የብልፅግና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከቀድሞ መንግስታት ፓሊሲ አንፃር ሲፈተሽ

አመሀ ኃይለማርያም ( ከሰሜን አሜሪካ)
ከዐፄ ኅይለ ሥላሴ እስከ መንግሥቱ ኅይለማርያም፤ ከመለስ ዜናዊ እስከ ዐቢይ አህመድ የዘመናዊዋ ኢትዮጵያ መሪዎች ማንነት፣ እሳቤ፣ ህልምና ምኞት በኢኮኖሚ አመራራቸው ውስጥ በእጅጉ ይንጸባረቃል፡፡ ከጽሑፌ መደምደሚያ ለመጀመር፣ የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኢኮኖሚ አመራር ብዙ ተስፋ፣ ትንሽ ተግባራትና ትልልቅ ስጋቶች የተስተዋሉበትና የሚያንዣብቡበት ነው። ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ እንዲሉ አበው ትንሽ ወደኋላ ለመመለስ ያህል 43 ዓመታትን በሥልጣን ያሳለፉትና በተማሪዎች እምቢተኝነት ከዙፋናቸው የተነሱት ንጉሡ ፊውዳላዊ በሆነ መዋቅር ያስተዳደሩት የነበረው ኢኮኖሚ ጥገኝነቱ በግብርና ላይ ሆኖ ተቋማዊ ኢኮኖሚስቶች (institutional economists) እንደሚሉት “በዝባዥ” የነበረ ሥርዓት ነበር፡፡ መገለጫውም የምርት ሂደት ሰንሰለቶች እንዲሁም የመሠረታዊ ምርት ግብአቶች የበላይ ጠባቂነት በባላባቱ ክፍል ተይዞ አብዛኛው አምራች ኀይል በገባርነት የሚተዳደርበት፣ ምሪቱ ካፒታሊስታዊ ሆኖ ስሪቱ ግን ወደ ባላባቱ ያጋደለ የኢኮኖሚ ሥርዓት ነበር፡፡
የዚህ ሥርዓት ካፒታሊስታዊ መግለጫዎች የሆኑት የገበያ ተኮር ተቋማት ስርጭት ግን የባላባቱ ክፍል በሚኖርባቸው አካባቢዎች የተገደበና እጅግ በጣም ውስንነት የሚስተዋልበት ነበር፡፡ ሥርዓቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን የባላባት ክፍል ፍላጎት ለማሟላት በሚያስችል መልኩ የተደራጀ ቢሆንም የጤና፣ የትምህርት፣ የመሠረተ ልማትና የገበያ ተቋማት ግንባታም ይካሄድ ነበር፡፡ ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑት አሁን ድረስ ያሉት መንግሥታዊና ለትርፍ የተቋቋሙ የመንግሥት ድርጅቶች፤ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የንግድ መርከብ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ…ወዘተ የተመሰረቱት በዚያን ጊዜ ነው፡፡ በአርባ ሶስቱ የንጉሡ አገዛዝ ዓመታት የጠቅላላ አገራዊ ምርት እድገት በዝቅተኛ ደረጃ ያድግ የነበረ ሲሆን አማካኝ እድገቱም ከ 2-5 በመቶ ይሆን ነበር፡፡ የመንግሥት በጀት ወደ ካፒታል በጀት ያጋድል የነበረ ሲሆን ጠንካራ ምንዛሬ ያለው መገበያያ (currency) የዘመኑ መገለጫ ነበር፡፡ የወቅቱ የበጀት ጉድለት በዝቅተኛ ደረጃ መቆየቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን ቢያመለክትም የካፒታል እጥረት ግን ኢኮኖሚውን የሚገዳደርበት ጊዜ ነበር፡፡ የመንግሥት ወጪ የተገደበ (restrained) ሆኖ ለረጅም ጊዜ የቆየ ሲሆን በአንጻራዊነት የተሻለ የምንጭ ልዩነት የሚስተዋልበት የመንግሥት ገቢ ሥርዓት ነበር፡፡ የንጉሡ አስተዳደር በእርዳታ ፍለጋና በውጭ ግንኙነት ረገድ ጠንካራ የሚባል አቅም ነበረው፡፡ ለዚህም ይመስላል ትልልቅ የሚባሉ የበረሃማነት መከላከል፣ የተፋሰስ ልማት፣ የተፈጥሮ ሀብት ፍለጋዎችና ልማት፣ የውሃ ኀይል ማመንጫዎች፣ የምርት ማቀነባበሪያዎች፣ የምርት ማጓጓዝ አደረጃጀትና የመሳሰሉት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በለጋሾች ድጋፍ ማጥናት፣ ማስጀመርና መተግበር የተቻለው፡፡ ብዙዎቹ ዛሬ ላይ “አገራዊ” ተብለው ትልቅ ፓለቲካዊ ዋጋ የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች የተጠነሰሱት፣ የተጠኑትና የዲዛይን ሥራ የተሰራላቸው በዚያ ወቅት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ለዚህም የሕዳሴው ግድብና በሶማሌ ክልል የሚገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋና ልማት ፕሮጀክቶች ማሳያ ናቸው፡፡
የኋላ ኋላ ግን በዝባዥ የነበረው የንጉሡ ኢኮኖሚያዊ አስተዳደር መዋቅር በአንድ በኩል የኢኮኖሚ ጫናው በመረረው አምራች ሕዝብ፣ በሌላ በኩል እየተቀየረ በመጣው ዓለም አቀፋዊ ኢኮኖሚያዊ ስሪት ውስጥ እያደገ የመጣው የገቢ ዋጋ ንረት (በዋናነት የነዳጅ ምርቶች ዋጋ) ባመጣው ወቅታዊ ኢኮኖሚያዊ አለመመጣጠንና ያን ተከትሎ በገነፈለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ተንገዳግዶ ለመውደቅ በቅቷል፡፡ አንባቢ በዚህ ላይ ሊይዝ የሚገባው የመዋቅራዊ አለመመጣጠኑ ውጤት ዕለታዊ ገጽታዎች ለተራዘሙ ዘመናት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄን በኅብረተሰቡ ውስጥ ሲያሥነሱ መኖራቸውን፣ ይህም በተዛባው ምሪትም ቢሆን (ጥቂት የገዢ መደብ አገልጋይ ባለሙያዎችን መፍጠርን አላማው ያደረገ) በተፈጠሩት የተማሪና የሙያተኛ ክፍሎች ለተራዘሙ ዘመናት ይስተዋል የነበረ መሆኑን ነው፡፡ በተጋጋለው የተማሪዎች፣ ባለሙያዎችና ጠቅላላ ሕዝባዊ አመጽ ንጉሡ ከሥልጣን ቢወገዱም እንዳለሙት መግባባት ያልቻሉት ተማሪዎች በሀልዮታዊ የትርጉም ልዩነት ጎራ ይዘው ሲፈሳፈሱ ሥልጣን መያዝ አልቻሉም። ይልቁንም የእነርሱን ፍስፍስ እንደድክመትና ጥሩ አጋጣሚ ያየው የታጠቀ ኃይል ራሱን ወደ ሥልጣን አስጠግቶ ለዘመኑ ስሜት በመረጠው ሐሳዊ ሶሻሊስታዊ (psedu-socialist) አስተዳደር ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት ማስተዳደር ቻለ፡፡ በኮሎኔል መንግሥቱ ኀይለ ማርያም የሚመራው የደርግ መንግሥት በኢኮኖሚ አስተዳደር ረገድ ከንጉሡ አስተዳደር የተለየ ነበር፡፡ የአስተዳደሩ ስሪት