የማንነት ፖለቲካ ምንነትና አደጋዎቹ ባህላዊ ማንነትን ፖለቲከኛ ስናደርግ ያመረትናቸው ችግሮች(ገለታው ዘለቀ )
የማንነት ፖለቲካ ይህን ስያሜውን ያገኘውና በሚታይ መልክ ብቅ ያለው በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ነበር። በዚሁ ወቅት የሴቶች ንቅናቄ፣ የጥቁሮች ንቅናቄ፣ የአካለ ስንኩላን ንቅናቄዎች፣ የብሔር ንቅናቄ በስፋት የታዩበት ጊዜ ነበር። የማንነት ፖለቲካ ወደ አካዳሚክ ዲስኩር የገባውም በዚሁ በቅርቡ ነበር።
የማንነት ፖለቲካ ስንልም በእነዚህ ማንነቶች ላይ የሚሰራ የፖለቲካ ቤት ማለታችን ነው። ወደዚህ ፖለቲካ የሚገቡ ሃይሎች ደግሞ የፕራይሞርዳያሊዝም ፍልስፍና አማኞችና ኢንስትሩመንታሊስቶች ናቸው ማለት ነው።
የማንነት ፖለቲካ በቡድን የወል ግብር፣ የወል ስብእና፣ የወል እሴት፣ የወል ቋንቋ፣ የወል መልክ ላይ የሚቆም የፖለቲካ ስልጣን ሩጫ ሲሆን ከማንነት ፖለቲካ ውስጥ አንዱ ቅርንጫፍ ደግሞ የብሄር ፖለቲካ ነው።
ሃይማኖታዊ ፖለቲከኛነት ከማንነት ፖለቲካ ጋር የተያያዘ በመሆኑም ዓለም ያሳለፈችበትን የፖለቲካ ሕይወት ስናይ በተለይ በሃይማኖት ላይ የተመሠረተ የሕዝብ አስተዳደር ቀደምትነት ያለው ሆኖ እናያለን።
ወደ ብሔር ፖለቲካ ስንመጣ እንደሌሎቹ የማንነት ፖለቲካዎች ሁሉ ማዕከላዊ ጉዳዮች ይኖሩታል። ከነዚህም ውስጥ የእውቅና ጉዳይና የሶሺዮ ኢኮኖሚክ ጉዳይ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ገለታው ዘለቀ (የባልደራስ ፅህፈት ቤትና ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ) የማንነት ፖለቲካየማንነት ፖለቲካ የማንነት ፖለቲካ የማንነት ፖለቲካየማንነት ፖለቲካ ምንነትና አደጋዎቹ ባህላዊ ማንነትን ፖለቲከኛ ስናደርግ ያመረትናቸው ችግሮች ቁጥር 02 መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም. 11 በማንነት ፖለቲካ ውስጥ በተለይም የአሜሪካ የጥቁሮችን ንቅናቄ ስናይ፣ የሴቶችን ንቅናቄ ስናይ የእውቅና ጉዳይ ማዕከላዊውን ቦታ ይይዛል። በአንፃሩ የኢትዮጵያን የብሔር ተኮር ፖለቲካ ስናይ ከእውቅናም ባሻገር የሶሺዮ ኢኮኖሚክና ሌሎች እድሎችን በቀጥታም በህቡዕም ይዞ የመነሳት ፍላጎት ይታይበታል።
የማንነት ፖለቲካ የምንለው በእንግሊዘኛው Identity የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን የመለየት (separation) ፖለቲካ ማለት ነው። ራሳችንን ከሌላው የሚለየንን ነገር በማውጣት በዚያ ላይ የሚቆም ፖለቲካ ማለት ነው። አይደንትቲ የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል ምን ያህል በሚመጥን መልኩ ተተርጉሞ ማንነት