ፈሪሃ እስክንድር (ጌጥዬ ያለው)
ደንበ – ተግባቦት
የዚህ መጣጥፍ ርዕስ እስክንድር ነጋ ከአሳሪዎቹ እንደሚበልጥ ለማሳየት የተሰየመ እንጂ ስጋ ለባሹን ሰው ከፈጣሪ ለማስተካከል እንዳልሆነ ይታወቅ፡፡ ‹ፈሪሃ እስክንድር›፤ ‹ፈሪሃ ፈጣሪ› ከሚለው ሀረግ ትይዩ ተደርጎ ሊተረጎም አይገባም፡፡ በችሎት ዘገባ ፍርድ መስጠት የተወገዘ ነው፡፡ የፍርድ ሂደቱን ሊያዛባ የሚያስችል ትንተና ማድረግም ክልክል ነው፡፡ በጋዜጠኝነት ውስጥ የችሎት ዘገባ ከጦርነት ዘገባ ያልተናነሰ ብዙዎችን የሚያስፈራ እንደሆነም አውቃለሁ፡፡ እስክንድር ነጋ እና በእርሱ መዝገብ የተከሰሱት ከደሙ ነፃ መሆናቸውን ለመፍረድ ግን ይህ ሁሉ አያስፈራም፡፡ ምክንያቱም የማያሻማ እውነት ከሩቅ ይታያልና ነው፡፡ ስለዚህ መጣጥፌን የምቀጥለው እነእስክንድርን በነፃ አሰናብቼ ይሆናል፡፡ እነኝህ ሁለት ደንቦች ይከበሩ፡፡
መነሻ
‹‹. . . ሕዝብን የምትጨቁኑበትን መንግሥት በፍፁም እቃወማለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት ልትገድሉኝ ትችላላችሁ፡፡ ሞት ስትፈርዱብኝም የምፀፀት ይመስላችኋል፡፡ እኔ በዚህ ብፀፀት እንደናተ ቂል ነኝ፡፡ መጥፎ ሥራችሁን እና ሕዝብን መጨቆናችሁን የምትተው ካልሆነ መቶ ጊዜ እሞታለሁ፡፡ እንደገና ብወለድ መቶ ጊዜ የገደላችሁኝ መሆናችሁንም ባስታውስ ይህ መቀጣጫ ሁኖኝ ዝም ልላችሁ አልችልም፡፡ . . .›› የሀቀኛው እና እምቢተኛው ደራሲ አቤ ጉበኛ ንግግር ነው፡፡ አቤ ይህንን ሃሳብ ‹አልወለድም› በተሰኘው ድርሰቱ ፅፎት ብቻ አላለፈም፡፡ የሕይወቱ መመሪያ አድርጎት በመንግሥት ስለት አልባ መሳሪያ ማለትም በዱላ ተደብድቦ አስከተገደለበት (ኤልያስ አያልነህ የአቤ ጉበኛ ብእራዊ ተጋድሎ በሚለው መፅሐፉ ይፋ አድርጎታል) ጊዜ ድረስ ኑሮበታል፡፡ የእስክንድር ነጋን ተመልሶ ወህኒ ቤት መግባት ሳስብ ይህ አባባል ትዝ ይለኛል፡፡ በሀቀኝነታቸው፣ ድፍረታቸውና ፅናታቸው ከአቤ ጋር ይመሳሰሉልኛል፡፡ በጀርመን የናዚዎች ክስ ምስክሮች በግልፅ ችሎት ተሰምተዋል፡፡ በተመሳሳይ በሩዋንዳ የጅምላ ጭፍጨፋ ክስ እማኞች በግልፅ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያም የደርግ ባለሥልጣናት በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰው ችሎት በቆሙ ጊዜ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ፊት ለፊት ግጥም አድርገው መስክረዋል፡፡ በእነእስክንድር ላይ ግን ሰዎች በመጋረጃ ተከልለው እንዲመሰክሩ ተደርጓል፡፡ አሁንም በድጋሜ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቹ ከመጋረጃ ጀርባ ቃላቸውን እንዲሰጡ ይባኝ ጠይቋል፡፡
እነእስክንድር ለምን ታሰሩ?
