የሀዘን መግለጫ !
በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ፓርቲ አባል ዕጩ በአቶ በሪሁን አስፈራው ላይ በመተከል ዞን በለስ ልዩ ቦታው ካርባር የተደረገውን የግድያ ወንጀል የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ እጅጉን እንደሚያወግዘው እየገለፀ ለሟች ቤተሰብ እና ለባልደርቦቹ መፅናናትን ይመኛል፡፡
Press Release
በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ፓርቲ አባል ዕጩ በአቶ በሪሁን አስፈራው ላይ በመተከል ዞን በለስ ልዩ ቦታው ካርባር የተደረገውን የግድያ ወንጀል የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ እጅጉን እንደሚያወግዘው እየገለፀ ለሟች ቤተሰብ እና ለባልደርቦቹ መፅናናትን ይመኛል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) በአፋር አርብቶ አደር ወገኖቻችን ላይ በተፈፀመው ግድያ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል። ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው የአፋር ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን ይመኛል። ኦሕዴድ/ብልፅግና ኢትዮጵያን ከቻለ አፍርሶ በራሱ ቀለም እንደገና ለመሥራት ይህ ካዳገተውም እንደ ሐረሩ የራስ መኮንን ሀውልት አፈራርሶ ለመተው እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ እናምናለን። ቅርሶችን ጨምሮ ነባር የኢትዮጵያ መገለጫዎችን የማፍረስ እና አንዳዶችን በአዲስ የመተካት እንቅስቃሴው መዳረሻም ይህ ነው። በሀገሪቱ የእርስ በእርስ ግጭቶችን በመቆስቆስ ማሕበራዊ ረፍት የመንሳት እንቅስቃሴው ቀጥሏል።
በአፋርና በሶማሌ ጎሳዎች መካካል የተፈጠረው መንግሥት ሰራሽ ግጭት አላማው ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት ነው። መንግሥታዊ ጥቃቶች፣ ትንኮሳዎችና ለወራሪ አሳልፎ የመስጠት ተግባራት እርስ በእርሳቸው ለማጠፋፋት መሆኑን ተረድተው የሶማሌ እና የአፋር ወንድማማች ጎሳዎች አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ባልደራስ ጥሪውን ያቀርባል።
ባለፉት ዓመታት በተለይ “ለውጥ” መጣ ከተባለበት ጊዜ አንስቶ በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን የዘር ፍጅት ወንጀል በአይነቱ እና በመጠኑ እየጨመረ መጥቷል ። ለዚህም ዋንኛው ምክንያት አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው መንግስት እንደሆነ ብዙ አስረጂ የሚሻ ጉዳይ አይደለም ።
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ ቦኔ ቀበሌ የተፈጸመው የዘር ፍጅት ወንጀል ከዚህ ቀደም በክልሉ ሲፈጸም ከነበረው አረመኔያዊ ተግባር የተለያየ አይደለም ። በዚህ ሰይጣናዊ ተግባር ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች፣ ወዳጅች እና ዘመዶች ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ጥልቅ ሐዘን ይሰማዋል።
ባለፉት ዓመታት በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን የዘር ፍጅት ወንጀል ለማስቆም “መንግስት ነኝ” የሚለው አካል አንዳች ተጨባጭ ነገር ሲያደርግ አልታየም ። ለዚህ ሁሉ ዕኩይ ተግባር “መንግስት” ተጠያቂ እያደረገ ያለው ኦነግ ሸኔ የተባለውን ገዳይ ቡድን ነው። ሆኖም ግን ይህ የዳቦ ስም የተሰጠው ገዳይ ቡድን “መንግስት ነኝ” ከሚለው ኃይል በትጥቅ ሆነ በስንቅ በልጦ አይደለም ። ከምንም በላይ ደግሞ “መንግስት” ንፁሃንን መታደግ ዋንኛ ተግባር መሆን ነበረበት። ይሁን እንጂ አንድ ጊዜ አይደለም በተደጋጋሚ እንዲህ አይነቱ ማንነትን መሰረት ያደረገ የዘር ፍጅት ወንጀል በአይነቱ እና በመጠኑ እየጨመረ ለመምጣቱ ዋናው ምክንያት መንግስታዊ ሽፋን ያለው ወንጀል እንደሆነ ባልደራስ አጥብቆ ያምናል።
ይህም በመሆኑ ዜጎች በማንነታቸው ተለይተው ለደረሰባቸው እና ለሚደርስባቸው የዘር ፍጅት ወንጀል፣ እንዲሁም ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከል ዳተኝነት በማሳየት ብቻ ሳይሆን ለዚህ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፃሚ ቡድን ሽፋን በመስጠት ጭምር አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው። “መንግስት” ዋንኛ ተጠያቂ ነው።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ መንግስታዊ ሽፋን የተሰጠውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በተመለከተ ሥር- ነቀል ለውጥ ለማምጣት ከሚያከናውናቸው የፖለቲካ ትግል ባሻገር ከሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተሟጋች ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በመሆን ይህንን ጉዳይ ከአገር ውስጥ ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ የሕግ ተቋማት በመውሰድ ወንጀለኞች በፍትሕ አደባባይ እንዲዳኙ በማድረግ የንጽሃን ደም ደም ከልብ ሆኖ እንዳይቀር አጥብቆ ይሰራል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
መጋቢት 22 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ
It was learnt that genocidal acts were committed in West Wollega Zone Bone Kebele in March 31, 2021. Balderas for True Democracy strongly condemn the genocide which has been taken as a normal social practice during the Abiy’s Administration. We are deeply saddened by the news and may God give the victims eternal rest.
