“ገበታ ለሀገር” – ከዶሮና ዓሳ ወግ አንጻር(ከማለፊያ ደርሰህ)
ዶሮና ዓሳ የቀረበ ገበታ አይተው ወግ ይጀምራሉ:: በገበታው ላይ የቀረበው ምግብ የዕንቁላል ጥብስና ዓሳ ነው:: ዶሮው “ይህ ገበታ ጣፋጭ ሆኖ ትላልቅ መሳፍንትና መኳንንት ተደስተው እንዲመገቡ ለማድረግ የእኔ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው:: ምክንያቱም እንቁላሉን የጣለችው ሚስቴ ዶሮ ነች፤ እንቁላሉ የሁለታችንም ዶሮዎች አበርክቶ ነው” ብሎ ተኩራራ::
ዓሳውም ተደንቆ “እናቱ የሞተችበትና ገበያ የሄደችበት እኩል ያለቅሳሉ” ብሎ ተረተና “ሰማህ ዶሮ፣ ገበታው ላይ ካለው ምግብ አንዱ ከዶሮ የተገኘ ዕንቁላል መሆኑ እርግጥ ነው:: ገበታው ላይ የቀረበው ዓሳ ግን እኔ ታርጄና ተበልቼ የቀረበ የእኔ አካል ነው::እኔ ነኝ” ብሎ ተናገረ:: ይህ የዶሮና የዓሳ ታሪክ በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) የቀረበውን “ገበታ ለሀገር” አስታወሰኝ::
የጽሑፌ ዋና ጉዳይ ግን ጠቅላይ ሚንስትሩ በ”ገበታ ለሀገር” ለመገንባት ላቀዷቸው የወንጪ፣ የጎርጎራ እና የኮይሻ ፓርኮች ግንባታ ከመንግሥት ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዝ መቆረጡን የተመለከተ ነው:: በሦስቱም ቦታዎች የሚገነቡት ፓርኮች ለቱሪዝም፣ ለኢኮኖሚ፣ የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና ለሌሎችም ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች እንደሚጠቅሙ አያከራክርም:: ዋናው ቁም ነገር ግን አሁን በበርካታ ችግሮች ለምትጠበሰው ሀገራችን ከዚህ የሚቀድሙ መሠራት ያለባቸው አጣዳፊ ጉዳዮች የሉም ወይ? የሚለው ነው::
ሀገራችን በዘረኝነት መርዝ በተዘራው ጎጠኝነት የተነሳ ሰው ውሎ መግባቱ አሳሳቢ በሆነበት፣ በበርካታ የሀገራችን ክፍሎች የበረሃ አንበጣ መንጋ ሰብል በማውደም ላይ ባለበት፣ የኑሮ ውድነቱ “ውድነት” በሚለው ቃል ሳይሆን እንደ “ሰደድ በሚንበለበል እሳት” በተመሰለበት፣ የብር የመግዛት አቅም ቀኑ እንዳለፈበት እንደ ትናንት ጋዜጣ ዋጋ ባጣበትና ገበያው በሳጥናኤል የሚመራ በሚመስልበት በዚህ ወቅት “ገበታ ለሀገር” አንገብጋቢ ሀገራዊ አጀንዳ ነውን?
በኑሮ ውድነቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመጠቃት ላይ ካሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የመንግሥት ሠራተኛው አንዱ ነው:: በማይመጥን ዝቅተኛ ደመወዝ በስቃይ የሚኖረው የመንግሥት ሠራተኛ ከዓመት ዓመት ከድኅነት ወለል በታች እየወረደ የበለጠ ድሃ እየሆነ ነው::
“ገበታ ለሀገር” – የእናት ሀገር ጥሪ?
