የወቅቱን የሃገራችንን የፖለቲካ እና ወታደራዊ ሁኔታ በማስመልከት ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ !

Press Release
የስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በተለይ የአዲስ አባባ የቅድመ ምርጫ ሂደት እና የድህረ ምርጫ የነጻ፣ የፍትሃዊነት እና የዴሞክራሲያዊ መመዘኛዎችን የማያሟላ መሆኑን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አስታውቋል።
“ገዥው ፓርቲ በዋና ፈፃሚነት፤ ምርጫ ቦርድ በተባባሪነት ዘርፈውታል። ይህም በመሆኑ በፍርድ ቤት ክስ መስርቻለው” ብሏል ፓርቲው ዛሬ ሐምሌ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው የምርመራ ውጤት።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የመጨረሻው የመራጮች ምዝገባ አሀዝ መሰረት በአዲስ አበባ 1.4 ሚሊዮን መራጮች ተመዝግበዋል። ይኸው ቦርድ አጠቃላይ የምርጫ ውጤቱን ይፋ ባደረገበት ዕለት እንዳስታወቀው ደግሞ በከተማዋ 1.8 ሚሊዮን ዜጎች ድምፅ ሰጥተዋል። ይህም አራት መቶ ሺህ ዜጎች በምርጫ ቦርድ ሳይመዘገቡ መምረጣቸውን ያረጋግጣል። በመሆኑም ዝርፊያውን የራሱ የምርጫ ቦርድ ሪፖርት የሚያረጋግጥ መሆኑን ባልደራስ ጠቁሟል።
በአዲስ አበባ የቅድመ ምርጫ ሂደትን አስመልክቶ ከዚህ ቀደም ሰኔ 1ቀን 2013 ዓ.ም. በ25 ገጾች በተዘጋጀው የዳሰሳ ጥናት የእጩዎች፣ መራጮች እና የፓርቲ አባላት የደህንነት ሁኔታ፤ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የታዩ
መሰናክሎችን እና በምርጫ ቦርድ በኩል የታዩ ችግሮች፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ፣ የመራጮች መዝገብባ እና የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምን አስመልክቶ ከፍተኛ ችግር የነበረበት እና የምርጫ መመዘኛ ትንሹን መስፈርት ያላሟላ እንደነበር ገልጿል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ 6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የአዲስ አበባ ምርጫ እና ድህረ ምርጫ ሂደትን በተመለከተ ባልደራስ ያካሄደውን የጥናት ውጤት በዋናው ቢሮ በዛሬው ዕለት በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርጓል ። የጥናት ውጤቱ በ30 ገጾች እና በ8 ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው። የሚከተሉትን አንኳር ጉዳዮችም ዳሷል፦
~ የድምፅ አሰጣጡን ስነ-ስርዓት እና የቆጠራ ሂደቱን
~ በድምፅ አሰጣጥ ሂደት በድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ የታዩ ክፍተቶችን
~ የቅሬታ አፈታት
~ የፓርቲ ወኪሎች ያጋጠሟቸው ተግዳሮቶች
~የምርጫ አስፈፃሚዎች ማንነት እና ያሳዩዋቸው ተግባራት
~ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች የነበራቸውን አሉታዊ ተፅዕኖ
~ በመራጮች ላይ የተፈጠሩ ጫናዎች
~ የምርጫ ጣቢያዎችን እና የምርጫ አዋጁን መቃኘት
በአጠቃላይ በድምፅ መስጫው ቀን እና በድህረ ምርጫው ቀናት የታዩ ህገ ወጥ ተግባራትን ዳሷል። መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን ሳይናሳዊ እና አስረጂ በሆኑ የአጠናን ስልቶች አቅርቧል።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ/ም የተደረገውን 6ኛ አገራዊ ምርጫ ድምጽ መስጫ ሂደት በተመለከተ መረጃዎችን በአዲስ አበባ ከተማ ካሉ የምርጫ ክልሎች በሙሉ በማሰባሰብ አጠናክሮ ለህዝብ ይፋ ለማድረግ በሚያስችል ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ፣ በድምጽ አሰጣጡ እና ቆጠራው የነበሩ ችግሮችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ ፓርቲያችን አቅርቦ ምላሽ በመጠበቅ ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አ/ቁ. 1162/11 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤትን ይፋ ከማድረጉ በፊት ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ውጤቱን ከመግለጽ እንዲቆጠቡ የሚከለክል ሕጋዊ ድንጋጌ በመኖሩ ፓርቲያችን እስካሁን ለሕግ ተገዥ በመሆን በድምጽ መስጫ ቀን የነበሩትን ችግሮች እና ውጤቱን በሚመለከት መግለጫ ከመስጠት ተቆጥቦ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ቦርዱ እስካሁን በተወሰኑ የአገራችን ክልሎች ያሉ ውጤቶችን ይፋ ከማድረጉ በስተቀር፣ በተሻለ መረጋጋት ውስጥ የተደረገውን የአዲስ አበባ ከተማን ውጤት አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ለህዝብ ይፋ ሳያደርግ ጊዜ እየወሰደ እንደሆነ ፓርቲያችን ያምናል፡፡
በፓርቲዎች የቀረቡ ቅሬታዎች እንዳሉ ሆነው፣ ቦርዱ ውጤቱን ያፋ ሳያደርግ በተድበሰበሰ ሁኔታ መቆየቱ አላስፈላጊ ለሆኑ እንቅስቃሴዎች በር የሚከፍት እንደሆነ ፓርቲያችን ይረዳል፡፡ አዲስ አበባን በተመለከተ በቦርዱ እጅ የገባው ውጤት የአንድ ፓርቲን የበላይነት እንደከዚህ በፊቱ የሚያረጋግጥ ሆነም አልሆነም፣ ፓርቲያችን እና ህዝቡ እውነቱን የማወቅ መብት አላቸው፡፡ ፓርቲያችን አሁንም የቦርዱን ሰብሳቢ፣ “ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የአዲስ አበባን ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት ለመራጩ ህዝብ ይፋ ያድርጉ” ብሎ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ሆኖም፣ ቦርዱ ውጤቱን ይፋ ለማድረግ ምክንያታዊ ያልሆነ ጊዜ አሁንም መውሰዱን የሚቀጥል ከሆነ፣ ፓርቲያችን በእጁ ያለውን የጥናት ሪፖርት ለህዝብ ይፋ ለማድረግ እና ለቀጣይ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመግባት የሚገደድ ይሆናል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ።
ድል ለእውነተኛ ለዲሞክራሲ !!!
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ፍትህ እንዲሰፍን ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ፣ አድሎአዊነትና ዘረኝነት እንዲወገድ፣ሕዝብ ከመፈናቀልና ከድህነት እንዲላቀቀቅ፣ አዲስ አበባ የራስ ገዝ አስተዳደር እንድትሆን እና ሌሎችም ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሰፍኑ የሚያስችል ሥርዓት ለማምጣት ጠንክሮ ሠርቷል፤እየሰራም ነው፡፡የሃገሪቱ መሪ ‹‹ከባልደራስ ጋር ግልጽ ጦርነት እንከፍታለን›› እያሉ በተናገሩበት ወቅት እንኳን ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ከመታገል ቁርጠኛ አቋሙ ወደ ኋላ አላለም፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በ6ኛው አገር አቀፍ ቅድመ ምርጫ ሂደት (Pre-election process) ላይ በተለያዩ ጊዜያት ሳይንሳዊ ጥናቶች አካሂዶ ዝቅተኛውን ዓለም አቀፍ የምርጫ መስፈርት የማያሟላ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ የምርጫ ሂደቱ የተበላሸ ከሆነ ውጤቱም በተመሳሳይ መንገድ ሊሆን እንደሚችል የሚጠበቅ ቢሆንም ባልደራስ በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ሲል በምርጫው የተሳተፈ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
ፓርቲያችን ከአራት ወራት በፊት ጀምሮ ባካሄዳቸው ከፍተኛ የምርጫ እንቅስቃሴዎች ወቅት ሕዝብ ከጎኑ መሆኑን በተለያዩ መንገዶች አረጋግጧል፡፡አዲስ አበቤ ለድርጅታችን በአሳየው ደጀንነትም ፓርቲያችን እጅጉን ኮርቷል፡፡ ያነሳነውን አዲስ አበባን ራስ ገዝ የማድረግ ጉዞ ሕዝባችን ከጎናችን በመሆን ስለሰጠን ድጋፍ ከልብ እናመሰግናለን፡፡ ለሰጣችሁንም ድምፅ ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህንኑ ወደ ፊትም አጠናክረን እንደምንሄድ በዚሁ አጋጣሚ እንገልፃለን ።
ዓላማችንን ከግብ ለማድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ ዕውቀታችሁን፣ ጊዜያችሁን፣ገንዘባችሁንና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ጭምር የለገሳችሁ የፓርቲው አመራሮች፣ የሕዝብ ተወካዮችና የአዲስ አበባ ምክር ቤቶች እጩዎች፣የምርጫው የቅስቀሳና የሎጂስቲክስ አካላት፣የባልደራስን የዴሞክራሲ ማዕዘን በመሆን የምርጫውን ሂደት ከሁለት ቀንና ሌሊት በላይ የተከታተላችሁ ወኪሎቻችን እና በተለያዩ እንቅስቃሴዎቻችን ላይ የተሳተፋችሁ ሁሉ የላቀ ምስጋና የምናቀርብላችሁ በታላቅ ደስታ ነው። በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ እና በሌሎችም ዓለማት የምትኖሩ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የድጋፍ ሰጭ ኮሚቴ እና የአማካሪ ቦርድ አባላት ላደረጋችሁት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ፣ ምክር እና አስተዋፆኦ ምስጋናችን እጅጉን ከፍ ያለ ነው፡፡
