balderas
Posts by :

የፍትህ ያለህ ፤ እኔም እጠይቃለሁ !!
እስክንድር ነጋን ጨምሮ የባልደራስ አመራሮች በእስር ላይ ሲማቅቁ አመት አለፈ። እነዚህ የፓለቲካ መሪዎች ከታሰሩ ጀምሮ አንድ አመት ሙሉ ያለ ምንም ፍርድ ታስረዋል። ይህ ድርጊት በኢትዮጵያም ሆነ በአለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት የለውም። አንድ ሰው በያዘው የፓለቲካ አመለካከት ሊሞገት እንጂ ሊታሰር አይገባም። ሃገራችን አማራጭ ፓሊሲ አለን ያሉትን ሁሉ ስታስር ነው የኖረችው።
ከዚህ የተነሳ መድብለ ፓርቲ ስርአታችን ሳይጀመር ሳያድግ ቀረ። ይህቺ ሃገር የሁላችን ሆና ሳለ መንግስት ተቋማትን እየተጠቀመ ተቃዋሚዎችን ማሰር ማንገላታት አይችልም። በተለይ አሁን ሁሉን አቀፍ ውይይት እርቅ እንዲመጣ በፓለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩትን የባልደራስ አመራሮች መንግስት ይፍታ። እነዚህ መሪዎች ሰላማዊ ትግላቸውን ይቀጥሉ። ፍትህ ለእስክንድር ነጋ! ፍትህ ለስንታየሁ ቸኮል! ፍትህ አስቴር ስየም ፍትህ ለአስካለ ደምሌና ፍትህ በፓለቲካ አመለካከታቸው ለታሰሩ ሁሉ!
አቶ ገለታው ዘለቀ

እኔ ስሜ ……….. የተባልኩ እጠይቃለሁ !
በሰላማዊ የነፃነት ታጋዮች እስክንድር ነጋ፣ ቀለብ ስዩም ፣ አስካለ ደምሌ እና ስንታየሁ ቸኮል ላይ እየደረሰ ያለው የፍትሕ እጦት፣ የሰብዓዊ መብት ገፈፋ እና ያለ ጥፋታቸው መታሰራቸው የመብት ረገጣ በመሆኑ ፤ በአስቸኳይ ከግፍ እስር እንዲለቀቁ
እጠይቃለሁ !!

” እኔም እጠይቃለሁ ፤ ለምን ?! “
” እኔም እጠይቃለሁ ፤ ለምን ?! “
ፍትሕ ለግፍ እስረኞች !!
በሰላማዊ የነፃነት ታጋዮች ላይ እየደረሰ ያለው የፍትሕ እጦት፣ የሰብዓዊ መብት ገፈፋ እና ያለ ጥፋታቸው መታሰራቸው የመብት ረገጣ መሆኑን በመግለጽ በአስቸኳይ ከግፍ እስር እንዲለቀቁ ” እኔም እጠይቃለሁ ፤ ለምን ?! ” የበይነ መረብ ዘመቻው ዛሬ በይፋ ተጀምሯል ፣ይቀላቀሉ !
ለዘመቻው የተዘጋጀው ፕሮፋይል ይሄ ስለሆነ ፤ ፕሮፋይል ምስልዎን በመቀየር ፣ጽሁፎችን በመጻፍ፣ ምስሎችን በማጋራት ሃሳብዎን ያንፀባርቁ !!
” እኔም እጠይቃለሁ ፤ ለምን ?! “

” እኔም እጠይቃለሁ ፤ ለምን ?! “
የማህበራዊ ድረ-ገፅ ዘመቻ ጥሪ!
” እኔም እጠይቃለሁ ፤ ለምን ?! “
ከጥቅምት አንድ እስከ ሦስት !
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልዳራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ አስቴር ስዩም እና ወሪ/ት አስካለ ደምሌ ከ1 ዓመት በላይ ያለ ጥፋታቸው ፤ ለዲሞክራሲ ፣ ለፍትሕ እና ለእኩልነት በመወገናቸው እና የፖለቲካ አመለካከታቸው እንደ ወንጀል ተቆጥሮ በግፍ ከታሰሩ ከአንድ አመት በላይ ሆኗል።
በዚህ ጊዜ ውስጥ አንዳች የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ አልቀረበባቸውም ። አመት ሙሉ ሲጓተት የከረመው የምስክሮች አሰማም ሂደት ከታችኛው ፍ/ቤት እስከ ሰበር ጠቅላይ ፍ/ቤት ተመሳሳይ ውሳኔ ቢሰጥም ምስክሮችም በግልጽ ችሎች መቅረብ እንዳማይችሉ መንግሥታዊው ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በተደጋጋሚ ገልጿል ። በዚህ መሐል ንጹሃን ያለ ብይን ከአንድ አመት በላይ በግፍ እስር እንዲቆዩ ተደርገው እየተጉላሉ ይገኛሉ ።
በእስር ቤት ውስጥ ከሌሎች እስረኞች በተለየ በአቶ እስክንድር ነጋ እና በአቶ ስንታየሁ ቸኮል ላይ የወህኒ ቤቱ አያያዝ እጅግ በጣም የከፋ ሆኗል ። ይህንን አስከፊ የእስር ቤት አያያዝ አስመልክቶ ፍርድ ቤት እስረኞቹን አስመልክቶ
የቂሊንጦ ወህኒ ቤት አፋጣኝ ማስተካከያ እንዲያደርግ ያስተላለፋቸው ትዕዛዞች አንዳቸውም ተግባራዊ አልተደረጉም ። እነ እስክንድር ፖለቲካዊ መብቶቻቸውን በመንግስት በሃይል ተነጥቀዋል ፣ ሰብዓዊ መብቶቻቸው እየተጣሰ ይገኛል።
ይህም በመሆኑ ፦ በሰላማዊ የነፃነት ታጋዮች ላይ እየደረሰ ያለው መንግስታዊ በደል ፣ የፍትሕ እጦት፣ የሰብዓዊ መብት ገፈፋ እና ያለ ጥፋታቸው መታሰራቸው አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ በአስቸኳይ ከግፍ እስር እንዲለቀቅ የሚጠይቅ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ የሆነ ” እኔም እጠይቃለሁ ፤ ለምን ?! ” በሚል መሪ ቃል የሦስት ቀን የበይነብ ዘመቻ ይደረጋል፡፡
ዘመቻው ሰኞ ከጥቅምት 1 እስከ ረብዕ ጥቅምት 3/2013 ዓ.ም የሚደረግ ሲሆን፤ የፖለቲካ እስረኞች እነ እስክንድር ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብርና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ይቀርባሉ። መረጃዎች በመለዋወጥ ፣ ለኢትዮጵያውያን፣ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰቡና ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በማሳወቅ ላይ ያተኩራል፡፡
የበይነ መርብ ዘመቻው በፌስ ቡክ፣ በቲውተር ፣ በኢንስታግራም፣ በአገር ውስጥና በውጭ ባሉ ሬዲዬ፣ ቴሌቪዥን ፣ በምስል በድምፅ በፎቶና በካርቶን ስዕሎች፣ በቪዲዬዎች ይደገፋል። እነኚህ መልዕክት አስተላላፊ ዘዴዎች በመዓከል ደረጃ የሚዘጋጁ እንዳሉ ሆነው ፤ የዘመቻውን ዋና ዓላማ ከግብ የሚያደርስ የትኛውንም አመራጭ ዘዴ ማንም ሰው በራሱ ፈጠራ መጠቀም ይቻላል ።
በዚህም መሠረት ፤ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች ፣ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ፣ የማህበረሰብ አንቂዎች ፣ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በሚካሄደው የበይነ መርብ ዘመቻ እንደተሳተፉ እና የሚመለከታችሁን ተግባራት እንድታከናውኑ በአክብሮት እንጠይቃለን።
” እኔም እጠይቃለሁ ፤ ለምን ?! “

እስር ቤት፤ ደርሶ መልስ
(ጌጥዬ ያለው)
የገዥው ፓርቲ የጎበዝ አለቃ (በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የምርጫና የምርጫ ስነ ስርዓት አዋጅ መሰረት በጉባኤ ያልተመረጠ) አብይ አሕመድ እንዳልተቀባ ንጉስ ድንገት ሥልጣን ላይ ጉች ካለ በኋላ ሆይ ሆይታው ብዙ ነበር። ሆኖም የጫጉላ ሽርሽሩ ከአንድ የጎጃም መኳንንት ሰርግና ምላሽ የበለጠ ጊዜ አልወሰደም። ከዓመት ባነሰ ጊዜ እውነቱ ተገለጠ። እውነተኛ ማንነቱን ከሕዝብ ለመደበቅ የስለላና የደህንነት ሙያው እምብዛም አልጠቀመውም ማለት ይቻላል።
የማይሰለቸው ፅኑ የነፃነት ታጋይ #እስክንድር ነጋ ብቅ አለና አስለፈለፈው። ‘ሙሴ’ ያሉት ሰው ሰዎችን በጅምላ ገድሎ፤ በነሲብ የሚቀብር ጨፍጫፊ ሆነ።
የጎበዝ አለቃው ከኤርትራ ጋር የነበረውን ቁርሾ ከልቶ አንድነት ሲፈጥር፤ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ሽርክ ሲሆን ዓለም በአድናቆት ዘግቦታል። ወቅቱ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሜክሲኳውያን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የግንብ አጥር ለማሳጠር ያወጀበት ነበርና “አሜሪካ ላይ የጥል ግንብ ሲገነባ ምስራቅ አፍሪካ ላይ የፍቅር ድልድይ ተሠራ” እያሉ በተለይ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን በንፅፅር ዘግበውታል።
በተመሳሳይ #የአብይ አሕመድ የጫጉላ ሰሞን ሳይደበዝዝ የዓለም የፕሬስ ቀን በአዲስ አበባ ተከብሯል። በዕለቱ ተዘግተው የነበሩ ገፀ ድሮች ተከፍተዋል፣ ሕትመታቸው ተቋርጠው የነበሩ ጋዜጦችና መፅሔቶች ዳግም ወደ ሥራ እንዲመለሱ በር ተከፍቷል፣ ስደተኛ የነበሩ ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙሃን ተመልሰዋል ወዘተ በሚል በዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ (CPJ) ጭምር ተመስግነዋል። በርግጥ በዓሉ የተከበረው በመንግሥት እና በሕዝብ ግንኙነት ሠራተኞቹ እንጂ በጋዜጠኞች ነበር ለማለት ያስቸግራል።
የሆነው ሆኖ የአዲስ አበቤው እስክንድር ነጋ እንቅስቃሴ የአብይ አሕመድን ጸረ አንድነት፣ ጸረ ዴሞክራሲ፣ ጸረ ታሪክ፣ ጸረ ቅርስ ከሁሉም በላይ ጸረ አማራ ዛር አውርዶ አስለፍልፎታል። ግልፅ ጦርነት ከማወጅም ባለፈ “ታስሮ ጀግና መሆን የሚፈልግ ጋዜጠኛ ነው ያለው” ተባለ። ይህ አደገኛ ንግግር ነው፤ ጥቂት የማይባሉ ጋዜጠኞችን እንዳይፅፉና እንዳይናገሩ አሸማቋል። ቅቤ አንጓች ጋዜጠኞችም እንደ ውዳሴ ማርያም በነጋ በጠባ ደጋግመውታል። በአንዳንድ የግል መገናኛ ብዙሃን፤ አርታኢዎች ዘጋቢዎችን አንገት የሚያስደፉበት መከራከሪያ ብሎም የየማለዳ ስብሰባዎች (Morning briefing) መክፈቻ መሆኑንም ሰምቻለሁ። ንግግሩ የቤተ መንግሥቱን አጥር ተራምዶ ፎቶ ግራፍ መነሳትን እንደ ታላቅ የጋዜጠኝነት ጀብዱ ከሚቆጥሩና ጆሴፍ ፑልቲዘርን የሆኑ ከሚመስላቸው የጋዜጠኝነት ደናግላን አንደበት ላይም አይጠፋም።
ጠቅላይ ሚንስትር ተብየው አምባገነናዊ ዘረኛ ሥልጣኑን የሚያስጠብቅባቸው ሦስት መሰረታዊ ሃይሎች አሉ። 1ኛው ወታደራዊ ሃይሉ ነው። 2ኛው የስለላ መዋቅሩ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “የማሕበራዊ ሚዲያ ሰራዊት” የሚሉት ቅልብተኛ ፌስቡክ ጎርጓሪ ነው። 3ኛው የሥልጣን ማስጠበቂያ ሃይል አዲስ አሰላለፍ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ቅርፁና አቀራረቡ ይለያይ እንጂ ነባር ነው። በትነግ ጊዜ ‘ዲጅታል ወያኔ’ በሚል መጠሪያ በቅርፅም ሆነ በአደረጃጀት ሳይለይ ይኸው ራሱ ነበር፤ አለም። በነገሥታቱ ጊዜም ቴክኖሎጂው ስላልነበር እንጂ ድርጊቱ ሥራ ላይ ውሏል። ሕዝባዊ ቅቡልነት የጎደላቸው መሪዎች ሲነግሱ ሀሰተኛ አፈ ታሪኮችን ያስነግሩ ነበር። ለእረኞችና ለአዝማሪዎች ግጥም እየተሰጠ መወድሰ ንጉስ እንዲስፋፋ ይደረጋል።
ጋዜጠኞችን ወደ ሚያሸማቅቁበት ፍረጃ ልመለስ፤ በየሀረጉ አዝማች እየከፈቱና እየዘጉ የጎበዝ አለቃውን አሸማቃቂ ንግግር ደጋግመው የሚያዜሙት በ3ኛው የዘረኛ ሥልጣን ማስጠበቂያ ፈርጅ የተሰለፉት ፌስቡክ ጎርጓሪዎች ናቸው። እኔም ይህን የእስር ጉዳይ ስፅፍ ‘ጀግና ለመባል ነው የታሰርከው’ የሚል ቢኖር ‘ጀግንነት ጥሩ ነውና አብረን እንጀግን’ ብል ኢ- ግብረ ገባዊነት የሚያስብል አይመስለኝም።
