የሃሳብ ልዩነት የችግር መፍትሔ ወይስ ምንጭ?
በህይወቴ ይችን ስንክሳር ዓለም ተቀላቅየ እዚህ ደረጃ እስከ ደረስኩበት ጊዜ ድረስ ለቅጥር አሻራ ለመነሳት ካልሆነ በቀር አንድም ቀን የፖሊስ ጣብያን ረግጨ አላውቅም፡፡ ለአሻራ በሄድኩበት ቀንም መለዮ ለባሽ አይቼ የተንቀጠቀጥኩበት ጊዜ አልነበረም፡፡ አሁን ግን የተለየ ነው፡፡ በፌደራል መንግሥት ወኽኒ ቤቶች ስር ውስጥ የሚገኘው ቃሊቲ ወኽኒ ቤት ስደርስና ወደ ውስጥ ገብቼ ልፈተሸ ስዘጋጅ የነበረኝ የፍርሃት ስሜት በቃላት የሚገለፅ አይደለም፡፡
የፍርሃቴ ምንጭ ደግሞ ልጠይቅ የሄድኩበት እስረኛ በቅርብ የማውቃት እና ሁሌም የሞራል ጀነሬተር የምትሆነኝ አስካለች ደምለው የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ኮከብ አባል ነች፡፡ ስለዚህ የባልደራስ አባል መሆን ብቻውን እንደ ወንጀል በሚቆጠርበት ሀገር የባልደራስ አባልን መጠየቅ ቢያስፈራ ኤይደንቅም ምክንያቱም ከግዙፉ እስክንድር ነጋ ትከሻ ላይ ያረፈው የፖሊስ ጡንቻ እኔን አንድ ተራ ሰው ሊፈጨኝ እምደሚችል እጠረጥር ነበርና፡፡ የታላቁን እስክንድር ነጋ ግዙፍነት የገለፅኩት በአካል ሳይሆን በአስተሳሰብ እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እንደ ምንም ፍተሻየን በሰላም ጨርሼ እራሴን እንዳረጋጋም ፖሊሶቹ እገዛ አድረገውልኝ ወደ ውስጥ ገብቼ ወዳጄን ሳስጠራ ዘወትር ከፊቷ ላይ ፈገግታ የማይለያት አስካል ብረድስት ላይ ተጥዶ እንደሚፈላ ውሃ እየተፍለቀለቀች ብቅ አለች፡፡ ለረዥም ጊዜ ተለያይተን ነበርና ሞቅ ያለ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ አሁን ስላለው ሁኔታና ለእስር ያበቃትን ሁኔታ ስጠይቃት የሰጠችን ምላሽ አንድም አሳዝኖኛል፡፡ አንድም አስቆኛል፡፡ ሳቁም በሀዘን የተለወሰ ቢሆንም የጥርስ ደሞ እንደሚሉት አበው፡፡ በተመስጦ ውስጥ ሁና ያጫወተችኝን ቃል በቃል እንደሚከተለው አቀርበዋል፡፡
አስካለች ደምለው ትባላለች ከአባቷ ከአቶ ደምለው ደሳለኝ እና ከእናቷ ዘውዱዓለም እንቢ አለ በ1983 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ቁስቋም በሚባል አካባቢ ተወለደች፡፡ አስካለች ለቤተሰብ 4ኛ ልጅ ስትሆን እትብቷ በተቀበረበት አካባቢ ከእድሜ እኩዮቹ ጋር እንደማንኛውም የአዲስ አበባ ህበረተሰብ ልጅ በእንክብካቤ እና በፍቅር በቤተሰብ እንክብካቤ አድጋለች፡፡ እድሜዋ ለት/ት ሲደረስ ከኩዮቿ ጋር በመሆን ቁስቋም ጣይቱ ብጡል የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት አብርሃ ወፅብሀ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት አምሀ ደስታ እና ኮተቤ ወንድ ይራድ ት/ቤት በመዘዋወር ስትማር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በመነን የካቲት 12 ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቃለች፡፡ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት በዲፕሎማ አካውንቲግ የተማረች ሲሆን በጌጅ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ደግሞ ዲግሪዋን በአካውንቲግ ሰርታለች፡፡ ወጣት አስካል ደምለው በወጣትነት ዘመኗ ብዙም ባትሄድበትም ከማህበራዊ ኃላፊነቷ ባሻገር የወጣትነት ጊዜዋን በስፖርቱ ዘርፍ እንጦጦ ተራራ ስፓርት ክበብ አትሌቲክስ ሰርታለች፡፡ በኪነ – ጥበብ ዘርፍ ደግሞ የኮሌጅ ላይፍ በሚል ርዕስ የወጣው ፊልም ላይ ታምራዊ የትወና ብቃቷን አሳይታለች፡፡ በይበልጥ በዚህ ፊልም ትታወቅ እንጅ በርካታ የተለያዩ ፊልሞችን በመሥራት ለዘርፉ የራሷን አሻራ አኑራለች፡፡
