞ ለተከሳሾችና ለጠበቆች መሰጠት እንዳለበት ጠይቀዋል። በዚህም የምስክሮችን ማንነት ለማወቅና መስቀለኛ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ እንደሚያስችላቸው ጠበቆች ሔኖክ አክሊሉ፣ ሰሎሞን ገዛኸኝ እና ቤተ ማርያም አለማየሁ ጠይቀዋል።
ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ስም ዝርዝራቸውን እንዲሰጥ በፍርድ ቤት አለመታዘዙን ጠቅሶ ተከራክሯል። ጠበቆችም ጉዳዩ ቀደም ሲል በተከራከሩበት የምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ መሰረት ሳይሆን በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕጉ የሚታይ በመሆኑ ለብቻው ልዩ ትዕዛዝ እንደማያስፈልገው እና ስም ዝርዝራቸው አስቀድሞ መሰጠት እንዳለበት በወንጀለኛ ሕጉ በግልፅ መቀመጡን ጠቅሰው ሞግተዋል። በተጨማሪም ቀደም ሲል በተወሰነው መሰረት በአንድ ችሎት ቢያንስ አራት ምስክሮች ማቅረብ ሲገባው ሁለት ብቻ ለማቅረብ መጠየቁ አግባብ እንዳልሆነ፤ ይልቁንም ያለ ፍትሕ ጊዜውን ለመግፋት ያለመ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በዚህም መሰረት የምስክሮችን ስም ዝርዝር አስቀድሞ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ወስኗል። ክርክሩ ካለፉት ችሎቶች የቀጠለ በመሆኑ ዳኞች ያለፈውን እንደ ማያውቁትና ለመወሰንም መቸገራቸውን ገልፀዋል። ዶሴውን ሳያነቡት መምጣታቸውንም ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ገና ዶሴው ሲጀመር በቅድመ ምርመራ ከወንጀል ነፃ ተብለው የተሰናበቱና በዚሁ መዝገብ ተከሰው የነበሩ ሰዎችን ስም ጭምር አሁን በክሱ ውስጥ እንዳሉበት አድርገው ዳኛው ሲጠሩ ተደምጠዋል። ሆኖም 6ኛ ተከሳሽ የነበሩትን ስም እንደጠሩ ከ5ኛ ተከሳሽ በኋላ ያሉት በነፃ የተሰናበቱ መሆኑ በጠበቆች ተነግሯቸው ከስህተታቸው ታርመዋል።
አዲሶቹ ዳኞች ራሳቸውን ለችሎቱ ባስተዋወቁበት ጊዜ ሙሉ ስማቸውን አልተናገሩም። ሰብሳቢ ዳኛው ዘላለም እንደሚባሉ ከተናገሩ በኋላ የቀኝ ዳኛው ይልማ፤ የግራ ዳኛዋ ደግሞ አርቡማ እንደሚባሉ ተናግረዋል።
በዛሬው ችሎት እስክንድር ነጋ እና አስቴር ስዩም ከመናገር ተቆጥበዋል። አስካለ ደምሌ ከዚህ በፊት በምርመራ ሰበብ ሲያንገላታት እና በባልደራስ ውስጥ ያላትን የትግል እንቅስቃሴ እንድታቆም መደለያዎችን ሲያቀርብላት የነበረ የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ባልደረባ ባለፈው ነሐሴ 28 ቀን ወደ ምትኖርበት ቃሊቲ ወህኒ ቤት ውስጥ ሄዶ እንዳነጋገራት ተናግራለች። በዚህም የወህኒ ቤት ፖሊሶችና አስቴር ስዩም በነበሩበት “በደል ያደረስኩብሽ በመንግሥት ታዝዤ ነው” ያላት መሆኑን ጠቅሳለች። ይህም ክሱ ሀሰተኛ መሆኑን የሚያስረዳ ከመሆኑም በላይ የደህንነት ባለሙያው በሕግ እንዲጠየቅላት ጠይቃለች። ለምርመራ ይዞት በነበረው የእጅ ስልኳ ውስጥ የነበሩ ሰነዶች መደምሰሳቸውንም ጠቅሳለች።
ስንታየሁ ቸኮል በበኩሉ የኩላሊት፣ የጉበት እና የጥርስ ህመሞች እንዳሉበት ጠቅሶ በፖሊስ አባላት ታጅቦ በመረጠው ሆስፒታል በግል ወጭው እንዲታከም ጠይቋል። አሁን እየታከመበት ያለው የወህኒ ቤት ክሊኒክ ሰዎች ተጣልተው ሲፈናከቱ በፕላስቲክ ከማሸግና ቁስል ከማጠብ የዘለለ አገልግሎት እንደማይሰጥም ተናግሯል።
ፍርድ ቤቱም ጉዳዮችን በቀጣይ ችሎቶች እንደሚያያቸው ገልጿል።
በዛሬው ችሎት አዳራሹ ጠቦ ሰዎች አስከሚመለሱ ድረስ በርከት ያለ ታዳሚ ተገኝቷል። የባለደራስን ምክትል ፕሬዚደንት አቶ አምሀ ዳኘውኝ ጨምሮ የድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣ የምርጫ 2013 ዕጩ ተወዳዳሪዎችና ሌሎችም ተገኝተዋል።
ወገኖቼ ለሚሞተው የዐማራ ህዝብ
ማን ይጩኽለት? ማን ያልቅስለት?