እንኳንስ ትርጉሙ ረክሶ ለመላጣውም፤ ለጎፈሬውም የተናኘው ጀግንነት ጥቂቶች ብቻ የሚታደሉት እውነተኛው ጀግንነትም ከወህኒ ቤት የሚገኝ ቢሆን መከራው ብዙ ነው። በዚህ መልኩ ሊያገኘው የሚፈልግም ያለ አይመስለኝም።
የወህኒ ቤቶቻችንን አስከፊነት የዜግነት ማህበራዊ ዋስትናቸውን ተነጥቀው በጓዳና የሚኖሩ ወንድሞቻችን ይነግሩናል። ፀሐዩን፣ ቁሩን፣ ነፋሱን፣ አቧራውን፣ ርሀቡን ጥሙን ተቋቁመው በጎዳና ሲኖሩ በአንዳንድ ወንጀሎች ተጠርጥረው እስር ቤት ይገባሉ። ቤት፣ ምግብና ልብስም በእስረኛ ወግ ያገኛሉ። ሆኖም የተሟላ ኑሮ ካለው እስረኛ እኩል የመፈቻ ጊዜያቸውን በጉጉት ይጠብቃሉ።
መታሰር የሚያጀግን ቢሆን ኖሮ ያጀግናል ባዩ ራሱ ከምኒልክ ቤተ መንግሥት ወጥቶ ቃሊቲ በተገኘ ነበር። እስረኞች ጀግና የሆኑት ለመርህ ቆመው ወንበዴን በመታገላቸው እንጂ እጃቸው ውስጥ ሰንሰለት ስለገባ አይደለም።
#እስራት (አምና)
በገዳ ማሕበር ርዕዮተ መንደር እንደሚመራ የገለፀው የአብይ አሕመድ ቡድን ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ ሦስት ጊዜ አስሮኛል። ሦስቱም በአማካኝ በየአንድ አመት ልዩነቶች የተደረጉ ናቸው። በመጀመሪያው በግልፅ የተነገረኝ ወይም የቀረበብኝ ክስ አልነበረም። ከቀላል ማስፈራሪያነት የዘለለ አልበረም። የአቤ ጉበኛን ሀውልት እያየሁ አድጌ፤ ከእስክንድር ነጋ ጋር እየኖርኩ ወንበዴን ብፈራ ታሪክስ ይቅር ይለኝ ይሆን?
2ኛው ባለፈው ዓመት በተከበረው ‘ኢሬቻ’ የሚሉት የጣኦት አምልኮ ቀን ዋዜማ ላይ የተፈፀመ ሲሆን ክሱ በመርማሪ ፖሊሱ በቢሮ ውስጥ ተነቦልኛል። ወንጀል የተባሉትም 1ኛ. ‘መሪ አልባው የአማራ ሕዝብ’ በሚል ርዕስ በፍትሕ መፅሔት የፃፍኩት መጣጥፍ ነው። 2ኛ. የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲን (ባልደራስ) ቢሮ በመጠቀም ወጣቶችን ለሽብር ማደራጀት የሚል ነው። ሦስት ሲቪል ለባሽ ፖሊሶች ቃሊቲ፤ አውቶብስ መነኻሪያ አካባቢ ከሚገኘው የባልደራስ ቢሮ ውስጥ አግኝተው በአቅራቢያ ወደ ሚገኘው የፖሊስ መምሪያ ከወሰዱኝ በኋላ የተረከቡኝ ፖሊሶች ስለተጠረጠርኩበት ወንጀልም ሆነ ስለ እኔ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ያመጡኝ ፖሊሶችም የአንድ ደህንነት ስም ጠርተው በእርሱ ትዕዛዝ ማምጣታቸውን ከመግለፃቸው ውጭ የነገሯቸው መረጃ አልነበረም። ከአንድ ጠባቂ ወታደር ጋር ቢሯቸው በር ላይ ረፋድ 5 ሰዓት ገደማ ጀምሮ ተቀምጨ የሚፈታኝም፤ የሚያስረኝም ጠፋ። የቀኑ ፈረቃ ፖሊሶችና ሌሎች ሠራተኞች ወጥተው የማታ ፖሊሶች ተተኩ። እስረኛ አልተባለም እንጂ ጠባቂየም ከሥሬ ንቅንቅ አላለም። ስልክ እየደወለ ‘ኑ ተቀበሉኝ’ በማለት ይነጫነጫል። በዚህ መሃል አንድ መርማሪ ፖሊስ ተገዶ ቃሌን እንዲቀበልና እንዲያስረኝ ታዘዘ። እንዳላመልጥ ሲጠብቀኝ የዋለው ወታደርም ተልዕኮውን ጨርሶ ከፖሊስ ጣቢያው ወጣ። መርማሪው ካመጡኝ ፖሊሶች የተቀበለውን የፍትሕ መፅሔት ቅጂ የሽፋን ገፆች እያገላበጠ እያየ “ምንድን ነው የፃፍከው?” አለኝ።
“አማሮች እየተመረጡ በጅምላ እየተገደሉ ነው። ከጅምላ ጭፍጨፋዎች መካከል በቅርቡ በመተከል የተፈፀመውን የሚተርክ መጣጥፍ ነው የፃፍኩት። ይህ ሕዝብ በየቦታው የሚጨፈጨፈው መሪ ስለሌለው ነው ብየ አስባለሁ” አልኩት። የሚበቃውን ያህል ትንሽ ትኩር ብሎ መፅሄቱን አየው። ወደ ውስጥ ገፅ ገብቶ ግን አንድም አንቀፅ ሲያነብ አላየሁትም። ለረጅም ሰዓት የጠረንጴዛው የውስጥ ተሳቢ ኪስ ውስጥ ስለነበር የተከሰስኩበትን ፅሁፍ በደንብ አንብቦት ይሆናል የሚል ግምት አለኝ።
“ወጣቶችን ለሽብር አደራጅተሀል” መባሌን በተመለከተም ለሕጋዊ የፖለቲካ ትግል ከማደራጀቴ በቀር አንዳች የጥፋት እንቅስቃሴ አለማድረጌን አስረዳሁ።
ቀጥሎ ባልተስተካከለ ሁኔታ (Unconditionally) ከመርማሪው ቢሮ ወጥቼ ወደ ጠባቧ የእስር ክፍል ገባሁ። የዚህ ክፍል የሌሊቱ ተረኛ ሓላፊ “ባልተሟላ የአስተሳሰር የመረጃ ጥንቅር (Unconditionally) አላስርም” በማለቷ
ከመርማሪው ተቀብሎ ከወሰደኝ ሌላ ፖሊስ ጋር ትንሽ ተከራከሩ። የክርክሯ ትርጉም የገባኝ በጧት ፍርድ ቤት እንዲያቀርቡኝ ስጠይቅ ነው። ከፖሊስ ጣቢያው የተለመደ የአሠራር ደንብ ውጭ ባልተሟላ ሁኔታ የታሠርኩት እዚያው ታግቼ ሰንብቼ ፍርድ ቤት ሳልቀርብ ክስም ሳይመሰረትብኝ በነፃ እንድለቀቅ የደህንነት መሥሪያ ቤቱ በመወሰኑ ነው። ለአምስት ቀናት ያህል ቃሊቲ ፖሊስ መምሪያ ስሰነብት መጀመሪያ ከጠየቀኝ መርማሪ ፖሊስ በተጨማሪ የተለያዩ የፖሊስ ሓላፊዎች እየተመላለሱ ስለመፅሔቱና ስለ ፅሁፉ ጠይቀውኛል። ከባልደራስ ጋር ስለተያያዘው ጉዳይ ግን እምብዛም አላነሱም። አንዳንድ ጥያቄዎቻቸው ተመስገን ደሳለኝን እንጂ ለጋዜጠኝነትም ሆነ ለፖለቲካ ለጋ የሆነ አምደኛን ያልያዙ አስመስለዋቸው ነበር። ለአብነትም “የመፅሔቱ የገቢ ምንጭ ምንድን ነው? የሚል ይገኝበታል። መልሴ “እኔ ምን አውቄ” የሚል ነበር።
