balderas
Posts by :
በወቅታዊ የፓርቲያችን እንዲሁም የሀገራችን ሁኔታ ላይ የተደረገ ውይይት
የባልደራስ ፓርቲ የስራ አስፈፃሚ አባላት የሆኑት ዶ/ር በቃሉ አጥናፉና አቶ ስንታየሁ ቸኮል በወቅታዊ የፓርቲያችን እንዲሁም የሀገራችን ሁኔታ ላይ ተወያይተወዋል። ውይይቱን ከታች ባለው ሊንክ (Link) በመግባት ይከታተሉ።
በኦሮሚያ ክልል በፅንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኞች ፕሮግራማዊ ተልእኮ እየተመራ ያለው የአማራን ዘር የማጥፋት ኢ-ሰብዓዊና አፀያፊ ድርጊት ሊቆም ይገባል
ምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ከጭጨፋ የተረፉ የ19 ቀበሌ ነዋሪዎች 40 ኪሎ ሜትር በእግር ተጉዘው ነቀምቴ ጊዳአያና ወረዳ መጠለላቸው ታውቋል፡፡ ከሞት አምልጠው ነቀምቴ ጊዳአያና ወረዳ የተጠለሉ ተፈናቃዮች በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው አሁንም ለሕይዎታችን አስተማማኝ ነገር የለም በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ ዓመታትን ያስቆጠረው የአማራ ተወላጆች ጭፍጨፋ አሁንም ድረስ መፍትሔ ያላገኘው፣ ጥቃቱ በኦህዴድ/ብልፅግና መንግስት የሚመራ በመሆኑ እንደሆነ ገሃድ እየወጣ መጥቷል፡፡
በሆሮጉድሩ ወለጋ በጃርቴ ጃርዴጋ ወረዳ በሻምቡ ከተማ እና ምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ በዚህ ሳምንት ከፍተኛ ጥቃት ከተደረገባቸው አካባቢዎች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡ ምስራቅ ወለጋ ዞን የጊዳ ኪረሙ ወረዳ መቀመጫ በሆነችው ኪረሙ ከተማ የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እንዳያውሉ እንቅፋት ፈጥራችኋል በሚል ሰበብ ታስረው የነበሩ ከ50 በላይ የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች በጅምላ መረሸናቸውን ከጅምላ ጭፍጨፋው አምልጠው የወጡ የአይን እማኞች መናገራችው በሚዲያ ተዘግቧል ።
ከህዳር 09/2015 ዓ/ም ጀምሮ በከተማዋ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ታስረው የነበሩ ከ50 በላይ የሚሆኑ እስረኞች ህዳር 20 ለህዳር 21 አጥቢያ በጅምላ መረሸናቸው አይዘነጋም። በህዳር ወር ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ሽብርተኛው ሸኔ እና የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ተቀናጅተው ባካሄዱት ኢ- ሰብአዊ ዘመቻ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሕይወታቸው ተቀጥፏል፤ከፍተኛ መፈናቀልም ደርሶባቸዋል፡፡
አማራን የመጨፍጨፍ እና የማፈናቃሉን አፀያፊና ዘረኛ ድርጊት የሚያስተባብሉ እና ሥራዬ ብለው የሀስት ዘመቻ የሚያናፍሱ በኦሮሞ ሕዝብ ስም የተደራጁ ፓርቲዎች፣ በተለይም የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግሬስ ሁለቱ ምክትል ሊቃነመናብርት እና የኦነግ የተለያዩ ክንፎች መሪዎች እና እነሱ የሚቆጣጠሯቸው ሚዲያዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት ሽብርተኛ ብሎ ከፈረጀው ከሕወሓት ቡድን ጋር በደቡብ አፍሪካ መደራደሩን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የአማራዎች ጭፍጨፋ ተጠናክሮ መቀጠሉ የአደባባይ ክንውን ሆኗል፡፡ የአሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኮሚዪኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ በቅርቡ ለሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ መንግስት ከኦነግ ሸኔ ታጣቂ ሽብርተኞች ጋር እንደማይደራደር እና ከአባ ገዳዎች ምሕረት ጠይቀው እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን መግለፁ አይዘነጋም፡፡ ይህ አባባል የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት በስውር ባሰማራው በሸኔ ላይ የሚጨክን ልብ የሌለው መሆኑን በግልፅ ያመለክታል፡፡ በተለይም በምስራቅ ወለጋ እና በአካባቢው ግድያ እና ዘረፋው አሁንም እየቀጠለ መሆኑን የሚገልፁት የጥቃቱ ሰለባዎች፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ሕይታቸውን ለማትረፍ ነቀምቴ ጊዳአያና ወረዳ ተጠልለው የሚገኙ ንፁሐንን መንግሥት የመከላከያ ሰራዊትን ወደ ቦታው ድረስ ልኮ ከሞት እንዲታደጋቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም አዳማጭ መንግሥት ያላገኙ ስለመሆኑ በገሃድ እየታዬ ነው፡፡
የተለያዩ ፅንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኛ ፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች መንግሥት ለምን ከሼኔ ጋር አይደራደርም በሚል ድርድር እንዲካሄድ እየገፋፋ ይገኛሉ፡፡ አማራ ኦሮሞን በቅኝ ግዛት ገዝቶታል በሚል የሃሰት ትርክት አስተሳሰባቸውን ያዛቡባቸውን የኦሮሞ ወጣቶች “ፋኖ ወደ ኦሮሞ ክልል ገብቶ ግድያ እየፈፀመ ነው” በሚል የሃሰት ዘመቻ በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ተማሪዎች አመፅ እንዲቀሰቀሱ በመገፋፋት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ዘመቻቸው የአመለካከት አምሳያቸው የሆነው ህውሓት በፋኖ ላይ የከፈተውን የሃሰት ውንጀላ በማጠናከር የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት መከላከያ ሠራዊትን በፋኖ ላይ እንዲያዘምት በመቀስቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡
እንደሚታወቀው በወለጋ እና በሰሜን ሸዋ አካባቢ እራሳቸውን ከህልውና ጥፋት እየተከላከሉ ያሉት በግፍ መገደልና መጠቃት ያንገሸገሻቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንጅ ከአማራ ክልል የተነሱ ፋኖዎች እንዳልሆኑ ይታወቃል፡፡ የፋኖን ስም ማጠልሸት የኦነግ – ብልጽግና፣ የኦነግ፣ የህወሓት እና የኦፌኮ የቀን ተቀን ተግባር መሆኑ እየታየ ነው፡፡ ይህም እነዚህ ድርጅቶች ከአማራ የፀዳች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እና በኢትዮጵያ ክስመት የትግራይ እና የኦሮምያ ሪፖብሊኮችን ለማዋለድ ሲመሠረቱ ጀምሮ ይዘው የተነሱትን የፖለቲካ ዓላማ እስካሁን ድረስ እያራመዱት እንደሚገኙ የሚያሳይ ተጨባጭ ክንውን ነው፡፡ ይህ አካሄዳቸው ህወሓት፣ ኦህዴድና ኦነግ የፖለቲካ ዓላማ አንድነት ያላቸው ፀረ- ኢትዮጵያ ድርጅቶች መሆናቸውን ይመሰክራል፡፡
ፓርቲያችን ባልደራስ በወለጋም ሆነ በሌሎች የኦሮምያ አካባቢዎች ማቆምያ በሌለው ሁኔታ እየተካሄደ ያለውን የአማራን ዘር የማጥፋት መንግሥታዊ መር ዘመቻ በፅኑ እየተቃወመ፣ የአማራው ማህበረሰብ ህልውናውን ከጥፋት ለመከላከል እያደረገ ያለው ተድጋሎ ተገቢ እና ህጋዊ መሆኑን በመግለፅ፣ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ባልደራስ የዩኒቨርስቲ መምህራን የጀመሩት የሥራ ማቆም አድማ ለመብታቸው መከበር እያደረጉ ያሉት ተቃውሞ ህጋዊ እና ሰላማዊ በመሆኑ፣ ከጎናቸው የሚቆም መሆኑን ለመግለፅ ይፈልጋል፡፡
የኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ የኢኮኖሚ ችግሮች ፣ ምክንያቶቻቸው እና መፍትሄዎቻቸው
አመሃ ዳኘው ተሰማ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ም/ሊቀመንበር
የሃገራችን ኢኮኖሚ ከኮቪድ እና ከእርስ በእርስ ጦርነቱም በፊት የነበረበት ሁኔታ አስከፊ ነበር። አሁን የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ያስከተለው ተጽዕኖ ሲጨመርበት ኢኮኖሚውን ከድጡ ወደ ማጡ በማስገባት የከፋ የችግር አረንቋ ውስጥ ከቶታል፡፡ መንግሥት ለራሱ እንዲስማማ እያደረገ በሚያወጣው መረጃ መሰረት በ2014 የዋጋ ግሽበቱ 38.9 በመቶ እንደነበር ቢገለፅም በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ 50% በላይ እንደሆነ ነዉ አንዳንድ መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡ የምግብ የዋጋ ግሽበት 57% በላይ ሁኗል፡፡ ይሄ የእስታቲስቲክስ መ/ቤት የሚያወጣዉ መረጃ ሲሆን፣ በተግባር ማንም ገብያ ወጥቶ አስቤዛ የሚሸመት ሰዉ እንደሚያዉቀዉ የምግብ ዋጋም ሆነ ሌሎች ከአስቤዛ ጋር የሚሄዱ ሸቀጣሸቀጦች ዋጋ ባለፉት ዓመታት ከነበሩበት ከሶስት እስከ አምስት እጥፍ መጨመሩን በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል። የመንግሥት ገቢ እና ወጭ ብቻ ሳይሆን የሃገራችን የንግድ ሚዛን መዛባት፣ የእዳ ጫናው እየከበደ መምጣት ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የኢኮኖሚ ሁኔታዉን አስፈሪና አሳሳቢ አድርጎታል፡፡
በዚህ በያዝነው አዲስ ዓመት በኢትዮጵያ የተመዘገበው የዋጋ ንረት መጣኔ ከሰሃራ በታች ካሉ አፍሪካ ሀገሮች በልጦ ተገኝቷል፡፡ ለዚህም ዋንኛው ምክንያት በተለይም ለእርሻ ምርት መጨመር እንዲሁም የግብርና ምርቶችን በግብዓትነት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችን ምርት ለመጨመር ዋነኛ ግብዓት የሆነው መሬት ከኢኮኖሚ አገልግሎት ይልቅ የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት በሚከተለው የነገድ ፖለቲካ ምክንያት የፖለቲካ መሳሪያነቱ አመዝኖ እንዲገኝ በመደረጉ ነው፡፡ የኢኮኖሚ መረጃዎች እንደሚያመለከቱት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1996 በኢትዮጵያ ለግብርና ምርት ሊውል ይችል የነበረው የመሬት አቅርቦት እና አጠቃቀም 91% የነበረ ሲሆን፣ ይህ አሃዝ በ2022 ወደ 16% ዝቅ ማለቱ ለዚህ አባባል ዋንኛ አመላካች ነዉ፡፡
በኢትዮጵያ ከተከሰተ የቆየው የፖለቲካ አመለካከት ፅንፈኝነት እና የነገድ ፖለቲካ እየተካረረ መምጣቱ የሃገራችንን የፖለቲካ ምህዳር አልፎ የኢኮኖሚውን ሁኔታ እያናጋ መምጣቱ አሌ ሊባል የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በሃገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ የመጣው የዋጋ ንረት፣ ንረቱን ተከትሎ የጨመረው የኑሮ ውድነት እና ብልሹ የግብይት ስርዓት ዋንኛው ምክንያት የመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች የሚነደፉበትን ወይም የሚቀዱበትን ዘውጋዊ የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተመርኩዘዉ ተግባራዊ የሚደረጉ የኢኮኖሚ መርሃግብሮች በገብያ ህገ ሳይሆን፣ አድሏዊ በሆነ የጥቅም ግንኙነት (Patronage network) አማካይነት የሚመሩ እንዲሆኑ በመደረጋቸው ነው፡፡