ማን በክብር ይቅበረው? መጠየቅ ያስፈልጋል።
ህገ-መንግስቱን እናስጠብቃለን ባዮችና ምለው የተገዘቱ መሪዎቹ
በአዲስ ምዕራፍ ፤ የወይን ጠጅ ስካር፥ ሁሉም ህዝቡንም ራሱንም ላይመለስ ክዷል፥ አንዱ በዘውድ ክብር ሌላው በንዋይ እቡይነት ድሆቹ ተረስተዋል።
ድርጅቶቹና መሪዎቹ የት ገቡ?
ስለእኛ ፍትህ እጦት ‘ይፈቱ’ ጥያቄ በማህበራዊ ሚዲያ ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ መሆኑን በሰማንበት ቅፅበት ከደም መሬቱ ወለጋ በዐማራ ህዝብ ላይ በተደጋጋሚ በኦህዴድ/ብልፅግና የሰለጠነ ኦነግ ሸኔ በተባለ ፥ አራጅ ቡድን ግፉዓን የዐማራ ተወላጆች በማንነታቸው ብቻና ብቻ እየወደቁ እንዳለ መስማት ለጆሮ እንኳን ይከብዳል። ግን ለምን?
“ክፉ ሰርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ
መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል” ይላል ቅዱስ ጴጥሮስ በትምህርቱ።
ጀግና ግፍ መስራት ሳይሆን ግፈኞችን መታገል ነው ሚናው። በዚች ሁለት ቀን ከወደ ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ሀሮ አዲስ ዓለም ቀበሌ በዐማራ ላይ የተፈፀመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ተጠያቂው ማነው? በማለት እንጠይቃለን። ዐቢይ አህመድ በአዲስ ምዕራፍ ጭፍጨፋውን አጠናክሮ ለመቀጠሉ የሚጠራጠር እንዴት ይኖራል? ይሄን እንድንለማመደው የሰጠን የሁልጊዜ ሞትና መፈናቀል ከሞታችን በላይ፤ ንጉሠ ነገሥቱ እንዳይቀየሙ በሚሉ መስፍኖች ዝምታችን ፈራሁት፥ እነዚህን ሳስብ መንፈሴ በሀዘን ስብራት ከዳኝ። እነዛ በዛ ሀሩር ጫካ የወደቁ ህፃናት፣ እነዛ የጣር ድምፆች የድረሱልን ጥሪ ያሰሙ አረጋዉያን ፣ እነዛ በየጫካው መቀነታቸውን አስረው የሚጮሁ እናቶችን ሳስባቸዉ መሪ እንደሌለው መንጋ እንደገደል ማሚቶ ድምፃቸዉ ለራሳቸው ሲያስተጋባ ማሰቡ እጅግ ያሳዝናል። ኧረ ኡፍፍፍ!