‹‹አዲስ አበባን ማዳን ኢትዮጵያን ማዳን ነው›› በሚል ዓላማ የጀመርነውን ጉዞ ገዥው ፓርቲ መሪዎቻችንን በማሰር ለማሰናከል ጥረት አድርጓል፡፡ነገር ግን ትግሉ የተነሳበትን ዓላማ ይበልጥ ከፍ አድርጎ በመቀጠሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የሚገዙት ሃሳብ ሆኗል፡፡በሀገር ውስጥ ያላችሁ አባላት እና በውጭ ሃገር የምትኖሩ ድጋፍ ሰጭዎች የተሸረበውን ሴራ በጣጥሳችሁ በመውጣት፣ በሰላማዊ ትግሉ ፋና ወጊ የሆኑ መሪዎችን ቀንዲል ከፍ ብሎ እንዲታይ ያደረጋችሁ ናችሁና በድጋሚ የባልደራስ አመራር በእናንተ ደስታና ኩራት እንደሚሰማው ይገልጻል ።
በባልደራስ ፓርቲ ቅድመ ምርጫ ሂደት ጥናት እንደተረጋገጠው በብዙ ውጥንቅጥ ውስጥ የታጀበው ዝቅተኛውን የምርጫ መመዘኛ ደረጃዎች ያላሟላው የሰኔ 14/2013 ዓ.ም. ምርጫ የመጣውን ውጤት ማሳየት ችሏል። እንደሌሎቹ ጊዜዎች ሁሉ የዘንድሮውንም ምርጫ ነፃ፣ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ከመንግሥት በኩል ምንም ቁርጠኝነት አለመኖሩን ፓርቲያችን ተገንዝቧል።
ከምርጫው ቀን ዋዜማ ጀምሮ በአዲስ አበባ ነዋሪ ላይ የፍርሃት ድባብ ለመፍጠር በከፍተኛ ደረጃ የታጠቁ የፓሊስ እና የመከላከያ አባላት የጦር መሣሪያቸውን ወድረው በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የስነ ልቦና ጫና ሲፈጥሩ ሰንብተዋል፡፡ ይህም ‹‹ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ይሏታል ጅግራ›› እንደሚባለው በምርጫው ሰሞን ከነበሩ ኢዲሞክራሲያዊ ትዕይንቶች አንዱ ነበር።
ምርጫውን ነፃ፣ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ጠቀሜታው በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት እና ተወዳድረው ለማሸነፍ ለሚፎካከሩት ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ለሚወክሉት ሕዝብ ጭምር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምርጫው ነፃ፣ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሳይሆን ሲቀር የሕዝብ ነፃነት ይገፈፋል፡፡ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሣል፡፡በዜጐች መካከል የደረጃ ልዩነት እና መሠል ችግሮች ተፈጥረው ህዝብ በፍርሃት አረንቋ ውስጥ ይወድቃል።እነዚህን ችግሮችን ለማስወገድ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከፍተኛ ሓላፊነት ያለበት መሆኑ ይታወቃል፡፡
በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የተከሰቱ ችግሮችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በጥልቀት እየመረመረው ይገኛል። እስካሁን በደረሰበት ሁኔታ ምርጫው ነፃ፣ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ አልነበረም የሚል መደምደሚያ ላይ የሚያደርሱ ተግባራት መኖራቸውን ፓርቲያችን ያምናል፡፡ ለአብነትም፡-
1. ድምፅ አሰጣጥንበ በተመለከተ ግንዛቤ ለመስጠት የተሰየሙት የምርጫ አስፈፃሚዎች የገዢው ፓርቲ እንዲመረጥ የሚረዳ ገለጻ ሲያካሂዱ የፓርቲዎች ወኪሎች እርምት እንዲያደርጉ ቢያስገነዝቡም አስፈፃሚዎች ብልሹ አሠራራቸውን አለማስተካከላቸው በችግርነት የታየ ጉዳይ ነው፡፡
2. በመራጮች ምዝገባ ወቅት ያልነበሩ አዳዲስ ንዑስ የምርጫ ጣቢያዎችን ከመክፈት በተጨማሪ ማንነታቸው የማይታወቁ የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው በድምፅ መስጫ ቀን ድምፅ ሲሰጡባቸው መቆየታቸው፣
3. አቅመ ደካሞችን፣ በእድሜ የገፉትን እና የአካል ጉዳተኞችን የመንግሥት ካድሬዎች ከምርጫ ህጉ ውጭ በማገዝ ስም በሚስጥር ድምፅ በሚሰጥባቸው ክፍሎች ይዘዋቸው በመግባት ጫና እየፈጠሩ የሚፈልጉትን ማስመረጣቸው፣
4. በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የባልደራስን የምርጫ ውጤት ቁጥሮች እየቀነሱ እንዲጻፉ መደረጋቸው፣
5. ባልደራስ የተመረጠባቸውን ወረቀቶች በስልት ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ ወይም የባከኑ ውጤቶች እንዲሆኑ መደረጋቸው፣
6. በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ያለው የመራጩ ቁጥር ቀድሞ የሚታወቅ ሆኖ እያለ በብዙ የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ድምፅ መስጫ ወረቀቶች ከመራጮች ቁጥር እንዲያንስ መደረጉና ወረቀቱ እስኪመጣ መራጮች በፀሀይ፣ በዝናብና በብርድ በርካታ ሠዓታት እንዲቆዩ መሆናቸው የተወሰኑት ሳይመርጡ ወደ የቤታቸው እንዲሄዱ አስገድዷቸዋል፡፡
7. ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ለውድድር የቀረቡ ፓርቲዎች በርካታ በመሆናቸውና በምርጫ ወረቀቱ ላይ በምርጫ አስፈፃሚዎች በቂ እና ግልጽ ማብራሪያ ባለመሰጠቱ የምርጫ ወረቀቱ በውስጡ ምን ያህል እጩዎች እንደያዘ አለመታወቁ ለመራጮች አስቸጋሪ ሁኔታን የሚፈጥር ሆኗል፡፡ይህም መራጩ በግልጽ ድምፅ የመስጠት ነፃነት እንዳይኖረው አድርጓል፡፡በዚህም የድምፅ መስጫ ወረቀቶች እንዲባክኑ ወይም መራጩ ላልፈለገው ድምፅ እንዲሰጥ ሆኗል፡፡ከላይ የተጠቀሱት በምሳሌነት ከሚነሱት ችግሮች እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የገዥው ፓርቲ በምርጫ ወቅት ለችግረኛ ሰዎች የተለያዩ መደለያዎች በመስጠት የሕዝብን ገንዘብ ለሥልጣን መሸመቻ ማድረጉ በምድር ቀርቶ በፈጣሪ ዘንድ ይቅር የማያሰኝ ተግባር ነው። በሌሎች ጊዜዎች የድሆችን ችግር ለማስወገድ ትኩረት የማይሰጠው ገዥው ፓርቲ በምርጫ ሠዓት ብቻ ማባበያ ይዞ መቅረቡ ነዋሪውን ለመደገፍ ሳይሆን ሥልጣኑን ለማቆየት የተጠቀመበት ዘዴ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ከምርጫ 97 ወዲህ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲበዙ የተደረገባቸው ምክንያቶች ኗሪዎች በረጃጅም ሰልፎች ላይ በመቆየት እንዳይንገላቱ ለማድረግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ዛሬ ምርጫ ጣቢያዎች እንደአሸን እንዲፈሉ በተደረገበት ወቅት መራጮችን ለማሰላቸትና ለማስመረር ይሁን ተብሎ የተከናወኑት ማጓተቶች ድምፅ ሰጭዎች እንዲንገላቱ ማድረጉ የሚያስተዛዝብ ሁኔታን ፈጥሯል። ቀን በፀሀይና በዝናብ፣ በምሽት እና በሌሊት ደግሞ በብርድ እንዲንገላታ የተደረገበትን ደባ ተቋቁሞ የተሰለፈው አዲስ አበቤ ድምፁን ለማን እንደሰጠ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጠንቅቆ ያውቃል ።
በገዥው ፓርቲና በምርጫ ቦርድ ለማሰላቸት ሆን ተብሎ በተፈጠረው ተስፋ የማስቆረጥ ሂደት ሳትመርጡ ለቀራችሁ፣ ሆን ተብሎ በተሠራ ደባ ካርድ እንዳታወጡ የተደረጋችሁ እና መምረጥ ያልቻላችሁ፣ ጊዜ በማጣት ካርድ ላልወሰዳችሁ፣እንዲሁም በአገራችን ሁኔታ ተስፋ በመቁረጥ የዜግነት ግዴታ መወጣት ያልቻላችሁ የናንተ ድምፅ ሀገራችን ከገባችበት ውጥንቅጥ ችግሮች መውጫ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ሆኖ ሳለ በመቅረቱ በእጅጉ ያስቆጫል።
የአሁኑ የኦህዴድ/ብልጽግና አባት የሆነው ህውሃት/ኢህአዴግ በምርጫ 2007 የ100% የአሸነፍኩ ጉዞ ከ2ዓመት በላይ በሥልጣን መቆየት እንዳልቻለ የ3 ዓመት ትውስታችን ነው።በህዝብ ያልተመረጠ መንግሥት ራሱን ይሸነግል ይሆናል እንጂ ረጅም ርቀት እንደማይጓዝ ከዚሁ ከሀገራችን ታሪክ መረዳት ይቻላል። ለነፃ፣ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዳኝነት የሚሰጠው ሕዝብ ነውና።
6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ‹‹ነፃ፣ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ አደርጋለሁ›› ይል የነበረው ኦህዴድ/ብልጽግና በምርጫው ዙሪያ እየተፈጸሙ ያሉት ድርጊቶች የማያልቅ ሀሰቱ ማሳያዎች ሆነዋል። ዜጎች እየተገደሉ፣ ሰብዓዊ መብታቸው እየተጣሰ፣ ንብረታቸው እየወደመ፣ እየተራቡ እና እየተደፈሩ፣የውጭ ወራሪ ኃይሎች ድንበር ጥሰው ሀገራችን ውስጥ ገብተው እንደፈለጉ እየሆኑ ‹‹ኢትዮጵያ አሸንፋለች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ሰፍኗል፡፡ … ›› የተሰኙት አባባሎች ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ከማለት ያለፈ ትርጉም የላቸውም።
የአዲስ አበባ ሕዝብ ለሰጠን ታላቅ ድጋፍና ፍቅር፣ ክብርና ሞገስ አሁንም ደግመን እናመሰግነዋለን። የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች እና አባላት በሕዝብ ፊት በተግባር ጭምር እየተፈተንን የሰላማዊ ትግል አርበኞች መሆናችንን አስመስክረናል፡፡
የዴሞክራሲ ኃይሎች ትንንሽ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ለማይቀረው የሰላማዊ ትግል ተደጋግፈን ሕዝብን በማስተባበር እንድንታገል ዛሬም እንደቀድሞው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጥሪውን ያቀርባል።
ብሔራዊ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም. የተካሄደወን የምርጫ ውጤት ይፋ ካደረገ በኋላ ከምርጫው ጋር በተያያዘ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ባልደራስ መግለጫ የሚሰጥ መሆኑን በአክብሮት ይገልጻል፡፡
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ድል ለእውነተኛ ዴሞክራሲ!!!
ሰኔ 18/2013ዓ.ም.