በሃገራችን ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት እየጨመረ መምጣቱ ህዝቡ እሮሮዉን በየጊዜዉ የሚያሰማበት ጉዳይ ሁኗል። በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣው የኑሮ ውድነት እየተባባሰ እንዲሄድ ያደረጉ ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም፣ እንደ ዋና ዋና ሊቆጠሩ የሚገባቸው ስድስት እንደሆኑ ፓርቲያችን ባልደራስ ያምናል፡፡ እነርሱም፡-
1ኛ/ የግብርና ምርታማነት ከህዝብ ቁጥር እድገት መጨመር ጋር አብሮ ሊሄድ አለመቻል አንዱ ነው፡፡ በሃገራችን በአሁኑ ጊዜ ያለው ምርታማነት በንጉሡ ዘመን ከነበረው ምርታማነት እምብዛም የተራራቀ አይደለም፡፡ ይህም ከህወሓት ዘመን ጀምሮ አሁንም የኦህዴድ/ የብልፅግና ፓርቲ ከሚከተለው የመሬት ፖሊሲ የመነጨ ነው፡፡ በንጉሱ ዘመን አማካይ የነበረው የግብርና ምርታማነት 9% ሲሆን በአሁኑ ዘመን ያለው አማካይ የግብርና ምርታማነት 12% ነው፡፡ በአንፃሩ በንጉሱ ጊዜ የነበረው አማካይ የሕዝብ ቁጥር ከሰላሣ ሚሊዮን ያልበለጠ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ የሃገራችን ሕዝብ ቁጥር ወደ አንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን እንደሚጠጋ ይታመናል፡፡ ይህም የ400% እድገት ነው፡፡
2ኛ/ የሃገሪቱ የብር መጠን በየጊዜው እና በተከታታይ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ምርትና አገልግሎት ለማዘዋወር ከሚያስፈልገው መጠን በላይ መንግሥት ከብሄራዊ ባንክ በሚወስደው ብድር መልክ እያሳተመ ገብያው ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግበት አሠራር ሌላው ነው፡፡ ይህ የአጠቃላይ የኢኮኖሚውን እድገት መጣኔ ያላገናዘበ (Excess money Supply) የገንዘብ ፖሊሲ በህወሓት ዘመን የተጀመረ ቢሆንም፣ በኦህዴድ/ብልፅግና ዘመን በከፍተኛ ደረጃ ተባብሷል፡፡ መንግሥት ይህን የሚያደርገው የበጀት ጉድለቱን ለማሟላት ነው፡፡ መንግሥት የበጀት እጥረቱን ሲያሟላ የቆየው በሃገር ውስጥ ብድር፣ ከውጭ በሚገኝ ብድር እና እርዳታ ነው፡፡ በሃገር ውስጥ የመንግሥት ብድር የሚሸፈነው ከንግድ ባንክ በሚገኝ ብድር እና ቀሪው በብሔራዊ ባንክ አማካይነት አዲስ ገንዘብ ታትሞ ለመንግሥት የመደበኛ ወይም የካፒታል በጀት መሸፈኛ እንዲውል በማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ በሃገራችን ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት ማለትም በ2000 ዓ.ም በኢትዮጵያ ውስጥ በሰው ኪስ፣ በትራስ ውስጥ የተደበቀዉ፣ በግልና በመንግሥት ድርጅቶች ሂሳብ ውስጥ የነበረው ጠቅላላ የብር መጠን 67 ቢሊዮን ብር ብቻ ሲሆን፣ ከአስራ ሦስት ዓመታት በኋላ ማለትም 2013 ዓ.ም በኢኮኖሚው ውስጥ ሲዘዋወር የነበረው ገንዘብ 870 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህም የገንዘብ አቅርቦቱ (Money Supply) 1,298% እድገት ማስመዝገቡን ያመለክታል፡፡ ባለፈው 2021 የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ላይ መንግሥት ብሄራዊ ባንክን በማዘዝ በአዲስ እንዲታተም ያደረገው የብር መጠን 83.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህም ከ2020 ከነበረው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲያነፃፅር የ169.4% እድገት እንደነበረው የብሄራዊ ባንክ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የገንዘብ አቅርቦቱ ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርት (GDP) ከ12 በመቶ በላይ ከሆነ ዉጤቱ የዋጋ ንረትን መጨመር እንደሆነ የኢኮኖሚ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በኢኮኖሚው ውስጥ እየናረ ለመጣው የዋጋ ንረት አንዱ ዓይነተኛ ምክንያት ይህ በየጊዜው እየታተመ ወደ ገብያ ውስጥ እንዲሰራጭ የሚደረገው በምርትና አገልግሎት ያልተደገፈ ሌጣ ብር ነው።
3ኛ/ ከህወሓት ኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን ጀምሮ እስከተተኪው የብልፅግና አገዛዝ ድረስ የቀጠለው የብርን የምንዛሬ ዋጋ የማርከስ (Devaluation) ፖሊሲ ለሃገራችን ኢኮኖሚ ቀውስና ቀውሱን ላስከተሉት የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ሌላው ዓይነተኛ ምክንያት ነው፡፡ ህወሓትም ሆነ ብልፅግና ለዚህ ፖሊሲያቸው የሚሰጡት ምክንያት የብር የምንዛሬን ዋጋ ማርከስ የሃገሪቱን የወጪ ንግድ ያበረታታል የሚል ነው። ይህ የመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የምርትና የአገልግሎት አቅርቦት እጥረት (Supply Constraint) ባለበት ሁኔታ የብርን ዋጋ በማርከስ የውጭ ንግድን ማበረታት አይቻልም፡፡ በሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ለውጪ ንግድ የሚላኩ ምርቶች አቅርቦት ከፍላጎት በላይ ሁኖ አያውቅም፡፡ እንደውም ለውጭ ንግድ የሚላኩ ምርቶች ሁሉም ለማለት በሚቻልበት ሁኔታ ከሃገር ውስጥ ፍጆታ እየተቀነሱ እንጂ የሃገር ውስጥ ፍላጎትን አሟልተው አያውቁም፡፡ ለምሳሌ ሥጋ፣ ፍራፍሬ እና ሰሊጥ እንዲሁም ሌሎች የሀገር ውስጥ ምርቶች የሃገር ውስጥ ዋጋቸው ለውጭ ገበያ ሲቀርቡ ከሚያስገኙት ዋጋ የበለጠ ነው። ወደ ውጭ የሚላኩት የውጭ ምንዛሬ ስለሚያስፈልግ ብቻ ነው፡፡ የእነዚህ ምርቶች የሃገር ውስጥ ፍጆታ ተቀንሶ ወደ ውጭ በሚላኩበት ጊዜ፣ የገብያ አቅርቦታቸው ከፍላጎት ያነሰ ስለሚሆን በሃገር ውስጥ የሚኖራቸው ዋጋ እየጨመረ ይሄዳል፡፡
ባለፉት በርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ ከውጭ ንግድ የምታስገኘው ገቢ በአማካይ ከ3 ቢሊዮን ዶላር እስከ 3.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኖ አያውቅም፡፡ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ሃገራችን ከውጭ ንግድ ያገኘችው ገቢ 4.1 ቢሊዮን ዶላር ደርሷ ነበር፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የሚላከው ምርት በማደጉ ሳይሆን፣ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በ2014 ዓ.ም በዓለም ገብያ ላይ የወርቅ ዋጋ በ700% በመጨመሩና የቡናም ዋጋ ከበፊቱ ዓመት ጭማሪ በማሳየቱ ነው፡፡
ይህ ብር ከአሜሪካ ዶላር ጋር ያለውን የምንዛሬ መጣኔ የማርከስ (Devaluation) ፖሊሲ መንግሥት የውጭ ንግድን ለማበረታታት የሚል ሽፋን ይስጠው እንጂ፣ ትክክለኛ እና እውነተኛ ምክንያቱ ጠቅላይ ሚ/ር አብይ የእናት ጓዳ የሚሏቸው የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና የዓለም ባንክ ለሚሰጧቸው ብድሮች በአስገዳጅነት ከሚቀርቡት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ቅደመ ሁኔታ (Conditionality)በመሆኑ ነው፡፡ መንግሥት የእነዚህን ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድርና ድጎማ እስከፈለገ ድረስ ፣በግዳጅነት የተጫነበት ፖሊሲ መሆኑን ለህዝብ የማይገለጠው ሚስጥሩ ነው፡፡ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ህወሓት ሥልጣን በያዘበት በ1991 (1983 ዓ.ም በኢትዮጵያ አቆጣጠር) እና ባለፈው ዓመት በ2022 (2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ አቆጣጠር) መካከል የብር የምንዛሬ መጠን ከብር 2.07 ለአንድ አሜሪካ ዶላር ወደ 52 ብር ለአንድ የአሜሪካ ዶላር የረከሰ ሲሆን፣ ይህም በእነዚህ ዓመታት የኢትዮጵያ ብር የረከሰበት መጠን ከ2,426% በላይ ሁኗል ማለት ነው፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ በእጅጉ እየናረ ለመጣው የዋጋ ንረት ሌላው ዓይነተኛ ምክንያት ይኸ የብርን የምንዛሬ መጣኔ የማርከስ ፖሊሲ ነው፡፡
4ኛ/ ከገብያ ኢኮኖሚ መርሆ ውጭ በነገድ ፖለቲካ ተፅእኖ የተዋቀረው እና የተበላሸው የግብይት ስርዓት ሌላው ለዋጋ ንረት በከፍተኛ ደረጃ መጨመር አብይ ምክንያት ነው፡፡ የገብያ ኢኮኖሚ በሰፈነባቸው ምዕራባውያን ሀገሮች በንግድ ዘርፍ ያለው የትርፍ መጠን በአማካኝ ከ15 – 20% ሲሆን፣ በሃገራችን የነጋዴው የትርፍ መጠን ከ100% እስከ 200%፣ አንዳንድ ጊዜ ከዚህም በላይ እንደሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጥናት ያረጋግጣል፡፡ የሃገራችን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ካዘጋጇቸው አንዳንድ ጥናቶች ለመገንዘብ እንደሚቻለው፣ በአሁኑ ጊዜ ከ500,000 በላይ በችርቻሮ የተሠማሩ ነጋዴዎች ሲኖሩ፤ ዋና ዋና ትላልቅ የጅምላ አስመጭዎችና አከፋፋዮች ከ30 እና 40 እንደማይበልጡ ይጠቁማሉ። ከህውሓት ዘመን ጀምሮ በብልፅግና የአገዛዝ ዘመንም የቀጠለው መንግሥት ከእነዚህ ዋና የጅምላ አስመጭዎች እና አከፋፋዮች ጋር ያለው ግንኙነት በኪራይ ሰብሳቢነት ግንኙነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ፣ ሌላኛው ለዋጋ ንረት ምክንያት እንደሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ያካሄዷቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ ፡፡ በዚህ ግንኙነት ምክንያት የመንግሥት አግባብ ያላቸዉ ተቆጣጣሪ መ/ቤቶች እነዚህን ዋና ዋና አስመጭና አከፋፋይ ድርጅቶች እንዲቆጣጠሯቸው አይፈለግም። ባንፃሩ እነሱ መስሪያቤቶቹን ተቆጣጥረዋቸዋል ማለቱ ይቀላል፡፡ በፕሮፖጋንዳ ደረጃ መንግሥት ለዋጋ ንረቱ መጨመር አነስተኛ ነጋዴዎችን በስግብግብነት ቢወነጅልም፣ ለዋጋ ንረቱ ቅጥ ማጣት የጅምላ አስመጭዎችና አከፋፋዮች ለቸርቻሪዎች በምን ያህል ዋጋ እንደሚያከፋፍሉ ገበያን የመቆጣጠርና የማረጋጋት ሚና አለኝ የሚለው የንግድና የቀጠናዎች ትስስር ሚ/ር ሲተነፍስ አይሰማም፡፡ ገብያን ለማረጋጋት ኃላፊነት የተሰጣቸው መንግሥታዊ ተቋማት ተልእኳቸውን በሚገባ አለመወጣታቸው ለዋጋ ንረቱ መባባስ አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩ የሚካድ አይደለም፡፡
