እጩ ተወዳዳሪ
በ2013 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ባልደራስን በዐዲስ አበባ ወክለው የቀረቡ እጩ ተወዳዳሪዎች።Balderas for true democracy 2021 national election candidates
ልጅ ጌታቸው ተስፋዬ ወ/ቂርቆስ
ልጅ ጌታቸው ተስፋዬ ወ/ቂርቆስ
#አራዳ ምርጫ ክልል 2/14
ባልደራስን መምረጥ የሕልውና ጉዳይ ነው !
የምርጫ ካርድ መውሰድ ደግሞ ጊዜ የማይሰጠው ነው!
ልጅ ጌታቸው ተስፋዬ ወ/ቂርቆስ እባላለሁ። በአራዳ ክ/ከተማ ምርጫ ክልል 2/14 ለሕዝብ ተ/ም/ቤት እጩ ተወዳዳሪ ነኝ።
አዲስ አበባን ከ1997 ጀምሮ የታገልከውን ተረኝነት ከሚያስቀጥሉና ካልመረጥካቸው መዳፍ በመረከብ ራስ ገዝ አድርገህ ከተማዋን የማስተዳደር ስልጣን እንዲኖርህ የሚያስችልህን የምርጫ ካርድ በእጅህ አስገባ።
የአዲስ አበባ ነዋሪ አካላዊና አዕምሮአዊ ልዕልና የሚጎናፀፈው የስልጣን ባለቤት ሲሆን ብቻ መሆኑን ተረድተህ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ድምፅህን የአንተን ባለቤትነት ለሚያረጋግጠው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ እንድትሰጥ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።
ፈጣሪ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሠላምና በበረከት ይጎብኝ!
ድል ለዲሞክራሲ!
ዶ/ር ንጋት አስፋው
ዶ/ር ንጋት አስፋው
#ካዛንቺስ ምርጫ ክልል 15
በምርጫ መሪ ይሾማል፣ መሪ ከሥልጣኑ ይወርዳል።ይህ ስልጡን አካሄድ ነው !
ዶ/ር ንጋት አስፋው እባላለሁ፡፡ Academic Rank ረዳት ፕ/ር ነኝ፡፡ የተወለድኩት አዲስ አበባ ከተማ፡፡ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርቴን ያጠናቀኩጽ አዲስ አበባ ነው፡፡ የመጀመሪያ ድግሪዬን በባሕር ዳር ኮሌጅ አጠናቅቄያለሁ፡፡ የድህረ ምረቃ ትምህርቴን በአውሮፓ በማኒጅመንት የትምህርት ዘርፍ ጨርሻለሁ፡፡
የሥራ መስክ፤
በአዲስ አበባ ዩኒቨስርቲ እና በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት ሰርቻለሁ፡፡ እንዲሁም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በሃላፊነት አገልግያለሁ፡፡ ሕዝባዊ ተሳትፎ፤ ከምኖርበት ወረዳ እስከ አዲስ አበባ አቀፍ በተለያዩ የልማት ዘርፎች በአስተባባሪነት ሰርቻለሁ፡፡
በአሁኑ ወቅትም በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ድርጅቴ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ለተወካዮች ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ አድርጎ መርጦኛል፡፡ የምወዳደረውም በአዲስ አበባ ከተማ በምርጫ ወረዳ 15 ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነው፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብት የሚረጋገጠው በምርጫ ብቻ ነው፡፡
በምርጫ መሪ ይሾማል፡፡ በምርጫ መሪ ከሥልጣኑ ይወርዳል፡፡ ይህ ስልጡን አካሄድ ነው፡፡
ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በፖለቲካ፤ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፍ ክንውኖች እምን ደረጃ ላይ እንዳለች መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በተለይም የአዲስ አበባ ሕዝብ፡፡ እድሜያችሁ ለምርጫው የደረሰ ሁሉ ጊዜ ሳትወስዱ ከላይ ለተጠቀሱት ውስብስብ የሀገራችን ሁኔታዎች መልስ ለመስጠት የምርጫ ካርድ ማውጣት ወሳኝ ነው፡፡
በምርጫ ካርድዎ መብትዎን ያስከብሩ።
የሰጡት ድምጽ በትክክል መተግበሩን በቅርበት ይከታተሉ።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ያሸንፋል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁን !!!
አፀደ ተስፋዬ
አፀደ ተስፋዬ
#በየካ ክ/ከ የምርጫ ክልል 16
የአምባገነኖች ሥርዓት በእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመተካት ምርጫው ቁልፍ መሣሪያ ነው !!