ልፈታ ሰዓታት ሲቀሩት አንድ የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ባልደረባ እንደሆነ የነገረኝ ሰው አነጋገረኝ። ኮፍያ ያደረገ፣ ወፍራም ጃኬት የለበሰ ሲሆን የተረጋጋና ቀይ ነው። ከንግግሩ አንዳንድ ድምፀቶቹ የትግርኛ ቋንቋ ተፅዕኖ ያለው ቢያስመስለውም ትግርኛ ተናጋሪ ለመሆኑ ርግጠኛ መሆን አልቻልኩም። ከአስመራ ለአብይ አሕመድ የተሰጠ ዳረንጎት ይሆናል የሚል ግምት አለኝ። ባለመግባባትና በጦፈ ክርክር በግምት ለ2 ሰዓታት ያህል ተነጋግረናል። ይሄኛው የባልደራስን ጉዳይ ፈፅሞ አላነሳም። ረጅም ሰዓት ወስዶ የተናገረው ኢትዮጵያ እሳት ውስጥ እንደሆነችና ከእሳት ለማውጣት ከመንግሥት ጋር መተባበር እንደሚገባ ነው። በተለይም እሳቱ ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ እንደማይገባ እያስረዳኝ ብዙ ደቂቃ ወስዷል። የእኔ ሃሳብ ‘እሳት ሆኖ እየፈጃት ያለው ራሱ መንግሥት ነው’ የሚል ነበር። በዚህ ጉዳይ ስንሟገት ነው ጊዜውን የጨረስነው። የማታው አዳሬ ሰላማዊ ስላልነበር ውስጤም ሆነ ውጫዊ ገፅታየ በቁጣ የተሞላ ነበርና አቋሜን ያለአንዳች ማለዘቢያ እንድገልፅ ረድቶኛል። በመጨረሻም እንድፈታ ፖሊሶችን አዝዞ ሄደ። ነገር ግን የፖሊስ መምሪያው ሓላፊ ነው መፍታት ያለበት ስለተባለ እሳቸው እስኪመጡ ረፋድ ላይ መፈታት ስችል እስከ ቀኑ አስር ሰዓት ገደማ ለመቆየት ተገደድኩ። በዚህ ጊዜም ‘ኢሬቻ እስከሚያልፍ አስራችሁት ቆዩ’ መባላቸውን ፖሊሶች ሲያወሩ ሰማሁ። በነገራችን ላይ በሰሞኑ እስርም ፍርዴን ከጨረስኩ በኋላ ለተጨማሪ 20 ቀናት የታሰርኩት ኢሬቻ እስከሚያልፍ ነው የሚል ግምት አለኝ።
ከዚህ በኋላ በአማራ ሕዝብ ላይ ተደጋጋሚ ጅምላ ጭፍጨፋዎች በመተከል፣ በወለጋ፣ በኢሉባቡር ወዘተ ተፈፅመዋል። ከጭፍጨፋም ተሸጋግሮ ከተሞች ወድመዋል። ይህ ሕዝብ ይባስ ብሎ የአብይ መፈንቅለ መንግሥት የፈጠረውን ጦርነት ተሸካሚ ሆኗል። ሲያጠቃ አፈግፍግ እያለ ማዕከላዊ መንግሥት ተብየው እጁን ጠፍንጎ ይዞ እያስገረፈው ይገኛል።
#እስራት (ዘንድሮ)
ከነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ መስከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ለ50 ቀናት ያህል በአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እና በቃሊቲ ወህኒ ቤት ታስሬያለሁ። ይሄኛውን እስራት የፈረደብኝም ሆነ የከሰሰኝ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው። ይህ ችሎት የእነ እስክንድር ነጋን (5 ሰዎች) ዶሴ እየዳኘ ያለ ሲሆን ሦስት ዳኞች አሉት። የቀኝ ዳኛዋ #እጥፍ ወርቅ በረዳ ፋጀራ ሲባሉ የግራ ዳኛው ደግሞ #ፈየራ ተሬሳ ጉተማ ናቸው። #ሳሙኤል ታደሰ የመሀል ዳኛው ናቸው። ደህንነት መሥሪያ ቤቱ ወይም/እና ቤተ መንግሥቱ ከጀርባ እንዳለ ቢጠረጠርም ከሳሾቼም ፈራጆቼም እነኝህ ግለሰቦች ናቸው።
የክሱ መሰረታዊ ሃሳብ በእነ እስክንድር ዶሴ ላይ በባልደራስ ጋዜጣ የፃፍኩት ሀተታ ነው። የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች ማለትም እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ የተከሰሱበት ተግባር ሀሰተኛ መሆን እና ክሱ በአስቸኳይ እንዲቋረጥ የሚያትት መጣጥፍ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ዳኞች ከገዥው ፓርቲ ፖለቲከኞች ቀጥተኛ ትዕዛዞችን እየተቀበሉ የሚፈርዱ መሆናቸውን ያተተ ሲሆን እስረኞች በወህኒ ቤት እየደረሰባቸው ያለውን የመብት ረገጣም አንስቷል። የዳኞች ክስ “ታማኝነታችንን አጥፍተሃል። ከአስፈፃሚው የመንግሥት አካል ትዕዛዝ አልተቀበልንም” የሚል ነው።
በዚህ ጉዳይ አንደኛ ተከሳሽ ሆኘ በደረሰኝ የመጥሪያ ደብዳቤ መሰረት ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ከላይ በተጠቀሰው ችሎት ቀረብኩ። በዚሁ ዕለት ከእነ እስክንድር ጠበቆች መካከል አንዱ ቤተማርያም አለማየሁ ሁለተኛ ተከሳሽ ሆኖ ሲቀርብ አሐዱ ራዲዮ ሦስተኛ ተከሳሽ ሆኖ በሥራ አስኪያጁና በጠበቃው ተወክሎ ቀረበ። ቤተ ማርያምን ቃለ መጠይቅ አድርጎ አሐዱ በሠራው ዜና ላይ “ችሎቱን ፖለቲካዊ ነው ብላችኋል” የሚል ነው የ2ኛ እና የ3ኛ ተከሳሾች ክስ። አሐዱ ጉዳዩ ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ መብት ጋር እንደሚያያዝ ካስረዳ በኋላ “ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የሚዳኝ ችሎት” ለማለት አስቦ “ፖለቲካዊ ችሎት” ማለቱንና ይህም ዘጋቢው ባለማወቅ የፈጠረው ስህተት እንጂ ችሎቱ ፖለቲካዊ ነው ብሎ እንደማያምን በገደምዳሜው በማስረዳቱ በነፃ ተሰናበተ። በተጨማሪም ቢሮ ተጠርቷል፤ ዳጎስ ያለ ምክር ሳይቀበል አይቀርም። ጠበቃ ቤተማርያምም ቃለ መጠይቅ የሰጠበት ራዲዮ ጣቢያ በነፃ ተሰናብቶ እርሱ ሊከሰስ የሚችልበት ምክንያት ባለመኖሩ በነፃ ተሰናብቷል። ሆኖም ክሱ ግን ፖለቲካዊ ነው ብሎ እንደሚያምን፤ ይህንንም በተደጋጋሚ በችሎት ላይና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃንም ሲናገር መቆየቱን አብራርቷል። ወደፊትም ይህንን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከማስረገጥም በላይ እነ እስክንድር ነጋ ለያዙት ሀቅ ሲል ከጥብቅና ሥራው በተጨማሪ የመብት አቀንቃኝነት ተግባሩንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል። እስከዚያ ዕለት ድረስ የነበረው የመብት ተቆርቋሪነት እንቅስቃሴ አነስተኛ በመሆኑ እንደሚቆጭም ገልጿል። አሁን ወደ ራሴ ዶሴ ልመለስ፦