5ኛ/ ተቋማዊ ሙስና፡- ከታች እስከ ላይ በመንግሥት ቢሮክራሲ ዉስጥ የተንሰራፋው ሙስና በሰጭው ዘንድ እንደ መደበኛ ወጪ እየተቆጠረ፣የዋጋ ንረቱን ወደ ተጠቃሚው ህብረተሰብ ማስተላለፍ የተለመደ ክንውን ሁኗል። በህዝቡ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ አየጨመረ የመጣውን የዋጋ ንረት ተመርኩዞ ለሚከሰተው የኑሮ ውድነት አንዱ ዓይነተኛ ምክንያት ተቋማዊ ሙስና ነው፡፡ ይህን ምክንያት በተመለከተ ማስተዋል የሚያስፈልገው በሃገራችን ያለው ሙስና በግለሰብ ባለሥልጣናት የሚፈጸም አስተዳደራዊ/ቢሮክራሲያዊ ሙስና ላይ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ ወደ ተቋማዊ ሙስና (Institutional Corruption) ደረጃ የተሸጋገረ የመሆኑ ገዳይ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ሙስና ከአስተዳደራዊ/ቢሮክራሴያዊ ሙስና ደረጃ አልፎ ተቋማዊ ሙስና ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አስተዳደራዊ ሙስና ማለት የመንግሥት ባለሥልጣኖች ለራሳቸው የግል ጥቅም ለማግኘት ሲሉ፣ በሥራ ላይ ያሉ ህጎችን በማጣመም ወይም እንደሌሉ በመቁጠር የሚፈፅሙት ህገ ወጥ የግል ብልፅግና የማግኘት ዘይቤ ነው፡፡ በአንፃሩ ተቋማዊ ሙስና የሚባለው ግን በህዉሃት/ኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን በጉልህ እንደታየዉ ገዥ ፓርቲዉ በበላይነት የሚመራቸዉን የመንግሥት ተቋማት ማለትም የህግ አውጭውን እና አስፈፃሚ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር፣ በሥራ ላይ ያለውን ህግ ለፓርቲዉ እና ፓርቲዉ ቁሜለታለሁ ለሚለዉ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል እንዲጠቅም በማድረግ ህግ የመደንገግን፣ እንደ ብሄራዊ እና የንግድ ባንኮች ያሉ የፋይናንሰ ተቋማት ለገዥ ፓርቲዉ ኩባንያዎች መገልገያ መሳሪያ ማድረግን፣ ከሃገሪቱ ህግ ዉጭ የፓርቲ ኩባንያዎች እንደ ግል የአክሲዮን ኩባንያዎች እንዲመዘገቡ በማስደረግ፣ በሃገር እና በህዝብ ሃብት እንደፈለጉ እንዲጠቀሙበት ማድረግን ያጠቃልላል። በአጠቃላይ “መንግሥትን በምርኮ በመያዝ “ (State Capture) እና በመንግሥት ዉስጥ ”ስዉር መንግሥት” (Shadow State) በማቋቋም፣ የገዥ ፓርቲው ጉምቱ አባላት ፓርቲዉ ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠራቸው ቁልፍ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ወሳኝ ባለሥልጣናት እንዲሆኑ በመመደብ “መንግሥትን የውንብድና ማስፈፀሚያ መሣሪያ “(Criminalization of the State) ሲያደርጉት ነው፡፡
በልማት ኢኮኖሚ ጥናት (Development Studies) ይህ ክስተት በዚሁ(criminalization of the state) በተሰኘዉ ስያሜው የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህ ክስተት እውን በሆነበት ሀገር መንግሥት የሚባለው ተቋም ከፊት ለፊት በሚታዩት ባለሥልጣናት ሳይሆን “ስውር መንግሥቱን” ተቧድነዉ በሚመሩት ለፓርቲዉ ታማኝ በሆኑ ከፍተኛ ካድሬዎች አማካይነት መንግሥታዊ ውንብድናን መፈፀም የመንግሥት ቋሚ ተግባር የሆነበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ክስተት በሃገር ሃብት አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ መዛባትን በመፍጠር የሃገር ሃብት ከመካከለኛውና በስፋት ከሚገኘው ዝቅተኛ ገቢ ከሚያገኜው የህብረተሰብ ክፍል ጉሮሮ ተነጥቆ ወደ ገዥ ፓርቲዉ እና ለፓርቲዉ ተባባሪ ወደሆኑ ባለሃብቶች የሚሸጋገርበት ክስተት ነው፡፡ የኢትዮጵያን መንግሥት ከሌሎች “በምርኮ ከተያዙ መንግሥታት” የሚለየው በኢኮኖሚው ውሥጥ ለሚታየው ተቋማዊ ሙስና መሰረት የሆነዉ የነገድ ፖለቲካው (ethnic politics) የመሆኑ ሁኔታ ነው፡፡ በነገድ አንድነት ላይ ተመርኩዞ የመንግሥት ስልጣንን በመያዝ የሃገር ሃብትን የመዝረፍ ባህል ልክ እንደ ህወሓት/ ኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን አሁንም በኦህዴድ/ የብልጽግና አገዛዝ ዘመን ዳብሯል። በቅርቡ የብልጽግና መንግሥት የሃብት ምዝገባ መርሃግብር ተጠናቀቀ በተባለበት ጊዜ፣ ዋዜማ የዜና ምንጭ አጣራሁ ብሎ ባወጣዉ ዘገባ መሰረት፣ ከ 2.3 ሚሊዮን የመንግሥት ሰራተኞች መካከል ሃብታቸዉን ይፋ አድርገዉ ያስመዘገቡ 72 ሽህ ብቻ መሆናቸዉ፣ በመንግሥታዊ ቢሮክራሲዉ ዉስጥ ሙስና ምን ያህል ስር እንደሰደደ ያመለክታል። ስለዚህ በሃገሪቱ ውስጥ ለዚህ አይነት የተንሰራፋ ሙስና መሰረት የሆነዉ የነገድ ፖለቲካ በህግ ሳይታደግ በኢኮኖሚው ውስጥ የተንሰራፋውን ተቋማዊ ሙስና ማስወገድ አይቻልም፡፡ ተቋማዊ ሙስና በተንሰራፋበት ሁኔታ ደግሞ በህብረተሰብ ዉስጥ ማህበራዊ ፍትህን የተመረኮዘ የሃብት ክፍፍል ሊኖር አይችልም።
6ኛ/ ባለፉት ሁለት ዓመታት በብልፅግና እና በህወሓት መካከል እየተካሄደ የነበረዉ ጦርነት በኢትዮጵያ ሃገራዊ ብሄረተኝነት ሁለገብ አሸናፊነት ሊጠናቀቅ የሚችልበት ሁኔታ ካልተፈጠረና፣ ለነገድ ፖለቲካው በመሣሪያነት እንዲያገለግል እስከተፈለገ ድረስ የተኩስ አቁሙ ስምምነት ዘላቂነት አጠራጣሪ ስለሚሆን፣ የኢኮኖሚ ቀውሱ እየባሰበት እንጂ እየተሻለው ሊሄድ አይችልም፡፡ እንደሚታወቀው ጦርነት የሃገር ሃብትን ለልማት ሳይሆን ለጥፋት የሚያውል አውዳሚ ክስተት ነው፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ለመከላከያ የሚውለው የመንግሥት በጀት ባለፉት አራት ዓመታት በየዓመቱ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የበጀት ጉድለት እንዲከሰት አድርጓል፡፡ የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት ደግሞ ይህን በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣ የበጀት ጉድለት በአብዛኛው ሲያሟላ የቆየዉ መጠኑ ብዙ የሆነ ገንዘብ በማተምና ወደ ገብያው እንዲረጭ በማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም ለዋጋ ንረቱ ሌላኛው ምክንያት አሁን የሰላም ስምምነት ተፈረመ እስከተባለበት ጊዜ ድረስ አላባራ ያለው ጦርነት ነው፡፡ ጦርነቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎች ከግብርና ሥራቸው እንዲፈናቀሉ እና የምግብ እርዳታ ፈላጊ እንዲሆኑ ማድረጉ፣ የምርት አቅርቦት ሳይጨምር ወይም እየቀነሰ ባለበት ሁኔታ የምርት ፍላጎት እየጨመረ ስለሚሄድ፣ በተላይ ለምግብ እህል ዋጋ መናር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል። እንደሚታወቀው የኦሮሙማው የኦህዴድ/ የብልፅግና መንግሥት ደግሞ በነገድ ፖለቲካ አራማጅነት እና በአማራ ጥላቻ አምሳያው የሆነው ህውሓት የስልጣን ተቀናቃኙ የማይሆንበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንጅ፣ ህውሓት ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ጨርሶ እንዲወገድ አይፈልግም፡፡ በአንደኛ እና ሁለተኛ ዙር ጦርነቶች ወቅት የብልጽግና መንግሥት ጦርነቱ እንዲራዘም ማድረጉ፣ ለሃገሪቱ የኢኮኖሚ መዳሽቅ የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ቅኝት አስተዋጽኦ ማድረጉ የማይካድ ነው፡፡
ከእነዚህ ዋና ዋና ምክንያቶች በተጨማሪ በሃገራችን ላለው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ተጨማሪ ተጓደኝ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነሱም መካከል አንዱ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ የተፈቀደው የፍራንኮ ቫሉታ ንግድ በባንክ ውጭ ምንዛሬ ተመንና በጥቁር ገብያው የውጭ ምንዛሬ ተመን መካከል ያለው ልዩነት እየሰፉ እንዲሄድ ማድረጉ እየታየ ነው፡፡ የእቃዎች ዋጋ ከጥቁር ገብያው የምንዛሬ ተመን መጨመር ጋር የተገናዘበ እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በገብያ ውስጥ የእቃዎች ዋጋ እየተወሰነ ያለው በፍላጎት እና አቅርቦት ብቻ ሳይሆን፣ በአብዛኛው የጥቁር ገብያን የምንዛሬ ዋጋ መሠረት እያደረገ በመሆኑ፣ ለዋጋ ንረት መባባስ ይህ በባንክ የብር /ዶላር የምንዛሬ ተመን እና በጥቁር ገብያው የምንዛሬ ተመን መካካል ያለው ልዩነት እየሰፋ መሄድ ለዋጋ ንረቱ መባባስ አስተዋፅኦው ጉልህ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በሃገራችን ፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት የዉጭ መዋእለነዋይ እየቀነሰ መምጣትም ለምርትና አገልግሎት እጥረት ብሎም ለዋጋ ንረት መጨመር ሌላው ምክንያት ነዉ።
- የኢኮኖሚ ችግሮች ማጠቃለያ
ከ1997 የምርጫ ሽንፈት በኋላ ህወሓት በልማታዊ ኢኮኖሚ ፅንሰሃሳብ ቅኝት ለተከታታይ ሁለት አስርት ዓመታት ከአፍሪካ አማካይ የኢኮኖሚ እድገት በላይ የሆነ እድገት ማስመዝገቡ አይካድም፡፡ የዚህ የእድገት ምንጭ ኢኮኖሚውን ከመዋቅራዊ የኋላቀርነት አዙሪት ቀለበት በሚያወጣ መልኩ አምራች በሆኑት የግብርና፣ ኢንዱስትሪ እና የማእድን ክፍላተ ኢኮኖሚዎች እድገት የተገኜ ሳይሆን፣ በመሰረተ ልማት (መንገድ ሥራ፣ በባቡር ሃዲድ መስመር ዝርጋታ እና የአየር ማረፊያዎች ግንባታ፣ በትምህርት እና ጤና ተቋማት ግንባታ) እንዲሁም በከፍተኛ ፕሮጀክቶች ማለትም እንደ ትላልቅ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች፣ ተጠናቀው ባላለቁ የስኳር ፋብሪካዎች፣ ወዘተ…) ላይ በርካታ ገንዘብ በማፍሰስ የተገኜ እድገት ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ ሊባል የሚችል የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ መሰረተ ልማት ግንባታ እጅግ ግዙፍ የውጭ ምንዛሬ እና የሃገር ውስጥ ገንዘብን የጠየቀ ነበር፡፡ ይህ በውጭ ምንዛሬ የተገኘ ብድር እና እርዳታ በንጉሡ ዘመንም ሆነ በደርግ የአገዛዝ ዘመን ሊገኝ ያልቻለ፣ የምእራቡ ዓለም ለኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግሥት ሥልጣን ላበቃው ለህውሓት/ኢህአዴግ መንግሥት ሊሰጠዉ የቻለዉ፣ የወያኔ መንግሥት የምእራቡ ዓለም ጉዳይ አስፈጻሚ ሁኖ በማገልገሉ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚ/ር አብይ አገዛዝም ጸረ አሜሪካ አቋም እንደሌለዉ አሜሪካኖች ጠንቅቀው ያውቃሉ።ጠቅላይ ሚ/ር አብይ በቅርቡ ለአንድ አሜሪካዊ መልክተኛ “ እኔ ለአሜሪካ ልሞት የተዘጋጀሁ ነኝ “ ሲሉ መናገራቸው ይህንኑ ነጥብ የሚያጠናክር ነዉ።
