አስቻይ ሁኔታዎች በሌሉበት የሚከናወን ምርጫ ሀገር በጉጉት ወደምትጠብቀው ሥርዓት አያሸጋግርም !
በሕብር ኢትዮጵያ፣
በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣
በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ፣
በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ እና
በእናት ፓርቲ
በጋራ የተሰጠ መግለጫ
ሀገራችን ኢትዮጵያ የምታካሂደው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ፍትህ፣ እውነተኛ ዲሞክራሲና ሠላም የራቀው ህዝባችንን አንድ እርምጃ ወደፊት በማራመድ በዚህ አቅጣጫ በምናደርገው ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ከፋች እንደሚሆን በማመን በምርጫው ሂደት ከመነሻው ጀምሮ የጎላ ተሳትፎ በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡
በታሪኳ ተዓማኒነት ያለው ምርጫ አካሂዳ ለማታውቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ ምርጫው ከታሰበበት/ በዕቅድ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ሲነገር የቆየውንና በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የገዥው ፓርቲ መሪዎች በተደጋጋሚ የሚናገሩትን በማሰብና ሕዝባችንም ይህ በታሪክ እውን ሆኖ ለማየት ካለው ከፍተኛ ፍላጎት አኳያ በጉጉት የሚጠበቅ ነበር፡፡
ምንም እንኳ በትክክለኛው ትርጉሙ ምርጫ የሚባልና የምርጫ መስፈርትን ከብዙ በጥቂቱም ቢሆን የሚያሟላ ነገር ሀገራችን አከናውና ባታውቅም ወደዚህ ምርጫ ስንገባ የተገባው ቃል እውን ሊሆን የሚችል ተስፋ ይዘን ነው፡፡ ምርጫ በአንድ ጀንበር /በምርጫው ቀን ብቻ/ የሚከናወን ሳይሆን የምርጫውን ነፃና ፍትሃዊነት ለመገምገም የምርጫውን ሂደት ከመነሻ እስከ ፍፃሜው በወጥነት መመልከትን የግድ ይላል፡፡
ከዚህ አኳያ በአንዳንድ ቦታዎች በሠላም እጦት ምክንያት በሌሎች ደግሞ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ በምርጫ አስፈፃሚው አካል ችግር እንደታየበት በመጤኑ ትንሽ በማይባል የሀገራችን ክፍል ምርጫው እንዲዘገይ የተደረገባቸው አካባቢዎች ቁጥር ቀላል የማይባል ቢሆንም ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ይካሄድባቸዋል በተባለው የሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የምርጫው ቀን እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ወቅት ያለፍንባቸውን የቅድመ ምርጫ ሂደት ውጣ ውረዶች መራጩና የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በዚሁ መሠረት፡-
በእጩዎች ምዝገባ ወቅት፡- በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ሆን ተብሎ እጩዎችን ላለመዝገብ በተለያዩ የምርጫ ክልሎች ከህግ አግባብ ውጪ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች በማስቀመጥ ቀላል የማይባል እንግልት በእጩዎቻችን ላይ ደርሷል፤
በመራጮች ምዝገባ ወቅት፡- የመራጮች ምዝገባ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ በአብዛኛው ያልተጀመረ ሲሆን/ምንም እንኳ ይህን ለማካካስ የምዝገባ ቀን ማራዘሚያ ቢደረግም / ከተጀመረም በኋላ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ለምዝገባ ሲመጡ ሆን ብሎ በማጉላላት መራጮች እንዳይመዘገቡ የተሰሩ ሥራዎች፤ በአንድ የምርጫ ጣቢያ የሚመዘገቡ መራጮች ቁጥር 1500 ብቻ መሆኑ አንዳንድ ቦታ ላይ የተፈቀደው ቁጥር ሞልቷል በሚል ምክንያት መራጮች እንዳይመዘገቡ እንቅፋት መሆኑ፤ የተመዝጋቢዎች ቁጥር የተቀመጠው ጣሪያ ላይ በመድረሱ መራጮች ሊመዘገቡ አለመቻላቸውም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲያውቀው ከተደረገ በኋላ ምንም እንኳ ንዑስ ጣቢያዎች እንዲከፈቱ አቅጣጫ ቢቀመጥም ንዑስ ጣቢያዎች በቶሎ ተከፍተው አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸው፤ አንዳንዶች የምርጫ ጣቢያዎች እና ንዑስ ጣቢያዎች የተቋቋሙበት ቦታ በተለይ በአዲስ አበባ ለዚህ ትልቅ ሀገራዊ ተግባር ማከናወኛ ከሞራል አኳያ የሚመጥኑ ባለመሆናቸው የመራጮች ደስተኛ ሆኖ ወደእነዚህ ጣቢያዎች ሄዶ አለመመዝገብ፤ እነዚህና የመሳሰሉት በጉልህ የታዩ ችግሮች በመራጭነት ሊመዘገብ የሚችለውን ሕዝብ በሚፈለገው መጠን እንዳይመዘገብ ያደረገው መሆኑ፤
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት፡- ምርጫው በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በሙሉ በሚባል መልኩ /አዲስ አበባ ብቻ ሲቀር/ የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄድ በከፍተኛ ችግር የታጀበ መሆኑ እነዚህም፡ በእጩዎች ላይ ግድያ መፈጸም፣ የግድያ ሙከራ እና ድብደባ መፈፀም፤ እጩዎችን ከህግ አግባብ ውጭ አስሮ ማንገላታት፤ ለምርጫ ቅስቀሳ ሲወጣ መቀስቀስ አትችሉም በማለት ብዙ ገንዘብ ወጥቶበት የተሰማራን ቅስቀሳ ተሽከርካሪና የድምፅ ሲስተም አግዶ በማዋል የምርጫ ቅስቀሳን በማስተጓጎል ለገንዘብ ኪሣራ መዳረግ፤ እጩዎች እንዳይቀሰቅሱ የግድያ ዛቻና ማስፈራራት በማድረስ የማሸማቀቅ ሥራ መስራት፤ እጩዎችን አስገዳጅ በሆነ ምልኩ ያለደመወዝ እረፍት እንዲወጡ ማስገደድ፤ እጩዎች ከእጩነት ራሳቸውን እንዲያገሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ጫና ማድረግ፣ የምርጫ ምልክት ያለባቸውን የቅስቀሳ ባነር ማውረድ፣ መቅደድ እና በምትኩ የብልጽግናን ምልክት መስቀል ወዘተ በስፋት የተስተዋሉና እየተስተዋሉ ያሉ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው።
እነዚህን ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች ከመፍታት አኳያ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ፓርቲዎቹ በቅርበት በመሥራት መፍትሄ ለማግኘት በተናጠል ጥረት ያደረግን ሲሆን በዚህ ረገድ የተወሰኑትን ችግሮች ለመፍታት ተሞክሯል፡፡ የመራጮች ምዝገባን አስመልክቶ የተቀመጠው በአንድ የምርጫ ጣቢያ የተመዝጋቢዎች ቁጥር ጣሪያ ቢነሣ የተከፈቱት ተጨማሪ ንዑስ ጣቢያዎች ለሕዝቡ በቀላሉ ተደራሽ ሆነው ምዝገባውን ማከናወን ቢቻል ከፍተኛ ቁጥር ያለው መራጭ መመዝገብ ይቻል እንደነበር በመግለጽ የምርጫ ቀኑ አስቀድሞ ከተያዘው ከግንቦት 28 ቀን ወደ ሰኔ 14 ቀን መገፋትን ተከትሎ የመራጮች ምዝገባ ቀን ለተወሰነ ጊዜ ክፍት እንዲደረግ
ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡
ከላይ ከብዙ በጥቂቱ የዘረዘርናቸው ችግሮች በአጠቃላይ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ በብዙ ችግሮችና ውጣ ውረዶች የተሞላ እንደነበር ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ሕዝባችን ይህን እንዲያውቅ ከማድረግ ጎን ለጎን ሀገራችን ኢትዮጵያ ከእኛ የምትጠብቀውን በግልጽ በመረዳት ሥልጣን ላይ ተጣብቆ ለመቆየት ከመፍጨርጨር ይልቅ በቃል የተነገረውን ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እውን የማድረግ ነገር ከቃል በዘለለ በቀጣይ ቀሪ ጥቂት ቀናትና በመርጫ ወቅት ገዥው ፓርቲና የመንግሥት የተለያዩ የአስተዳደር አካላት ይህን በተግባር እውን የማድረግ ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅና ይህንኑ ለግብር ከፋዩ ሕዝብ ማሳየት እንደሚገባ አጠንከረን መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቅ
አዲስ አበባ
ሰኔ 6 ቀን 2013 ዓ.ም.