ባልደራስ ለአዲስ አባባ ባዘጋጀው ማኒፌስቶ ዙሪያ ከእጩዎች ጋር ምክክር አደረገ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ ለፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የተወከሉ እጩዎች ፤ለአዲስ አበባ በተዘጋጀው የምርጫ ማኔፌስቶ መርሐግብር ወይም አብይ ጉዳዮችን አፈፃፀም በተመለከተ ፤ውይይት እና ምክክር ።
Balderas Latest News
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ ለፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የተወከሉ እጩዎች ፤ለአዲስ አበባ በተዘጋጀው የምርጫ ማኔፌስቶ መርሐግብር ወይም አብይ ጉዳዮችን አፈፃፀም በተመለከተ ፤ውይይት እና ምክክር ።
1. ኢ/ር ጌታነህ ባልቻ ምርጫ ክልል 1እና 9
2. ልጅ ጌታቸው ተስፋዬ ምርጫ ክልል 2/14
3. አርኪቴክት አለሙ ጌታቸው ምርጫ ክልል 3
4. ኢ/ር ቢኒያም መለስካቸው ምርጫ ክልል 4
5. ወ/ሮ ፅጌረዳ ቀለመወርቅ ምርጫ ክልል 5
6. አቶ ፀጋዬ እንግዳ ምርጫ ክልል 6
7. አቶ ዘለሌ ፀጋስላሴ ምርጫ ክልል 7
8. ወ/ት ዘቢባ በኢብራሂም ምርጫ ክልል 8
9. አቶ አዲሱ ሀረገውይን ምርጫ ክልል 10
10. ኢ/ር ሰለሞን ተሰማ ምርጫ ክልል 11
11. ወ/ሮ መሶበወርቅ ቅጣው ምርጫ ክልል 12/13
12. ዶ/ር ንጋት አስፋው ምርጫ ክልል 15
13. ወ/ት አፀደ አሰፋ ምርጫ ክልል 16
14. ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ምርጫ ክልል 17
15. ዶ/ር ሰለሞን ገዛኸኝ ምርጫ ክልል 18
16. ኢ/ር አለማየሁ ንጋቱ ምርጫ ክልል 19
17. አቶ ገለታው ዘለቀ ምርጫ ክልል 20
18. ኢ/ር አንተነህ በለው ምርጫ ክልል 21/22
19. ዶ/ር ብርሃኑ ዘለቀ ምርጫ ክልል 23
20. ዶ/ር ወንድአጥር ንጋቱ ምርጫ ክልል 24
21. ዶ/ር ቴወድሮስ ኃ/ማርያም ምርጫ ክልል 25
22. ዶ/ር አለማየሁ ጎዳና ምርጫ ክልል 26/27
23. አቶ አምሃ ዳኘው ምርጫ ክልል 28
በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በነገው ዕለት መጋቢት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ከጠዋት 2:30 ሰዓት ጀምሮ በአዚማን ሆቴል ” አዲስ አበባ ትላንት እና ዛሬ ” አስመልክቶ በተጋባዥ እንግዶች ጥናታዊ ጽሑፍ የሚቀርብ ሲሆን ፤ በእለቱ ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች እና አባላት ጋር ውይይት ይካሄዳል ።
ዝግጅቱ ለሁሉም የብዙሃን መገናኛ ክፍት በመሆኑ ባልደራስ ጥሪውን ያቀርባል።
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ዛሬ መጋቢት 15 ቀን የከፍተኛው ፍርድ ቤት ችሎት ቀርበዋል። ፍርድ ቤቱ ብይን መስጠት የሚችለው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ካወቀ በኋላ እንደሆነ በመጥቀስ ለሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚዳኘው የይግባኝ ችሎት የፊታች መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ስድስት ኪሎ በሚገኘው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ይካሄዳል።
የባልደራስ ፕሬዚደንት አቶ እስክንድር ነጋ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ የጠየቀበት ሰነድ ግልባጭ እንዲሰጣቸው በዛሬው ችሎት ቢይቁም አልተሰጣቸውም። ዐቃቤ ሕግ በሰዓቱ ሰነዱን አለመያዙን ገልፆ በሌላ ጊዜ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል።