የአገዛዙ ሊቀ መንበር አብይ አሕመድ በወያኔ/ኢሕአዴግ እቅፍ ያደጉ እንደመሆናቸው እስክንድር ነጋን ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ፓስተር አብይ ከፈጣሪያቸው ይልቅ ፈሪሃ እስክንድር ያደረባቸው ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ እንደ ፈጣሪ በበጎ ባይሆንም በክፉ ይፈሩታል፡፡ ፈርተውም ይፈታተኑታል፡፡ እነእስክንድር የታሰሩት ለጅምላ ጨፍጫፊው የአብይ አገዛዝ ስላልተመቹ በመፈራታቸው እንደሆነ እያንሰላሰልን ወደ ፍርሀቱ ቀዳሚ መገለጫ እንለፍ፡-
‹‹. . .የሚቀጥለው ምርጫ ፍፁም ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ አብርሃ ደስታ (አብርሃ ምሳሌ ነው) ካሸነፍህ በ24 ሰዓታት ውስጥ አቅፌ አስረክብሃለሁ፡፡ ሳታሸንፍ አሁን ባለአደራ፤ አደራ እንደሚባለው አይነት ጨዋታ የምትጫዎት ከሆነ ግን ግልፅ የሆነ ጦርነት ውስጥ እንገባለን ማለት ነው፡፡ ይሄ መታወቅ አለበት፡፡ የፖለቲካ አቋም ያለው ሰው ቢፈልግ በግሉ፤ ቢፈልግ በፓርቲ መወዳደር ይችላል፡፡›› በዚህ ንግግራቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ በወቅቱ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት በሚል አደረጃጀት ይንቀሳቀስ የነበረውን ሲቪክ ሕዝባዊ ተቋም አስጠነቀቁ፡፡ ለተቋሙ መሪ እስክንድር ነጋ ያላቸውን ፍርሀት የገለፁበትም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ፖለቲካዊ የሲቪክ ተቋም እንዲኖር እንደማይፈቅዱም ተናገሩ፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን ከሚወዳደር ግለሰብና ተቋም ውጭ ፖለቲካውን መተቸትና መግራት የሚችል ተቋም መኖር የለበትም የሚል ነበር ይህ ንግግራቸው፡፡ ምክንያቱም ለፖለቲካ ሥልጣን የሚወዳደር ከሆነ ከወያኔ በወረሱት ሴራ ለመጥለፍ ያመቻቸዋል፡፡ ‹ለሕዝብ ጥቅም ሳይሆን ራሱን ሥልጣን ላይ ለማውጣት ነው የሚቸኩለው› ለሚሉት የአባይ ጠንቋይ ወሬ ይመቻቸዋል፡፡ ለዚህም ነው ‹አብይ ወያኔ የጣለውን እንቁላል ነው ሰብሮ የወጣው› የምንለው፡፡
የአብይ አሕመድ አገዛዝ የከለከለው እስክንድር የሲቪክ ተቋም እንዳያቋቁም ብቻ አይደለም፡፡ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሀገር ውስጥ እንዳይመሰርትም ጭምር ነው፡፡ ‹ሰናይ› ቴሌቪዥንን ለመመስረት በሀገር ውስጥ የአክስዮን ሽያጭ ተጀምሮ ነበር፡፡ ሆኖም እንኳንስ የስርጭት ፈቃድ ሊሰጠው ጉዳዩን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫዎችም እንዳይሰጡ በመከልከሉ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ የተሰበሰበው አክስዮንም ለባለቤቶቹ ተመልሷል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን እስክንድር ነጋ ጠብ ጫሪ አልነበረም፡፡ ቴሌቪዥኑንም ሆነ የሲቪክ ተቋሙን ምስረታ ትቶ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ፈቀዱት የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ ተመለሰ፡፡ (እዚህ ላይ ባልደራስ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ እንዲመጣ የሕዝብ ግፊትም እንደነበረበት አይካድም)
ነገሩ የጨነቀው ርጉዝ ያገባል ሆነ፡፡ ባልደራስ የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ ቢመጣም ፈሪሃ እስክንድር በአብይ ላይ አደረ፡፡ ድርጅቱ የምስረታ ጉባዔውን ለማካሄድ ከነጋዴ የተከራየውን የሆቴል አዳራሽ በመንግሥት ተከለከለ፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ መጠሪያ ስሙን እና መሪውን ጎዳና ላይ በተደረገ ስብሰባ መርጦ መንገድ ላይ የተመሰረተ የመጀመሪያው ፓርቲ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ባልደራስ እንደ ግራ ዘመም የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ በፕሮቶኮል ፖለቲካ ብቻ ተወስኖ አልቀጠለም፡፡ ከቢሮና ከአዳራሽ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ በእያንዳዱ የአስተዳድራዊ ችግሮች ሰለባ ዜጋ ቤት የወረደ ሥራውን ጀመረ፡፡ እስክንድር ፓርቲውን በሦስት መልኩ ለማንቀሳቀስ ችሏል፡፡ አንደኛው በግራ ዘመም ፖለቲከኞች የተለመደው የፕሮቶኮል ፖለቲካ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ የአገዛዙ ተጎጂዎችን የሚያፅናናበትና መልሶ የሚያቋቁምበት የአክቲቪዝም ፖለቲካ ነው፡፡ ሦስተኛው የመረጃ ፖለቲካ ነው፡፡ ይህ አጫጭር መረጃዎችን በልዩ ልዩ መንገዶች ከማድረስ ጀምሮ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን በተከታታይ እስከ መስጠት የሚደርስ ሲሆን በመረጃ እና ማስረጃ የተደገፈ ፖለቲካዊ ትንተና ነው፡፡ ዛሬ በየአካባቢው እየተፈፀመ ያለው ጅምላ ጭፍጨፋ እና የኦሮሙማ ወረራ አስቀድሞ ያመላከታቸው የዚህ ትንተና ውጤቶች ናቸው፡፡ በእነኝህ ሦስት የእንቅስቃሴ ምህዋሮቹ የአብይ አሕመድን አገዛዝ ፖለቲካዊ ውንብድና አጋልጧል፡፡ ሊያቀርቡትም ሆነ ሊያጠቁት ቢሞክሩ የሚንበረከክ አልሆነም፡፡ የጠቅላይ ሚንስትሩ ፅህፈት ቤት በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ያሰማራቸው ዘላፊ ሰራዊቶች እስክንድር የአእምሮ ህመምተኛ እንደሆነ ለማስመሰል ብዙ ጥረዋል፡፡ የእስካሁኑ የመጨረሻው አማራጭ ሰበብ ፈልጎ ማሰር ሆኗል፡፡ እስክንድር ዳግም በሽብር መከሰሱ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሰሙ መደረጉም ሌላኛው አስገራሚ ጉዳይ ነው፡፡ ታህሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. የዋለው ችሎት ደግሞ ከወትሮው የተለየና የችሎት ድሪቶ ሳይሸፍነው እውነት የተገለጠበት ታሪካዊ ክስተት ነበር፡፡
ከታህሳስ 16 እስከ መጋቢት 29
ታህሳስ 16 በዋለው ችሎት እነእስክንድር የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደረጉ ችሎቶችም ጭምር በመጭው ምርጫ እንዲዘጋጁ የፍትህ ሂደቱ እንዲፋጠንና ከእስር እንዲወጡ ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡ ለአንድ ወር ከ20 ቀናት የተራዘመ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ለቀጠሮዎች መራዘም ጉዳዩ ከችሎቱ አቅም በላይ መሆኑንንም ዳኞች ደጋግመው ገልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነእስከንድር ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደብዳቤ ቢፅፉም አወንታዊ ምላሽ አላገኙም፡፡ አሁንም ለ3 ወራት ከ15 ቀናት ተራዝሞ ተቀጥረዋል፡፡ ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ የእነእስክንድርን ደብዳቤ ሙሉ ቃል ቀጥሎ አስቀምጨዋለሁ፡-
ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዘደንት
እና
ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዘደንት
ጉዳዩ፡- የተፋጠነ ፍትህ ስለመጠየቅ
በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት እነ እስክንድር ነጋ በተከሰስንበት የወንጀል መዝገብ፣ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ምክንያቶች አቅርበን፣ ጉዳያችንን የያዘው ችሎት የተፋጠነ ፍትህ እንዲሰጠን መጠየቃችን ይታወሳል፡-
1ኛ. ተከሳሾች በህጋዊ መንገድ የተመዘገበ የፖለቲካ ድርጅት አባላት መሆናችንን፣
2ኛ. የታሰርነው በያዝነው ዓመት ይደረጋል ተብሎ እቅድ በተያዘለት ምርጫ ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ በነበርንበት ጊዜ መሆኑን፣
3ኛ. የክሱ አላማ፡-
ሀ. ጥፋተኝነታችንን በፍ/ቤት አረጋግጦ ለማስቀጣት አለመሆኑን
ለ. በኮቪድ 19 ሳቢያ ተዘግተው የቆዩት ፍ/ቤቶች ያሉባቸውን የተደራረቡ መዝገቦች ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ዋስትና የሚያስከለክል ክስ በመመስረት ጉዳዩ በእንጥልጥል እያለ በምርጫው እንዳንሳተፍ ማድረግ መሆኑን፣
ሐ. በምርጫው እንዳንሳተፍ በፈጠራ ክስ የታሰርን መሆናችንን፣
መ. በተዘዋዋሪም ቢሆን፣ ፍ/ቤት የዚህ ህገ-ወጥ ተግባር ተባባሪ መሆን እንደሌለበት
4ኛ. ፍ/ቤቱ ከምርጫ ጋር ባሉታዊ መልኩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ላለመነካካት ለመዝገቡ ፈጣን ውሳኔ መስጠት እንዳለበት፣ ይህንንም ለመተግበር የሚከተሉትን የመፍትሄ እርምጃዎች አስፈላጊ እንደሆኑ፣
ሀ. በ1998 ዓ.ም በእነ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል መዝገብ እንደተደረገው፣ ይህን መዝገብ ብቻ የሚመለከት ችሎት እንዲቋቋም፣
ለ. እንደገና፣ በ1998 ዓ.ም በእነ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል መዝገብ እንደተደረገው ጉዳዩ በየእለቱ በተከታታይ እንዲታይ፣
ሐ. በምርጫው የሚሳተፉ እጩዎች ምዝገባ ከመጀመሩ በፊት በመዝገቡ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ መሰጠት እንዳለበት አሳስበናል፡፡
በዚህም መሠረት፣ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም በነበረን ቀጠሮ ምላሽ እናገኛለን ብለን ጠብቀን የነበረ ቢሆንም፣ በዕለቱ ተግባራዊ ምላሽ ሳናገኝ ቀርተናል፡፡ ችሎቱ በሰጠን የቃል ምላሽም፣ ጥያቄያችንን ለበላይ አካል አቅርቦ ምላሽ እንዳልተሰጠው አስረድቶናል፡፡
ስለዚህም፣ አሁን ጥያቄያችንን የበላይ ስለሆናችሁ የህግ ተርጓሚው አካላት እያቀረብን ሲሆን፣ በሀገራችን በቀጣይነት የሚደረገው ምርጫ ፍትሃዊና ሰላማዊ እንዲሆን በዚህ በኩል አስተዋፅኦ እንድታደርጉ በትህትና እንጠይቃለን፡፡
ከሠላምታ ጋር!
