በመከራና እንግልት ያልተበገረው ደፋሩና ጀግናው ውድ የኢትዮጵያ ልጅ እስክንድር ነጋ ይፈታ(ነብዩ ውብሸት)
የወታደራዊ አስተዳደር ደርግ መንግሥት በ1960ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በእስክንድር ነጋ ወላጆች ላይ የተለያዩ በደሎች በማድረሱ ጨቅላውን እስክንድርን ይዘው ወደአሜሪካ ተጓዙ፡፡ እስክንድር በአሜሪካ በቆየበት ወቅት ኢትዮጵያውያን የደርግን መንግሥት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፎች ሲያካሂዱ እሱም በዚያ በለጋ የተማሪነት ዘመኑ ሰላማዊ ትግሉን ተቀላቅሎ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
የደርግ መንግሥት ወድቆ ሕወሀት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ፣ እስክንድር ነጋ በ1985 ዓ.ም. ወደ ሀገርቤት ተመለሰ። ጊዜ ሳያጠፋም በጋዜጠኝነት ሞያ የካበተ ልምድ ከነበረው ከተፈራ አስማረ ጋር በመጣመር “ኢትዮጲስ” የተሰኘች ሳምንታዊ ጋዜጣን በማሳተም በወቅቱ ሀገሪቷን በመሣሪያ ኃይል ከተቆጣጠሩት ወያኔና ሻእቢያ ጋ የጦፈ የብዕር ጦርነት ገጠመ።
ከ1985 ዓ.ም. እስከ 1987 ዓ.ም. ባሉት ሁለት ዓመታት ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት በቆሙ ወደ 40 በሚደርሱ መጽሔቶች ላይ ምሁራዊ ጽሑፎች እንደ ውሃ ጅረት ሲፈሱ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ ጽሑፎች የወያኔንና የሻብያን መሪዎች በብስጭት ጨርቅ ሲያስጥሉ፣ የአዲስ አበባን ነዋሪ የተቃጠለና የአረረ አንጀት ቅቤ አጠጥተዋል፡፡ የእነ እስክንድር “ኢትዮጲስ” ጋዜጣም እጅግ ተወዳጅ ከመሆኗ የተነሳ፣ የጋዜጣ መሸጫ ዋጋ ከአንድ ብር ያነሰ የነበረ ቢሆንም፣ በጋዜጣ አዟሪዎች እጅ፣ እስከ ሰባት ብር በሚደርስ ዋጋ ትሸጥ ነበር።
በዚያን ወቅት አብዛኛው ሕዝብ የኑሮ በጀቱ እስኪቃወስ ድረስ መጽሔትና ጋዜጦችን እንደ መደበኛ የምግብ አስቤዛው እየገዛ ስለሀገሩ ጉዳይ ያነብ ነበር፡፡ የሕዝብን ቀልብና አእምሮን ከማረኩና የወያኔን ካምፕ ካሸበሩ የኢትዮጲስ ጽሑፎች መካከል “የማትረባ ፍየል” በሚል ርእስ በካርቱን መልክ የወያኔውን መሪ ምስል ለጥፋ ያስነበበችው እትም ከእነ እስክንድር የብዕር ትሩፋቶች አንዷና የማትረሳ ሆና በብዙዎች ዘንድ ትታወሳለች።
ከ1987 ዓ.ም. በኋላ የብዕር ጦርነቱን መቋቋም ያቃተው ወያኔ የጋዜጣና መጽሔት አዘጋጆችን ማሳደድ እና ማሠር ጀመረ። ከ40 ይበልጡ የነበሩ የብዕር ምርት ይታፈስባቸው የነበሩ መጽሔቶችና ጋዜጦች በአጭር ጊዜ እየከሰሙ ሄዱ። የእነ እስክንድር ኢትዮጲስ ጋዜጣም እጣ ፈንታ ተመሳሳይ ሆኖ፣ እስክንድር ነጋና ተፈራ አስማረ ወደ ወህኒ ቤት ተወረወሩ። የነፃው ፕሬስ አከተመለት በሚባል ደረጃ ተሽመደመደ። በሁለት ዓመታት ውስጥ ጥሩ የማንበብ ልምድ ያዳበረው የአዲስ አባባ ህዝብም፣ ድብርት ውስጥ ገባ። የወያኔ የድንቁርና አስተሳሰብ ብቻውን ተንሰራፍቶ በከተማዋ ነገሠ። የየሳምንቱ የህዝብ ዋና መነጋገሪያ የነበሩት የጋዜጣ ጽሑፎች በእነእስክንድር የእስርቤት ውሎና አዳር እንዲሁም በፍርድ ቤት ችሎት ላይ በሚያሳዩት ጽናትና ጀግንነት ተተካ። የእነእስክንድር ከወያኔ ጋር ያደረጉት ድፍረትና ጀግንነት የተሞላበት የፍርድቤት ሙግትና ሰላማዊ የብዕር ጦርነት ለተተኪው ወጣት ጋዜጠኞች አርዓያነትን እያተረፈ መጣ።
