የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋ ከቃሊቲ የላከው መልዕክት!
“ህዝቡ የምርጫ ሰራዊት መሆን አለበት። ይሄ ምርጫ የሚወስነው የአምስት ዓመት፣ የአስር ዓመትን ዕጣ ፋንታ አይደለም የትውልድን እንጂ።
ስለዚህ ፣ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ምርጫ ካርድ እንዲወስድ፣ እንዲመርጥና ምርጫውን በታዛቢነት በንቃት እንዲከታተል ጥሪ አቀርባለሁ “
ድል ለዲሞክራሲ
Balderas Latest News
“ህዝቡ የምርጫ ሰራዊት መሆን አለበት። ይሄ ምርጫ የሚወስነው የአምስት ዓመት፣ የአስር ዓመትን ዕጣ ፋንታ አይደለም የትውልድን እንጂ።
ስለዚህ ፣ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ምርጫ ካርድ እንዲወስድ፣ እንዲመርጥና ምርጫውን በታዛቢነት በንቃት እንዲከታተል ጥሪ አቀርባለሁ “
ድል ለዲሞክራሲ
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ እና ባልደራስ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን “የቀጣይ 2013 አገር አቀፍ ምርጫ እድሎችና ስጋቶች” በሚል መሪ ኃሳብ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመጋበዝ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የወከሉ ተሳታፊዎች እና ጋዜጠኞች ተገኝተዋል። `በመርኃግብሩ ላይ ከተገኙት መካከል ፖለቲከኛ አቶ ሙሳ አደምንና ከትዴፓ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ከነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ ዶ/ር አብዱልቃድር፣ ከእናት ፓርቲ መምህር ኪሮስ፣ከኢዜማ አቶ አበበ አካሉ፣ዶ/ር ጫኔ ከበደ እና ሌሎችም ተገኝተዋል።
የአብን ም/ሊቀመንበር አቶ የሱፍ ኢብራሂም እና የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር አብዱልቃድር ለፓናል ውይይቱ መነሻ የሚሆን የዳሰሳ ጹሁፎችን አቅርበዋል።
የቀረቡትን የመነሻ ጹሁፎች መነሻ በማድረግ እነ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ ሙሳ አደም፣ መ/ር ኪሮስና ዶ/ር ጫኔ ከበደ በቅድሚያ መድረኩን ያዘጋጁትን አብንንና ባልደራስን በማመስገን የፓርቲያቸውንና የግል እይታቸውን አጋርተዋል። ኢዜማ በቀጣይ መሰል የውይይት መድረኮችን እንደሚያዘጋጅ በነበረው የውይይት መድረክ የፓርቲው ም/መሪ ዶ/ር ጫኔ ከበደ ተናግረዋል ።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ጋር በመተባበር “የምርጫ 2013 ተስፋና ስጋቶች” በሚል ርዕስ በራስ አምባ ሆቴል ነገ ሚያዚያ 07/2013ዓ.ም ከጥዋቱ 3፡00 ስዓት ጀምሮ ውይይት ያካሂዳል።
ዝግጅቱ ለሁሉም የብዙሃን መገናኛ ክፍት በመሆኑ ሁሉም የሚዲያ አካላት በሥፍራው ተገኝተው እንዲዘግቡት ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ጥሪውን በአክብሮት ያቀርባል።
በጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚደረገው ችሎት ለዛሬ ሚያዝያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ተቀጥሮ የነበረው ችሎት ‘ፕላዝማው ተበላሽቷል’ በሚል ለፊታችን ሚያዝያ 15 ቀን ተዘዋውሯል። ይኸው ችሎት ከዚህ በፊት ለመጋቢት 28 ተቀጥሮ የነበረ ሲሆን ከሦስቱ ዳኞች መካከል አንዱ ባለመገኘታቸው ነበር ለዛሬ የተሸጋገረው።
የህሊና እስረኞች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ከፕላዝማ ይልቅ በችሎቱ ፊት ለፊት ለመቅረብ ቢጠይቁም አዎንታዊ ምላሽ አላገኙም። ፕላዝማው ትናንት አመሻሽ ድረስ ሲሠራ እንደነበር ማወቃቸውን የገለፁት የህሊና እስረኞች ወድያውኑ አስተካክሎ ከቀትር በኋላ ችሎቱን ማከናወን ይቻል እንደነበርም ተናግረዋል። ይህ እንኳን ባይሆን እስከ ሚያዝያ 15 ማራዘሙ ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል። “ብይን ሳይሰጠን ምርጫውን ማሳለፍ ስለተፈለገ ፍርድ ቤቶች ሆን ብለው እያጓተቱብን ነው” ብለዋል እስረኞቹ።
