ሀገርን የማዳን ጥሪ – የመጨረሻው መጀመሪያ
ከባልደራስ ሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ሰጪ ቡድን የተሰጠ
ሀገርን የማዳን ጥሪ (Balderas Support in North America )
ለብዙ ሺህ አመታት በአባቶቻችን መስዋዕትነት የቆየችው ሀገራችን
ዐይናችን እያየ እጃችን ላይ ሳትፈርስ ሁላችንም በአንድ ላይ ልንቆም ይገባል!
የተከበራችሁ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣
እኛ ኢትዮጵያዊያን የዛሬ ሦስት ዓመት በአገራችን የተካሄደው ለውጥ በልባችን ውስጥ ሰንቆት የነበረው ተስፋ ከህሊናችን በቀላሉ የሚጠፋ አይደለም፡፡ እንዲህ እንደዛሬው ተስፋችን የህልም እንጀራ ሆኖ መቅረቱ እውን ሳይሆን፤ ያንን ታላቅ ተስፋ በተለያየ ጎራ የነበርን ሁሉ ለሀገራችን ካለን ቀናኢ ምኞት እና ጉጉት የተነሳ በአንድነት “ሆ!” ብለን ተቋድሰናል፡፡ የተሰጠን ተስፋ መሬት ላይ ወርዶ ፍሬውን እናይ ዘንድም እንደየአቅማችን ደክመናል፡፡
በእርግጥ ብዙዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ባዶ ቃል ጋር በፍቅር ወድቀው የጫጉላ ሽርሽር ላይ በሚምነሸነሹበት በለውጡ መጀመሪያ ወቅት ሁሉም በተቀደደለት ቦይ ፈስሶ ነበር ማለች አይቻልም፡፡ ይልቁንም ነገሮችን አካሄድ በጥንቃቄ መርምረው የኦሮሙማውን መንግሥት የቃልና የተግባር ግጭት ነቅሶ በማጋለጥ በለጋነቱ እንዲታረም ያካልሆነ ግን ታላቅ አገራዊ ጥፋት እንደሚከተል በማለዳ የማንቂያ ደውል የደወሉ ብልሆች አልጠፉም፡፡ ለዚህም የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት፣ አቶ እስክንድር ነጋ ግምባር-ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ደውሉን ሰምተን ተገቢውን ምላሽ የሰጠን በእውኑ ስንቶቻችን ነን? ያ ገና በማለዳ ችግሩ ሥር ሳይሰድ የተሰጠን ወርቃማ ዕድል እንደ ዋዛ አምልጦናል፡፡ ከዚያም በኋላ በተለያየ ጊዜ ለውጡ አቅጣጫውን መሳቱን ያመላከቱ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ቢኖሩም ጆሮ ሳይሰጣቸው ታልፈዋል፡፡ በግለሰብ ስብዕና ግንባታ እና በባዶ የተስፋ ቃል ላይ ስናተኩር ሀገራዊ ህልውናን ችላ አልነው፡፡ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ይመጣሉ፣ ይተካሉ፡፡ ሀገራችን ግን ከእኛ በፊት ነበረች፤ ከእኛም በኋላ ትቀጥላለች፤ መተኪያም የላትም፡፡
አንኳር የሆኑ እና የሚያመሳስሉንን ጉዳዮች ትተን ጊዜያዊ በሆኑ በጥቃቅን ልዩነቶቻችን ላይ ስንመሰጥ የህወሀት/ኢህአዴግ የበኩር ልጅ የሆነው ኦህዴድ/ብልጽግና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የጥፋት መዋቅሩን
በመዘርጋት መጠነ-ሰፊ የዘር ጭፍጨፋውን በነፃነት እንዲያካሄድ መንገዱን አመቻቸንለት፡፡
አሁን ከአንድ መራር እውነት ጋር መጋፈጥ ግድ ብሎናል፡፡ ያ ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት የተሰጠን የተስፋ ስንቅ መክኖ በታላቅ ሀገራዊ ውርደት፣ ሀዘን እና ተስፋ መቁረጥ ተተክቷል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቁ ጥያቄ ብልጽግና ሳይሆን ህልውና ነው፡፡ እድገት ሳይሆን ሰላም፣ መረጋገት እና ደህንነት ነው፡፡