አፀደ ተስፋዬ መንግስቱ እባላለሁ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ በየካ ክ/ከ የምርጫ ክልል 16 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እወዳደራለሁ።
የትመህርት ደረጃዬ ፡-
1. Sociology and Social Work BA (የመጀመሪያ ዲግሪ )
2. Educational Planning and Management BA (የመጀመሪያ ዲግሪ)
3. Human Resource and Organizational Development MA (የማስተርስ ዲግሪ) አለኝ እንዲሁም ሁለት(2) ጠቃሚ የሆኑ ጥናታዊ የሆኑ መጽሐፎችን አሳትሜአለሁ ፣ በሙያዬ የጥናትና ምርምር ባለሙያ ነኝ።
በዜጎች ላይ ማንነታቸውን እና ሀይማኖታቸውን መሰረት በማድረግ እየደረሰባቸው ያለውን የዘር ማጥፋትና ኢሰብአዊ ጭፍጨፋ ፓርቲያችን ባልደራስ አጥብቆ የሚቃወም ሲሆን በመዲናችን አዲስ አበባ ዘርን መሠረት በማድረግ እየደረሱ ያሉ በርካታ ችግሮችን አሰወግዶ ሰላም፣ እኩልነት እና ዲሞክራሲያዊ አሠራር እንዲሰፍን ባልደራስ ጠንክሮ እየሠራ ይገኛል።
በሀገርና በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን አስከፊ የአምባገነኖች ሥርዓት በእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመተካት ምርጫው ቁልፍ መሣሪያ ነው ፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ ነዋሬዎች በሙሉ ይህን ጉዳይ በትኩረት በማየት ያለን እድል ምርጫና ምረጫ ብቻ በመሆኑ የምርጫ ካርድ በማውጣት ድምፃቹህን ለባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ እንድትሰጡ ስል በትህትና እጠይቃለሁ፡፡
ድል ለእውነተኛ ዴሞክራሲ !
እናሸንፈለን !!!
አለሙ ጌታቸው
አለሙ ጌታቸው
#በልደታ ክ/ከተማ የምርጫ ክልል 4
ሀሎ አዲስ አበባ ! ልጆችህን በመምረጥ ራስህን ማስተዳደር የምትጀምርበት ጊዜው አሁን ነው!
አለሙ ጌታቸው እባላለሁ። ገላን ፣አቃቂ ጨርቃጨርቅና አቃቂ አድቬንቲስት ሚሽን ት/ቤቶች የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ተከታትያለሁ። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአርኪቴክቸርና ከተማ ፕላን (ልደታ ከሚገኘው ህንፃ ኮሌጅ) በ1989 ዓ.ም. በዲግሪ ተመርቄ በአዲስአበባ፣በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎችና በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በሰለጠንኩበት ሙያ አገልግያለሁ።
በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ እጩ ሆኜ በልደታ ክ/ከተማ የምርጫ ክልል 4 ለተወካዮች ም/ቤት እወዳደራለሁ።
አዲስ አበባ የሀገራችን ኢትዮጵያ፣የአፍሪካና አለም አቀፋዊ ማዕከል ብትሆንም ከተማችንና እኛ ነዋሪዎቿ በስሟ ብቻ ከመጠራት ባለፈ እንደግለሰብ ለመኖር የሚያስችሉን የሥራ እድልና መኖሪያ ቤት የመሳሰሉ መሠረታዊ ፍላጎቶች እንደ ሰማይ የራቁን ሲሆን፡ እንደ ማኅበረሰብ የሚያስፈልጉን ደረጃቸውን የጠበቁ የጤና፣የትምህርት፣የትራንስፖርት የመሳሰሉት አገልግሎቶች የሉንም። ይባስ ብሎ በከተማችን ዙሪያ ካለው ማህበረሰብ ጋር የጎሪጥ እንድንተያይና ግጭቶች ውስጥ እንድንገባ ተደርገናል።
ለዚህ ሁሉ ችግር ዋናው ምክንያት በማያውቁን ፖለቲከኛ ሞግዚቶች እንድንተዳደር መደረጉ ሲሆን መፍትሄው በሀገራችን በኢትዮጵያና በከተማችን አዲስ አበባ በማንደራደር የአዲስ አበባ ልጆች እጅ መሆኑን አምናለሁ።
የልደታ ህዝብ እኔን ልጅህን ብትመርጠኝ የቆየ ችግራችንን በራሳችን እንፈታዋለን ለምንወዳት ሀገራችንም ምሳሌ እንሆንላታለን።
የምርጫ ካርድ መሳሪያህ ነው! አሁኑኑ እንድትመዘገብና ካርድህን በእጅህ እንድታስገባ ወንድማዊ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
ፍትህ ለአዲስ አበባ! ፍትህ ለኢትዮጵያ!
ሰሎሞን ገዛኸኝ
ሰሎሞን ገዛኸኝ
#ቂርቆስ ክ/ከተማ ምርጫ ክልል 18
አዲስ አበባ ለአዲስ አበቤዎች በተለየ እና ለመላ ኢትዮጵያውያን እንድትሆን ሰላማዊ የትግል ጥሪ ለመላው አዲስ አበባ ነዋሪዎች !!