በተደጋጋሚ እየተገፋ ያለው ችሎት ይግባኝ ለማከራከር የተቀጠረ ሲሆን መዝገቡ ሳይከፈት ነው በቀጥታ ለቀጣዩ ችሎት የተዘዋወረው ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ችሎት በግፍ እስር ላይ የሚገኙት አራቱ የህሊና እስረኞች ባሉበት ወህኒ ቤት ውስጥ ሆነው በፕላዝማ ሲቀርቡ ዶሴውን በውጭ ሆነው የሚከታተሉት አምስተኛ ተከሳሽ ፍርድ ቤት በአካል ቀርበው ነበር። ይሁን እንጂ ተከሳሹ በቦታው መኖራቸውን ዳኞች ሳያስተውሉ ቀርተዋል። በመሆኑም ችሎቱ ላይ ‘አልቀረቡም፤ ቀርቤያለሁ’ የሚል ውዝግብ ተፈጥሯል።
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች የፊታችን ሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በከፍተኛው ፍርድ ቤት ሌላ ችሎት ይቀርባሉ። በከፍተኛው ፍርድ ቤት እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት መካከል የተዋረድ ክርክር በማድረግም ያለ ብይን ጊዜው እየተጓተተ ይገኛል ።
ኢትዮጵያ ብዙህ ስትሆን ብዙሃነትን ማስተናገድ ግዴታዋ ነው፡፡ ብዙሃነት ለማስተናገድ የሚያስችል ስርዓተ መንግሥት ስናስብ የፌደራል ሥርዓቱ ቀዳሚ አጀንዳ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የፌደራል ሥርዓቱን ህጸጾችና በጎ ጎኖች በመገምገም የፌደራል ሥርዓታችን ኢትዮጵያዊ እንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚነሳው ኣንዱ ዋና ኣጀንዳ ይሄ ሲሆን አዲስ የፌደራል ሥርዓትን ለኢትዮጵያ ያስተዋውቃል፡፡ የኢትዮጵያ ጣምራ ፌደራል ሥርዓት ይባላል፡፡ የፌደራል ሥርዓት ጽንፈኛ የሆነውን ፖለካችንን በማስታረቅ ኢትዮጵያን ባለሁለት ክንፍ የፌደራል ሥርዓት ኣድርጎ ሰላምና እድገትን ለማምጣት ያስችላል፡፡ ይህ ሃሳብ ሃገር በቀል ሲሆን ለኢትዮጵያ ሽግግር አማራጭ ፍኖተ ካርታ ይሆናል ፡፡
“ጣምራ ፌደራሊዝም” የተሰኘው መጽሐፌ ታትሞ ገበያ ላይ ውሏል :: እንድታነቡ እጋብዛለሁ !!
አቶ ገለታው ዘለቀ
በዓለም ዙሪያ በተለይም በአሜሪካና በአውሮጳ ክፍለ ዓለማት የሚኖሩ እውነተኛ ሀገር ወዳድ የኢትዮጵያ ልጆች በዐማራ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በመቃወም እንዲሁም የፖለቲካ እስረኞች ለሆኑት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ከፍተኛ አመራሮች እስክንድር ነጋ ፣ አስቴር ስዩም ፣ ስንታየሁ ቸኮል እና አስካለ ደምሌ የግፍ እስር የተቃውሞ ድምፃቸውን ማሰማት ቀጥለዋል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በመላው ዓለም እየተቀጣጠለ ላለው የግፉአን ድምጽን የማሰማት እንቅስቃሴ ተሳታፊ ለሚኾኑ ውድ ኢትዮጵያውያን ኹሉ ያለው ታላቅ አክብሮትና ምስጋና ለመግለጽ ይወዳል።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ ለፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለአዲስ አበባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወከሉ እጩዎች በዛሬው እለት በራስ አምባ ሆቴል ፤ መጪውን ምርጫ አስመልክቶ የተለያዩ መርኃግብር እየተካሄደ ይገኛል ።
የዕለቱ መርኃግብር በግፉ ለተገደለው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ፓርቲ አባል ዕጩ ለአቶ በሪሁን አስፈራው የሕሊና ጸሎት በማድረግ የተጀመረ ሲሆን ፤ በአቶ በሪሁን አስፈራው የተደረገውን የግድያ ወንጀል የመርኅግብር ታዳሚዎች በጽኑ አውግዘዋል።
በራስ አምባ ሆቴል እየተካሄደ ያለው ዝግጅት ቀን ሙሉ የሚቀጥል ሲሆን ፤ የተለያዩ ዝግጅቶች ይካሄዳል ። በዝግጅቱ ላይ የባልደራስ እና የአብን ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል ። የዚህን ዝግጅት ሙሉ ዘገባ የምናቀርብ ይሆናል ።
ድል ለእውነተኛ ዲሞክራሲ !!