1ኛ. ተከሳሽ እስክንድር ነጋ
2ኛ. ተከሳሽ ስንታየሁ ቸኮል
3ኛ. ተከሳሽ ቀለብ ስዩም
4ኛ. ተከሳሽ አስካለ ደምሌ
ግልባጭ፡-
ለኢትዮጵያ፡- ምርጫ ቦርድ
ለኢትዮጵያ፡- ሰብአዊ መብት ኮሚሽን
ታሪክን ሽሽት (የችሎት ማስታወሻ)
ታህሳስ 16 በዋለው ችሎት ተከሳሾችን እና ዳኞችን ካላግባቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ የመረጃ ስነዳ ጉዳይ ነው፡፡ ተከሳሾች ከእምነት ክህደት ቃላቸው ጋር የሚሰጡት ማብራሪያ በድምፅ ተቀርፆ ቢቀመጥላቸው ደስተኛ እንደሚሆኑ ገልፀው ይህ እንኳን ባይሆን የሚናገሩት ከአራት መስመር የእጅ ፅሁፍ ያልበለጠ ኃሳብ ቃል በቃል እንዲፃፍላቸው ጠየቁ፡፡ ከሦስቱ ዳኞች መካከል ቃላቸውን እየመዘገቡ የነበሩት የግራ ዳኛዋ በዚህ ተስማምተዋል፡፡ ሆኖም በአፍታ ልዩነት ምላሳቸው ታጠፈ፡፡ የሃሳቡን ጭብጥ እንጂ እያንዳዱን ቃል እንደማይመዘግቡ ተናገሩ፡፡ ንግግሩ ቃል በቃል ወረቀት ላይ እንዲሰፍርለት በተለይ እስክንድር ነጋ በብርቱ ተሟገተ፡፡ ‹‹የምናገረው ዝም ብሎ የሕግ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ እንደማንኛውም ወንጀል የሚታይ አይደለም፡፡ የታሪክ ጉዳይ ነው፡፡ የፖለቲካ ጉዳይ ነው፡፡ ቃል በቃል ይመዝገብልኝ፡፡›› በማለት ጠየቀ፡፡ እንዲመዘገብለት የፈለገው ንግግር ቃል በቃል የሚከተለው ነው፡-
‹‹ሁሉም በሚያየው ሁሉም በሚሰማው በእግዚዓብሔር ስም እኔ ንፁህ ነኝ፡፡ አብረውኝ የተከሰሱትም ንፁህ ናቸው፡፡ ይህ ክስ አንድም እውነት የለበትም፡፡ በታሪክ ፊት እያደረ እውነቱ ግልፅ ይሆናል፡፡››
ይህንን የሰሙት ዳኛዋ ‹‹የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምኩም፡፡ እውነቱ እያደረ ግልፅ ይሆናል›› ብለው መዘገቡት፡፡ ዳኞች ጉዳዩን ቃል በቃል ለመመዝገብ ያልቻሉት በሰዓት ማነስ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አለመመዝገብ ብቻ ሳይሆን ተከሳሾች ቅሬታቸውን በደብዳቤ እንዲያሳውቁ በማዘዘ በግልፅ ችሎት እንዳይናገሩም ተደጋጋሚ ክልከላዎች ተደርገዋል፡፡ ይህም በግልፅ ችሎት የሚታደሙት ጥቂት ሰዎችም ሆኑ በመገናኛ ብዙሃን በኩል ዘገባው የሚደርሰው ሕዝብ ትክክለኛ መረጃ እንዳይኖረውና ነገ የታሪክ ምስክር እንዳይሆን የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ በችሎቱ ላይ ፀጉሩን እየፈረፈረ ክስ የሚቀያይረው ጎረምሳ ዐቃቤ ሕግም ክሱን ከታሪክና ከፖለቲካ ለማራቅ ይሞክራል፡፡ ከመደበኛ ክሶች ጋር ለማመሳሰል ላይ ታች ይላል፡፡
