ሰበር ዜና
Breaking News Announcement
የችሎት ውሎ
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በማገዱ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ለዛሬ የቀጠረውን የእነ እስክንድር ነጋን ችሎት ሳይዳኝ ቀረ፡፡ በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩምና አስካለ ደምሌ ዛሬ ሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በቀጠሯቸው መሠረት የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ይሁን እንጂ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እያከራከረው በሚገኘው የይግባኝ ዶሴ ብይን ባለመስጠቱ ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ያለ አንዳች ውሳኔ መዝገቡን ሳይገልጥ በቀጥታ ለሚያዝያ 28 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ከሦስቱ ዳኞች መካከል አንዱ ባለመገኘታቸው መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ሊዳኝ የነበረው የእነ እስክንድር ነጋ ጉዳይ ለሚያዝያ ስድስት ቀን 2013 ዓ.ም. መራዘሙ ይታወሳል። በመሆኑም ይግባኝ ለማከራከር የተቀጠረው መዝገብ ሳይከፈት በቀጥታ ለቀጣዩ ችሎት ተዘዋውሯል። የህሊና እስረኞች ጠበቆች ዳኞች ከቀትር በኋላ ተሟልተው እንዲቀርቡ፣ ይህ ካልተቻለም በሁለተኛው ቀን እንዲቀርቡ፣ እነኝህን አማራጮች ማድረግ ካልተቻለ ግን ችሎቱ ተከሳሾችን በነፃ እንዲያሰናብታቸው ጠይቀዋል። ሆኖም ዳኞች ውድቅ አድርገውታል።
ባሉበት ወህኒ ቤት ውስጥ ሆነው በፕላዝማ የቀረቡት እነ እስክንድር ነጋ በበኩላቸው ጉዳዩ ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ጋር የተያያዘ መሆኑን እና ላለፉት ዘጠኝ ወራት ያለ ውሳኔ በቀጠሮዎች እየተጉላሉ መሆኑን ጠቅሰው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ስድስት ኪሎ በሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአካል መቅረብ ሲገባቸው ችሎቱን በፕላዝማ እንዲከታተሉ መደረጉም ስህተት እንደሆነ በዕለቱ ተናግረዋል።
ለሚያዝያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ተቀጥሮ የነበረው ችሎት ‘ፕላዝማው ተበላሽቷል’ በሚል ለፊታችን ሚያዝያ 15 ቀን ተዘዋውሯል። የህሊና እስረኞች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ከፕላዝማ ይልቅ በችሎቱ ፊት ለፊት ለመቅረብ ቢጠይቁም አዎንታዊ ምላሽ አላገኙም። ፕላዝማው እስከ ቅርብ ሰዓት ድረስ ሲሠራ እንደነበር ማወቃቸውን የገለፁት የህሊና እስረኞች ወድያውኑ አስተካክሎ ከቀትር በኋላ ችሎቱን ማከናወን ይቻል እንደነበርም ተናግረዋል። ይህ እንኳን ባይሆን እስከ ሚያዝያ 15 ማራዘሙ ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል። “ብይን ሳይሰጠን ምርጫውን ማሳለፍ ስለተፈለገ ፍርድ ቤቶች ሆን ብለው እያጓተቱብን ነው” ብለዋል የህሊና እስረኞቹ።
በከፍተኛው ፍርድ ቤት እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት መካከል የተዋረድ ክርክር በማድረግም ያለ ብይን ጊዜው እየተጓተተ ይገኛል። ያለ አንዳች ብይን ለሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱም የፍርድ ሂደቱን የማጓተቱ አካል ነው። ‘ዳኛ የለኝም፣ ፕላዝማ ተበላሸብኝ’ እያለ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚያደርገው ማጓተትም ከፍተኛውን ፍርድ ቤት እንደማገድ ይቆጠራል።