በነ እስክክንድር መዝገብ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ምስክር የመስማት ሂደት በዐቃቤ ህግ ምክንያት ቀረ !
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩምና አስካለ ደምሌ በዛሬው ዕለት ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በአካል ቀርበዋል።
ከዚህ ቀደም በዋለው ችሎት ዛሬ ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች እንዲሰሙ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ዐቃቤ ህግ ምስክሮቼ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል ፣ ማንነታቸውንም በግልጽ እንዳይታወቅ ፣ የመኖሪያ አካካቢ ለውጥ ለማድረግ እፈልጋለሁ። በመሆኑም ይህን ጉዳይ ለማከናወን ከተቋሙ ውጪ የገንዘብ ድጋፍ ከመንግስት ስለሚያስፈልግ ሌላ ተለዋዋጭ ቀጠሮ ይስጠኝ በማለት ምስክሮቹን ማቅረብ አለመቻሉን ለፍርድ ቤት አስታውቋል።
የግፍ እስረኞች ጠበቆች በበኩላቸው ዐቃቤ ህግ ምስክሮችን እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል ። ይሁን እንጂ ዐቃቤ ህግ የፍ/ቤት ትዕዛዝ አላከበረም። በቸልተኝነት የትዕዛዝ ጥሰት ፈፅሟል። ከዚህም በተጨማሪ አንድ አመት ሙሉ ደንበኞቻችን ዐቃቤ ህግ ምስክሮች ማቅረብ ባለመቻሉ በፍትህ እጦት ለእስር ተዳርገዋል ። አመቱን ሙሉ የተለያየ ምክንያት በማቅረብ ዐቃቤ ህግ የፍርድ ቤቱን ሂደት ሆን ብሎ ሲያዘገይ ቆይቷል። በመሆኑም የዐቃቤ ሕግ ጥያቄው የህግም የሞራልም መሰረት ስለሌለው መዝገባቸው ተዘግቶ በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
የግራና ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው ፍ/ቤቱ፤ በምስክሮች ደህንነት ላይ ለአንድ አመት ክርክር ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሷል። ስለሆነም ዐቃቤ ህግ ያቀረበው አቤቱታ ቀጠሮ የሚያስቀይር ሆኖ አላገኘሁትም በማለት ዐቃቤ ህግ አሉኝ የሚላቸውን ምስክሮች ነገ ሐምሌ 9 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
ዛሬ በዋለው ችሎት በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት ቅጥር ጊቢ ፣ በፍትህ ችሎት አዳራሽ እና ከፍርድ ቤት ቅጥር ጊቢ ውጪ ተገኝተዋል ። የግፍ እስረኞች እነ እስክንድር በችሎት ለተገኙ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ
ሐምሌ 8/ 2013 ዓ.ም