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ባለፉት አራት ወራት የቅድመ ምርጫ እንቅስቃሴው በሃራዊ እና በአዲስ አበባ ነክ ጉዳዮች ፓርቲው የሚያራምደውን ፖሊሲዎች ለከተማው ሕዝብ በተለያዩ መድረኮች እና የቅስቀሳ ዜዴዎች ለማሳገንዘብ ጥረት ሲደርግ ቆይቷል፡፡
በሃገር አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያለውን አመለካከት በሃገር አቀፍ ማኒፌስቶው አስፎሮ አሰራጭቷል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማን ሕዝብ በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ/ም በሚካሄደው ምርጫ ቢመርጠው፣ ስር የሰደዱ የከተማይቱን ችግሮች ለመፍታት የነደፋቸውን ፖሊሲዎች ደግሞ በአዲስ አበባ ማኒፌስቶው አማካይነት በዝርዝር አቅርቧል፡፡
በዛሬው የቅድመ ምርጫ የባልደራስን የምረጡን ቅስቀሳ መርሃግብር መጠናቀቂያ ፕሮግራም ላይ ፓቲያችን ባልደራስ ለአዲስ አበባ ሕዝብ ለማስገንዘብ የሚፈልጋቸው ጉዳዮች ለየት ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህም ጉዳዮች ፓርቲችን ባልደራስ በተመለከተ በኦህዴድ/ብልፅግና በገሃድ ጥብቅና በቆሙለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ በስውር እየተነዛብ ያለውን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ምንነት ይፋ በማውጣት ባልደራስ የማይወክሉ መሆናቸውን አስረግጠን ለማቅረብ ነው፡፡
1ኛ/ አዲስ አበባን በተመለከተ በመርህ ደረጃ ልዩ ጥቅም አራማጆች ጋር በመርህ ደረጃ የማንስማማ መሆኑን፣ በአንድ ሀገር ሕዝብ መካከል አንዱ ጥቅም ሰጭ፣ አንዱ ጥቅም ተቀባይ እንዲሆን መፈለጉ ህጋዊም ዲሞክራሲያዊም አይደለም የሚለው አቋማችን ለምን ጊዜም አይቀየርም፡፡ እንደዚህ ዓይነት አባባል በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መካተቱ አግባብ አለመሆኑን ደጋግመን ገልፀናል፡፡ ሕገ መንግስቱም በሕዝብ ይሁንታ እንዲቀየር ለሪፈረንደም እንዲቀርብ በሰላማዊ መንገድ የምንታገልለት የፀና አቋማችን ነው፡፡
ይህ አቋማችንን የማይቀበለው የኦሮሞ ሕዝብ ሳይሆን የነገድ ፓለቲካ አራማጆች የሆኑ የኦሮሙማ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ናቸው ብለን እናምናለን፡፡ ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎቱ ከሌሎች ወንድም ከሆኑ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ጋር በአንድ ሃገር ሕዝብነት ሰሜት በሰላም፣ በእኩልነት እና በወንድማማችነት የጋራ ሃገራችንን ኢትዮጵያን እያለማ የጋራ ተጠቃሚ ሆኖ መኖርን እንደሆነ እንዳችም ጥርጥር የለንም፡፡ ይሁንና የማንነት ፖለቲካን ካላራመዱ የሕዝብ ድጋፍ እንደማያገኙ የተራዱ የኦሮሞ ፅንፈኛ የነገድ ፖለቲከኞች ባልደራስ የኦሮሞን ሕዝብ እንደሚጠላ በማስመሰል ፓርቲያችን ላይ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ሲነዛብን ቆይቷል፡፡ ባልደራስ ኦሮሞ ማበረሰብ ጋር አንዳችም ጠብ የለውም፡፡ ምክንያቱም የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ወንድም የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች የተለዩ ጥቅም ይሰጠኝ ብሎ ጠይቆ እንደማያውቅ፣ ይህን ጥያቄ የሚያራግቡት ፅንፈኛ ብሄርተኞች ብቻ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ከእነሱም ጋር ቢሆን ፓርቲያችን ባልደራስ ከተመሰረተ ጀምሮ እስካሁን ሲያደርግ እንደቆየው የሚታገለው በሰላማዊ መንገድ እና በሰላማዊ የፖለቲካ ዘይቤ ብቻ ነው፡፡ ባልደራስ የሚያራምደው የፖለቲካ አስተሳሰብ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ማህበረሰቦች በጋራ ጥቅም መርሆች አማካይነት በሰላም አብረው እንደኖሩት በዚያው መልክ እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ፖለቲካን በሰለጠነ፣ በዘመነ፣ በፀብ ሳይሆን በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ልዩነት መፍታት የሚቀበል ይህን አካሂድ ብቻ የሚያራምድ የፖለቲካ የተከተለ ነው፡፡
የኦሮሞ ማህበረሰብን ጨምሮ ሌሎችንም በርካታ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ዘላቂና መሰረታዊ ጥቅም የሚከበረው በሰላማዊ መንገድ እንጅ በፀብ እና በብጥብጥ እንዳልሆነ ፓርቲያችን ባልደራስ የፀና እና የማይናጋ አቋም አለው፡፡
ሌላው በፓርተያችን ላይ የብልፅግና ፓርቲ በጥቅም በመግዛት በደጋፊነት ባሰማራቸው የኢትዮጵያ ሙስሊም በማይወክሉ ብድኖች ባልደራስ ፀረ- እስላም ነው እሉ ስለሚያስነዙት የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ነው፡፡ ባልደራስ እንደሌሎች ፅንፈኛ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ታሪክ ትርክት ሰለባ አይደለም፡፡ ባልደራስ ጥንታዊ ሃገራችን ኢትዮጵያ የአብርሃም ኃይማኖቶች የሆኑት የክርስትና የእስልምና እና የአይሁድ ኃይማኖቶች ጥንታዊ መዳረሻ እንደሆነች ይቀበላል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ እነዚህ ኃይማቶች ከመነጩበት ከመካከለኛው ምስራቅ ብትወርስም ከራሷ ባህልና ልማድ ጋር አዋህዳ፣ ወዝና ጠረኗን በውስጣቸው አስርጻ ፍፁም ሀገራዊ እምነቶች እንዲሆኑ አድርጋ ኮትኩታ በማሳደግ በህዝቡ ውስጥ ስር እንዲሰዱ አድርጋለች፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም ሀገሮች ቀድማ እነዚህን ወንድማማች የአብርሃም ኃይማኖቶች ሀገራዊ ቅርፅና መገለጫ እንዲኖራቸው አድርጋ ያቆየቻቸው ኃይማኖቶች በመሆናቸው ፓርቲያችን ባልደራስ በኢትዮጵያ ክርስትና እና በኢትዮጵያ እስልምና መካከል አድሏዊ ፖለቲካ አይከተልም፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ታላላቅ ኃይማኖቶች የሚያራምዷቸው እምነቶች ከኢትዮጵያ ልዩ ሀገራዊ ባህሪ ጋር የተቆራኙ መሆናቸውን ፓርቲያችን ያለማወላወል ይቀበላል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በሃገራችን ያለው ሕዝብ የተቀበላቸው ኃይማኖቶች በእውነተኛ እኩልነት እና ነፃነት እምነታቸውን ማራመድ፣ የእምነት ጉዳዮቻቸውን አለ መንግስት እና ፖለቲካ ተፅእኖ፣ ጫና፣ አድሏዊ እና ጣልቃ ገብነት ሳይደረግ በራሳቸው በአማኞችና አማኞች በነፃነት በሚቀበሉት አመራር ብቻ እየተመራ ሊከናውን ይገባል የሚል ፅኑ እና የማይናወጥ አቋም አለው፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ ቢመርጠውም በማናቸውም ሁኔታ ሳያዛንፍ ተግባራዊ የሚያደርገው ይህንኑ አቋሙን እንደሆነ ለክርስትና እና ለእስልምና ቤተ እምነቶች እና ለምእመናኖዎቻቸው ለማስገንዘብ ይፈልጋል፡፡ ፓርቲችን ባልደራስ ለሙስሊም ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ለማስገንዘብ የሚፈልገው ሰላምን ወንድማማችነት፣ እውነትን፣ ለጋስነትን፣ ከሚያስተምር ቂምና ጥላቻን፣ ራስ ወዳድነትን የሚያወግዝ ኃይማኖታዊ አስተምህሮን የሚከተል ወገናችን ከሆነው ሕዝብ ሙስሊም ጋር በፍቅር እና በሰላም እና የአንድ ሃገር ልጅነትን አብሮ መኖርን እንጅ ምንም ዓይነት የጥላቻ አመለካከት የማናራምድ መሆናችንን እንዲገነዘብልን እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ ውጭ አንድ እምነትን የሚያገል አመለካከት ለሀገር ሰላም ጠንቅ መሆኑን ጠንቅቆ የሚገነዘብ ፓርቲ ነው፡፡
በፓርቲያችን ላይ የሚነዛው ሌላው ሃሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ደግሞ ባልደራስ በአዲስ አበባ ህዝብ ቢመረጥ የብልፅግና አባል የነበሩ የከተማው መስተዳድር ሠራተኞችን ከሥራ ያባርራል እየተባለ የሚነዛው የሃሰት ወሬ ነው፡፡ ባልደራስ በከተማው ቢመረጥ የብልፅግና አባል የሆኑ የመንግስት ሰራተኞችን ማባረሩን ተገቢ ነው ብሎ አያምንም፡፡ የፓርቲ አባልነታቸውን እንደጠበቁ የመንግሥት ሥራ መበስራት እንዲቀጥሉ እናደርጋለን፡፡
ሌላው በፓርቲያችን ላይ እየተነዛ ያለው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ባልደራስ በፀብ እና በፍጥጫ የሚያምን ፓርቲ ነው ስለሚባለው ነው፡፡ ባልደራስ የሚያራምዳቸውን የፖለቲካ አመለካከቶች በደም ፍላት እና በስሜት የተቀበላቸው አመለካከቶች አይደሉም፡፡ አውጥቶ አውርዶ፣ መክሮ እና አስመክሮ፤ በሰነድነት ሰንዶ ለሃገራችን ኢትዮጵያ በአጠቃላይ እና ለአዲስ አበባ ሕዝብ በተለይ ይበጃሉ ብሎ የተቀበላቸውን ነው፡፡ ባልደራስ ከፀብ እና ከፍጥጫ ሃገራችን ኢትዮጵያም ሆነች የሁላችንም ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ ይጠቀማሉ ብሎ ለአንድ ደቂቃም አምኖ አያውቅም፡፡ በዚያው ልክ ተረኝነትን፣ አድርባይነትን፣ ተቅለስላሽነትን ይፀይፋል፡፡ ፓርቲችን ባልደራስ እውነትን እውነት፣ ሃሰትን ሃሰትን ነው ብሎ በይፋ መቆምን እንደ ትክክለኛ መርህ አድርጎ ይቀበላል፡፡
ልዩነት በገሃድ እውጥቶ በፀብ አጫሪነት ሳይሆን በውይይት መፍታትን፣ በውይይት የማይፈታ ነገርን በማሳደርና መልሶ ለውይይት በማቅረብ፣ በዚያም መልኩ ካልተፈታ በሰላማዊ መንገድ በሪፈረንደም በህዝብ ዳኝነት እንዲፈቱ ለማድረግ በፅናት የሚታገል ፓርቲ ነው፡፡ በማጎብደድ የሃገር እና የሕዝብ ችግር ይፈታል የሚል እምነት የለውም፡፡ አሁን እየታዩ እንዳለው አካፋን አካፋ ማለት ካልተቻለ ሀገር እና ህዝብን ወደ አስከፊ ሁኔታ እየተመራ እንደሆነ ማስገንዘቡ አስፈላጊ ነው፡፡ ፓርቲችን በዚህ አጋጣ ሃገራችን ለገባችበት ሁለንተናዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ቀውስ መፍትሄው በመንግስት እና በአጋሮቹ ፍላጎት ብቻ በተፅእኖ የሚገፋው “ብሄራዊነት” የሌለው ምርጫ ሳይሆን አካታች በመሆኑ መልኩ የሚጠራ እና የሚካሄድ ብሔራዊ ውይይት እንደሆነ ፅኑ እምነት አለው፡፡፡፡
