መንግሥት በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የመሰረተው ሀሰተኛ ክስ በአስቸኳይ ይቋረጥ !
(ጌጥዬ ያለው)
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ከፍተኛ አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር (ቀለብ) ስዩም እና አስካለ ደምሌ የፖለቲካ አመለካከታቸው እንደ ወንጀል ተቆጥሮ በግፍ ከታሰሩ ከአንድ አመት በላይ ሆኗል። በዚህ ጊዜ ውስጥ አንዳች የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ አልቀረበባቸውም፤ ክሱ ፍፁም ሀሰት በመሆኑ ሊቀርብም አይችልም። የሚቀርብ እንኳን ቢሆን እንደ መሰረታዊ ክሱ ሁሉ ማስረጃ ተብየውም የቅጥፈት ከመሆን አይድንም። የእስር ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ሀምሌ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. የጀመረውን የምስክሮች አሰማም ሂደት ለመቀጠል ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ሳይሰየም ቀርቷል። በአንፃሩ ጠበቆችም ሆኑ ተከሳሾች በሌሉበት ባካሄደው ድብቅ ችሎት ለጥቅምት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ፍርደ ገምድል ቀጠሮ ነው፤ ችሎቱን በያዙት ዳኞች የተቆረጠ መሆኑም ያጠራጥራል። የዚህ ችሎት ሰብሳሲ ዳኛ ሳሙኤል ታደሰ ይባላል። ሌሎች ሁለቱ ዳኞች ፈየራ ቶሌራ እና እጥፍወርቅ በረዳ ፋጀራ ናቸው። ሦስቱም ፖለቲካዊ ትዕዛዞችን እየተቀበሉ እንደሚፈርዱ ምልክቶች ብዙ ናቸው። ምልክቶችን ለጊዜው ልተዋቸውና ወደፊት በምፅፋቸው የዳኞችና ዐቃቢያነ ሕጎች የስብዕና ግምገማ እመለስባቸዋለሁ። ለአሁን ግን ከመንግሥታዊ የመረጃ ምንጮች የደረሰኝን ጉዳይ ላጋራችሁ። ለሀምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. በዚሁ ችሎት በነበረው ዶሴ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቹን በግልፅ ችሎት ይዞ እንዲቀርብ ነበር የታዘዘው። ሆኖም ብቻውን ከሳሽም መስካሪም ሆኖ ቀረበና ጉዳዩን ከፍሬ ነገር አውርዶ የስነ ስርዓት ጉዳዮች ክርክር ለማድረግ ሞከረ። በዚህም ስንታየሁ ቸኮል የችሎቱን ስነ ስርዓት በመጣስ እንዲከሰስ ጠይቆ ነበር (በርግጥ ታዳሚውን ጭምር ሲዘልፍ የዋለው ደመላሽ ኢጀታ የተባለ ዐቃቤ ሕግ ነው) የሆነው ሆኖ በዕለቱ ችሎቱን በዝምታ አልፎት ነበር። ከችሎት መልስ እነ ደመላሽ ኢጀታ “ተከሳሾችና ጠበቆቻቸው እንደ ጭራቅ እየሳሉን ነው። እኛም፤ ዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤቱም ተወርፏል። ችሎቱን የፖለቲካ መድረክ አድርገውታል” በማለት ለአለቃቸው ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፍቃዱ ፀጋዬ አቀረቡ። ፍቃዱ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ለአቶ ብርሃነ መስቀል ወጋሪ ደውሎ የሆነውን