ፀጋዬ እንግዳ
አዲስ_ከተማ ምርጫ ክልል 6
ባልደራስን መምረጥ የነገውን ሕልውናችንን የማረጋገጥና አዲስ አበባንም ሆነ ኢትዮጵያን የማዳን ውሳኔ ነው !!
ፀጋዬ እንግዳ ምናለ እባላለሁ፡፡ በስነ-ሕይዎት ትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ አለኝ፡፡ በመቀጠልም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ምርምርና ልማት ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪ አግኝቻለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በማኔጅመንት ዲግሪ አለኝ፡፡ የተለያዩ የሥራ አመራርና የሰው ሀብት አስተዳደር ስልጠናዎች ወስጃለሁ፡፡
የስራ ልምድ በተመለከተ፡ ለረጅም አመታት በመምህርነት፤በአሰልጣኝነትና በር/መምህርነት የካበተ ልምድ አለኝ፡፡ የስራ-ፈጠራ ክህሎትም አለኝ፡፡ ትውልድን በእውቀትና በስነ-ምግባር በሚቀርጽ ሙያ መሰማራቴ ከፍተኛ የሕሊና እርካታ ይሰጠኛል፡፡ መጽሐፍ ማንበብና ፖለቲካዊ ሁነቶችን መከታተል እወዳለሁ፡፡
በ2013 ዓ/ም በሚካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲን በመወከል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የምርጫ ክልል 6 ለፌድራል የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እጩ ተወዳዳሪ ነኝ፡፡
የሕይዎት ህልሜ በክፍለ ከተማውም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ያለውን ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መቅረፍና ሁሉም የአዲስ አበባ ነዋሪ ደህንነቱና ሰላሙ ተጠብቆ በእኩልነትና በነፃነት የሚኖርበትን ስነ-ምህዳር መፍጠር ይሆናል፡፡
በተለይም ከአዲስ አበባ ሕዝብ ከ60 – 70% ወጣት እንደመሆኑ መጠን ወጣቱ በፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን፤ከደባል ሱሶች የፀዳ አምራችና ተማራማሪ፤ መልካም ስነ-ምግባር የተላበሰ ስብእና እንዲኖረው ፤ ያለምንም አድልኦ በእኩልነት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርአት እንዲዘረጋ በቁርጠኝነት ተግቸ እሰራለሁ፡፡
የተከበራችሁ የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ሕዝብ ሆይ ምርጫህ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ይሁን፡፡ ባልደራስ በአዲስ አበባ ከተማ ወርድና ቁመት ልክ የተሰራ፤የአዲስ አበባ ሕዝብ ነፍስና ስጋ ተዋህደው የፈጠሩት ብቸኛ የቁርጥ ቀን ፓርቲ ነው፡፡ ባልደራስን መምረጥ የነገውን ሕልውናችንን የማረጋገጥና አዲስ አበባንም ሆነ ኢትዮጵያን የማዳን ውሳኔ ነው፡፡
ምረጡኝ በታማኝነትና በፅናት ለማገልገልና የጋራ ችግሮቻችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታትና ታሪክ ለማድረግ ማንኛውም ምድራዊ ሃይል የማይበግረን መሆኑን አረጋግጣለሁ፡፡ ከተባበርንና በፅናት አንድ ላይ ከቆምን የማንፈታው ችግርና ተግዳሮት አይኖርም፡፡
የተከበራችሁ የአዲስ አበባም ሆነ የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ሕዝብ ሆይ ለቀጣይ 5 አመት ይወክለኛል፤መብትና ጥቅሜን ያስጠብቅልኛል ብለው የሚያስቡትን እጩ ለመምረጥ ጊዜው ሳያልፍ የምርጫ ካርድዎን ያውጡ፤ካርድዎን በአግባቡ ይጠቀሙ፡፡ ምርጫዎ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ይሁን፤ባልደራስን በመምረጥዎ አይፀፀቱም፡፡
ድል ለዲሞክራሲ!
ለአዲስ አበባ ሕዝብ መብትና ነፃነት በመታገላቸው የሕሊና እስረኛ ለሆኑት የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራሮች ዘላለማዊ ክብርና ምስጋና ይድረሳቸው !