ተከሳሾች በሚናገሩበት ጊዜ ዳኞች ቶሎ ቶሎ ጣልቃ እየገቡ ያስቆሟቸዋል፡፡ ስንታየሁ ቸኮል ቀጠለ፡- ‹‹<አሥራ አራት ሰዎች ገድላችኋል> ተብለን ነው የተከሰስነው፡፡ እኛ ተፈናቅለው፣ በኮሮና ምክንያት ተቸግረው 14 ሰዎች መግበናል፡፡ አልገደልንም፡፡ ይህንን ሕዝብ ያውቀዋል፡፡ ፍፁም የሀሰት ክስ ነው የቀረበብን፡፡ ውስጣችን ተቃጥሏል፡፡ እኛ ውስጥ እውነት አለ፡፡ ይህንን ስሙን ነው ያልነው፡፡ ከለበስነው ቢጫ ልብስ (የእስር ቤቱ) ጀርባ እውነት አለ፡፡ ልንደመጥ ይገባል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሊያስቆመን አይገባም፡፡ ማንንም አልበደልንም፡፡ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ፖለቲካዊ ነው፡፡ ስለዚህ ፖለቲካዊ ቋንቋ ተጠቅመን ነው የምንከራከረው፡፡ የእኛ ክስ ከእኛ መዝገብ በተጨማሪ አጠቃላይ የፍትሕ ስርዓቱን ያሳያል፡፡ በሚቀጥለው ምርጫ ተሳትፈን ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ተረኛው ኃይል በሀሰት ክስ ነው ያሰረን፡፡ ባልደራስ በምርጫ እንዳይሳተፍ ማሰር አይቻልም፡፡ ሕዝብ ማሰር አይቻልም›› የምሀል ዳኛው አቋረጠው፡፡ ሲናገር ለስ እራሱ ብቻ መሆን እንዳለበት እና ‹እኛ› እያለ በጋራ መደብ መግለፅ እንደሌለበት ምክር ይሁን ማስጠንቀቂያ ያልለየለት ሃሳብ ተናግረው ዳኞች ወደ ሦስተኛዋ ተከሳሽ አስቴር ስዩም አልፈዋል፡፡ ‹አስቴር› የትግል ስሟ ነው፡፡ ዶሴው የሚጠራት ግን ቀለብ ስዩም በሚለው ነው፡፡
ለመንፈቅ ያህል በጀርባ ህመም እየተሰቃየች እንደሆነ ተናግራ ህክምና እንድታገኝ ፍርድ ቤቱን ጠየቀች፡፡ ይህ ባለፉት ችሎቶችም ጭምር ስታቀርበው የነበረ ጥያቄ ነው፡፡ ቀለብ ስዩም ሕፃን ልጇን ባለቤቷ መምህር በለጠ ጌትነት ወህኒ ቤት እያመላለሰ የምታጠባ እናት ነች፡፡ የወንጀል ድርጊቱን እንዳልፈፀመች ስታብራራ ከተናገረችው ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡-
‹‹ባለፈው ስርዓት (ሕወሓት/ኢሕአዴግ ማለቷ ነው) የሰው ወይም የሰነድ ማስረጃ ሳይቀርብብኝ በምሀል ዳኛ ‹‹ጠርጥረንሻል›› ተብዬ ተቀጥቻለሁ፡፡ ይሄን በሚመስል ችሎት ተዳኝተናል፡፡ ዳኞች ከስርዓቱ ተፅዕኖ ነፃ ሆናችሁ እንድትዳኙን እጠይቃለሁ፡፡ ችሎቱ ላይ አድሏዊነት አይቻለሁ፡፡ እኛ ተከሳሾች ነን፡፡ በልባችን ውስጥ መድሃኒያለም የሚያውቃት እውነት አለች፡፡ ለዐቃቤ ሕግ እና ለእኛ እኩል እድል እየተሰጠን አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ክሱ የሀሰት ነው፡፡ ፖለቲካዊ ነው፡፡ በማንነታችን ላይ የተደረገ የብሔር ክስ ነው፡፡ የbalance ክስ ነው፡፡ (እዚህ ላይ ‹ጃዋር ታስሮ እስክንድር አይቀርም› በሚል የደቦ ሚዛንን ለማስጠበቅ የተፈፀመ ክስ እንደሆነ መጠቆሟ ነው) እምነትን የካደ ክስ ነው፡፡ ሰብዓዊነትን የጣሰ ነው፡፡ የፍትሕ ስርዓቱን ያዋረደ ክስ ነው፡፡ ዐቃቤ ሕግ የስርዓቱ ቡችላ ነው፡፡››