በዚህ አጋጣሚ ወንድም በሆነው የትግራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ፣ ጦርነቱ ተሳታፊ ባልሆኑ ዜጎች ላይ በሃገር መከላከያ አባላትና በኤርትራ ጦር እየደረሰ ያለውን ጥቃት፣ በክልሉ ሴት እህቶቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን የፆታዊ መደፈር ፓርቲችን ባልደራስ በፅኑ የሚደርሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ባልደራስ በፅኑ ያወግዛል፡፡ ፓርቲችን ባልደራስ በትግራ እየደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ የፖለቲካዊና ወታደራዊ ቀውስ ፍልሚያ ተከትሎ በአካባቢው እያንዣበበ ያለው የርሃብ አደጋ ህዝቡን ክፉኛ እየጎዳው መሆኑን ስለሚገነዘብ በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ የሕወሓት ተልእኮ ተሸካሚ ያልሆኑ የትግራ ልሂቃን ከአማራው የፖለቲካ ልሂቃን እና ከሌሎች ሃገራዊ ኃይሎች ጋር በመገናኘት የድህረ ሕወሓት የግትራይ የፖለቲካ ቀውስ ስለሚፈታበት ሁኔታ ምክክር እንዲደርጉ ፓርቲያችን ለሚመለከታቸው የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ኢትዮጵያ ከሃያላን ምዕራባውያን ጋር የገባችበትን የሃገራዊ ግንኙነት ቀውስ በተመለከተ የፓርቲያችን የባልደራስ አመለካከት ግልፅ ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ በቅድሚ የአባይ ወንዝ መገደብ ለኢትዮጵያ ልማት ቁልፍ ግብዓት መሆኑን ፓርቲችን ያምናል፡፡ በመሆኑም የብልፅግና መንግስት እየተዘጋጀበት ያለውን የግድቡን ሁለተኛ ሙሌት በታቀደለት ፕሮግራም መሰረት መሞላቱን ፓርቲያችንን ባልደራስ በፅኑ የሚደግፍ ሲሆን፣ ይህን አስመልክቶ ምዕራባዊያን ሃያላን ሀገሮች የሚያራምዱትን ለግብፅ እና ለሱዳን ያዳላ አቋም ፓርችን በፅናት ይቃወመዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰሜን ምዐራብ ድንበር በወራሪ የሰሜን የሱዳን ሠራዊት ተጥሶ እና ስፋት ያለው የሃገራችን ሉዓላዊ ግዛት ተወሮ ባለበት ሁኔታ፣ ይህን ወረራ ለመቀልበስና የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ለማስመለስ አንዳችም ተጨባጭ እርምጃ ሲወስድ የማይታየው የብልፅግና መንግሥት ምዕራባውያን ሃያላን ሀገሮች ባለሥልጣኖች ላይ ያደረጉትን የጉዞ ማዕቀብ እና ቀድሞውንም የሚታወቀውን የህወሓት ደጋፊነታቸውን በማጣቀስ የሃገራችን ሉዓላዊነት እንደተደፈረ አድርጎ የሚያቀርበው ፕሮፖጋንዳ አሳዛኝ ነው፡፡ የኤርትራ ጦር ትግራይ ውስጥ እንዲቆይ መደረጉ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ የማያስገባ መሆኑን ለማድበስበስ ይፈልጋል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ፓርቲያችን ባልደራስ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃገሮች መሆናቸውን ቢገነዘብም፣ በሁለቱም ሀገሮች ያለው ህዝብ በኃይማኖት፣ በቋንቋ በባህል እና በፌደል ሳቀር የተሰናሰለ አንድ ህዝብ መሆኑን ያምናል፡፡ ቀደም ሲል ወደ መለያየት ያመሩ ምክንያቶች ታርመው፣ የሁለቱ ሃገሮች ግንኙነት በወታደራዊ ጉዳዮች ከመረዳዳት በዘለለ ወደ ስርዓት መነግስታት ጥምረትነት ደረጃ ከፍ እንዲል ቢደረግ ለሁለቱም ሃገሮች ሕዝብ ይጠቅማል የሚል የፀና አመለካከት አለው፡፡
በመጨረሻም ባልደራስ 6ኛውን የምርጫ የሀገራችን ህዝቦች በታሪካቸው በድምፃቸው መንግሥትን የሚመርጡበት፣ የህዝብ ድምፅ በትክክል የሚከበርበት እንዲሆን ፓርቲያችን ይመኛል፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ገዥው ፓርቲ ጨምሮ ለነፃ ፍትሃዊና ሰላማዊ ምርጫ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን በትህትና እናቀርባለን፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ
ድል ለዲሞክራሲ!!!
የአንጋፋውን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ሊቅ፣ የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን ሕልፈተ ሕይወት የሰማነው፣ በጥልቅ የሐዘን ስሜት ነው፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣የኢትዮጵያ፡ቁዋንቁዎችንና ፡ሥነጽሑፍ እንዲኹም ታሪክ አስመልክተው ፣አያሌ የጥናትና የምርምር መጻሕፍትን ያበረከቱ ብርቅ፡ኢትዮጵያዊ፡ምሁር፡ነበሩ።
የቋንቋ ፣የሥነ ጽሑፍ፣የታሪክና የሥነመለኮት ሊቁ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ በተለያዩ አገራዊና አህጉራዊ የፖለቲካ እድገት አስተዳደርና ዴሞክራሲያዊ ነክ ጉዳዮች ላይ ይሰጡዋቸው፡በነበሩቱ በሳል ሀሳቦቻቸው እና ትችቶቻቸው ይታወቁ፡ነበር።
እኚህ ሀገራቸውን ወዳድ፣ ዓለም አቀፋዊ ምሁር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
አማካሪ ምክር ቤት አባላት መካካል አንዱ በመሆን፣ ለፖርቲያችን ያበረከቱት አስተዋጽዖ እጅግ የጎላ ነበር ። ለዚህም አኩሪ ተግባራቸው፣ ፓርቲያችንና ታሪክ፣ኹሌም ስማቸውን በክብር ሲያወሳ ይኖራል። ስለኾነም፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፣ በመላው የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎቹ ስም፣በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ሕይወት ማለፍ የተሰማውን ልባዊ ሐዘን እየገለጸ፣ለነፍሳቸው እረፍትን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ደግሞ የልብ፡መፅናናትን ይመኛል።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
1. የጥናቱ መሰረታዊ ሀተታ (Statement of the Problem)
እንደ “UDHR“(1948) ክፍል 3 አንቀፅ 21 ድንጋጌ መሠረት የመንግሥት ሥልጣን መሰረቱ የሕዝቡ ፈቃድ ይሆናል፤ይህ ፈቃድም በየተወሰነ ጊዜ በሚደረግ እውነተኛ ምርጫ አማካኝነት የሚካሄድ ሲሆን ምርጫም በምስጢራዊ የድምጽ አሰጣጥ ወይም መሰል ነፃ ሂደት ሁሉን አቀፍና እኩል አሳታፊ በሆነ መንገድ የሚካሄድ ይሆናል።
በተመሳሳይ ሁኔታ “ICCPR“ (1966)አንቀጽ 25 ድንጋጌ መሰረት እያንዳንዱ ዜጋ በዘር፣ቀለም፣ፆታ፣ቋንቋ፣ሐይማኖት፣የፖለቲካ ወይም የሌላ አመለካከት፣ብሔር፣ወይም ማሕበራዊ ዳራ፣ሐብት፣ትውልድ ወይም ሌላ አቋም” ላይ ተመስርቶ ምንም አይነት አድልዎ ሳይደረግበት እንዲሁም ምክንያታዊነት በሌላቸው አላስፈላጊ ክልከላዎች ሳቢያ “በእውነተኛ ምርጫዎች [መምረጥና መመረጥ]”ከመሳተፍ ሳይከለከል እንዲሳተፍ የሚያስችለው ዕድል ሊፈጠርለትና የመሳተፍ መብት ሊሰጠው ይገባል ይላል። የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 38 ድንጋጌ በ“UDHR“ ላይ የተቀመጠውን የፍትሀዊና የነፃ ምርጫ መርሆዎች ከማካተቱም ሌላ፣ይህ መብት በሥራ ላይ ሲውልም ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ለምሳሌ ያህል ከ“UDHR“ መንፈስ ጋራ በሚጣጣም መልኩ እንዲተገበርና ትርጓሜም እንዲሰጠው ጭምር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንገስት አንቀጽ 13 ያሳስባል።
ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ይህንን ቢደነግግም በሌላ በኩል ግን የምርጫ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 እነኝህን ዓለም አቀፍ የፍትሀዊና ነፃ ምርጫ መርሆዎች የሚጥስ ሆኖ እናገኘዋለን፤ለምሳሌ ያህል በአንድ ቦታ ከአንድ በላይ የምርጫ ጣቢያ እንዳይከፈት የሚከለክለውንና በአንድ ምርጫ ጣቢያ ከ 1,500 በላይ መራጮች እንዳይመዘገቡ የሚያግደውን ድንጋጌዎች መጥቀስ ይቻላል።
ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች ያላቸውን የስራ እንቅስቃሴ፣ የምርጫ ጣቢያዎች የስራ ሁኔታ፣ ከአለማቀፍ ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ መመዘኛዎች እና ከአለማቀፍ የሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ ድንጋጌዎች፣ ከህገ መንግስቱ እና ከምርጫ ህጉ አንፃር ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገምና እና በምርጫ ቦርድ አዲስ የተከፈቱ 32 ንዑስ የምርጫ ጣቢያዎችን ያሉበትን ደረጃ ለመቃኘት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለመመዘን በሰጠው አቅጣጫ መሰረት ጥናት ማድረግ አስፈላጊ ሁኖ ተገኝቷል፡፡
2. የጥናቱ ዋና ዓላማ
የጥናቱ አላማ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ (pre-election process) አካል የሆነውን የመራጮች ምዛገባ ሂደት (voter registration) ከነፃና ፍትሀዊ ምርጫ መርሆዎች አኳያ ምን ያህል ይጣጣማል የሚለውን ጉዳይ በጥናት ማረጋገጥ ሲሆን በመራጮች ምዝገባ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን፣ የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት ሁኔታ እና አጠቃላይ የቅድመ ምርጫውን ሂደት የሚዳስስ ጥናት ነው፡፡
