በህወሓትና በኦህዴድ/ብልፅግና መሃል ያለው የስልጣን ሽኩቻ እንጅ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት እንዳልሆነ ይታወቃል። በሶስተኛው ዙር ጦርነት ወቅት በኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት በኩል የህወሓትን የመዋጋት አቅም ሙሉ በሙሉ እንዲንኮታኮት ማድረግ መቻሉ በገሃድ ታይቷል። ይሁንና በሁለት ምክንያቶች ኦህዴድ/ብልጽግና በጦርነት ያገኘዉን ድል ያረጋገጠለትን የደቡብ አፍሪካ ስምምነት በናይሮቢ ስምምነት እየሻረዉ እንደሆነ የሰሞኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ኦህዴድ/ብልጽግና የህዉሃት ወታደራዊ/ፖለቲካዊ አደረጃጀት እንዳይከሰም የሚፈለገባቸዉ ምክንያቶች ሁለት እንደሆኑ የታመናል። አንደኛዉ ከላይ እንደተጠቀሰዉ ከህዉሃት ጋር በነገድ ፖለቲካ አመለካከታቸዉ እና በአማራ ጥላቻቸዉ አንድ መሆናቸዉ ሲሆን፣ ሁለተኛዉ ደግሞ የምዕራባውያን ደጓሚዎቹን በተለየም የአሜሪካንን ተፅእኖ ለመቋቋም አለመቻሉ ወይም አለመፈለጉ ነዉ።
ከህወሓት ጋር ከሚያመሳስለው የፀረ- አማራነት እና የፀረ ኢትዮጵያ ብሔርተኝነት አጀንዳ አንፃር አሁንም የኦህዴድ/ብልፅግና ፓርቲ ከህዉሃት ጋር በናይሮቢ የተፈራረመዉ ስምምነት የአማራ ማህበረስብ በህዉሃት በጉልበት የተቀማዉን ታሪካዊ አካባቢዎች ለህዉሃት አሳለፎ ለመስጠት ያለመ መሆኑ እየተስተዋለ ነዉ። በዚህ አካሄድ ሰላምን ለዘለቄታዉ ማስፈን አይቻልም። ዘላቂ ሰላምን ማስገኘት የሚቻለዉ የትግራይን ህዝብ ስብአዊ ክብር የሚያስጠብቅ፣ የትግራይ ህዝብ ከአጎራባች የአማራ፣የአፋር፣ የኤርትራ ወንድማዊ እና አህታዊ ማህበረሰቦች ጋር በሰላም እና በፍቅር አብሮ ለመኖር የሚያስችል፣የእርዳታ አቅርቦት ሳይስተጓጎል የሚቀርብበት፣ በተቻለ ፍጥነት መሰረታዊ አገልግሎቶች የሚመለሱበት ሁኔታ ሲፈጠር ነዉ። ይህ እዉን ሊሆን የሚችለዉ ደግሞ የኦህዴድ/ብልጽግና መንግስት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጀርባ ከህዉሃት ጋር የሚያደርገዉን የመሞዳሞድ ፖለቲካ ሲተውና የትግራይ ህዝብ የነገድ ፖለቲካ አራማጅ ከሆኑት ከኦህዴድ ብልጽግና እና ከህወሃት የፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ የሆኑ፣ የህውሃት የአማራ ጠልነት፣ የተስፋፊነት እና የዘረኝነት ልክፍት ያልታጣባችዉ፣ ህወሃትን የሚጸየፉ አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲቋቋሙ ሲደግፍ እና እንዲበረቱ ተግቶ መስራት ሲችል ነዉ።
“ድመት መንኩሳ ጠባዩዋን አትረሳ” እንደተሰኘዉ የሃገራችን ብሂል፣ ህወሃት የአሽባሪነት ተፈጥሮው ሊለቀዉ የማይችል እና ከውልደት አስከ መጃጀት ድረስ የተጣባዉ ባህሪው ነው፡፡ በድርድሩ ተገኘ የተባለው ውጤት ህወሃትን ትጥቁን በማስፈታት ብቻ ሳይወሰን፣ ማናቸዉንም አይነት ወታደራዊ/ፖለቲካዊ አደረጃጀቱን ማምከን የማይችል እና የማይፈለግ ከሆነ፣ ወደፊት አራተኛ ዙር ጦርነት ላለመቀስቀሱ ዋስትና ማግኘት አይቻልም። በሌላ በኩል ጦርነቱ በተኩስ አቁም ስምምነት ተቋጭቷል ቢባለም፣ወደፊት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀዉ ብሄራዊ ውይይት በጦርነቱ ለደረሰዉ ጥፋት የሽግግር ጊዜ ፍትህ እንዲሰጥ፣አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ፣ ተበዳዮች በተገቢዉ ሁኔታ እንዲካሱ ካላስቻለ፣ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሚቻል አይሆንም። በተጨማሪም በህገመንግስቱ ላይ ብሄራዊ ውይይት ተከፍቶ የህገ መንግስቱ ዋንኛ መገለጫ የሆነዉ የነገድ ፖለቲካን የሚመለከቱ አንቀጾች በሙሉ እንዲሻሩ ሳይደረግ፣ ይህ ፖለቲካ በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የፈለፈላቸዉ የማነነት እና የዉስጥ ወሰን ችግሮች ሳይፈቱ፣ የድርድሩም ሆነ የውይይቱ ውጤት ህወሃትን ከሽብርተኝነት ሊስት አስወጥቶ ህጋዊነትን በማላበስ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ተጫዋች እንዲሆን በማድረግ የሚቋጭ ከሆነ፣ ለሃገራችን ስር የሰደዱ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማስገኘት አይቻልም።
