የባልደራስ የምርጫ ዘመቻ ዝግጅት ማብቂያ ፕሮግራም ላይ የተደረገ ንግግር
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ባለፉት አራት ወራት የቅድመ ምርጫ እንቅስቃሴው በሃራዊ እና በአዲስ አበባ ነክ ጉዳዮች ፓርቲው የሚያራምደውን ፖሊሲዎች ለከተማው ሕዝብ በተለያዩ መድረኮች እና የቅስቀሳ ዜዴዎች ለማሳገንዘብ ጥረት ሲደርግ ቆይቷል፡፡
በሃገር አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያለውን አመለካከት በሃገር አቀፍ ማኒፌስቶው አስፎሮ አሰራጭቷል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማን ሕዝብ በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ/ም በሚካሄደው ምርጫ ቢመርጠው፣ ስር የሰደዱ የከተማይቱን ችግሮች ለመፍታት የነደፋቸውን ፖሊሲዎች ደግሞ በአዲስ አበባ ማኒፌስቶው አማካይነት በዝርዝር አቅርቧል፡፡
በዛሬው የቅድመ ምርጫ የባልደራስን የምረጡን ቅስቀሳ መርሃግብር መጠናቀቂያ ፕሮግራም ላይ ፓቲያችን ባልደራስ ለአዲስ አበባ ሕዝብ ለማስገንዘብ የሚፈልጋቸው ጉዳዮች ለየት ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህም ጉዳዮች ፓርቲችን ባልደራስ በተመለከተ በኦህዴድ/ብልፅግና በገሃድ ጥብቅና በቆሙለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ በስውር እየተነዛብ ያለውን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ምንነት ይፋ በማውጣት ባልደራስ የማይወክሉ መሆናቸውን አስረግጠን ለማቅረብ ነው፡፡
1ኛ/ አዲስ አበባን በተመለከተ በመርህ ደረጃ ልዩ ጥቅም አራማጆች ጋር በመርህ ደረጃ የማንስማማ መሆኑን፣ በአንድ ሀገር ሕዝብ መካከል አንዱ ጥቅም ሰጭ፣ አንዱ ጥቅም ተቀባይ እንዲሆን መፈለጉ ህጋዊም ዲሞክራሲያዊም አይደለም የሚለው አቋማችን ለምን ጊዜም አይቀየርም፡፡ እንደዚህ ዓይነት አባባል በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መካተቱ አግባብ አለመሆኑን ደጋግመን ገልፀናል፡፡ ሕገ መንግስቱም በሕዝብ ይሁንታ እንዲቀየር ለሪፈረንደም እንዲቀርብ በሰላማዊ መንገድ የምንታገልለት የፀና አቋማችን ነው፡፡
ይህ አቋማችንን የማይቀበለው የኦሮሞ ሕዝብ ሳይሆን የነገድ ፓለቲካ አራማጆች የሆኑ የኦሮሙማ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ናቸው ብለን እናምናለን፡፡ ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎቱ ከሌሎች ወንድም ከሆኑ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ጋር በአንድ ሃገር ሕዝብነት ሰሜት በሰላም፣ በእኩልነት እና በወንድማማችነት የጋራ ሃገራችንን ኢትዮጵያን እያለማ የጋራ ተጠቃሚ ሆኖ መኖርን እንደሆነ እንዳችም ጥርጥር የለንም፡፡ ይሁንና የማንነት ፖለቲካን ካላራመዱ የሕዝብ ድጋፍ እንደማያገኙ የተራዱ የኦሮሞ ፅንፈኛ የነገድ ፖለቲከኞች ባልደራስ የኦሮሞን ሕዝብ እንደሚጠላ በማስመሰል ፓርቲያችን ላይ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ሲነዛብን ቆይቷል፡፡ ባልደራስ ኦሮሞ ማበረሰብ ጋር አንዳችም ጠብ የለውም፡፡ ምክንያቱም የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ወንድም የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች የተለዩ ጥቅም ይሰጠኝ ብሎ ጠይቆ እንደማያውቅ፣ ይህን ጥያቄ የሚያራግቡት ፅንፈኛ ብሄርተኞች ብቻ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ከእነሱም ጋር ቢሆን ፓርቲያችን ባልደራስ ከተመሰረተ ጀምሮ እስካሁን ሲያደርግ እንደቆየው የሚታገለው በሰላማዊ መንገድ እና በሰላማዊ የፖለቲካ ዘይቤ ብቻ ነው፡፡ ባልደራስ የሚያራምደው የፖለቲካ አስተሳሰብ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ማህበረሰቦች በጋራ ጥቅም መርሆች አማካይነት በሰላም አብረው እንደኖሩት በዚያው መልክ እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ፖለቲካን በሰለጠነ፣ በዘመነ፣ በፀብ ሳይሆን በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ልዩነት መፍታት የሚቀበል ይህን አካሂድ ብቻ የሚያራምድ የፖለቲካ የተከተለ ነው፡፡
የኦሮሞ ማህበረሰብን ጨምሮ ሌሎችንም በርካታ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ዘላቂና መሰረታዊ ጥቅም የሚከበረው በሰላማዊ መንገድ እንጅ በፀብ እና በብጥብጥ እንዳልሆነ ፓርቲያችን ባልደራስ የፀና እና የማይናጋ አቋም አለው፡፡
ሌላው በፓርተያችን ላይ የብልፅግና ፓርቲ በጥቅም በመግዛት በደጋፊነት ባሰማራቸው የኢትዮጵያ ሙስሊም በማይወክሉ ብድኖች ባልደራስ ፀረ- እስላም ነው እሉ ስለሚያስነዙት የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ነው፡፡ ባልደራስ እንደሌሎች ፅንፈኛ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ታሪክ ትርክት ሰለባ አይደለም፡፡ ባልደራስ ጥንታዊ ሃገራችን ኢትዮጵያ የአብርሃም ኃይማኖቶች የሆኑት የክርስትና የእስልምና እና የአይሁድ ኃይማኖቶች ጥንታዊ መዳረሻ እንደሆነች ይቀበላል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ እነዚህ ኃይማቶች ከመነጩበት ከመካከለኛው ምስራቅ ብትወርስም ከራሷ ባህልና ልማድ ጋር አዋህዳ፣ ወዝና ጠረኗን በውስጣቸው አስርጻ ፍፁም ሀገራዊ እምነቶች እንዲሆኑ አድርጋ ኮትኩታ በማሳደግ በህዝቡ ውስጥ ስር እንዲሰዱ አድርጋለች፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም ሀገሮች ቀድማ እነዚህን ወንድማማች የአብርሃም ኃይማኖቶች ሀገራዊ ቅርፅና መገለጫ እንዲኖራቸው አድርጋ ያቆየቻቸው ኃይማኖቶች በመሆናቸው ፓርቲያችን ባልደራስ በኢትዮጵያ ክርስትና እና በኢትዮጵያ እስልምና መካከል አድሏዊ ፖለቲካ አይከተልም፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ታላላቅ ኃይማኖቶች የሚያራምዷቸው እምነቶች ከኢትዮጵያ ልዩ ሀገራዊ ባህሪ ጋር የተቆራኙ መሆናቸውን ፓርቲያችን ያለማወላወል ይቀበላል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በሃገራችን ያለው ሕዝብ የተቀበላቸው ኃይማኖቶች በእውነተኛ እኩልነት እና ነፃነት እምነታቸውን ማራመድ፣ የእምነት ጉዳዮቻቸውን አለ መንግስት እና ፖለቲካ ተፅእኖ፣ ጫና፣ አድሏዊ እና ጣልቃ ገብነት ሳይደረግ በራሳቸው በአማኞችና አማኞች በነፃነት በሚቀበሉት አመራር ብቻ እየተመራ ሊከናውን ይገባል የሚል ፅኑ እና የማይናወጥ አቋም አለው፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ ቢመርጠውም በማናቸውም ሁኔታ ሳያዛንፍ ተግባራዊ የሚያደርገው ይህንኑ አቋሙን እንደሆነ ለክርስትና እና ለእስልምና ቤተ እምነቶች እና ለምእመናኖዎቻቸው ለማስገንዘብ ይፈልጋል፡፡ ፓርቲችን ባልደራስ ለሙስሊም ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ለማስገንዘብ የሚፈልገው ሰላምን ወንድማማችነት፣ እውነትን፣ ለጋስነትን፣ ከሚያስተምር ቂምና ጥላቻን፣ ራስ ወዳድነትን የሚያወግዝ ኃይማኖታዊ አስተምህሮን የሚከተል ወገናችን ከሆነው ሕዝብ ሙስሊም ጋር በፍቅር እና በሰላም እና የአንድ ሃገር ልጅነትን አብሮ መኖርን እንጅ ምንም ዓይነት የጥላቻ አመለካከት የማናራምድ መሆናችንን እንዲገነዘብልን እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ ውጭ አንድ እምነትን የሚያገል አመለካከት ለሀገር ሰላም ጠንቅ መሆኑን ጠንቅቆ የሚገነዘብ ፓርቲ ነው፡፡
በፓርቲያችን ላይ የሚነዛው ሌላው ሃሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ደግሞ ባልደራስ በአዲስ አበባ ህዝብ ቢመረጥ የብልፅግና አባል የነበሩ የከተማው መስተዳድር ሠራተኞችን ከሥራ ያባርራል እየተባለ የሚነዛው የሃሰት ወሬ ነው፡፡ ባልደራስ በከተማው ቢመረጥ የብልፅግና አባል የሆኑ የመንግስት ሰራተኞችን ማባረሩን ተገቢ ነው ብሎ አያምንም፡፡ የፓርቲ አባልነታቸውን እንደጠበቁ የመንግሥት ሥራ መበስራት እንዲቀጥሉ እናደርጋለን፡፡
ሌላው በፓርቲያችን ላይ እየተነዛ ያለው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ባልደራስ በፀብ እና በፍጥጫ የሚያምን ፓርቲ ነው ስለሚባለው ነው፡፡ ባልደራስ የሚያራምዳቸውን የፖለቲካ አመለካከቶች በደም ፍላት እና በስሜት የተቀበላቸው አመለካከቶች አይደሉም፡፡ አውጥቶ አውርዶ፣ መክሮ እና አስመክሮ፤ በሰነድነት ሰንዶ ለሃገራችን ኢትዮጵያ በአጠቃላይ እና ለአዲስ አበባ ሕዝብ በተለይ ይበጃሉ ብሎ የተቀበላቸውን ነው፡፡ ባልደራስ ከፀብ እና ከፍጥጫ ሃገራችን ኢትዮጵያም ሆነች የሁላችንም ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ ይጠቀማሉ ብሎ ለአንድ ደቂቃም አምኖ አያውቅም፡፡ በዚያው ልክ ተረኝነትን፣ አድርባይነትን፣ ተቅለስላሽነትን ይፀይፋል፡፡ ፓርቲችን ባልደራስ እውነትን እውነት፣ ሃሰትን ሃሰትን ነው ብሎ በይፋ መቆምን እንደ ትክክለኛ መርህ አድርጎ ይቀበላል፡፡
ልዩነት በገሃድ እውጥቶ በፀብ አጫሪነት ሳይሆን በውይይት መፍታትን፣ በውይይት የማይፈታ ነገርን በማሳደርና መልሶ ለውይይት በማቅረብ፣ በዚያም መልኩ ካልተፈታ በሰላማዊ መንገድ በሪፈረንደም በህዝብ ዳኝነት እንዲፈቱ ለማድረግ በፅናት የሚታገል ፓርቲ ነው፡፡ በማጎብደድ የሃገር እና የሕዝብ ችግር ይፈታል የሚል እምነት የለውም፡፡ አሁን እየታዩ እንዳለው አካፋን አካፋ ማለት ካልተቻለ ሀገር እና ህዝብን ወደ አስከፊ ሁኔታ እየተመራ እንደሆነ ማስገንዘቡ አስፈላጊ ነው፡፡ ፓርቲችን በዚህ አጋጣ ሃገራችን ለገባችበት ሁለንተናዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ቀውስ መፍትሄው በመንግስት እና በአጋሮቹ ፍላጎት ብቻ በተፅእኖ የሚገፋው “ብሄራዊነት” የሌለው ምርጫ ሳይሆን አካታች በመሆኑ መልኩ የሚጠራ እና የሚካሄድ ብሔራዊ ውይይት እንደሆነ ፅኑ እምነት አለው፡፡፡፡
