የድንጋይ ሽበት (በቃሉ ሰው መሆን)
የድንጋይ ሽበት
እስኪ ልጠይቅሽ እውቀት ተናገሪ
ገድ ነሽ መሰጠት ወይንስ መርማሪ
ጨለማውን ገላጭ ብርሀን አብሳሪ
የተቆለፈውን ሚስጥርን ሰርሳሪ፤
በዘመን ዥረት ውስጥ ጥበብ አቀባባይ
በትናንቱ በኩል የዛሬውን ሁነሽ የነገን የምትስይ
በዘመን ፍሰት ውስጥ እየተጠራቀምሽ
ጥልመቱን ድቅድቁን ድንቁርናን ገርሳሽ
እስኪ ልጠይቅሽ እውቀት ተናገሪ
ለመድሽ ወይስ ነሳሽ ዋጥሽ ሳትመረምሪ
በመጠይቅሽ ላይ መጠይቅ ደራርበሽ
በውዝግብ ዓለም በመንታ መንገድ ላይ ቀጠልሽ እንደዋለልሽ
ወይስ መልስ አገኘሽ ለጥያቄዎችሽ
እስኪ ልጠይቅሽ እውቀት ተናገሪ
ጉዞሽ እንዴት ነበር ቁልቁለት ነው ዳገት
ምን አትርፎ ይሆን እንዲያው ያለፍሽበት
ካለፈው ምን ወሰድሽ ምን ሰጠሸ ለመጪው
እህህ…
እንዲም ነኝ እንዲያም ነኝ የምለውም የለኝ
የሰጡኝን ሁሉ ነሺ ተቀባይ ነኝ
በዘመን ዥረት ውስጥ ሳልጸንስ የማምጥ
ሳልጠይቅ አውቄ ሳልቀድም የምበልጥ
የሆንኩትን ሳልሆን
ያልሆንኩትን የሆንኩ
ሳልወለድ የሞትኩ
ያለስንቅ የተጓዝኩ
ሳልጀምር የደረስኩ
ብክንክን መናኛ ለመሆን ተዳረኩ፤
ግና…..
መናኛ መሆኔ በመቸት ሲለካ
በአንድ አውድ በስዬ ባንዱ አራለው ላካ
በአንዱ ፈክቼ በሌላው ከስማለው
የሆንኩትን ልሆን እንዳልሆንኩ ሆናለው
አንድዜ አበጅጄ አንድዜ እበጃለው
በአንዱ ቤዥቼ በአንዱ እቤዣለው፤
በአንዱ ቃዥቼ በሌላ አልማለው፤
እራሴን በራሴ መዝኜ ባየውም
ፍሬ-ዘርን እንጂ ማብቀያ አይደለሁም
መብቀያዬ ሰው ነው መብሰያዬ እድሜ
የምጓዝ በቀና ስተቴን አርሜ
ለትውልድ የምተርፍ ቀስሜ አቅስሜ
ሲቃና ሰልቼ ሲታመም ታምሜ
ሲፈጥን ሰግሬ ሲደክም አዝግሜ
የተጎዳኘሁኝ በሰው ህላዌ ውስጥ
ሲጠል ሰፍፌ ሲሰምጥ የምዘቅጥ
ባንድ ጎኔ ብስል ባንደኛው ጥሬ ነኝ
ባንደኛው መንገዴ ጪንጫ ይገጥመኛል
መብቀያም ማበቢያም አልሆንሽ ይለኛል
ማለፊያም መድረሻም አልሆንሽ ይለኛል
ቆሞ ቀር ሆኖ ገትሮ ያስቀረኛል
አማትሬ እንዳላይ ገዝፎ ይከልለኛል
ነጭ ቆቡን ደፍቶ ጠቁሮ ይታየኛል
በድንጋይ ላይ በቅሎ ገዝፎ ይታየኛል
አንተ ማነህ ስለው ይሰወርብኛል
ልዳስህም ብልው አልያዝ ይለኛል
ሳይጀምር ጨርሶ ወድቆ ይጥለኛል
የመክሰሬ ሚስጥር የመናኛነቴ
ዋና መገለጫው የድንጋይ ሽበቴ
ልዩ ዋቢነቱም “መራራ ፍሬዬ መራራ እድገቴ”
(በቃሉ ሰው መሆን)