እንደተባለ አላውቅም። የማንነት ፖለቲካ ከሚባል የመለያ ፖለቲካ ቢባል የተሻለ ይመስላል። ለማናቸውም ግን ፖለቲካችን በአይደንትቲ ላይ ከቆመ በልዩነት ላይ ቆመ ማለት ሲሆን በዚህ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ዜጎች ራሳቸውን ከሌላው በሚለያቸው ነገር ላይ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያደርግ ከባቢ ውስጥ እንገባለን። ቡድኖች ልዩነታቸውን ያጠብቃሉ። ልዩነት በጣም ሞቅ ያለ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው። ለምን ልዩነትን ይፈልገዋል? ለምን ያጎላዋል? ካልን አንዳንዱ በአሲምሌሽን ደንብሮ ሲሆን አንዳንዱ ደግሞ በብሄር ኢንተርፕሩነርስ እየተነዳ የሚሄድ ስለሆነ ነው። አሲምሌሽን ያስፈራው አካል ደንብሮ ጽንፍ ሄዶ የልዩነት ፖለቲካ አምጥቶ ራስን በራስ ማስተዳደር በየቤት ማደር እያለ ሲሰብክ እንዲሁም ደግሞ አንዳንድ የፖለቲካ ስልጣን ጥም ያላቸው ነገር ግን ተወዳድረው ማሸነፍ ሲያቅታቸው አቋራጭ የስልጣን መስመር አድርገው የሚያዩት ይህ የልዩነት ፖለቲካ በመሆኑ በዚያ ላይ ለመወጣጣት ስለሚጠቀሙበት ነው። ኢትዮጵያን መቃረጥ ይፈልጋሉ። በተለይ በብዙህ ሃገራት ውስጥ በኣንጻራዊነት የብሄር ፖለቲካን የሚፈልጉት ለሂቃን የሚነሱት ከሁለት ኣቅጣጫ ሲሆን በጣም ኣነስተኛ ብዛት ካለው ቡድንና ከፍተኛን ቁጥር ከሚይዘው የብሄር ኣባላት መካከል ሆኖ ይታያል። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ኣነስተኛ ቁጥር ያለውን ቡድን ወክለው ማእከላዊ መንግስትን ለመቆጣጠር የሚሹት የብሄር ኢንተርፕሩነርስ የሚኖራቸው ድብቅ ኣጀንዳ በብዙሃኑ ዋጋ በቀላሉ ቡድናችንን መለወጥ እንችላለን፣ ቡድናችንን ካሳመጽነው ብዙሃኑን ስለሚፈራና ለውጥን ስለሚፈራ ኣጥብቆ ይደግፈንና ረጅም ዘመን እንገዛለን የሚል ሲሆን ብዙ ከሆነው ብሄር የሚወጡ ኢንተርፕሩነርስ ደግሞ ይህን ብዛት ይዘው ስልጣን ይገባኛል ለማለት ትልቅ የመከራከሪያ ሎጂክ ስለሚመስላቸው ነው። ቁጥሩን ይዘው በዚህ ቁመት ልክ ይገባኛል እያሉ መቆየቱ ወደ ስልጣን ያመጣናል ብለው ስለሚያምኑ ከዚህ ብዙሃን የሚወጡ ኢንተርፕሩነርስ ይህንን ግዝፈት ለስልጣን መወጣጫ ሊጠቀሙበት ስለሚፈልጉ የብሄር ፖለቲካ እንዲጠፋ ኣይፈልጉም። ወደ ስልጣን ለመሄድ መንገድ ያቀላል ብለው ያምናሉ። ብዛቱን ይዘው ፍረዱን ይላሉ። ያ ኣነስተኛ ቁጥር ያለው ስልጣን ላይ ካለ ደግሞ በብዙው የምጠቀመው ኣለ ብሎ ስለሚያምን እንዲሁ የብሄር ፖለቲካው ይጠቅመኛል ብሎ ኣለቅም ይላል። በዚህ መሃል ቁጥራቸው በመሃል ያሉ ወደ ስልጣን ያልመጡት ብሄሮች ደግሞ ብሄራዊነት ይሻላል፣ በኣይዲዮሎጂ ላይ ተመስርተን ወደ ስልጣን እንሩጥ የሚል ነገርን ማራገብ ይመርጣሉ። በኣጠቃላይ የብሄር ፖለቲካ በዚያም በዚህም ከፍትህ ጥያቄ ይልቅ የጥቂት የስልጣን ጥመኞች ኣቋራጭ መንገድ ተደርጎ ስለሚወሰድ በጣም ተወጋዥ ያደርገዋል።
በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ላይ በማንነት ፖለቲካ ጐልተው የሚገለጹት የብሔር ፖለቲካና የሃይማኖት ፖለቲካ ሲሆኑ መንግሥታቸውን በሃይማኖት ማንነት ላይ ያቆሙ እንደ ሳውዲ አረቢያ ያሉ አገራት በቀደምትነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ አገሮች ሃይማኖታዊ በሆነ ሕግ የአገሮቻቸውን ሕገ-መንግሥት የሚያስተዳድሩ ሲሆን ብዙ አገራት ግን መንግሥትንና ሃይማኖትን፣ ዘርን ወይም ብሄርንና ፖለቲካን ነጥለው ወደ ዘመናዊ አስተዳደር ተሻግረው ይታያል። ወደ ብሔር ፖለቲካ ስንመጣ በአንዳንድ አገራት ለምሳሌ ሕንድና ኔፓል እንዲሁም በተወሰነ ደረጃ ኢንዶኔዥያ የሚታይ ሲሆን በብሔር ፖለቲካ ውስጥ ደፍሮና ጠልቆ የገባ እንደ ኢትዮጵያ የለም። ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት በተለየ መንገድ በጥልቀት የብሔርን ፖለቲካ የምታራምድ አገር ናት። የብሄር ፖለቲካዊ ማንነት እስከ መገንጠል የሚሄድባት አገር በዚህች ፕላኔት ላይ ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ ወደዚህ ፖለቲካ በመምጣት ያተረፈችውንና ያጣችውን እያነሳን ከመወያየታችን በፊት በአጠቃላይ የብሔር ፖለቲካ ምን ተፈጥሮ እንዳለው እንይ።
የብሔር ፖለቲካ የማንነት ፖለቲካ ነው ስንል በተለይ ብዙህ በሆኑ አገሮች ብሔሮች በባህላዊ ቡድነኝነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ድርጅቶችን ይመሠርቱና በዚህ ባህላዊ ማንነት ላይ ለዚህ ባህላዊ ማንነት ጥላ ሆነው የሚቆዩበት ጠገግ ነው። በርግጥ ፖለቲካ ምንጊዜም ቢሆን ከማንነት አይወጣም። ብሔራዊ አጀንዳ ይዞ የሚመሠረት የፖለቲካ ድርጅትም ያው ብሔራዊ ማንነትን እንደ ማንነት መገለጫው አድርጎ ነው የሚቆመው። ጥያቄው ፖለቲካ ከአካባቢ ማንነት ወደ ሃገራዊ ማንነት ማደግ አለበት ነው።
የብሔር ፖለቲካ ችግር የቡድንን ማንነት እንደማይለወጥ አልፋና ኦሜጋ ማየቱ ነው። ይሁን እንጂ ብዙ ብሔር ባለበት አገር አንድ ብሔር የራሱን ቡድን ልዩ ቋንቋ ሲናገር በማየቱ ለይቶ ቢያየውም ሁዋላ ወደ ውስጥ ማየት ሲጀምር ማይክሮ ማንነቶች መታየት መጀመራቸው አይቀርም። ከብሔር በታች ያሉ ጎሳ እንበለው ወይም ሌላ እንበለው ሌሎች አነስተኛ ክፍፍሎች መድመቅ ይጀምራሉ። የመልክዓ ምድር ክፍፍሎች፣ የአነጋገር ዘየዎች ሳይቀሩ ለብቻ ስንሆን ልዩነት ሆነው መውጣታቸው አይቀርም። በመሆኑም የልዩነትን የመጨረሻ ቅንጣት ፍለጋ ያንከራትተናል። ለዚህ ነው ዘመናዊ ዴሞክራሲ በሰው ልጆች ልዩነት የመጨረሻ ቅንጣት በሆነው የግለሰብ ልዩነት ላይ መመሠረት ይሻላል ብሎ የሚያምነው። በግለሰቦች መብት ላይ ያተኮረ ከዚያም ቡድኖችን የሚንከባከብ የፖለቲካ መሠረት መፍጠሩ መንግሥት የገዛ ህዝቡን ለመድረስና ለመርዳት ቀና መንገድ ይሆንለታል። እንደ ኢትዮጵያ ባለች አገር ውስጥ ልዩነትን እናንሳ ካልን ከብሔር በላይ ነገድ አለ። ከዚያም ደግሞ ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምስራቅ፣ ምእራብም ልዩነትን ሊሰሩልን ይችላሉ። ከፈለግን።
በሳይንሳዊ ክፍፍል የዘር ቆጠራ የናይሎ፣ የኩሽ፣ የሴምና የኦሞ ቋንቋ ተናጋሪዎች ነን። ወደ ታች ደግሞ በብሔር ከዚያም ጎሳ እያለ የደም ሃረግን ተከትሎ ይወርዳል። በብሔር ላይ የፖለቲካ ቤትን ለመሥራት የሚያስችል የፍልስፍና መሠረቱ ብዙ ግልጽ አይደለም። አንዳንዶቹ ብሔርን ከደም ሐረግ ጋር በማያያዝ ቡድኖች በብሔር ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ጨዋታ ቢያደርጉና ፌደራሊዝም በዚያ ቢቀረጽ አስተዳደሩ ትጋትንና ርኅራኄን ተግባቦትን ያመጣል ከሚል ይመስላል። ችግሩ ግን ማይክሮ ማንነቶች ማለቂያ ስለሌላቸው ይህ ፍልስፍና ትርጉም እንዲያጣ ያደርገዋል፡ : በአጠቃላይ ስናይ የብሄር ፖለቲካ በሁለት ይከፈል ይመስላል። አንደኛው ፕሪሞርዲያሊዝም ሲሆን ይህ ኣስተሳሰብ ብሄርን የደም ሃረግ ውጤት አድርጎ ያያል። የብሄሩን አባላት የሚያስተሳስረው ውጪያዊ የሆነው ባህልና ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የስነ ህይወት ትስስር ጉዳይ አለ ብሎ ያምናል። በዚህ ፍልስፍና ላይ የሚቆም የብሄር ፖለቲካ የፕሪሞርዲያሊዝም እምነት የሚከተል ነው ማለት ነው። በሌላ በኩል በብሄር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ባህልንና ቋንቋን እንደ ማንነት መገለጫ ኣይቶ በነዚህ ልዩነቶች ላይ የፖለቲካ ቤቱን ሰርቶ ነገር ግን ብሄርን የደም ትስስር ውጤት ኣድርጎ ኣያይም። የፕሪሞድሪያሊዝም ተቃራኒ የሆነው አስተሳሰብ ብሄርን ማህበራዊ ስሪት ወይም ሶሻሊ ኮንስትራክትድ ነው ብሎ ያምናል። ይሄ እምነት ብዙ የዓለም ምሁራንንና ፖለቲከኞችን ይገዛል። ይህ ማለት አንድ ሰው እናትና ኣባቱ ኦሮሞ ሆነው ትግራይ ውስጥ ተወልዶ ቢያድግና ትግርኛ ቢናገር የትግራይ ብሄር ይሆናል ማለት ነው። ማንነት የሚገጸው በዘር ሳይሆን በቋንቋና ባህል ነው። በዚህ አገባብ ብሄር የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳብ ነው ማለት ነው። በኢትዮጵያ ሁኔታ ስናይ ግን የብሄር ፖለቲካው የተመሰረተው በፕራይሞር ዳያሊዝም ኣስተሳሰብ ነው። ስለሆነም የብሄር ፖለቲካ ወይም ብሄር በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ጽንሰሃሳብ ሳይሆን የማይነካ የማይገሰስ የደም ሃረግ ጨዋታ ነው ማለት ነው።