ሀገር ችግር ላይ ስትወድቅ ለልጆቿ (ለዜጎቿ) የድረሱልኝ ጥሪ ታቀርባለች:: ከ42 ዓመት በፊት ሀገራችን ያጋጠማትን ክፉ ጊዜ ለአብነት ላንሳ:: ኢትዮጵያ በ1969 ዓ.ም በምስራቅ 700 ኪሎ ሜትር በደቡብ ደግሞ እስከ 300 ኪሎ ሜትር ድረስ በሱማሊያ ጦር በተወረረችና የሰሜን ተገንጣይ ኃይሎች ኤርትራን ለማስገንጠል አስመራና ዙሪያዋን በከበቡት ቀውጢና ፈታኝ ወቅት ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሚያዝያ 04 ቀን 1969 ዓ.ም “እናት ሀገርህ ተወራለች፤ ተነሥ! ታጠቅ! ዝመት!” ብለው የእናት ሀገር ጥሪ አቀረቡ:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪውን ተቀብሎ 300 ሺ ሰው ታጠቅ ጦር ሰፈር በመክተት በአጭር ጊዜ ሰልጥኖ ሰኔ 18 ቀን 1969 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሰልፍ አደረገ:: ወደ ጦር ግንባር ዘመተ:: አበቃላት የተባለችው ኢትዮጵያም የሱማሊያን ጦር ጠራርጋ ከድንበርዋ በማስወጣት አይበገሬነቷን አረጋገጠች:: ዕድሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች በአጠቃላይ ሕዝቡ ጦር ግንባር ለዘመተው ኃይል ደጀን በመሆን ባደረገው ሁለገብ ድጋፍ ያ ክፉ ቀን ታለፈ:: ኢትዮጵያም ከውርደት ዳነች:: በኋላም ከሰሜን ተገንጣይ ኃይሎች ጋር በተደረገው ረጅምና አሰልቺ ጦርነት ደርግ በአዋጅ በማስገደድ የመንግሥት ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን በአንድ ዓመት ክፍያ በተደጋጋሚ ዓመታት እንዲከፍሉ አድርጓል::
ሲያልቅ አያምር እንዲሉ ደርግም ወደቀ:: ኤርትራም ተገነጠለች:: ሕወሓትም የዘረኝነት መርዙን በሀገራችን ዘራ:: በ1983 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ በኢትዮጵያ፣ በሻዕቢያና በኢሕአዴግ (ሕወሓት) እና ሻዕቢያ መካከል በአሜሪካዊው ኸርማን ኮህን አደራዳሪነት የሰላም ድርድር ተካሔደ:: ደርግ አብቅቶለት ነበር:: ኸርማን ኮህን ኢሳይያሥ አፈወርቂን አሳምነው አሰብ ለኢትዮጵያ እንዲሆን ድርድር እንዲካሔድ ሲጠይቁ መለስ ዜናዊ “አሰብ የኤርትራ ናት” በሚል ሀሳቡን ውድቅ እንዳደረጉባቸው ኮህን ለተለያዩ ሚዲያዎች ገልጸዋል:: ሕወሓት በዚህ ታሪኩ አለማፈሩ ይገርመኛል:: ታሪክ ይቅርታ በማይደረግለት ስህተት መዝግቦታል::
ሀገርን የተፈጥሮ፣ የጦርነት እና ሌሎች ችግሮችና አደጋ ሲያጋጥማት አንድ ዜጋ እንኳን ገንዘቡንና ሕይወቱን ሊሰጥ የተገባ ነው:: በዚህ በኩልም ኢትዮጵያውያን የሚያኮራ ታሪክ እንዳለን ይታወቃል:: በቅርብ ዘመናት ኢትዮጵያውያን ከማጂ እስከ ጃጂ፣ ከመቀሌ እስከ ሞያሌ፣ ከኦሜድላ እስከ ጋምቤላ፣ ከጅጅጋ እስከ ጅጋ፣ ከበደሌ እስከ ቶጎ ውጫሌ፣ ከጠገዴ እስከ ጎዴ፣ ከሁመራ እስከ ሰመራ በአንድነት ያነሳሳቸው ታላቁ የአባይ ግድብ ነው:: የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ለግድቡ በሦስት የተለያዩ ዓመታት የሦስት ወር ደመወዙን ለግሷል:: ልገሳው ወደ ቦንድ እንዲዛወር በመደረጉ ደስተኛ ነው:: ኢትዮጵያውያንን ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ያስማማ በኩር ብሔራዊ አጀንዳ በመሆኑ ሠራተኛው ተቸግሮም ቢሆን ደመወዝ በመለገሱ ለሀገሩ ታላቅ ድርሻ አበርክቷል:: በዚህም እንደሚኮራ ይታመናል::
ዓሳው – የመንግሥት ሠራተኛ