The genocide that has been committed upon our citizens has been increasing in the past three years and the genocide committed during Abiy’s administration has been exceptional in its brutality, with which the Sect of Oromo Liberation Front set out to destroy the Amhara farmers in various parts of the Country, in Oromia Regional States, in Benishangul Gumz, Northern Shoa, Guraferda(in the Southern Regional State) and the like.
Needless to mention, the fundamental duty of any government is to protect its citizens against imminent danger. That is, any government has the legal and moral obligation to protect and promote citizens’ rights; however, disgracefully, the ‘Government of Ethiopia’ has intentionally denied the Amhara farmers access to adequate security protection. The government of Abiy has never been dedicated to preventing genocide, ethnic cleansing and crimes against humanities for the last three years and we repeatedly recall the shameful failure of the ‘Government’ to prevent citizens from genocidal acts.
Now, it is clearly learnt that the widespread or systematic genocide scheme done on Amhara farmers has been committed, with knowledge of the government. Confronted with the extensive perpetration of unspeakable atrocities and genocide after Abiy came to power, Balderas for True Democracy has articulated an unparalleled call for justice for those who become voiceless citizens of Ethiopia. In response, the ‘Government of Ethiopia’ seems to take joint action with the Sect of Oromo Liberation Front and create havoc on the people of Ethiopia. It is clear beyond reasonable doubt that the notion of crimes against humanity, ethnic cleansing and genocide has evolved under the intent of the government.
Balderas for True Democracy, in addition to the political struggle we have gone through, has been making a commitment to bring perpetrators of these crimes to justice in collaboration with national and international human right advocacy groups.
Balderas for True Democracy
April 1, 2021
Addis Ababa
የሀገራችን ህዝብ ለዘመናት በተጫኑበት ኢዲሞክራሲያዊና አምባገነን አገዛዞች የተነሳ፣ በነጻነት እጦት፣በስቃይ እና በመከራ ኑሮውን እንዲገፋ ተደርጓል። ጭቆናን አስወግዶ የሚፈልገውን ፍትህ እና እኩልነት እውን ለማድረግ ከፍትኛ ዋጋ መክፈሉም እሙን ነው።
ይሁንና የሃገራችን የለውጥ ፍላጎት እና እንቅስቃሴ ጅማሮው ሳይሳካ፣ ለቀጣዩ ዴሞክራሲያዊ ትግል ተስፋ ሊሆን የሚችል መሰረታዊ የትርክትና የመዋቅር ክለሳ እንኳ ሳይደረግ አምባገነንነትና ዘረኝነት የእጅ ለውጥ ብቻ እያደረጉ የሚፈራረቁባት ሆናለች። በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ያለፈው ህዝባችን አሁንም ዲሞክራሲን፣ እኩልነትንና ዘላቂ ሰላምን በመሻት ለነጻነት የሚያደርገውን ትግል አጠንክሮ እንደቀጠለ ይገኛል።
የዚህ አይነት መልክና ይዘት ተላብሶ የተደራጀው የተፎካካሪ ሀይል ለሰርጎ ገቦች የተጋለጠ፣ በተፈጥሮው ደካማና ተሰባሪ ከመሆኑም በላይ የአምባገነኑን ስርአት ራዕይ አቀንቃኝ እስከመሆን ደርሶ እንደነበር ይታወሳል። በተጨማሪ የተቃውሞው ጎራ እርስ በርሱ በፍረጃና በሴራ መጠላለፍ ምክንያት በቁርሾ እንዲሞላ በማድረግ የጋራ ሀገራዊ ስምሪት መውሰድ እንዳይችል አድርጎት ቆይቷል።
በዚህ ሂደት ውስጥ አምባገነኖችን በጋራ መታገል ጥረት ከማድረግ ወርደው በመናኛ ፍላጎቶችና በጥቃቅን ልዩነቶች ዙሪያ ታጥረው ሲሻኮቱ በመካከል የባከነው ጊዜ እና የሰው ህይወት የሚያስቆጭ ነው።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሀገራችንን ለድሜ ልክ ዝቅታ የዳረጋት የጥላቻ ትርክት፣ ትርክቱን መሰረት አድርገው የተደነገጉ ህግጋትና የተዘረጉ መዋቅሮች ተከልሰው መላ ኢትዬጵያውያን በእኩልነት፣ በወንድማማችነት፣ በፍትህና በሰላም የሚተዳደሩነት ዘላቂ ስርአት በማስፈን በተለምዶ “መንታ ቅኝት” ያለው የትግል እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። የአብን ስትራቴጂክ ግብ መላውን ኢትዬጵያዊ የፍትሀዊ አማካኝ ተጠቃሚ በማድረግ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ የፖለቲካ ማእቀፍ እንዲፈጠር ሲሆን የድርሻውን ለማበርከት አበክሮ እየሰራ ያለ ንቅናቄ ነው።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ባልደራስ/ ደግሞ የኢትዬጵያዊ ህብር አይነተኛ መገለጫ የሆነችውን የአድስ አበባ ከተማ ህዝብ ከከፋፋይና ከጥላቻ ፖለቲካ ነፃ ለማድረግና ህዝቡ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ እንዲረጋገጥ ለማስቻል በሚል የተደራጀ ስለመሆኑ በሰፊው የሚታወቅ ነው።