“አሁንም እድሎች ሙሉ በሙሉ አላለፉም፤ አፋጣኝ ፍትሕ ስጡን እና ከእስር ቤት ወጥተን ለምርጫው አስተዋፅኦ ማድረግ እንፈልጋለን” ሲሉ አቶ እስክንድር ጠይቀዋል።
የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኞች በበኩላቸው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አፋጣኝ ምላሽ ከሰጠ እነርሱም ፈጣን ብይን እንደሚሰጡ ገልፀዋል።
አቶ ስንታየሁ ቸኮል ወቅቱ ዐብይ ፆም የሚጾምበት መሆኑን ጠቅሰው የምልኮ ስፍራ ወዳለበት የእስር ቤቱ ክፍል (ዞን) አራቱንም የህሊና እስረኞች ወህኒ ቤቱ እንዲያዘዋውራቸው ጠይቀዋል። ይህ ካልሆነም በያሉበት የአምልኮ ስፍራ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱ ወህኒ ቤቱን ያዝዝ ዘንድ አሳስበዋል። እምነታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በምትፈቅደው መሰረት በፀበል ቅዱስ መፈወስ እንደሚፈልጉ የጠቆሙት አቶ ስንታየሁ ፀበል እንዲገባላቸውም ጠይቀዋል። ከዚህ በፊት ቤተሰቦቻቸው ያመጡትን ፀበል ወህኒ ቤቱ አላስገባ ብሎ መልሶታል።
ወ/ሮ አስቴር ስዩም በበኩላቸው “የመደመር መንገድ የተባለው የጠቅላይ ሚንስትሩ መፅሐፍ እስር ቤት ውስጥ እየገባ ነው። ‘ሀገር ስታምጥ’ የተሰኘውን የእኔን መፅሐፍ ግን ማስገባት አልቻልኩም። ተከልክያለሁ። ለምን?” ሲሉ ጠይቀዋል።
የባልደራስ ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋ ከቃሊቲ
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ እና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ፤ በዛሬው ዕለት መጪው ሃገር አቀፍ ምርጫ በትብብር ለመስራት መስማማታችን ለህዝብ ይፋ ሆኗል ። ይህ ትብብር የአብን እና የባልደራስ ብቻ እንዳይሆን ፥ ባልደራስ ለባለፉቱ ወራት ይፋዊ ጥሪ ለፓርቲዎች በማቅረቡ ፤ በአዲስ አበባ ላይ የተጋረጠውን አደገኛ ችግር፤ በእኩል ለመጋፈጥ እና በዲሞክራስያዊ የምርጫ ሥርዓት፣ ለህዝብ ጠንካራ ተመራጭ ትብብር ለመፍጠር የተቻለንን ጥረት አድርገናል።
አሁንም ቢሆን አዲስ አበባን ለመታደግ ቁርጠኛ ፍላጎት ካላቸው ፣ በተለይ የልዩ ጥቅም ፍላጎት የማይቀበሉ ፣ አዲስ አበባ የኗሪዎች መሆኗን እና የኢትዮጵያዊያን መናገሻ ከተማ እንደሆነች በጽኑ ከሚያምኑ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ስለ አዲስ አበባ ለመምከር እና በጋራ ለመስራት ፤ ባልደራስ ከግማሽ መንገድ በላይ በመሄድ ከዚህ ቀደም ላቀረበው የአብረን እንስራ የትብብር ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል ።
በዛሬው ዕለት ፤የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ እና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ፓርቲ በጋራ ለመስራት ይፋዊ የትብብር ስምምነት መገለጡ ፤ትብብሩ ለኢትዮጵያ ተስፋ ፤ ለአዲስ አበባ የህልውና ጉዳይ ነው ! ይህ ትብብር እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ የባልደራስ እና የአብን ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት እንዲሁም ፣ ይህ ትብብር እዚህ ደረጃ እንዲደርስ በአገር ውስጥ እና በውጪ የሚገኙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ላሳዩት ድጋፍ ፤ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ !
በተለይ በመጪው ምርጫ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ ፣ ለአዲስ አበባ የሚበጀውን ለመምረጥ የተግባር ሰው መሆን ግድ ነው።
አዲስ አበባን ማዳን ኢትዮጵያ ማዳን ነው !
ትብብር ለእውነተኛ ዴሞክራሲ !!
ድል ለዲሞክራሲ !!!