ኦህዴድ/ብልፅግና የተባለ መርዝኛ ድርጅት በመንፈስ አባቱ ኦነግ ሸኔ_ ዐማራን የማጥፋት ተልዕኮ ከእናት ድርጅቱ ውርስ በወሰደው ክፉ ሴራ ዛሬም ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል። ይህን በአይናችን እየተመለከትን የዐማራ ሊሂቃን ዝምታው ያስተዛዝባል። አውቆ በማልመጥ እና በጥቅም በመታወር የሹመት ድንዛዜ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ፍዘት ውስጥ ገብቷል። በወለጋ ጫካ እንደ ጎርፍ የሚፈሰው እነዚህ ዐማሮች ሞታቸው አንገብግቦት ሬሳቸው በጅብ ሲበላ የቆመ ድርጅት የለም። ይመለከተኛል የሚል የክልሉ መንግስት ስለሟቾቹ ዜና መስማት አይፈልግም። በኦህዴድ/ ሸኔ መንግስታዊ ድጋፍ በሰራዊትና በሎጀስቲክ የታገዘ ግድያ ሲፈፀም ያለንበት የመከራ ዘመን እንዴት አይነት የፈተና ጊዜ እንደሆነ ማየት ይቻላል።
እኔ እንደ አንድ ወገን ሁሉም ሰዉ መንግስት አልባ ስለሆኑ እነዚህ ንፁሓን ዐማሮች መጮህ ይገባዋል። የሚሞተው የሰዉ ልጅ ነው እየወደቀዉ ያለው አንገቱ ላይ ባለ ማሕተብ ነው። የሚሞተው አምላኩን በመፍራቱ ነው። የሚሞተው ፍርሃ እግዜር ስላለው በደልን ስለሚጠየፍ ነው።
ይህን እስከመቼ እንታገስ?
በድሆች ሞትና መፈናቀል አዝኜ ራሴን ለማፅናናት ይችን በቅዱስ መፅሐፍ አገኘሁ፦ “ወዳጆች ሆይ እናንተ የተወደዳችሁ ብርቱዎች መከራ በመቀበላችሁ የክርስቶስ መከራ ተካፋይ በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ” ተብሎ እንደተፃፈው በመከራችሁ መሪር ሐዘን ተሰምቶኝ ጩኸታችሁን አምላክ ይመለከት፤ ፍርድም ይሰጥ ዘንድ በፈጣሪ ዘንድ ከልብ እማፀናለሁ። በቃ ይለን ዘንድ ትጉና ለምኑ እንደተባለው ማለቴ ነው።
ያልተሰሰተ ህዝባዊነት -ለሃያ አመታት
—
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ መሥራችና አመራር ፖለቲከኛ #ስንታየሁ ቸኮል በአዲስ አበባ የአፍላነት ጊዜውን በትግል
እያሳለፈ የሚገኝ ታጋይ ነው። አገሩ ኢትዮጵያን ዕጅግ አብዝቶ የሚወደው ስንታየሁ ቸኮል በ1972 ዓ.ም በምስራቅ ጎጃም ደብረኤልያስ በተባለ ታሪካዊ ስፍራ ተወለደ።
ስንታየሁ ቸኮል ገና በተወለደ በሶስት አመቱ ነበር ወደ አዲስ አበባ ከወላጅ እናቱ ጋር በመምጣት ኑሮውን የጀመረው። እድሜው ለትምህርት ሲደርስ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመኖሪያ አካባቢው በሚገኘው ፊት አውራሪ ላቀ አድገህ ትምህርት ቤት በመግባት “ሀ” ብሎ ጀመረ። በፊት አውራሪ ላቅ አድገህ ት/ቤት የጀመረው ቀለም የመቅሰም ጉዞ እስከ አብዮት ቅርስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደርሶ ነበር። ይሁን ዕንጅ በጊዜው የነበረው የ19 93ቱ የተማሪዎች የፖለቲካ የለውጥ እንቅስቃሴ ግለት ሊያስቀምጠው ስላልቻለ፣ ስንታየሁ ቸኮል ወደ ድርጅት ትግል በማምራት ተቀላቀለ።