አዲስ አበባ ከተማ የኗሪዎቿ መሆኗን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት የጋራ ትግል መነሻ ዴሞክራሲን፣ ነፃነትን፣ ፍትህንና እኩልነትን በማስፈን ላይ የተመሰረተ ሲሆን አንዳች ቅቡልነት ያለው መርህ ወይም ምክንያት ማጣቀስ የማይችሉ ሀይሎች ከተማዋ የአንድ ንጥል ብሄር ንብረት መሆኗን በይፋ በመግለፅ የማታገያ አጀንዳ በማድረግ ህዝቡ በነሱ ፍቃድና ይሁንታ መኖር እንዳለበት አድርገው ያወጁት ያልተገራ ፍላጎት የጋረጠበትን የህልውና ስጋት መቀረፍ እንዳለበት አብንና ባልደራስ የጋራ ፖለቲካዊ አቋም ወሰደዋል።
የሀገራችን ኢትዬጵያ መድናና የመላ ህዝቧ ሰላማዊ መኖሪያ ሆና ዘመናትን የተሻገረችው አዲስ አበባ መደበኛና ነባር ምልከታ ሊቸራት ሲገባ ከልቦለድ የመነጨ የዘረኞች “የልዩ ጥቅም”ቀንበር ጊዜ በረዘመ ቁጥር የህግና የፖለቲካ ቋጠሮው እየጠበቀ መምጣቱና ይዘቱ “በኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና በአዲስ አበባ መስተዳደር ስምምነት” እንደሚወሰን በተሻሻለው ቻርተር መደንገጉ ከተማዋንና ህዝቧን ከአንድ ወገን በተሰባሰበ የፖለቲካ ሀይል ይሁንታ፣ ፍፁም ቁጥጥርና ጥበቃ ስር ለማዋል የተወሰነ መሆኑን ያሳያል። አብንና ባልደራስ ይሄን አምባገነናዊ፣ ፍትህ አልቦ፣ ዘረኛ፣ አግላይና በመጨረሻም የግጭትና የብሄራዊ ደህንነት አደጋ የሆነ አፍራሽ እንቅስቃሴ በጋራ ተሰልፈው ለመታገል ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ትብብሩ በቀጣይ እንዲፈጠርና እንዲጎለብት ለምንፈልገው የሀገራዊ በጎ ሀይሎች ጥምረት እርሾ ሆኖ እንዲያገለግል የታለመ ነው። አስቻይነት የሌለውና በህግ የተደነገገው የጊዜ ገደብ ጉዳይ በነባራዊ ተግዳሮቶች ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን በማረጋገጥ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተመሳሳይ አንድምታ ያላቸውን ጉዳዬች ባስተናገደበት ሁኔታ ትብብሩ ለህጋዊ እውቅና ሲቀርብ በመፍቀድና በመመዝገብ እንዲያፀድቀው የሚቀርብ ይሆናል።
በዚህ መነሻነት ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ትግል በመጪው ሃገራዊ ምርጫ የመራጮችን የጋራ ፍላጎትና ራዕይ ለማሳካት የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ/አብን/ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ባልደራስ/ በጋራ የምንሰራበት የፖለቲካ ትብብር ፈጥረን ለመስራት መወሰናችንን ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዬጵያውያን፣ ለመላው አማራ ህዝብና ለአድስ አበባ ህዝብ ስናበስር በታላቅ ደስታ ነው። ሌሎች ፓርቲዎችን ጨምሮ በሁለቱ ፓርቲ አመራሮች መሃከል ለወራት ሲካሄድ የነበረው ረጂምና አድካሚ ድርድር ፍሬ አፍርቶ መጪውን ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የአብን እና የባልደራስ ትብብር አሸናፊ ሆኖ መውጣት የሚያስችላቸውን የጋራ ስልቶች ቀይሰው በይፋ መንቀሳቀስ ጀምረዋል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ/አብን/ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ/ባልደራስ/ አጠቃላይ የኢትዬጵያ ህዝብ፣ የአማራ ህዝብ እና የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪ ህዝብ በበደል ውስጥ አምጠው የወለዷቸው የቁርጥ ቀን ልጆቹ እንደመሆናቸው መጠን በተባባረ ክንድ በህዝባችን ላይ የተጫነውን የመከራ ቀንበር እንዲወርድ ከመቸውም ግዜ በላይ በጋራ ትብብር ለመታገል በቁርጠኝነት ተሰልፈዋል፡፡
አብን በጽንፈኞች የተሳሳተ ትርክት መነሻነት በአማራ ህዝብ ላይ በተከታታይ የሚደርሰው ግፍ ድምጽ በመሆን በመጀመሪያው ረድፍ ሆኖ ትግሉን እየመራ ይገኛል። አብን የሀገራችን ኢትዬጵያን ደህንነት ለማረጋገጥና ህልውናዋን ለማስቀጠል አንድ ወሳኝ አምድ የሆነው የአማራ ህዝብ በልዩ ሁኔታ ተፈርጆ የሚጠቃበትን የፅንፈኞች ስሁት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለመግታት የሚያስችል ልዩ ማዕቀፍ ሆኖ የተደራጀ ሲሆን ታሪካዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስሪቱ በኢትዬጵያዊነት፣ ምልከታውም በወንድማማችነት፣ በፍትህና በዴሞክራሲ የተቃኘ ስለመሆኑ ውሎ ያደረ ጉዳይ ነው።