በግፍ የታሰሩት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ከፍተኛ አመራሮች አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮል በሚኖሩበት ጠባብ የእስር ቤት ክፍል ውስጥ የት.ሕ.ነ.ግ. አማፂያን ቡድን መሪዎች አቶ ስብሃት ነጋ እና ዶ/ር አብርሀም ተከስተ ተጨምረዋል። የአማፂው መሪዎች በቁጥጥር ስር ከዋሉ ጀምሮ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል ውስጥ የቆዩ ሲሆን ዛሬ ወደ ቃሊቲ ወህኒ ቤት ተወስደዋል። ከሌሎች ክፍሎች ተመርጦ እነ እስክንድር ያሉበት ጠባብ ክፍል ውስጥ እንዲያርፉም ተደርጓል።
ይህም የተደረገው በመካከላቸው ያለውን የአመለካከት ልዩነት ተጠቅመው እርስ በእርስ ለትንኮሳ እንዲገባበዙ ታቅዶ እነደሆነ እነ እስክንድር ገልፀዋል። “ሌሎች ክፍሎች አሉ። እኛን ወደዚያ ቀይሩን፤ ይህ ካልሆነም እነርሱን ወደ ሌላ ክፍል ውሰዱልን” የሚል ጥያቄ ለወህኒ ቤቱ አገዛዝ እንዳቀረቡ የገለፁት የህሊና እስረኞች ‘ከበላይ አካል ታዝዘናል’ በሚል ጥያቄያቸው ተቀባይነት አለማግኘቱን ገልፀዋል።
ኦሕዴድ/ብልፅግና እንደሚፈልገው ፈፅሞ ለትንኮሳ እና ለብሽሽቅ እንደማይጋበዙም ጠቁመዋል። ይህንን ለእስር ቤቱ አገዛዝ ጨምረው አስረድተዋል።
መንግሥት ሓላፊነት ተሰምቶት እስረኞች አዕምሯቸው ሳይረበሽ እንዲኖሩ ያደርግ ዘንድ ባልደራስ ያሳስባል። ይህንን ሳያደሮግ ቢቀር ግን በእስረኞች ላይ ለሚደርስ ማንኛውም አይነት ችግር በሕዝብ፣ በታሪክና በሕግ ፊት ተጠያቂ መሆኑን በድጋሜ ሊያጤነው ይገባል።
ዛሬም ድል ለዴሞክራሲ!
በድብቅ ካልሆነ ምስክሮችን አላቀርብም በማለት ፤ ዐቃቤ ሕግ የእግድ ደብዳቤ ይዞ ቀረበ !
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አስቀድሞ በሰጠው ቀጠሮ መሰረት ፤ በዛሬው እለት የካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ዐቃቤ ህግ ምስክሮችን አቅርቦ እንዲያስመሰክር ትዕዛዝ የተሰጠበት ቀን ነው ።
ይሁን እንጂ ዐቃቤ ህግ ከጠቅላይ ፍ/ቤት የእግድ ደብዳቤ በማቅረቡ ፤ ከፍተኛ ፍ/ቤት በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት በዛሬው እለት ዐቃቤ ህግ ምስክሮችን አላቀረበም ። ከዚህ ቀደም ምስክሮችን ከመጋረጃ ጀርባ በድብቅ ማቅረብ አለብኝ በማለት ዐቃቤ ህግ አቅርቦት የነበረውን ጥያቄ ፤ በዚሁ ፍ/ቤት ውድቅ የተደረገ ሲሆን ፣ በጉዳዩ ላይ ይግባኝ የተባለው ጠቅ/ፍርድ ቤት የከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔ በማጽናት ምስክሮች በግላጭ ይቀረቡ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል ።
ይሁን እንጂ ፤ በከፍተኛ ፍ/ቤት እንዲሁም በጠቅ/ፍቤት ውሳኔ የተሰጠበትን የምስክሮች አቀራረብ በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ሰበር ሰሚ ችሎት ዐቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቋል ።ሰበር ሰሚ የቀረበለትን ይግባኝ ተመልከቱ ፤ ጠቅላይ ፍ/ቤት ጉዳዩን ግራና ቀኝ አከራክሩ ይወስን በማለት ፤ መልሶ ወደ ጠቅላይ ፍ/ቤት መርቶታል።
ጠቅላይ ፍ/ቤት ከዚህ ቀደም ምስክሮች በግልጽ ችሎት ይቅረቡ በማለት የወሰነውን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው ፤ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የዐቃቤ ሕግ
