ምስክሮች በግልፅ ችሎት ይሰሙ ወይስ በድብቅ የሚለውን ፍርድ ለመስጠት ለግንቦት 4 ተለዋዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ !
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ፤ በዛሬው እለት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ከቃሊቲ እስር ቤት ሆነው በፕላዝማ ቀርበዋል።
ዛሬ በዋለው ችሎች ይጠበቅ የነበረው ፤ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች በግልፅ ችሎት ይሰሙ ወይስ በድብቅ የሚለውን ፍርድ ለመስጠት የተያዘ ቀጠሮ ነበር ፤ ሆኖም ግን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ” መዝገቡን መርምሬ አልጨረስኩም፣ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት እና ያላለቁ ሥራዎች አጠናቅቄ ብይን ለመሰጠት ” ጊዜ ያስፈልገኛል ብሏል ።
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ፍ/ቤቱ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል በማለት ያቀረበውን ምክንያት ከሰሙ በኋላ ፤ የባልደራስ ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ ” ደጋግመን እንደምንገልጸው እኛ የሚጠብቀን የምርጫ ፉክክር አለ ። በተደጋጋሚ የተለያየ ምክንያት እየተሰጠ እየተገፋ ያለው ችሎት በእኛ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያደረገብን ነው። ፍ/ቤቱ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት የአጭር ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ ውሳኔ ይስጥን ” ብሏል ።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ፤ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች በግልፅ ችሎት ይሰሙ ወይስ በድብቅ የሚለውን ፍርድ ለመስጠት ለግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ከሰዓት 8፡00 ሰዓት ተለዋዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ።