ዳኛው የሉም? (ጌጥዬ ያለው)
በእነ እክንድር ነጋ መዝገብ ላይ ከዚህ በፊት የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እና ሰበር ሰሚ ችሎት “ዳኞች ተሟልተው አልቀረቡም”፣ “መዝገቡን አልመረመርንም”፣ “ፕላዝማ ተበላሽቷል” በሚሉ ሰበቦት እስከ አንድ ወር ድረስ የረዘሙ ተለዋጭ ቀጠሮዎች ይሰጡ ነበር። በዚህም ምክንያት ምስክሮች በግልፅ ችሎት ይቅረቡ?፣ ከመጋረጃ ጀርባ ይቅረቡ?፣ በዝግ ችሎት ይቅረቡ በሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ሲሟገቱ ከአንድ አመት በላይ ሆነ።
ይኸው ጉዳይ ዘንድሮም ቀጥሏል። ከበላይ ፍርድ ቤቱ የተማረው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ዛሬ ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጧት በዋለው ችሎት ቀጣዩን ችሎት በዚሁ ቀን ከቀትር በኋላ ለማድረግ ቀጥሮ ነበር፤ ነገር ግን ከሦስቱ ዳኞች መካከል አንዱ ማለትም የቀኝ ዳኛው ባለመገኘታቸው በቀጠሮው መሰረት ክርክሩን ሳያስቀጥል ቀርቷል። ሁለቱ ዳኞች ብቻ ቢሰየሙም ክርክሩን እንደ ታዳሚ ከማዳመጥ ውጭ ብቻቸውን መፍረድ እንደማይችሉ ለችሎቱ ተናግረዋል። የቀኝ ዳኛው ቤተሰብ ታሞባቸው ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንደሄዱ ሰብሳቢ ዳኛው ተናዘዋል።
ይህንን ሲሉ ከጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት የማውቃት ዝነኛ አባባል ትዝ አለችኝ። “ጋዜጠኛ አይሞትም! አይታመም!” አባባሉ ምንም አይነት ችግር ቢደርስብህ ለጊዜው የተመደብህበትን የጋዜጠኝነት ሚና በጊዜው መወጣት አለብህ የሚል ነው። በዚህ መርህ የእናታቸውን አስክሬን እቤታቸው አጋድመው እንባቸውን እያዘሩ ዜና ለማንበብ ወደ ስቱዲዮ የሚገቡ ጋዜጠኞች ዓለም ላይ በርካታ ናቸው። ወታደር እንኳን በሚያፈገፍግበት ጦር ሜዳ መሀል ገብተው የጥይት ብልጭታ በካሜራቸው የሚቀርፁ ዘጋቢዎች የትየለሌ ናቸው። በርግጥ “የታክሲ ሰልፍ ረዘመ፤ መንገድ ተዘጋጋ” ብለው በዜና ሰዓት ሙዚቃ የሚያስጮሁ ምንግዴ ጋዜጠኞችም ሩቅ ሳንሄድ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ሞልተዋል።
ሰው ጤፉ ዳኛም ታዝዘው ይሁን ወይም ፈቅደው ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት ችሎቱን አጉላልተዋል። እውን ቤተሰባቸው ታመው ከሆነ ፈጣሪ ይማርላቸው። ብዙ ልወቅሳቸው አልፈልግም። የሙያ ስነ ምግባራቸውን ለራሳቸው እተወዋለሁ። ምክንያቱም እንኳን የሙያ ስነ ምግባራቸው ምለው የተሾሙበት፤ የሚያሽቃብጡት ሕገ መንግሥትም ተከብሮ አያውቅም። ግን ግን ድርጊታቸው ችሎት መድፈር አይደለም ወይ? አያስቀጣም ወይ?
