እነ እስክንድር ነጋ ወደ ቂሊንጦ እንዲዘዋወሩ ቃሊቲ ወህኒ ቤት ጠየቀ
#በአስቴር ስዩም ላይ የድብደባ ሙከራ ተደርጓል
#ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 17 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል
በቃሊቲ ወህኒ ቤት በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር (ቀለብ) ስዩም እና አስካለ ደምሌ ዛሬ ግንቦት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በአካል ቀርበዋል። በችሎቱም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሰረት የአምልኮ ስፍራ እንዲዘጋጅላቸው ከዚህ በፊት ያቀረቡትን ጥያቄ በድጋሜ አንስተዋል።
ፍርድ ቤቱ ሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ባዘዘው መሰረት የአምልኮ ስፍራውን በተመለከተ ሦስት የወህኒ ቤቱ የሥራ ሓላፊዎች ተገኝተው አብራርተዋል። ሓላፊዎቹ የኅሊና እስረኞች ያሉበትን የእስር ቤቱ ንዑስ ክፍል ወይም ዞን ለመቀየር እንደሚቸገሩ ገልፀው ባሉበት ዞን ለመሥራትም ጠባብ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም ያለው አማራጭ እነ እስክንድር ነጋ ወደ ሌላኛው የፌዴራል ወህኒ ቤት ቂሊንጦ እንዲዘዋወሩ ማዘዝ መሆኑን ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ ይህንን እንዲያዝዝም ጠይቀዋል።
ወንዶቹን ሳይጨምር አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ባሉበት ዞን ቤተ ክስርቲያን መሥራት ካልተቻለ ከሌላ ዞን እየተመላለሱ እንዲያመልኩ ጠይቀዋል።
“አምላክን ማምለክ አልቻልንም። ሃይማኖት በራሱ ዜጎችን ያንፃል። ስነ ምግባርን ያስተካክላል። እሴታችንም ነው። ለአምልኮ ብቻ ወደ ሌላ ዞን ብንሄድ ጥሩ ነው” በማለት ወ/ሮ አስቴር ስዩም ጠይቀዋል።
ይሁን እንጂ ቃሊቲ ወህኒ ቤትን ወክለው በችሎት የተገኙት የእስር ቤት ሓላፊ ይህ እንደማይቻል ገልፀዋል። “ሌላ ቦታ ሄደው ቢያመልኩ ችግር የለብንም። ነገር ግን ደህንነታቸው ያሳስበናል። አንድ ጊዜ ቀለብን ‘በሀጫሉ ግድያ ተጠርጥረሻል’ በሚል አንዲት ፍርደኛ ልትደበድባት ነበር። እኛ ነን ያዳናት፤ ይኸው ራሷም ታውቃለች” ብለዋል ሓላፊዋ።
ፍርድ ቤቱ የአምልኮ ሥፍራውን ጉዳይ በሌላ ችሎት እንደሚመለከተው ገልፆ ፀበል ግን ለአራቱም የኅሊና እስረኞች በአስቸኳይ እንዲገባላቸው አዝዟል።
“አንድ ሰው ታሞ ሀኪም መድሃኒት ሲያዝዝለት ይገባለታል። ጸበልንም እኛ በዚያ መልኩ ነው የምንረዳው። ‘እንፈወስበታለን፤ ይግባልን’ ካሉ አስፈላጊው ፍተሻ ተደርጎለትና ተቀምሶ ሊገባላቸው ይገባል። በጸበል እፈወሳለሁ ያለ ሰው ሊከለከል አይገባም። የሁዳዴ ጾም ሳይፈታ ነበር ያዘዝናችሁ። አሁን ፆሙ ከተፈታ 15 ቀን አልፎታል። እስከ አሁን ማዘግየታችሁ ስህተት ነው። በአስቸኳይ ሊገባላቸው ይገባል” ብለዋል ሦስቱ ዳኞች በሰጡት የጋራ ብይን።
የምስክሮችን አሰማም በተመለከተ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲያከራክረው የቆየውን ጉዳይ ራሱ እንዲወስን ባለፈው ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በዋለው ችሎት እንደገና ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት መልሶታል። ይህንንም አከራክሮ ለመወሰን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ለፊታች ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ይሁን እንጂ ዐቃቤ ሕግ አሁንም ጉዳዩን በይግባኝ ያጓትተዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህንን የተረዱት የእነ እስክንድር ነጋ ጠበቃ እስረኞች ያለ ፍርድ እየተጉላሉ ያሉት በዐቃቤ ሕግ ህንዝላልነት መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል። ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ‘ተዘለፍኩ’ የሚል ቅሬታ አሰምቷል። ተከሳሾች “የጋራ አቋማችን ነው፤ ህንዝላል ለመሆኑ ማስረጃዎች አሉ” ብለዋል።
ወ/ሪት አስካለ ደምሌ ከዚህ በፊት ወደ ተንቀሳቃሽ ስልካቸው በመደወል ጭምር መንግሥት ስለላና በደል ያደርስባቸው እንደነበር ጠቅሰው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንዲያጣራላቸው ያዝዝ ዘንድ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
እነ እስክንድር ነጋ ከሃምሌ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በግፍ እስር ላይ የሚገኙ ሲሆን እስከ ዛሬው ችሎት ድረስ የስረ ነገር ክርክር አልተጀመረም።
ጌጥዬ ያለው