ኦነግ ሸኔ በከፈተው ጦርነት ምክንያት የአ.አ- ጎጃም መስመር ተዘጋ
“መንግስት ካለ መረጃውን ለህዝብም ለመንግስትም አድርሱልን”። ይህ መልእክት ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም ሲጓዙ የነበሩ ተሳፋሪዎችና ሹፌሮች ያስተላለፉት መልክት ነዉ።
በዛሬው እለት ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ጎጃም መስመር ሲጓዙ የነበሩ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች፣የጭነት መኪኖች፣እስክሬን የጫኑ መኪኖች፣ የግለሰብ መኪኖች እንዲሁም አገር አቋራጭ ነዳጅ እና ሸቀጣሸቀጥ የጫኑ መኪኖች በሙሉ አሊ ዶሮ አካባቢ ኦነግ ሸኔ በከፈተው ከፍተኛ ጦርነት አማካኝነት መንገድ ላይ ለማደር ተገደዋል።
መረጃውን ያደረሱን ተጓዦች እንደሚሉት በአካባቢው እጅግ ጠንካራ ጦርነት ነው እየተካሔደ ያለው። እነዚህ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ግለሰቦች በተጨማሪም እጅግ ብዛት ያለው መከላከያ እኛን እያለፈ ከወደ አዲስ አበባ ወደ አሊ ዶሮ ወይም ጦርነቱ ወደ አለበት ቦታ ሲጓዝ ቢታየም፤ አሁን ሰላም ነው እለፉ የሚላቸው አካል አላገኙም። በማከልም “ህፃናት፣ አዛውንቶች፣ በሽተኞች፣ ሬሳ የጫኑ ሀዘንተኞች ሳይቀሩ መንገድ ላይ አድረናል” ብለዋል።
የሚደርስልን መንግስት ባይኖርም እንኳ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቅልን መረጃውን አድርሱልን ሲሉ ተማፅኗቸውን አሰምተዋል።
ይህ መረጃ እስከደረሰን ሰአት ድረስ ከአዲስ አበባ ጎጃም የሚያስኬደው መንገድ እንደተዘጋ ነበር።