የሀብት ክፍፍል ሚዛናዊነት (distributive fairness) ለማምጣት የሚተጋ፣ መሠረታዊ የምርት ግብአቶች ባለቤትነትንም ለሰፊው ሕዝብ የመለሰ ነበር፡፡ የአስተዳደሩ የመጀመሪያ እርምጃ እንደውም መሬትን ለአራሹ ኅብረተሰብ ክፍል በመመለስ የፊውዳላዊ ምርት ሥርዓትን መሰረት መናድ ነበር፡፡ በዚህም ከፍተኛ ህዝባዊ ተቀባይነት (ለጊዜውም ቢሆን) ማግኘት ችሏል፡፡ የደርግ መንግሥት ኢኮኖሚያዊ አስተዳደር እንደ ንጉሡ ሁሉ በጠቋሚና መካከለኛ ዘመን እቅዶች የሚመራ ሲሆን ትኩረቱ አንፃራዊ እኩልነት የሚስተዋልበት ኅብረተሰብ መገንባት የሚል ነበር፡፡ ችግሩ ይህ አንጻራዊ እኩልነትን መፍጠር የሚለው ሶሻሊስታዊ አጀንዳ ግለሰባዊ ኢኮኖሚያዊ ማበረታቻዎችን (economic incentive) ) ማዳከሙና ይህም ምርታማነትን በመገደብ ሀብት ፈጠራን ማኮስመኑ ነው፡፡ ባልተፈጠረ ሀብት ላይ የተጫነው ሀብትን የማከፋፈል መዋቅራዊ ስሌት ኅብረተሰቡን በጋራ ወደ ባለጸግነት ከመምራት ይልቅ ወደ ጋራ ድህነት እንዲያሽቆለቁል አደረገው፡፡ ምንም እንኳን የምርት አላባዎች ባለቤትነትን ቢረጋገጥም የግብአት እጥረት ጠፍንጎ ይዞት የግብርና ምርታማነት ከዳዴ የተሻለ ጉዞ ማድረግ አልቻለም፡፡ እንደውም ከ17 ዓመታት ውስጥ ግማሽ ያህሉን በእንፉቅቅ ነው ሲሄድ የነበረው፡፡ በውስጣዊ የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት እንዲሁም በውጪ ኀይሎች የድንበር ይገባኛል ጥያቄ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ደርግ፣ ከገቢው ወጪው በመብዛቱ ዕድሜውን የገፋው “በሶሻሊስታዊ ወንድማማችነት” በሚሰጡት ብድሮችና ድጎማዎች ነበር፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ ላይነቃነቅ የተቸከለው የመገበያያ ገንዘብ ፓሊሲ ትክክለኛ የምንዛሬ ሥርዓትን አለመከተሉ ሳያንስ ችካሉን ለማስጠበቅ የሚወጣው ድጎማ እጅጉን ብዙ ነበር፡፡ በጥቅሉ የደርግ ሥርዓት ኢኮኖሚ ከጅምሩ ለውድቀት የተፈጠረ (destined to fail) መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ይህም ሆኖ ሥርዓቱ ትምህርትን፣ ጤናንና እንዲሁም የግብርና ቴክኖሎጂን በማቅረብ ረገድ ከፍ ያለ እመርታን ማስመዝገብ መቻሉ ተመዝግቧል፡፡
የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም ዓለም አቀፋዊ የበላይነቱን ባረጋገጠበትና የምሥራቅ ሶሻሊስታዊ ርዕዮት ከሶቪየት ኅብረት መፈራረስ በኋላ ኀልዮታዊ ኑባሬው በተሸነፈበት ወቅት ነበር የደርግ ሥርዓትን በተራዘመ የትጥቅ ትግል የረታው ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን የመጣው፡፡ ለ17 ዓመታት በትጥቅ ትግል ያሳለፈው ሶሻሊስታዊ ኀይል ወደ ሥልጣን በመጣበት ወቅት ያጋጠመውን ርእዮተ ዓለማዊ ግጭት ለማጣጣምና ከዓለም አቀፍ እውነታ ጋር ለማስማማት በሚል ባያምንበትም የነጻ ገበያ ኢኮኖሚያዊ አስተዳደርን መሪ ሥርዓቱ አደረገ፡፡ በወቅቱ አገሪቱ የምትከተለው ሥርዓት “ነጭ ካፒታሊዝም” መሆኑን መሰከረ፡፡ ደርግ በመጨረሻዎቹ የጭንቅ ቀናቶች የተገበረው የቅይጥ ኢኮኖሚ መርህ በዘመነ ኢሕአዴግ ተለጥጦ ሥራ ላይ ዋለ። ኢሕአዴግ የፍላጎትና አቅርቦት ንጽጽር ገበያውን የሚመራበት፣ መሠረታዊ የኢኮኖሚ ግብአቶች በግለሰብ ባለቤትነት የሚተዳደሩበት፣ የሀብት ባለቤትነት ያለገደብ የተፈቀደበት፣ የገበያ ሰንሰለቶች ያለ ኮታና ያለ ጫና የሚሠሩበት፣ የገበያ ተቋማት በነጻነት የሚደራጁበት፣ እንዲሁም ሀብት ፈጠራ ኢኮኖሚያዊ ማበረታቻ የሚያገኝበት ሥርዓት ሊፈጥር እንደሚፈልግ ይፋ አደረገ፡፡ ይህን ተከትሎ የመገበያያ ገንዘቡ ከቋሚ የምንዛሬ ምጣኔ ወጥቶ በተመጠነ መልኩ በባንኮች ውድድር የሚወሰን እንዲሆን ተደረገ፡፡ በተራዘመ ጦርነት ውስጥ ያለፈውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መገንባት ግን ቀላል ሥራ አልነበረም፡፡ የነበረውን የአገሪቱን ፓለቲካና ዓለም አቀፋዊ ሚዛናቸውን ተጠቅመው የምዕራቡ ሀገራትም ኢትዮጵያ የእነርሱን ፓለቲካል ኢኮኖሚ ሞዴል ትከተል ዘንድ ጫና ማሳደራቸው አልቀረም፡፡ በዚህ ረገድ የዓለም ባንክና የአይ ኤም ኤፍ ሚና እጅጉን የጎላ ነበር፡፡ እነዚህ ተቋማት በፋይናንስ እጥረት ተይዛ ጭንቅ ውስጥ ለነበረችውና ገና ከጦርነት ድቀት ለመውጣት በማጣጣር ላይ ለነበረችው ሃገራችን ያቀረቡላት አማራጭ የፋይናንስ ድጋፋቸውን የምትሻ ከሆነ የባንክና የቴሌኮምና፣ የመጓጓዣ ሴክተሮቿን ለውድድር ክፍት እንድታደርግና የገንዘብና የውጪ ንግድ ሥርዓቱም ገበያ መር (liberalized) እንዲሆን ማድረግ ነበር፡፡ ከጥንስሳቸው ጀርባ የነበረው ዋነኛ አጀንዳ ግን የምዕራቡ ዓለም ትልልቅ ኩባንያዎች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዋነኛ የሚባሉትን ዘርፎች በጠዋቱ ይቆጣጠሩ ዘንድ የእጅ አዙር የፓሊሲ ድጋፍ ማድረግ ነበር፡፡ ታዋቂው ኢኮኖሚስትና የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ጆሴፍ ስቲግልዝ “Globalization and Its Discontents” በሚለው መጽሐፉ የወቅቱ የኢትዮጵያ ፓሊሲ አውጪዎች (በዋነኛነት መለስ ዜናዊ) ይህን የፓሊሲ ጫና ለመቋቋም ከፍተኛ ትግል ማድረጋቸውንና በመጨረሻም በእምቢተኝነት ጸንተው ሊያገኙት የነበረውን ጊዜያዊ የማገገሚያ የገንዘብ ድጋፍ ማጣታቸውን ይገልጻል፡፡ ስቲግልዝ ይህን ትግል ነጻ የሆነ የፓሊሲ ማውጣት አቅም የመፍጠር ትግል ሲለው በወቅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እነዚህ ተቋማት ሲያስፋፉት ከነበረው የመዋቅራዊ ማሻሻያ ፕሮግራም (Structural Adisustment Program) እና በተለያዩ ኢኮኖሚዎች ከተፈጠረው አሁንም ድረስ ዳፋው ካልጠፋው ሂደት ኢትዮጵያን የታደጋት ነው ይላል፡፡
