6ኛው ሃገራዊ ምርጫ እንዲታገድ ባልደራስ ፍርድ ቤትን ጠየቀ !
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ከፍተኛ አመራሮች ፤ፕሬዚዳንት አቶ እስክንድር ነጋ ጨምሮ ፣ አስቴር ስዩም ፣ ስንታየሁ ቸኮል እና አስካለ ደምሌ ፤በተመለከተ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እጩ እንዳይሆኑ ሰጥቶት የነበረውን ውሳኔ በመሻር በዕጩነት እንዲመዘገቡ ትዕዛዝ መስጠቱ የሚታወቅ ነው።
በውሳኔው መሰረት ምርጫ ቦርድ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲፈጽም ባልደራስ በደብዳቤ የተጠየቀ ቢሆንም፤ ምርጫ ቦርድ የፍርድ ቤት ውሳኔን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚቸገር እና ተፈጻሚ እንደማያደርግ በደብዳቤ ምላሽ ሰጥቷል ።
ይህን ተከትሎ የባልደራስ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ በማካሄድ ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለህግና ለፍትህ ተገዢ አለመሆኑን አጽኖት በመስጠት
የፍትሕ ሂደቱ ጠብቆ አፈፃፀም እንዲቀጥል በወሰነው መሰረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የአፈጻጸም መዝገብ ከፍቷል ።
ፍ/ቤቱ የባልደራስ አቤቱታ በመቀበል ፤ ምርጫ ቦርድ እንደ ፍርዱ ፈጽሞ እንዲቀርብ ለግንቦት 26 ቀን 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፊታችን ሰኔ 14 ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ እንዲታገድ፤ ባልደራስ ባቀረበው አቤቱታ ላይ ምርጫ ቦርድ ምላሽ እንዲሰጥ በተመሳሳይ ቀን ቀጠሮ መሰጠቱን የባልደራስ የሕግና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሔኖክ አክሊሉ ገልጸዋል ።