የባልደራስ ፓርቲ አማራጭ የኢኮኖሚ ሞዴል
ዜጎች በተፈጥሮ እኩል በመሆናቸው የሰብዓዊ እንዲሁም የዜግነት መብታቸው መከበር አለበት፡፡ ተዘዋውሮ የመስራት፣ የመወሰን፣ ሀብት የማፍራት፣ በተገቢው ፍትሕ የመዳኘት እንዲሁም ንቁ ተሳትፎ የማድረግ እኩል ዕድል እና መብት አላቸው፡፡ በዘር፣ በቀለም፣ በሀብት፣ በጾታ፣ በሀይማኖት፣ በአመለካከት፣ ወዘተ. ላይ የተመሰረተ አድልዎ ተገቢ አይደለም ብሎ ባልደራስ ያምናል። አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ከተማ ናት ሲልም በዚሁ የማያወላውል መርሑ እና ፅኑ እምነቱ ጭምር ነው፡፡ ይሁን እንጂ የቀድሞ መንግሥት ላለፉት በርካታ አመታት በተከተለው የተሳሳተ የኢኮኖሚ ሞዴል እና አስተዳደር ሳቢያ የዋጋ ግሽበት፣ የተዛባ የሀብት ክፍፍል፣ አድሎዊነት፣ የመብት መገፈፍ እንዲሁም ድህነት ተፈጥሯል፡፡ በኢኮኖሚው የወደፊት ሁኔታ እምነት ማጣት (Economic Uncertainty) ጭምር ተከስቷል፡፡ በተለይ አዲስ አበባን ማዕከል ካደረገ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ መጠኑ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የሃገር ገንዘብ ወደ ውጭ አገራት ሸሽቷል፡፡ ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ አዲስ አበባን ጨምሮ የመላ ኢትዮጵያንን ገፅታ መቀየር የሚችል ነው:: ነበርም፡፡
ችግሩ ገዝፎ ዛሬም በርካታ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎችን በአገራችን አምጥቷል፡፡ እንደ ባልደራስ እምነት አዲስ አበባን ራስ ገዝ ማድረግ ይህን የመሰሉ የኢኮኖሚ እምነት ማጣትን አስወግዶ የሚሸሸውን ከፍተኛ የአገር ሀብት ቀንሶ ለልማት በማዋል የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ ብሎም የፖለቲካ ችግራችንን በጥልቅ ፖሊሲ መቅረፍ ይቻላል ብሎ የተነሳው፡፡ የኢኮኖሚ ችግራችንን ለመቅረፍ የሚረዳ የተሻለ የኢኮኖሚ ሞዴል ተገቢ እና አስፈላጊ ነው በሚልም ረጅም ጊዜ ሰጥቶ ታትሮል፡፡ በርካታ የሆኑ ዓለም ዓቀፍ የኢኮኖሚ ሞዴሎችን እንዲሁም የተከተልናቸውን ጭምር በከፍተኛ የዘርፉ ባለሙያዎች በጥልቀት ሲመረምር ቆይቷል፡፡ ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም የፖሊሲ አማራጩንም ሰንቆ በ 6ኛው አገራዊ ምርጫ በተሻለ ከፍተኛ አማራጭነት ተወዳዳሪ ሆኖ በውድ ኢትዮጵያውያን ሊዳኝ ለውድድር ቀርቦ ይገኛል፡፡
እንደሚታወቀው የቀድሞ መንግስት በልማታዊ መንግስት ስም ሁሉን ልማት ልሥራ በሚል አውራ ፓርቲ ታጅቦ ያስመዘገበውን ውጤት ከሌሎች አገሮች ጋር በተነፃፃሪ ጥናት ቀምረን ወደ ኃላ መቅረታችንን አምነን ቀጥለናል፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ሞዴል በዘውጌ ፖለቲካ የተተበተበ በመሆኑ በአገራችን ተሞክሮ መንግስታዊ ሙሱናውን ብቻ የጉድ አድርጎት አልፎል፡፡ ሌላው በአፍሪካ አገሮች ውስጥ ተሞክሮ ውጤት ያላመጣው ምዕራባውያኑ ያልተጠቀሙበት የኢኮኖሚ ሞዴል ልቅ የሆነ የነፃ ገበያ ሞዴል ነው፡፡ ይህም ታዳጊ አገሮች ገበያቸውን ለትላልቅ ኩባንያዎች ክፍት እንዲያደርጉ የሚወተውት በመሆኑ በተለይ ለኪራይ ሰብሳቢ ከበርቴዎች መፈልፈል ምቹ ሁኔታን ፈጥሮል፡፡
በመሆኑም ባልደራስ ፓርቲ ለኢትዮጵያ የሚበጃት የኢኮኖሚ ሞዴል አግላይ የሆነ የዘውግ ፖለቲካን አስቀርቶ በሁሉ አቃፊ መተካት አለበት ብሎ አማራጭ የኢኮኖሚ ሞዴልን ለይቷል፡፡ አማራጭ ፖሊሲውን በጥልቀት እንዲሁም ወደፊት ተኮር (Forward looking) በማድረግ ቀርፆል፡፡ በገበያ ዲሲፕሊን የሚመራ በውድድር ላይ የተመሰረተ የገበያ ኢኮኖሚ ሞዴልን መከተል ለአገራችን ፍቱን መድሃኒት ነው ብሎ ቀምሮል፡፡ ለተግባራዊነቱ ሲልም በእውነት ለመትጋት ቆርጦል፡፡ እንደ ባልደራስ እምነት መንግስት ከሙስና፣ ካላስፈለጊ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዲሁም ከአድሎዊነት ፀድቶ የግል ዘርፉን በማበረታታት፣ በመደገፍ እና በመቆጣጠር የላቀ ሚናው ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገትን ሊያመጣ ይችላል የሚል ፅኑ እምነት አለው፡፡ በግል ባለሀብቶች የማይደፈሩ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ የሕግና የአሰራር ክፍተቶችን መድፈን፣ የመሬት አቅርቦትን በፍትሀዊ መንገድ እንዲዳረስ ማድረግ፣ ህግና ውለታዎችን ማስከበር፣ ከተማው በማስተር ፕላን መሰረት እንዲመራ ማድረግ፣ ጠንካራ የሕግ አውጪና አስፈፃሚ ተቋምን መገንባት ወዘተ የመንግስት ቁልፍ ተግባሮች ይሆናሉ፡፡ ለስኬቱ ምርጫችሁ ባልደራስ ይሁን::
ከትላንት ተምሮ ነገን ማለምለም የሚቻለው በእጃችን ላይ በሚገኝው ካርዳችን ብቻ ነው፡፡
ባልደራስ በዕውቀት፣ በብስለት እንዲሁም በእውነት እና ከእውነተኞች ጋር የሚያደርገው ትጋቱ ይለያል ስንል በምክናየት ነው!!!
የዘውትር ምኞቴ ለአገሬ እና ለመላ ዜጎቾ ቸር ቸሩን ያሰማ ነው!!!!
* * * * *
ኢንጂነር ዓለማየሁ ንጋቱ
በን/ስ/ላ/ክ/ከተማ ምርጫ ክልል 19 የባልደራስ የፓርላማ ዕጩ ተወዳዳሪ
ድል ለእውነተኛ ዴሞክራሲ