የሟሸሸው ኢኮኖሚ እየተነቃቃ፣ ማዕከላዊ መንግሥቱም ሥልጣኑን እያጠናከረ፣ የአንድ ወቅት ታጋዮች የአሁኑ መሪዎችም ማስተዳደርን እየተለማመዱት፣ አንጻራዊ ሰላምም እየሰፈነ ሄደ ሲባል ነበር ከኤርትራ ጋር የድንበር ግጭት የተቀሰቀሰው። የባሩድ ጠረን ላለቀቀው፣ በሁለት እግሩ ለመርገጥ ለሚታትረው፣ ከውጪ ጫናም ጋር ለሚታገለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጦርነቱ ከባድ ፈተና ነበር፡፡ በመሠረተ ልማት፣ በመልሶ ግንባታ፣ በመሠረታዊ አገልግሎት አቅርቦቶች፣ በሰላምና መረጋጋት፣ በግብርና ጥገናዊ ማሻሻል፣ በትምህርትና በጤና አቅርቦቶች ማሻሻል ረገድ ለውጥ ለማምጣት የመልሶ ግንባታ ስትረቴጂን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ለነበረው የመለስ ዜናዊ መንግሥት በቀድሞ የትግል አጋሮቹ የተቀሰቀሰበት እሳት ታላቅ ፈተና ነበር፡፡ በአንድ በኩል ወረራውን ያልተዘጋጀበት በመሆኑ በሰው ኀይልና በመሣሪያ አቅም ረገድ አደረጃጀታዊ ፈተና ጋርጦበታል፡፡ ከጦርነቱ በአሸናፊነት ለመውጣት የበተነውን ተመላሽ ሠራዊት መሰብሰብ፣ የሰለጠኑና በቀድሞው ሠራዊት ውስጥ የነበሩ ወታደሮችና ኃላፊዎችን ማሳመን፣ ፍቃደኛ ዘማቾችን መመልመልና ማሰልጠን የመሳሰሉት ከፍተኛ ወቅታዊ ወጪ የሚጠይቁ ሥራዎችን ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል በተራዘመው ትግል ውስጥ ካካበታቸው (ባብዛኛው ከደርግ ሠራዊት ከተማረኩ) መሳሪያዎች በተጨማሪ አዳዲስ የጦር መሣሪያዎችን መግዛት አስፈላጊ ነበረ፡፡ ይህ በወቅቱ ከነበረው ኢኮኖሚያዊ እውነታ አንጻር ከቶ የሚቻል የማይመስል ነበር፡፡ በምዕራቡ ዓለም እገዛ እንዲሁም በፈጣንና ሁሉን አቀፍ ኅብረተሰባዊ ምላሽ በአሥር ሺዎች የሚቆጠር የሕይወት መስዋዕትነት ጦርነቱ ቢጠናቀቅም ጠባሳው ግን አሁንም ለሁለቱም ሃገራት ኢኮኖሚዎች አሉታዊ ውርስ ሆኖ ቀጥሏል፡፡የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መዘዙ ለገዢው ፓርቲም የተረፈ ነበር፡፡ በጦርነቱ አካሄድና አፈጻጸም ስትራቴጂ ላይ ያልተሰማሙት የበረሃ ጓዶች በውስጣቸው የነበረውን ልዩነት አደባባይ አውጥተውት የገዢው ፓርቲ አስኳል የሚባለው ህወሃት የመሰንጠቅ አደጋ ተጋረጠበት፡፡ በኢኮኖሚ አመራር ረገድ ይህ ውስጣዊ ልዩነት እና ተከትሎት የመጣው የህወሃት ክፍፍል አዎንታዊ ሚና ነበረው፡፡ በቀድሞው ጊዜ ከመልሶ ግንባታ የዘለለ ሕልም ላልነበረው አስተዳደር የሚጠበቅበት ነገር ከፍ ያለ መሆኑንና ይህም የዜጎችን ሁለንተናዊ ሁኔታ በመቀየር ብቻ የሚረጋገጥ መሆኑን ያሰመረ ዕድልን ፈጥሯል፡፡ ለዚያም ነው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገትና የመለስ ዜናዊን ታላቅነት የሚያወድሱ ተንታኞች ሁሉ የኢኮኖሚ ካላንደራቸው ከዚህ ወቅት የሚነሳው፡፡ የውስጥ ከፍፍሉን በቦናፓርቲዝም ትንታኔ ያሸነፈው መለስ ዜናዊ ተቀናቃኞቹን በተለያየ ስልት ከአካባቢው ካራቀ በኋላ ዋነኛ ትኩረቱን የሚመርጠውን ኢኮኖሚያዊ ትልም በማሰላሰል፣ በመጻፍና በመተግበር ላይ አተኮረ፡፡ የድርጅቱ ፓለቲካዊ ኀልዮት አስቀድሞ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ተብሎ የተሰየመ እንደመሆኑ፣ መለስ እርሱኑ በማጽናት የማስፈጸሚያውን ስልት ደግሞ “ልማታዊ መንግሥት” አደረገ፡፡ በብዙ መልኩ የሊበራል መንግሥት ፅንሰ ሐሳብ ተቃራኒ የሆነው ልማታዊ መንግሥት ዋነኛ ትኩረቱ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ ሆኖ የሰው ኀይል ግንባታን፣ የበቃ ኪራይ ስብሰባ ተቋማዊ ግንባታን፣ የበጀት አጠቃቀም ጥንቁቅነትን እና ጥብቅ የገንዘብ ፓሊሲን ዋነኛ መርሆቹ ያደርጋል፡፡ ኢኮኖሚ “ለገበያና ለገበያተኞች ብቻ መተው የለበትም፤ ይልቁንም መንግሥት ንቁ ተሳታፊ ሊሆንበት ይገባል” የሚለው ይህ ኢኮኖሚያዊ መርህ ኢኮኖሚውን ከዳር ቆሞ መመልከተን እጅጉን ይጠየፋል፡፡ በአንጻሩ የገበያ ክፍተትን ከመሙላት ባሻገር ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍ ያለ ሚና የሚኖራቸውን ተዋንያን በመምረጥና በመደገፍ ረገድ መንግሥት ንቁ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ ያምናል፡፡ ለዚህም ሲባል መንግሥት ሆን ብሎ የገበያ መዛባቶችን እስከመፍጠር ሊሄድ የሚችል ሚና እንደሚኖረው ያስባል፡፡ መለስም ሆነ ሀይለማርያም ኢትዮጵያን የመሯት በዚህ ከምሥራቃዊ እስያ ሀገሮች በተኮረጀና ነባራዊ ህልውናው የሊበራል መንግሥትን በመጋፋት ላይ በሆነ ኢኮኖሚያዊ መርህ ነው፡፡ ምንም እንኳን ሐሳባዊ ህልውናው ካፒታልን በመቆጠብ ልማትን ማረጋገጥና የዜጎችን ሕይወት ማሻሻል ቢሆንም ልማታዊ መንግሥት በኢትዮጵያ ያስከተላቸው ውጤቶች ዝንጉርጉር ነበሩ፡፡
በአንድ በኩል መርሁ ፈጣን የጠቅላላ ኢኮኖሚያዊ ምርት (GDP) እድገትን፣ የተሻለ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን፣ የማኅበራዊ አገልግሎት አቀራረብን ማሻሻል፣ ከፍ ያለ የውጪ መዋዕለ ነዋይ መሳብን አስችሏል። በሌላ ወገን ከፈጣን የሕዝብ ቁጥር ጋር የተደመሩት ከፍተኛ የድህነት ጫና፣ እየጨመረ የመጣ የሥራ አጥነት፣ መሻሻል ያቃተው የውጪ ንግድ፣ ከፍተኛ የእዳ ጫና እና እያደገ የመጣ የሀብት ልዩነት የሚያንገላታው ነው፡፡ ለነገሩ ባንድ በኩል ልማታዊ መንግሥቱ የራሱ ጠላት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለምን ቢሉ በቂ ሥራ ሊፈጥር ያልቻለ ኢኮኖሚ ይዞ ቢንገታገትም ቅሉ በሌላ ወገን በሚያፈሰው ሀብት በሚገነባቸው (በሚያበቅላቸው ቢባል ይቀላል) ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሺዎች የሚቆጠሩ ግማሽ ብስል የሆኑ ተመራቂዎችንም ያፈራል፡፡ ከእውነታው ያልታረቀ በሚመስል መልኩ የትምህርትና የተመራቂዎቹ የጥራት ደረጃ በየዓመቱ መውረዱን ትተነው እንኳን፣ የተመራቂዎቹ ብዛት ከመቅጠር አቅም ጋር ይመጣጠን ዘንድ አለመሠራቱ ልማታዊው መንግሥት የራሱን እግሮችን እያሰረ እንደነበር የሚያሳብቅ እውነታ ነው፡፡ ከ70 በመቶ በላይ ሕዝቧ ከ35 ዓመት ዓመት በታች ለሆኑባትና የድህነት መጠንዋ ወደ 38 በመቶ በሚደርስባት አገር ከመንግሥት መዋቅሩ መምጣት ያለበት የተቀናጀ ኢኮኖሚያዊ አመራር ቢሆንም የልማታዊ መንግሥቱ ሌላው ገጽታ ግን እየተባባሰ የመጣ የሀብት ብክነትና ሙስና ነው፡፡ ልማታዊ ጣልቃ ገብነትንና ስትራቴጄካዊ ከለላን እንደ ባርኔጣ የደፉት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ባንድ ወገን ከፍ ያለ የሀብት ብክነት የሚያስተናግዱ ሲሆኑ በሌላ ወገን ለአስተዳዳሪዎቻቸው ዕለታዊ ከበርቴነት በራቸውን ወለል አድርገው የከፈቱ ነበሩ፡፡ ነገሩ የተባባሰው ደግሞ የልማታዊ መንግሥቱ ሀሳብ አመንጪና የበላይ ጠባቂ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ከሞቱና በእግራቸውም ፓለቲካዊ ካፒታላቸው እጅግ የመነመነ የሆኑት አቶ ኀይለማርያም ደሳለኝ በቦታቸው ከተተኩ በኋላ ነው፡፡ የአቶ መለስ ሞት “መንግሥታዊ ሌቦችን” በእጅጉ ያበረታታ ሲሆን የአመራር ክፍተትን በመፍጠር የሀብት ብክነትን በአንድ ጊዜ ሰማይ ያደረሰ ክስተት ነበር፡፡ እዚህ ጋር መታሰብ ያለበት ነገር ከጠቅላላ ኢኮኖሚው ወደ 85 በመቶ የሚደርሰው ተጠቃሚነት (consumption) የመንግሥት ሲሆን ይህም በአገልግሎት፣ በፕሮጀክት፣ በቋሚ ንብረትና በአላቂ እቃ ግዢ የሚገለጽ ነው፡፡ ስለሆነም የአንድ ለሊት ሀብታሞችን የመፍጠሪያው ስልት ሙስና ከሆነ ያለመንግሥታዊ አጋሮቻቸው እውን የማይሆን መሆኑን ነው፡፡ የሆነውም ይኸው ነው፡፡ የሀብት ብክነቱና ሙስናው መስፋፋቱ ሳያንስ በላዩ ይኸው አለአግባብ የተገኘ ሀብት በሚፈጥረው የዋጋ ንረት ድሃው ሕዝብ ዋጋ መክፈሉ ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነበር፡፡ የድሃውን ኑሮ ለመደገፍ ተብለው የሚከናወኑ የድጎማ ተግባራት ሳይቀሩ ከፍ ያለ ብክነትና፣ የተንሰራፋ የጥቅመኝነት ሰንሰለትና ገደብ የለሽ ሙስና የሚስተዋልባቸው ሆኑ፡፡ ኮስማናው የአቶ ኀይለ ማርያም ፓለቲካዊ ካፒታልም ቁጥጥርን የማይቻል አድርጎት ስግብግብነቱ ልክ አጣ፡፡
“የተቀናጀ የአዲስ አበባና አካባቢዋ ማስተር ፕላን” የተባለውን እቅድ ተቋውሞ የጀመረው ሕዝባዊ እምቢተኝነትም የትኩረት አድማሱን አስፍቶ ሁለንተናዊ ነጻነት፣ ፍትሐዊ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ የፍትሕና ርትዕ መስፈን፣ ተጠያቂነት፣ ተግባራዊ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ መንግሥታዊ ግልጽነትንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በማንገብ አገሪቱን ይወዘውዟት ያዙ፡፡ ለወትሮው ለዚህ አይነት ተቃውሞ ምላሹ ጉልበት የነበረው ኢህአዲግ መራሹ መንግሥት ባንድ ወገን በተቃውሞው ስፋት በሌላ ወገን በግልጽና በድብቅ ከተቃውሞው ወገን በቆሙት የራሱ አባላት ጫና አጣብቂኝ ውስጥ ገባ፡፡ ለውጥ ግን በቀላሉ ሊመጣ አልቻለም፡፡ ከሦስት ዓመታት ሕዝባዊ እምብተኝነት፣ ከብዙዎች ሞትና አካል መጉደል፣ ከሺዎች እስር፣ ከብዙ ሃብት ብክነትና ውድመት፣ ከተንሰራፋ ኢኮኖሚያዊ መቀዛቀዝ፣ ከሁለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች፣ ከብዙ ማኅበራዊ ቀውስ (መፈናቀል፣ ስደትና አለመረጋጋት) እንዲሁም ከብዙ ምልጃና ውጪያዊ ጫና በኋላ ኢሕአዴግ ራሱን ወደመመልከት ዞረ፡፡ የግንባሩ ሊቀ መንበር እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኀይለ ማርያም ደሳለኝ ራሳቸውን ከሥልጣን ማግለላቸው ለአዲስ አመራር መምጣት በሩን ከፈተ፡፡ ለ17 ቀናት የተራዘመ ግምገማ ያደረገው ኢሕአዴግም አዲሱን ሊቀመንበሩን ዐቢይ አህመድን አገኘ፡፡ በዜጎችም ልብ ውስጥ ጭላንጭል ተስፋ ፈነጠቀ፡፡ የዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ 7 ዓመት ዓመት ከስድስት ወራት የሆነው ሲሆን ይገመገምባቸው ዘንድ የሚያስችሉ በርካታ ርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ፓለቲካዊ ርምጃዎቹን ለጊዜው ትተን ኢኮኖሚያዊ ርምጃዎቹ ላይ እናተኩር፡፡ የአስተዳደሩ ትልቁና ዋነኛው ርምጃ ለትርፍ በሚሰሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ረገድ የወሰደው ርምጃ ነው፡፡ በዚህም ባንድ ወገን የተወሰኑትን የልማት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ለግል ባለሀብቶች ለመሸጥ ሲወስን በሌላ ወገን በተወሰኑ ሌሎች ላይ ደግሞ የተወሰነውን ያህል ድርሻ ለግል ባለሃብቶች ለማስተላለፍ ወሰነ፡፡ ምንም እንኳን ይህ ጉዳይ በገዢው ፓርቲ ውስጥ እንደ አጀንዳ ከቀረበ ቢቆይም ባለመግባባቶች ቆይቶ ውሳኔ የተሰጠበት የዐቢይ አስተዳደር ወደሥልጣን በወጣ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ነበር፡፡ ይህን ውሳኔ ግዙፍ የሚያደርገው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ለብዙ ዓመታት እንደማይነኩ ጫፎች ሲቆጥራቸው የነበሩት፣ ገቢ በማስገኘት ረገድም ቁልፍ ሚና የነበራቸው የመንግሥት የንግድ ተቋማት የተካተቱበት በመሆኑ ነው። ውሳኔው የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ መርከብና ሎጅስቲክ ኢንተርፕራይዝ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የባቡር ኮርፖሬሽን በውስጡ ማቀፉ ነው፡፡ ከዚህ በመለስ ይህ ውሰኔ የስኳር ፋብሪካዎችን፣ የማዳበሪያ ፋብሪካዎችንና ሌሎች ድርጅቶችን ያካተተ ነበር፡፡በርግጥም ውሳኔውና ለውሳኔው መነሻ ሆነዋል የተባሉት ችግሮች አለመጣጣም ይታይባቸዋል፡፡ እንደ መንግሥት ገለጻ ይህ ውሳኔ አካታች፣ ቀጣይነት ያለውና የዘመነ ኢኮኖሚ ለመፍጠር በሚል የተወሰነ ነው፡፡ በሌላው ወገን መንግሥት ራሱ ደግሞ ውሳኔው የብድር ጫናን ለማቅለል፣ የውጪ ምንዛሬን ለማግኘት፣ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና መንግሥታዊ ወጪን ለመቀነስ የተወሰደ እርምጃ ነው ይላል፡፡ በሁለቱም ወገን የሚነሱት ምክንያቶች እውነተኛ ቢሆኑ እንኳን የመድረሻና የመንገድ አለመጣጣም ይስተዋልባቸዋል፡ ፡ መዋቅራዊ ችግር ጠፍንጎት ዝቅተኛ የግብርና ምርታማነት፣ የተንሰራፋ የገበያ ዝንፈትና ረዥም የገበያ ሰንሰለት፣ ያልተደራጀ የገበያ ቁጥጥርና አቅም፣ በመንግሥት ጥገኝነት የተፈጠረና ተወዳዳሪነትን የሚፈራ የግል ዘርፍ፣ እየሰፋ የመጣ የውጭ ንግድና ክፍያ ሚዛን፣ የተንሸዋረረ የጉልበት ገበያና ሌሎች አያሌ ችግሮች ለሚዘውሩት ኢኮኖሚ ሁነኛ መላው የመንግሥት (የህዝብ) ተቋማትን ወደ ግል ማዛወር ነው የሚለው መከራከሪያ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ በዚያ ላይ ይህ ሁሉ የሚሆነው ግልጽ የሆነ የሽያጭ ሥርዓት ባልተደራጀበት፣ የአክስዮን ገበያ መሠረተ ልማት በሌለበት፣ የመንግሥት ተቋማት የመቆጣጠር አቅም ባልጠነከረበት፣ ፓለቲካዊ ምኅዳሩ በጥገኛ ባለሃብቱ ስር በወደቀበት ሁኔታ መሆኑን ነገሩን የበለጠ ግራ ያደርገዋል፡፡ ለነገሩ ተባለ እንጂ አፈጻጸሙ ዓመታትን መውሰዱ እሙን ነው፡፡
አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ አመራርን ከማጠናከር ጋር በተያያዘ ጠ/ሚ ዐቢይ ያከናወኑት ተግባር የኢኮኖሚ አመራር ተቋማትን መሪዎች መቀየር፣ አደረጃጀታቸውን ማሸጋሸግ እና ተጠሪነታቸውንም ማስተካከል ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት ውስጥ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የቀድሞ ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን (የአሁኑ የፕላንና ልማት ኮሚሽን)፣ ብሔራዊ ባንክ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን (አሁን የገቢዎች ሚኒስቴር) እና ሌሎችም የፌደራል ተጠሪ መ/ቤቶች ይገኙበታል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የዐቢይ አስተዳደር ያደረጋቸውን የበዙ የተሿሚዎች ሽግሽግና ቅየራዎች ላስተዋለ ሰው ውስጣዊ መረጋጋትን ማግኘት እንደቸገረው ይጠቁማል፡፡ በዚህ ላይ ታይቶ በየማይታወቅ ሁኔታ የሚታየው የፌደራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነት መሻከር፣ ትከሻቸውን ያደነደኑ ክልሎች መብዛት፣ በብዙ አካባቢዎች የራቀው ሰላም፣ ለፓለቲካዊ አላማ በመዋቅሩ ድጋፍ የተፈለፈሉ የወጣት ንቅናቄዎች እያደር እየገነነ የመጣ ጥቅመኝነትና እምቢተኝነት፣ የተስፋፋ የደቦ ፍርድ፣ ከሥራቸው ተገዝግዘው የሳሱ የታች መዋቅሮች፣ በየአካባቢው እያደር እያየለ የመጣ አክራሪ ብሔርተኝነት እንዲሁም በትርምስ የተሞላ የፓለቲካ ምኅዳር ማስተዳደርን (governability) ከባድ አድርጎታል፡፡ ይህም አሉታዊ ተጽእኖውንም በኢኮኖሚው ላይ ማሳደሩ አልቀረም፡፡ እርግጥ ነው የዐቢይ አህመድ አስተዳደር በምኞት ረገድ አይታማም፡፡ ብዙዎቹ ተንታኞችም ምኞቱን (intent) ሲጠይቁ አይታዩም፡፡ ብቃትና ውጤታማነቱ ላይ ግን ብዙ ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡
ኢኮኖሚውን ከመምራት አኳያ ትልቁ ጉድለቱ ይህ ነው የሚባል ግልጽ የፓሊሲ ሰነድ የሌለው መሆኑ ነው፡ ፡ የዚህ ግልጽ የኢኮኖሚ መምሪያ ሰነድ አለመኖሩ ደግሞ ባንድ በኩል የውጪ ኀይሎች እንደልባቸው እንዲጋልቡት የፈቀደ ሲያስመስልበት በሌላ ወገን የሚወስዳቸው ፓሊሲዎች መናበብ የሌላቸውና በውጤት ረገድ ተቃርኖ የሚስተዋልባቸው እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ አንድ ሁለቱን ለማየት ያህል፡ አስተዳደሩ ወደሥልጣን በመጣ በተወሰኑ ወራት ነበር ገደብ ያለው የበጀት ፓሊሲ (restrained fiscal policy) እንደሚከተል፣ በዚህም ዋነኛ ትኩረቱ ወጪን መቀነስ (expenditure saving) እንደሚሆን ያስታወቀው፡፡ ይህን ተከትሎም አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በበጀታቸው ውስጥ እንዳያካትቱ የተነገራቸው አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በዓመቱ መጀመሪያ የበጀት እቅዳቸውን ለገንዘብ ሚኒስቴር ሲያስገቡ ይህንኑ አደረጉ፡፡ ብዙዎቹም እጃቸው ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን መጨረስ ላይ ያተኩሩ ዘንድ ሆነ፡፡ ይህ በሆነ በወራት ጊዜ ውስጥ ግን በተለመደው የፕሮጀክት ዝግጅትና ትገበራ ሥርዓት ውስጥ ያላለፉና በጠቅላይ ሚኒስቴሩ አነሳሽነት እንዲወጡ የተነገረላቸው ቢሊዮን ብሮችን በወጪነት የሚጠይቁ የአዲስ አበባ ወንዝ ዳር ልማትና የቤተ መንግሥት ልማት ፕሮጀክቶች ታወጁ፡፡ ለፈጻሚዎቹም ዱብዳ የሆኑት እነዚህ ፕሮጀክቶች በምን ልኬት ፊሲካል ገደብን እንደሚደግፉ ግልጽ አይደለም፡፡ እሱ ቀርቶ በምን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፋይናንሻል ሚዛን ጊዜውን የዋጁ እንደሆኑ እንኳን አይታወቅም፡፡ ወሳኝ የሚባሉ የኃይል ልማት፣ የመስኖና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፕሮጀክቶች ተገፍተው ለእነዚህ ቅድሚያ የመስጠቱ ጉዳይም ለማንም ግልጽ አይደለም፤ ማብራሪያም የለውም፡፡ በዚህ ላይም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ለተገልጋይ የተመቹ በማድረግ ስም የተያዘው የግዢ ቸበርቻቻ (buying frenzy) እንደምን ከውጪ ቁጠባ ጋር እንደሚሄድ ግልጽ አይደለም፡፡ በላዩ ላይ ለመስተንግዶና ታይታ ለበዛባቸው ፕሮግራሞች የሚወጣውን ወቅታዊ (recurrent) ወጪ ላስተዋለ ግራ መጋባቱ ቢያይልም አይገርምም፡፡ በዚህ ሁሉ እንግዲህ ምኞትና ተግባር ለየቅል መሆኑ እሙን ነው፡
