ለ1997 ዓ.ም. ሰማዕታት ቋሚ መታሰቢያ ይቁምላቸው!
ያለፈው ይብቃ!
ለ1997 ዓ.ም. ሰማዕታት ቋሚ መታሰቢያ ይቁምላቸው!
ባለፈው አመት ልክ በዛሬዋ ቀን የዚህን ተመሳሳይ መግለጫ አውጥተናል። ዛሬም እንደግመዋለን፤ የ1997 ምርጫ ሰማዕታትን ሁልጊዜም ስናስታውሳቸው እንኖራን። እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም ቋሚ መታሰቢያ እንደመቆምላቸው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ይጠይቃል።
1997 ዓ.ም. በኢትዮጵያውያን ዘንድ በዘመናት መካከል የማይረሳ ጊዜ ነበር፡፡ እልፎች ኢትዮጵያውያን የንጋት ምልክት ያዩ መስሏቸው ለምርጫ የወጡበት ጊዜ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ወያኔ/ኢህአዴግ በምርጫ ውሳኔ ስልጣኑን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ የሀገራችን ወጣቶች ለተቃውሞ ወጡ፡፡ ሠላማዊ ተቃውሟቸው “ ድምፃችን ይከበር፣ ኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ የምትደዳረው ሕዝብ በመረጣቸው ወኪሎች ነው፣ ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ” የሚል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በጊዜው ስልጣን ላይ በነበሩት በአቶ መለስ ዜናዊ የጭፍጨፋ ትዕዛዝ በተለይ የአዲስ አበባ ወጣቶች ረገፉ፡፡
በጭፍጨፋው ለጋ ወጣቶች፣ የነገ ተስፋዎች መተኪያ የሌለውን ሕይወታቸውን አጡ፡፡ አዲስ አበባ አነባች፤ ወላጆች ሀዘን ተቀመጡ ፣ እናቶችና አባቶች አነቡ፡፡ እነዚያ ለህዝብ ድምጽ መከበርና ለዴሞክራሲ ሲሉ የተሰው ወጣቶች ከሞቱ እነሆ 16 ድፍን ዓመታት ሆኑ፡፡
እነዚህ ሰማዕታት የሞቱለት፣ ሌሎች የአካል ጉዳት፣ እስርና ስደትን የከፈሉበት የህዝባዊ መንግሥት ምስረታ አስራ ስድስት ዓመታት ቢሞላውም፣ ዛሬም ለኢትዮጵያ የንጋት ምልክት አልታየም፡፡ ዛሬም የእነዚያ ሰማዕታት ደም “ነፃነትና ዴሞክራሲ” እያለ ይጮሃል፡፡
በመሆኑም፣ ዛሬ ላይ ሆነን የወገኖቻችንን መስዋዕትነት ስናስብ፣ ንፁኀን የሞቱለትን ትግል ከዳር ለማድረስ ቃል እየገባን መሆን እንዳለበት ባልደራስ ያምናል፡፡ እንዲሁም፣ መስዕዋትነቱን ለከፈሉት ለእነዚያ ብርቅ የኢትዮጵያ ልጆች ቋሚ መታሰቢያ እንዲቆም ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ አቋም እንድንወስድ እንዳለፈው ዓመት ሁሉ ዘንድሮም በድጋሜ ሀገራዊ ጥሪ እናስተላለፋለን፡፡
በተለይም ያለፈው ስህተት እንዳይደገም ሁላችንም በጋራ ልንሠራ ይገባል። የገዥው ፓርቲ አውራ አብይ አሕመድ በዘንድሮው ምርጫ ግርግር የሚኖር ከሆነ ምላሽ መስጠት የሚችል የፀጥታ ሃይል እንዳላቸው አስቀድመው አስፈራርተዋል። አደገኛ አዝማሚያ ነው። ይህ በወታደር ጉልበት የመመካት አባዜ ወደ መለስ ዜናዊ እብሪተኛ ርምጃ እንዳይወስዳቸው ሊጠነቀቁ ይገባል። የሕዝብን ድምፅ በማክበር ከቀድሞ አለቃቸው አስተሳሰብ አንዲወጡ፣ ሕዝብን ዳግም ባለመጨፍጨፍ ከታሪክ ተወቃሽነት እንዲድኑ እንጠይቃለን። እኛ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ያለፈው ጥፋት አንዳይደገም የበኩላችንን አስተዋፅ ማድረግ ይጠበቅብናል። መላው የአዲስ አበባ ኗሪ ብሎም ሁሉም ኢትዮጵያዊ መብቱን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲያስከብር እንጠይቃለን።
በተጨማሪም፣ የ1997 ዓ.ምቱን ጭፍጨፋ ለማጣራት የተቋቋመው ኮሚሽን ያቀረበውን ሪፖርት ፓርላማው ለታሪክ እንዲያስቀምጠው እንዳለፈው ዓመት ሁሉ ዘንድሮም እየጠየቅን፣ ለዚህም ተግባራዊነት ይህ መግለጫ ለፓርላማው ገቢ እንዲሆን ወስነናል፡፡
ክብር መስዕዋትነት ለከፈሉ የዴሞክራሲ አርበኞቻችን
ሰኔ 1 ቀን 2013 ዓ.ም.
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