balderas
Posts by :
ህመሙ _አመመኝ
አቶ ስንታየሁ ቸኮል የኅሊና እስረኛ ከቂሊንጦ
እስክንድር ነጋ የድርጅቴ መሪ ራስ ነው!
ለኔ ደግሞ የሥራ አለቃዬ ነው!
እስክንድር ታላቅ ወንድሜ መካሪዬ ነው።
እስክንድር ለጋራ መስዋዕትነት የተጠራን የቁርጥ ቀን የሀገሬ ሕብረ_ቀለም ሃቀኛ ጓዴ ነው።
ከመሪዬ ጋር በአንድ ቤት ውስጥ ሆነን በተቀራረበ መኝታ ላይ እንዴት እንዳዳረ አውቃለሁ። ህመሙ- አመመኝ… ላብ በሚያጠምቅ ምጥ ..እእእእእ… የጥዝጣዜ ስሜት ቦታው ላይ መፍትሄ አጥተህ መጋራት ከባድ ነው። ቁጭት የተቀላቀለበት ህመም ብስጭት መራር ሀዘን ብቻ ያሳዝናል።
ዛሬ ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ,ም ጠዋት 1:00 ሰዓት ላይ እስክንድር እንደወትሮው ወደ ውጭ እያነከሰ ወጣ እንዴት እንዳደረ ስሜቱን አውቃለሁ፤ “ለምን ትወጣለህ ተኛ እንጅ እስክንድር” አልኩት። ለሊቱን ሙሉ እንዳልተኛ እና እግሩ በጣም እንዳመመው ነገረኝ። ይህን እኔም ስለሰማሁት ወዲያው በሙቅ ውሃ ለማሸት ሞከርኩ ግን ብዙም አልተቻለም። እጅግ የከፋ ህመሙ ተሰምቶት ነበር። በአስቸኳይ ወደ እክምና እንዲሄድ ለተረኛ ፖሊስ መኮንን ተናገረ.. ወደ ፖሊስ በመሄድ የእስክንድር እግር መሰበሩ በህክምና ተነገረው ።
በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በሥርዓቱ ዕቅድና ተልዕኮ የተደበደበው እስክንድር ነጋ፣ ዛሬ ከሰዓት ቦኃላ በፖሊስ ሆስፒታል በተደረገለት ህክምና ፣ በግራ እግሩ ላይ አውራ ጣቱ መሰበሩ በራጂ ታውቋል።
በዚህም መሠረት፣ ለሚቀጥሉት ስድስት ሳምንታት የሚቆይ ጄሶ ተደርጎለታል እንደሚቆይ ተነግሮታል።
ጠንካራው መሪያችን እስክንድር ነጋ ከማረሚያ ቤት ሆኖ ያስተላለፈው መልዕክት፣ ስሜት ቀስቃሽ ወኔ የሚጠግን ነበር።
“…በሰሜን ያለውን ጦርነት አስባለሁ። የታሰሩትን አባሎቻችንን አስባለሁ። አጥንታችንን መስበር ይቻላል። ትግላችንን ግን መስበር አይቻልም ” ብሏል።
ወኔ ያለው አመራር ይህ ነው። እስክንድር ነፍሱ ለእውነት የተጠራች ጀግና ታጋይ ነው። አምላኩን ሁሌም የማይረሳ በችግር ላይ ሆኖ ስለፍቅር ይቅርታ የሚሰብክ ደቀመዝሙር ነው።
የኛን ችሎት ለመታደም የመጡ የባልደራስ ፈርጦቻችን እናተ በርቱዎች በመስዋዕትነታችሁ ኮርተናል በመከራችሁ ብናዝንም ይህ እስራችሁ ግን ተመንዝሮ ህዝብ ይከፍላችዋል። ታሪክ ይክሳችዋል! ስለእኛ ዋጋ የምትከፍሉ ስለሀገራችሁ መፃሂ ዕድል ዛሬ በቆራጥ ትግል ያላችሁ ጓዶች ሁሉ እመነኙ ህዝብ አይረሳችሁም ከዚች ጠባብ እስር ቤት ሆነን እናስባችዋለን እናከብራችዋለን።
ድል ህዝባችን!
ድል ለሃቀኛ ታጋዮች!
የእስክንድር እግር መሰበሩ በህክምና ተረጋገጠ !
በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በዕቅድ የተደበደበው እስክንድር ነጋ፣ ዛሬ ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በፖሊስ ሆስፒታል በተደረገለት ህክምና ፣ በግራ እግሩ ላይ ያለው አውራ ጣቱ መሰበሩ በራጂ ተረጋግጧል።
በዚህም መሠረት፣ ለሚቀጥሉት ስድስት ሳምንታት የሚቆይ ጄሶ ተደርጎለታል።
እስክንድር ከማረሚያ ቤት ሆኖ ባስተላለፈው መልዕክት፣ “በሰሜን ያለውን ጦርነት አስባለሁ። የታሰሩትን አባሎቻችንን አስባለሁ። አጥንታችንን መስበር ይቻላል። ትግላችንን ግን መስበር አይቻልም ” ብሏል።
በጅምላ ከታሰሩት መካከል ሁለቱ በዋስ ሲለቀቁ 40ዎቹ ለሰኞ ተቀጠሩ !
የእነ እስክንድር ነጋን የችሎት ውሎ ለመታደም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በጥቅምት 11/2014 ዓ/ም የሄዱ 42 የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች በትላንትናው ዕለት በፓሊስ ታፍሰው መታሰራቸው ይታወቃል።
አቶ እስክንድር በእስር ቤት የደረሰባቸውን ድብደባ በችሎት የሰሙ ታዳሚዎች እያለቀሱ ችሎቱን አቋርጠው የወጡ ሲሆን ፤ ከችሎት ወጥተው በመንገድ ላይ ፖሊስ በጅምላ አፍሶ በልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ውስጥ ቆይተው ፤ ምሽት አንድ ሰዓት ወደ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው ታስረው ነበር። ዛሬ ጠዋት 4 ሰዓት በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።
ፖሊስ በዛሬው ችሎት እንደገለጸው ተጠርጣሪዎቹ ” ችሎት ውስጥ ረብሸዋል፣ ሲወጡ ደግሞ ፍትህ የለም ፣ መንግስት የለም በማለት ሁከት እና ብጥብጥ በመቀስቀስ ” ሲንቀሳቀሱ መያዙን ገልጿል ። ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ የምስክሮችን ቃለ ለመቀበል እና ማስረጃቸውን ለማሰባሰብ የ14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ቆጠሮ ጠይቋል።
የ42ቱ ተጠርጣሪዎች ጠበቆች ፖሊስ ያቀረበው የጊዜ ቀጠሮ አቤቱታ ውድቅ እንዲሆን በመጠየቅ ፤ ” በችሎት ውስጥ ተፈጸመ ለተባለው ድርጊት ፖሊስ የሚመለከተው ሳይሆን በወቅቱ ችሎቱ በራሱ ትዕዛዝ የሚሰጥበት ነው። ሆኖም ግን ችሎቱ ምንም አይነት ትዕዛዝ ባልሰጠበት ፖሊስ ያቀረበው አቤቱታ ተገቢ አይደለም” ብለዋል ።
ከዚህም በተጨማሪ ” ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀበት ምክንያት በሕግ ምንም አይነት ድጋፍ ” የለውም በማለት የጊዜ ቀጠሮው ውድቅ እንዲሆን በመጠየቅ ከእስር እንዲለቀቁ ለፍ/ቤት ጥያቄ አቅርበዋል ።
ግራና ቀኙን ያከራከረው ፍርድ ቤት ሁለት ህፃናት ልጆች ያላቸውን ተጠርጣሪዎች በዋስትና እንዲወጡ፣ የተቀሩትን ደግሞ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ወደ 3 ቀን በመቀየር ለፊታችን ሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲቀርቡ፣ እንዲሁም የተጠርጣሪዎቹን ተሳትፎ ለይቶ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል ።
እስረኞች በተያዙበት ወቅት ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ችሎቱም ለደረሰባቸው ጥሰት ክስ ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጿል ።
በጅምላ ከታሰሩት መካከል ሁለቱ በዋስ ሲለቀቁ 40ዎቹ ለሰኞ ተቀጠሩ !
በአቶ እስክንድር ነጋ ላይ ስለተፈጸመው ከባድ ድብደባ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስቸኳይ ማብራሪያ እንዲሰጠን እንጠይቃለን!!!
