የግፍ እስረኞቹ አቶ ካሳሁን ደስታ እና አቶ ናትናኤል ያለምዘውድ ነገ እና ከነገ ወዲያ ፍ/ቤት ይቀርባሉ
በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጉዳይ አስፈፃሚ እና ንቁ ተሳታፊ የሆኑት አቶ ካሳሁን ደስታ ባለፈው ታህሳስ 06/2015 ዓ.ም ፍ/ቤት መቅረባቸው ይታወሳል። ችሎቱም ተጨማሪ 7 ቀናትን ሰጥቶባቸው ነበር። በዚህም መሰረት ነገ ሀሙስ 13/04/2015 ዓ.ም በአራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የሚቀርቡ ይሆናል።
ሌላው በግፍ እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ የምክር ቤት አባል እና ንቁ ተሳታፊ የሆኑት አቶ ናትናኤል ያለምዘውድ በ05/04/2015 ዓ.ም ፍ/ቤት መቅረባቸው ይታወሳል። ችሎቱም ፖሊስ ከጠየቀባቸው 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ዘጠኝ ተጨማሪ ቀናትን ፈቅዶ ነበር። በዚህም መሰረት ከነገ በስቲያ (አርብ ታህሳስ 14/2015 ዓ.ም) በአራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ይቀርባሉ።
ሁለቱም የግፍ እስረኞች የተከሰሱት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ት/ቢሮ አማካኝነት በህገወጥ መንገድ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ በአዲስ አበባ ት/ቤቶች መሰቀልንና፣ የኦሮሚያ ክልል መዝሙር መዘመርን ተከትሎ በተማሪዎች፣ በመምህራን እና በወላጆች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ መርታችኋል እና አስተባብራችኋል በሚል ነው።