ዐቃቤ ሕግ ሥነ ስርዓት ሲል፤ በተመሳሳይ ቅፅበት ዳኞች ንግግሯን እንድታቆም አዘዙ፡፡ ታላቁን ሕግ ጥሰው ንፁሃንን በሀሰት ክስ የዶሮ ማደሪያ በሚመስል እስር ቤት ውስጥ እያሰቃዩ ለትንሽዬ የችሎት ስነ ስርዓት መቆርቆር አስቂኝ ነው፡፡ ዛፉን ከግንዱ ቆርጠው ከጣሉት በኋላ ለቅጠል ደህንነት እንደ መጨነቅ ይቆጠራል፡፡ ዐቃቤ ሕግን ‹‹የሥርዓቱ ቡችላ›› ማለት ተገቢ እንዳልሆነ ዳኞች እያብራሩ ነው፡፡ እስክንድር በተራው ዳኛውን አቋረጠው፡፡ ‹‹የተከበረው ፍርድ ቤት አባባሉ እኛም የምንጋራው ነው፡፡ ‹ዐቃቤ ሕግ የሥርዓቱ ቡችላ ነው› ማለት እውነት መናገር እንጂ ዘለፋ አይደለም፡፡›› በዚህ ጊዜ ስንታየሁ ቸኮልና አስካለ ደምሌ ‹‹የጋራ አቋማችን ነው፡፡ ቃሉ ይገልፀዋል›› በማለት በጋራ ተናገሩ፡፡
በዚህ ንግግራቸው እንዲቀጡለት ዐቃቤ ሕግ ዳኞችን ጠየቀ፡፡ ከተከሳሾች በላይ ራሳቸው እውነቱን ከነማስረጃው እያወቁ ንፁሃንን በሃሰት ክስ የሚያሰቃዩ ወንጀለኞች መሆናቸውን የሚያውቁት ዳኞች ጉዳዩን በይቅርታ አለፉት፡፡
‹‹የመንግሥት ሠራተኛ ሆኜ ሥሠራ በጥቅማጥቅም ደልለው ኃሳቤን ለማስጣል ሞክረዋል፡፡ ከደረጃየ በላይ አመራር እንድሆን እና የጋራ መኖሪያ ቤት እንዲሰጠኝ ተጠይቄያለሁ፡፡ በኋላም ‹መንግሥት ደሞዝ እየከፈለሽ መንግሥትን መቃወም አትችዪም› ተብያለሁ፡፡ ሦስት ጊዜ ታግቻለሁ፡፡ ደህንነቶች (መንግሥታዊ ሰላዮች ማለቷ ነው) አስፈራርተውኛል፡፡ በተመሳሳይ የመንግሥት የወረዳ አመራሮች አስፈራርተውኛል፡፡ ለችሎቱ መናገር የማልችላቸው ወንጀሎች ተፈፅመውብኛል፡፡ ‹የአማራ እና የደቡብ ተወላጆችን አንድ ላይ አደራጅተሻል› ተብየ ነው የተወነጀልኩት፡፡ የደህንነቶችን ስልክ ቁጥር መዝግቤ ይዣለሁ ማንነታቸው ይጣራልኝ፡፡›› አለች አስካለ ደምሌ፡፡
ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተው ካጠናቀቁ በኋላ ችሎቱ 3 ወር ከ15 ቀናት ጉዳዩን ወደ ኋላ አስረዝሞ ለመጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ፡፡ ይህ ራሱን ችሎ ከፍርድ የሚስተካከል ቀጠሮ ያላግባብ የተራዘመ መሆኑን በመጥቀስ እንዲያጥርላቸው ተከሳሾች ጠየቁ፡፡ ይህ ከጉርምርምታም አልፎ ስርዓቱን የጠበቀ ቢሆንም እንኳን የችሎቱን ድባብ ለብ አደረገው፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ጠባቧ የችሎት አዳራሽ ውስጥ የተገኘው ታዳሚ በግዳጅ እንዲወጣ ተደረገ፡፡ ወታደሮች በአዳራሹ የነበሩ ጋዜጠኞችን ጭምር አስወጡ፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ወታደሮች ገቡ፡፡ ‹ቡችላ› የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ችሎቱ ላይ እንደተሰማ ጀምሮ የተለያየ መለዮ የለበሱ ወታደሮች ቁጥር እየበዛ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተከሳሾች፣ ዳኞች፣ ጠበቆች፣ ዐቃቤ ሕግ እና ታዳሚዎች እርስ በእርስ እንዳይተያዩም የወታደሮች ብዛት እንቅፋት ሆኖ ነበር፡፡ ዳኞች ሳይቀር ተከሳሾች በሚናገሩበት ጊዜ ፊት ለፊት እንዳይተያዩ እየከለሏቸው ወታደሮችን ‹ዞር በሉ› ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ እኔም በበኩሌ የሚናገሩትን እያዳመጥኩ የማስታወሻ ደብተሬ ላይ ከመፃፍ በቀር ለማየት ተቸግሬ ነበር፡፡ ከአጠገቤ ቁመውና ተቀምጠው የምፅፈውን እየተከተሉ የሚያነቡ ፖሊሶች እንደነበሩ ደርሸበታለሁ፡፡
