ዜና
Balderas Latest News
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ንቁ አባል እና ጉዳይ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ካሳሁን ደስታ ዛሬ ጠዋት፤ በትላንትናው ዕለት 03/04/2015 ዓ.ም ለታሰሩት አቶ ናትናኤል ስንቅ ለማቀበል ሄደው ነበር። ሆኖም በሄዱበት ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ (ላዛሪስት ፔኒሲዮን) የሚገኘው የጉለሌ ፖሊስ መምሪያ በዛው አግቶ አስቀርቷቸዋል።
አቶ ካሳሁን ፓርቲያቸውን እና ሀገራቸውን በትጋት እያገለገሉ የሚገኙ ሰላማዊ-ታጋይ ናቸው።
አቶ ናትናኤል የአለምዘውድ ታሰሩ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ንቁ አባል የነበሩት አቶ ናትናኤል ያለምዘውድ ባልታወቁ ደህንነቶች ዛሬ በሰፈራቸው ቀጨኔ መድሃኒአለም አካባቢ ተይዘዋል።
አቶ ናትናኤል ያለምዘውድ ቀድሞው ህወሃት መራሹ መንግስትም ሆነ በአሁኑ የኦሮሞ-ብልፅግና መራሹ መንግስት በተደጋጋሚ ታስረዋል።
በወቅታዊ የፓርቲያችን እንዲሁም የሀገራችን ሁኔታ ላይ የተደረገ ውይይት
የባልደራስ ፓርቲ የስራ አስፈፃሚ አባላት የሆኑት ዶ/ር በቃሉ አጥናፉና አቶ ስንታየሁ ቸኮል በወቅታዊ የፓርቲያችን እንዲሁም የሀገራችን ሁኔታ ላይ ተወያይተወዋል። ውይይቱን ከታች ባለው ሊንክ (Link) በመግባት ይከታተሉ።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን እንዲያካሂድ ውሳኔ ተላለፈ
በቀን 20/03/2015 ዓ.ም በቁጥር አ1162/11/782 በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተፃፈ ደብዳቤ ፓርቲው ሊያደርግ ያቀደው ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ እንዲችል በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት አይቶ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ እንዲሁም የፓርቲው ም/ፕሬዚዳንት አቶ አመሃ ዳኜው ምክትል ፕሬዚዳንትነት በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት የተከናወነ መሆኑን በማረጋገጡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ሰጥቶታል፡፡
በመሆኑም በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የምትገኙ አባላትና ደጋፊዎቻችን እንኳን ደስ አላችሁ እያልን፤ ጉባኤው የሚካሄድበትን ቀን በቀርቡ የምንገልፅ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡ በተጨማሪም ፓርቲያችን እንደዚህ ቀደሙ ለጉባኤው መሳካት የምታደርጉትን ጥረት፣ ድጋፍና አስተዋጽኦ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ድል ለዲሞክራሲ!!!
ኦነግ ሸኔ በከፈተው ጦርነት ምክንያት የአ.አ- ጎጃም መስመር ተዘጋ
“መንግስት ካለ መረጃውን ለህዝብም ለመንግስትም አድርሱልን”። ይህ መልእክት ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም ሲጓዙ የነበሩ ተሳፋሪዎችና ሹፌሮች ያስተላለፉት መልክት ነዉ።
በዛሬው እለት ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ጎጃም መስመር ሲጓዙ የነበሩ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች፣የጭነት መኪኖች፣እስክሬን የጫኑ መኪኖች፣ የግለሰብ መኪኖች እንዲሁም አገር አቋራጭ ነዳጅ እና ሸቀጣሸቀጥ የጫኑ መኪኖች በሙሉ አሊ ዶሮ አካባቢ ኦነግ ሸኔ በከፈተው ከፍተኛ ጦርነት አማካኝነት መንገድ ላይ ለማደር ተገደዋል።
መረጃውን ያደረሱን ተጓዦች እንደሚሉት በአካባቢው እጅግ ጠንካራ ጦርነት ነው እየተካሔደ ያለው። እነዚህ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ግለሰቦች በተጨማሪም እጅግ ብዛት ያለው መከላከያ እኛን እያለፈ ከወደ አዲስ አበባ ወደ አሊ ዶሮ ወይም ጦርነቱ ወደ አለበት ቦታ ሲጓዝ ቢታየም፤ አሁን ሰላም ነው እለፉ የሚላቸው አካል አላገኙም። በማከልም “ህፃናት፣ አዛውንቶች፣ በሽተኞች፣ ሬሳ የጫኑ ሀዘንተኞች ሳይቀሩ መንገድ ላይ አድረናል” ብለዋል።
የሚደርስልን መንግስት ባይኖርም እንኳ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቅልን መረጃውን አድርሱልን ሲሉ ተማፅኗቸውን አሰምተዋል።
ይህ መረጃ እስከደረሰን ሰአት ድረስ ከአዲስ አበባ ጎጃም የሚያስኬደው መንገድ እንደተዘጋ ነበር።
ለቤተመንግስት መስሪያ ሲባል ዜጎች ተፈናቅለው ወደ ጎዳና ሊወጡ ነው
ከወር በፊት በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 10 እየተሠራ ነው በሚባለው ቤተ-መንግሥት ሳቢያ የአካባቢው ነዋሪዎች ቅያሪ ቦታ ቤት መቀለሻ ገንዘብ ሳይሰጣቸው በላያቸው ላይ ሊፈርስ እንደሆነ ከነዋሪዎቹ በደረሰን ጥቆማ መሠረት አቤቱታቸው ሰሚ ያገኛል በሚል ተስፋ ፓርቲያችን ባልደራስ መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ቤቶቹን በነዋሪዎቹ ላይ የማፍረስ ሂደቱ ለጊዜውም ቢሆን ተገትቶ ነበር፡፡ ይሁንና አሁንም የየካ ክ/ከተማ ወረዳ 10 ነዋሪዎች ምንም ምትክ ቦታ እና የመሥሪያ ገንዘብ ሳይሰጣቸው ቤታቸው ላያቸው ላይ ሊፈርስ እንደሆነ በድጋሚ በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡
በ13/03/2015 ዓ.ም የወረዳው የመሬት አስተዳደር ሀለፊዋ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመምጣት፤ በሶስት ቀን እቃችሁን አውጡ ቤታችሁ ይፋርሳል እንዳሏቸው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። ይህም የአካባቢውን ህብረተሰብ ድንጋጤ ውስጥ መክተቱን ተናግረዋል። ትዐዛዙ የደረሳቸውም በፅሁፍ ሳይሆን በቃል ብቻ መሆኑን ነዋሪዎቹ በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡ በፅሁፍ እንዲሰጧቸው ቢጠይቁም እንደተከለከሉ ተናግረዋል። ይኽ አሠራር ተጠያቂነትን የመሸሽ የተለመደ አካሄድ ነው፡፡ አቤቱታ ሰሜ ባይኖርም ውሳኔው በፅሁፍ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
የሃዘን መግለጫ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በአሜሪካን የባልደራስ ደጋፊ የነበሩትን ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወዬሳን ድንገተኛ ሞት ሲሰማ ከፍተኛ ሀዘን ተሰምቶታል። አቶ ዳዊት ከበደ በጋዜጠኝነት ሙያ ለረጅም ጊዜ ሀገራቸውን በቅንነት ያገለገሉ ከመሆኑም ባሻገር ሙያቸውን አክባሪ፣ ትሁትና ቅን ሰው ወዳድ እንደነበሩ የሚታወቅ ነው።
ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ የፓርቲያችን መሥራችና ፕሬዚዳንት ከነበሩት ከጀግናው እስክንድር ነጋ ጋር የነበራቸው ሙያዊ ግንኙነትና ወንድማዊ ቀረቤታ ለብዙዎቻችን የባልደራስ አባላትና ደጋፊዎች የሚሰማንን ሀዘን የበለጠ የመረረ ያደርገዋል።ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የተሰማውን መሪር ሀዘን እየገለፀ ለመላው ቤተሰባቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው መጽናናትን ይመኛል።
የትግል አጋራችን የነበሩትን የወንድማችን ነፍስ በአፀደ ገነት ያኑርልን!