ከካድሬና ካድሬ ቀመስ፣ ከገንዘብ እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት ካላቸው ሌባ የመንግሥት ሠራተኞችና በ‹ኤክስፐርቲዝነት› ሙያቸው የተሻለ ክፍያ ከሚያገኙ ጥቂት ሠራተኞች በስተቀር አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ ኑሮው የሰቆቃ ነው:: ምሳቸውን ሳይበሉ የሚውሉ፣ ሲያማቸው እንኳ መታከሚያ በማጣት በሽታቸውን ተሸክመው የሚሰቃዩ ሠራተኞች እንዳሉ ይታወቃል:: ለሠራተኞቻቸው ነጻ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ብቻ ናቸው:: አብዛኛዎቹ ባለ በጀት መስሪያ ቤቶች ለሠራተኞቻቸው ነጻ የሕክምና አገልግሎት አይሰጡም::
ኅብረተሰቡም ቢሆን ለመንግሥት ሠራተኞች የሚሰጠው ክብር ዝቅ ያለ ነው:: በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ በአነስተኛ ደመወዝ ተመግቦ፣ለብሶ፣ቤተሰብ ያለው ቤተሰቡን አስተዳድሮና ልጆቹን አስተምሮ መኖር በአስማት ካልሆነ በቀር እንዴት ይቻላል? ሲያስቡት ያማል::
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶክተር) ወደ ስልጣን እንደመጡ የመንግሥት ሰራተኛ በነጻ የሚያገለግል መሆኑን በመግለጽ ማሞካሸታቸው ይታወሳል:: በወቅቱም የበርካታ መንግሥት ሠራተኞች ተስፋ መብራት ጀምሮ ነበር:: በኋላ ግን በተደጋጋሚ ባደረጓቸው ንግግሮች፣ ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ መጨመር የኑሮ ውድነቱ እንዲጨምር ከማድረግ ውጭ የሚፈይደው ነገር የለም በማለት ተናግረዋል::
ጠቅላይ ሚንስትሩ በስልጣን ዘመናቸው ለመንግሥት ሠራተኛው አንድ ሳንቲም የደመወዝ ጭማሪ አላደረጉም:: ቀደም ሲል በባለበጀት መስሪያ ቤቶች የሚሰራ አንድ ሠራተኛ የደረጃ ዕድገት ሲያገኝ ያገኘው ጭማሪ በሙሉ ይከፈለው ነፃ ሃሳብ “ገ ቁጥር 04 ታህሳሥ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. 13 ነበር:: ጠቅላይ ሚንስትሩ ከመጡ በኋላ ግን አንድ ሠራተኛ የደረጃ ዕድገት ካገኘ የሚከፈለው ለ3 ተከፍሎ በ3 ዓመታት ውስጥ ነው:: በምሳሌ አስደግፌ እንዳስረዳ ይፈቀድልኝ:: አንድ ሠራተኛ ከሐምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የብር 900.00 ጭማሪ የደረጃ ዕድገት ቢያገኝ የመጀመሪያው ብር 300.00 የሚከፈለው እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም፣ ሁለተኛው ብር 300.00 የሚከፈለው እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም እና ሦስተኛው ብር 300.00 የሚከፈለው እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ነው:: የተጨመረለትን ብር 900.00 በሙሉ የሚያገኘው በሦስተኛ ዓመቱ ነው:: ይህ በዘመነ ብልጽግና በመንግሥት ሰራተኛው ላይ እየተፈጸመ ያለ ግፍ ነው::
በርግጥ መንግሥት፣የመንግሥት ሠራተኛውን ኑሮ ቀዳዳ ሁሉ የሚሞላ የደመወዝ ጭማሪ የማድረግ አቅም እንደሌለው ይታወቃል:: የኑሮ ውድነቱ መነሻና መድረሻ መፍትሔ ለመንግሥት ሠራተኛ ከሚጨመር የደመወዝ ጭማሪ ጋር አይገናኝም:: በምጣኔ ሀብት ባለ ሙያዎች ዘንድ ለዋጋ ግሽበት መንስዔና መፍትሄ ቁልፉ ጉዳይ “የፍላጎትና የአቅርቦት መጣጣም” እንጂ ለመንግሥት ሠራተኛው ደመወዝ የመጨመርና ያለመጨመር ጉዳይ አይደለም:: ደመወዝ ሳይጨመርም በብርሃን ፍጥነት የዕቃዎች ዋጋ ግሽበት ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይታይም::
በዚህም አንጻር “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ በ“ገበታ ለሀገር” ስም አብዛኛው ሠራተኛ ሳያምን በካድሬ አደረጃጀት የአንድ ወር ደመወዙን እንዲሰጥ መደረጉ የመንግሥት ሰራተኛን ደመወዝ እንደመንጠቅ ይቆጠራል::