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ፕሬዚደንት አቶ እስክንድር ነጋ በሚኖሩበት ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ውስጥ ጥቅምት 11/2014 ዓ.ም. ንጋት 12፡20 ደቂቃ ላይ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል፡፡
ከአቶ እስክንድር ነጋ ጋር አብረው በእስር ላይ ያሉት የፓርቲው የአደረጃጀት ጉዳዮች ሓላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል ጥቅምት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በነበረው የፍርድ ቤት ቀጠሮ የተገኙ ሲሆን የባልደራስ ፕሬዘዳንት ወህኒ ቤት ውስጥ በተደራጀ የውንብድና ቡድን መደብደባቸውን ተናግረዋል። በዚህም ምክንያትም አቶ እስክንድር ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
ከችሎት መልስ የአቶ እስክንድር ጠበቆች፣ ቤተሰቦቻቸው፣ የባልደራስ አመራሮችና አባላት ወደ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ሄደው ለመጠየቅ ቢሞክሩም አቶ እስክንድር ከታሰሩበት ክፍል ወጥተው ማነጋገር አልቻሉም። ሆኖም በተፈጸመባቸው ድብደባ ግንባራቸው፣ ዓይናቸው አካባቢ እና ጉልበታቸው ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ፓርቲያችን አረጋግጧል። ነገር ግን ለደረሰባቸው ጉዳት የተደረገላቸው ህክምና አለመኖሩም ታውቋል። ስለዚህ በአስቸኳይ ቤተሰቦቻቸው ወደ መረጡት ሆስፒታል ተወስደው እንዲታከሙ እንጠይቃለን።
ድብደባው በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና መሥሪያ ቤቱን በቀጥታ በሚቆጣጠረው ጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ሊፈጸም እንደቻለ መገመት አስቸጋሪ አይሆንም። ይህም የኅሊና እስረኞችን በተለይም የአቶ እስክንድር ነጋን ህይወት ለመቅጠፍ የሕብረተሰቡን አስተሳሰብ ማለማመጃ ምዕራፍ እንደሆነ ባልደራስ ይረዳል። በመሆኑም ስለተፈጸመው ከባድ ድብደባ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቀጥታ ለሕዝብ መግለጫ እንዲሰጥ እንጠይቃለን።
ፓርቲያችን ይህንን የሚለው አቶ እስክንድር ነጋ ከዚህ በፊት በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ፣ በቃሊቲ ወህኒ ቤት እንዲሁም ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በወታደር ቁጥጥር ስር በዋሉበት ጊዜ እና ቢሯቸው ውስጥ የደረሱባቸውን በመጠን የተለያዩ ድብደባዎች ሁሉ በማስታወስ ነው።
ከዚህ ጋ በተያያዘም ጥቅምት 11/2014 ዓ.ም. በነአቶ እስክንድር ነጋ የፍርድ ሂደት ችሎት ታድመው የነበሩ 42 የፓርቲያችን አባላት ታፍሰው ልደታ ክፍለ ከተማ የፖሊስ መምሪያ ከቆዩ በኋላ አመሻሹ ላይ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው እንዲታሠሩ ተደርገዋል። ከታሠሩት ውስጥ 12ቱ ሴቶች መሆናቸውም ተረጋግጧል፡፡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የታሠሩት አባሎቹ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ ይጠይቃል።
ድል ለዴሞክራሲ!!!
መረጃ ! በእስክንድር ነጋ ላይ በማረሚያ ቤት ድብደባ ተፈጽሞበታል
በእስክንድር ነጋ ላይ በማረሚያ ቤት ድብደባ ተፈጽሞበታል ። በዚህም ምክንያት ጉልበቱ መቁሰሉን ዋና ሳጅን መስፍን ይልማ የተባሉ የቂሊንጦ ወህኒ ቤት የፈረቃ ሓላፊ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል! በዛሬው ዕለት እስክንድር ነጋ ችሎት መቅረብ አልቻለም ።
ይህም በመሆኑ በተከታታይ ምስክር የመስማት ቀጠሮ ተሰርዞ ፤ ለፊታችን ሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ተዘዋውሯል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ችሎት ለመታደም የተገኙ በጅምላ ታፍሰው ልደታ ፖሊስ ጣቢያ መምሪያ ተወስደዋል ።
አጠቃላይ ዝርዝር መረጃዎችን ወደኋላ እንመለስበታለን።
ነገም እንደዛሬው የሞራል ግዴታችንን እንወጣ!