የምዕራቡ ዓለም ህውሓት/ኢህአዴግ የኢትዮጵያ መንግሥትን ስልጣን ከተቆጣጠረ ጀምሮ በቆየባቸዉ 27 ዓመታት፣ የብልጽግናን ከአራት ዓመት በላይ የአገዛዝ ዘመን ጨምሮ ላለፉት ሠላሳ አንድ በላይ ዓመታት ከ 110 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የዉጭ ምንዛሪ በብድርና በእርዳታ ወደ ሃገራችን እንዲገባ አድርጓል፡፡ በ2011 (2019 በፈረንጅ) ብቻ በአሜሪካ ይሁንታ የብልጽግና ፓርቲ ለሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ከአይ ኤም ኤፍ ፣ከዓለም ባንክ እንዲሁም ከሁለትዮሽ ግኑኝነት ዘጠኝ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፈሰስ የተደረገ ሲሆን፣በ2014(በ2021 አውሮፓ አቆጣጠር) ኢትዮጵያ ከግብጽ ቀጥላ በአፍሪካ ሁለተኛዋ የአሜሪካ የእርዳታ ተቀባይ ሃገር መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ። ብዙም የዉጭ እርዳታ እና ብድር ያልተገኜበትን ሃምሳ ዓመታት የሚጠጋውን የንጉሡ ዘመን ትተን፣ አስራ ሰባት ዓመታት በቆየው የደርግ የአገዛዝ ዘመን ኢትዮጵያ ከምእራቡ ዓለም በእርዳታ እና በብድር መልክ በዉጭ ምንዛሪ ያገኜችው ለልማት ሊውል የሚችል ገንዘብ(Official Development Assistance) ከ 7.3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚበልጥ አልነበረም፡፡
እንደሚታዎቀዉ የምዕራቡ ዓለም የሚሰጠው እርዳታ እና ብድር በሰብዓዊነት መመዘኛ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ መንግሥት የካፒታል እና የመደበኛ ባጀት ጉድለትን ለማካካስ እንዲውል የተመደበን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የህወሓት/ኢህአዲግ መንግሥትም ሆነ የሱ ውላጅ የሆነው የኦሮሙማዉ የኦህዴድ/ የብልፅግና መንግሥት በግድ ማሟላት የነበረባቸው (Conditionalities) ነበሩ፤ አሁንም አሉ፡፡ ይህን የውጭ የመዋእለ ነዋይ ፍሰት ለማግኘት የህወሓት/ኢህአዴግም ሆነ የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት ማሟላት የነበሩባቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲ እርምጃዎች የሚከተሉት ነበሩ፣አሁንም ናቸዉ ፡-
1ኛ/ ብር ከዶላር ጋር ያለውን የምንዛሬ ጥምረት እንዲረክስ ማድረግ /Devaluation/
2ኛ/ መንግሥት ለግሉ ዘርፍ አመች እንቅስቃሴ መሰናክል የሆኑ ደንቦችን፣ መመርያዎችን እና አሰራሮችን መሰረዝ እና የሚሻሻሉትን ማሻሻል፣(Deregulation)
3ኛ/ መንግሥት በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የቁጥጥር ሚና እንዲያለዝብ ማድረግ (Liberalization)
4ኛ/ የሃገር ውስጥ ገበያን ላልተገደበ የውጭ ካፒታል ተሳትፎ ክፍት እንዲሆን ማድረግ ወዘተ… እና ከዚህ ተዛማጅ የሆኑ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ዘርፍ እርምጃዎችን መዉሰድ፣(opening the national market to foreign competition in the name of globalization)
5ኛ/ የመንግሥት ትላልቅ የኢኮኖሚ ተቋማትን ማለትም እንደ ኢትዮ ቴሌኮም፣ አየር መንገድ፣ ባንኮች ያሉትን እንደ ምድር ባቡር፣ የመርከብ አገልግሎት ያሉ የሎጅስቲክ ተቋማትን፣የኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅራቢ የሆነውን መብራት ኃይልን በከፊል ወይም በሙሉ ወደ ግል ይዞታ ማዛወር /Privatizatcon/ ወይም በሌላ አነጋገር እነዚህን ትላልቅ የሃገር ዉስጥ መንግሥታዊ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ለዉጭ ኩባንያዎች መሸጥን የሚያጠቃልሉ ናቸዉ።
በህዉሃት እና በብልጽግና መንግሥት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ብድር/ድጎማ አላቅም ብሎ የነበረዉ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት አሁን ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ወዲያዉኑ አስተናግዳለሁ ማለቱ፣ የጦርነት መቆም ሌላ ተጨማሪ አስገዳጅ ሁኔታ እንደነበር መገንዘብ አያዳግትም።
በሃገራችን የኢኮኖሚ ሙያ ጠበብት በተለይም የኢኮኖሚ ፖሊሲ አጥኝ በሆኑ የልማት ፖሊስ ሃሳብ አመንጭዎች (Development Studies Experts) መካከል የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለዓለም ገበያ ብርግድ አድርጎ በመክፈት፣ ገርበብ አድርጎ በመክፈትና ጨርሶ አለመክፈትን በሚመለከት የተጧጧፈ ክርክር ሲካሄድ ቆይቷል፤ አሁንም በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ብርግድ አድርጎ በመክፈትና ባለመክፈት መካከል ተሟጋች የልማት ፖሊሲ አመንጭ ምሁራን ዘንድ እየቀረቡ ያሉ አስተያየቶች የራሳቸው ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንዳላቸው የሚቀበሉ የልማት ፖሊሲ አመንጭዎች ሌላ ሶስተኛ ጎራ ፈጥረዋል፡፡ ሦስተኛው ጎራ የሁለቱንም ደካማ ጎኖች በመተው ጠንካራ ጎናቸውን በማቀናጀት ተግባር ላይ ማዋል ይቻላል ብሎ ያምናል። ኢኮኖሚውን ለውጭ ውድድር የመክፈቱ ፖሊሲ ከውጭ ተፅእኖ ነፃ በሆነ መልኩ መከናዎን አለበት፣ በሩን በአንድ ጊዜ ብርግድ አድርጎ መክፈት ሳይሆን፣ተለቅ ተልቅ ያሉ የሃገር ውስጥ መንግሥታዊም ሆኑ የግል ድርጅቶች/ ኩባንያዎች ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን አቅም ከገነቡ በኋላ ቢከፈት ይሻላል የሚል ነው፡፡ የሃገራችን ኢኮኖሚ ከተተበተበበት የኋላቀርነት አዙሪት ቀለበት ሊያስወጣ የሚችለው የእድገት ጓዳና ይህን ዓይነት ኢኮኖሚዉን ለዉጭ ዉድድር የማዘጋጀት ፖሊሲ የተከተለ ሊሆን ይገባል የሚል ነው፡፡
ሶስተኛዉ ጎራ በሃገራችን በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ያሉ ኩባንያዎች አብዛኛዎቹ በካፒታል፣ በሥራ አመራር ልምድ እና በገብያ ትስስር እንዲሁም በዘመናዊ ቴክኖሎጅ አጠቃቀም ገና ባልዳበሩበት ሁኔታ፣ ኢኮኖሚውን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ማድረግ፣ ተወዳዳሪ ያልሆኑ የሃገር ውስጥ ኩባንያዎች በውጭ ኩባንያዎች እንዲዋጡ፣ ወይም ከገበያው እንዲወጡ የማድረግ ውጤት ስለሚኖረው፣ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በውጭ ኩባንዎች ተፅእኖ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ ያደርጋል ብሎ ያምናል። በዚህ ሂደት የሚገኝው ውጤት ሚዛን ያልጠበቀ የኢኮኖሚ እድገት (Economic Gronth) ሊሆን ቢችልም፣ እድገትን (Growth) ከማህበራዊ ፍትህ (social equity) ጋር ያቀናጀ የኢኮኖሚ ልማት (Econoimic Development) አያስገኝም የሚል እምነት አለዉ፡፡
በተለይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የተለጠጠ አደረጃጀታቸው ወጪ ቆጣቢ እንዲሆኑ አላደረጋቸዉም። የአስተዳደር እና የአመራር ነፃነት ስለሌላቸው አትራፊም ሆነ ተወዳዳሪ ሲሆኑ አልታየም። በመሆኑም ትላልቅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከተፈለገ የተሟላ የአስተዳደር እና የአመራር ነፃነት (Management autonony) ሊኖሯቸው የግድ ይላል፡፡ ይህም ማለት የመንግሥት የልማት እና የአገልግሎት ድርጅቶች የነገድ የፖለቲካ ድርጅቶች ካድሬዎች የሚፈነጩባቸው ሊሆኑ አይገባም ማለት ነው። የሃላፊዎች ምደባም ሆነ በተዋረድ የሚደርግ ምደባ፣ እድገት ወዘተ ከሙያ ብቃት አንጻር ብቻ እንጅ ከነገድ ማንነት ጋር ጨርሶ ሊገናኝ አይገባም ማለት ነው፡፡
ሁለተኛውን አማራጭ የሚያራምዱት ደግሞ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ከዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መልክ የልተሣሠረ ዝግ የሆነ ሃገራዊ ኢኮኖሚ ስለሌለ፣ ፍፁም ዝግ የሆነ፣ የውጭ ውድድርን የማያስተናግድ የኢኮኖሚ ሞዴል እንከተል ማለቱ ትክክል ስለማይሆን፣ የሃገራችን ኢኮኖሚ ለውጭ ውድድር ክፍት መሆን አለበት ይላሉ፡፡ ሶስተኛውን የፖሊሲ አቅጣጫ የሚደግፉ የኢኮኖሚ ምሁራን ደግሞ በውድድር አለንጋ የማይሸነቆጡ የሃገር ውስጥ ኩባንያዎች ምንጊዜም ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ ሊሆኑ ስለማይችሉ፣ ኢኮኖሚው ለውጭ ውድድር ክፍት መሆኑ የሃገር ውስጥ ኩባንያዎች ጠንክረው ተወዳዳሪ ሁነው እንዲወጡ ይረዳል የሚል አመለካከትን ያራምዳሉ። የሁለተኛዉ እና የሶስተኛዉ ጎራ ልዩነት ኢኮኖሚዉ ለዉጭ ዉድድር የሚከፈትበት ጊዜ መች እና ምን ሁኔታዎች ሲሟሉ ነዉ በሚሉ ነጥቦች ብቻ ነዉ የሚለያዩት።
ሶስተኛዉ ጎራ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ወደ ሃገር ዉስጥ መጋበዝ የሚኖርባቸዉ ተለቅ ተለቅ ያሉ የሃገር ዉስጥ ኩባንያዎች ትክክለኛ በሆነ የመንግሥት የፖሊሲ ድጋፍ ከውጭ ኩባንያዎች የሚያጋጥማቸዉን ውድድር በብቃት መቋቋም እና አትራፊ ሆኖ መቀጠል የሚችሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ከተደረጉ በኋላ፣መንግሥት የዉጭ ኩባንያዎችን የረቀቀ አሰራር ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅሙን በአስተማማኝ ደረጃ ከገነባ በኋላ ቢሆን ይመረጣል የሚል አቋም ያራምዳል። ከዚህ በኋላ የሃገር ዉስጥ ኩባንያዎች ለውጭ ውድድር ቢጋለጡ፣ ተወዳዳሪነታቸው ለውጤታማነታቸው መንደርደሪያ ሆኖ ይበልጥ ጎልብተው ለሃገር ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እና ለተገልጋዩ ህብረተሰብ እርካታን ሊያስገኙ ይችላሉ የሚል የፖሊሲ ሃሳብ ያራምዳል፡፡