የመጣው ሥርዓት ሁሉ ጉልበቱን የሚፈትሸው በመንግሥት ሠራተኛው ላይ ነው:: የሚያሳዝነው ነገር ቢኖር የመንግሥት ሠራተኛው የግልገልና ዋና ካድሬዎች የስብሰባ ማድመቂያ፣ንግግር መለማመጂያ፣በአግባቡ ያልተኮረጁና ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያልተዛመዱ ፍልስፍናዎች መሞከሪያና በስሙ የሚነገድበት የኅብረተሰብ ክፍል መሆኑ ነው::
በዘመነ ሕወሓት ሥራ ለመቀጠር፣በሥራ ላይ ዕድገት ለማግኘትና የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ለማግኘት መስፈርቱ በወንዝ ልጅነት መጠቃቀም፣ ጎጠኛ መሆንና በጎጠኞች መረብ ስር መሆን ነው:: ይህን ያደረገ ካድሬ ሹም ይመሰገናል እንጂ አድሎ እንዳደረገ አይቆጠርም:: ይህ ክፉ ሥራ በዘመነ ብልጽግና ተጠናክሮ በመቀጠሉ ”ዓሳው – የመንግሥት ሠራተኛ” እንደ ዶሮው እንቁላሉን ሳይሆን ራሱን እየሰጠ እየተበለተ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው::
ዶሮው – ካድሬ ሹም
“መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ” እንዲሉ ብልጽግና ፓርቲ የቀድሞው ኢሕአዴግ ቁጥር 2 ነው:: ከኢሕአዴግ ላይ ሲቀነስ ሕወሓት፤ ሲደመር አጋር ድርጅቶች (ኢሕአዴግ – ሕወሓት + አጋር ድርጅቶች) ማለት ነው::
ሕወሓት የበጋ መብረቅ ወርዶበት ሳያስበው ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ከተባረረ ማግስት ጀምሮ ሕወሓትን የተኩት ከተላላኪነት ያለፈ ሚና ያልነበራቸው ያሳደጋቸው ተላላኪዎቹ ከእሱ ብሰው ተገኝተዋል:: የታዘብነውም ተተኪዎቹ ይሉኝታ የሌላቸው፣ በጎሳ ፍቅር ያበዱ፣ከብሔራዊ ልማትና ከብዙኃን ፍላጎት ይልቅ የግል ስልጣንና ሀብት በማካበት ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ነው:: የሕወሓትን “ተራራ ማንቀጥቀጥ” ገድል የማስተጋባት ተግባር ፈጽመው አሁን ደግሞ ብልጽግናን የማጋነን ዘይቤ የጀመሩት የትናንቱ ካድሬዎች መርሕ አልባ በመሆናቸው ፈጥነው የሚሰለፉት ከአሸናፊዎች ጋር እንደሆነ ይታወቃል::
አብዛኛዎቹ ካድሬ ሹማምንት ከሁሉም በላይ ራሳቸውን የሚያስቀድሙ፣ የሾማቸው አካል ፊቱን ካጠቆረባቸው የሚኖሩበት ቪላ ቤትና ኮብራ መኪና ሲነጠቁ እየታያቸው ሌት ተቀን የሚቃዡ እንጂ በራሳቸው የሚተማመኑ አይደሉም::
እነዚህ ካድሬ ሹማምንት በኅብረተሰቡ ውስጥ የተሻለ ኑሮ የሚኖሩ፣ መንግሥት ማለፊያ ቤትና ምርጥ መኪና የሰጣቸው፣ የተሻለ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ያላቸው፣ በውጭ ሀገር ጉዞ ዶላር የሚሰበስቡ እና ኢመደበኛ በሆነ ዘዴም መሬቱን እና ገንዘቡን የሚሰበስቡ ናቸው:: ጠቅላይ ሚንስትሩንና እሳቸውን የከበቧቸውን ለማስደሰትና “ንሴብሆን” ለመሻማት እሽቅድምድም ውስጥ ገብተዋል:: እነዚህ ባለስልጣኖችና የብልጽግና ካድሬዎች ለ”ገበታ ለሀገር” የወር ደመወዛቸውን ቢሰጡ እንደ ዶሮው እንቁላሉን ሰጡ እንጂ እንደ ዓሳው ራሳቸውን አልሰጡም::
በሀገራችን እየተለመደ የመጣው አንድ ባለስልጣን በጎሳ ሰንሰለት ውስጥ እስከታቀፈና የፖለቲካውን ቀይ መስመር እስካላለፈ ድረስ የፈለገውን ቢያጠፋ ጠያቂ የሌለው መሆኑ ነው:: አጥፍቷል ተብሎ ቢነሳም ሌላ የተሻለ ወንበር ላይ ይቀመጣል እንጂ ተጠያቂ አይሆንም:: ከዚህም አንጻር የመንግሥት ሠራተኛውና ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል እንደ ዓሳው ራሱን እየሰጠ ካድሬው ሹም ደግሞ እንደ ዶሮው ዕንቁላሉን እየሰጠ በሹመት ላይ ሹመት እየጨመረ ዕድሜውን ይገፋል::
በመጨረሻም ዐብይ አህመድ (ዶክተር) በኑሮ ውድነት ከቤተሰቡ ጋር በመሰቃየት ላይ የሚገኘው የዓሳ ተምሳሌት የሆነውን የመንግሥት ሠራተኛ “ገበታ ለሀገር” በሚል ሰበብ የሚቆረጥበት ሙሉ ደመወዝ በፍጹም አግባ አለመኾኑን ሊረዱት እንደሚገባ መልእክቴን አስተላልፋለሁ::