ከላይ በሰፊው እንደተመላከተው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ላይ የተጋረጡ የህልውና አደጋዎችን ለመከላከል፣ የከተማዋ ህዝብም ራሱ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመረጣቸው እንደራሴዎቹ የመተዳደር መብቱን ለማስከበር ባሚያደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ በብቃትና በንቃት በነሳተፍ አያሌ መስዋዕትነቶችን በመክፈል የቀጠለ መሆኑን ራሱ ህዝቡ በተግባር ኖሮ ያረጋገጠው ሀቅ ነው። ከላይ በተጠቀሱት መሰረታዊ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ ግቦች ዙሪያ ሁለቱ ድርጅቶች በፅኑ የሚጋሯቸውን አቋሞች መሰረት በማድረግ ቀጣይ ለሚደረገው ጠንካራና የተቀናጀ የህዝብ ትግል ወሳኝ የማታገያ አጀንዳ እንዲሆኑ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በሃገር አቀፍ ደረጃ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ መላው የሀገራችን ህዝብ፣ በተለይም የአማራ ህዝብና የአዲስ አበባ ህዝብ የተደቀነባቸውን የህልውና አደጋ በትብብር ከመታገል ውጭ ሌላ ተጨባጭ የመፍትሄ አማራጭ እንደሌለ መተማመን ላይ ደርሰዋል።
ከዚህ ቀደም በጋራ አብረውን ለመስራት ንግግር ጀምረው ሳለ በተለያዩ ምክንያቶች በትብብሩ ለመዝለቅ ያልቻሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁንም ጊዜው አለመርፈዱን ተገንዝበው በጎ ፍላጎት ካሳዩን ከግማሽ መንገድ ባላይ ተጉዘን ለመቀበል ዝግጁ መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን።
የፈጠርነው ትብብር አርአያ መሆን የሚችልና ከትላንት ለተሻለ አዲስ የፖለቲካ ባህል ማሳያ ፈር ቀዳጅ እንደመሆኑ ከምርጫ በኃላም ትብብሩ ጎልብቶ፤ የሀገራችንን ህዝብ ለዘመናት የቆየ የፍትህ ትግል ዳር ለማድረስ እንዲሁም የመላው ኢትዬጵያዊ የሆነችውን የአዲስ አበባ ከተማን ዓለም አቀፍነት የሚመጥን አመራር ለመስጠት ለመፍጠር ከወዲሁ አብረን መቆም ጀምረናል።
አብንና ባልደራስ የአዲስ አበባ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ዴሞክራሲያዊ መብት አክብረው ከሚቀበሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ትብብር በመፍጠር የከተማዋ ህዝብ በፌደራል መንግስቱ ውስጥ ተወክሎ እንደሁሉም ህዝብ ጥቅሙን ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ትግል የማሳለጥ ሚና እንደሚኖረው ለማሳወቅ እንወዳለን።
አዲስ አበባ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥረት የተገነባች፣የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ ብትሆንም፣ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የተነሱ ተረኞች ከተማይቷን በልዩ ጥቅም ስም የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ብቸኛ ንብረት ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ በጋራ አጥብቀን እናወግዛለን። በከተማይቱ እና ነዋሪዎቿ ላይ የተደቀነውን ይህ አደጋ ለመከላከል ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ/ ባልደራስ/ በዋነኛነት እያካሄደ ያለውን ትግል አብን የሚያድንቅ እና በሙሉ ልብ ከጎኑ እንደሚሰለፍ ቃል ይገባል። በአንጻሩም ባልደራስ ፓርቲ በጽንፈኞች ሴራ ኢላማ እንዲሆን በተደረገው የአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍ እና በደል ለማስቀረት በቁርጠኝነት አብን ለሚያደርገው ትግል ክብርና እውቅና እንደሚሰጥ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ስምምነታችን የተበላሸውን የሀገራችንን ፖለቲካ ባሕል በማስተካከል፣ በውይይትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል አብሮ መቆም እንደሚገባ ከማሳየት ባሻገር፣ ሌሎች ለተመሳሳይ አላማ ያነገቡ ፓርቲዎችም ይህን ፈለግ ተከትለው የትብብሩ አካል እንዲሆኑ ፅኑ ፍላጎት አለን።
በመጨረሻም በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ጽንፈኛ ሃይሎች በሚፈጽሟቸው የሽብር ድርጊቶች ምክንያት እየደረሰ ያለውን ሞት፣የአካል ጉዳት፣መፈናቀል እና የንብረት ውድመት ለማስቆም በየእርከኑ ያሉ የፌደራል እና የክልል መንግስታት ሃላፊዎች ተግተው እንዲሰሩ ጥሪ እናቀርባለን።
በተለይ ችግሩ ተባብሶ በሚገኝባቸው የኦሮሚያ፣ የቤንሻንጉል እና አንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች የሚገኙ የመንግስት አስተዳደርና የፀጥታ አካላት ችግሩን የሚመጥን ሀላፊነት በመውሰድ ንፁሀንን ከጥቃት እንዲከላከሉና ወንጀለኞችን ለህግ እንዲያቅርቡ በአፅንኦት እንጠይቃለን።
መሰረተ ቢስ በሆነ ክስ ተወንጅለው ለእስር የተዳረጉትንና የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን የተነፈጉ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እናሳስባለን። ትህነግ በለኮሰው ጦርነት በትግራይ ክልል ህግ ለማስከበር እየተካሄደ ባለው ዘመቻ የንጹሃን ዜጎቻችንን ደህንነት እና የሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ልዩ ትኩረት እንዲደረግና የሰብአዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማሳሰብ እንወዳለን።
መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ/ባልደራስ/
አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን
1ኛ. ከሁሉ አስቀድመን፣ በአገራችን ምዕራብ ኦሮምያ ክልል፣ ወለጋ ውስጥ፣ በሆሮጉድሩ ወረዳ ውስጥ ከየካቲት 27 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ በተፈጸመ ጥቃት ከ60 በላይ ንጹሃን ዜጎች በኦህዴድ/ብልጽግና ይሁንታ እና በኦነግ ሸኔ አድራጊነት የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባ ለሆኑ የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን ባልደራስ ይገልጻል፤ የሟቾችን ነፍስ ፈጣሪ በአጸደ ገነት ያኑርልን፡፡ ለውድ ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን፡፡ ፓርቲያችን በአማራ እና በሌሎች ንጹሃን ዜጎች ላይ ሆነ ተብሎ ለሚፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ኦነግን ከኤርትራ በረሃ ወደ አገር ቤት ከነትጥቁ እንዲገባ ያደረገው፣ በኦሮምያ ክልል ጸጥታ መዋቅር ውስጥ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ እንዲካተት ያደረገው እና በመንግሥታዊ ስልጣኑ ሽፋን በመስጠት ለዚህ አሸባሪነት ደረጃ የዶ/ር አብይ አህመድ አስተዳድር ከማንም በላይ ተጠያቂ እንደሆነ ፓርቲችን ባልደራስ በጽኑ ያምናል፡፡
ይሄንን አረመኔያዊ ወንጀል የፈጸሙ እና እንዲፈጸም ያደረጉ ሁሉ በፈጣሪም ሆነ በምድሩ ሕግ የሚጠየቁበት ጊዜ እሩቅ አይደለም ። ፓርቲያችንም ለዚህ እውን መሆን በትጋት እንደሚሰራ መግለጽ ይወዳል፡፡ በኦሮምያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ሳያቋርጥ ለባለፉት 3 ዓመታት የቀጠለው የዜጎች ሞት እና መፈናቀል ክልሉን እየመራ ያለው ኦህዴድ/ብልጽግና፣ በተረኝነት አገርን ከመዝረፍ ውጪ መምራት እንደማይችል ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ሃቅ ነው፡፡ ይህ ኃይል ተጨማሪ ዓመታትን በስልጣን ላይ ሲቆይ አገራችን ኢትዮጵያ ወደማትወጣበት ውስጣዊ እና አካባቢያዊ ገደል ውስጥ ይዞ የሚገባ ስለሆነ በቃ ሊባል የሚገባበት ምእራፍ ላይ ደርሰናል፡፡
ይህን መሰል በዜጎች ላይ የሚፈጸም ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ንብረት ማውደም እና ዘረፍ ከምንም በላይ መንግስታዊ ሽፋን የተሰጠው እንዲህ አይነቱ ዕኩይ ተግባር ባለበት ሁኔታ፤ የዘንድሮ ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግ መንግስት ጸጥታ የማስጠበቅ እና የዜጎችን ደህንነት ፣ የፖለቲካ ኃይሎች በሰላማዊ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚኖራቸው እንቅስቃሴ አደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑ ፓርቲያችን ይገነዘባል። በተጨማሪ መንግስት እንዲህ አይነቱ ዳተኝነት የሚያሳየው በሥልጣን ለመቀጠል ካለው የሥልጣን ጥመኝነት ነው ብሎ ፓርቲያችን ያምናል፡፡
2ኛ. የፓርቲያችን ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ እና ሌሎች ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች በተረኛው ኦህዴድ/ብልጽግና መራሹ መንግሥት ከሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ በግፍ እስር ላይ ያሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እነ እስክንድር ነጋ ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ኦህዴድ/ብልጽግና ምስክሮችን በግልጽ አቅርቦ ሊያስመሰክርባቸው እንዳልቻለ የፍርድ ሂደቱን የሚከታተለው መላው የአገራችን ህዝብ ያውቀዋል፡፡
እነ አቶ እስክንድር ነጋ አላግባብ ለእስር የተዳረጉት የፈጸሙት አንዳች የሚያስጠይቅ ነገር ኖሮ ሳይሆን፣ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ እንዳይሳተፉ ፓለቲካዊ ውሳኔ ተሰጥቶ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ፍርድ ቤቶችን በሃሳብ የበለጠውን ለማጥቂያነት መጠቀምን ከህወሃት/ትህነግ የተማረው ደቀ መዝሙሩ ኦህዴድ/ብልጽግና፣ ከትህነግ አሳዛኝ ፍጻሜ ምንም የተማረው ነገር ስለሌለ ተመሳሳይ የታሪክ ፍጻሜን ለመድገም እየተንደረደረ እንደሆነ የሚያሳይ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
ይህ በፍትህ ስርዓቱ መሣሪያነት አመራሮቻቸን ላይ የሚደርሰው በደል ሳያንስ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እነ አቶ እስክንድር ነጋ ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ በባልደራስ ፓርቲ ስም እጩ ሆነው እንዳይቀርቡ የሰጠው ውሳኔ አመራሮቻችንን ከገዢዎች ጋር ተደርቦ እንደማጥቃት አድርገን ቆጥረነዋል፡፡ በእነ አቶ እስክንድር ነጋ የፍርድ ሂደት ላይ የሚሳለቀው ዐቃቤ ሕግም ሆነ ይሄን ሰበብ አድርጎ የመመረጥ መብታቸውን በከለከለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መካከል ልዩነት ለማየት አይቻልም፡፡
ባልደራስ አቶ እስክንድር ነጋን በፓርቲው ስም እጩ አድርጎ በየካ ምርጫ ወረዳ አቅርቧቸው የነበረ ቢሆንም በ20/06/2013 ዓ/ም በተጻፈ ውሳኔ በሕግ ጥላ ስር ስለሆ በእጩነት መቅረብ እንደማይችሉ አሳውቆናል፡፡ ፓርቲው በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት በሕጉ መሠረት አቤቱታችንን ያቀረብንለት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤትም በ29/06/2013 ዓ/ም ለቅሬታችን በጽሁፍ በተሰጠው ውሳኔ በተመሳሳይ መልኩ በእጩነት መቅረብ እንደማይችል ምላሽ ሰጥቶናል፡፡
