ውድ ኢትዮጵያውያን እንዳንዘናጋ በመጨረሻው የመሸጋገሪያ ድልድይ ላይ እንገኛለን!!!
ግልፅ ነው ኢትዮጵያን ለማላቅ ቅን የሆኑ በርካታ እንዳሉን ሁላ አብዛኞቹ ግን በፍረሃት አዙሪት ተውጠዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉት ራስ ወዳድ ሆነውም ታዝበናል፡፡ የታላቋን ኢትዮጵያ ፍሬ ለማየት የሌሎችን መስዋትነት መጠበቅ መብታቸው እስኪመስል ድረስ ዳር ይዘው የሚገኙም በዝተው ተገኝተዋል፡፡ ለምን? ብሎ መጠየቁ በራሱ ምላሽ የሌላው ፈተና በመሆን ቀጥሎብን ይገኛል፡፡
በአንድ አገር እየኖሩ አገር ያለችበትን ሁኔታ እየተረዱ እንዲሁም የገዛ ወገንን ማህበረሰባዊ ምስቅቅልን እየሰሙ ለመፍትሔው አለመተባበሩ ምን ያህል የበዛ እራስ ወዳድነት ነው? የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡ እርግጥ ነው ጥቂት ነገር ግን አደገኛ የሆኑ የአገር ፍቅር የሌላቸው በካይ አሰናካዮች እንዳሉን እንረዳለን፡፡ በርካታ ገዢ ሐሳብ ያላቸው እንዳሉ ሁላ የሐሳብ ባዶ እራስ ወዳዶች እንዳሉንም አናውቃለን ፡፡ ግን ለምን? ብለን ዛሬም ጠልቀን ለመጠየቅ ግን እንገደዳለን?:::
እኛ ባልደራሶች ቢቻል እውነት፣ ቅንነት፣ ቀናነት እና መልካም-ሥነ ምግባር እንደ አገር ከዳር ዳር መላቁ ስብዕናችን ቢሆን እንመርጣለን፡፡ ግባችን ለመላ ሕዝባችን የተመቸች፣ ከአድልዎ የነፃች፣ ለእኔ ሳይሆን ለኛ የሚል ትውልድን በገፍ የገነባች፣ የትም ሠርተን፣ የትም ነግደን እና ተዋልደን በነፃነት እና ያለስጋት የምንዛዞርባት ታላቋን ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ እንታትራለን፡፡ መለያየትን በመጠየፍ፣ ለአንድነት እና ለመመጋገብ የተጋች እንዲሁም ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ምሳሌ እና አርዓያ የሆነች ታላቋን ኢትዮጵያን ተጋግዞ ለመገንባት የሡልጡንነት እና ሠላማዊ መንገዱ ምርጫ እና በምርጫ ብቻ የመሸናነፍ ሡልጡንነት ነው ብለን ለሂደቱ ዘውትር በቅንነት እንትጋለን፡፡
ይሁን እንጂ በዘመናችን ፍፁም የሆኑ ሰወኛ ጥያቄዎች ይወዘውዙናል፡፡ ራስን ከማንገስ በላይ ለሌላ ደሃ ወገን በርግጥ የሚጠቅም ሂደት ነውን ብሎ ማሰብን፣ በማይገባ ሥነ ምግባር ከመድከም ይልቅ በሕዝብ ለመዳኘት መምረጥን፣ ከመጠላለፍ ይልቅ በሐሳብ የበላይነት ለመገዛት መወሰንን፣ ለገዛ የተመቸ ኑሮ ከመጨነቅ ይልቅ እንደ ሰወኛ ፍጡር ሌላው ወገኔስ ብሎ መጨነቅን፣ በማይገባ ተግባር ለመቅደም እና ለመቀዳደም ከመትጋት ይልቅ በእውነት መገዛት እና መግዛትን የመረጠ ትውልድ መገንባትን ሂደቱ ያዘለ ነውን? ወዘተ የሚሉት ናቸው፡፡
ውድ የአዲስ አበቤ ነዋሪዎች ምንም ሆነ ምን ወሳኙ የምርጫ ካርድን ያለተስፋ መቁረጥ በመያዝ ለውሳኔ መዘጋጀቱ ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡ ማጉረምረሙ፣ መውቀስ እና መወቃቀሱ ብቻ አያሻግረንም ደሞም በእድገት ከፍ አያደርገንም፡፡ መፍትሔው የጥበበኞች መፍትሔን በፍጥነት በገፍ መጨበጡ ብቻ ነው፡፡ እርሱም የምርጫ ካርድን የትም ገብቶ እና ፈልጎ በመያዝ የዴሞክራሲ ሥረዓታችንን ለማላቅ መትጋቱ የጊዜው ብቸኛው አማራጭ ነው ብሎ ከልብ ማመኑ ተገቢ ነው፡፡ በርካታ አገራት የሠለጠኑትም ሆነ የማህበረሰባቸውን ፍላጎት በገፍ ያሟሉት ይሄኛውን አማራጭ የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት ልቀታቸው ነው፡፡
ታዲያ እኛስ ውድ መላ አዲስ አበቤዎች ለተሻለ ብቃት እና ሐሳብ ቅድሚያ ከመስጠት በላይ ምን አማራጭ አለን እንዲሁም ምንንስ ይዘን እንጠብቃለን?
በኢንጅነር ዓለማየሁ ንጋቱ
ድል ለእውነተኛ ዴሞክራሲ