የሰለጠነ ራዕይ ለታላቋ ከተማችን
አዲስ አበባ በማንኛውም የድህነት መለኪያ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ በከተማችን 24 በመቶ ነዋሪዎች ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ። ታይቶ የማይታወቅ የሀብት ልዩነት ተፈጥሯል። እድሜያቸው ለስራ ከደረሰ 5 ወጣቶች አንዱ ፣ ከ3 ሴቶች አንዷ ሥራ የላቸውም።
በአዲስ አበባ በርካቶች የራሳቸው መጠለያ የላቸውም ወይም በወዳደቁ ቤቶች ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ንፁህ የመጠጥ ውሃና መፀዳጃ ቤት በቀላሉ አያገኙም፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርትና የጤና አጠባበቅም ለአብዛኛው ነዋሪ ብርቅ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ አቅቷቸዋል፡፡ ከ300 ሺህ በላይ የእለት ምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች አሉ፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን መመገብ ባለመቻላቸው በርካታ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ቀርተዋል፡፡ በትምህርት ቤት ውስጥም በርሃብና በጠኔ ራሳቸውን እስከመሳት የሚደርሱ ህፃናት ጥቂት አይደሉም፡፡
የከተማችን ነዋሪ የድህነት መጠን በየጊዜው እየተባባሰ ከመሄዱ የተነሳ ችግሩ ከጎጆ ወደ ጎዳና በስፋት እየወጣ ይገኛል። አዛውንቶች ድህነት ክብራቸውን አሸንፎ ጎዳና ላይ ለምጽዋት ጥሏቸዋል። ሕጻናት በለጋ እድሜያቸው ትምህርታቸውን ጥለው ማስቲካና ሲጋራ በየጎዳናው እየሸጡ ቤተሰባቸውን የመደጎም ሸክም ወድቆባቸዋል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የህዝብ ፓርቲ ነው። ባልደራስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስኬት የሚለካው ከሚፈጠሩ ሚሊዮኒየሮች ብዛት ወይም ከሚኮለኮሉ ሕንፃዎች ብዛት ሳይሆን የከተማዋ ሕዝብ ካለበት አስከፊ ድህነት በፍጥነት ተላቅቆ የተሻለ ኑሮ መኖሩን ሲያረጋግጥ ነው ብሎ ያምናል።
ስለሆነም የፓርቲያችን ተቀዳሚ ዓላማ የኢኮኖሚ ሥርዓቱን ለሁሉም በዕኩልነትና በፍትሃዊነት የሚያስተናግድ ማድረግ ነው፡፡ በወገኖቻችን ላይ የተንሰራፋውን ድህነት ለመቀነስ ፣ የሥራና የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የተረጋጋ የገበያ ሁኔታ እንዲፈጠርና የዋጋ ግሽበቱ የዜጎችን በልቶ የማደር አቅም እንዳይፈታተን የተለያዩ የቁጥጥርና ክትትል ሥራዎች ይሰራል።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የአዲስ አበባን ራስ ገዝነት በማረጋገጥና የከተማው የመሬት ግብይት በህግና በስርአት እንዲመራ በማድረግ የዋጋ ንረት እንዲቀንስና የኑሮ ውድነት ዝቅ እንዲል ይሰራል፡፡ አዲስ አበባን ለሁላችንም የምትመች ከተማ ያደርጋል።
(የባልደራስ የአዲስ አበባ ምርጫ ማኒፌስቶ)
ድል ለእውነተኛ ዴሞክራሲ
ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም