የደራ አማራን የዘር ጭፍጨፋ አስመልክቶ ከባልደራስ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
በወያኔ መራሹ ኢሕአዲግ መንግሥት በሥራ ላይ እንዲውል የተደረገው የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት እና ህገ መንግሥቱ ያዋለደው የነገድ ፖለቲካ እንዲሁም የነገድ ፖለቲካው ያዋቀረው የቋንቋ ፌደራሊዝም በአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ፍጅት እንዲፈጸም በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይ የኦሕዲድ ብልጽግና ሊቀመንበር የሆኑት ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ የሃገሪቱ መሪ ከሆኑ ጀምሮ በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው ጭፍጨፋ በዓይነትም ሆነ በቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡
ደራ በሰሜን ሸዋ ዞን የምትገኝ 85 በመቶ አማሮችና 15 በመቶ ኦሮሞዎች የሚኖሩባት አካባቢ መሆኗን የታሪክ መዛግብት ይመሠክራሉ፡፡ ደራ – ሸዋን፣ ጎጃምን እና ወሎን የምታገናኝ ሥፍራ ናት፡፡ በህወሃት ይመራ በነበረው የኢህአዴግ የሥልጣን ዘመን ህወሃት እና ኦህዲድ ባካሄዱት ስምምነት ከአማራ ተነጥቃ ለኦሮሚያ መሰጠቷ አይዘነጋም፡፡ የደራን ነባር ዲሞግራፊ ለመቀየር የኦሮሚያ አመራሮች የተለያዩ ተግባራትን መፈጸማቸው ይታወቃል፡፡ ነዋሪው በሚደርስበት ተጽዕኖ ምክንያት ወደ አማራ ክልል እንመለስ ብሎ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ መንግሥት ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ብሎ የሚጠራው የኦነግ ጨፍጫፊ ቡድን የደራን ሕዝብ በመግደልና በማፈናቀል ተግባር ላይ መሠማራቱ የዘወትር ዜና ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ሰሞኑንም የአሸባሪው ኃይል አባላት የደራ ዋና ከተማን ጉንዶ መስቀልን እና በዙሪያዋ ያሉ አካባቢዎችን በመውረር ከ70 በላይ አማሮችን በግፍ ገድለዋል፡፡
ኦነግ-ሸኔ የሚል የዳቦ ስም የተሰጣቸው የኦነግ እና የኦህዴድ ህገ-ወጥ ታጣቂ ኃይሎች አማራን የመጨፍጨፍ እና የማፈናቀል እንቅስቃሴቸውን አጠናክረው በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በሻሸመኔ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በሰሜን ሸዋ – አጣዬ፣ ገብረ ጉራቻ፣ ደራ . . .፣ በምዕራብ ሸዋ – ዳኖ፣ አምቦ፣ . . . ፣ በምዕራብ እና በምሥራቅ ወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች አማራውን በአሰቃቂና በአሳዛኝ ሁኔታ የመግደል፣ ንብረቱን የመዝረፍና የማውደም፣ ከሞት የተረፉትን ኗሪዎች ከቀያቸው የማሰደድ ድርጊቶች ሲፈጸምባቸው ቆይቷል፡፡ እነዚህ ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ተግባራት ሰሞኑንም በሰሜን ሸዋ ደራ እና በወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች አለማባራት ቀጥለዋል፡፡
የደራ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ህዳር 10/2015 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ በላከው ደብዳቤ የሸኔ ቡድን በጀማ በረሃ ውስጥ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ከፍቶ አሸባሪዎችን እየፈለፈለ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ በደራ ላይ ከሰባት ጊዜ በላይ ወረራ አካሂዶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግደሉን፣ እንዲሁም የደራ መንገድ በአሸባሪዎቹ ከተዘጋ አንድ ዓመት ያለፈው መሆኑን ጠቅሷል፡፡ የደራ አማራ በዘሩ እየተመረጠ የሚፈጸምበትን ግድያ ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዲያስቆሙለትም የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴው ተማጽኖውን በደብዳቤ አቅርቧል፡፡
በአብዛኛው በግብርና ሙያ በመሰማራት ከራሳቸው በተጨማሪ ለሌሎች ወገኖቻቸው የሚተርፉት የደራ አማሮች ዛሬ በዘረኞች ከቀያቸው ተፈናቅለው በአዲስ አበባ እና በሌሎችም አካባቢዎች በየጎዳናዎቹ ፈሰው እጆቻቸውን ለልመና ሲዘረጉ ማየት ምንኛ አሳዛኝ ነገር ነው፡፡
በደራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት አስከፊ ተግባር ለማስቆም መንግሥት ለጊዜው በሚከተሉት እርምጃዎች ማለትም፣
1. በደራና ባካባቢው እየተፈጸመ ያለውን ጭፈጨፋ ለማስቆም መንግሥት ባስቸኳይ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ሥፍራው በማስገባት ሕዝቡን እንዲያስጠበቅ፣
2. ኦነግ ሸኔ ተብሎ በሚጠራው እና በጀማ በረሃ አካባቢ በሚገኘው ማሰልጠኛው ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወስድ፣
3.ሽብርተኛው እየፈጸማቸው ባሉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው በመመለስ በቂ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በመስጠተ እንዲቋቋሙ እንዲያደርግ፣
4.የደራ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ላቀረባቸው ጥያቄዎች በጎ ምላሽ እንዲሰጡ፣
ባለደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በአጽንኦት ያሳስባል፡፡
የባልደራስ ለዕውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
ህዳር 16/2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