“ከኢዴፓ” 1993 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2013 ዓ.ም ላለፉት ሃያ አመታት በተለያዩ ድርጅቶች ቁጥሩ የበዛ ዋጋ ከፍሏል። የህወሓት/ኢህአዴግ ከፋፋይ ዘወጌ ብሔርተኝነት አምርሮ ታግሏል። ለህይዎቱ ሳይሳስት ገና በአፍላ እድሜዉ በዶክተር አድማሱ ገበየሁ ይመራ የነበረውን “ኢዴፓን” በ1993 ዓ.ም በመቀላቀል አስቸጋሪ የፈተና ጊዚያትን ጀመረ።
ስንታየሁ ቸኮል በወቅቱ የወረዳ 20 አመራር በመሆን እና በህዛባዊ ቅስቀሳዎች ውስጥ በመሳተፍ በትጋት አገልግሏል። የ”ምርጫ 1997″ የቅንጅት ፓርቲ አባላት እና በዋናነት በወቅቱ የተመለመሉ የምርጫ ታዛቢዎች ተገቢውን ስምሪት በመስጠት ሃላፊነቱን ተወጥቷል። በወቅቱ ዕጩ በመሆን ለተሳተፉት የቅንጅት አመራር አቶ ክፍሌ ጥግነህ በተወዳደሩበት ወረዳ 20 ምርጫ ጣቢያ 1 -ዋና ታዛቢ በመሆን እና ተገቢውን ሃላፊነት በመጣት ከፍተኛ ዉጤት አስመዝግቧል።
የ”1997 ምርጫ” ውጤትን ህወሓት/ኢህአዴግ”አልቀበልም” ማለቱን ተከትሎ በ1998 ዓም በተፈጠረው ህዝባዊ ቁጣ ሰበብ፣ስንታየሁ ቸኮል በህውሓት የደህንነት ቡድን ታፍኖ በዝዋይ እስር ቤት ስምንት ወራትን በሰቆቃ አሳልፏል።
የመጀመሪያው ዕጅግ አስቸጋሪ የዕስራት ጊዜ ነበረ። የቅንጅት ከፍተኛ አመራር በነበሩት ፕ/ሮ መስፍን ወልደማሪያም፣ ወ/ሪ ብርቱካን ሚዴቅሳ፣ ኢንጅነር ግዛቸዉ ሽፈራው፣ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ እና በሌሎች ጉምት አመራሮች አሰባሳቢነት በድጋሜ በ2001 ዓ.ም አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ተቋቋመ።በዚህ ወቅት የፓርቲው መስራች አባልና የአዲስ አበባ ወጣቶች ኃላፊ በመሆን ስንታየሁ ቸኮል እስከ 2007 ዓ.ም አገልግሏል።
በህዎሓት/ኢህአዴግ የትግል ዘመን ከዘጠኝ ጊዜ በላይ በማዕከላዊ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ እና በሸዋሮቢት እየታሰረ የህወሓትን አምባገነናዊ ስርዓት በልበ-ሙሉነት ተጋፍጧል። በወቅቱ በኢትዮጵያ ብሎም በአዲስ አበባ የህዝብ ቁጣ በተቀሰቀሰ ቁጥር የህወሓት ደህንነቶች ሰበብ እየፈለጉ ስንታየሁ ቸኮልን በተደጋጋሚ የእስር ሰላባ ሲያደርጉት ባጅተዋለ።
በትህነግ/ኢህአዴግ ተደጋጋሚ አፈናና ዕንግልት ከትግል ሜዳ ያልራቀው ጀግናው ስንታየሁ ቸኮል፤ ከአንድነት ፓርቲ መልስ ሰማያዊ ፓርቲን በመቀላቀል ትልቅ የትግል ጀብዱ ፈፅሟል።
ስንታየሁ ቸኮል ቤተሰቡን እና ኑሮውን በመተው ለህይዎቱ ሳይሳሳ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት እና ዕኩልነት ታግሏል። ወጣቱ ፖለቲከኛ ቤተሰቡን የሚወድ፣ ህዝብን አክባሪና የምስጉን ባህሪ ባለቤት መሆኑን በቅርበት የሚያውቁት ይመሰክሩለታል።
ስንታየሁ ቸኮል የአሁኑ የኦህዴድ/ኦዴፓ/ ሊቀ መንበር እና የወቅቱ ጠ/ሚንስትር ወደ ስልጣን ሲመጡ፣ በወቅቱ ባሰሙት የኢትዮጵያዊ አንድነት ዲስኩር ዕውነት መስሎት ድጋፍ ከሰጧቸው ፖለቲከኞች መካከል እንዱ ነበረ። ሰኔ 16 2010 ዓ.ም የተካሄደውን የድጋፍ ሰልፍ ሃሳብ ከማመንጨት ጀምሮ ፣ ዋነኛ የሰልፍ አስተባባሪና ባለቤት በመሆን አጋርነቱን በተግባር አሳይቷል።