በዛሬው የእነ እስክንድር ነጋ ችሎት ላይ ለመታደም የፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ድረስ መጥታችሁ ‘አዳራሽ ሞልቷል’ በሚል ችሎቱን ሳትታደሙ የተመለሳችሁ የፍትሕ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ተቆርቋሪዎች በርካቶች ናችሁ። ከኅሊና እስረኞች ጎን መሆናችሁን ስላሳያችሁን በእጅጉ እናመሰግናለን።
ችሎቱን የታደማችሁም ሆነ የተከለከላችሁ አጋርነታችሁን አሳይታቸሰኋልና ፈጣሪ አጋር ይሁናችሁ። የሞራል ግዴታችሁን መወጣታችሁ በታሪክ ተመዝግቦ ለትውልድ እንደሚተላለፍም ተስፋ እናደርጋለን።
ችሎቱ ነገም ጥቅምት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ይቀጥላል። በነገው ችሎት ሁለቱ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች በኅሊና እስረኛው እስክንድር ነጋ ላይ በግልፅ ችሎት ምስክርነታቸውን እንደሚሰጡም ይጠበቃል። በተጨማሪም ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ የ12 ሀሰተኛ ምስክሮቹን ስም ዝርዝር ለችሎቱ ያቀርባል።
ስለዚህ ነገም እንደዛሬው አጋርነታችንን እንድገም። የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ከጧቱ 3 ሰዓት ላይ እንገናኝ።
ዐቃቤ ሕግ በእነ እስክንድ ነጋ ላይ የሚቀርቡ ምስክሮች ዝርዝር በሚዲያ እንዳይቀርብ ያቀረበውን አቤቱታ ፍ/ቤት ውድቅ አድርጎታል
በዚህም መሰረት ፦
በነ #እስክንድር ነጋ ላይ ከነገ ጥቅምት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በግልፅ ችሎት እንዲመሰክሩ ዐቃቤ ሕግ የዘረዘራቸው ሰዎች ስም ዝርዝር:-
1. ፈንታሁን አሰፋ
2. መንበረ በቀለ
3. ወርቁ ታደሰ
4. ፍፁም ተሰማ
5. ደረጀ ግዛው
6. ቴዎድሮስ ለማ
7. ያየህ ብርሃኑ
8.ጌትነት ተስፋዬ
9. ትንሳኤ ማሞ
ቀሪ የ12 ምስክሮች ስም ዝርዝር ነገ ጧት እንዲቀርብ ታዝዟል። ከላይ ከተጠቀሱት መካከል ሁለቱ ነገ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የችሎት ክለሳ
ጌጥዬ ያለው
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ዛሬ ጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. የእነ እስክንድር ነጋን መዝገብ ቁጥር 260175 ገልጦ የይስሙላ ክርክሩ ቀጥሏል። ባለፈው ጥቅምት 5 ቀን በተቀጠረው መሰረት ዐቃቤ ሕግ በግልፅ ችሎት እንዲያቀርባቸው የታቀዱ ምስክሮች ስም ዝርዝር ለመገናኛ ብዙሃን፤ በተለይም ከሳሽ እንደ እንኩሽ በሚፈራው ፌስቡክ ይገለፅ ወይስ ድብቅ ይሁን በሚል ጭብጥ ተከራክረዋል። ባለፈው ጊዜ ከችሎት የጠፉት ዳኛ ዛሬ ተሰይመዋል። ከጧት በተደረገው ክርክር ላይ ብይን ለመስጠት ለዛሬ ከቀትር በኋላ 8:30 ችሎቱ ተመልሶ እንዲሰየምም ተቀጥሯል።
ዐቃቤ ሕግ የዘጠኝ ምስክሮችን ስም ዝርዝር ለዳኞች፣ ለጠበቆች እና ለኀሊና እስኞች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ የሰጠ ሲሆን በመገናኛ ብዙሃን ይገለፅ ወይም አይገለፅ የሚለው ጭብጥ በቀጣዩ ችሎት ይወሰናል። ዐቃቤ ሕግ ቀሪ 11ዱ ምስክሮች በግልፅ ችሎት ለመቅረብ ፈቃደኛ እንዳልሆኑለት እና እያግባባቸው እንደሆነ ተናግሯል። ፈቃደኛ ከሆኑ እንደሚያቀርብ ካልሆኑ ግን ማስመስከር እንደ ማይችልም ተናግሯል።
የእነ እስክንድር ነጋ ጠበቆች ሔኖክ አክሊሉ፣ ቤተማርያም አለማየሁ እና ሶሎሞን ገዛኸኝ በበኩላቸው ጉዳዩን በመቃወም ተከራክረዋል። በተለይም በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕጉ ቁጥር 124 እና ቁጥር 136 መሰረት ዐቃቤ ሕግ “ምስክሮቼ ፈቃደኛ ከሆኑ አቀርባለሁ፤ ካልሆኑ ግን አላቀርብም” ማለቱ ስህተት እንደሆነ እና ባልተረጋገጠ አማራጭ ያቀረበው አቤቱታ ቅቡልነት ሊኖረው እንደ ማይገባ ገልፀዋል።