በዚህ አጋጣሚ ወንድም በሆነው የትግራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ፣ ጦርነቱ ተሳታፊ ባልሆኑ ዜጎች ላይ በሃገር መከላከያ አባላትና በኤርትራ ጦር እየደረሰ ያለውን ጥቃት፣ በክልሉ ሴት እህቶቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን የፆታዊ መደፈር ፓርቲችን ባልደራስ በፅኑ የሚደርሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ባልደራስ በፅኑ ያወግዛል፡፡ ፓርቲችን ባልደራስ በትግራ እየደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ የፖለቲካዊና ወታደራዊ ቀውስ ፍልሚያ ተከትሎ በአካባቢው እያንዣበበ ያለው የርሃብ አደጋ ህዝቡን ክፉኛ እየጎዳው መሆኑን ስለሚገነዘብ በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ የሕወሓት ተልእኮ ተሸካሚ ያልሆኑ የትግራ ልሂቃን ከአማራው የፖለቲካ ልሂቃን እና ከሌሎች ሃገራዊ ኃይሎች ጋር በመገናኘት የድህረ ሕወሓት የግትራይ የፖለቲካ ቀውስ ስለሚፈታበት ሁኔታ ምክክር እንዲደርጉ ፓርቲያችን ለሚመለከታቸው የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ኢትዮጵያ ከሃያላን ምዕራባውያን ጋር የገባችበትን የሃገራዊ ግንኙነት ቀውስ በተመለከተ የፓርቲያችን የባልደራስ አመለካከት ግልፅ ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ በቅድሚ የአባይ ወንዝ መገደብ ለኢትዮጵያ ልማት ቁልፍ ግብዓት መሆኑን ፓርቲችን ያምናል፡፡ በመሆኑም የብልፅግና መንግስት እየተዘጋጀበት ያለውን የግድቡን ሁለተኛ ሙሌት በታቀደለት ፕሮግራም መሰረት መሞላቱን ፓርቲያችንን ባልደራስ በፅኑ የሚደግፍ ሲሆን፣ ይህን አስመልክቶ ምዕራባዊያን ሃያላን ሀገሮች የሚያራምዱትን ለግብፅ እና ለሱዳን ያዳላ አቋም ፓርችን በፅናት ይቃወመዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰሜን ምዐራብ ድንበር በወራሪ የሰሜን የሱዳን ሠራዊት ተጥሶ እና ስፋት ያለው የሃገራችን ሉዓላዊ ግዛት ተወሮ ባለበት ሁኔታ፣ ይህን ወረራ ለመቀልበስና የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ለማስመለስ አንዳችም ተጨባጭ እርምጃ ሲወስድ የማይታየው የብልፅግና መንግሥት ምዕራባውያን ሃያላን ሀገሮች ባለሥልጣኖች ላይ ያደረጉትን የጉዞ ማዕቀብ እና ቀድሞውንም የሚታወቀውን የህወሓት ደጋፊነታቸውን በማጣቀስ የሃገራችን ሉዓላዊነት እንደተደፈረ አድርጎ የሚያቀርበው ፕሮፖጋንዳ አሳዛኝ ነው፡፡ የኤርትራ ጦር ትግራይ ውስጥ እንዲቆይ መደረጉ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ የማያስገባ መሆኑን ለማድበስበስ ይፈልጋል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ፓርቲያችን ባልደራስ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃገሮች መሆናቸውን ቢገነዘብም፣ በሁለቱም ሀገሮች ያለው ህዝብ በኃይማኖት፣ በቋንቋ በባህል እና በፌደል ሳቀር የተሰናሰለ አንድ ህዝብ መሆኑን ያምናል፡፡ ቀደም ሲል ወደ መለያየት ያመሩ ምክንያቶች ታርመው፣ የሁለቱ ሃገሮች ግንኙነት በወታደራዊ ጉዳዮች ከመረዳዳት በዘለለ ወደ ስርዓት መነግስታት ጥምረትነት ደረጃ ከፍ እንዲል ቢደረግ ለሁለቱም ሃገሮች ሕዝብ ይጠቅማል የሚል የፀና አመለካከት አለው፡፡
በመጨረሻም ባልደራስ 6ኛውን የምርጫ የሀገራችን ህዝቦች በታሪካቸው በድምፃቸው መንግሥትን የሚመርጡበት፣ የህዝብ ድምፅ በትክክል የሚከበርበት እንዲሆን ፓርቲያችን ይመኛል፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ገዥው ፓርቲ ጨምሮ ለነፃ ፍትሃዊና ሰላማዊ ምርጫ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን በትህትና እናቀርባለን፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ
ድል ለዲሞክራሲ!!!