ካለፉት በርካታ ዓመታት ተግባራዊ ክንውን እንደታየው ደግሞ ሁሉም የግል ድርጅቶች ውጤታማ፣ ሁሉም በመንግሥት ይዞታ ስር ያሉ ድርጅቶች ደካማ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ በመንግሥት ይዞታ ስር ሁነው በአንጻራዊ መልኩ የአመራርና የአስተዳደር ነፃነት የተጓናፀፉት በተለይ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም ኢትዮ ቴሌኮም ያሉት ውጤታማ ሁነው ከመገኘታቸውም ባሻገር ለሃገራችን ኩራት ሁነዋል፡፡ይኸ አባባል መብራት ኃይልንም ይጨምራል። እነዚህ መንግሥታዊ የአገልግሎት ዘርፍ ድርጅቶች ላለፉት ሰላሳ በላይ ዓመታት የአስተዳደር ነፃነታቸዉ በገዥ ፓርቲዎች ጣልቃገብነት ተነጥቆ በነበረበት ሁኔታ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ከቻሉ፣ አግባብነት የሌለው መንግሥታዊ ጣልቃገብነት ከእነአካቴው ቢወገድላቸው እና ሙያን መሠረት ያደረገ (meritocracy) አሠራርን ተከትለዉ ቢሆን ኑሮ፣ አሁን ካስመዘገቡት የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ይችሉ እንደነበር መገንዘብ አያዳግትም፡፡ እነዚህን ኩባንያዎች መንግሥት እራሱ አለአግባብ ጣልቃ እየገባ ሲያውካቸው ከከረመ በኋላ ይህንንም ጣልቃገብነት ተቋቁመው ለሃገር እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የመንግሥት ኩባንያዎችን ለውጭ ኩባንያዎች በከፊልም ሆነ በሙሉ እንዲሸጡ የብልፅግና መንግሥት የሚያራምደው ፖሊሲ የዓለም የፋይናንስ ድርጅቶች ያሳደሩበትን ተፅእኖ መቋቋም ካለመቻል ወይም ካለመፈለግ የመነጨ ነዉ። ለጊዜያዊ የበጀት ችግር ማስተንፈሻ ሲባል የኢትዮጵያን ብሔራዊ ሃብት ለዘለቄታው ለባእዳን አሳልፎ መስጠት፣ እስትራቲጃዊ እይታ የጎደለዉ ፖሊሲ መሆኑ ግልፅ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ ካለፈ ደግሞ የሃገር ኩራት የሆኑ ኢትዮጵያዊ ተቋማትን ለዉጭ ሃገራት ኩባንያዎች መሸጥ፣ ከሃገራዊ ብሄረተኝነት ይልቅ ለነገድ ማንነት ቅድሚያ ከሚሰጥ የጠበበ የፖለቲካ አመለካከት ሊመነጨ እንደሚችል መጠርጠርም ይቻላል።
እነዚህ የሃገር ኩራት የሆኑ ድርጅቶች በውጭ ኩባንያዎች እንዲገዙ ከመ ፍቀድ ይልቅ ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በአቻነት እንዳይወዳደሩ የሚያደርጓቸውን መንግሥት በውስጥ የአስተዳደር ሥራቸዉ የሚያደርገውን ጣልቃገብነት በማቆምና የተሟላ የውስጥ አስተዳደር ነጻነት እንዲኖራቸው በማድረግ፣መ/ቤቶች በገዥ ፓርቲ ካድሬዎች ሳይሆን፣ ከፖለቲካ ተፅእኖ ነፃ በሆኑ ባለሙያዎች እንዲመሩ፣ ቅጥርም ሆነ እድገት ሙያን ብቻ መሰረት አድርጎ እንዲከናወን በማድረግ፣ በአጠቃላይ እነዚህ ድርጅቶች ከመንግሥት የሚደርስባቸዉ ተጽእኖ እንዲቋረጥ በማድረግ ብቻ ውጤታማነታቸውን እና ተወዳዳሪነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምሩ ለማድረግ ይቻላል፡፡ እነዚህን የሃገር ሃብት የሆኑ የመንግሥት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች መሸጥ ሳይሆን፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ስርፀት፣ በዓለም አቀፍ የገብያ ትስስር በመሳሰሉት ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በበቂ ሁኔታ ለመወዳደር የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶች እንዲያገኙ በቂ ድጋፍ በማድረግ፣ የውጭ ተወዳዳሪ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲወዳደሯቸው የሚያደርግ ፖሊሲን መከተል፣ ውድድሩን ይበልጥ ውጤታማ በማድረግ የሃገራችንን ኢኮኖሚ ልማት ሊያፋጥን ይችላል፡፡
በተጨማሪም ዉድድሩ ፍትሃዊ እንዲሆን የዉጭ ኩባንያዎች ወደ ሃገር ዉስጥ እንዲገቡ ከመጋበዛቸዉ በፊት ቀደም ሲል እንደ ተጠቀሰዉ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን የዉጭ ምንዛሪ ከደንብ ዉጭ ወደ እናት ኩባንያዎቻቸዉ ከደንብ ውጪ የማሸሽ የረቀቀ አሰራር ለመከታተል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅምን መገንባት ያስፈልጋል፡፡ መደገፍ ያለበት ይህን ዓይነት የሃገራችንን የመንግሥትም ሆነ የግል ኩባንያዎች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ ሊያደርግ የሚችል በገብያ ኢኮኖሚ መርሆዎች ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው፡፡
ቀደም ባሉ ገጾች እንደተመለከተው ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የገባዉ መጠኑ ከፍ ያለ የውጭ ብድር እና እርዳታ በአቻነት ከፍተኛ የሆነ የሃገር ውስጥ ገንዘብን በተከታታይ ማተምን በማስከተሉ፣ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ለከፍተኛ የዋጋ ንረት እና ተያያዥ ለሆነው የኑሮ ዉድነት እንዲሁም እየተስፉፉ ከሄደው ምዝበራ ጋር የተያይዞ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ፍልሰትን በማስከተሉ፣ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ለከፍተኛ መናጋት ተጋልጧል፡፡
የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የመዋእለ ነዋይ ፍላጎት ክፍተት ለማሟላት በህወሓትም ሆነ በኦህዴድ/ብልፅግና የአገዛዝ ዘመን የውጭ ብድርንና በየጊዜው ገንዘብን በከፍተኛ መጠን ማተምን እንደ ዓይነተኛ መፍትሄ አድርገው መውሰዳቸው ይታወቃል፡፡ ችግሩ በከፍተኛ የውጭ ብድርና በከፍተኛ የሃገር ውስጥ ገንዘብ ህትመት ሊተገበሩ የታቀዱ ብዙዎቹ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ከነገድ ፖለቲካው ጋር በተያያዘ እና የኪራይ ሰብሳቢነትን መሠረት ላደረገ የነገድ ፖለቲከኞች ሃገራዊ ምዝበራ እንዲሁም በሙያዊ የፕሮጀክት የአመራር እጦት ምክንያቶች ፕሮጀክቶቹ የሚጠናቀቁበት ደረጃ ላይ ደርሰው የወጣባቸውን የውጭ እዳ እና የሃገር ውስጥ ብድር ለመመለስ ሳይችሉ፣ የብድር መክፈያ ጊዜያቸው መድረሱ፣ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ የእዳ ክፍያ ጫና ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል።
የኦህዴድ/ብልጽግና መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት ከመድረሱ በፊት ያልተሳካለትን ሀገሪቱ ያለባትን የዉጭ እዳ የብድር ክፍያ ጊዜው እና የአከፋፈሉ ሁኔታ እንዲታይለት እና አስተያየት እንዲደረግለት ምእራባውያን አበዳሪ ሀገሮችን እና መሣሪያዎቻቸዉ የሆኑትን የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድርጅቶች ተለማምጦ ያልተሳካለትን፣ አሁን ከስምምነቱ በኋላ አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኝነታቸዉን ገልጸዋል፡፡ይህ ሃቅ የሚስረዳዉ ጭብጥ ምእራባዉያን ሃያላን አገሮች የፋይናንስ አቅማቸዉን በመጠቀም የብልጽግና መንግሥት በህዉሃት ላይ እየወሰደ ያለዉን የተሳካ ወታደራዊ እርምጃ በአስቸኳይ ተኩስ አቁም ስም እንዲያቋርጥ ማድረግ መቻላቸዉን ነዉ።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ የሃገራችንን ኢኮኖሚ ቀፍድደው የያዙ ችግሮች የላይ ላይ የገፅታ ምክንያቶች የብልፅግና መንግሥት እከተላለሁ የሚለው “የነፃ” ገበያ ፖሊሲዎች “(Liberal Economic Polices) ሲሆኑ፣ እውነተኛ (Real) ምክንያቱ ግን ህወሓትም ሆነ የኦሮሙማዉ የብልፅግና መንግሥታት ሃገርን ሳይሆን ነገድን መሠረት በማድረግ የያዙትን የፖለቲካ ስልጣን ለማጠናከር ፣ የውጭ ብድርና ከፍተኛ የሃገር ውስጥ የገንዘብ ህትመት ዋንኛ መሣሪያዎቻቸው ሁነው በመገኘታቸዉ ነው፡፡ ለውጭ ምዕራባውያን የበለፀጉ ሃገሮች እንጅ ለህዝቦቻቸው ተጠሪ ያልሆኑ እንደነዚህ ያሉ መንግሥታት የህዝቦቻቸውን ጥቅም ሊያራምዱ ከሚችሉ በሃገራዊ ብሔርተኝነት ላይ ከተመሰረቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ይልቅ ፣ የሥልጣን ቆይታቸውን ሊያራዝሙ ይችላሉ ብለው በማሰብ፣ የበለፀጉ ምእራባውያን ሃገሮች የሚጭኑባቸውን “የነፃ ገበያ” የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በፀጋ መቀበልን ስለሚመርጡ ነው፡፡
በመሠረቱ እንኳን አሁን የዓለም ኢኮኖሚ በጥቂት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በሞኖፖል ተይዞ በሚገኝበት ዓለም ቀርቶ፣ የካፒታሊስት ስርአት ገና እያቆጠቆጠ በነበረበት ዘመን “ነፃ ገብያ” የሚባል ኢኮኖሚ ኑሮ አያውቅም፡፡ በሶሻሊዝም ላይ የካፒታሊስቱ ስርዓት የበላይነትን ከተጎናፀፈ ከ1990ዎቹ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ጀምሮም ሆነ የአፍሪካና የእስያ ሃገሮች ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጡባቸው ከ1950 ዎቹ እና ስልሣዎቹ ዓመታት ጀምሮ ተግባራዊ የተደረጉ ሃገራዊ የኢኮኖሚ ሞዴሎች ደግሞ የገብያ ኢኮኖሚ እና የልማታዊ ኢኮኖሚ ሞዴሎች በመባል የሚታዎቁ ናቸው፡፡ የምእራቡ ዓለም የበለፀጉ ሃገሮች እና በእነሱ የሚደገፉት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በአሁኑ ጊዜ በታዳጊ ሃገሮች ላይ በ”ነፃ ገበያ” ሞዴል (Liberal Economy) ሽፋን፣ እነሱ የኢንዱስትሪ አብዮት ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ ያልተከተሉት የኢኮኖሚ ሞዴል ነው፡፡ ኢኮኖሚያችሁን ለውጭ ውድድር ክፈቱ፣ የ “ግሉባላይዜሽን” ዓለም አቀፍ ሂደትን ተቀላቀሉ” እያሉ የሚወተውቱት፣ ታዳጊ ሃገሮችን የእነሱ ጥገኛ አድርገው ለማስቀረት ነው፡፡ እንደ ቻይና፣ ህንድና ደቡብ ኮሪያ ወዘተ ያሉ በሃገራዊ ብሔርተኝነት ላይ የተመሠረተ የልማታዊ ኢኮኖሚ ሞዴል የሚከተሉ ሃገሮች በአጭር ጊዜ ምእራባውያን ሃገሮች የደረሱበት የልማት ደረጃ ላይ ያደረሳቸዉን የልማታዊ የኢኮኖሚ ሞዴል የምእራቡ ዓለም ማጥላላቱ ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ የአፍሪካ ሃገራት ብቅ እንዲሉ ካለመፈለግ የመነጨ መሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡
በዚህ ጽሁፍ ቀደም ባሉ ገጾች ለማቅረብ በተሞከሩት ትንተናዎች መሰረት በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሃገራችን ያጋጠማት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር መንግሥት የሚከተላቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ውጤት መሆኑ አጨቃጫቂ አይደለም። የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት ለሃገር እና ለህዝብ ጠቃሚ ያልሆኑ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ለመተውና ለህዝብ እና ለሃገር በሚጠቅሙ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ለመተካት የማይፈልገው ይህን ቢያደርግ ፣ ሃገራዊ ሳይሆን የነገድ ድጋፍን እና የምእራባውንን የበጀት ድጎማ እና የኢንቬስተመንት ብድር መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥልጣኑ የቆመባቸውን ሁለት እግሮቹን እንደሚያጣ ስለሚቆጥረው ነው፡፡