እኔ-እናቴ ሰላም ዋሉ
ማዘር-እግዚያብሄር ይመስገን
እኔ- ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፖርቲ ዎች ነን ከተማችንን ለማዳን የእርስዎ ድምጽ ያስፈልገናል ካርድ አውጥተዋል ?!
ማዘር- አዎ አውጥቻለሁ ልጄ ባልደራስ ማለት የዛ ጀግና የእስክንድር ነጋ ነው አይደል ?!
እኔ-አዎ እናቴ !
ማዘር-እንደው ምን አድርግ ነው የሚሉት?
እኔ- እናቴ እውነትን ስለያዘ ይፈሩታል ፤ ከምርጫ ውጭ ለማድረግ ነው ። ሀሳብን ግን ማሰር አይችሉም የሱን ዓላማ ይዘን እስከመጨረሻው እንሄዳለን።
ማዘር- እየውልህ ልጄ አሰሩትም ፈቱትም እንመርጠዋለን። አሰሩትም ፈሩትም ያሸንፋቸዋል ። እሱ የፍቅር ሰው ስለሆነ ፍቅር ደሞ የአሸናፊነት መንገድ ነው ። አደራ እናንተም የአለቃችሁን መንገድ ተከተሉ ።በርቱ እናንተ እያላችሁ ሃገር አትፈርስም ተስፋ አለን ተባረኩ።
በአዳም ውጅራ
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ቀኝ ዘመም (Center to right) ፓርቲም ነው። ባልደራስ ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በሀቀኛው ጋዜጠኛ እና በፅኑው የሰብዓዊ መብቶች ታጋይ በአቶ እስክንድር ነጋ መሪነት በጎዳና ላይ ተመሰረተ። የግል ኩባንያ ከሆነው ኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል በዘጠና ሺህ ብር የተከራየውን የስብሰባ አዳራሽ በአምባገነኑ መንግሥት ተከልክሎ ጎዳና ላይ ቅድመ መሥራች ጉባኤውን በማድረግ አቶ እስክንድር ነጋን ፕሬዚደንቱ አድርጎ መርጦ ተቋቋመ።
ቀጥሎም የካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መ.ኢ.አ.ድ.) ዋና ፅህፈት ቤት በተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ አቶ እስክንድር ነጋ በቃለ መሀላ ስነ ስርዓት መሪነታቸውን ተቀብለዋል። የብሔራዊ ምክር ቤት አባላትም ተመርጠዋል። ለዚህ ፓርቲ መሰረቱ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ባልደራስ አዳራሽ የተመሠረተው የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ነው። ባለ አደራ ምክር ቤቱ አላማው የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ ሳይሆን ፖለቲካውን የሚገራ የሲቪክ ተቋም ሆኖ የመቀጠል ፍላጎት ቢኖረውም በመንግሥት ክልከላ ሳይሳካ ቀርቷል። ከዚያም ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት መጣ።
በባልደራስ እምነት መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይባላሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ባለሙሉ ሥልጣን ነው። ሀገሪቱን የማስተዳደር ሥልጣን ከሕዝብ ይመነጫል። ባልደራስ ፕሬዚደንታዊ የመንግሥት አወቃቀር እንዲኖር ይታገላል። በፌዴራል መንግሥቱ ሥር የክፍላተ ሀገር መሥተዳድሮች እንዲኖሩም ይሻል። አብዛኛው የሥልጣን ክፍፍል ለፌዴራል መንግሥቱ መሰጠት አንዳለበት ያምናል። አዲስ በሚዘጋጀው ሕገ መንግሥትም የክፍለ ሀገር መስተዳድሮች ላይ የፌዴራል መንግሥቱ የሥልጣን የበላይነት እንዳለው ሊደነገግ ይገባል።
በኢትዮጵ ብቸኛው የሉዓላዊነት ባለቤት የፌዴራል መንግሥቱ ነው። ክፍላተ ሀገር (ኦሕዴድ/ብልፅግና ክልል የሚላቸው) ከመስተዳድርነት የዘለለ ሥልጣን ሊኖራቸው እንደማይገባ ባልደራስ ያምናል። ለዚህም እየታገለ ያለ የፖለቲካ ፓርቲ ነው። ባልደራስ የአዲስ አበባ ኗሪዎች የመኖሪያ ቤት እና የከተማ መሬት ባለቤት መሆን እንዳለባቸው ያምናል። መሬት የመንግሥት መሆኑ ቀርቶ የዜጎች መሆን አለበት።