ድርድሩ ግልፅነትና አሳታፊነት የጎደለዉ በመሆኑ እጅግ ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት የደረሰባቸዉን የአማራ እና የአፋር ማህበረሰቦች ጥቅም ሳያማክልና ቁስላቸውን ሳያደርቅ ብሄራዊ መግባባት ብሎ ነገር የሚታሰብ አይሆንም፡፡
1. በድርድሩ የአማራና አፋር ማህበረሰቦችን ጥቅም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሂደቱ ተሳታፊ መሆን ሲገባቸዉ፣ይህ እንዲሆን አልተደረገም። ፓርቲያችን ባልደራስ ከህዝብ ጀርባ የተደረገ፣ ተጎጅ ማህበረሰቦችን ያላካተተ የጓዳ ድርድር እና ስምምነት ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም ያስገኛል የሚል እምነት የለዉም።
2. በደቡብ አፍሪካዉ ድርድር በኦህዴድ/ብልጽግና እና በህዉሃት መካከል ያለዉ ልዩነት ህገመንግስቱን መሰረት በማድረግ እንዲፈታ ስምምነት ላይ መደረሱ ይፋ ሁኗል። ይህ የስምምነቱ አንቀጽ ህወሃት ከህገመንግስቱ በፊት ከአማራዉ ታሪካዊ ይዞታዎች በሃይል ነጥቆ የያዛቸዉን ወልቃይት እና ራያን ወደ ትግራይ ክልል ማስመለሰን ግብ አድርጎ የተቀረጸ ነዉ። ይህ አንቀጽ ሌላ ዙር ግጭትና ጦርነት የሚቀሰቀስና ሃገራችን የሚያስፈልጋትን ሰላም እንዳታገኝ የሚያረጋት በመሆኑ፣ ባልደራስ ይህን የስምምነቱን አንቀጽ አጥብቆ ይቃወማል።
3. በአማራ ክልል በገለልተኛ አካላት የተጠና ጥናት በፌደራል መንግስት እና በአማራ ክልላዊ አስተዳደር ተደጋጋሚ የክተት ጥሪ መነሻነት የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት እና ሉአላዊነት አለመገሰስ፣ለህልውናዉ መጠበቅ እና ለሰብአዊ ክብሩ መከበር ሲል ባካሄደዉ ተጋድሎ ወደ 1 ትሪሊዬን የሚገመት የሀብት ውድመት እንደደረሰበት አመላክቷል። በስምምነቱ ዉስጥ ለዚህ ጉዳት ፍትሃዊ ተጠያቂነት ሊኖር እና ካሳ የሚከፈልበት ሁኔታ ሊካተት ሲገባ አልተካተተም። ይህን ስምምነት በኦህዴድ/ብልጽግና እና በህዉሃት መካከል ተቀባይነት እንዲያገኝ ያስገደዱት የምዕራቡ አለም እና በተለየም የአሜሪካ መንግስት በጦርነቱ ምክንያት ትግራይን ጨምሮ በአማራና እና በአፋር ክልሎች ለደረሰዉ እጅግ ግዙፍ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት ማካካሻ የሚሆን እርዳታ እንዲሰጡ በስምምነቱ ዉስጥ ማሻሻያ እንዲካተት ሊደረግ እንደሚገባ ፓርቲያችን ባልደራስ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
4. በጦርነቱ የህይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ የተዋጊ ቤተሰቦች፣ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸዉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የፋኖ፣ የአማራ ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ፣ ለአፋር ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ የደረሰባቸዉን ጉዳት የሚመጥን ካሳ እንዲመደብላቸው ፓርቲያችን ባልደራስ አበክሮ ያሳስባል፡፡
ባልደራስ ለእዉነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
አዲስ አበባ
ህዳር 5/2015 ዓ.ም