ኢትዮጵያ እንግዲህ የፖለቲካ መሠረቶቿን ያደረገችው በዚህ ከላይና ከታች ልዩነትን ፖሊሲ የማንነት ፖለቲካ የማንነት ፖለቲካ 12 ቁጥር 02 መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በከላና በአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ ላይ በቆመ የፖለቲካ መሠረት ላይ ሲሆን ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ማለትም የብሔር ማንነትን ወደ ፖለቲካ ካስጠጉ አገሮች የምትለየው ከብሄር ፌደራሊዝሙ ባሻገር የብሄር ፖለቲካን በማስተናገዷ ነው። ለዚህ ነው እንደ ኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካን ጠልቆ የገባበት አገር የለም የሚያስብለን። ለምሳሌ ስዊዘርላንድን ብንወስድ አስተዳደሯ ለቋንቋ ትኩረት የሰጠ ሲሆን ነገር ግን የፌደራል ስርዓቷ በካንቶኖች የተከፋፈለ ነው። ስዊዘርላንድ ውስጥ አራት የቋንቋ ኮሚኒቲዎች ያሉ ሲሆን አስተዳደሯ ግን በሃያ ስድስት ካንቶኖች ወይም ስቴቶች የተዋቀረ ነው። ገዢ ፖለቲካዋም በብሄራዊ ማንነት ላይ የተመሰረተ በስዊዝ ማንነት ላይ የተመሰረተ ነው። በአንፃሩ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ማንነት ያላቸውን ፓርቲዎች ከውጪ በሪዘርቭ አስቀምጣ ዋናውን የፖለቲካ ሜዳ የያዙት የብሔር ፖርቲዎች ናቸው። በኢትዮጵያና በስዊዘርላንድ መካከል ያለው ዋና መሰረታዊ ልዩነት የስዊዘርላንድ ቡድኖች ለስዊዝነት የሰዋቸው ጉዳዮች አሉ። ከነዚህም ውስጥ ፖለቲካዊ ማንነትና ግዛት ናቸው። እነዚህን ሁለቱን ስዊዝ የወሰደችው ሲሆን ከዚያ በመለስ ያለውን ቋንቋና ባህልን ግን ቡድኖች ጠብቀው ይኖራሉ። ኢትዮጵያ በአንጻሩ ለኢትዮጵያዊነት ያስቀረችው ቁምነገር የለም። ፖለቲካዊ ማንነት፣ ግዛት፣ ታሪክ፣ ቋንቋ ፣ባህል ሁሉ በየቡድኑ የተያዙ ናቸው። ለኢትዮጵያዊነት እንደስዊዝ የሰዋነው ባለመኖሩ ነው ትልቁ ልዩነት።
ሕንድ አገር በርግጥ አንዳንድ በማንነት ላይ የቆሙ አካባቢያዊ ፓርቲዎች ቢኖሩም ሥልጣኑን የያዘው በብሔራዊ ማንነት ላይ የተመሠረተ ፓርቲ ነው። ጥቂት የሆኑት የብሔር ፓርቲዎች ከኢትዮጵያ በተቃራኒው ከውጪ በተጠባባቂነት የተቀመጡ ተፅዕኖ የሌላቸው ናቸው። እንዴውም ህንድ አሁን ከማጠፋቸው ራሱ ጊዜ እየጣላቸው ይሄዳል ብላ ለጊዜው ችላ ያለቻቸው ነው የሚመስሉት።
የኢትዮጵያ የብሄር ፖለቲካና ፌደራሊዝም ከውስጥ ወደ ውጭ ሲታይ
የብሄር ፖለቲካ ዓለማቀፋዊ ቢሆን ዓለም ምን ትሆናልች?