ነገረው። ይህ ሰው የፍቃዱን ፀጋዬን ትዕዛዝ ተቀብሎ ዳኞችን ገሰፃቸው። በሁለተኛው ቀን በተሰየመው ችሎት የቀኝ ዳኛዋ እጥፍወርቅ በረዳ ፋጅራ “ትናንት ረስተነው ነው ያልነገርንህ፤ አቶ ስንታየሁ ከዚህ በኋላ ፖለቲካ እንዳትናገር ፍርድ ቤቱ አዝዟል” አለች። ያም ሆነ ይህ ሁለተኛ አመቱን በያዘው የእነ እስክንድር ዶሴ ዳኛ ተብየዎች በመላሾ የሚሰሩ የመከራ ዳቦ ጋጋሪዎች እንጂ የሕግ ባለሙያዎች አለመሆናቸውን ታዝቤያለሁ።
#የዶሴው ሂደት
እነ እስክንድር በወታደሮች ቁጥጥር ስር ከዋሉበት ጊዜ ጀምሮ ከሃያ በላይ ለሆኑ ጊዜያት በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በአካል ቀርበዋል። በዚሁ ችሎት ጥቂት የማይባሉ የደብዳቤ ክርክሮች ተደርገዋል። መንግሥታዊው ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ በመጠየቁ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እና በዚሁ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በርካታ ‘የፕላዝማ ቴሌቪዥን’ እና የደብዳቤ ክርክሮች ተደርገዋል። ሆኖም ይህ ጉዳይ ከአንድ አመት በላይ ጊዜ ቢጨርስም የፍሬ ነገር ክርክር አልተጀመረም። ዐቃቤ ሕግ የጠቀሳቸው የሰው ምስክሮች በግልፅ ችሎት ይቅረቡ፣ ከመጋረጃ ጀርባ ይቅረቡ ወይስ በዝግ ችሎት ይቅረቡ በሚል ብቻ ሆን ተብሎ የፍትሕ አሰጣጥ ሂደቱ በእጅጉ ተንቀራፏል። በየደረጃው ያሉ ፍርድ ቤቶችና የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መንግሥት ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ሲል ግለሰቦችንና ተቋማትን የሚያጠቃባቸው መሳሪያዎች ሆነዋል። መንግሥት ዐቃቤ ሕግን እንደ ጦር፤ ፍርድ ቤቶችን እንደ ጋሻ በመጠቀም ባልደራስን እየወጋ ይገኛል። ይህም የገዥው ፓርቲ አለቃ አብይ አሕመድ “ባለአደራ፤ ባልደራስ የሚባል ነገር አልቀበልም። ወደ ግልፅ ጦርነት እገባለሁ” በማለት በጎሰሙት የጦርነት ነጋሪት መሰረት እየተፈፀመ ያለ ነው።
በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተደረጉ ችሎቶች በተደጋጋሚ ‘ፕላዝማ ተበላሽቷል፣ ዳኞች ተሟልተው አልተገኙም እና መዝገቡን በቀጠሮው መሰረት አልመረመርንም’ በሚሉ አንካሳ ሰበቦች ሲጎተቱ ከርመዋል።
በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕጉ ቁጥር 184 መሰረት በትዕዛዝ ላይ ይግባኝም ሆነ ሰበር አቤቱታ ሊቀርብበት አይችልም። ይግባኝን አጠቃሎ ማቅረብ የሚቻለው ዋናው ጉዳይ ተጠናቆ ብይን ሲያገኝ ነው። ገና በሂደቱ ላይ ጥቃቅን ጉዳዮችን እያነሱ ይግባኝ ማለት ጉዳዩ በሚገባው የጊዜ ፍጥነት ብይን እንዳያገኝ ስለሚያደርግ በሕግ በማያሻማ መልኩ ተከልክሏል። ጠበቆች ይህንን ለችሎቱ ቢያስረዱም ዳኞች ለዐቃቤ ሕግ ይግባኝና የሰበር አቤቱታ በመፍቀድ የጋሻነት ሚናቸውን እየተወጡ ነው። በዚህ መሀል ተከሳሾች ያለ ብይን ከአመት በላይ እንዲቆዩ አድርጓል፤ እየተጉላሉም ነው።