ነገር ግን፣ የእጩዎችን መስፈርት የሚያስቀምጠው “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር” አ/ቁ. 1162/11 አንቀጽ 31(1)(ሠ) “ማንኛውም ሰው በሕግ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ የመምረጥ ወይም የመመረጥ መብቱ ያልተገፈፈ” እንደሆነ በእጩነት መቅረብ እንደሚችል በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 20(3) መሠረት የተከሰሱ ሰዎች “በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር” ወይም ንፁህ ሆኖ የመገመት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ ይሄ መብትም ዓለማቀፍ ተቀባይነት ያለው እና አሁን ዓለም በደረሰበት ደረጃ ክርክር የሚነሳበት አይደለም፡፡
ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለእነ አቶ እስክንድር ነጋ ብቻ የሚሰራ ሕግ ያለ እስኪመስል ድረስ፣ ያለውን ግልጽ ሕግ ወደጎን በመተው እነ እስክንድር ነጋ በምርጫው እንዳይወዳደሩ የመመረጥ መብታቸው ላይ እራሱን እንደ ፍ/ቤት በመውሰድ የሰጠው ውሳኔ፣ ቦርዱን እንደተቋም ያለውን ተዓማኒነት በእጅጉ የሚጎዳ እንደሆነ ተረድተናል፡፡ ቦርዱ በ2007 ዓ/ም ከነበረው የፕ/ሮ መርጋ በቃና አመራር ኮምፒውተራይዝድ ከመሆን ባለፈ ያለውን ፖለቲካዊ ጫና ተቋቁሞ ወገንተኝነቱን ለእውነት ብቻ እንደሆነ ለማሳየት ተስኖታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የቦርዱ ውሳኔ፣ የ6ኛውን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ እና ገለልተኛነት በጥያቄ ምልክት ውስጥ እንድንከት አድርጎናል፡፡ ይሄ ከብልጽግና ጋር በመናበብ የተደረገ የሚመስለው የቦርዱ እርምጃ፣ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት እንደሆነ ባልደራስ ያምናል፡፡ በሕግ ጥላ ያሉ ዜጎችን የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ያለምንም የፍ/ቤት ቤት ውሳኔ መግፈፍ የጀመርነውን የዴሞክራሲ ጉዞ ያጨነግፈው እንደሆነ እንጂ የሚያጎለብተው አይሆነም፡፡ ለአቶ እስክንድር ነጋ የተመዘዘ የክልከላ ካርድ ነገ በማናቸውም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን ጥርጣሬ የለንም፡፡ በእነ አቶ እስክንድር ነጋ ዴሞክራሲያዊ መብት መገፈፍ ላይ ከገዢው ፓርቲ እኩል ምርጫ ቦርድ የወሰደው አቋም የማይተካ ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ በዚህ ታሪካዊ የስህተት ውሳኔው፣ ቦርዱን እንደተቋም የማውረድ ውጤት ብቻ ሳይሆን፣ በአገራችን ለሚከሰተው ችግር ቦርዱ እራሱ አንድ ምንጭ እንደሆነ ፓርቲያችን ያምናል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ፓርቲያችን እየተፈጸመ ያለውን በደል ለሕዝብ ይፋ ከማድረግ ባሻገር፣ ወደ መደበኛ ፍ/ቤት በመውሰድ ለተቋቋሙት ልዩ የምርጫ ችሎቶች በገለልተኛነት ፍርድ እንደሚሰጡ ወይም በገዢው ፓርቲ ረጅም እጅ የተጠለፉ መሆናቸውን መፈተሽ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በምርጫ ቦርድ ያለውን ሂደት በሙሉ ጠብቆ የጨረሰው ፓርቲያችን በቀጣይ ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ የፍትህ ተቋሙን ገለልተኝነት ከወዲሁ ለመፈተሽ ወስኗል፡፡
እስክንድር ነጋ ፣ ስንታየሁ ቸኮል ፣ ቀለብ ስዩም እና አስካለ ደምሌን ነጻ አስወጥቶ በአገራቸው የፖለቲካ ጉዳይ ተሳታፉ እንዲሆኑ ፓርቲያችን እያደረገ ያለው ትግል ሁሉንም ተቋማቶቻችንን በማጋለጥ ይቀጥላል፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ተከብራ ትኖራለች
ድል ለዲሞክራሲ!!!
መጋቢት 2, 2013 ዓ.ም
በኦሮሚያ፤ ሆሮጉድሩ ወለጋ አቤ ደንጎሮ አማራዎች ካለፈው ቅዳሜ የካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እንደ አዲስ በነሲብ እየተገደሉ ነው። የሚገደሉትም በመንግሥታዊ የእዝ መዋቅር በታገዘ ታጣቂ ቡድን ነው። ከግድያ የተረፉት ታግተው ወደ ጫካ ተወስደዋል። ሕፃናት እየታነቁ ወንዝ ውስጥ መወርወራቸውንም ከአካባቢው የወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ። በጉጂ፤ አማሮ ተመሳሳይ ብሔር ተኮር ጥቃቶች እየተፈፀሙ ነው።
በመሆኑም ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) በንፁሃን ላይ በደረሰው ግድያ የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ መንግሥት በአማራ ላይ የጀመረውን የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ እንዲያቆም ያሳስባል። ከግድያ የተረፉትን ወደ ቀደመ ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲመልስ እንጠይቃለን።
በተመሳሳይ በየመን፤ ሰንዓ ከተማ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያዊያን በሚገኙበት የስደተኞች መጠለያ ላይ የእሳት ቃጠሎ ደርሶ በርካቶች ሙተዋል። ባልደራስ ለቤተሰቦቻቸው እና ለመላው ኢትዮጵያውያን መፅናናትን ይመኛል። ፈጣሪ የሟቾችን ነፍስ ይማር!
