የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች የምስራቅ ወለጋ አጎራባች በሆነው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ሚዢጋ ወረዳ ታንካራ ቀበሌ ታህሳስ 01/2015 ዓ/ም ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ የኦሮሚያ ልዩ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ በርካታ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን የሰባቱን ሟቾች አስከሬን ብቻ መቅበር ተችሏል፡፡
በሀይል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገቡት የኦሮሚያ ፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ የተገደሉ ህፃናት፣ሴቶችና አዛውንቶች አስከሬን በየጫካው ወድቆ እንደሚገኝ ከጥቃቱ የተረፉ የዐይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
ታህሳስ 01/2015 ዓ/ም መነሻቸውን ከምስራቅ ወለጋ አርጆ ጉደቱ ከተማ ያደረጉ የኦሮሚያ ልዩ ኃይሎች ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሀይል በመሻገር በካማሺ ዞን ሚዢጋ ወረዳ ታንካራ ቀበሌ ልዩ ስሙ መንደር 42 ነዋሪዎች ላይ ተኩስ መክፈታቸው ታውቋል።
የቤኒሻንጉል ክልል ፀጥታ ኃይሎች ለመከላከል ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም ከአቅማችን በላይ ነው በሚል አፈግፍገዋል።በከባድ መሳሪያ የተመቱ በርካታ ቁስለኞች ህክምና አላገኙም ተብለዋል። ወላጆቻቸው ተገድለውባቸው ተረካቢ ያጡ ህፃናት መኖራቸውም ተጠቁሟል።
ከጥቃት የተረፉት የዐይን እማኞች እንዳሉት ከሆነ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች ወሰን አልፈው ወደ ቤኒሻንጉል ክልል በመግባት ከገደሏቸው ሰዎች በተጨማሪ በርካታ ቁጥር ያላቸው የአማራ ተወላጆችን የቀንድ ከብቶች ገድለው መኖሪያ ቤቶችንም በከባድ መሳሪያ አውደመዋቸዋል።
ይሕ ዜና እስከ ተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ከ10 ሺ በላይ የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ታንካራ ቀበሌ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ተጠልለዋል። የኦሮሚያ ልዩ ኃይሎች ዳግም ጥቃት ይከፍቱብናል በሚል ከባድ ጭንቀት ላይ መሆናቸውም ታውቋል፡፡ በተያያዘ ዜና ከኪረሙ ወረዳ የአማራ ተወላጆችን ንብረት የኦሮሚያ ልዩ ሀይል በ28 መኪና ጭኖ በማጓጓዝ ላይ እያለ በአንገር ጉትን ከተማ በሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል።
ከኪረሙ ወረዳ ተጓጉዞ፣ በኦሮሚያ የፀጥታ ሐይሎች እንዲሁም በኦነግ ሸኔ ታጅቦ የመጣው የአማራ ገበሬዎች ንብረት በጉትን ከተማ መነኻሪያ በመከላከያ ሠራዊት ተይዞ ይገኛል። በኦሮሚያ ክልል ግድያ ፤ዘረፋ እና ማፈናቀል ሕጋዊ ተግባሮች ሆነው የመንግስት ድጋፍ እንደሚሰጣቸውም ከቦታው የሚወጡ በርካታ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