በመሆኑም ጉዳዩ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከሚገባው በላይ ተጓቷል። በወያኔ/ኢሕአዴግ ዘመን በእነ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል መዝገብ እንደተደረገው ሁሉ ጉዳያቸው በየቀኑ እንዲታይና አፋጣኝ ፍትሕ እንዲሰጣቸው እነ እስክንድር ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት አቶ ገብረ መስቀል ዋቅጋሪ እና ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ደብዳቤ ቢፅፉም ጉዳያቸው ከመጤፍ አልተቆጠረም። ይባስ ብሎ በስም የተጠቀሱት የገዥው ፓርቲ ሹመኞች ከምክትል ዐቃቤ ሕግ አቶ ፈቃዱ ፀጋዬ ቀጥተኛ የስልክ ትዕዛዝ በመቀበል በችሎት የተሰየሙ ዳኞችን ሲያዝዙ ከርመዋል። ዳኞች ለሙያቸው ሊኖራቸው ከሚገባ ስነ ምግባር አንፃር የስብዕና ግምገማ የማድረጉ አስፈላጊነትም ለዚህ ነው።
ዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ታዳሚያን እና መገናኛ ብዙሃን በተገኙበት በግልፅ ችሎት እንዲያቀርብ የእስር ፍርድ ቤት ወስኗል። ዐቃቤ ሕግም ይግባኝ በማለት ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወስዶታል። ይሁን እንጂ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኙን ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል። የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም የይግባኝ ሰሚ ችሎቱን ውሳኔ በማፅደቁ ጉዳዩ ወደ እስር ፍርድ ቤት ተመልሷል። ይኸው ፍርድ ቤት የቀደመ ውሳኔውን በመድገም 21 የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች በግልፅ ችሎት እንዲቀርቡ አዘዘ። ዐቃቤ ሕግ ትዕዛዙን ከተቀበለ በኋላ ሦስት የምስክር ማሰሚያ ቀናትን ብቻውን ተገኝቶ በቀሪዎቹ ሁለት ቀናት ውስጥ “ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረብኩት የሰበር አቤቱታ አለኝ” በሚል ማገጃ ይዞ ቀርቧል። በዚህ ምክንያት አንድ አመት ሙሉ ሲጓተት የከረመው የምስክሮች አሰማም ሂደት አሁን በፍርድ ቤቶች የተዋረድ ክርክር እየተጓተተ ይገኛል። ዐቃቤ ሕግ በግልፅ ችሎት ሊቀርቡ የሚችሉ ምስክሮች እንደሌሉትም ተናግሯል። በመሆኑም መንግሥት ባቀረበው ሀሰተኛ ክስ ላይ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ ችሎቱ መዝገቡን ዘግቶ ዶሴውን በአስቸኳይ ሊያቋርጥ ይገባል።
#ኢትዮጵያዊነትን የሚፀየፈው የችሎት ፕሮቶኮል
የእነ እስክንድርን ችሎት ለመከታተል በአዳራሽ ውስጥ የሚገኙ ታዳሚያን የአለባበስ ገደብ ተጥሎባቸዋል። ችሎቱ ኢትዮጵያዊነትን የሚያነፀባርቁ የሀገር ባሕል እና አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ አልባሳትን ከመፀየፍም አልፎ በግልፅ ከልክሏል። ‘አልባሳቱ ለእስረኞች ድጋፍ እንደመስጠት የሚተረጎሙ በመሆናቸው ሚዛናዊ ሆነን ለመፍረድ ያስቸግሩናልና እንዳይለበሱ’ ሲል የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በግልፅ አዝዟል። ይህ የሀገርን ክብር ከመግፈፉም በተጨማሪ የዜጎችን የፈለጉትን የመልበስ መሰረታዊ መብት የሚጥስ ነው።