ከዚህ ሁኔታ ጋር በተዛመደ መልኩ ሌላ ቁምነገር መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ምእራባውያን የበለፀጉ ሀገሮች በተለይም አሜሪካ የኢትዮጵያ እንድትበታተን ወይም ፖለቲካዋ እንዳይረጋጋ አይፈለጉም።አለመፈለጋቸው ከራሳቸዉ እስትራቲጅያዊ ጥቅም አንጻር አስለተው ነው። ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ቻይናና ሩስያ እጃቸዉን ወደ አፍሪካ ቀንድ አስረዝመዉ ያስገባሉ የሚል ስጋት አላቸዉ። ጦርነቱ በአስቸኳይ በድርድር ይፈታ እያሉ በብልጽግና መንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ያሉትም ለዚህ ነዉ። ለዚህም ነው በአሁኑ ጊዜ ህወሓትና የኦህዴድ/ ብልፅግና ተቻችለው፣ በኢትዮጵያ ሃገራዊ ብሔርተኝነት ኪሣራ የነገድ ፖለቲካን አስፍነው ኢትየጵያን አብረው እንዲገዙ፣ በመሃከላቸው መጠፋፋት ሳይሆን እርቅ እንዲሰፍን ፣ በብልፅግና መንግሥት ላይ የኢኮኖሚ ጫና፣ በህውሓት ላይ ደግሞ የእርዳታ እና ዲፕሎማሲያዊ ጫና እና ተፅእኖ በማድረግ እርቅ እንዲፈጥሩ ለማድረግ የቻሉት። የጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩትን ወገኖች ሁሉ ሳያሳትፍ፣ በህዉሃት እና በኦህዴድ/ ብልጽግና መካከል በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ ተደረገ የተባለዉ ስምምነት የትግራይ ታጣቂዎችን የቡደን እና ቀላል መሳሪያዎቻቸዉን የሚያስፈታ እና የክልሉን ልዩ ኃይል የሚበትን እንደሆነ ከሚዲያ ሪፖርቶች ለመገንዘብ ተችሏል። ከህዉሃት ተፈጥሮ አንጻር ይህ አይነት ስምምነት ላይ መደረሱ ህዉሃት የሽብርተኝነት ምድቡ ተነስቶለት፣ በህጋዊነት ሽፋን ለመቀጠል የቀየሰዉ ስልት ሊሆን እንደሚችል ቢገመትም፣ ለጌዜዉም ቢሆን ጦርነቱ መቆሙ እዉን እና ዘለቄታዊ ከሆነ፣ በሃገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳደረዉ ጫና እንደሚቀንስ ስለሚታመን፣ ከዚህ አንጻር በአወንታዊ መልኩ መቀበል ይቻላል።
- የመፍትሄ ሃሳቦች
ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በአስከፊ የኑሮ ውድነት እየተለበለበና በከፍተኛ የከተማ እና የገጠር ሥራ አጥትነት እየተቸገረ ይገኛል፡፡ ይህን አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የብልፅግና መንግሥት የኢኮኖሚ ፓሊሲዎቹ የተቀመሩበትን የፖለቲካ አመለካከት መቀየር ይኖርበታል። እንደሚታወቀው 50% የሆነውን ጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት የሚያስገኘው፣ 83% የሆነውን የወጪ ንግድ ምርት የሚያቀርበው፣ 80% ለሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥራ የፈጠረው የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ነው፡፡ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ምርትና ምርታማነት ሳይሻሻል የኢትየጵያ ኢኮኖሚ ከመዋቅራዊ የኋላ ቀርነት አዙሪት ቀለበት ሊላቀቅ የሚችልበት ሁኔታ የለም፡፡ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዳያድግ ጠፍሮ የያዘው ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ህወሓትና የኦሮሙማዉ የኦህዴድ/ የብልፅግና መንግሥታት ሞተን እንገኛለን እንጅ አንቀይርም የሚሏቸውን መሬትን ለዜጋ ሳይሆን በቡድን መብት ስም ለነገድ የሰጠ፣ መንግሥትን ጂኦግራፊያዊ /አካባቢያዊ በሆነ መልክ ሳይሆን ቋንቋን ዋነኛ መመዘኛ ላደረገ አወቃቀር የዳረገ የፖለቲካ ፖሊሲን፣ ብሎም እነዚህ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች መዋቅራዊ ሁነዉ እንዲቀጥሉ ያስቻላቸዉን ሕገመንግሥት መቀየር የግድ ይላል፡፡ የሕገመንግሥቱ መቀየር ከሚያስከተለዉ የተመቻቸ የፖለቲካ መደላደል ዉጭ አሁን በሕገመንግሥቱ የፖለቲካ ቅኝት የተነደፉ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን መቅረፅም ሆነ ተግባራዊ ማድረግም አይቻልም፡፡
3.1 ከመሬት ፖሊሲው እንጀምር
በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላጋጠመው ከፍተኛ ቀውስ እና ለዋጋ ንረቱ መባባስ ቀደም ሲል ከተገለፁ ለሃገርና ለህዝብ የማይጠቅሙ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በተጨማሪ የመሬት አቅርቦትና በመሬት የመጠቀም መብት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መሄድ ዓይነተኛ ምክንያት ሊሆን በቅቷል፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2013 የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማህበር ባካሄደው ጥናት 96 በመቶ የነበረው መሬትን የማቅረብና በመሬት የመጠቀም መብት በ2021 ወደ 21 በመቶ ዝቅ ብሏል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግር ሊቀረፍ ያልቻለዉ፣ ለግብርና እና ከግብርና ጋር ለተሳሰረው አግሮ- ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ወሳኝ የሆነው መሬትን በአግባቡ የመጠቀም መብት እየተሻሻለ ሳይሆን እየዘቀጠ በመሄዱ፣ በኢኮኖሚው ላይ እያሳደረ ያለው ጫና በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ነዉ። ይህም ሊሆን የቻለው ቀደም ሲል ህወሓት አሁን ደግሞ የኦህዴድ/የብልፅግና መንግሥት ከሚከተለው የነገድ ፖለቲካ አንፃር፣ መሬትን በአሁኑ ጊዜ ማግኘት የሚቻለው አንድም በሙስና አለበለዚያም ደግሞ በወረራ በመሆኑ ነው፡፡ ትልቁ የሃገራችን ሃብት መሬት ሲሆን፣ መንግሥት ፖለቲካን መነሻ በማድረግ በሚከተለው የመሬት ፖሊሲ ምክንያት ይኸ ትልቁ የሃገራችን ሃብት ታንቆ እየመከነ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ መሬት ብቻ ሳይሆን በመሬቱ ላይ የሚገኘው ብዛት ያለው የሰው ጉልበት በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ ሳይውል፣ ኢኮኖሚው ለከፍተኛ ሥራ አጥነትና የተደበቀ ስራ አጥነት(Disguised unemployment)፣ ለከፍተኛ የዋጋ ንረት እየተጋለጠ መሆኑን የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ አባል የሆነበት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር እንዲካሄዱ ያስደረጋቸዉ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
መሬት የኢኮኖሚ መሣሪያ ሳይሆን የፖለቲካ መሣሪያ (Instrument) እንዲሆን በመደረጉ፣ ሰፊ ምርታማ ሊሆን ይችል የነበረ የመሬት ሃብት እየባከነ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በህወሓት እና በብልፅግና ዘመን መሬትን የመሸጥ የመለወጥ መብት ለባለሥልጣናት እንጅ ለገበሬው የተሰጠ ባለመሆኑ፣ ባለሥልጣናት እየከበሩ ገበሬው የሚደኸይበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ዋጋ ከሆንግኮንግ፣ሲንጋፖር፣ሻንጋይ፣ኒውዮርክ እና ቶኪዮ ከተሞች የመሬት ዋጋ ጋር ተነፃፃሪ እንዲሆን ያደረገው በመሬትና በመሬት ነክ አገልግሎቶች ሙስናና ብልሹ አሠራር በመስፈኑ ነው፡፡ መሬትን በሊዝ ጨረታ የማቅረቡ ሂደት በከተማው ውስጥ ያለውን የመሬት ፍላጎት ያላገናዘበ፣ በቁጥ ቁጥና በተራዘመ ጊዜ የሚካሄደው በጨረታ የሚሰጥ የመሬት አቅርቦትን በከተማዉ ካለው መሬትን የማልማት ፍላጎት በእጅጉ ያነሰ በመሆኑ፣ መሬት ደግሞ ለግብርናም ሆነ ለኢንዱስትሪ ምርቶች ለአገልግሎት ዘርፍ ዋንኛ ግብአት በመሆኑ ፣ መንግሥት የተከተለው የከተማ የመሬት ፖሊሲ ለአጠቃላዩ የዋጋ ንረት እየጨመረ መሄድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጥናት ያመለክታል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከመላው አፍሪካ አራሹ ገበሬ ለሚያርሰው መሬት ባለቤት ያልሆነባት ብቸኛዋ ሃገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ በኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚሆነው በገጠር የሚኖረው ህዝብ ሃያ በመቶ የሚሆነውን በከተማ የሚኖር ህዝብ መቀለብ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣በአገሪቱ ባለዉ የመሬት ፖሊሲ ምክንያት ለራሱ የሚሆን በቂ ምርት ለማምረት አልቻለም፡፡ በአንፃሩ የገበሬው የመሬት ባለቤትነት በተረጋገጠባቸው የዳበሩ ሃገሮች አምስት በመቶ እና ከዚያ በታች የሆነ በገጠር የሚኖር አራሽ ዘጠና አምስት እና ከዚያ በላይ የሆነውን የከተማ ህዝብ በበቂ ሁኔታ ይቀልባል፡፡ በኢትዮጵያ የመሬትን ፖሊሲ በመለወጥ ብቻ ረሃብና እርዛትን ብቻ ሳይሆን፣ የምግብ እጥረትን ከነአካቴዉ በማስወገድ የኑሮ ውድነትን መቀነስ እንደሚቻል በርካታ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
ለዚህ ተጨባጭ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ መስከረም 25/2015 ዓ.ም ባወጣው እትሙ ላይ ይህን ርእስ በተመለከተ አንድ በገጠር ይኖሩ የነበሩ እናቱን ለመቅበር ከውጭ ሃገር የመጣ ዲያስፖራ ወደ ገጠር ሂዶ ያጋጠመውን ተሞክሮ በሚከተለው አኳኋን ጋዜጣው አትቶ አቅረቦታል፡፡ የእናቱን ለቅሶ ለመድረስ ወደ ገጠር የሄደው ሰው በሄደበት ጊዜ እህል ተስብስቦ ያለቀበት ወቅት ስለነበረ፣ የእርሻ መሬቱ ሁላ ሳይታረስ ባዶ ሆኖ ይመለከታል፡፡ ከተመለከታቸው የእርሻ መሬቶች መካከል አንደኛው ከሌሎች እርሻ መሬቶች በተለየ ሁኔታ በመሃሉ አንድ አነስተኛ ምንጭ ያልፍበታል። ይህ ከውጭ የመጣ ሰው ለምንድነው የምንጩን ውሃ በመጠቀም የመሬቱ ባለቤት በበጋ ወቅት የተለያዩ ምርቶችን የማያመርተው ብሎ ራሱን ይጠይቃል፡፡ ለጥያቄው መልስ ለማግኘት የነበረው ጉጉት ዘመዶቹ የመሬቱ ባለቤት ቤት እንዲወስዱት እንዲጠይቅ ይገፋፋዋል፡፡ የመሬቱ ባለቤት (ይቅርታ ትክክል የሚሆነዉ ተገልጋይ ቢባል ነዉ) ቤት ደርሶ ሰላምታ ከተለዋወጠ በኋላ አባወራውን ሊጠይቅ የፈለገውን ጥያቄ ያነሳባቸዋል፡፡ መሬቱን ሰንጥቆ በሚያቋርጠው ምንጭ በመጠቀም በበጋ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ለምን ማምረት እንዳልቻሉ ይጠይቃቸዋል፡፡ የገበሬው አባወራ ጥያቄው ከፈረንጅ ሃገር የእናቱን ሃዘን ለመድረስ የመጣ መሆኑን በመገንዘብ “አየህ ልጄ አንተ እንዳልከው ይህን የያዝኩትን መሬት አቋርጦ የሚያልፈውን የምንጭ ውሃ ተጠቅሜ በበጋ የተለያዩ ምርቶች ባመርት፣ የወረዳው ሃላፊዎች(የገዥ ፓርቲ ካድሬዎች) በመስኖ የምታለማ ከሆነ ይህ ሁሉ መሬት ላንተ ይበዛብሃል ብለው መሬቱን ቆርሰው ይወስዱብኛል፡፡ በመሆኑም ክረምት ሲመጣ ብቻ ነው ጠብቄ የማርሰው” ብለው ይመልሱለታል፡፡