በመሀል ዳኛው ችሎት ላይ የተነበበው ዘለግ ያለ መጣጥፍ “መንግሥት በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የመሰረተው ሀሰተኛ ክስ በአስቸኳይ ይቋረጥ” የሚል የርዕሰ አንቀፅ ርዕስ አለው። የተነሱት የክስ ጥያቄዎች ሦስት ናቸው፦
1ኛ. የፍርድ ቤቱን ተዓማኒነት መንጠቅ
2ኛ. የዳኝነት ነፃነት እንደሌለ መጥቀስ
3ኛ. ኢ-ሚዛናዊ ትንታኔ መኖር ናቸው።
#መልሶቼ
የፍርድ ቤቱን ተዓማኒነት በተመለከተ አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በተደጋጋሚ ስዳስሰውና ስገመግመው እንደኖርኩ አስረዳሁ። ፅሁፉም የግምገማው ውጤት ሲሆን ዳሰሳዎቼ ሁሉ ያረጋገጡልኝ ችሎቱ ገለልተኛ አለመሆኑን እንደሆነ ጠቅሻለሁ። “በፅሁፉ እንደገለፅኩት መንግሥት እነ እስክንድር ነጋን እና ባልደራስን ለመውጋት ዐቃቤ ሕግን እንደ ጦር፣ ፍርድ ቤቶችን ደግሞ እንደ ጋሻ እየተጠቀመ መሆኑን አምንበታለሁ። ወደፊትም በድጋሜ ልፅፈው እችላለሁ” አልኩ። በዕለቱ በዋለው ችሎት ሰብሳቢ ዳኛው የተለመደ ርጋታቸውና አባቱ እንደተቆጣው ልጅ መቅለስለሳቸው ከትሕትና ጋር
GtyeBald, [11.10.21 22:51]
እንደተጠበቀ ቢሆንም ሌሎች ሁለቱ ዳኞች ግን ከወትሮው በተለየ ፍጥነት እና ትኩረት ይታይባቸው ነበር። ጥያቄዎቹ ሲጠቃለሉ ሦስት ፈርጅ ይኑራቸው እንጂ ከላይ ከላይ ሲጠይቁኝ የነበሩት እነኝህ ናቸው። በጥቅሉ በዕለቱ ችሎት የተሰየሙት ሦስቱም ዳኞች ናቸው ከሚባል ይልቅ እጥፍወርቅና ፈየራ ከሳሽ ዐቃቢያነ ሕጎች፤ ሳሙኤል ደግሞ ወላዋይ ዳኛ ነበሩ ቢባል ገላጭ ነው።
#ሚዛናዊነት ሲባል
በጋዜጠኝነት ሚዛናዊነት (balance) ሲባል የዜጎች ፍትሐዊ የሚዲያ ተገልጋይነት ማለት ነው። አንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም ለጥቂት ወገኖች ብቻ ድምፅ እንዳይሆንና ሌላው ወገን እንዳይታፈን የሚያትት ነው። ሚዛናዊነት ከዜና አላባውያን፤ ምናልባትም ከጋዜጠኝነት አላባውያን መካከል አንዱ ነው። ሆኖም ሚዛናዊ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ሙያው ይመክራል እንጂ ጋዜጠኛም ይሁን ሌላ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ “ለምን ሚዛናዊ አልሆንክም” ተብሎ በሕግ አይገደድም። እርሱ የሰሜን ዋልታ ልሳን ነኝ ካለ፤ ደቡብ ዋልታ እንዲሄድ ወይም የምድር ወገብ ላይ እንዲቆም ሕግ አያስገድደውም።
ሙያና ሙያተኝነት የሚከበርበት ሀገር ሲሆን የሙያ ማሕበራት ይህንን ሊገሩና የአስታራቂነት ሚናውን ሊወስዱ ይችላሉ። ዜና ከቤተመንግስት ተፅፎ በሚመጣባት ኢትዮጵያ ግን የሚዛናዊነትን ጉዳይ አንስቶ የሚከስ ዳኛ ሸረኛ እንጂ የሕግ ባለሙያ ሊሆን አይችልም። ስለ ጋዜጠኝነት የሙያ ስነ ምግባር ከመጨነቁ በፊትም የሕግ ሙያዊ ስብዕናውን ሊሸጥ አይገባም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሚዛናዊ መሆን ተገቢ ነው በሚል ተስማምተን እንቀጥል። ከላይ በስም የተጠቀሱት ሦስት ዳኞች የመንግሥት ሹመኞች ናቸው። መንግሥት ደግሞ ራሱ የሚዲያ ባለቤት ነው። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተባሉ አንደበቶች አሉት። እነኝህ በውስጣቸው በርካታ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች ያሏቸው ናቸው። የየብሔሮች መገናኛ ብዙሃን ጣቢያዎች አሉ። ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና ዋልታ ቴሌቪዥን የተባሉ የገዥው ፓርቲ ንብረቶች አሉ። 3ቱ ሹመኛ ዳኞች ከጠቀስኳቸው በተጨማሪ ሌሎች በርካታ አንደበቶችን መጠቀም ይችላሉ። ድምፅ አልባ አይደሉም። ጋዜጠኝነት ደግሞ የድምፅ አልባዎች ድምፅ እንጂ የመንግሥት አጃቢ አይደለም። በመሆኑም የነፃገት ታጋዮች፤ የግፍ እስረኞች ድምፅ ነኝ ስል ሹመኞች ለእኛም ጩህ ሊሉኝ አይገባም።
በአጠቃላይ ክሱ እነ እስክንድር ነጋን ታሪክ አልባ የማድረግ እንቅስቃሴ ነው። ይህ የግፍ ክስ፣ የግፍ እስር፣ የግፍ ችሎት ታሪኩ ዕለት በዕለት ተሰንዶ ለመጭው ትውልድ እንዳይተላለፍ ለማድረግ ያለመ ነው። ለጊዜው አልተሳካም።
ጦርነት የግድ ከሆነ !
የሀሰት ክስ እየተመሰረተብኝ በእስር ያሳለፍኳቸው ዓመታት ይኸው ዘንድሮ አሥራ አንድን ረግጠው አልፈዋል፡፡ በወራት መቁጠር ካቆምኹኝ እንደሆነ ቆይቻለሁ፡፡ እሥረኛውን ዓመት አሰልቼ መቶ ሃያ ሲሆንብኝ፣ ለእኔም ለአድማጩም ስለ ወራት ማውራቱ ይሻላል ብዬ ወሰንኹ፡፡ ያለቅጥ ከብዶ እንዲታይ አልፈልግም፡፡ ለዚህች ሀገር ዲሞክራሲ ከእኔ በላይ የከፍሉትን ሳስብ አንገቴን እደፋለሁ፡፡ አካላቸው የጎደለ፣ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉት ደግሞ አንደበቴን ይቆልፉታል፡፡
