ስንታየሁ ቸኮል ማን ነው?
ያልተሰሰተ ህዝባዊነት -ለሃያ አመታት
—
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ መሥራችና አመራር ፖለቲከኛ #ስንታየሁ ቸኮል በአዲስ አበባ የአፍላነት ጊዜውን በትግል
እያሳለፈ የሚገኝ ታጋይ ነው። አገሩ ኢትዮጵያን ዕጅግ አብዝቶ የሚወደው ስንታየሁ ቸኮል በ1972 ዓ.ም በምስራቅ ጎጃም ደብረኤልያስ በተባለ ታሪካዊ ስፍራ ተወለደ።
ስንታየሁ ቸኮል ገና በተወለደ በሶስት አመቱ ነበር ወደ አዲስ አበባ ከወላጅ እናቱ ጋር በመምጣት ኑሮውን የጀመረው። እድሜው ለትምህርት ሲደርስ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመኖሪያ አካባቢው በሚገኘው ፊት አውራሪ ላቀ አድገህ ትምህርት ቤት በመግባት “ሀ” ብሎ ጀመረ። በፊት አውራሪ ላቅ አድገህ ት/ቤት የጀመረው ቀለም የመቅሰም ጉዞ እስከ አብዮት ቅርስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደርሶ ነበር። ይሁን ዕንጅ በጊዜው የነበረው የ19 93ቱ የተማሪዎች የፖለቲካ የለውጥ እንቅስቃሴ ግለት ሊያስቀምጠው ስላልቻለ፣ ስንታየሁ ቸኮል ወደ ድርጅት ትግል በማምራት ተቀላቀለ።
“ከኢዴፓ” 1993 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2013 ዓ.ም ላለፉት ሃያ አመታት በተለያዩ ድርጅቶች ቁጥሩ የበዛ ዋጋ ከፍሏል። የህወሓት/ኢህአዴግ ከፋፋይ ዘወጌ ብሔርተኝነት አምርሮ ታግሏል። ለህይዎቱ ሳይሳስት ገና በአፍላ እድሜዉ በዶክተር አድማሱ ገበየሁ ይመራ የነበረውን “ኢዴፓን” በ1993 ዓ.ም በመቀላቀል አስቸጋሪ የፈተና ጊዚያትን ጀመረ።
ስንታየሁ ቸኮል በወቅቱ የወረዳ 20 አመራር በመሆን እና በህዛባዊ ቅስቀሳዎች ውስጥ በመሳተፍ በትጋት አገልግሏል። የ”ምርጫ 1997″ የቅንጅት ፓርቲ አባላት እና በዋናነት በወቅቱ የተመለመሉ የምርጫ ታዛቢዎች ተገቢውን ስምሪት በመስጠት ሃላፊነቱን ተወጥቷል። በወቅቱ ዕጩ በመሆን ለተሳተፉት የቅንጅት አመራር አቶ ክፍሌ ጥግነህ በተወዳደሩበት ወረዳ 20 ምርጫ ጣቢያ 1 -ዋና ታዛቢ በመሆን እና ተገቢውን ሃላፊነት በመጣት ከፍተኛ ዉጤት አስመዝግቧል።
የ”1997 ምርጫ” ውጤትን ህወሓት/ኢህአዴግ”አልቀበልም” ማለቱን ተከትሎ በ1998 ዓም በተፈጠረው ህዝባዊ ቁጣ ሰበብ፣ስንታየሁ ቸኮል በህውሓት የደህንነት ቡድን ታፍኖ በዝዋይ እስር ቤት ስምንት ወራትን በሰቆቃ አሳልፏል።
የመጀመሪያው ዕጅግ አስቸጋሪ የዕስራት ጊዜ ነበረ። የቅንጅት ከፍተኛ አመራር በነበሩት ፕ/ሮ መስፍን ወልደማሪያም፣ ወ/ሪ ብርቱካን ሚዴቅሳ፣ ኢንጅነር ግዛቸዉ ሽፈራው፣ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ እና በሌሎች ጉምት አመራሮች አሰባሳቢነት በድጋሜ በ2001 ዓ.ም አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ተቋቋመ።በዚህ ወቅት የፓርቲው መስራች አባልና የአዲስ አበባ ወጣቶች ኃላፊ በመሆን ስንታየሁ ቸኮል እስከ 2007 ዓ.ም አገልግሏል።
በህዎሓት/ኢህአዴግ የትግል ዘመን ከዘጠኝ ጊዜ በላይ በማዕከላዊ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ እና በሸዋሮቢት እየታሰረ የህወሓትን አምባገነናዊ ስርዓት በልበ-ሙሉነት ተጋፍጧል። በወቅቱ በኢትዮጵያ ብሎም በአዲስ አበባ የህዝብ ቁጣ በተቀሰቀሰ ቁጥር የህወሓት ደህንነቶች ሰበብ እየፈለጉ ስንታየሁ ቸኮልን በተደጋጋሚ የእስር ሰላባ ሲያደርጉት ባጅተዋለ።
በትህነግ/ኢህአዴግ ተደጋጋሚ አፈናና ዕንግልት ከትግል ሜዳ ያልራቀው ጀግናው ስንታየሁ ቸኮል፤ ከአንድነት ፓርቲ መልስ ሰማያዊ ፓርቲን በመቀላቀል ትልቅ የትግል ጀብዱ ፈፅሟል።