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሀገር መገንጠልን በመብትነት ሲፈቅድ መሬትን የሚያርስ ገበሬ ምርታማነቱን ሁለት እና ሶስት እጥፍ በመጨምር ራሱን ጠቅሞ ሃገሩን አንዳያለማ፣ ላቡን አንጠፍጥፎ በሚያርሰውን መሬት ላይ የተሟላ የባለቤትነት መብት እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ በተለይም ደግሞ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት “የነፃ ገብያ ፖሊሲ” እንከተላለን በሚሉት በህወሓት እና በብልፅግና የአገዛዝ ዘመኖች፣ ገዥ ፓርቲዎቹ በሚያራምዱት የመሬት ፖሊሲ ምክንያት ገበሬዎች የሚያርሱትን መሬት አቅማቸው እና የመሬቱ ለምነት በሚፈቅደው መጠን የእርሻ መሬታቸውን አልምተው፣ እራሳቸውንም ሆነ ሃገራቸውን እንዳይጠቅሙ የተሟላ የመሬት ባለቤትነት መብት አለመከበሩ የመሬት ምርት እና ምርታማነት እንዳይጨምር ዋንኛ ደንቃራ መሆኑ በግልጽ ሊታዎቅ ይገባል፡፡
የህውሓትም ሆነ የብልፅግና ፓርቲ መሬትን ለብሄረሰብ እንጅ የግል ገበሬ ይዞታ እንዲሆን አንፈቅድም የሚሉበት ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነው፡፡ የመሬት ባለቤት የሆኑት የክልል መንግሥታት ጢሰኛ ሆኖ ለሚገኘው ገበሬ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የሚያቀርቡት የፓርቲ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ምርጫ ሊደርስ አካባቢ መሬትን እናከፋፍላለን ብለው የሚነሱት ቀደም ሲል የህወሓት አሁን ደግሞ የብልፅግና የወረዳ እና ቀበሌ አስተዳዳሪዎች/ካድሬዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የወረዳ ካድሬዎች ገዥ ፓርቲውን ካልመረጥክ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር አታገኝም፤ መሬቱንም በገጠር ከሚገኘው ከፍተኛ የሥራ አጥነት ቁጥር አንፃር እናሸጋሽጋለን በሚል የሚነሱት ምርጫ ሊደርስ አካባቢ ስለሆነ፣ የነገድ ፖለቲካን መመሪያዉ አርጎ ለሚከተል ገዥ ፓርቲ መሬት የፖለቲካ እንጅ የኢኮኖሚ መሣሪያ ሊሆን አይችልም።
ከዚህም በተጨማሪ መሬት ለነገድ ተከልሎ መሰጠቱ በአሁኑ ጊዜ በስፋት እንደሚስተዋለው ለግድያና ለዘር ማጥፋት እንዲሁም ለተለያየ አይነት በሰብአዊነት ላይ ለሚፈጸም ጥቃት ዋንኛ መንስኤ መሆኑ በገሃድ እየታየ ነዉ፡፡ የነገድ ፖለቲካ አራማጅ ፖለቲከኞች የኢትዮጵያ ሕዝብን መሬት በቋንቋ ለሚዛመዷቸው ብቻ በመደልደል፣ በየክልሉ ለዘመናት በሰላም አብረዉ ሲኖሩ የቆዩ ሌሎች ማህበረሰቦችን በማፅዳት፣ የፖለቲካ ድጋፍ የሚሸምቱበት እና የስልጣን ዘመናቸውን የሚያራዝሙበት የፖለቲካ ስልት በሃገራችን ግጭት፣ ጦርነት እና የዘር ማፅዳት ዘመቻዎች እንዲከናወኑ በግልፅ የሚታይ ምክንያት መሆኑን መካድ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማንነትን መሠረት ካደረገ እና መዋቅራዊ ከሆነ የኋላ ቀርነት አዙሪት ቀለበት (Poverty Cycle) ለማላቀቅ፣ በወል ከተያዙ የከብት አርቢ ይዞታዎች ዉጭ ያለዉ የሚታረስ መሬት የግለሰብ ዜጋ መብት ሆኖ መሬትን የማልማት የማከራየት፣ የመሸጥ እና የመለወጥ ውሳኔ የገበሬው እና የገበሬዉ ውሳኔ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የግብርና ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግና የዋጋ ንረትን ለመከላከል ብሎም የኑሮ ውድነትን ለማቅለል የሚቻለው የኢትዮጵያ የመሬት ፖሊሲ ሲለወጥ ብቻ ነው፡፡
3.2 የነዳጅ ዋጋ አተማመን እና የነዳጅ ድጎማን ማስቀረትን በተመለከተ
የኑሮ ውድነትን በከፍተኛ ደረጃ በማባባስ ላይ የሚገኘው ሌላዉ ምክንያት መንግሥት ድጎማን በማስቀረት የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው እንዲጨምር የማድረጉ የፖሊሲ አቅጣጫ ነው፡፡ የኢኮኖሚ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የማምረቻ እና የማከፋፈያ ወጭን በመጨመር የዋጋ ንረትን በማባባስ የኑሮ ውድነት በተፋጠነ እና ቀጥተኛ በሆነ ሁኔታ እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን ያመለክታል፡፡ መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ገንዘብ በማተም የሚያካክስ እስከሆነ ድረስ ፣የነዳጅ ድጎማን ከማንሳት ቢቆጠብ የተሻለ እንደሚሆን አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
የነዳጅ ድጎማን በማስቀረት የህዝቡ የኑሮ ወድነት እንዲባባስ ከማድረግ ይልቅ በነዳጅ ግዥ አቅርቦትና ነዳጅን በማከፋፈል ረገድ ከነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጀምሮ አሁን ወደ አርባ የተጠጉ ዋና ዋና የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎችን የትርፍ ህዳግ መርምሮ ማስተካከያ ማድረጉ፣ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋን ጭማሪ ተመርኩዞ እየተከሰተ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማስታገስ ይቻላል የሚሉ ከዘርፉ ባለሙያዎች በተገኙ መረጃዎች ላይ የተመረኮዙ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ይሰማል፡፡ በዘርፉ ላይ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች ተገዝቶ ወደ ሃገር ለገባው ነዳጅ በተገቢው ሁኔታ አለመሰራጨት በኢትዮጵያ ያሉ የነዳጅ ማደያዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን በምክንያትነት ይነሳል፡፡ አነስተኛ የህዝብ ቁጥር ካላቸው ኬንያ (1900 ማደያዎች) እና ኡጋንዳ (2900 ማደያዎች) ጋር ሲነፃፀር 120 ሚሊዮን ህዝብ ባለበት ሃገራችን ያሉት የነዳጅ ማደያዎች 1,200 ብቻ መሆናቸው እና የእነዚህም ጅኦግራፊያዊ ስርጭት በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በጣም በተራራቀ ቦታ መሆኑ፣ ነዳጅ ለኮንትሮባንድ ንግድ እንዲጋለጥ ያደረገ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል፡፡ አብዛኞቹ የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ዴፖዎች የሌሏቸው መሆኑ ለኮንትሮባንድ ንግድ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከተቆጣጣሪው መስሪያ ቤት የቁጥጥር መላላት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በነዳጅ ግዥ፣ ክፍፍልና ስርጭት ሂደት የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት በሊትር 0.25 ሳምንት የትርፍ ህዳግ እንዲኖረው ሲደረግ፣ የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች በሊትር 19 ሳንቲም፣ ቸርቻሪዎቹ የነዳጅ ማደያዎች በሊትር የ23 ሳንቲም የትርፍ ህዳግ እንዲይዙ መደረጉ ይታወቃል፡፡
ለነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ከኩባንያ የትርፍ ህዳግ (Company profit margin) በተጨማሪ ለወጭ መሸፈኛ (Cost recovery) በሚል መልክ የተመደበ ፣ በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ የሚያደርግ ህዳግ እንዳለ የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት ከቤንዚን የ22 ሳንቲም ትርፍ ሲወስድ፣ የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ከቤንዚን የ42 ሳንቲም፣ ከነጭ ጋዝ 38 ሳንቲም፣ ከናፍጣ 38 ሳንቲም ማርጅን አላቸው፡፡ ይህ ህዳግ አከፋፋይ ኩባንያዎች በወጪ መሸፈኛ መልክ ከሚያገኙት በሊትር 0.42 ሳንቲም በተጨማሪ የሚሰጥ የኩባንያ የትርፍ ህዳግ ነው፡፡ ይህ የዋጋ ቀመር የነዳጅ ዋጋ መጠን እየጨመረ እንዲሄድ በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ፣ በህዝቡ ላይ እየደረሰ ካለው የኑሮ ጫና አንፃር ተገምግሞ በከፍተኛ ደረጃ ሊስተካከል ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ነደጅ አቅርቢ ድርጅት ከአከፋፋዮች እና ከቸርቻሪዎች የበለጠ የትርፍ ህዳግ እንዲይዝ መደረጉም አግባብ አይደለም፡፡ መንግሥታዊ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ የገንዘብ ማስገኛ (እንቁላል ጣይ ዶሮ) ድርጅት እንዲሆን ከመፈለግ አንፃር ታይቶ ከሆነም፣ በሕዝብ ላይ እያሳደረ ያለውን የኑሮ ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት አሠራርን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ የነዳጅ ድርጅት የነዳጅ ዋጋን የማረጋጋት ተልእኮ የተሰጠው የልማት ድርጅት ሁኖ እያለ፣ ከግል የነዳጅ ማደያዎች በላይ እንዲያተርፍ መደረጉ ከህብረተሰቡ ጉሮሮ በመንጠቅ የኑሮ ውድነትን የሚያባብስ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በህወሓት ዘመን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዓለም አቀፍ የነዳጅ ግዥ ጨረታ አውጥቶ የገዛበትን ዋጋ ብሔራዊ ባንክ ቢያውቀውም ይፋ የማድረግ አሠራር ባለመከተሉ፣ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ሽሽት የተጋለጠ እንደነበር ይደመጥ ነበር፡፡ ያ ዓይነት አሠራር በኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት ዘመን ለመቀጠል አለመቀጠሉ ሊፈተሽ ይገባል።
የኢንዱስትሪው ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት የነዳጅ ወጪን መቀነስ ብቻ ሳይሆን ከድፍድፍ ዘይት ነዳጅን በማጣራት ሂደት የሚገኙ ተዛማጅ የሆኑ እንደ ተሽከርካሪ ሞተር ዘይት፣ የሞተር ቅባቶች እንዲሁም ሬንጅን የመሳሰሉ ተረፈ ምርቶችን በቀነሰ ዋጋ ለማቅረብ በሃገር ውስጥ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ መገንባት አስፈላጊነቱ በዘርፉ ባለሙያዎች የታመነበት ነው፡፡