በሕጉ መሰረት ሁሉም ምስክሮች ተጠቃለው በመጀመሪያው ቀን መቅረብና በስነ ስርዓቱ መሰረት ቃለ መሀላ ፈፅመው ችሎቱ በሚሰጣቸው ቅደም ተከተል እማኝነታቸውን መስጠት እንዳለባቸው አስረድተዋል።
እያስፔድ አበጀ የተባለ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕጉ ያልተሟላ መሆኑን ጠቅሶ ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን እንዲቀበል አስረድቷል። ይህም ባልተፃፈ ሕግ እንዲፈርዱ መጠየቅ ነው። ለእነ እስክንድር ነጋ ሀሰተኛ የሽብር ክስ ሲባል አዲስ ሕግ እንዲዘጋጅ ወይም በጠበቆች የተጠቀሰው የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ዐቃቤ ሕግ በእነ እስክንድር ላይ የቀረበውን ክስ ለማስረዳት በሚያመቸው መልኩ እንዲሻሻል ምክረ ሃሳብ ያቀረበበት ጥያቄም ይመስላል። ዐቃቤ ሕግ ይህንን ሲል እርሱ እራሱ ሕጉን የመፍጠርም፣ የማፅደቅም፣ የመሻርም፣ የማሻሻልም መብት እንዳለው በሚያስረዳ መንፈስ ነበር። የመገናኛ ብዙሃን የችሎት አዘጋገብን በተመለከተም በሕጉ የተቀመጠው ገደብ በቂ እንዳልሆነ ገልጿል።
በመሆኑም ከፍሬ ክርክሩ ውጭ ከካድሬ ስልጠና የሚመሳሰል ሰፊ ንግግር አድርጓል። እስክንድር ነጋ ተቃውሞ እንዳለው ጠቅሶ በመነሳት “ሌክቸር ነው እየተሰጠን ያለው” በማለት ባያስቆመው ኖሮ የእያስፔድ አበጀ ንግግር የሚቋጨው ዳኞችን እና ጋዜጠኞችን ‘ሂሳችሁን ዋጡ!’ በማለት ሳይሆን አይቀርም ነበር።
በዚህ ችሎት አመቱን ሙሉ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ሲያከራክር ከርሞ ለዚህ መዝገብ ጥቅም ላይ አይውልም ተብሎ የተዘጋው የምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 በድጋሜ ተመልሶ ለክርክር ቀርቧል። ነሐሴ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ሰበር ሰሚ ችሎቱ በሰጠው ብይን መሰረት ለምስክሮች በችሎቱ የሚደረግ ጥበቃ እንደሌለ መወሰኑን ያስታወሱት ዳኞች ዐቃቤ ሕግ ተመልሶ እንደ አዲስ ለክርክር እንዲያቀርበው ግን ፈቅደውለታል። በመሆኑም የክርክር ሂደቱ እየተከለሰ ይገኛል።
በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕጉ ቁጥር 184 መሰረት ይግባኝ የሚጠየቀው ተጠቃሎ ብይን ከተሰጠ በኋላ ቢሆንም ሕገ ወጡ ዐቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እና ሰበር ሰሚ ችሎት አቤት እንዲል ተፈቅዶለት የፍርድ አሰጣጥ ሂደቱን ከአንድ ዓመት በላይ ሲያንቀራፍፍ ከርሟል። አሁን ደግሞ በአዲስ ዳኞች ችሎቱን እየደገመው ይገኛል።
እንደ ሌሎች ችሎቶች ሁሉ የዛሬው ችሎትም ወታደራዊ ነበር። ታዳሚው ተወደረ ስናይፐር እና በአስለቃሽ ጭስ ጭምር አዳራሽ ውስጥ እየተጠበቀ ታድሟል።
ስንታየሁ ቸኮል በፖሊስ ታጅቦ ከእስር ቤት ውጭ በሚገኝ ሆስፒታል በግሉ ወጭ እንዲታከም ባቀረበው ጥያቄ ላይ ምላሹን እንዲሰጥ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ችሎት የተጠራ ቢሆንም ሳይቀርብ ቀርቷል።
ለሀገርና ለህዝብ መብትና ጥቅም በሰላማዊ መንገድ ሲታገሉ ለታሰሩት ድምጽ እንሁን!
ከአንድ አመት በላይ በግፍ እስርቤት ለሚገኙት የዘመናችን የሰላት ታጋይ እንቁዎች እስክንድር ነጋ፣ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እንዲሁም አስካል ደምሌ ከእስር እንዲፈቱ የሞራል ግዴታችንን እንወጣ !
ነገ ማክሰኞ ጥቅምት 9, 2014 ዓ. ከጠዋቱ 3:00 ሰአት ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንገናኝ።