የእነዋለልኝ መኮንን ትግል የተላላኪነት ሚና እንደነበር ምሁራን ተናገሩ
በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ ጠንሳሽ እንደነበር የሚነገርለት ዋለልኝ መኮንን እና በተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ የነበሩ የትግል አጋሮቹ የጀብሀ መልዕክተኞች እንደነበሩ ምሁራን ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩትና በተለያዩ የፖለቲካ ትንታኔያቸው የሚታወቁት ብሎም የ‹ሀገራዊ ብሔርተኝነትና ዘውጋዊ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ› መጽሐፍ ደራሲ አቶ አምሀ ዳኘው ዋለልኝ መኮንን የአማራ ተወላጅ ቢሆንም የተገንጣይ ፖለቲካ አቀንቃኙ የጀብሀ ተላላኪ እንደነበር እማኝ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አቶ አምሀ ይህንን ያሉት ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡ እንደ እሳቸው ማብራሪያ ‹የብሔሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ› በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተዘጋጅቶ በተማሪዎች መድረክ ላይ በዋለልኝ መኮንን የተነበበውና ‹ታገል› በተሰኘው የተማሪዎች ጋዜጣ የታተመው ባለ አምስት ገፅ ሁፍ በጀብሀ የተፃፈ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ አስተማሪና ተመራማሪ የሆኑት ምሁር በበኩላቸው ዋለልኝ ፖለቲካዊ ሀሳቦችን የሚያብሰለስል በሳል አዕምሮ እንዳልነበረው በመግለጽ ‹‹ዋለልኝ የሰነቀረው ነገር ነው፣ ለዚህ ፖለቲካዊ ዝቅጠት›› የዳረገን ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በአንጽፃሩ ባለፈው ዓመት መንግሥት ባዘጋጀውና የኦሮሞ እና የትግራይ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች ተመርጠው በታደሙበት የዋለልኝ መኮንን 50ኛ ዓመት ዝክረ በዓል ላይ የተገኙ የኦነግ እና የመኢሶን አባላት የነበሩ የተማሪዎች ንቅናቄ ተሳታፊዎች ጽሁፉን ራሳቸው ተማሪዎች በጋራ አዘጋጅተውት በዋለልኝ መነበቡን ገልጸው ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል ዲማ ነግዎ ይጠቀሳሉ፡፡