ችሎቱ ከጧቱ የቀጠለ በመሆኑ በአጭር ደቂቃ ሊጠናቀቅ የሚችል ነበር። ከልደታ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለመድረስም ከ10 ደቂቃ የሚበዛ ጊዜ የሚወስድ አይመስለኝም። በመሆኑም አንድ አፍታ ከሆስፒታል ተመልሰው ዳኝተው መሄድ የሚችሉበት ዕድል ሙሉ በሙሉ ዝግ አልነበረም። በተጨማሪም ሌላ ዳኛ መተካት ይቻል ነበር። ይህ እንዳይሆን ግን ሁሉም ዳኞች ለስልጠና መውጣታቸውን ሰብሳቢ ዳኛው ተናግረዋል። ቤተሰብ ታመመባቸው የተባሉት ዳኛም ችሎቱ በተሰየመበት ሰዓት የስልጠና አዳራሹ ውስጥ ታይተዋል የሚል ጭምጭምታ ደርሶኛል።
በዛሬው ቀጠሮ ችሎቱ የሁለት ምስክሮችን እማኝነት ሊሰማ የነበረ ቢሆንም ለቀጣዩ ሳምንት ተሸጋግሯል። በዚህም ዳኛው የእነ እስክንድር ነጋ የእስር ቤት እድሜ ላይ የአንድ ችሎት የቀጠሮ ጊዜ ጨምረዋል ማለት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለዐቃቤ ሕግ ሌላ የቅጥፈት ጊዜ ይሰጠዋል።
በጧቱ ችሎት ዐቃቤ ሕግ የምስክሮችን ስም ዝርዝር እና የዳኝነት ጭብጦቻቸውን ይዞ እንደሚቀርብ ቢታዘዝም ተግባራዊ አላደረገም። ይልቁንም በግልፅ ችሎት እንዲመሰክሩ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የታዘዙ ምስክሮች ስም ለመገናኛ ብዙሃን እንዳይጠቀስበት ጠይቋል። ለዚህም ሲባል ስማቸውን ለዳኞች ብቻ በምስጢር ያሳወቀ ሲሆን ለተከሳሾችና ለጠበቆች ግን እንዳይሰጥበት ጠይቋል። ይህ ዝግ እንጂ ግልፅ ችሎት እንዳልሆነ በመጥቀስ እነ እስክንድር ነጋ ተቃውመውታል። “ጧት የተወሰነው አሁን መከበር አለበት። ቢያንስ ይቀርባሉ የተባሉት ሁለት ምስክሮች ማንነት በትዕዛዙ መሰረት አሁን ይነገረን። ስማቸውም በሚዲያ ይፋ ቢደረግ ሕጋዊ ይሆናል። የምስክሮች በሚዲያ ይፋ መሆን ተጠያቂነት (Acountablity) እንዲኖር እንጂ ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ለማስፈራራት አይደለም” ብሏል እስክንድር ነጋ።
በተጨማሪም “ዐቃቤ ሕግ ሐሰተኛ ምስክሮች የማቅረብ ልምድ ያለው ነው” ብሎ ንግግሩን ሲቀጥል ሰብሳቢ ዳኛው ጣልቃ ገብተው እስክንድር ነጋን ለማስቆም ሞክረዋል። እንደዚህ አይነት ድምዳሜ መስጠት ተገቢ እንዳልሆነም አብራሩ።
እስክንድር እንደገና በመቀጠል “እኛ አስር አመት እስር ቤት ስንኖር ይህንን ዐቃቤ ሕግ እናውቀዋለን። በሀሰት ሲከሰን፤ በሀሰት ሲያስመሰክርብን ኖሯል። አሁንም አልተቀየረም። ይሄ መንግሥት ያመነው ጉዳይ ነው። ይሄ ችሎት ሊክደው አይገባም። የሁለቱ ምስክሮች ስም አሁን ይነገረን” አለ።
“ግልፅ ችሎት ማለት ምን ማለት ነው? መስፈርት የለውም ወይ? ከመገናኛ ብዙሃን ከተደበቀ ምኑ ነው ግልፅነቱ? ከዚህ በፊት ተከራክረንበት አይደለም ወይ? ችሎቱ ለምን አቋም አይኖረውም?” በማለት አስቴር ስዩም ጨመረች። ሆኖም ለእነዚህ ጥያቄዎች ሁሉ መልስ መስጠት የሚቻለው ዳኞች ተሟልተው ሲቀርቡ በመሆኑ ውሳኔዎች ወደ ቀጣዩ ችሎት ተገፍተዋል።
“470 ቀን እስር ቤት ውስጥ ነው ያለነው። ልጆቻችን 470 ቀን እያለቀሱ ነው። ዐቃቤ ሕግ ለምስክሮቹ እንደሚጨነቀው ለእኛ ልጆችም ማሰብ ያስፈልጋል” ያለው ስንታየሁ ቸኮል በበኩሉ የኩላሊትና የጉበት ህመም ያለበት በመሆኑ ከእስር ቤት ውጭ ባለ የህክምና ተቋም በግሉ እንዲታከም ጠይቋል። ለዚህም በቀጣዩ ችሎት ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ምላሽ እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱ ጠርቷል።
ዐቃቤ ሕግ ከዚህ በፊት 21 ምስክሮችን እንዲያሰማ የተጠየቀ ሲሆን ከዘጠኝ በላይ ምስክሮችን ማግኘት እንዳልቻለ አስታውቋል። የዘጠኙን ስም ዝርዝር ለዳኞች ብቻ በምስጢር ሰጥቷል። በማነኛቸው ተከሳሾች ላይ እና በምን ውስን ድርጊት ላይ እንደማመሰክሩ የዳኝነት ጭብጥ እንዲያቀርብ ቢታዘዝም ትዕዛዙን ጥሷል። ማንን በምን ጉዳይ ላይ እንደሚያስመሰክር ዝርዝር መግለጫ አለማዘጋጀቱንም ተናግሯል።