የሕክምና ባለሙያዎችን ጥያቄ እና እስር አስመልክቶከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

በሀገራችን በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ሀገራት የሕክምና ት/ቤቶች (Medical Colleges) ለመግባት፣ ብዙ ዋጋ መክፈል ይጠይቃል። ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃም የሕክምና ት/ቤት የሚገቡ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተናን በከፍተኛ ውጤት የሚያልፉ ተማሪዎች ናቸው። እነዚህ ተማሪዎች፣ በዩኒቨርስቲ ቆይታቸውም ሆነ በትምህርቱ ይዘት ምክንያት ከአብዛኛው የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በላቀ ሁኔታ የትምህርት ጫና የሚበዛባቸው እና ይህንንም ተወጥተው ለመመረቅ የሚደርሱ ናቸው። ከሌሎች የትምህርት ዘርፎች በተለየ መልኩ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ቢሰላ እንኳ ተምሮ ለመመረቅ በትንሹ 19 አመታትን በትምህርት ያሳልፋሉ።
ነገር ግን በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ያለፉና ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት ለማትረፍ ቀን ከሌት ደፋ ቀና የሚሉ የሕክምና ባለሙያዎች የሚያገኙት ገቢ ከሙያ ችሎታቸው ጋር የማይመጥን እጅግ ዝቅተኛ ደሞዝ ነው፡፡ በተለይም የብልፅግና አገዛዝ የመንግሥትን መንበረ ስልጣን ላይ ከተቆጣተረ ጀምሮ የምግብ እና የመሰረታዊ መገልገያዎች ዋጋ በአራት እና በአምስት እጥፍ አያሻቀበ ባለበት ሁኔታ፣ በነዳጅ ጭማሪ ምክንያት የትራንስፖርት ዋጋ ጣራ በነካበት፣ የቤት ኪራይ ዋጋ አልቀመስ ባለበት ሁኔታ፣ አይደለም የወር ደሞዝን ጠብቆ ለሚኖር፣ አትራፊ ለሆኑ ነጋዴዎችም ኑሮን መግፋቱ ከባድ ሆኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ “መኖር ከበደን፣ የደሞዝ ጭማሪ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎቻችን ይከበሩ!” ብለው ተቃውሟቸውን ፍፁም ሰላማዊ በሆን መንገድ ላሰሙ የሕክምና ባለሙያዎች፣ አገዛዙ የሰጠው ምላሽ እጅግ አሳፋሪ ሆኗል። አገዛዙ የመኖር እና የእንጀራ ጥያቄን “ፓለቲካዊ ነው፣ የፅንፈኛ ፖለቲካ ሃይሎች ግፊት ነው፤ የጠላት እጅ አለበት” ወ.ዘ.ተ በማለት ለማፈን እየሞኮረ ይገኛል። የዚህ አሳፋሪ ድርጊቱ ዋንኛ መገለጫ ደግሞ በእስር እና እንግልት ላይ የሚገኙ ሀኪሞች እና የጤና ባለሙያዎች ጉዳይ ነው። የጤና ባለሙያዎቹ ጥያቄያቸው የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ እንጂ ሌላ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ይዘት ወይም ከስልጣን ጥያቄ ጋር የተያያዘ የፖለቲካ እንድምታ ያለው አይደለም፡፡ ለዓመታት ለጥያቄያቸው ተገቢው ምላሽ እንዲሰጣቸው በሰለጠነ መልኩ ሲያሳስቡ ቆይተዋል። የጤና ባለሙያዎች ጥያቄዎቻቸውን ያቀረቡበት ፍፁም ሰላማዊ በሆነ በሰለጠነ መንገድ ነው፡፡ ለጥያቄያቸውም መደመጥ ያሳዩት በአንድነት የመቆም ፅናት በእጅጉ የሚያስደንቅ ነው።
በአንፃሩ የብልጽግና አገዛዝ በአደባባይ ወጥቶ ሰላማዊ ጥያቄ ያቀረበ የጤና ባለሙያን በማሰር እና ጥያቄውን በተሳሳተ መንገድ በመፈረጅ የመረጠው አካሄድ የለመደውን የጦርነት መንገድ እንጅ ከሰላማዊ ትግል ጋር ጨርሶ የተፋታ እና የማይተዋወቅ መሆኑን በገሃድ አስመስክሮበታል፡፡ አገዛዙ በተደጋጋሚ እንደሚታየው በሰላማዊ መልኩ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ሁሉ በኃይል ለማፈን የማይፈነቅለው ጉድጓድ እንደሌለ እያሳዬ ነው። ይህም ህዝብ በፍራቻ ከላይ የሚወርድ ትዛዝ እንጂ ወደላይ የሚቀርብ ጥያቄ እንደሌለ እንዲያምን እና በፍራቻ ተቀፍድዶ እንዲኖር ለማድረግ በአገዛዙ የተሸረበ ሴራ ነው። እንዲህ አይነቱ ተግባር ደግሞ በተደጋጋሚ ጊዜ በተለያዩ የአምባገነን መንግስታት ሲደረግ የቆየ እና አሁንም በብልፅግና አገዛዝ እየተፈፀመ ያለ ድርጊት ነው።