በዚህ ሁኔታ ከሌሎች ጋዜጠኞችና ታዳሚያን ጋር አዳራሹን ለቅቄ እንድወጣ ሁለት ወታደሮች እየተፈራረቁ ቢያዝዙኝም ታሪካዊ ክስተቱን የመዘገብ ግዴታ እንዳለብኝ አስረድቼ በሙግት ሳልወጣ ቀረሁ፡፡ ቀጥሎ የሆነው ሁሉ በዝግ ችሎት ነበር፡፡ ታዳሚውና ጋዜጠኞች እንዳይወጡ እነእስክንድር አጥብቀው ቢጠይቁም በታጣቂ ኃይል ሁሉም ወጥተዋል፡፡ ‹‹መታፈናችንን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ንገሩ›› እያሉ ታዳሚውን ተሰናበቱ፡፡ ይህንን ሲሉ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሁሉም ተከሳሾች ጀርባቸውን ለዳኞች ሰጥተው ሙሉ በሙሉ ወደ ታዳሚው ዙረው ነበር፡፡ የታዳሚያኑም ሆኑ የእነርሱ እጆች ከፍ ብለው የመኪና መስታውት እንደሚወለውል አይነት እየተወዛወዙ ነው፡፡
‹‹እባካችሁ የተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ በጣም ረዝሞብናል፡፡ እባካችሁ ስሙን፡፡ በምርጫ መሳተፍ አለብን›› አለ እስክንድር፡፡ ሌሎች ተከሳሾችም እየተቀባበሉ ለምርጫ መዘጋጀት እንዳለባቸው ጠቅሰው አፋጣኝ ፍትሕ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡ የዳኛ እና የጊዜ እጥረት እንዳለበት ጠቅሶ ችሎቱ ይህንን አለመቀበሉን አረዳቸው፡፡
‹‹እናንተም የመንግሥት አገልጋዮች ናችሁ፡፡ ተለጣፊዎች ናችሁ፡፡ በዚህ ችሎት መዳኘት በራሱ ያሳፍራል›› አለቻቸው አስካለ ደምሌ፡፡ በዚህ ጊዜ በንግግሯ የተበሳጩት ወታደሮች ችሎቱ ሳይዘጋ እጆቻቸውን በካቴና አስረው ከአዳራሹ አስወጧቸው፡፡ በር ላይ ከደረሱ በኋላ ዳኞች እንደገና እንዲመልሷቸው አዘዙ፡፡ ‹‹ከእኛ ጋር ያልተግባባነው በቀጠሮ ነው አይደል? ለሌሎቻችሁ ክብር ሲባል ይቅርታ አድርገንልሻል›› ብለው የመሀል ዳኛው የዕለቱን ችሎት ዘጉት፡፡ ይህንን ሲሉ ‹ከእናንተ ጋር የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት የለንም፡፡ ትክክል ናችሁ፡፡ መሰረታዊ ሀሳባችሁ ስህተት የለበትም› ለማለት የፈለጉ ይመስለኛል፡፡ ይህንን በግልፅ ለመናገር የተቀመጡበት ወንበር ባይፈቅድላቸውም እንኳን ልቦናቸው እንደሚያንሰላስለው መገመት አይከብድም፡፡ እነእስክንድር እንደገና እጆቻቸውን በካቴና ታሠሩ፡፡ ቀደም ብሎ ከአዳራሽ የተባረረው ታዳሚ በር ላይ በጭብጨባ ተቀበላቸው፡፡ ጭብጨባው ሳይቋረጥ በመስታዎት ፋንታ በፍርግርግ ብረት የተሸበበው አውቶብስ ውስጥ በወጠምሻ ወታደሮች ታጅበው ገቡ፡፡