ምስክሮች እንዳይሰሙ የእግድ ትዕዛዝ አውጥቷል ።
በዚህም መሰረት ፤ ዛሬ በከፍተኛ ፍ/ቤት ቀጠሮ ተሰጥቶት የነበረውን የዐቃቤ ህግ ግልጽ የምስክሮች አሰማም ሂደት
አልተካሄደም ። ይህም በመሆኑ የፊታችን የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጠቅላይ ፍ/ቤት እግድ ባወጣበት የምስክሮች አቀራረብ ላይ ቀጠሮ ተሰጥቷል ።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት ፤ እኛ በቀጠረንው መሰረት ችሎቱ እንዳይቀጥል እግድ መጥቶብናል ። የጠቅላይ ፍ/ቤት የእግድ ትዕዛዝ ውሳኔ ተከትለን ችሎቱ እንዲቀጥል ፤ ለመጋቢት 15 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተናቸዋል ብለዋል ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በከፍተኛ የኩላሊት ህመም እየተሰቃየ የሚገኘው አቶ ስንታየሁ ቸኮል ፤ ተገቢውን ህክምና ለማግኘት በተደጋጋሚ ለፍ/ቤት ያቀረበው አቤቱታ ምንም ምላሻ አለማግኘቱን አስመልክቶ፤ በዛሬው እለት በድጋሚ ለፍ/ቤት አቤቱታ አቅርቧል ።
ይሁን እንጂ ፍ/ቤቱ የማረሚያ ቤት አስተዳደር በቀረበው የህክምና ጥያቄ ላይ አስተያየት ይስጥበት በማለት ምላሽ ሰጥቷል ። በህመም ላይ የሚገኘው ስንታየሁ ቸኮሎ ” እኔ በከባድ ህመም እየተሰቃየሁ እንዴት ሆኖ ነው ማረሚያ ቤት በእኔ ህመም አስተያየት ይስጥበት የሚባለው ” በማለት ለፍ/ቤቱ ምላሽ ሰጥቷል ። ፍ/ቤቱ ግን ማረሚያ ቤት አስተያየት ይስጥበት በማለት፤ ጉዳዩ በቀጠሮ የሚታይ ሳይሆን በፍ/ቤት ቢሮ በደብዳቤ ልውውጥ እንዲሆን ትዕዛዝ ሰጥቷል ።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በዓለም ዙሪያ ለሚገኝ ጥቁር ሕዝብና በዓሉን ለሚያከብሩ የሰው ልጆች ሁሉ መልካም የአድዋ ድል በዓል እንዲሆን ይመኛል። የዘንድሮውን በዓል የምናከብረው እጅ ከፈንጅ ከያዝነው መንግሥታዊው የታሪክ ሌባ ቡድን ጋር ተፋጠን ነው። ይህ ቡድን ንጉሰ ነገስት እምዬ ምኒልክን እና ብርሐን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱን ከአድዋ ታሪክ ለመሰረዝ እየተፍጨረጨረ ይገኛል። በምትኩ መንግሥታዊ ሥልጣኑን ተጠቅሞ የራሱን ልብ ወለድ ከመፃፍ አላወተተም።
ስለዚህ ባልደራስ የታሪክ ዝርፊያውን የሚያስቆም ታሪክ አድን ግብረ ሃይል እንዲቋቋም ለሕዝብ በተለይም ለከፍተኛ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ ለምሁራን፣ ለሲቪክ ድርጅቶች፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎችና ለታሪክ ባለሙያዎች ሀገራዊ ጥሪውን ያቀርባል።
ሕዝባችን የታሪክ ዝርፊያውን በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃኑ እንዳሳየው ሁሉ አምርሮ ሊቃወመው ይገባል። ጀግኖች አርበኞቻችን ይዘውት የዘመቱትን ንፁህ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቃላማ እና ድሉን ብሎም ታሪኩን የሚወክሉ አልባሳትን በመልበስ በአድዋ ዘማቹ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን እና በእምዬ ምኒልክ ሀውልት ዙሪያ በዓሉን እንዲያከብር ሀገራዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ሰንደቃላማ እና ከላይ የተጠቀሱትን አልባሳት ማግኘት የማትችሉ ብሎም በተጠቀሰው ቦታ መገኘት የማትችሉ በያላችሁበት በቻላችሁት መጠን እና ሁኔታ በዓሉን ታከብሩ ዘንድ ባልደራስ ያሳስባል።