የአሥራ አንዱን ዓመታት እስር ያሳለፍኩት እየታሰርኩ እየተፈታኹ እንጂ፣ በአንድ ግዜ ቆይታ አልነበረም፡፡ በእስረኛ ቋንቋ “ተመላላሽ” እባላለሁ፡፡ ይኸኛው አሥራኛው እስሬ መሆኑ ነው፡፡ በአሳሪዎቹ አያያዝ ከሆነ፣ ይኸኛው ከዘጠኙ መሠረታዊ የሆነ ልዩነት አላየሁበትም፡፡ በመጀመሪያዎቹ ስድስት እስሮች በአብዛኛው በፖሊስ ተደብድቤያለሁ፡፡ በመጀመሪያው እስር የምታቃጥል ጥፊ አቅምሰውኛል፡፡ ያቺ ጥፊ ቀስ ብላ ተገልብጦ ወደ መገረፍ (“ወፌ ላላ” ይሉታል እስረኞች) አድጋለች፡፡ በተለምዶ አባባል፣ታሪኩ ብዙ ነው፡፡ ሆኖም፣ የእኔ መደብደብና መገፋት ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር ከለብ ለብ የሚያልፍ አይደለም፡፡ እንዳላጋንን እሰጋለሁ፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ የትህትና አበባል አይደለም፡፡ እውነታው ነው፡፡
ይህም ሆኖ፣ ይኸኛው እስር እንደ አዲስም የምቆጥረው ነው፡፡ በዘጠኙ እስሮች ለህዝብና ለሀገር ዋጋ የከፈሉትን —- የሞቱትን፣ የቆሰሉትን፣ የተሰደዱትን፣ የተገደሉትን —- በአደባባይ ክብር ስንነፍጋቸው አላስታውስም፡፡ ግፍ ስሪዎቹ ሳይቀሩ ግፍ የተቀበሉትን የሞራል ልዕልና ለመካድ ከመንገድ ወጥተው ሲባክኑ አላስተዋልኹም፡፡ ከ1966ቱ አብዮት በኋላ የተዳከሙ ቢሆኑም፣ “ይሉኝታ”፣ “ጨዋነት” የምንላቸው ነገሮች ትዝ ይሉኛል፡፡
አሁን ነገሮች ተለዋውጠዋል፡፡ በዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን፣ ይህ ሁሉ “ነበር” ሆኗል፡፡ “አይነኬ” ብሎ ነገር ቀርቷል፡፡ ሁሉም ይንጓጠጣል፣ ይሾብፍታል፣ ይሳቅበታል፣ ይጣጣላል፣ ይዋረዳል፡፡ ይኸው በዚህ ዙር እስሬ የድርሻዬን ተቀብያለሁ፡፡ “ጀግና” ተብዬ አልቀረኹም፡፡ እሰዬው! ለሀገር፣ ለህዝብና ለእውነት የሚከፈለው ዋጋ በጨመረ ቁጥር፣ የመጨረሻው ፍሬ —-ዲሞክራሲ! አንድነት! —- ይበልጥ ጣፋጭ ነው የሚሆነው፡፡
ይህን ጉዳይ በዚሁ ብንዘጋው ምነኛ መልካም በሆነ፡፡ ግን ሌላ መዘዝ አለው፡፡ “ የጋራ ጀግና” እንዳይኖረን መደረጉ አንድ አደጋ ነው፡፡ “የጋራ ቁስል” እንዳይኖረን እየተደረገ መሆኑ ደግሞ፣ አደጋውን ይበልጥ ያሳድገዋል፡፡ ያለ ጋራ ጀግናም፣ ያለ ጋራ ቁስልም እንደ ሀገር መኖር አንችልም፡፡ ያንዣበበብን አደጋ በስሜኑ የሀገራችን ክፍል ያለው ጦርነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡
ከሰሜን የጦርነት ቀጠናዎች —- ትግራይ፣ ዐማራና አፋር—- የሚወጡ ዜናዎች የጅምላ ግድያዎችና አስገድዶ መደፈሮች መፈፀማቸውን እያበሰሩን ይገኛሉ፡፡ የእኛ ምላሽ ምን ሆነ? ለሁሉም ሰለባዎች እንጀታችን ባባ? ለሁሉም ሰለባዎች የሀዘን አንገታችንን ደፋን? አላደረግነውም! “የማይካድራ ጭፍጨፋ አልተፈፀመም” ብለን ሽንጣችንን ይዘን የምንክድ ሰዎች፣ “የአክሱም ጭፍጨፋ ተፈፅሟል” ብለን ብራ ከረዬ ስንል ዓይናችንን አናሽም፡፡ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በአክሱም ጭፍጨፋ ስለመፈፀሙ መግለጫ ሲያወጡ አምርረን የምንከፋ ሰዎች፣ ስለማይካድራ ተመሳሳይ መግለጫ ሲያወጡ ከልብ እንፈነጥዛለን፡፡
የአንዱ ሞት የጋ ሞት፣ የአንዱ ቁስል የጋራ ቁስል፣ የአንዱ በደል የጋራ በደል፣ የአንዱ ውድቀት የጋራ ውድቀት መሆኑ አልታይ ብሎናል፡፡ እንዲሁም፣ ይባስ ብሎ፣ የአንዱ ሞት፣ ቁስልና በደል የእኛ ድል የሚመስለን በጣም በዝተናል፡፡ የህፃናትና የአረጋዊያን ሰቆቃ እንኳን ልባችንን አልጋራ ብሎናል፡፡ አሳሳቢ ነው – በእጅጉ አሳሳቢ፡፡
እኛ እኮ እንዲህ አልነበርንም! እኛ እኮ ይህ አይደለንም! መቼ ነው መተሳሰብና መተዛዘን ያቆምነው? እኛ እኮ በአንድ ጣራ ሥር የምንፀልይ፣ ለአንድ ሰንደቅ ዓላማ ህይወት እየሰጠን የኖርን፣ ለጎረቤታችን ደራሽ የሆንን፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንደሰትና የምናዝን፣ ሰብሎቻችንን በአንድ አውድ የምንበላ፣ ልጆቻችንን በትዳር የምንገምድ፣ ሚሥጥሮቻንንና ህልሞቻችንን በአደራ የምንሰጣጥ፣ “አንተ ትብስ፣ እኔ እብስ” መባባልን የምናውቅ ህዝብ ነን፡፡ ይህንን ነው “ ኢትዮጵያውያን በኃይማኖት የተገራን ነን “የምንለው፡፡ ከዚህ ውጭ ያመጣነው ፈሊጥ የእኛ አይደለም፡፡ ባዕድ ነው፡፡
አሁን የሆነውን፣ የተጠናወተንን አባዜ አውቀነዋል? “የጠላት ወገንን ሳቆቃ አላይም፣ ስለመከራው አልሰማም አልናገርም” እያልን ብቻ አይደለም፡፡ የጠላት ወገንን ሰቆቃ ውሸት ነው ብለን ካልተከራከርን፣ ካልሳቅንበት፣ ካላጓጠጥነው የአእምሮ እረፍት ተስኖናል፡፡ እድሉ ከተገኘም፣ የጠላት ሬሳ ጎን ቆመን በሞባይላችን ሰልፊ ለመነሳት ወደ ኋላ የማንል ሆነናል፡፡ እንደ ሰው ልጅ፣ እንደ ሀገር ልጅ መተሳሰብና መተዛዘን አቅቶን ዓለም በአግራሞት የሚመለከተን ትራጅዲዎች ሆነናል፡፡
መለወጥ አብን፡፡ ለራሳችን ብለን መለወጥ አለብን፡፡ ሰብዓዊነታችንን፣ ህሊናችንን፣ ነፍሳችንን ለመታደግ መለወጥ አለብን፡፡ በየትኛውም ወገን ሆነን አጥብቀን የምንሻው ድል፣ ፈጣሪ ከሰጠን ህገ – ልቦና የሚበልጥ አይደለም፡፡ የተቀደሰን ዓላማ የኃጥያት መንገድ ያረክሰዋል፡፡ ይህ ነው የታሪክ አንኳር አስተምሮ። መንገዳችንን ለማስተካከል መለወጥ አለብን፡፡