በዚህ ምክንያት አንዳዶች የለበሱትን ላለማውለቅ ሲሉ ከችሎቱ ርቀዋል። በተይም የዘወትር አለባበሳቸው ሀገርኛ የሆነ እና በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት ያጌጠ አለባበስን ልምድ ያደረጉ ሰዎች ችሎቱን መታደም አልቻሉም። በእናታቸው ጀርባ ታዝለው ከሄዱ ሕፃናት ራስ ላይ ሳይቀር የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ቀለም የያዙ የክር ኮፍያዎች በካፊያና በብርድ ሰዓት በፖሊስ እጅ ወልቀዋል። ከእጅ ስልኮቻቸው የውስጥ ሰነዶች መካከል የሰንደቅ አላማውን ቀለም የያዙ ፎቶ ግራፎች የያዙ ሰዎች አንድም ችሎቱን እንዳይታደሙ ተከልክለዋለ፤ ሌላም ፎቶ ግራፉን እንዲደመስሱ ተደርጓል።
ይህ ሀገራችን እንዴት ባለ ኢትዮጵያ ጠል ስርዓት እጅ እንደወደቀች ማሳያ ነው። በመሆኑም በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል። ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሊታገሉት የሚገባ የሉዓላዊነት ጉዳይም ነው።
#የወህኒ ቤት አያያዝ
በቂሊንጦ በእነስክንድር ላይ እየተፈጸሙ ያሉ የመብት ጥሰቶች ሊቆሙ ይገባል፡፡
ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ከቃሊቲ እስር ቤት በባሰ እና በከፋ ደረጃ የእሥረኞች መብት የሚረገጥበት ሆኗል። ከሌሎች የፖለቲካም ሆነ የደረቅ ወንጀል እስረኞች በተለየ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚደንት ለሆኑት ለአቶ እስክንድር ነጋና ለድርጅት ጉዳዮች ሓላፊው አቶ ስንታየሁ ቸኮል የወህኒ ቤቱ አያያዝ አስጨናቂ ሆኗል። በተለይም ከ6ኛው ዙር አገር አቀፍ ምርጫ በኋላ ጭቆናዎች ጨምረዋል።
የእነአቶ እስክንድር ነጋ የክስ ጉዳይ የሚታይበት ፍርድ ቤት እስረኞቹ እንዲፈቀድላቸው ያስተላለፋቸው ትዕዛዞች አንዳቸውም ተግባራዊ አልተደረጉም። ለአብነትም እስክንድር ነጋ ከባለቤቱ ከወ/ሮ ሰርካለም ፋሲል እና ከልጁ ናፍቆት እስክንድር ጋር በስልክ እንዳይገናኙ ዛሬም እንደተከለከለ ነው። ቤተሰብ፣ የፓርቲ የትግል አጋሮች፣ የሀይማኖት አባቶችና ሌሎችም እንዳይጠይቁ ክልከላ ይደረግባቸዋል። ጸበልና ቅባቅዱስ አሁንም እንዳይገቡላቸው ተደርገዋል፡፡
በቂሊንጦ ወህኒ ቤት ከሰኞ እስከ አርብ በቀን አንድ ሰው ብቻ ስንቅ እንዲያቀብል ተፈቅዷል፤ ያውም ከአራት እስከ አምስት በሚደርሱ ፖሊሶች ታጅቦ። ስንቅ አቀባዩ ለአንድ ደቂቃ ያህል እንኳን አብሮ መቆየት አይችልም።
በአጠቃላይ እነ እስክንድር ፖለቲካዊ መብቶቻቸውን ተነጥቀዋል። ሰብዓዊ መብቶቻቸው እየተጣሱ ነው። የቀድሞው የሶማሌ ‘ክልል’ መሪ አብዲ ኢሌ በጅግጅጋ ንፁሃንን ከጅብ ጋር ያስር ነበር። በጥላቻ የሰከሩ የቂሊንጦ ወህኒ ቤት ሓላፊዎች አራት እግር አይኑራቸው እንጂ ጂቦች ናቸው።