በአጠቃላይ ዓለም በተለይ የብሄር ፖለቲካን ከሰፈሯ አርቃ ነው የሚታየው። ርግጥ ነው በጥንት ጊዜ የፖለቲካ ርእዩት ባልዳበረበት ጊዜ ዓለም በጎሳና በነገድ አስተዳደር ስር ቆይታለች። ይሁን እንጂ የአሁኗ ዓለም ከጎሳ ይልቅ በርእዮት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካና ዴሞክራሲ ስለማረካት ይህንን ፖለቲካ ትታው ይታያል።
እስቲ እንደዚህ እናስብ። ከፍ ሲል እንዳልነው የብሄር ፖለቲካን አለማቀፍ እናድርገው እስቲ። በእንበል ገበያ ውስጥ እንሁንና የዓለም ሃገራት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ተመክሮ ወስደን ፖሊሲ በብሄር እንደራጅ ቢሉ ዓለም ምን ትሆናለች? ብለን እንጠይቅ። ዓለም የብሄር ፌደራል ስርዓትን ልከተል ብትል፣ በየብሄሯ በየቋንቋዋ ፖለቲከኛ መሆን ቢያምራት ዓለም ትፈርሳለች። ሃገሮች ሁሉ ይፈርሳሉ። የብሄር ፖለቲካ ዓለምን ያፈርሳል። ሩቅ ሳንሄድ አህጉራችንን አፍሪካን ስናይ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ አፍሪካውያን በሁለትና በሶስት የአፍሪካ ሃገር ተበትነው ይታያል። ለምሳሌ የኪንያሩዋንዳን ቋንቋ የሚናገሩ ማህበረሰቦች በሩዋንዳ፣ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና በኦጋንዳ ይገኛሉ። አፍሪካ እንደ አህጉር 3000 የሚገመቱ ብሄሮች ያሏት ሲሆን በአማካይ 56 ብሄር በአንድ የፖለቲካ ጠገግ ስር ሰፍሯል ማለት ነው። አፍሪካ በብሄር ፖለቲካ ውስጥ ብትገባ ወይም ወደየ ብሄሯ ማሸጋሸግ ብትፈልግ አህጉሪቱ ትፈርሳለች ብቻ ሳይሆን ፈርሳም አገር አትመሰርትም። የብሄር ፖለቲካን በዓለም አደባባይ ላይ ስናየው ዓለምን የሚያፈርስ ሲሆን በኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ በገዛ ቤታችን ውስጥ ያመጣብንንና ሊያመጣብን የሚችለውን ችግር ዝቅ ሲል እንመልከት። በዚህ ዘመን የብሄር ፖለቲካን እንከተል ስንል የሚከተሉትን ችግሮች እናተርፋለን። ሚዛናዊ ለመሆን ያሉትን ጥሩ ጎኖችም እንዘረዝራለን። በመጀመሪያ ከሚበዛው አሉታዊ ጎኑ እንነሳ።
አሉታዊ ጎኖቹን አንድ ሁለት እያልን ከማንሳታችን በፊት እስቲ አንድ ዝንባሌ የሚስብ ጥያቄ በአረማሞ እናንሳ። ጥያቄው ይህ ነው። የሰውን ልጅ ማንነቶቹን ሁሉ ፖለቲከኛ ስናደርግበት ሰው ምን ይሆናል? ምን ዓይነት ማህበር ይመሰርታል?
የሰውን ሁለንተናዊ ማንነት ፖለቲካዊ ስናደርግ ምን ችግር ይገጥመናል?
የሰው ልጅ የተደራራቢ ማንነቶች ውጤት ነው። ይህ ማንነቱ ግለሰቡን ከግለሰብ ማንነቱና ከቡድን ህይወቱ አንጻር ይገልጸዋል። በሃገር ጥላ ስር የሚሰፍሩ ዜጎች በጉልህ ከሚገልጿቸው የቡድን ማንነቶች መካከል ሃይማኖት፣ ብሄር፣ ጎሳ፣ መልክዓምድር የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። ታዲያ የሰው ልጅ ሃገራዊ ማህበር ሲመሰርት ይህንን ማንነቱን ሁሉ የፖለቲካ መደራጃ ቢያደርገው ምን ይሆናል? የሚለው ጥያቄ በጣም መሳጭ ነው። ዜጎችን ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ የተወለዱበትን አካባቢ፣ እሴቶቻቸውን ሁሉ ፖለቲከኛ ብናደርግባቸው መጀመሪያ የምናጠፋው ይህንን ማንነታቸውን ራሱን ነው። ከዚያ ሲለጥቅ ደግሞ ወደ ጎን ከሌሎች ማንነቶች ጋር ግጭትን እንዲያመርቱ እናደርጋቸዋለን:: ከዚያ ሲለጥቅ ደግሞ ለዋናው ማህበራቸው