ድል ለዴሞክራሲ
ባልደራስ ለዕውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ
የካቲት 2013
የባልደራስ ለዕውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎች በእስር ላይ የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች ባልተገኙበት ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ መስጠቱ ተገቢነት የለውም።
አቃቤ ሕግ ምስክሮችን በግልፅ ችሎት አቅርቤ ምስክር ማሰማት አልችል በማለት ሰበብ መሪዎቻችን የተፋጠነ ፍትህ እንዳያገኙ እየሰራ መሆኑን ከጅምሩ ፓርቲያችን ይረዳል።
ጠ/ፍ/ቤቱ የቀጠሮ ቀን ከመወሰኑ አስቀድሞ የመከራከሪያ ጭብጡን ግልባጭ ጠበቆቻችን በተደጋጋሚ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም ምላሽ ሳያገኙ ቀርተዋል።
ግልባጩ ለተከሳሽ የባልደራስ አመራሮችም ባልደረሰበት ሁናቴ ዛሬ ጠ/ፍ/ቤቱ ለቀጣይ መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ግራ ቀኙን ለማከራከር በሚል ቀጠሮ ሰጥቷል።
ይህ ደግሞ አመራሮቻችን የተፋጠነ ፍትህ አግኝተው በቀጣይ በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ተሳትፈው በህዝብ እንዳይዳኙ ሆን ተብሎ ዕንቅፋት መፍጠር መሆኑን ተገንዝበናል። ህዝቡም ይረዳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፤ ገና ከጅምሩ የፍትሕ ሥርዓቱ በሕግ እና በእውነት እንዲመራ የዛሬን ብቻ ሣይሆን የወደፊቱን ጭምር በማሰብ ፤ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋ ፥ ” ይህ እንደ-ማናቸውም የወንጀል ጉዳይ አይደለም ፤ ይህ ታሪክ ነው ። ነገ በታሪክ የሚጠቀስ የፍትሕ ሥርዓት ነው ።
ከሁሉም በፊት ፤ ሁሉንም በሚያውቀው በፈጣሪ ፊት ! እንዲሁም በህዝብ ፊት ጥፋተኞች አይደለንም ። ፈጥኖ ይሁን ዘግይቶ ነፃ እናወጣለን!
ጊዜው የምርጫ ነው ፤ የሚጠብቀን ህዝብ አለ ፤ በህዝብ መዳኘት እንፈልጋለን ። ለምርጫ እየተዘጋጀን ባለንበት ወቅት ነው በሐሰት ክስ የታሰርነው ፤ ይህን ፍርድ ቤት ፤ በፈጣሪ ስም እና በኢትዮጵያ ህዝብ ስም የምንጠይቀው የተፋጠን ፍርድ እንዲሰጠን ነው ። ” በማለት እስክንድር ገና ከጅምሩ አጽኖት በመስጠት በፍ/ቤት የተናገረው ቃል ነው !!!
በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝብ የአገራችን የፍትህ ስርዓት የቀብር ዋዜማ ላይ መሆኑን በመረዳት ፤ በቀጣይ ለምናደርገው ማንኛውም ሰላምዊ ትግል ከጎናችን እንዲሆን እንጠይቃለን!
ባልደራስ ከያዛቸው ሰላማዊ ትግሎች አንዱ በቀጣይ በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ ነው። ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ፤ በምርጫ ካርዱ ሰለዕውነተኛ ፍትህ እንዲተጋ እንጠይቃለን!
ድል ለዴሞክራሲ
ባልደራስ ለዕውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ
የካቲት 2013
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) እንኳን የሶማሌው ጀኔራል ዚያድ ባሬ ወራሪ ጦር ድል ለተደረገበት 43ኛው የካራማራ የድል በዓል አደረሳችሁ እያለ በዓሉን ስናከብር ሉዓላዊነታችንን በማስከበር ሊሆን እንደሚገባ ያሳስባል። ከአድዋ እስከ ካራማራ በወርሃ የካቲት የምንዘክራቸው የድል በዓላት ዛሬም ሉዓላዊ ክብራችንን እንዴት መጠበቅ እንዳለብን ምሳሌዎች ናቸው። በአባቶቻችን ዘመን ያልተደፈረች ኢትዮጵያ በእኛ ዘመን አትንበረከክም። ከተንበርካኪነት ዲፕሎማሲ ልንወጣ ይገባል። የአደግዳጊነት ታሪክ የለንም። በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንሥት ግብፅ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ብትሞክርም አፄው በአባይ እንደሚጎዷት ገልፀው አደብ አስገዝተዋታል። በ1632 ዓ.ም. ፖርቹጋሎች ለወታደራዊ ድጋፍ ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ሆኖም ከመጡበት አላማ ውጭ የሀገራቸውን ሀይማኖት በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ሲሠሩ ተደረሰባቸው። የወቅቱ መሪ አፄ ፋሲል ወዲያውኑ ከኢትዮጵያ ምድር አስፈተለኳቸው። ወቅቱም ‘በር የመዝጋት ዘመን’ እየተባለ ይጠራ ነበር።
ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አስረኛው የአብዮት በዓላቸውን ሲያከብሩ “በርከታ ገንዘብ አፍስሳችሁ ደግሳችኋል። ሀብት አባክናችኋል” የሚል ትችት ከተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች መጣባቸው። መንግሥቱም “በርገጥ በርካሽ ወጭ መሰብሰቢያ አዳራሽ ሠርተናል። ነገር ግን ምን አይነት ኪችንና ሳሎን እንደምንገነባ እናንተን አናማክርም” በማለት ገድበዋቸዋል። የተጠቀሱት መሪዎች የመሪነት የውሃ ልክ ናቸው እያል አይደለም። የሀገርን ሉዓላዊነት ከማስከበር አንፃር ያደረጉት ተግባር ግን ይህ ትውልድ ሊወርሰው የሚገባ ነው።