2.1. የጥናቱ ዝርዝር ዓላማዎች
የዚህ ጥናት ዝርዝር ዓላማዎች፡-
ነባር እና አዲስ (ሚያዝያ 15/2013 ዓ.ም ጀምሮ የተከፈቱ) የምርጫ ጣቢያዎችን ያሉበትን ሁኔታ ማዳሰስ፣
በመራጮች ምዝገባ ሂደት ውስጥ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን መቃኘት፣
የምርጫ ሂደቱ (pre-election process) ከነፃና ፍትሀዊ ምርጫ መርሆዎች አኳያ ያለበትን ሁኔታ መገምገም፡፡
3. የጥናቱ አስፈላጊነት (Significance of the Study)
ይህ የዳሰሳ ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የታዩ ተግዳሮቶችን የሚዳስስ ሲሆን የጥናት ውጤቱ ለተለያዩ የባለ ድርሻ አካላት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ የምርጫ ቦርድ፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች እና በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከጥናቱ ግኝት ሊጠቀሙ የሚችሉ ሲሆን ማህበረሰቡም፣የምርጫ ታዛቢዎችም፣የአለም አቀፍ ማህበረሰብ እና ታዛቢዎችም ከጥናቱ ውጤት ስለ መራጮች ምዛገባ ሂደት(voter registration) ያለበትን ሁኔታ ሊገነዘብ ይችላል፡፡
4. የጥናቱ ወሰን (Scope of the Study)
ይህ ጥናት በዋነኛነት የሚያተኩረው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ብቻ የሚያካትት ሲሆን በምርጫ ጣቢያዎች እና በምዝገባ ሂደቱ የታዩ ችግሮችን ነቅሶ ማውጣት ነው፡፡
5. የጥናቱ የምርምር ዘዴዎች
ይህ ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የሚታዩ የምርጫ ምዝገባ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት፤ ቅሬታዎች እና አጠቃላይ ተግዳሮቶች ለመለየት ታስቦ የተደረገ ሳይንሳዊ ጥናት ነው፡፡ ይህ ምርምር የምርጫ ወቅታዊ ሁኔታውን ለማብራራት የሚያግዘውን የገላጭ ምርምር (Descriptive research) አይነት ተጠቅሟል፡፡ የገላጭ ምርምር የዳሰሳ ጥናት መንገድን በመጠቀም ጥናቱ ተጠናቅሯል፡፡
ጥናቱ ዓይነታዊ (Qualitative) የምርምር ዘዴ የተጠቀመ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ የምርጫ ምዝገባ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት፤ ቅሬታዎች እና አጠቃላይ ተግዳሮቶች ለመለየት ተሞክሯል፡፡ ጥናቱ ሁለት አይነት የመረጃ ምንጮችን ማለትም ቀዳማይ የመረጃ ምንጭ (primary source) እና ካልዓይ የመረጃ ምንጭ (secondary sources) አገልግሎት ላይ አውሏል፡፡
5.1. የናሙና አወሳሰድ እና አመራረጥ ስልት
ይህ ምርምር ከተጠያቂዎች ግልፅ፣ ዝርዝር፣ ተጨባጭ፣ ተገቢ እና ወቅታዊ መረጃን ይፈልጋል፡፡ ጥናቱ የምርጫ ምዝገባ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን፤ የምርጫ ምዝገባ ሰራተኞችን እና በምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙ የፀጥታ አካላትን ለመምረጥ ወካይነትን (representativeness) እና የመረጃ ሁሉን አካታችነት (generalizability of the data) መርሆዎች በመከተል ሁሉን አቀፍ እና ተጨባጭ መረጃ ለመሰብሰብ ከተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ናሙናዎችን ወስዷል፡፡ ጥናቱ የሁሉንም ክፍለከተሞች አደረጃጀት ያማከለ በመሆኑ የስብጥር ናሙና (stratified sampling) በመጠቀም ክፍለ ከተሞች በሁለት ክፍል ማለትም ውስጣዊ (inner) እና ውጫዊ (Peripherian) ደረጃ በሚል እንዲከፈሉ ተደረጓል፡፡
የጥናት ቡድኑ መረጃዎችን ለመሰብሰብ እና ለመተንትን ከሚያዚያ 20/2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 04/2013 ዓ.ም የተጠቀመ ሲሆን መረጃ የተሰበሰበባቸው ክፍለ-ከተሞች ብዛት ዘጠኝ ሲሆኑ እነርሱም ቦሌ፣ የካ፣ኮልፌ፣ ጉለሌ፣ ንፋስ ስልክ፣ አራዳ፣ አዲስ ከተማ፣ ልደታና አቃቂ ክፍለ ከተሞች ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ አንደ ሺ ስድስት መቶ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል የጥናት ቡድኑ መቶ ነባር ምርጫ ጣቢያዎችን እና ከሚያዚያ 15/2013ዓ.ም. በኃላ በምርጫ ቦርድ የተከፈቱ ሰላሳ ሁለት ንኡስ ጣቢያወችን ያካተተ ሲሆን በአጠቃላይ መቶ ሰላሳ ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች አካቷል፡፡ ምንም እንኳን በዓይነታዊ (Qualitative) የምርምር ዘዴ ወካይነት የጥናት ዘዴው ባህሪ ባይሆንም ጥናቱ ከአስር ፐርሰንት በላይ ናሙና ተወስዷል፤
በዚህ ጥናት የተሳረፉ የማህበረሰብ ክፍሎች የምርጫ አገልግሎት ተጠቃሚዎች፣ በምርጫ ጣቢያው አካባቢ ያሉትን ነዋሪዎች እና አገልግሎት በሚሰጥበት ምርጫ ጣቢያ የሚገኙ የፀጥታ አካላት(ፖሊሶች እና ጥበቃዎች) ናቸው፡፡
5.2. የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች
ጥናቱ የቅድመ ምርጫ አገልግሎት አሰጣጥን፣ የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት ሁኔታን እና የመራጮችን ቅሬታዎች በተመለከተ ትክክለኛ፣ ወቅታዊ እና ታማኝ መረጃዎችን ለመሰብሰብ የሚከተሉትን የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች አገልግሎት ላይ ውለዋል፤
የጥናት ቡድኑ በቀጥታ በአካል በመገኘት ሁኔታዎቹን የመረመረ ሲሆን የተለያዩ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን ተጠቅሟል፡፡ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች ምልከታ እና በምስል መረጃዎችን(ቪዲዮዎች) የተደገፈ ቃለ መጠይቅ ሲሆን በምርጫ ጣቢያወች ላይ የተቀመጡ ምልክቶችና ፅሁፎች በጥናቱ ትንተና ያልተካተቱ ማስረጃዎችም በአባሪነት ቀርበዋል፡፡
5.3. የመረጃ ትንተና ዘዴና አቀራረብ
የመረጃው ወጥነት እና ምሉዕነት በመረጃ ሰብሳቢዎች ከተረጋገጠ በኋላ ከቃለመጠይቅ እና ከምልከታ የተገኘው መረጃ ወደ ፅሁፍ ተቀይሯል፡፡ ከዚያም ፅሁፉን በተደጋጋሚ በማንበብ፤ ኮድ በማድረግ እና ዋና ዋና ጭብጦችን በመለየት ለመተንተን ተሞክሯል፡፡ በመቀጠልም ንዑሳን ጭብጦችን ከዋና ጭብጥ ስር በማደራጀት ትንታኔ የመስጠት ተግባር ተከናውኗል፡፡ የመረጃውን ትክክለኛነት ለማጠናከር በእያንዳንዱ የጥናት ጥያቄዎች ወይንም ግቦች ስር ከባለ ጉዳዬች፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከፀጥታ ኃይሎች፣ ከምልከታ፣ የተገኙ መረጃዎች በአይነታዊ ሃተታዎች አብረው ቀርበዋል፡፡ የጥናቱን መረጃ በመጠቀም የጥናቱ ውጤቶች በተለያዩ ክፍሎች ተከፋፈለው ቀርበዋል፡፡
5.4. የጥናቱ ተዓማኒነት ማረጋገጫ መንገዶች
የአጥኝ ቡድኑ የሚከተሉትን የጥናቱ ተዓማኒነት እና ትክክለኛነት ማረጋገጫ መንገዶችን ተጠቅሟል፡፡ የመረጃ መሰብሰቢያ መንገዶችን እና የጥናቱን አጠቃላይ እቅድ በባለሙያ ተተችቷል፤ ዋናው ጥናት ከመጀመሩ በፊት ቅድመ ጥናት ተካሂዷል፤ በመቀጠልም ሳይንሳዊ ተቀባይነት ያላቸውን የመረጃ መሰብሰቢያ መንገዶችን በመጠቀም መረጃ ተሰብስቧል፡፡
ተዓማኒነት፡ የጥናቱን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ በተለያዩ የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች የተሰበሰቡት መረጃዎች እና ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች የተገኙ መረጃዎችን በአንድ ላይ በማቀናጀት የመረጃውን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ ጥረት ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የመረጃ ሰብሳቢዎች የትምህርት ደረጃ ጥናቱ ከሚጠብቀው የትምህርት ደረጃ በላይ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የጥናቱ የመጀመሪያ ትንታኔ በአጥኝ ቡድኑ በጋራ ተመርምሯል፤ እንዲሁም የመጀመሪያ የጥናት ትንታኔ በአንድ የከፍተኛ ተመራማሪ እንዲገመገም ተደርጓል፡፡
5.5.የጥናቱ ምስጢራዊነት እና ሌሎች የስነ-ምግባር ጉዳዮች
የመሳተፍ ነፃነት፡ መረጃ በመስጠት በጥናቱ የተሳተፉ አካላት በጥናቱ ላይ የመሳተፍ መብታቸው እንዲከበር ተደርጓል፡፡ የጥናቱ ምንነት እና አጠቃላይ አላማ ማብራሪያ ከተደረገላቸው በኋላ ፈቀደኝነታቸውን ተጠይቀው ፈቃደኛ የሆኑት ብቻ እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡
ምስጢራዊነት፡ የጥናቱን ምስጥራዊነት በተመለከተም፡ መረጃ በመስጠት በጥናቱ የተሳተፉ አካላት የሚሰጡትን መረጃ ምስጢራዊነቱ የተጠበቀ እንደሚሆን መረጃው በተሰበሰበበት ጊዜ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከጥናቱ አገልግሎት ውጭ ምንም አይነት መረጃ ለማንም ተላልፎ እንደማይሰጥ ተነግሯቸዋል፡፡ ይህንንም ለመጠበቅ መረጃው በሚተነተንበት ወቅት የተጠያቂዎች ስም አልተጠቀሰም፡፡
6. በዳሰሳ ጥናቱ የተደረሰባቸው ግኝቶች
የጥናት ቡድኑ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት የሚከተሉትን የምርምር ግኝቶች ለማግኘት ችሏል፡፡ የምርምሩ ግኝቶች በፅንሰ ሀሳብ ተዛማጅነት በአራት ክፍሎች የተከፈሉ ሲሆን በእያንዳንዱ ክፍል ስር የምርምር ግኝቶች በአስረጅነት ቀርበዋል፡፡
6.1. የምርጫ አስተዳደር ድክመቶች
በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫ አስፈፃሚዎች የስራ ትጋት እና የስራ ግብረ-ገብነት እንደሚጎላቸው የጥናት ውጤቱ ያመለክታል፡፡ የሚከተሉት የጥናት ግኝቶች ከብዙ በጥቂት እንደ አስረጅነት የቀረቡ ናቸው
በአንድ ምርጫ ጣቢያ የምርጫ አስፈፃሚዎች ባንክ ቤት ሄደዋል በማለት የምርጫ አስፈጻሚ ያልሆነች ህፃን ልጅ ‘’ካርድ አንዴት አንደሚሰጥ አሳይተውኝ ነበር አሁን ጠፋኝ’’ እያለች ስታስተናግድ ነበር፡፡
በ16 ምርጫ ጣቢያዎች ካርድ ያላለቀ ቢሆንም የምርጫ አስተባባሪዎች ጣቢያዎችን ዘግተዋል፤ ከምክንያቶች ውስጥ ደሞዝ አልተከፈለንም የሚለው አንዱ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ለጥበቃ ሰራተኞች ‘’ዛሬ እንደማንገባ ተናገር‘’ የሚል መልዕክትና የምርጫ አስፈፃሚዎች እንደነገሩት እና አብዛኛው የምርጫ አስፈፃሚ ያለ ምንም ምክንያት እንደሚቀሩ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የምርጫ አስፈፃሚዎች በሰዓቱ እንደማይገቡና/አርፍደው ይገቡና አምስት ሰዓት ሳይሞላ መልሰው ዘግተው ይወጣሉ(ቀጨኔ መዳኅኒዓለም ቤ/ክርስቲያን ፊት ለፊት)፤
የምርጫ አስፈፃሚዎች እስከ 8:24 ድረስ ቢሮ እንደማይገቡ የቃለ መጠየቅ ተሳታፊዎች አስረድተዋል(ንፋስ ስልክ ክ/ከተማ፣ ጀሞ)
በአጠቃላይ የቀረቡት ሃሳቦች እንደሚያስረዱት ከሆነ የምርጫ አስፈፃሚዎች የሚጠበቅባቸውን የስራ ኃላፊነት እንዳልተወጡ ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምርጫ አስፈፃሚዎች አመላመል፣ ስለ ምርጫው ያላቸው ግንዛቤ፣ በምርጫው ላይ ገለልተኛ አለመሆናቸው የምርጫ አስፈፃሚዎች ትጋት ማነስ እንደ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡
ዳሩ ግን ይህ ሁሉ ችግር የሚያጠነጥነው ምርጫውን በሚያስተዳድረው በምርጫ ቦርድ ላይ ነው፡፡ ለሚዲያ ፍጆታ ይውል ዘንድ ምርጫ ቦርድ በየጊዜው ህዝቡ ምርጫ ካርድ እንዲወስድ በመገናኛ ብዙኃን ይለፍፋል መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን የተለየ ነው፡፡ መራጮች ምርጫ ካርድ መውሰድ አልቻሉም፡፡ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የመራጮችን የምዝገባ ሂደት ተዘዋውረው ለመገምገም ምርጫ ቦርድ ምቹ ሁኔታን አለመፍጠሩ ችግሩ በዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል፡፡
6.2. የምርጫ ጣቢያ- ነክ ጉዳዬች
A. የምርጫ ጣቢያዎች የምዝገባ ሂደት እና ያሉበት ሁኔታ
ለምሳሌ የቀረቡ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ጣቢያው ያለበት ሁኔታ
1 ብዛት ያላቸው ናቸው በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ተመዝጋቢ እየመጣ የምርጫ አስፈፃሚዎች 1500 መዝግበው የተዘጉ ናቸው (ብዛታቸው 43)
2 አያት ጸበል አካባቢ በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ረዘም ላለ ግዜ 1,500 ሞልቶብናል በማለት ለምዝገባ የሚመጡ ተመዝጋቢዎችን ይመልሳሉ፡፡
3 ጉለሌ ምርጫ ጣቢያ 16/17 በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች በአንድ የምርጫ ጣቢያ ክልል ውስጥ ከአንድ በላይ ምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተዋል
4 ኮልፌ፣ ምርጫ ጣቢያ 11
በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ለብዙ ቀናት የምርጫ አስፈፃሚዎች 1500 ሳይመዘግቡ ዘግተዋል
5 እየሱስ ቁጥር 2 የጋራመኖሪያቤት፤ኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ
ወረዳ 1 ምርጫ ጣቢያ 10 በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ለብዙ ቀናት የምርጫ አስፈፃሚዎች በተጋነነ መልኩ ዘግይተው ወደ ስራ ይገባሉ፤ ከስራም ያለ ስዓቱ ቀድመው ይወጣሉ
ከላይ ባለው ሰንጠረዥ መረዳት እንደሚቻለው በርካታ ቁጥር ያላቸው የምርጫ ጣቢያዎች 1500 የምርጫ ካርድ ሰጥተው የዘጉ ሲሆን በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦች የምርጫ ካርድ እንዳልወሰዱ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ 1500 ሳይመዘግቡ የተዘጉ የምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉም ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምርጫ ጣቢያዎች ያለ ስዓቱ እንደሚዘጉም የጥናት ውጤቱ ያመለክታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአንድ የምርጫ ጣቢያ ክልል ከአንድ በላይ ምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱ እንደነበር የጥናት ቡድኑ በምልከታው አመላቷል፤ይህ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ካወጣው ህግ ጋር የሚፃረር ነው፡፡
ከላይ በሰንጠረዡ ማየት እንደሚቻለው በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ተመዝጋቢ እየመጣ የምርጫ አስፈፃሚዎች 1500 መዝግበው የተዘጉ ናቸው፡፡ ከላይ እንደቀረበው መረጃ 43 የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች እንደተዘጉ ተረጋግጧል፤ ይህ ጥናት 12ፕርሰንት የሚሆነውን የምርጫ ክልል ይወክላል ብንል፤ በጥናቱ ያልተካተቱ የምርጫ ጣቢያዎችን ግምት ውስጥ ካስገባን ወደ 358 የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች 1500 መዝግበው ሊዘጉ እንደሚችሉ ከጥናቱ መረዳት ይቻላል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ አዲስ ከተከፈቱ 32 የምርጫ ጣቢያዎች ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች ብቻ ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ በጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በአንድ የምርጫ ጣቢያ 1500 ብቻ እንዲመዘገብ በሚያዘው የምርጫ ህግ ስሌት ሲታሰብ እንኳን 32 የምርጫ ጣቢያዎች ሙሉ በሙሉ ቢከፈቱ ሊመዘገብ የሚችለው አጠቃላይ የሰዎች ብዛት 48000 ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ቁጥር ደግሞ ካልተመዘገበው የማህበረሰብ ቁጥር አንፃር ሲቃኝ በጣም ትንሽ ቁጥር ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ደንብን ያልተከተሉ እንደነበር የጥናት ቡድኑ አረጋግጧል፡፡ የሚከተለው ሰንጠረዥ ለአስረጅነት የሚሆኑ መረጃዎች ያሳያል፡፡
ተ.ቁ የምርጫ ጣቢያው ስም የምርጫ ጣቢያው ልዩ ባህሪ
1 አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ኮዬ ልማት በፍቅር ከብሎክ 739-762 ኮንዶሚኒየም ምርጫ ጣቢያ 26/27-700 ቤት 3 የሀሰት ምስክር እያቀረቡ የምርጫ ካርድ እንደሚያወጡ ጥቆማ ደርሶናል
2 ቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 12 አባ ሻሜ ምርጫ ጣቢያ ቁማር ቤት አጠገብ ያለ ምርጫ ጣቢያ ነው
3 የካ ክ/ከተማ ወረዳ 3 አስተዳደር የቀበሌ 18 (1) ምርጫ ጣቢያ ሀ ልዩ ቦታ 18 ቀበሌ መዝናኛ ክበብ ምርጫ ጣቢያው መጠጥ ቤት ውስጥ ነው
4 አዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 3 ምርጫ ጣቢያ 14 ጄሪ ኬክ ቤት ሄዳችሁ ውሰዱ የሚል ማስታወቂያ ተለጥፏል
5 49 አደባባይ ምርጫ ጣቢያ ተመዝጋቢ የለም ብለው ካርዶቹን ይዘው ሌላ ቦታ ሄደዋል
ከሰንጠረዡ ለመረዳት እንደሚቻለው የምርጫ አስፈፃሚዎች ተመዝጋቢ የለም ብለው ካርዶቹን ይዘው ሌላ ቦታ እንደሚሄዱ የጥናት ቡድኑ አረጋግጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የምርጫ ካርድ ሊሰጥባቸው በማይችሉ ቦታዎች ላይ ተመዝጋቢዎች ሂደው መወሰድ እንዳለባቸው በማስታወቂያ እንደሚገለፅላቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት ቦታ(መጠጥ/ቁማር ቤት) መሆናቸው ከምርጫ ህጉ ጋር የሚፃረር እንደሆነ በጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምርጫ ካርድ መውሰድ የማይገባቸው(ምናልባት) ከሌላ አካባቢ የመጡ ዜጎች የሀሰት ምስክር በማቅረብ የምርጫ ካርድ እንደሚወስዱ በጥናቱ የተረጋፈጠ ጉዳይ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጥናት ቡድኑ ባደረገው ምልከታ መሰረት አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት አካባቢ ለምርጫ ምዝገባ ለሚመጡ ዜጎች ምቹ እንዳልሆኑ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የሚከተሉት የጥናት ግኝቶች ከብዙ በጥቂት እንደ አስረጅነት የቀረቡ ናቸው፡፡
በግለሰብ መኖሪያ ቤት የተከፈተ የምርጫ ጣቢያ
በተጨማሪም አንድ የምርጫ ጣቢያ ጫት በሚቃምበት አካባቢ የተከበበ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በእንዲህ አይነት ምቹ ባላሆኑ ቦታዎች የተከፈቱ የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ነፃ ሁነው እንዳይንቀሳቀሱ እና የምርጫ ካርድ እንዳይወስዱ ተፅዕኖ እንደሚፈጥሩ ለመገመት አያዳግትም፡፡
B. የምርጫ ጣቢያዎች ተደራሽነት