ስንታየሁ ቸኮል ቤተሰቡን እና ኑሮውን በመተው ለህይዎቱ ሳይሳሳ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት እና ዕኩልነት ታግሏል። ወጣቱ ፖለቲከኛ ቤተሰቡን የሚወድ፣ ህዝብን አክባሪና የምስጉን ባህሪ ባለቤት መሆኑን በቅርበት የሚያውቁት ይመሰክሩለታል።
ስንታየሁ ቸኮል የአሁኑ የኦህዴድ/ኦዴፓ/ ሊቀ መንበር እና የወቅቱ ጠ/ሚንስትር ወደ ስልጣን ሲመጡ፣ በወቅቱ ባሰሙት የኢትዮጵያዊ አንድነት ዲስኩር ዕውነት መስሎት ድጋፍ ከሰጧቸው ፖለቲከኞች መካከል እንዱ ነበረ። ሰኔ 16 2010 ዓ.ም የተካሄደውን የድጋፍ ሰልፍ ሃሳብ ከማመንጨት ጀምሮ ፣ ዋነኛ የሰልፍ አስተባባሪና ባለቤት በመሆን አጋርነቱን በተግባር አሳይቷል።
ወጣቱ ፖለቲከኛ በዚህ ደረጃ የደከመለት አዲሱ አስተዳደር በቅፅበት ሃዲዱን መሳቱን በመረዳት ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን ለዳግም ትግል ተነሳ። ይህንን ተከትሎ “የአዲስ አበባ የባለቤትነት” ጥያቄ እንዲጎለብት እና እንዲቀጣጠል የትግሉን ችቦ ከለኮሱ አንዱና ዋነኛ ሰዎች ውስጥም ሆነ።
በ2011 ዓም የቀድሞው “ባለአደራው” የአሁኑ ባልደራስ ፓርቲ ሲቋቋም ሀሳብ በማመንጨት የአዲስ አበቤን ትግል ከጉምቱ ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ ጋር በመሆን እንዲጀመር ተግቷል።
በአደረጃጀት መዋቅር ውስጥ ጉልህ የአመራርነት ሚና በመውሰድ ለላቀ ትግል በመዘጋጀት በነበረበት ወቅት በኦህዴድ/ አመራሮች ሰኔ 17/2011 ዓም በአማራ ክልል እና አዲስ አበባ በተፈጠረ ችግር ሰበብ በማድረግ ለስድስት ወር በእስር እንዲቆይ ፈረዱበት።
በተረኛው ኦህዴድ ዳግም ዕስራት ያልተሰለቸው ስንታየሁ ቸኮል የቤተሰብ ኃላፊነቱን ለውዷ ባለቤቱ ወዴ በመተው ላዳግም ከፍ ላለ ትግል ቆርጦ ተነሳ።በዚህ ሂደት የባልደራስ ለዕውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲን ከመመስረት ጀምሮ ተቋሙን በድርጅት ጉዳይ ሃላፊነት እና በስራ አስፈፃሚነት በመያዝ “የአዲስ አበባን የባለቤትነት” ጥያቄ ያቀጣጥለው ጀምር።በአዲስ አበባ ቅርሶች ሲፈርሱ፣ዜጎች በማንነታቸው ሲፈናቀሉ፣የጋራ መኖሪያ ቤቶች(ኮንደሚኒየሞች) በታከለ ዑማ መሪነት ሲዘረፉ፣መሬት ሲወረር፣አስተዳደራዊ ቦታዎች በአንድ ቋንቋ ተናገሪዎች ሲሞላ እግር ከዕግር እየተከተለ በድፍረት ለዓለም ህዝብ ያጋልጥ ያዘ።በዚህ ድርጊቱ በተረኛው ኦህዴድ ያልተወደደው ስንታየሁ ቸኮል ጥርስ ውስጥ ገባ።
ይህንን ተከትሎ ሰኔ 22/2012 ዓ.ም የአርቲስት አጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ምክንያት በማድረግ የኦህዴድ/ብልፅግና ተረኛው ስርዓት ስንታየሁን ከፓርቲው ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋ፣ከሴቶች አደረጃጀት ሰብሳቢ አስካለ ደምሌ እና የክ/ከተማ አደራጃ ቀለብ ስዮም ጋር ታፍነው ታሰሩ። ተረኛው ስርዓት በጀመረው የሴራ ፖለቲካ የበሬ ወለደ ክስ በማዘጋጀት ያለ ፍትህ አንድ አመት ከሶስት ወራት በእስር እየማቀቀ ይገኛሉ። ስንታየሁ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ነው። ሶስት ልጆቹን እና ታታሪዋን ውዷ ባለቤቱን ውዴን ትቶ፣ ለሰላማዊ ህዝባዊ ትግል በመቆም ዛሬ ላይ በግፍ ስለ ነፃነት ሲል በቂሊንጦ ወህኒ ቤት ይገኛል።
ወጣቱ ፖለቲከኛ ስንታየሁ ከኢዴፓ እስከ አንድነት ፓርቲ፣ ከሰማያዊ እስከ ባልደራስ ባደረገው ፍፁም ሰላማዊ ትግል ምክንያት በአምባገነኖች አስራ አንድ ጊዜ ታስሯል። ተንገላቷል። ቤተሰቡን በመተው ጭምር ለህዝብ ጥያቄ ዋጋ ከፍሏል።
“እኛን ማሰር ይቻላል፤ የትግሉን መንፈስ ማሰር ግን አትችሉም።” በሚለው አባባሉ የሚታወቀው ስንታየሁ ቸኮል ዛሬም ስለ ፍትህ በእስር ቤት ዋጋ እየከፈለ ይገኛል።
ስንታየሁ ቸኮል ንፁህ ነው። ፍቱት!!!
የህሊና እስረኞች ባስቸኳይ ይፈቱ !!!
ጥቅምት 2014
ወግደረስ ጤናው