ወጣቱ ፖለቲከኛ በዚህ ደረጃ የደከመለት አዲሱ አስተዳደር በቅፅበት ሃዲዱን መሳቱን በመረዳት ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን ለዳግም ትግል ተነሳ። ይህንን ተከትሎ “የአዲስ አበባ የባለቤትነት” ጥያቄ እንዲጎለብት እና እንዲቀጣጠል የትግሉን ችቦ ከለኮሱ አንዱና ዋነኛ ሰዎች ውስጥም ሆነ።
በ2011 ዓም የቀድሞው “ባለአደራው” የአሁኑ ባልደራስ ፓርቲ ሲቋቋም ሀሳብ በማመንጨት የአዲስ አበቤን ትግል ከጉምቱ ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ ጋር በመሆን እንዲጀመር ተግቷል።
በአደረጃጀት መዋቅር ውስጥ ጉልህ የአመራርነት ሚና በመውሰድ ለላቀ ትግል በመዘጋጀት በነበረበት ወቅት በኦህዴድ/ አመራሮች ሰኔ 17/2011 ዓም በአማራ ክልል እና አዲስ አበባ በተፈጠረ ችግር ሰበብ በማድረግ ለስድስት ወር በእስር እንዲቆይ ፈረዱበት።
በተረኛው ኦህዴድ ዳግም ዕስራት ያልተሰለቸው ስንታየሁ ቸኮል የቤተሰብ ኃላፊነቱን ለውዷ ባለቤቱ ወዴ በመተው ላዳግም ከፍ ላለ ትግል ቆርጦ ተነሳ።በዚህ ሂደት የባልደራስ ለዕውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲን ከመመስረት ጀምሮ ተቋሙን በድርጅት ጉዳይ ሃላፊነት እና በስራ አስፈፃሚነት በመያዝ “የአዲስ አበባን የባለቤትነት” ጥያቄ ያቀጣጥለው ጀምር።በአዲስ አበባ ቅርሶች ሲፈርሱ፣ዜጎች በማንነታቸው ሲፈናቀሉ፣የጋራ መኖሪያ ቤቶች(ኮንደሚኒየሞች) በታከለ ዑማ መሪነት ሲዘረፉ፣መሬት ሲወረር፣አስተዳደራዊ ቦታዎች በአንድ ቋንቋ ተናገሪዎች ሲሞላ እግር ከዕግር እየተከተለ በድፍረት ለዓለም ህዝብ ያጋልጥ ያዘ።በዚህ ድርጊቱ በተረኛው ኦህዴድ ያልተወደደው ስንታየሁ ቸኮል ጥርስ ውስጥ ገባ።
ይህንን ተከትሎ ሰኔ 22/2012 ዓ.ም የአርቲስት አጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ምክንያት በማድረግ የኦህዴድ/ብልፅግና ተረኛው ስርዓት ስንታየሁን ከፓርቲው ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋ፣ከሴቶች አደረጃጀት ሰብሳቢ አስካለ ደምሌ እና የክ/ከተማ አደራጃ ቀለብ ስዮም ጋር ታፍነው ታሰሩ። ተረኛው ስርዓት በጀመረው የሴራ ፖለቲካ የበሬ ወለደ ክስ በማዘጋጀት ያለ ፍትህ አንድ አመት ከሶስት ወራት በእስር እየማቀቀ ይገኛሉ። ስንታየሁ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ነው። ሶስት ልጆቹን እና ታታሪዋን ውዷ ባለቤቱን ውዴን ትቶ፣ ለሰላማዊ ህዝባዊ ትግል በመቆም ዛሬ ላይ በግፍ ስለ ነፃነት ሲል በቂሊንጦ ወህኒ ቤት ይገኛል።
ወጣቱ ፖለቲከኛ ስንታየሁ ከኢዴፓ እስከ አንድነት ፓርቲ፣ ከሰማያዊ እስከ ባልደራስ ባደረገው ፍፁም ሰላማዊ ትግል ምክንያት በአምባገነኖች አስራ አንድ ጊዜ ታስሯል። ተንገላቷል። ቤተሰቡን በመተው ጭምር ለህዝብ ጥያቄ ዋጋ ከፍሏል።
“እኛን ማሰር ይቻላል፤ የትግሉን መንፈስ ማሰር ግን አትችሉም።” በሚለው አባባሉ የሚታወቀው ስንታየሁ ቸኮል ዛሬም ስለ ፍትህ በእስር ቤት ዋጋ እየከፈለ ይገኛል።
ስንታየሁ ቸኮል ንፁህ ነው። ፍቱት!!!
የህሊና እስረኞች ባስቸኳይ ይፈቱ !!!
ጥቅምት 2014
ወግደረስ ጤናው