የእነ እስክንድርን አርዓያነት የተከተሉ ብዙ የብዕር ታጋዮች የወያኔን ሀገር አፍራሽ አስተሳሰብ በጽሑፎቻቸው ሞግተዋል፡፡ በትግላቸውም ብዙ መከራና እንግልትን ተቀብለዋል። እንደዚያም ሆኖ እንደ እስክንድር ነጋ ወያኔ ኢሕአዴግን እየታሠረና እየተፈታ በጽናት ለረዥም ጊዜ ሲታገል የኖረ ብዕረኛ የለም።
የነፃው ፕሬስ በድጋሚ ባቆጠቆጠበትና ወያኔ ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ላይ 23 ለባዶ በተሸነፈበት፤ በ1997ቱ ታሪካዊ ምርጫ ወቅት እስክንድር ነጋ ያሳትማቸው የነበሩት “ምኒልክ” እና “አስኳል” ጋዜጦች ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትራመድ ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር። “ምኒልክ” እና “አስኳል” ጋዜጦች በየሳምንቱ ከመቶ ሺ በላይ፣ ለሚደርስ የአዲስ አበባ ነዋሪ ያቀርቧቸው የነበሩት ታሪካዊና ፖለቲካዊ የሆኑ በሳል መጣጥፎችና ትንተናዎች በንባብ ወዳዱ ኅብረተሰብ ልብ ውስጥ ዛሬም ታትመው ይኖራሉ።
ወያኔ እስክንድር ነጋን ከ1987 እስከ 2010 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ውስጥ ለአስር ዓመታት አስሮታል፡፡ ነገር ግን እውነተኛ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመገንባትና የማየት ህልምና ራዕይ የሰነቀ ቆራጥ ስነልቦናውን መስበር አልቻለም።
እስክንድር ነጋ ለ27 ዓመት የታገለው ግፍ ሠሪው ወያኔ ከሥልጣን ከተወገደ 3 ዓመት አለፈው፤ ነገር ግን የለውጥ ኃይል ነኝ የሚለው ተረኛው መንግሥት እስክንድር ባልሠራው ወንጀል ካሠረው አንድ ዓመት አልፎታል። ኦሕዲድ መራሹ ኢሕአዲግ እስክንድር ነጋን በጠላትነት ያየባቸው ምክንያቶች በርካታ ናቸው፡፡ ከነዚህ መካከል፣ ሀገራችን በታሪክ አይታ በማታውቀው ሁኔታ ዜጎች በማንነታቸው እየተለዩ የዘር ፍጅት ሲፈጸምባቸው ለእነሱ ድምጽ በመሆን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቁና አቤቱታ ማቅረቡ፣ የኦሕዴድ ብልጽግና መንግሥት በተረኛ ገዥነትና በማናለብኝነት ስሜት ሕዝብን ከሕዝብ የሚያቃቅር እርምጃዎች ሲወስድ መቃወሙ፣ ገዥው መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ህዝብን ከኖረበት መንደሩ ሲያፈናቀል፣ የንብረትና የመሬት ወረራን ሲፈጽምና፣ የቅርስ ማውደም ተግባራትን ሲያከናውን መከራከሩ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡
አንዲት ሀገር ብዙ መምህራን፣ ጸሓፍት፣ ሀኪሞች፣ ተመራማሪዎች፣ የጦር መኮንኖች ሌሎችም በተለያዩ ዘርፎች የሰለጠኑ ባለሙያዎች ሊኖሯት ይችላሉ። ነገር ግን ጥሩ የሀገር መሪ ከሌላት ሀገሪቱ ከጉዳት ላይ መውደቋ የማይቀር ነው፡፡ የተለያዩ ሃገራት ታሪኮች እንደሚያሳዩት መሪዎች እራሳቸውን እያስቀደሙ ሀገርንና ሕዝብን ሲጎዱ ምሁራን ተስፋ እየቆረጡ፣ ሀገራቸውን እየጣሉ ይሰደዳሉ። ከ1966 ዓ.ም. በፊት ኢትዮጵያውያን በስደተኝነት አይታወቁም ነበር። ከ1966 ዓ.ም. በኋላ ግን በመሰደድ ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን በተለይም ምሁራን እጅግ በርካታ ሆኑ።
በሌላ በኩል ሀገራት፣ በቂ ምሁራን ባይኖሯቸውም ጥሩ መሪ ካገኙ ለሀገር የሚጠቅሙ ምሁራንን በየእውቀት ዘርፉ ለማፍራት ብዙ አይቸግራቸውም። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የቆየ ጥንታዊ ታሪክና ሥልጣኔ ያላቸው ሀገራት የወደቀውን ሁለንተናዊ ገጽታቸውን ለመመለስ በህዝብ ተቀባይነት ያለው ሩቅ አሳቢ ጠንካራ መሪ ማግኘት የግድ ይላቸዋል።