ይህ ሁሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፣ በጦርነቱ ያሉት ሁለቱ ተፋላሚዎች እኩል የሞራልና የፖለቲካ ዋጋ አላቸው ማለት አይደለም፡፡ አንዱ ጋር እውነት፣ አንዱ ጋር ጥፋት አለ፡፡ አንዱ ወገን ጦርነቱን ለኩሷል፣ ሌላኛው ለመከላከል ተገድዷል፡፡ አንዱ ወገን ሀገርን ለማስቀጠል፣ ሌላኛው ለመበተን ይታገላል፡፡ የአንደኛው ጥላቻ ከሌላኛው የላቀ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ታሪክ በየትኛው በኩል እንደቆመም
እናውቃለን።
ግን ግን፣ ድል የሚገኘው በጦር ግንባር ብቻ አይደለም፡፡ ፍልሚያው ብዙ ግንባሮች አሉት፡፡ የአሻራ (legacy) ግንባር አለ፡፡ አሻራችን ከተለያዩ ወንጀሎች ንፁህ መሆን አለበት፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት – The end does not justify the means ። የልጆቻችን ግንባር አለ፡፡ ልጆቻችን በሞራል ልዕልናችን መኩራት አለባቸው፡፡ የህሊና ግንባር አለ፡፡ ህሊናችንን የሚኮሰክስ ነገር መኖር የለበትም፡፡ የታሪክ ግንባር አለ፡፡ መጪውን ትውልድ የሚያጨቃጭቅ ውርስ ማስተላለፍ የለብንም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ሁሉን የሚያወቀው፣ ሁሉን የሚስማው፣ ሚሥጥራችን ሁሉ የማይሰወርበት ኃያሉ ፈጣሪ ፊት ተጠያቂ ለመሆን የምንቆምበት ግንባር አለ፡፡ በእሱ ፊት ለምህረት እንኳን ብቁ ሆነን ካልተገኘን፣ ሁሉ ነገራችን ዜሮ ይሆናል፡፡
ጦርነት ባይኖር ይመረጣል፡፡ ጦርነት የግድ ከሆነ ግን፣ ፍትሃዊ ጦርነት ይሁን፡፡ ፍትሃዊ ጦርነት መተሳሰብና መተዛዘን ያለበት፣ ራህራሄን የሚያወቅ፣ ጥላቻ፣ በቀልና አዋራጅነት የሌለበት ነው፡፡ ጦርነት የግድ ከሆነ፣ ለሰላምና ለፍቅር የሚደረግ ጦርነት ይሁን። ጦርነት ለማስቀረት የሚደረግ ጦርነት ይሁን፡፡
እስክንድር ነጋ፣ የፖለቲካ እስረኛ ከቂሊንጦ

If there must be war in Ethiopia…
A prisoner of conscience for many of the past 15 years, Eskinder Nega smuggled out the following plea from his detention in Addis Ababa.
If not in how my incarcerators have treated me, then in how I have been handed by government sponsored trolls on the internet, this episode of my eleven years (and counting) imprisonment under a series of false charges is a novel experience. Gone are days of yore, where the dignity of those who experienced suffering and our empathy for their trials was universally acknowledged.
Enter our present times, where any would be noble martyr has been transfigured into a public joke, a caricature of the ultimate attention seeker. But while the dethronement of wannabe martyrs may be desirable, the concomitant assault against empathy in the public domain is profoundly troublesome.
Consider the two sides of Ethiopia’s ongoing internal war. Beginning in trickles and then in flood like thrust came stories of impending famine, mass murders and gang rapes in all the conflict zones of Ethiopia’s three northern regions – Tigray, Amhara and Afar. And while limitations imposed by lack of access to the conflict zones blurs the full picture, human rights organisations have been able to verify a series of gross rights violations by all the belligerents.
But none of these chronicles of callous cruelties – against children, women, the elderly – has transcended the political divide and resonated with the other side. Tears have indeed been shed, petitions signed, and rallies held, but always unwaveringly for one’s side, never the other.
