የካቲት 12፤ እየወደቁ የማሸነፍ ተምሳሌት
(የህሊና እስረኛው ስንታየሁ ቸኮል ከቃሊቲ ወህኒ ቤት ያስተላለፈው መልዕክት)
አገር ወዳዶቹ አብርሐ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በግራዚያኒ ላይ በሠሩት ጀብዱ ከ30 ሺህ በላይ ወገኖቻችን ወድቀዋል። የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን ነው። ነገር ግን የካቲት 23 ደግሞ የድል ቀን ነው። የአድዋ ቀን ነው። የማሸነፍ ቀን ነው። እየሞቱ ማልቀስ ብቻ ሳይሆን እየወደቁ ድል እንዳለ አድዋ ምስክርነቱን ሰጥቷል።
እንደ እግዜአብሔር ፈቃድ በቀጣዩ አመት የሰማዕታቱን መታሰቢያ ቀን መንገድ ተዘግቶ ከሚከበሩ በዓላት በእኩል ድምቀት በሰፊው እናከብራለን።
የካቲት 23 እንዳሸነፍነው ሁሉ በምርጫ ሰራዊት ይህንን ጀብዱ መድገም የዚህ ትውልድ ሓላፊነት ነው። 84ኛው የየካቲት 12 ሰማዕታት ዓመታዊ መታሰቢያ ቀንን ስናከብር እያለቀስን መኖር ብቻ ሳይሆን እየወደቅን ማሸነፍም እንዳለ በጣሊያን ማሳየታችንን ያስታውሰናል። በግራዚያኒ ማሳየታችንን መልሶ ይነግረናል።
ጣሊያን በድጋሜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ሽንፈቱን በበቀል ለመቀየር ነበር። ይሁን እንጂ በወቅቱ የነበሩ አባቶች ዋጋ ከፍለው አገር አስረክበውናል። ይህንን የነፃነት ተጋድሎ የዛሬው ትውልድ ሊደግመው ይገባል። አንባገነንነትን ሊያሸንፍ ይገባል።
መላው የአዲስ አበባ ወጣት፣ መላው ሕዝባችን፣ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ከፋፍለህ ግዛው ያመጣብህን የሴራ ፖለቲካ ለመጨረሻ ጊዜ በካርድህ በማሰናበት በምርጫ ሰራዊት ድገመው። በዚህም የአባቶቻችህን ድል ከልስ። ይህ የሰማዕታቱን አደራ መጠበቅ ነው።
በመጨረሻም የዚህ ትውልድ አባል ሆይ ከፊትህ አድዋ ይጠብቅሀል። የምርጫ አድዋ ቁሞልሀል። የተዘጋውን በር በምርጫ ካርድ ማስከፈት የታሪክ ግዴታ ነውና ከፊታችን ድል ቁሟል። ዛሬም አድዋ አለ! ዛሬም ድል አለ!
ክብር ለጀግኖች አባቶቻችን!
ክብር ለሰማዕታቱ!