ከመዋቅራዊ አላባዎች ረገድ የዐቢይ አህመድ አስተዳደር ይህ ነው የሚባል የፓሊሲ እርምጃ አልወሰደም፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታት ባለበት እየረገጠ ያለው የውጪ ንግድ በዚህም ዓመት ዓመት አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ነው፡፡ ባለፉት አስር ወራት የተስተዋለው የወጪ ንግድ ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር በ1.3 በመቶ የቀነሰ ነው፡፡ በስርጭትም ሆነ በገበያ መዳረሻ ረገድም ይህ ነው የሚባል ለውጥ አልተስተዋለበትም፡፡ ይህ ማለት የውጪ ምንዛሬ ግኝቱ አሁንም ለፍቶ አደር ኢትዮጵያውያን በሚልኩት ሃዋላ እና በእርዳታ ሰጪዎች ችሮታ ላይ የተገደበ ሆኖ ቀጥሏል ማለት ነው፡፡ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ለብሔራዊ ባንክ የተሰጠ ዋና ሥራ ነው፡፡ ይህም የገንዘብ ፓሊሲ መገለጫነቱ ያይላል፡፡ እንዲሁም ኢኮኖሚስቶች ማንኛውም የዋጋ ንረት የገንዘብ ፓሊሲ ውጤት ነው ይላሉ፡፡ ይህን የሚሉት ብሔራዊ ባንኩ የገንዘብ አቅርቦትን በመወሰን የዋጋ እድገትን ማስተካከል የሚችል አቅም እንዳለው ሲያመለክቱ ነው፡፡ ታዲያ ለዓመታት በዋጋ ንረት የተማረረ ሕዝብ ባደረገው የተራዘመ የእምቢተኝነት ጫና ወደ ሥልጣን የመጡት ጠ/ሚር ዐቢይ በሥልጣን በቆዩበት ዓመት የዋጋ ንረት ከሁለት አሀዝ ሊወርድ አለመቻሉ የፓሊሲ መሳሪያ እጥረት ወይስ የፓለቲካ ቁርጠኝነት እጦት ማስባሉ አይቀርም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የአንድ ኩንታል ጤፍ አማካይ ዋጋ ከ17,000 ብር የዘለለ ሲሆን 1 ኪሎ ስጋም 3000 ብር ይሸጣል፡፡ መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ከዳቦ እስከ ዘይት ከፍተኛ ጭማሪ ያስተዋሉ ሲሆን አማካኝ ወርሃዊ የዋጋ ንረቱም 15.9% ነው፡፡ በዚህ ረገድ የምናስተውለው ነገር ባንድ በኩል የገንዘብ ፓሊሲው ላለው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ተመጣጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳልቻለ ሲሆን በሌላ መልኩ አስተዳደሩ የእቃዎችን አቅርቦት በተለይም የመሠረታዊ ሸቀጦች ለማሻሻል የወሰደው እርምጃ አለመኖሩን ነው፡፡ ችግሩን ተቀምጠው ቢያዩት ራሱን ይፈታ ይመስል፡፡ ሌላው መሠረታዊ ጫና ከመንግሥት ኢንቨስትመንት ሥርዓት የሚመነጭ ሲሆን ይህም በዋናነት ከመመሪያ እጦት ይመነጫል፡፡ የመንግሥት ኢንቨስትመንት ለዐቢይ አህመድ መንግሥት ቅርቃር ሆኗል፡፡ አስተዳደሩ ወደ ሥልጣን በመጣበት ወቅት ከፍተኛ ውጪያዊ ተቀባይነትን እንዲያገኝ ካስቻሉት መስመሮች አንዱ ለግል ዘርፉ ከፍ ያለ አትኩሮት እሰጣለሁ ብሎ ቃል መግባቱ ነበር፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለ በግብርና፣ በገጠር ልማት፣ በማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ በቴክኖሎጂ፣ በማጓጓዣ፣ በኀይል ልማት፣ በአገልግሎት ዘርፍ የከፋ የመሠረተ ልማት እጥረት ባለበት ሀገር የግል ሀብቱ ራሱ እንዲመጣ የሚያስችል የመንግሥት ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም ሃቁ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁንም ቢሆን የመንግሥት ኢንቨስትመንት እጅከአስፈላጊው የመንግሥት ኢንቨስትመንት ጋር እንዴት ይታረቃል ወይም ይጣጣማል ነው፡፡ ላም እሳት ወለደች ነው ነገሩ፡፡ አይተዉት ነገር እጅግ አስፈላጊ ነው፤ አያረጉት ነገር ቃሉ ሌላ ነው፡፡ ሌላው ከዚህ ጋራ የሚያያዘው ነገር ግን አስተዳደሩ ምንም እንኳን የፍትሃዊጉን የሚያስፈልገው መሆኑ ነው፡፡ አጣብቂኙ ታዲያ ከአጋሮች የተገባው ቃልና እሱን ተከትሎ የመጣው ድጋፍ ተጠቃሚነት ጥያቄ ወደ ሥልጣን ቢገፋውም አሁንም ቢሆን ግልጽ የሆነ የልማት ፕሮጀክቶች መረጣና ቅደም ተከተል ማስያዝ ሥርዓት የሌለውና ያልነደፈም መሆኑ ነው፡፡ የብድር ጫናን በተመለከተ ሃገሪቱ አሁንም ቢሆን የብድር ሸክሟ እንዳስጎነበሳት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የዐቢይ አህመድ አስተዳደር የተከላቸው መስመሮች ሶስት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ተጨማሪ ብድሮችን በኮንሴሽናል ብድሮች (ረዥም የመክፈያ ጊዜና አነስተኛ ወለድ ባላቸው) መገደብ ነው፡፡ ሁለተኛው የተወሰኑ ብድሮችን መዋቅር (የመክፈያ ጊዜና ወለድ ምጣኔ) ከኮመርሻል ወደ ኮንሴሽናል መቀየር ነው፡፡ ሌላውና የመጨረሻው እርምጃ የመክፈያ ጊዜአቸው የደረሰ ብድሮችን የመክፈያ ጊዜ ማራዘም ነው፡፡ ከሶስቱ ርምጃዎች የተሻለ ውጤት የተመዘገበው በመጨረሻው ነው፡፡ በሌሎቹ ረገድ አፈፃፀሙ ያን ያህልም ነው፡፡