አድዋን በማስመልከት በኦሕዴድ/ብልፅግና የተጀመሩ ማናቸውም ፕሮጀክቶች የታሪክ ዝርፊያው አካል እንደሆኑ እናምናለን። በመሆኑም ጅምሮቹ እንዲቋረጡ ባልደራስ ይጠይቃል።
በተለይም ከአመት በፊት በአቶ ታከለ ኡማ መሪነት በአዲስ አበባ የተጀመረው የአድዋ ሙዚየም ግንባታ ፕሮጀክት አሁኑኑ ሊቋረጥ ይገባል። ምክንያቱም አላማው የታሪክ ነጠቃ እና ዳግማዊ ምኒልክን ከአድዋ የድል ታሪክ ማሸሽ ነው። ይህ ደግሞ ከሀዲነት ነው። ለዚህም ነው የሙዚየሙን ግንባታ ባልደራስ ገና ከጅምሩ ከአንድ አመት በፊት የተቃወመው። ይህ ትውልድ መንግሥታዊ ክህደትን በመቃወም ታሪክ እንዲያስቀጥል ፓርቲያችን ሀገራዊ ጥሪውን ያቀርባል።
የግንባታው መሰረት ገና መሬቱን ሳይለቅ የዘንድሮው የድል በዓል ማክበሪያ አርማ ተብሎ እምዬ ምኒልክን ያገለለ አዲስ የአድዋ መገለጫ ምልክት ወጥቷል። የሙዚየሙን ግንባታ የምንቃወመው በሚከተሉት አበይት ምክንያቶች ነው፦
፩. ከመርህ አንፃር እንዲህ አይነት ሙዚየም መገንባት ያለበት በዴሞክራሲያዊ ሂደት በሕዝብ በተመረጠ መስተዳድር በመሆኑ ነው።
፪. ገንቢው ቡድንና ማህበራዊ መሰረቱ የአድዋ ድልን በበጎ የሚረዱ አለመሆናቸው፤ ከተማውን የተቆጣጠረውና ሙዚየሙን የሚገነባው ሃይል የአድዋ ድልንም ሆነ ምኒልክን በመጥፎ የሚረዳ ነው። ድሉን ራሱን መጥፎ አድርጎ የሚቆጥር ነው። የምኒልክን ሃውልት ይፍረስ የሚል የፖለቲካ ማሕበራዊ መሰረት ያለው ነው። ያውም በሰላማዊ መንገድ አይደለም፤ በሃይል አፈርሳለሁ የሚል ነው። ስለዚህ ድርጊቱ ለከሳሽ የዳኝነት ሥልጣን እንደመስጠት ይቆጠራል።
፫. የታሪክ ሽሚያ ነው። እስከ ዛሬ የአድዋ ድል በአዲስ አበባ የሚከበረው ምኒልክ ሀውልት ሥር ነው። ከዚህ በኋላ ማክበሪያ ማዕከሉ ይህ እንዳይሆን ታስቦ ነው የፕሮጀክቱ ግንባታ የተጀመረው። ስትራቴጂያዊ ግቡ ይህ ነው። ኦሕዴድ በሁለት በኩል ማለትም በአዲስ አበባ መስተዳድር እና በኦሮሚያ መስተዳድር በኩል ተሰልፎ በዓሉን ወደ መስቀል አደባባይ እየወሰደው ይገኛል።
፬. ታሪኩን ለማንሻፈፍ ነው። የፈጠራ ታሪኮችን ለመጨመር ነው።
፭. የሙዚየሙ ግንባታ በራሱ የከተማው ኗሪ አንገብጋቢ ጥያቄ አይደለም። ታሪኩን ለማጥፋት ያለሙ ፖለቲከኞች ተነሳሽነት ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን በመረዳት በሰላማዊ ሕዝባዊ ተቃውሞ ታሪኩን እንዲያስቀጥል ባልራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሀገራዊ ጥሪውን ያቀርባል።
ድል ለዴሞክራሲ!
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በነገው ዕለት የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም ከጠዋት 3 ሰዓት ጀምሮ በሀርመኒ ሆቴል ” የአዲስ አበባ የራስ ገዝ ጥያቄ ” አስመልክቶ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ለብዙሃን መገናኛ ጥሪ ማስተላለፍ የሚታወቅ ነው።
ሆኖም ግን በሀርመኒ ሆቴል ምክንያት ማምሻውን በደረሰን መረጃ መሠረት፤ የነገውን ዝግጅት ማካሄድ እንደማይችል ተገልጿል ።
ይህም በመሆኑ ባልደራስ ጉዳዩን አጣርቶ የደረሰበትን ነገር የሚገልጽ መሆኑን እየገለጽን ፤ ጥሪ ያስተላለፍንላችሁ የብዙሃን መገናኛ በሙሉ ፤ የነገው ጥሪ ለሌላ ቀን መተላለፉን እንድታውቁ በአክብሮት እንጠይቃለን።
#ማስታወሻ ፦ ባልደራስ የነገውን ዝግጅት አስመልክቶ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ከታች በተገለጸው መልኩ አስፈላጊውን ሁሉ አድርጓል ።