በፕላዝማ መበላሸት ምክንያት በዛሬው ችሎት ሊዳኝ የነበረው የእነ እስክንድር ነጋ ጉዳይ ለሚያዝያ 15 ተዛወረ !!
በጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚደረገው ችሎት ለዛሬ ሚያዝያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ተቀጥሮ የነበረው ችሎት ‘ፕላዝማው ተበላሽቷል’ በሚል ለፊታችን ሚያዝያ 15 ቀን ተዘዋውሯል። ይኸው ችሎት ከዚህ በፊት ለመጋቢት 28 ተቀጥሮ የነበረ ሲሆን ከሦስቱ ዳኞች መካከል አንዱ ባለመገኘታቸው ነበር ለዛሬ የተሸጋገረው።
የህሊና እስረኞች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ከፕላዝማ ይልቅ በችሎቱ ፊት ለፊት ለመቅረብ ቢጠይቁም አዎንታዊ ምላሽ አላገኙም። ፕላዝማው ትናንት አመሻሽ ድረስ ሲሠራ እንደነበር ማወቃቸውን የገለፁት የህሊና እስረኞች ወድያውኑ አስተካክሎ ከቀትር በኋላ ችሎቱን ማከናወን ይቻል እንደነበርም ተናግረዋል። ይህ እንኳን ባይሆን እስከ ሚያዝያ 15 ማራዘሙ ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል። “ብይን ሳይሰጠን ምርጫውን ማሳለፍ ስለተፈለገ ፍርድ ቤቶች ሆን ብለው እያጓተቱብን ነው” ብለዋል እስረኞቹ።
በተደጋጋሚ እየተገፋ ያለው ችሎት ይግባኝ ለማከራከር የተቀጠረ ሲሆን መዝገቡ ሳይከፈት ነው በቀጥታ ለቀጣዩ ችሎት የተዘዋወረው ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ችሎት በግፍ እስር ላይ የሚገኙት አራቱ የህሊና እስረኞች ባሉበት ወህኒ ቤት ውስጥ ሆነው በፕላዝማ ሲቀርቡ ዶሴውን በውጭ ሆነው የሚከታተሉት አምስተኛ ተከሳሽ ፍርድ ቤት በአካል ቀርበው ነበር። ይሁን እንጂ ተከሳሹ በቦታው መኖራቸውን ዳኞች ሳያስተውሉ ቀርተዋል። በመሆኑም ችሎቱ ላይ ‘አልቀረቡም፤ ቀርቤያለሁ’ የሚል ውዝግብ ተፈጥሯል።
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች የፊታችን ሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በከፍተኛው ፍርድ ቤት ሌላ ችሎት ይቀርባሉ። በከፍተኛው ፍርድ ቤት እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት መካከል የተዋረድ ክርክር በማድረግም ያለ ብይን ጊዜው እየተጓተተ ይገኛል ።