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከነዋሪው ህዝብ ጋር የማይጣጣሙ እና ቁጥራቸው አነስተኛ እንደነበር ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የሚከተሉት የጥናት ግኝቶች ከብዙ በጥቂት እንደ አስረጅነት የቀረቡ ናቸው
በቦሌ እና በየካ በተለይም በኮንደምኒየሞች ውስጥ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች አነስተኛ ከመሆናቸውም በላይ የቦታ ርቀታቸውም በጣም ሠፊ ሲሆን ከነዋሪዎች ጋር አለመመጣጠን እጅጉን መኖሩን የጥናት ቡድኑ ተመልክቷል
በሌላ ሁኔታ በአራዳ፣ በአዲስ ከተማ እና ልደታ ክፍለ ከተሞች የምርጫ ጣቢያዎች በአንድ ቤት ውስጥ ከአንድ በላይ ምርጫ ጣቢያዎች አነደሚገኙ የጥናት ቡድኑ ተመልክቷል፡፡
የምርጫ ጣቢያዎች በአብዛኛው ምንም አይነት መለያ የሌላቸው ሲሆን የቦታ አቀማመጣቸውም ለመራጮች ምቹና ተደራሽ አለመሆናቸውን ተረጋግጧል፡፡
ቀጨኔ መዳኅኒዓለም ቤ/ክተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ስያሜ የሌለው ምርጫ ጣቢያ ታይቷል፤
ኮንዶሚኒየሞች(ጀሞ፣የካ፣ አባዶ፣አራብሳ፣ኃይሌ ጋርመንት፣ገላን፣ቡልቡላ፣ ቱሉዲምቱ፣ ኮየ ፈቸ) እንዳልተመዘገቡ ቅሬታ አለ
ከላይ እንደተጠቀሰው አብዛኛዎች ኮንዶሚኒየሞች አባውራ እና እማውራ ሲኖራቸው ለነዚህ አባውራዎች እና እማውራዎች የተመደበው የምርጫ ጣቢያ በቂ አለመሆኑ ታይቷል፡፡ ከምርጫው በፊት የህዝብ ቆጠራ አለመካሄዱ ለእንዲህ አይነት ችግሮች ምክንያት ሲሆን የምርጫ ቦርድ ትክክለኛ ግምታዊ ስሌት አለመጠሙ የችግሩን ስፋት አግዝፎታል፤
የምርጫ ቦርድ የምርጫውን ሂደት በተመለከተ ለማህበረሰቡ ተገቢውን መረጃ ማቅረብ የሚጠበቅበት ቢሆንም፣ የመረጃ እጥረት ግን የመራጮችን የምዝገባ ሂደት አወሳስቦታል፤አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎችም እንዳይታወቁ አድርጓታል፡፡
በውስጣዊ ወይም በነባር ክፍለ ከተሞች ውስጥ ብዙ ነዋሪ በሌለበት ቦታ በርካታ ምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን ውጫዊ/ማስፋፊያ በሆኑ ክፍለ ከተሞች ለምሳሌ (በየካ፣ቦሌ፣ አቃቂ) በቂ ምርጫ ጣቢያ እንደሌለ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ በማስፋፊያ ክፍለ ከተሞች ላይ በሚገኙት የምርጫ ጣቢያዎች በፖለቲካ ግፊት ምክንያት በቡድን ከኦሮሚያ ክልል እየመጡ የምርጫ ካርድ ቀድመው ስለወሰዱ በነዚህ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ ማግኘት አልቻሉም፡፡
የጥናቱ የምልከታ ውጤት እንደሚያሳየው የኮንደሚኒየም ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ ለመውሰድ በጣም ሲቸገሩ አጥኝ ቡድኑ ተመልክቷል፤በተለይም ኮታ ሞልቷል ተብለው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲንከራተቱና በስተመጨረሻም አምስት ስድስት ቦታ ደርሰው ተስፋ ቆርጠው የተመለሱ እንዳሉ ለመረዳት ተችሏል፡፡
6.3. የምርጫ ካርድ ከሚወስዱ ግለሰቦች ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዬች
የመራጮነት ካርድ ከሚወስዱ ግለሰቦች ማንነት ጋር በተያያዘ በርካት ችግሮች የታዩ ሲሆን ለአስረጅነት የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በቃለ መጠየቁ የተሳተፈ ግለሰብ የሚከተለውን ብለዋል፡
ከአምቦ/ከሰንዳፋ የመጡ ዜጎች ካርድ ያወጣሉ(ንፋስ ስልክ)የቪዲዬ ማስረጃ
በተጨማሪም ይህን ጉዳዩን አስመልክቶ ሌላው ተሳታፊ እንዲህ ብላለች፡-
ከብሄር ማንነት በተጨማሪ የእምነት ማንነትም የምርጫ ካርድ በመወሰዱ ሂደት አስተዋፅዖ ነበረው፤ የሙስሊም እና የኦሮሞ ማንነት የሌላቸው ዜጎችን አናሰተናግድም እያሉ እነደነበር ከአካባቢው ፖሊስ የተገኘ የድምጽ ሪኮርድ ያሳያል(አባሻሜ የተባለ ጣቢያ፣ቦሌ ቡልቡላ)፣የቪዲዬ ማስረጃ
በተመሳሳይ ሁኔታ በጥናቱ የተሳተፉ አካላት የሚከተሉትን ብለዋል፡
የምርጫ ካርድ የሚሰጡ መዝጋቢዎች ‘’አማርኛ አንችልም በኦሮምኛ አናግሩን’’ በማለት አማርኛ መናገር የማይችሉትን ካርድ ሳይሰጡ መልሰዋቸዋል(ጎሮ በተባለ ቦታ)፣
ሌላው የክልል መታዎቂያ አንቀበልም የሚሉ ምርጫ ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ የኦሮሚያ መታወቂያ የያዙ አየተጠሩ እንደሚሰጣቸው ለማረጋገጥ ተችሏል፤ መዝጋቢዎች ከብሄር ማንነት ጋር በተያያዘ መታወቂያ እያዩ የአማራ ክልል መታወቂያ ከሆነ ይመልሳሉ፣የኦሮሚያ ክልል መታወቂያ ከሆነ ደግሞ የምርጫ ካርድ ይሰጣሉ(መብራት ኃይል አካባቢ፤አያት ጸበል ኮንዶሚኒየም)፣
በሶስት ምስክር የምርጫ ካርድ አንሰጥም ብለው ተመዝጋቢ አባረዋል(መብራት ኃይል አካባቢ)፣
መዝጋቢዎች ካርድ ጨርሠው፣ በር ዘግተው የስም ዝርዝር እያዩ ምርጫ ካርድ እያዘጋጁ እንደነበር የጥናት ቡድኑ ተመልክቷል(ጣፎ ኮንደሚኒየም 3ኛ በር)፣
ጣቢያዎች ዝግ በሆኑበት በአርበኞች በዓል የምርጫ ጣቢያውን ከፍተው ኦሮምኛ ተናጋሪ የሆኑ ግለሰቦችን ብቻ ሲያስተናግዱ እንደነበር በምልከታ ሂደቱ ለመረዳት ተችሏል (ቦሌ አራብሳ ቤቶች ልማት ፕሮጄክት ግቢ)፤
እንደ ጥናቱ ተሳታፊዎች ገለፃ የምርጫ ካርድ የሚታደለው የዜጎችን ማንነት መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሆነ ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡
6.4. መራጮች የምርጫ ካርድ መወሰድ አለመቻላቸው
የጥናት ቡድኑ ባደረጋቸው ቃለ-መጠይቅ አብዛኛው ማህበረሰብ የምርጫ ካርድ እንዳልወሰደ ለመረዳት ተችሏል፡፡ እንደ አስረጅነት የቀረቡ የጥናት ግኝቶችን እንመልከት
አራት አምስት ቀናት ተመላልሰን ካርድ የለም ተባልን፤ የምርጫ አስፈሚዎች አስር ስዓት ላይ ዘግተው ይወጣሉ(ምርጫ ጣቢያ 14)፣
ብዙ ሰው የምርጫ ካርድ አልወሰደም፤ ሂደው አጣን ብለው ሲመለሱ አያለሁ(ምርጫ ጣቢያ አያት ቁጥር አንድ)፣
አንዳንድ ግለሰቦች በግላቸው በርካታ የምርጫ ካርድ እንደሚወስዱ ታውኳል፤
ዜጎች የክፍለ-ሀገር መታወቂያ ይዘው፤ ከስድስት ዓመት በላይ አዲስ አበባ እየኖሩ፣አስመስክረው የምርጫ ካርድ ማውጣት አልቻሉም(አያት)
ከላይ ከቀረቡት የቃለ መጠይቅ ምላሾች መረዳት እነደሚቻለው ዜጎች የምርጫ ካርድ ለመወሰድ እንዳልቻሉ ለመረዳት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች በርካታ የምርጫ ካርዶች ያላግባብ ማውጣታቸው፣ ከአጎራባች የኦሮሚያ ወረዳዎች እየመጡ ሰዎች ካርድ መወሰዳቸው፣ የምርጫ ቦርድ ከነዋሪዎች ጋር ተመጣጣኝነት ያለው የምርጫ ጣቢያዎችን አለመክፈቱ፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች የስራ ትጋት ማነስ ለተፈጠሩ ችግሮች መንስኤዎች እንደሆኑ ለመረዳት ይቻላል፡፡
7. ማጠቃለያ እና መደምደሚያ
የጥናቱ አላማ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ (pre-election process) አካል የሆነውን የመራጮች ምዛገባ ሂደት (voter registration) ከነፃና ፍትሀዊ ምርጫ መርሆዎች አኳያ ምን ያህል ይጣጣማል የሚለውን ጉዳይ በጥናት ማረጋገጥ ሲሆን በመራጮች ምዝገባ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን፣ የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት ሁኔታ እና አጠቃላይ የቅድመ ምርጫውን ሂደት የሚዳስስ ጥናት ነው፡፡
ጥናቱ ዓይነታዊ (Qualitative) የምርምር ዘዴ የተጠቀመ ሲሆን ጥናቱ የሁሉንም ክፍለከተሞች አደረጃጀት ያማከለ በመሆኑ የስብጥር ናሙና (stratified sampling) በመጠቀም ክፍለ ከተሞች በሁለት ክፍል ማለትም ውስጣዊ (inner) እና ውጫዊ (Peripherian) ደረጃ በሚል እንዲከፈሉ አድርጓል፡፡የጥናት ቡድኑ በቀጥታ በአካል በመገኘት ሁኔታዎቹን የመረመረ ሲሆን የተለያዩ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን ተጠቅሟል፡፡ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች ምልከታ እና በምስል መረጃዎችን(ቪዲዮዎች) የተደገፈ ቃለ መጠይቅ ሲሆን በምርጫ ጣቢያወች ላይ የተቀመጡ ምልክቶችና ፅሁፎች በጥናቱ ትንተና ያልተካተቱ ማስረጃዎችም በአባሪነት ቀርበዋል፡፡ የሚከተሉት ግኝቶች የጥናቱ ዋና ዋና መደምደሚያዎች ናቸው፡፡
• የምርጫ አስፈፃሚዎች የሚጠበቅባቸውን የስራ ኃላፊነት እንዳልተወጡ ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምርጫ አስፈፃሚዎች አመላመል፣ ስለ ምርጫው ያላቸው ግንዛቤ፣ በምርጫው ላይ ገለልተኛ አለመሆናቸው የምርጫ አስፈፃሚዎች ትጋት ማነስ እንደ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ዳሩ ግን ይህ ሁሉ ችግር የሚያጠነጥነው ምርጫውን በሚያስተዳድረው በምርጫ ቦርድ ላይ ነው፡፡ ለሚዲያ ፍጆታ ይውል ዘንድ ምርጫ ቦርድ በየጊዜው ህዝቡ ምርጫ ካርድ እንዲወስድ በመገናኛ ብዙኃን ይለፍፋል መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን የተለየ ነው፡፡ መራጮች ምርጫ ካርድ መውሰድ አልቻሉም፡፡
• በርካታ ቁጥር ያላቸው የምርጫ ጣቢያዎች 1500 የምርጫ ካርድ ሰጥተው የዘጉ ሲሆን በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦች የምርጫ ካርድ እንዳልወሰዱ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ 1500 ሳይመዘግቡ የተዘጉ የምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉም ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምርጫ ጣቢያዎች ያለ ስዓቱ እንደሚዘጉም የጥናት ውጤቱ ያመለክታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአንድ የምርጫ ጣቢያ ክልል ከአንድ በላይ ምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱ እንደነበር የጥናት ቡድኑ በምልከታው አመላክቷል፤ይህ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ካወጣው ህግ ጋር የሚፃረር ነው፡፡
• የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት ቦታ(መጠጥ/ቁማር ቤት) መሆናቸው ከምርጫ ህጉ ጋር የሚፃረር እንደሆነ በጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡
• በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከነዋሪው ህዝብ ጋር የማይጣጣሙ እና ቁጥራቸው አነስተኛ እንደነበር ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በውስጣዊ ወይም በነባር ክፍለ ከተሞች ውስጥ ብዙ ነዋሪ በሌለበት ቦታ በርካታ ምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን ውጫዊ/ማስፋፊያ በሆኑ ክፍለ ከተሞች በተለይ በኮነደሚኒየሞች የሚገኙ ዜጎች ለምሳሌ (በየካ፣ቦሌ፣ አቃቂ) በቂ ምርጫ ጣቢያ እንደሌለ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ በማስፋፊያ ክፍለ ከተሞች ላይ በሚገኙት የምርጫ ጣቢያዎች በፖለቲካ ግፊት ምክንያት በቡድን ከኦሮሚያ ክልል እየመጡ የምርጫ ካርድ ቀድመው ስለወሰዱ በነዚህ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ ማግኘት አልቻሉም፡፡
• ከብሄር እና የእምነት ማንነትም ጋር በተያያዘ የምርጫ ካርድ እንደሚታደል ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ መራጩ ህዝብ በማንነቱ እየተለየ የምርጫ ካርድ እንደሚታደል ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምርጫ ካርድ መውሰድ የማይገባቸው(ምናልባት) ከሌላ አካባቢ የመጡ ዜጎች የሀሰት ምስክር በማቅረብ የምርጫ ካርድ እንደሚወስዱ በጥናቱ የተረጋፈጠ ጉዳይ ነው፡፡ የምርጫ ሂደቱ ሁሉን አቀፍ እና እኩል አሳታፊ መሆን እንዳለበት የተቀመጠ ቢሆንም ከላይ እንደተመለከትነው የምርጫ ጣቢያዎች የአሰራር ሁኔታ ከዚህ መርህ በተቃራኒ መልኩ እየሰሩ መሆኑን መገንዘብ እንችላለን፡፡
• አንዳንድ ሰዎች በርካታ የምርጫ ካርዶች ያላግባብ ማውጣታቸው፣ ከአጎራባች የኦሮሚያ ወረዳዎች እየመጡ ሰዎች ካርድ መወሰዳቸው፣ የምርጫ ቦርድ ከነዋሪዎች ጋር ተመጣጣኝነት ያለው የምርጫ ጣቢያዎችን አለመክፈቱ የችግሮች መንስኤዎች እንደሆኑ ለመረዳት ይቻላል፡፡
• የምርጫ ቦርድ አቋቋምኳቸው ያላቸው ንኡስ ጣቢያዎች ግልጽ አድራሻ አለመኖራቸው ፣በፍለጋ ቦታዎች አለመገኘታቸው፣ በአንድ ቦታ ላይ በተለይም በአንድ ቤት በርካታ ጣቢያዎች መገኘት፣በተከለከሉ ቦታዎች ማለትም በመጠጥ ቤቶች፣ በግለሰብ መኖሪያ ቤቶች፣ በጫት ቤቶች ላይ ምርጫ ጣቢያዎችን መክፈት ከምርጫ ህጉ በተቃራኒ ያሉ አሰራሮች እንደሆኑ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡
• ከላይ ከተዘረዘሩት ግኝቶች አንጻር የ6ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ከቅድመ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሂደት አንፃር ሲፈተሸ ነፃና ፍትሀዊነት የሚጎድለው፤ የቅድመ ምርጫ መራጮች ምዝገባ አንፃር መርሆዎች ያልተከተለ እና በበርካታ ችግሮች የተተበተበ እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል፡፡
• ምንም እንኳን እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቢኖሩም ከህዝባችን ጋር በመሆን የምርጫውን ሂደት በከፍተኛ ትኩረት በመከታተል የምርጫ ሂደቱ ፍትሀዊ እንዲሆን ትግላችንን እንቀጥላለን፡፡
8. የመፍትሄ ሃሳብ
ከቀረበው ዝርዝር ጥናት አንጻር ጥናቱ የሚከተሉትን የመፍትሄ ሀሳቦች ያቀርባል፡፡
• የምርጫ ጣቢያዎችን ከማብዛት ይልቅ በአንድ የምርጫ ጣቢያ 1500 የምርጫ ካርድ ብቻ እንዲመዘግብ የተቀመጠው ቁጥር ተሰርዞ የቁጥሩ ወሰን ሊጨምር ይገባል፤
• የምርጫ ካርድ ያልወሰዱ ዜጎች ካርድ ያገኙ ዘንድ የምርጮች የምዝገባ ካርድ ማውጫ ጊዜ መራዘም እንዳለበት እንጠይቃለን፤
• በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ያልሆኑ ተመዝጋቢዎች በርካታ የምርጫ ካርድ ስለወሰዱ ምርጫ ቦርድ ይህንን ጉዳይ አጣርቶ እርምጃ እንዲወስድ እናሳንባለን፤
• በማስፋፊያ ክፍለ ከተሞች ውስጥ የተካሄደው የምዝገባ ሂደት በርካታ ችግሮች ስላሉበት የምርጫ ምዝገባ ሂደቱ በምርጫ ቦርድ እንዲጣራ እንጠይቃለን፤
• የመራጮች ምዝገባ ሂደት ግልፅነት ስለሚጎድለው እና በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ስለሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ ታዛቢዎች የምዝገባ ሂደቱን እንዲያጣሩ፤
• የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት ቦታ በምርጫ ህጉ መሰረት እንዲሆን ምክረ-ሀሳብ ማቅረብ እንወዳለን፤
• የምርጫ አስፈፃሚዎች በግብረ-ገብነት የታነፁ፤ገለልተኛ የሆኑ እና የስራ ትጋት ያላቸው ዜጎች እንዲሆኑ ማሳወቅ እንወዳለን፡፡
ከባልደራስ ሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ሰጪ ቡድን የተሰጠ
ሀገርን የማዳን ጥሪ (Balderas Support in North America )
ለብዙ ሺህ አመታት በአባቶቻችን መስዋዕትነት የቆየችው ሀገራችን
ዐይናችን እያየ እጃችን ላይ ሳትፈርስ ሁላችንም በአንድ ላይ ልንቆም ይገባል!
የተከበራችሁ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣
እኛ ኢትዮጵያዊያን የዛሬ ሦስት ዓመት በአገራችን የተካሄደው ለውጥ በልባችን ውስጥ ሰንቆት የነበረው ተስፋ ከህሊናችን በቀላሉ የሚጠፋ አይደለም፡፡ እንዲህ እንደዛሬው ተስፋችን የህልም እንጀራ ሆኖ መቅረቱ እውን ሳይሆን፤ ያንን ታላቅ ተስፋ በተለያየ ጎራ የነበርን ሁሉ ለሀገራችን ካለን ቀናኢ ምኞት እና ጉጉት የተነሳ በአንድነት “ሆ!” ብለን ተቋድሰናል፡፡ የተሰጠን ተስፋ መሬት ላይ ወርዶ ፍሬውን እናይ ዘንድም እንደየአቅማችን ደክመናል፡፡
በእርግጥ ብዙዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ባዶ ቃል ጋር በፍቅር ወድቀው የጫጉላ ሽርሽር ላይ በሚምነሸነሹበት በለውጡ መጀመሪያ ወቅት ሁሉም በተቀደደለት ቦይ ፈስሶ ነበር ማለች አይቻልም፡፡ ይልቁንም ነገሮችን አካሄድ በጥንቃቄ መርምረው የኦሮሙማውን መንግሥት የቃልና የተግባር ግጭት ነቅሶ በማጋለጥ በለጋነቱ እንዲታረም ያካልሆነ ግን ታላቅ አገራዊ ጥፋት እንደሚከተል በማለዳ የማንቂያ ደውል የደወሉ ብልሆች አልጠፉም፡፡ ለዚህም የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት፣ አቶ እስክንድር ነጋ ግምባር-ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ደውሉን ሰምተን ተገቢውን ምላሽ የሰጠን በእውኑ ስንቶቻችን ነን? ያ ገና በማለዳ ችግሩ ሥር ሳይሰድ የተሰጠን ወርቃማ ዕድል እንደ ዋዛ አምልጦናል፡፡ ከዚያም በኋላ በተለያየ ጊዜ ለውጡ አቅጣጫውን መሳቱን ያመላከቱ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ቢኖሩም ጆሮ ሳይሰጣቸው ታልፈዋል፡፡ በግለሰብ ስብዕና ግንባታ እና በባዶ የተስፋ ቃል ላይ ስናተኩር ሀገራዊ ህልውናን ችላ አልነው፡፡ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ይመጣሉ፣ ይተካሉ፡፡ ሀገራችን ግን ከእኛ በፊት ነበረች፤ ከእኛም በኋላ ትቀጥላለች፤ መተኪያም የላትም፡፡
አንኳር የሆኑ እና የሚያመሳስሉንን ጉዳዮች ትተን ጊዜያዊ በሆኑ በጥቃቅን ልዩነቶቻችን ላይ ስንመሰጥ የህወሀት/ኢህአዴግ የበኩር ልጅ የሆነው ኦህዴድ/ብልጽግና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የጥፋት መዋቅሩን
በመዘርጋት መጠነ-ሰፊ የዘር ጭፍጨፋውን በነፃነት እንዲያካሄድ መንገዱን አመቻቸንለት፡፡
አሁን ከአንድ መራር እውነት ጋር መጋፈጥ ግድ ብሎናል፡፡ ያ ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት የተሰጠን የተስፋ ስንቅ መክኖ በታላቅ ሀገራዊ ውርደት፣ ሀዘን እና ተስፋ መቁረጥ ተተክቷል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቁ ጥያቄ ብልጽግና ሳይሆን ህልውና ነው፡፡ እድገት ሳይሆን ሰላም፣ መረጋገት እና ደህንነት ነው፡፡
ባለፉት ሁለት ቀናት በሰሜን ሸዋ መንግስት-መር በሚመስል መንገድ በተፈፀመው ጭፍጨፋ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ ጥልቅ ሀዘን የተሰማው ሲሆን በተሰማን ጥልቅ ሀዘን ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ምንም አይነት የምርጫ ቅስቀሳ ፕሮግራም እንደማይኖር ማሳወቅ እንወዳለን፡፡ በሞት ለተለዩን ወገኖቻችን ፈጣሪ እረፍትን እንዲሰጣቸው እየተመኘን፤ ለተጎዱ ቤተሰቦች መፅናናትን እንመኛለን፡፡
በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ፓርቲ አባል ዕጩ በአቶ በሪሁን አስፈራው ላይ በመተከል ዞን በለስ ልዩ ቦታው ካርባር የተደረገውን የግድያ ወንጀል የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ እጅጉን እንደሚያወግዘው እየገለፀ ለሟች ቤተሰብ እና ለባልደርቦቹ መፅናናትን ይመኛል፡፡