አገዛዙ ባለሙያዎቹ ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀብሎ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ አግባብ ባለው ኹኔታ መልስ ባለመስጠቱ በባለሙያዎቹ በኩል የሥራ ማቆም እርምጃው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። በዚህም በመንግሥት ቸልተኝተኝነት ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለከባድ አደጋ እንዲጋለጥ እየተደረገ መሆኑን ባልደራስ ተገንዝቧል። አገዛዙ የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የተለመለደውን የሚዲያ ቅጥፈት ማስተጋባት መጀመሩ ለሕዝብ ጥያቄዎች ያለውን ንቀት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በጤና ባለሙያዎች ጥያቄ ዙሪያ አገዛዙ በእልህ እና በማንአለብኝነት እያስተላለፋቸው ያሉ ውሳኔዎች ኢትዮጵያን ከባድ አረንቋ ውስጥ የሚከቱ ናቸው።
ቀድሞውን በችግር መጫኛ የተተበተበው የኢትዮጵያ የጤና ስርዓት አሁን ላይ በመንግሥት ግብዝ አካሄድ ወደ ሞት አፋፍ እየተገፋ ነው። የጤና ባለሙያዎች መኖር ሳይችሉ የሚኖር የጤና ስርዓት የለም። ዛሬ በጅምላ የሚታሰሩ እና ለዳቦ ጥያቄ ምላሽ የተነፈጋቸው የጤና ባለሙያዎችን ነገ ለምልክት እንኳ ማግኘት ሊከብድ የሚከብድበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የጤና ባለሙያዎች ሲያደርጉት የቆዩትን እና እያደረጉት ያሉትን ፍፁም ሰላማዊ ተቃውሞ ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ሀሳብ ከመስጠት በመቆጠብ በጥንቃቄ ሲከታተል ቆይቷል።
ፓርቲው ይህንን ያደረገበት ምክንያት አገዛዙ ሰላማዊ እና ሙያዊ ጥያቄን ፖለቲካዊ መልክ ሰጥቶ ማፈን መፈለጉን በመረዳቱ በሃኪሞች ጥያቄ ላይ አገዛዙ ለሚሰነዝረው የሃሰት ፍረጃ ምክንያት መሆን ስላልፈለገ ነው።
ይሁን እንጂ አሁን ላይ በጤና ባለሙያዎች ላይ የሚደርሰው እስር እና በተገልጋዩ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው መጉላላት በመባባሱ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ለመስጠት ተገዷል ። በዚህም መሠረት ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የሚከተሉትን ማሳሰቢያዎች ያቀርባል።
- የታሰሩ የሕክምና ዶክተሮች ለሌሎች የጤና ባለሙያዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፤
- የሕክምና ዶክተሮቹ እና መላ የጤና ባለሙያዎች የሚያነሷቸውን ጥቄዎች ፍፁም ከፍረጃ በራቀ መልኩ እንዲሰሙ እና ጥያቄዎቻቸው አግባብነት ባለው መልኩ እንዲመለሱላቸው፤
- የብልፅግና አገዛዝ እስካሁን በጤናው አገልግሎት መተጓገል ምክንያት ህክምና ላላገኙ ታካሚዎች ይፋዊ ይቅርታ እንዲጠይቅ
- መንግሥት ሁሉንም ፖለቲካዊ ያልሆነ የጥቅማጥቅም ጥያቄ ከስልጣን ቆይታው ጋር በማያያዝ ለሕዝብ ስቃይ ደንታቢስ በመሆን የሕዝብን መከራ ከሚያራዝሙ ግብዝ አካሄዶች እንዲታቀብ ፓርቲያችን ያሳስባል።
በመጨረሻም በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁ ጥያቄዎቻችሁን በዘመናዊ፣ በሰለጠነ እና ሰላማዊ በሆነ የተቃውሞ ዘይቤ በመጠቀም ላቀረባችሁ የጤና ባለሙያዎች ባልደራስ ያለውን አክብሮት እየገለፀ፣ ጥያቄዎቻችሁ በአስቸኳይ እንዲመለሱ ገዥውን መንግሥት በአፅንኦት ያሳስባል።
የባልደስራ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