ሰሎሞን ገዛኸኝ እባላለሁ።
በትምህርት ደረጃዬ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪና በዓለም አቀፍ ህግ የማስተርስ ዲግሪ ፣ በሙያዬ ጠበቃ እና የህግ አማካሪ ስሆን፤ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲን በመወከል ለህዝብ ተወካዬች ምክር ቤት ቂርቆስ ክ/ከተማ ምርጫ ክልል 18 እወዳደራለው።
አዲስ አበቤ የከተማዎን ባለቤትነት በሰላማዊ ትግል ለማረጋገጥ በቀሩት ጥቂት ቀናት ውስጥ የምርጫ ካርድዎን በማውጣት አዲስ አበባን ለማዳን ካርድ መያዝ ወሳኝ ጉዳይ ነው ። ባልደራስን ይምረጡ !!
ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ሁላችንም የበኩላችንን እንወጣ።
ድል ለእውነተኛ ዲሞክራሲ !!!
ፅጌረዳ ቀለመወርቅ
ፅጌረዳ ቀለመወርቅ
#አዲስ_ከተማ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 5
ከተማዬን በባለቤትነት ለማስተዳደር እኔ ትክክለኛ ሰው
እንደሆንኩ አምናለሁ !!
ፅጌረዳ ቀለመወርቅ እባላለው አዲስ አበባ ተወልጄ ያደኩ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል 3 አመታት በደቡብ ክልል 2 አመታት አገሬን በታማኝነት ህዝቤን በቅንነት አገልግያለሁ፡፡ በአገሪቱ ከሚነገሩ በርካታ ቋንቋዎች ውስጥ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ እንዲሁም ጉራጌኛን በመግባቢያነት እጠቀማለው፡፡
በአሁኑ ሰአት በከተማችን አዲስ አበባ ተፅእኖ ፈጣሪ ከሆነው እና ብዙዎች በጉጉት ለመምረጥ የምርጫውን ቀን ብቻ በሚጠብቁት በባደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ እጩ ነኝ፡፡ የምርጫ ቦታዬ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 5 ሲሆን ለተወካዮች ምክር ቤት ሴት እጩ ተወዳዳሪ ነኝ፡፡
ከተማዬን በባለቤትነት ለማስተዳደር እኔ ትክክለኛ ሰው እንደሆንኩ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም በከተማዋ የሚታየው የፍትህ፣ የሰላም ፣ የቤት፣ የመልካም አስተዳደር የትራንስፖርት ፣ የስራ አጥነት ችግር ውስጥ የለፍኩ እና በማለፍ ላይ የምገኝ የከተማዋ የህዝብ ልጅ ነኝ፡፡
እኔን ቢመርጡ ከተማዋን በልጆቿ የማስተዳደርና የከተማዋ ባለቤትነትዎን የማረጋገጥ እድል ያገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ከልጆችዎ ጋር በመሆን የከተማዋን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በጋራ ለመሥራት እና የራስዎን ከተማ በራስዎ ለማሳደግ ከእድገቷም ፍትሀዊ ተጠቃሚ ለመሆን እንዲሁም አልፎ በዙሪያዋ ካሉት ሕዝቦች ጋር በጋራ ሰርቶ የኔ የኛ የሚለውን እና ልዩ ጥቅም በሚል የሚያነታርከውን ድህነት ወለድ ጥያቄ በዘለቄታው ለልጅ ልጆቻችን እረፍት በሚሰጥ መልኩ ይመልሳሉ፡፡
የምርጫ ካርድ አሁኑኑ በአቅራቢያው በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ በመሄድ ያውጡ ፤ ለመራጭነት ይመዝገብ።
ሰላም ለናንተ ይሁን
አመሰግናለሁ፡፡
ዘቢባ ኢብራሂም
ዘቢባ ኢብራሂም
#ጉለሌ ክ/ከተማ የምርጫ ክልል 8
ምርጫችሁ በተግባር ለከተማዋ ነዋሪዎች ድምፅ ለሆነው
ባልደራስ ይሁን !
ዘቢባ ኢብራሂም እባላለሁ ተወልጄ ያደኩት በአዲስ አበባ አሜሪካን ጊቢ ሰፈር ሲሆን በኮምፒተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪና በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ማስተርስ እንዲሁም በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፖርቲ ውስጥ የፋይናንስ ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊ በመሆን ፓርቲዬን እያገለገልኩ እገኛለሁ።
በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክ/ከተማ የምርጫ ክልል 8 የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ነኝ።
የአዲስ አበባ ነዋሪ እራሱ በመረጣቸውና የነዋሪውን እኩል ተጠቃሚነት በሚያስቀድሙ ባለመተዳደሩ፤ በተለይም ወጣቱ ወርቃማ የሥራ ዕድሜውን ለነገ የሚለው ሳይኖረው በከንቱ ማባከኑ ቁጭት ፈጥሮብኝ ፤ አዲስ አበባን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ለማድረግና ነዋሪዎቿን እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ ቁርጠኛ የሆነውን ባልደራስን ተቀላቅያለሁ።
አዲስ አበባን ማዳን ኢትዮጵያን ማዳን ነው !!