የብልፅግና መንግሥት እስትራቴጅካዊ የኢኮኖሚ የፖሊሲ እይታ ቢኖረው ለከተማ ውበት የገፅታ ግንባታ እንዲሁም ለቢሮዎች እድሳት የሚያወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለነዳጅ ማጣሪያ ግንባታ ቅድሚያ በመስጠት ቢያውለው፣ የኑሮ ውድነትን ከማቅለል በተጨማሪ ነዳጅን በተመለከተ ድንገተኛ እና ያልታሰቡ አደጋዎች ቢያጋጥሙ፣ ለተወሰነ ጊዜ ችግርን ለመቋቋም ይረዳ ነበር፡፡
የነዳጅ ዋጋን ተከታታይ ጭማሪ ተከተሎ በህዝቡ ላይ እየከበደ የመጣዉን የኑሮ ዉደነት ለማቅለል የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብን በተመለከተ ለዘለቄታዉ የዉሃ፣የንፋስ፣ የጽሃይ እና የመሬት ዉስጥ እንፋሎት(Geotermal) የኃይል ምንጭ አማራጮች ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ አስፈላጊ ነዉ። የአጭር ጊዜ መፍተሄዎችን በተመለከተ ግን ነዳጅን በሃገር ውስጥ ፈልጎ ከማግኘት በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ማቋቋም፤ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የመሸጫ ዋጋ ህዳግን፣ እንዲሁም አከፋፋይ ኩባንያዎች የተመደበላቸውን ሁለት ዓይነት የዋጋ ህዳግ ቀንሶ ወደ አንድ ዓይነት ማዉረድን ማጠቃለል ይኖርበታል። እነዚህን ሁለቱን ማለትም የኩባንያ የትርፍ ህዳግ እና የኩባንያ ወጭ ማካካሻን ህዳግ ለነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች መስጠት አግባብ አይደለም። ከሁለቱ አንዱን በመተዉ የሚገኘውን ቅናሽ ለነዳጅ ማደያ ባለቤቶች እንዲጨመር ማድረግ ያስፈልጋል። ለነዳጅ ማዳያ ባለቤቶች በጭማሬነት የሚመደብላቸውም የትርፍ ህዳግ ተጨማሪ ነዳጅ ማደያዎች እንዲከፈቱ የሚያበረታታ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ የሚተርፈው የትርፍ ህዳግ ወደ ድጎማ ፈንድ ተመላሽ እንዲሆን ተደርጎ፣ ፈንዱ እንዲጠራቀምና የድጎማ ማንሳቱ ሁኔታ በተቀራረበ ጊዜና በአንድ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እንዳይሆን ቢደረግ፣ ነዳጅ በዋጋ ንረት ላይ የሚያሳድረውን ከባድ ተጽእኖ ያስታግሳል፡፡ በተጨማሪም የነዳጅ ስርጭትን በማስተካከል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲበረታታ ስለሚያደርግ የኑሮ ውድነትን ለማቅለል ይረዳል፡፡
3.3 የብሔራዊ ባንክ አሠራርን በተመለከተ
የዳበረ ኢኮኖሚ ባላቸው ሀገሮች የየአገሮቹ ብሔራዊ ባንኮች በአደረጃጀትም ሆነ የፋይናንስ ፖሊሲን በማውጣትና በማስፈፀም ረገድ ከአስፈፃሚው መንግሥታዊ አካል የአሰራርም ሆነ የፖሊሲ ነፃነታቸው ሊደፈር በማይችልበት ህጋዊ ማእቀፍ ስር የተቋቋሙና የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ የበለፀገ ኢኮኖሚ ባላቸው ሀገራት ከአስፈፃሚው የመንግሥታዊ አካል ይልቅ በሚከተሉት የፋይናንስ ፖሊሲ አማካይነት ቁልፍ የሆነውን ኢኮኖሚን የማነቃቃት እና ዋጋን የማረጋጋት ሚና የሚጫወቱት ብሔራዊ ባንኮች ናቸው፡፡ በእነዚህ ሀገራት የፋይናንስ ፖሊሲዎችን የማውጣትና የመቆጣጠር ኃላፊነታቸውን የሃገር መሪዎች ሳይቀሩ ሊዳፈሩ እና ጣልቃ ሊገቡባቸው አይችሉም፡፡
የገበያ ኢኮኖሚን በተከተሉ ሀገሮች ብሄራዊ ባንኮች የገንዘብ አቅርቦትንም ሆነ የወለድ መጣኔን በመወሰን ረገድ ብቸኛ ባለቤት በመሆናቸው፣ ተልእኮአቸዉን በመወጣት ረገድ ጣልቃ የሚገባባቸዉ ባለመኖሩ፣ የገንዘብ አቅርቦትን እና የወለድ መጣኔን በመወሰን ሃላፊነታቸዉ ዋጋን ከማረጋጋት ጀምሮ የኢንቨስትመንት ካፒታል እንዲበረታታ በማድረግ፣ የሥራ አጥነት ሊቀንስ የሚችልባቸውን ፖሊሲዎች አፍላቂዎች በመሆናቸዉ፣ብሄራዊ ባንኮች የየሃገሩን ኢኮኖሚ በማነቃቃትና በማረጋጋት ረገድ ወሳኝ ሚና የሚጫዎቱ ናቸው፡፡ ይህን የሚያደርጉትም የፖለቲካ ገጽታን ከግምት ዉስጥ በማስገባት በሚፈበረኩ ኢኮኖሚ ነክ መረጃዎች ሳይሆን፣ እዉነትን መሰረት አርገዉ በሚነሱና ተጨባጭ በሆኑ የሃገራዊ ኢኮኖሚ መረጃዎች ጥናት እና ትንተና ላይ ተመርኩዘው ነው፡፡
በንጉሠነገሥቱም ሆነ በደርግ ዘመን እንደ ህወሓት/ኢህአዴግ በተለይም ደግሞ እንደ አሁኑ የኦህዴድ/ ብልጽግና ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ ከፍተኛ በሆነ የዋጋ ንረት ምክንያት ታይቶ ለማይታወቅ የኑሮ መጎሳቋል አልተዳረገም ነበር። በንጉሠነገሥቱ ዘመን ብሄራዊ ባንኩ የገንዘብ አቅርቦትን እና (money supply) የወለድ መጣኔን (interest rate) መጠን መወሰነን በተመለከተ ጣልቃ የሚገባበት የበላይ አካል ባለመኖሩ፣ እነዚያ መንግሥታት ይከተሉ የነበሩት የፋይናንስ ፖሊሲም ወግ አጥባቂ ስለነበር፣ የብድር አስተዳደሩም ከሙስና የጸዳ ስለነበር፣ የዋጋ ንረት የሚታወቅ አልነበረም። በደርግ ዘመንም ቢሆን ገንዘብ ሚኒስቴር በሚሾማቸዉ የቦርድ አባላቱ አማካይነት መንግሥት በብሄራዊ ባንክ ላይ የተወሰነ ተጽእኖ ቢኖረዉም፣ደርግ ይከተል ከነበረዉ ሁሉንም የኢኮኖሚ ተቋሞች በስሩ ያደረገ የሶሺያሊዝም የኢኮኖሚ ፍልስፍና አንጻር መንግሥት ከግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ጋር በሙስና የመተሳሰር አጋጣሚ አልነበረዉም። በደርግ ዘመን የሃገሪቱ ብሄራዊ ባንክ እንደአሁኑ ዘመን ቀልቡን የተገፈፈና በመንግሥት የገንዘብ አታሚነት ሚና ላይ ያተኳረ ስላልነበረ፣ ይከተል የነበረዉ የፋይናንስ ፖሊሲም ከመንግሥት አንጻራዊ የሆነ ነጻነት ነበረዉ። ስለሆነም በደርግም ዘመን በተለይ በመጨረሻዎቹ አስር ዓመታት( ከ1972 እስከ 1982 )ይካሄድ የነበረዉ የእርስ በርስ ጦርነት እየተባባሰ በመጣበት እና የመከላከያ ወጭ ከመንግሥት ገቢ አንጻር ሰማይ ነካ በተባለባቸዉ ዓመታት እንኳ፣ የዋጋ ንረቱ በአማካይ ከ 5.2% በላይ ሁኖ አያያዉቅም ነበር። በመሆኑም አንደኣሁኑ የብልጽገና ዘመን የዋጋ ንረቱ ከ 40% በላይ ደርሶ ህዝብን ያስጨነቀና የህዝብ የቀን ተቀን መወያያ ርእስ አልነበረም።
በሃገራችን ብሄራዊ ባንክ የአደረጃጀት እና የፋይናንስ ፖሊስ አመንጭነቱን በአስፈጻሚው መንግሥታዊ አካል የተነጠቀ፣ የአሰራር ነፃነቱን የተገፈፈ፣ የመንግሥት የገንዘብ አታሚ ድርጅት ከመሆን ያልዘለለ ተቋም መሆኑ፣ ሌላው ኢኮኖሚው አሁን የደረሰበት አዘቅት ውስጥ እንዲወድቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ምክንያት ነው፡፡ ኢኮኖሚው ወደ ተሃድሶ ጎዳና እንዲያመራ ከተፈለገ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአደረጃጀት፣ የአሠራር እና የፋይናንስ ፖሊሲ አመንጭነትና አስፈጻሚነት ሙሉ ነፃነት እንዲከበር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የሃገራችንን ኢኮኖሚ አሁን ከገባበት አዘቅት ዉስጥ እንዲወጣ የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር አይቻልም።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን እንዲያካሂድ ውሳኔ ተላለፈ
የደራ አማራን የዘር ጭፍጨፋ አስመልክቶ ከባልደራስ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ለቤተመንግስት መስሪያ ሲባል ዜጎች ተፈናቅለው ወደ ጎዳና ሊወጡ ነው
የሰላም ድርድሩን አስመልክቶ ከባልደራስ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ።
1. በድርድሩ የአማራና አፋር ማህበረሰቦችን ጥቅም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሂደቱ ተሳታፊ መሆን ሲገባቸዉ፣ይህ እንዲሆን አልተደረገም። ፓርቲያችን ባልደራስ ከህዝብ ጀርባ የተደረገ፣ ተጎጅ ማህበረሰቦችን ያላካተተ የጓዳ ድርድር እና ስምምነት ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም ያስገኛል የሚል እምነት የለዉም።
2. በደቡብ አፍሪካዉ ድርድር በኦህዴድ/ብልጽግና እና በህዉሃት መካከል ያለዉ ልዩነት ህገመንግስቱን መሰረት በማድረግ እንዲፈታ ስምምነት ላይ መደረሱ ይፋ ሁኗል። ይህ የስምምነቱ አንቀጽ ህወሃት ከህገመንግስቱ በፊት ከአማራዉ ታሪካዊ ይዞታዎች በሃይል ነጥቆ የያዛቸዉን ወልቃይት እና ራያን ወደ ትግራይ ክልል ማስመለሰን ግብ አድርጎ የተቀረጸ ነዉ። ይህ አንቀጽ ሌላ ዙር ግጭትና ጦርነት የሚቀሰቀስና ሃገራችን የሚያስፈልጋትን ሰላም እንዳታገኝ የሚያረጋት በመሆኑ፣ ባልደራስ ይህን የስምምነቱን አንቀጽ አጥብቆ ይቃወማል።
3. በአማራ ክልል በገለልተኛ አካላት የተጠና ጥናት በፌደራል መንግስት እና በአማራ ክልላዊ አስተዳደር ተደጋጋሚ የክተት ጥሪ መነሻነት የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት እና ሉአላዊነት አለመገሰስ፣ለህልውናዉ መጠበቅ እና ለሰብአዊ ክብሩ መከበር ሲል ባካሄደዉ ተጋድሎ ወደ 1 ትሪሊዬን የሚገመት የሀብት ውድመት እንደደረሰበት አመላክቷል። በስምምነቱ ዉስጥ ለዚህ ጉዳት ፍትሃዊ ተጠያቂነት ሊኖር እና ካሳ የሚከፈልበት ሁኔታ ሊካተት ሲገባ አልተካተተም። ይህን ስምምነት በኦህዴድ/ብልጽግና እና በህዉሃት መካከል ተቀባይነት እንዲያገኝ ያስገደዱት የምዕራቡ አለም እና በተለየም የአሜሪካ መንግስት በጦርነቱ ምክንያት ትግራይን ጨምሮ በአማራና እና በአፋር ክልሎች ለደረሰዉ እጅግ ግዙፍ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት ማካካሻ የሚሆን እርዳታ እንዲሰጡ በስምምነቱ ዉስጥ ማሻሻያ እንዲካተት ሊደረግ እንደሚገባ ፓርቲያችን ባልደራስ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
የሃዘን መግለጫ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በአሜሪካን የባልደራስ ደጋፊ የነበሩትን ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወዬሳን ድንገተኛ ሞት ሲሰማ ከፍተኛ ሀዘን ተሰምቶታል። አቶ ዳዊት ከበደ በጋዜጠኝነት ሙያ ለረጅም ጊዜ ሀገራቸውን በቅንነት ያገለገሉ ከመሆኑም ባሻገር ሙያቸውን አክባሪ፣ ትሁትና ቅን ሰው ወዳድ እንደነበሩ የሚታወቅ ነው።
ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ የፓርቲያችን መሥራችና ፕሬዚዳንት ከነበሩት ከጀግናው እስክንድር ነጋ ጋር የነበራቸው ሙያዊ ግንኙነትና ወንድማዊ ቀረቤታ ለብዙዎቻችን የባልደራስ አባላትና ደጋፊዎች የሚሰማንን ሀዘን የበለጠ የመረረ ያደርገዋል።ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የተሰማውን መሪር ሀዘን እየገለፀ ለመላው ቤተሰባቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው መጽናናትን ይመኛል።
የትግል አጋራችን የነበሩትን የወንድማችን ነፍስ በአፀደ ገነት ያኑርልን!