በአዲሱ የጆ ባይደን አስተዳድር የሚመራው የአሜሪካ መንግሥት ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ላይ ያሳየው አጉራ ዘለል ጣልቃ ገብነት በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። ሳይጋበዝ ጓዳችን ውስጥ ገብቶ በውስጥ ጉዳያችን ከመወሰኑም በላይ እርስ በእርስ የሚከፋፍል ነው። በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በኩል የወጣው መግለጫ አልፎ ተርፎ የአማራና የትግራይ ‘ክልሎችን’ የአስተዳድር ወሰን ለመቅደድ የዳዳው ሆኖ አግኝተነዋል። “የአማራ ሃይሎች ከትግራይ ይውጡ” የሚለው አገላለፅ የሚያንፀባርቀው ይህንኑ ነው። የአማራ ልዩ ሃይል የሚገኘው የራሱ የአማራው ሕዝብ አፅመ ርስት በሆኑት ወልቃይት፣ ጠለምትና ራያ ላይ ነው። በአሁኑ ጊዜ የእነኝህ አካባቢዎች አስተዳድር ወያኔ ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት ይተዳደሩበት ወደ ነበረው ግዛታቸው ተመልሰዋል። ኗሪዎች በርካታ አሥተዳድራዊ ጉዳዮችን የሚያስፈፅሙት ባሕር ዳር በሚገኘው የአማራ መስተዳድር ነው። በመሆኑም ትግራይ ውስጥ የከተመ የአማራ ወታደራዊ ሃይል የለም። የአማሪካ መንግሥት ወያኔ ቅብ የትግራይ ፅንፈኛ ብሔርተኞች እየተንከባለሉ የተነፈሱትን ከማስተጋባት ይልቅ እውነታውን ሊያገናዝብ ይገባል።
የተባለው ሆኖ ቢሆን እንኳን የኢትዮጵያን የጓዳ ድስት አሜሪካ የምታማስልበት አመክንዮ የለም። ሊኖርም አይገባም። ‘አማራ ከትግራይ ይውጣ፤ ትግራይ ከአማራ ይውጣ’ ማለት ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያ ውጭ እንደማለት ነው። ፓርቲያችን ለዚህ ቅጣንባር የለሽ ውሳኔ ኢትዮጵያን የማፍረስ ፍላጎት ያለው ከማለት ውጭ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በቅርቡ በማዕከላዊ መንግሥቱና በትግራይ መካከል ስላለው የወያኔን አማጺ ቡድን የማስወገድ እንቅስቃሴ ላይ ከኬንያው ፕሬዚደንት ጋር ተወያይተዋል። ይህም ከትንኮሳ ሌላ ስም ሊሰጠው አይችልም። በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ማግኘት ያለባቸው የኢትዮጵያን መሪ እንጂ የኬንያን አልነበረም። በአፍሪካ ሕብረት በኩል ኬንያ የምታስፈልግበት አጀንዳ ቢኖር እንኳን ኢትዮጵያን ማነጋገር ይቀድማል። ኬንያና አሜሪካ በሚያደርጉት ውይይት ላይም ባለጉዳይዋ ሀገር ልትሳተፍ ይገባል።
አሜሪካ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ እንዲወጡም ጠይቃለች። በቅድሚያ ወታደሮቹ ስለ መግባት አለመግባታቸው ተጨባጭ መረጃ ሊቀርብ ይገባል። ገብተውም ከሆነ ዋና ከተማቸውን አስመራን በሚሳኤል ለደበደበው የወያኔ አማጺ ቡድን ተመጣጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ እናምናለን። ንፁሃን ትግሬዎች ላይ ጉዳት አድርሶ ከሆነ ባልደራስ ይቃወማል። ሆኖም ግን ይህን ለመቃወምም ሆነ ከግዛቷ ለማስወጣት ኢትዮጵያ በቂ ነች። የአሜሪካ ድጋፍ አያስፈልጋትም። ኢትዮጵያ እስከፈለገች ድረስ የኤርትራንም፣ የሩሲያንም፣ የቱርክንም ጦር ሰራዊት ማስገባት ሉዓላዊ መብቷ ነው። ኢትዮጵያ ከፈለገች የኤርትራ ወታደሮችን ከማስገባትም በዘለለ ሰፊ የጦር ማዕከል ልትገነባላቸው ትችላለች። አሜሪካ ከወደደችው ሀገር ጋር የጦር ስምምነት ስትፈፅም ኢትዮጵያን እንደማታስፈቅደው ሁሉ ኢትዮጵያም ከወደደችው ሀገር ጋር የጦር ቃል ኪዳን ትዋዋላለች።
በኢትዮጵያ፤ ትግራይ የሚደረገው የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ወያኔ ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜም ግምኛ ሥር ሰዶ የቆየ ነው። “የወያኔ ፖሊሶች አስገድደው ደፈሩን” በሚል የተንቤን ሴቶች ሰላማዊ ሰልፍ መውጣታቸው ይታወሳል። ሴት ልጅ ከባሏ ዓይን ስር በታጣቂ ሃይል ተገዳ ስትደፈር ኖራለች። ይህ መቆም አለበት። ከወያኔ በኋላም ቀጥሎ ከሆነ በገለልተኛ ተቋማት ተጠንቶ ተጨባጭ መረጃ ሊቀርብ ይገባል።
በአሜሪካ መንግሥት በኩል የቀረበው ግን የአንድ ወገን ጩኸትን ብቻ ያስተጋባ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ሉዓላዊነትን ለማስከበር ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት እንዲሠራ ባልደራስ ያሳስባል። ካለፈው ጥቅምት መጨረሻ ማለትም ወያኔ ማዕከላዊ መንግሥት ላይ ጦርነት ከከፈተበት ጊዜ ጀምሮ የሱዳን ወራሪ ሰራዊት ጓንግ ወንዝን ተሻግሮ ኢትዮጵያ ገብቷል። ይህ አስቸኳይ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል። ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነትም የአብይ አሕመድና የኢሳያስ አፈወርቂ የግል ሽርክና እንደሆነ ቀጥሏል። ስምምነቶች ለሁለቱም ሀገራት ሕዝቦች ግልፅ ተደርገው መንግሥታዊ ቅርፅ ሊይዙ ይገባል። በተጨማሪም አቶ ኢሳያስ በኢትዮጵያ ጉዳይ ከአላስፈላጊ ጣልቃ ገብነቶች እጃቸውን እንዲሰበስቡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ያሳስባል።
ድል ለዴሞክራሲ!