ከሁሉም የበለጠው የዐቢይ አስተዳደር ፈተና የሚመነጨው ግን እየተስፋፋ ከመጣው ሥራ አጥነትና እሱን ለማቃለል ተብለው ከተፈጠሩ ፕርግራሞች ውጤት አልባነት ነው፡፡ ምንም እንኳን የሥራ እጥነት ችግሩ እየተስፋፋ ቢሆንም አስተዳደሩ ከቀድሞዎቹ አቻዎቹ የወረሳቸውን የሥራ ፈጠራ ስትራቴጂዎች እንደያዘ ያዘግማል፡፡ የቀደሙት የሥራ ፈጠራ ስትራቴጂዎች በጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት፣ በመንግሥት ፕሮጀክቶች እንዲሁም በግል ሥራ ፈጠራ ድጋፍ የተወሰኑ ነበሩ፡፡ ነገሩን ነው እንጂ የግል ሥራ ፈጠራ ድጋፍ የለም ቢባል ይሻላል፡፡ ሁለቱን የቀደሙትን የሥራ ፈጠራ መንገዶች ለመደገፍም የጥቃቅንናአነስተኛ አደረጃጀቶች እንዲሁም የወጣቶች ተዘዋዋሪ የሥራ ፈጠራ ፈንድ ሥራ ላይ የዋሉ ሲሆን አፈፃፀማቸው ግን ደካማ፣ ፈጠራ የሚጎለው፣ ሀብት አባካኝ፣ ውጤትን ያላማከለ፣ የኢንተርፕራይዝ ቁጥር ብቻ ማዕከል ያደረገ ለወጣቶቹ በቂ ድጋፍ የማያደርግ፣ የአሰራር ምቹነት የሚጎለውና በብድር ፍቃድና አከፋፈል (approval and disbursement) መካከል ከፍተኛ መዘግየት ያለበት ነው፡፡ ይህ የሥራ ፈጠራ ስትራቴጂ በሁለት ወገን ድክመት አለበት፡፡ በአንድ ወገን ስትራቴጂው ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ ለግሉ ዘርፍ የሥራ ፈጠራ ድጋፍን የነፈገ ነው፡፡ በሌላ በኩል አደረጃጀቱና አሰራሩ የተንዛዛ፣ ወጪ የሚጠይቅ፣ ለጥቅመኝነት የተመቻቸ፣ ግለሰብ ሥራ ፈጠራዎችን የማያበረታታ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በሀገሪቱ የተመዘገቡ የሥራ ፈላጊዎችና በየዓመቱ የሚፈጠሩ ሥራዎች ልዩነት የትየሌለ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ የተጋጋለ የብሔር ፓለቲካ፣ አውዳሚ የማኅበራዊ ሚዲያ ትርክት፣ጦርነት እያደገ የመጣ የገንዘብና ፓለቲካ ጥምረት እንዲሁም የፀጥታ መዋቅሩ ድክመት ተጨምሮበት ሥራ አጡ ወጣት የግጭት አዙሪቱ ዋነኛ ተዋናይ እየሆነ ነው፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ መነሳት የሚኖርበት ሌላኛው ጉዳይ የፋይናንስ ዘርፉ አፈጻጸም ነው፡፡ የዐቢይ አህመድ አስተዳደር ትኩረት ካደረገባቸውና የ “ለውጡ” ማማዎች ከሚባሉት አንዱ የሆነው የፋይናንስ ሥርዓቱ ነው፡ጊዜው ትንንሽ የፋይናንስ ሱቆች የሚፈሉበት ሳይሆን ትልልቅና ተወዳዳሪ የፋይናንስ ተቋማት ይፈጠሩ ዘንድ ያሉበት መሆኑን ልብ ይሏል፡ ፡ ከዚሁ ዘርፍ በተያያዘ የዐቢይ አህመድ አስተዳደር አንፃራዊ ክፍትነት ያሳየ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በኬንያና በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ባንኮች እግራቸውን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት እያኮበኮቡ ነው፡፡ አገራዊው የፋይናንስ ዘርፍ ታዲያ ተወዳዳሪነቱ ይረጋገጥ ዘንድ በሰው ኀይል፣ በአስተዳደር፣ በቴክኖሎጂና በአሰራር ረገድ እንዲዘምን መገፋፋት ያለበት ሰአት አሁን ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም በዘርፉ የሚታዩ መረን የለቀቁ ብልሹ አሰራሮችን ማረምም ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ብልሹ አሰራር በተንሰራፉባቸው በብድር አሰጣጥ፣ በውጪ ምንዛሬና በኮምሽን እንቅስቃሴዎችም ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ይሻል፡፡ በዚህ ረገድ አስተዳደሩ የውጪ ምንዛሬ አፈቃቀድን ማዕከላዊ በዓለም አቀፍ ዋጋ ተመን ላይ የተመሠረተ ለማድረግ የሞከረ ቢሆንም እርምጃው ደግሞ የLC አፈቃቀድን በማሰረዘም የገቢ ንግድ እቃዎች ዋጋን በማናር የራሱን ጫና እያሳደረ ነው፡፡
በአጠቃላይ ያለፈው 7 ዓመት ብዙ ተስፋ፣ ትንሽ ተግባራትና ትልልቅ ስጋቶች የተስተዋሉበትና የሚያንዣብቡበት ነው፡፡ ተስፋዎቹን ወደተግባር ከመቀየርና ስጋቶችን ከማስወገድ አንጻር የዐቢይ አህመድ አስተዳደር ሊወስዳቸው የሚገባቸው እርምጃዎች በማመላከት እናጠቃልል፡፡ በዋናነት ከአስተዳደሩ የሚጠበቀው የሚመራበትን የኢኮኖሚ መርህ ግልጽ ማድረግና ሰንዶ ለኢኮኖሚ ተዋናዮች ሁሉ ግልፅ ማድረግ ነው፡፡ ወዲህም ይህ ሰነድ የፓሊሲ ተገማችነት ሲያሰርጽ ወዲያውም ከዓመት በኋላ ይመጣ ዘንድ ባለው ምርጫ ገዢው ፓርቲ በምን ማዕቀፍ ሊመረጥ እንደሚፈልግ ግልጽ ያደርጋል፡፡ ኢንቨስትመንትና ገበያን ከማረጋጋት እንዲሁም አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እርግጠኝነትን ከማሳደግ አንጻር የፓሊሲ ግልፅነት የሚኖረው ሚና የጎላ ነው፡፡ በዚሁ ሰነድ ውስጥ ግን:
- መዋቅራዊ ተግዳሮቶችን (ቀርፋፋ የግብርና ምርታማነት እድገት፣ ተቸክሎ የቀረው ኤክስፓርት፣ ሥራ እጥነት፣ ዝቅተኛ የኢንዱስትሪ ውጤት እድገት እየሰፋ የመጣ የንግድ ሚዛን ጉድለትና የክፍያ ምጣኔ፣ የዋጋ ንረትና የመሳሰሉት) የመፍቻ መንገዶች ሊመላከቱ ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የግሉን ዘርፍ ማበረታታት እንደተጠበቀ ሆኖ ግልጽ በሆነ መልኩ የመንግሥት ኢንቨስትመንት የሚፈስባቸው ቦታዎችና ምጣኔው መገለጽ አለበት፡፡
- የግሉን ዘርፍ የማበረታታት እንቅስቃሴ ከሥራ ፈጠራ አቅም ጋር የተቆራኘ እንዲሆን ማድረግ ይገባል፡፡
- . ለኢኮኖሚያዊ ፓሊሲ አተገባበር እንቅፋት የሆነው በፌደራልና በክልል መንግሥታት መካከል ያለ የመጠራጠርና የጠላትነት ግንኙነት በፓለቲካ ቁርጠኝነት መፈታት ይኖርበታል፡፡
- የፌደራል መንግሥቱ የውጪ ቁጠባ ፓሊሲ በቀን ተቀን ተግባራት መገለጽ ያለበት ሲሆን በዝርዝር የፕሮጀክት መረጣና ማጽደቂያ ሥርዓት መደገፍ አለበት፡፡