ባለፉት 60 ዓመታት በመልካም መሪ እጦት በተሰደዱበት ስለቀሩት ኢትዮጵያውያን ምሁራን በቁጭት መንፈስ እንዳነሳነው ሁሉ፣ ከስደት በፈቃዳቸው ተመልሰው ለሀገራቸው አርዓያነት ያለው ሥራን ስለሠሩ በጣት የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ገድል ሳንመሰክር ማለፍ አይገባንም። ከእነዚህ አንዱ ታሪኩን እየዘከርንለት ያለነው በአሜሪካን ሊገኝ የሚችለውን የተደላደለ ኑሮ በ20ዎቹ ዕድሜው ጥሎ ሀገሩን የሙጥኝ ያለውን እስክንድር ነጋ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለሀገር የጠቀሙ ታሪክ ሠሪ ሊቃውንትን እና ታላላቅ የሀገር መሪዎችን ስታፈራ የነበረች ጥንታዊት ሀገር ናት። ይህን ማድረግ የቻለችው ደግሞ ከትውልድ ወደትውልድ ሲሸጋገር በቆየው በመሪዎቻችን የአመራር ጥበብ መሆኑ አሌ አይባልም። የኢትዮጵያ መሪዎች አንድነቷን የጠበቀች ሀገር ያስረከቡን፣ እውነተኛ የሀገር ፍቅርና ፈሪሀ እግዚአብሔር የነበራቸው፣ ሀገራዊ ኃላፊነትን ለመሸከም ወደኋላ ያላሉ፣ ጥበበኛ የሆኑ፤ በራሳቸውና በሕዝባቸው የሚተማመኑ፣ ቆራጥና እውነተኛ መሪዎች ስለነበሩ ነው። ኢትዮጵያ እንደዚህ ዓይነት መሪዎችን ካየች 60 ዓመታት አለፏት። ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለሀገር ህልውናና እድገት የሚቆሙ መሪዎችን ማፍራት ተስኗት የቁልቁለት ጉዞ እየተጓዘች ትገኛለች። በዚህ የቁልቁለት ዘመን ለኢትዮጵያ ትንሳኤ መምጣት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ መሪዎችን ማግኘት መታደልን ይጠይቃል። በዚህ ረገድ ሀገራችንን ኢትዮጵያን ከገባችበት መቀመቅ ሊያወጧት የሚችሉ ተስፋ የሚጣልባቸው ጥቂት ጥበበኛ የፖለቲካ መሪዎች እንዳሉ አይካድም። ላለፉት 30 ዓመታት በጽናት የታገለ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያልተለየው፣ ጀግና፣ ቆራጥ፣ ጽኑ፣ የዘመናችን የብእር አርበኛ፣ ኢትዮጵያዊ አንድነትና ሉዓላዊነት አጀንዳን አድርጎ የሚያራምድ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆነው እስክንድር ነጋ ለኢትዮጵያችን ተስፋዋ ነው።
በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ከገባችበት እጅግ አስቸጋሪ ከእርስ በርስ ጦርነትና ውስብስብ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውጥንቅጥ ችግሮች ልትወጣ የምትችለው እንደ እስክንድር ነጋ ያሉ ለዲሞክራሲና ለፍትህ በጽናት የታገሉ መሪዎችን ቦታ ስትሰጥ ብቻ ይሆናል። የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ የአዲስ አበባ ኗሪ፣ ሀገር ሁነኛ መሪ አጥታ፣ በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመስበት በዚህ አስከፊ ወቅት፣ መሪውን እስክንድር ነጋን ችላ ሊል ከቶ አይገባም። ሕዝብ ለሀገሩ፣ ለባንዲራው፣ ለራሱና ለልጆቹ ህልውና ሲል መሪውን እስክንድር ነጋን ከእስር የማስፈታት ታሪካዊ ሓላፊነቱን ነገ ከነገወዲያ ሳይል ዛሬውኑ ሊወጣ ይገባል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅልን!
( ነብዩ ውብሸት )
ነሃሴ 2013 ዓ.ም.