This is not who we are. When did we lose our empathy? I remember a time when we prayed side by side, when we fought under the same flag, when we laughed and cried together, when we joyed over and ate our harvests as one, when we tied our children in matrimony, when we whispered our secrets and dreams to each other, when were our brothers’ keepers.
Do we know what we have now become? There is more to us than mere “I shall look, hear, speak no evil about my side”. For now, we insist gawping, laughing, mocking, and denying the suffering on the other side. And I fear too few of us will pass a chance for a cute selfie with a victim on the other side. We have become a spectacle to the world, shocking for our lack of empathy for the plight of our fellow citizens, our fellow humans. We must change. We must change for our sake.
We must change to sustain our humanity, our conscience, our soul. No victory is greater than the God embedded morals in our hearts. Of the numerous lessons of history, none is greater than the knowledge the end, however noble, never justifies the ignoble means. Only at our peril do we fail to heed this caution against moral permissiveness. In change lies our only hope.
We cannot and must not deny that the two sides do not have moral and political equivalence. One side is on the right and the other not. One side needlessly fired the first shots and the other had no choice but to shoot back. One side fight to preserve and the other to shatter a nation. And we know one side strives to hate more than the other. We also know on which side history stands.
But ultimately, true victory will not be secured on the battlefront alone. For there are multiple fronts. There is victory to be secured in the legacy we leave behind, in the stories we tell our children, in the pages of history, in the deep interiors of our conscience, in the face of our creator who hears and sees all, who knows the entire breadth and depth of our secret desires, thoughts and deeds. It is better not to wage war.
But if it is an absolute necessity, let it be on terms of a just war. Such is just war: a war where empathy has a place, a humane war as far as possible, a war without hate, a war without vengeance, a war without triumphalism.
If there must be war, let it be war for peace, for love, a war to end war.
ቃሉን የሚኖረው እስክንድር ፤ ” የዲሞክራሲ ፈተና “
የ “VOA Africa” ጋዜጠኛ ትጠይቃለች እስክንድርን ከ9 ዓመት የዕስር ቤት ቆይታ በኋላ…
“ድጋሜ እታሰራለሁ ብለህ ትሰጋለህ?”
እስክንድር :- ቀጠለ …”መሰል አዝማሚያዎች ይታያሉ ። የመከሰት ዕድሉም ሰፊ ነው።ይሁን ዕንጂ ዳግም ዕስር ኖረም አልኖረም ልክ እንደ ሳውዝ አፍሪካ፣ጋና፣ቦትስዋናና እንደሌሎች የአፍሪካ አገራት በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እስኪሰፍን ድረስ በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ። እንጽፋለን።”
ልክ የዛሬ ሶስት ዓመት ነበረ ለውጥ መጣ በተባለ ማግስት ይህንን ያለው።ጀግናው እስክንድር ዛሬም ዕውነተኛ ዴሞክራሲ፣ዕኩልነት፣ፍትህ፣አንድነት በማለቱ በተረኛው ኦህዴድ መራሹ ስርዓት ዛሬም ዕስር ቤት ወድቋል። እስክንድር ዕውነት ነው።እስክንድር የፅናት ተምሳሌት ነው።እስክንድር ቃሉን የሚኖር ታላቅ ስብዕና ያለው ሰው ነው።
እስክንድርን ፍቱት!!
https://www.facebook.com/Balderas.Ethio/videos/243982614159001/