በባልደራስ ስም ሃክ በተደረጉ የፌስቡክ አካውንቶች የሃሰት መረጃ የሚያሰራጩ ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የባልደራስ ሥ/አስፈጻሚ አስጠነቀቀ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚይዘው አቋም የሚገለፀው፡-
1. በራሱ የተረጋገጠ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ ላይ
2. በጽ/ቤቱ በኩል የተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በሚላኩ አቋም መግለጫዎች ነው፡፡
ከእነዚህ ውጭ በማናቸውም ሁኔታ የሚወጡ ፅሁፎች ባልደራስን አይወክልም፡፡ በመሆኑም የጥቅምት 21/15 ዓ.ም “ጌጥዬ ያለው” በሚል ሀክ በተደረገ የፌስቡክ ገፅ ላይ የፓርቲያችን አቋም ያልሆነ ባለ 4 ገፅ መግለጫ መጻፉ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በፊትም “ጌጥዬ ያለው” በሚለው ፌስቡክ ገፅ ላይ ገፁን በመጥለፍ ሀሰተኛ መረጃ ወጥቶ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ይህን ዓይነት የተሳሳተ ተግባር የምታደርጉ ግለሰቦችም ይሁን ቡድኖች በፓርቲያችን ስም የተወናበደ መግለጫ ከማውጣት እንድትቆጠቡ ስንል እናሳስባለን፡፡
ድል ለዲሞክራሲ!
ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከ60 በላይ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ለቤተመንግስት ማስፋፊያ በሚል በመንግስት ሀይሎች መፍረሳቸው ተነገረ
ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ብሎክ አንድ ፤ሶስት እና አራት የሚገኙ ነዋሪዎች ቤታችን በሕግ ወጥ መንገድ በመንግስት ሀይሎች ፈርሶብናል ብለዋል፡፡
የቀጠና አንድ ቁልቢ ኮሚቴ አመራሮች እንደተናገሩት ከሆነ ከ60 እስከ 65 የሚደርሱ ቤቶች በቀን 17 2/2015 ዓ.ም በመንግስት ሀይሎች ከጠዋቱ 11፡30 ጀምሮ በኃይል ፈርሰዋል ፡፡
ቤቶቹ የፈረሱት አዲስ ይገነባል በተባለው የቤተ-መንግስት ፕሮጀክት ውስጥ ገብተው በመገኘታቸው እንደሆነም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡
የቤት ፈረሳው በማህረሰቡ ተቃውሞ ለጊዜው የቆመ ቢሆንም ይፈርሳሉ በተባሉት አካባቢዎች 884 አባውራዎች እንደሚኖሩ ታውቋል፡፡
በመንግስት ኃይሎች ቤታቸው የፈረሰባቸው ከ60 በላይ ሚሆኑ ነዋሪዎች አሁን ላይ በፈረሰው ግማሽ ቤት ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ጫካ ለተባለው ፕሮጀክት መጀመሪያ ቅየሳ ባደረገበት ወቅት ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ማህበረስብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ እና ህብረተሰቡም የልማቱ አካል እንደሚሆኑ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጠቁመዋል፡፡
ከመንግስት ጋር ከተስማማችሁ የቤቱን መፍረስ ለምን ትቃወማላችሁ ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም ቤታችን እየፈረሰ ያለው የላይኛው ያሉት የመንግስት አካል ሳያውቀው በዝቅተኛ የስልጣን እርከን ባሉ ባለስልጣኖች ፈቃድ በህገ ወጥ መንገድ ስለ ሆነ ነው ብለዋል። እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ድረስ ሄደው መጠየቃቸውን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ባሉ ባለስልጣናት መካከል የተለያየ ምላሽ የተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ አክለውም፦ አሁን ላይ ጉዳዩን ለመንግስት አካል ቅሬታችን ማድረስ እንዳንችል አፈና እና እስር እየተፈፀመብን ነው ብለዋል፡፡
ቅሬታ ያቀረቡ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን ገልፀው ምንአልባትም በዝቅተኛ የአመራር ደረጃ የሚገኙ አካላት መሬቱን ለባለሀብት ሽጠውት ይሆናል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም መንግስት የገባልንን ቃል እንዲያከብር እና ቤታችን ከመፍረስ እኛንም ከስቃይ ይታደገን ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ነዋሪወቹ የሕጋዊነት ጥያቄ እንደሌለባቸውም ተናግረዋል፡፡