ይህ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ ሊሆን ይገባል። ለዚህም ፓርቲው እየታገለ ነው። የአዲስ አበባ ኗሪዎች ሁሉ እኩል ናቸው። በአዲስ አበባ ላይ ማንኛውም አካል ልዩ ጥቅም ሊኖረው አይገባም። ከተማችን ራስ ገዝ እንድትሆን ባልደራስ ይታገላል። ፓርቲው ሀብትን ከማከፋፈል ይልቅ ሀብት መፍጠር ላይ ያተኮረ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ ያምናል። ለዚህም የግሉን ክፍለ ምጣኔ ሃብት ማጠናከር ያስፈልጋል። ኦ.ነ.ግ. እና ሕ.ወ.ሓ.ት. ሰራሹን ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በዴሞክራሲያዊ ሂደት መናድ፣ አባቶች ያወረሱንን ታሪክና ቅርስ ተንከባክቦ ማስቀጠል፣ ፍትሕና ዴሞክራሲን ማስፈን፣ እምነትን መጠበቅ፣ የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በአንክሮ የሚታገልባቸው አምዶች ናቸው።
ክቡር አቶ አምሀ ዳኘው የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ ክቡር ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የተከበራችሁ እጅግ የምናከብራችሁ ደጋፊዎቻችን እና የፓርቲያችን አባላት በቅድሚያ በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የሚወዳደሩ የፓርላማ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት እጩዎቻችንን ለመተዋወቅና በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ጥሪያችንን አክብራችሁ በመምጣታችሁ በራሴና በባልደራስ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስም ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ዛሬ ሀገራችን እጅግ በጣም ውስብስብ በሆኑ ከፍተኛ ችግሮች ተተብትባ በመቃተት ላይ የምትገኝበት ጊዜ ነው፡፡ እውነተኛ የሆኑ አገር ወዳድ ዜጎች የኢትዮጵያ ስቃይ ስቃያቸው፣ ችግሯ ችግራቸው፣ መከራዋ መከራቸው በመሆኑ ከገባችበት አዘቅት ለማውጣ የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ መገደል፣ መፈናቀል፣ መታሰር፣ የኑሮ ውድነት መናር፣ መራብ፣ መታረዝ፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማካሄድና የመናገር መብቶች መነፈግ፣ ከቦታ ወደቦታ በሰላም መንቀሳቀስ አለመቻል እና መሰል ችግሮች የዕለት ከዕለት ኑሯችን ሆነዋል፡፡ ዛሬ ህወሃት በሥልጣን ላይ ባይኖርም እሱ ያዘጋጀው ሰዎችን በዘር አለያይቶ የሚያባላውና ሃገርን የሚበታትነው ህገ መንግሥት ግን በኢህአዴግ ቁጥር ሁለት ወይም በብልጽግና ፓርቲ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ጽንፍ የረገጡ አክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች ወያኔ ከሚፈጽማቸው ተግባራት በባሰና ይሉኝታ በሌለው መንገድ ሁሉም የእኛ – ኬኛ በማለት ቤቶችን እና መሬትን እየተቀራመቱ ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ከላይ እስከታች ያሉ ቁልፍ የሥራ ቦታዎችን በአንድ ዘር ያስይዛሉ፡፡ ጠቃሚ የገቢ ማስገኛ ተቋማትንም እንደዚሁ በቁጥጥራቸው ሥራ ያውላሉ፡፡ ዜጎች በማንነታቸውና በሀይማኖታቸው ምክንያት በገጀራ ሲቆራረጡ፣ በቢላዋ ሲታረዱ፣ ሆዳቸው በስለት እየተሰነጠቀ ጽንሶች በሜዳ ላይ ሲጣሉ፣ አስከሬኖች እንደአልባሌ እቃ እየተወረወሩ በአንድ ጉድጓድ ሲቀበሩ፣ ንብረቶቻቸው ሲዘረፉ፣ ቤቶቻቸው በእሳት ሲጋዩ፣ ቤተ እምነቶቻቸው ሲቃጠሉ እና ሌሎችም ከፍተኛ ሰቆቆ ሲፈፀምባቸው ሰላማቸውን የመጠበቅና መብታቸውን የማስከበር ግዴታ ያለበት በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሊታደጋቸው አልቻለም፡፡ አዲስ አበባ ላይም ‹‹ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ይገባናል›› ከማለት አልፈው ‹‹በአዲስ አበባ የባለቤትነት መብት አለን›› በማለት ከፍተኛ በደል እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ዘረኛ አስተሳሰባቸውን በመቃወም ፍትሃዊ ሥርዓት ለማስፈን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ‹‹አዲስ አበባ የኗሪዎቿ ናት፡፡ አዲስ አበባ የመላው ኢትዮጵያውያን ናት፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ናት፡፡ በአዲስ አበባ የተወለዱና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች ተወልደው በከተማዋ የሚኖሩ እኩል ባለመብቶች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ በራሷ ልጆች መመራት አለባት፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ውህድ ማንነት ያላቸው ናቸው፡፡›› የሚል መርህ ይዞ በመነሳት ሕዝቡን በማታገል ላይ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባ በዙሪያዋ ካሉ አካባቢዎች ጋር በማስተር ፕላን ልትተሳሰር ይገባል፤ የከተማዋ ነዋሪዎችም በዙሪያዋ ባሉ ቦታዎች ያለምንም መሸማቀቅ ቤት የመሥራት እና የንግድ ተቋማትን የማቋቋም የዜግነት መብታቸው ምንም ሳይሸራረፍ ሊጠበቅላቸው ይገባል ብሎ ባልደራስ ያምናል፡፡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አምባገነንነትን፣ ዘረኝነትን፣ ግለኝነትን፣ አድሎአዊነትን፣ አሉባልተኝነትን እና ቡድነኝነትን ይዋጋል፡፡ በአሁን ወቅት በእስር ላይ የሚገኘው እስክንድር ነጋ ለባልደራስ መመሥረትና መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ የፈጸማቸው አኩሪ ተግባራት በድርጅቱ አባላት፣ እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጭ ባሉ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ እንዲኖረው አድርገውታል፡፡ ዛሬ እያካሄድን ያለው ትግል የሞት የሽረት ወይም የመኖር ያለመኖር መሆኑን ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል፡በኦሮሞ ብልጽግና እየተመራ ያለው ኢህአዴግ ቁጥር 2 የአዲስ አበባን ሕዝብ በእንጀራ ልጅነት እየተመለከተ የተለያዩ በደሎችን እያደረሰበት ይገኛል፡፡ በርካታ ወጣቶች ተምረው በአደጉባት ከተማ የበይ ተመልካች ሆነው አለሥራ ተቀምጠዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች ከገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን ግብር እየተጣለባቸው ከመስኩ ወጥተዋል፡፡ ብዙ ኗሪዎች ቤት በላያቸው ላይ እየፈረሰባቸው ቤት የለሽ ሆነዋል፡፡ ኗሪዎች የኮንዶሚንየም ቤት ለማግኘት ለዘመናት ገንዘብ በባንክ ቢቆጥቡም የቤት ባለቤትነት ዕድል ለአንደኛ ደረጃ ዜጎች እንጂ ለቆጣቢዎቹ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ አዲስ አበቤ የተነፈጉትን መብቶቹን ለማስከበር ማንን መምረጥ እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል ብለን እናምናለን፡፡ በሃገርና በሕዝብ ላይ በደል እያደረሰ ያለውን አስከፊ ሥርዓት በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ለመተካት ምርጫው ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ባልደራስ በእጅጉ ያምናል፡፡ የምርጫ ካርድ አምባገነኖችን ከስልጣናቸው እንደሚያወርዳቸው እንደምትገነዘቡም ይረዳል፡፡ በመሆኑም እናንተ ደጋፊዎቻችን ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት ቤተሰቦቻችሁን፣ ጓደኞቻችሁን እና ወዳጆቾቻችሁን ሁሉ በማስተባበር በነቂስ ወጥታችሁ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲን እንድትመርጡ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡ ምርጫው እንዳይጭበረበርም በትኩረት እንድትከታተሉ እናሳስባለን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ !!!
ድል ለዲሞክራሲ!!!