የጋራ ማንነት እናሳጣለን:: ከዚያ ሲለጥቅ ደግሞ የዋናውን የህብረት ቤታቸውን ወይም የሃገራቸውን የፖለቲካ ጨዋታ ሴማ እናሳጣዋለን። አንድ ሃገር ስብስብ የተባለን ሁሉ ፖለቲከኛ ማድረግ ቢፈልግና ብሄርን፣ ሃይማኖትን፣ ብሄራዊ ማንነትን፣ ጂኦግራፊን፣ ነገድን ሁሉ ለፖለቲካ ቤት መስሪያነት ቢፈቅድ ያ ሃገር የሚፈጥረው የፖለቲካ መስመር ምርጫውን ያበላሻል። ሃገራችን ኢትዮጵያ ከሰውነቶቻችን መሃል ፖለቲከኛ እንዳይሆን የከለከለችው ሃይማኖታችንን ብቻ ነው። በሃይማኖት ላይ መደራጀትን በህገ መንግስት ከልክላለች። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ኣንቀጽ 11 ይህንን ይደነግጋል። ከዚህ ውጭ ግን ብሄርን፣ መልክዓምድርን፣ ብሄራዊ ማንነትን ወይም ኢትዮጵያዊነትን፣ ነገድን፣ ጥምረትን፣ ሃሳብን ሁሉ መሰረት ኣድርጎ ፖለቲካ መጫወት ይቻላል። ይህ ደግሞ እጅግ ብዙውን የሰውን ማንነት ፖለቲከኛ ከማድረጉም በላይ በዚህ ዓይነት ኣሰላለፍ ሃገራዊ ራእይ ማየትና ሃገራዊ ምርጫ ማሰብ ለጋራ ቤት ኣብሮ መስራት የማይታሰብ ነው። ሃገር የሚባለውን ትልቅ ማህበር ስንፈጥር ከሚኖሩት ስብስቦች መካከል ፖለቲከኛ የምናደርገውን መምረጥ ኣለብን። ዓለም ካሉት ስብስቦች መካከል ብሄራዊ ማንነትን ለፖለቲካ መደራጃነት ይፈቅድና ሌላውን ማለትም በብሄር መደራጀትን፣ በሃይማኖት መደራጀትን፣ በመልክዓምድር መደራጀትን ወዘተ ይከለክላል። ኢትዮጵያ ብዙውን ማንነታችንን ፖለቲሳይዝ ማድረጓ ያመጣብን ችግር ሃገራችን ወደ መድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዳትሻገር ከማድረጉም በላይ ለምርጫ እንዳንመች ለቅንጅት እንዳንመች ኣድርጎናል። የሰውን ሁለንተና ፖለቲከኛ ካደረግንበት የምናጋጨው ነገር ብዙ ነው። ፖለቲካ በተፈጥሮው ግጭትን የያዘ ነው። በፖሊሲ መጋጨት፣ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ማለት በፖለቲካ ውስጥ ጤነኛ ነገር ነው። አንዱ ፓርቲ ከሌላው የተሻለ ፖሊሲ እንዳለው እያሳየ ሌላውን እያኮሰሰ በማሳየት ነው ለምርጫ የሚሮጠው። በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ ይህ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ጨዋታ መልካም ነገር ነው። የፖለቲካ ወጉም ይሄ ነው። ነገር ግን ይህ የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ጨዋታ ወደ ብሄር ማንነት ሲሄድና ብሄርን ፖለቲከኛ ስናደርግ በቀጥታ ግጭቶችን ወደ ብሄር እናወርዳለን ማለት ነው። ብሄር ፖለቲከኛ ሲሆን በብሄሮች መካከል እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ግጭትን እናመጣለን ማለት ነው። ይህ ችግር በጣም ኣደገኛ የሆነ ችግር ስለሚያመጣ ማህበራችንን ይበጠብጣል። ስለዚህ ነው ማንነትን ፖለቲከኛ ስናደርግ የማህበራችንን መንጋ ይበትናል የሚያስብለን። ከማንነቶች መካከል ብሄራዊ ማንነትን ለፖለቲካ መደራጃነት መርጦ ሌሎቹን ማንነቶች በራሳችሁ ምህዋር ላይ ዙሩ ማለት ዴሞክራሲያዊና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መርህ ነው። እኛ በአንጻሩ ማንነትን ሁሉ ለፖለቲካ መደራጃነት ስንፈቅድ የወጣልን ዴሞክራቶች የሆንን መስሎን ከሆነ ተሳስተናል። ስለዚህ ማንነቶችን ሁሉ ፖለቲከኛ ከማድረግ መውጣት ያስፈልጋል።