- . የመሠረታዊ ሸቀጦች አቅርቦትን ከመንግሥት መስመር አውጥቶ ለግል ዘርፉ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ግን በጠንካራ መንግሥታዊ የቁጥጥር ሥርዓት መታገዝ አለበት፡፡
- አስተዳደሩ የብድር አስተዳደር ሥርዓቱን ስጋት መቀነስን ባማከለ መልኩ መከለስ አለበት፡፡ ሥርዓቱንም ከፓለቲካ ጥላ ማፅዳት አለበት፡፡
- የገንዘብ ፓሊሲ አስተዳደሩ በነጻ ብሔራዊ ባንክ እንዲመራ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ይህም የገንዘብ ፓሊሲው እንደተንከባላይ የፊሲካል ፓሊሲ መሳሪያ የሚቆጠርበትን አሠራር እንዲቀር ያደርጋል፡፡
- . ለዚህ ግን ብሔራዊ ባንኩን ነጻና በሞያተኞች የሚተዳደር ማድረግ ይጠይቃል፡፡
- የኢኮኖሚ አስተዳደር ተቋማትን ታማኝና በሙያተኛ የተደራጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የትምህርት ዝግጅት ብቻውን ዋጋ እንደሌለው በመረዳት ሙያዊ ልምድንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አንጻር ሁሉንም ነገር ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ የመውሰድ አባዜም ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ የቄሳርን ለቄሳር እንዲሉ ተቋማዊ ኃላፊነት ከመወሰን ነጻነት ጋር በአግባቡ ሊከፋፈል ይገባል፡፡
- ይተገበር ዘንድ ያለው የመንግሥት ድርጅቶችን ድርሻ ወደ ግል የማስተላለፍ ተግባር ከመተግበሩ በፊት ሁለንተናዊ የገበያ ማሻሻያ ተግባራት መከናወን አለባቸው፡፡ ይህም ገበያ የሚተዳደርባቸውን ሕግጋት ማሻሻል፣ የገበያ ተቋማትና መሠረተ ልማት ማሻሻል፣ የተቆጣጣሪ አካላትን አቅም መገንባት፣ ፀረ ውድድር እንቅስቃሴዎችን የሚዳኙ ተቋማትን አቅም ማጠናከር፣ የሸማች ከለላ ተቋማትን መገንባትና ማጠናከር፣ የአእምሮአዊ ሀብት ጥበቃ ሥርዓትን ማጠናከርና የመሳሰሉትን ይጨምራል፡፡
ማጠቃለያ
በዚህ የገበያ መር ኢኮኖሚ የማቋቋም ሒደት ውስጥ መንግሥት የሚኖረው የፖሊሲ ነፃነት ነው። በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን የልማታዊመንግሥት የልማት አካሄድን በመቃወም ሲተቹ የነበሩት የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደሥልጣን በመጡ በስድስት ወራት ውስጥ ያመቻቹት ከፍተኛ የሆነ የብድር መጠን እንዲሁ የመጣ አይደለም። ይልቁንም የድርጅቶቹ ዋና ጉዳይ የሆነው ለምዕራባውያን ድንበር የለሽ ካፒታል የገበያ ዕድሎችን ማመቻቸትና እንቅፋቶችን ለማንሳት የተደረገ ክፍያ ነው። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ገንዘባቸውን ብቻ ሳይሆን፣ የሙያ ዕገዛ ይሰጣሉ የሚባሉ የእነሱን ሥልጡን ባለሙያዎችም በከፍተኛ ክፍያ በተለያዩ ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በዕርዳታ፣ አቅም ግንባታና ትብብር ስም ያስቀምጣሉ። በገንዘብና በሰው ኃይል የታገዘውን በመንግሥት መዋቅርና አሠራር ውስጥ ያላቸውን መገኘት ተጠቅመውና ኢትዮጵያን የመሰሉ አገሮች ሁሌም የሚጋፈጡትን መዋቅራዊ ተግዳሮትና የኢኮኖሚ ቀውስ እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው የፖሊሲ፣ የሕግና የአሠራር ውሳኔዎች ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ያሳድራሉ። ወሳኝ የሚባሉ አብዛኛውን ሕዝብ የሚመመለከቱ ውሳኔዎችም በእነዚህ ዓለምአቀፍ ድርጅቶችና መሪዎች አስተሳሰብና ፍላጎት ላይ ተመሥርተው እንዲወሰኑ ከፍተኛ ጫና ያሳድራሉ። በብዙ አፍሪካ አገሮችይኼ ተሳክቶላቸዋል፣ በኢትዮጵያም እየተሳካላቸው ይገኛል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች የመክፈት ሒደት ውስጥ በመገናኛ ብዙኃን የሚነገሩ የገበያ ውድድርን የሚያበረታቱና በበጎ የሚሣሉ ማስታወቂያዎች ሳይቀሩ፣ የእነዚህን ተቋማት ባርኮት ሳይቀበሉ ወደ ሕዝቡ አይደርሱም ነበር። ስለዚህም አገር በቀል የሚል ስም ቢሰጠውም አሁን የምንገኝበት የፖለቲካ–ወ–ኢኮኖሚ የፖሊሲና የውሳኔ መስጫው ምኅዳር በሕዝብ ከተመረጠው መንግሥት እኩል ወይም በሚበልጥ መልኩ የሌሎች አካላት ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሆኑ ልብ ማለት ግድ ይላል።
በመቀጠል በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነጋገር ውስጥ በጉልህ የሚስተዋለው የመንግሥትን በልማት ውስጥ ያለውን የማይተካ ሚና የማናናቅና የማሳነስ አመለካከት መገራት አለበት። በየትኛው ዘመን ባለ የአገራችን የኢኮኖሚ ልማት ሒደት ውስጥ መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ ሳይወጣ የቀረበት ዘመን የለም። በአሁኑ ዘመን የኒዮሊበራል ርዕዮተ ዓለም መፍለቂያ የሆኑት ምዕራባውያንም ቢሆኑ የግሉ ክፍለኢኮኖሚ ከልክ ያለፈ ሚና ወደ ቀውስ ውስጥ ሲከታቸው ኢኮኖሚውን የሚታደገው መንግሥት ነው። ስለዚህም በእውነታው ዓለም የሌለና ተጨባጭ ያልሆነውን ዕይታ በመረጃና በዕውቀት በተደገፈ መንገድ ማረቅ ያስፈልጋል።
በመጨረሻም ኢትዮጵያን እንደ ግዙፍና ሰፊ የገበያ ዕድል ብቻ ከሚያስቧት ዓለም አቀፍ ከበርቴዎች ጋር የሚኖረንን መስተጋብር፣ እኛም ልክ እንደእነሱ የገበያ ሒደት ቅልጥፍናንና ትርፍን ብቻ በሚያሰላ አመለካከት ልንቃኘው አይገባም። በአገራችን ውስጥ መዋቅራዊና ታሪካዊ በሆነ ሒደት የተገለሉ፣ ለኢኮኖሚያዊ ብዝበዛ በቀላሉ የተጋለጡና የሚጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ አውቀን ፖሊሲዎቻችን ማኅበራዊ ፍትሕንና ፍትሐዊነትን ያማከሉ መሆናቸው ልናረጋግጥ ይገባል፡፡