ወደ ፓለቲካው እንዴት መጣሽ ተከታይ ጥያቄዬ ነበር? በምኖርበት ሀገር ኢትዮጵያ በተለይ አዲስ አበባ ሕዝብ ላይ ላልፋት 27 ዓመታት ውስጥ የነበረው በደል እና ስቃይ እንዲሁም ጭቆናን ለመረዳት በጥበብ ሙያ ውስጥ ከመኖሬም በላይ የአዲስ አበባ ሕዝብ የችግር /የጭቆና/ ጅራፍ እኔንም ጨምሮ ይገርፈኝ ነበርና ለመረዳት ቀላል ነበር፡፡ እናም ያንን ዘግናኝ ሥርዓት ለመገርሰስ እና ለመጣል ሀሳባቸው ከሃሳቤ ጋር ቅርብ ከሆኑ አካላት ጋር እንደማንኛውም ተራማጅ ወጣት ሲብሰከሰክ ነበር፡፡
በመሥሪያ ቤትም ሆነ በመኖሪያ አካባቢና ከሚቀርቡኝ አካላት ጋር ይህ የጨለማ ዘመን ተገፎ የብርሃን ዘመን የሚመጣበትን ጊዜ በተስፋ እንጠብቅ ነበር፡፡
ሆኖም የፈራነው ደረሶ ብናየውም በማይታመን መልኩ ከጫፍ እስከ ጫፍ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር በሚል ለይስሙላ መፈክር የተታለለው ሕዝብ ግልብጥ ብሎ በቄሮ እና በፋኖ ደም እና አጥንት የተገኘን ለውጥ የለውጥ መሪ ብለው የሕዝብን ለውጥ በመንጠቅ ወደፊት ሲመጡ ድጋፍን ሲያሳይ እኔም ከህዝቡ ጋር የዚህ ሴራ ሰለባ ነበርኩ፡፡ ለውጥ የመጣ መስሎኝም ለተወሰነ ጊዜ ከእነ ሙሉ ድጋፊ አምኘ ተቀበልኩት፡፡ እየቆየሁ ስሄድ ግን ለውጡ በማር የተለወሰ መርዝ መሆኑን ለመረዳት የፖለቲካ ጠበብት መሆንን ወይም አምላክ መሆንን አይጠይቅም ምክንያቱም ማንም ነገሮችን ማስተዋል የሚችል ሰው በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ ለዚህና መሰል ነገሮች ወጣት አስካለች ደምለው አስከትላ ስትናገር በጋሞና በሲዳሞ ወጣቶች እና ህዝቦች ላይ የተሠራው ፓለቲካዊ ሴራ የደቡብ ህዝቦች መፈናቀልና ጭፍጨፋ የአማራ ህዝቦች ጭፍጨፋና ጭቆና ከ27 ዓመት በ2 ዓመት ውስጥ ጎልቶ ሲታየኝ፤ ተረኛ ነን ባዮች ቆንጨራ፣ ሜጫ እና ዱላ ይዘው ሲወጡ መንግሥታዊ ሽፋን ሲሰጣቸው ባዶ እጃቸውን ይዘው ለሚወጡት የአዲስ አበባ ልጆች እና ሌሎች ከብሄሮች ግን ሁከት ፈጣሪዎች እየተባሉ ወደ ጦላይ መወርወርን እያየ ፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ ንብረት በጠራራ ፀሀይ ሲዘረፍ እያየ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ሲካሄድ እያየ ሕገ ወጥ ስም ብሄርን ብቻ መሠረት ያደረገ ሰዎች ለዓመታት ላባቸውን ጠብ አድርገው ያፈሩት ሀብታቸውን በለሊት እንደ ሽፋታ ሲያወድሙባቸው፣ ቅርስ ሲፈርስና ሲወድም፣ የሀገር ታሪክ ሲጠለሽና ሲዘቅጥ እያየ፣ በግንባታና በልማት ሰበብ የሀገር ሃብት ያለምንም ህጋዊ ጨረታ የሕዝብ ሀብት ሲዘረፍ እያየ፣ ለውጥ አለ የሚል አካል ካለ አንድም የተረኝነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ነው በሌላ መንገድ ደግሞ ሳይካትሪስት የሚያስፈልገው መሆን አለበት፡፡
ሁላችንም ቢሆን ከዚህ በኋላ በሃይ ባይ በጦርነት ሳይሆን የሕዝብ ቅቡልነት ማግኘት የሚቻለው በሃሳብ የበላይነት ብቻ ነው፡፡ ማንኛውም አካል ሀሳቡን ይዞ መጥቶ በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ ሃሳብን በመሸጥ ብቻ የሕዝብን ስልጣን መረከብ ይቻላል፡፡ የሚል ጣፋጭ እሳቤውን አራምዶ የሕዝብን ስሜት ከተቆጣጠረ በኋላ ብርቱ፣ ምጡቅ እና ባለተራማጅ ራዕይው በታላቁ እስክንድር ነጋ ለሰላም፣ ለፍትህ፣ ለእድገት፣ ለእውነተኛ ዲሞክራሲና ለሕዝብ ደህንነት ዘላቂ የመፍትሄ ሀሳቡን በማቅረብ ህዝቡን በቀላሉ መማረኩን ሲረዳና አየር ላይ ተንሳፎ እንደሚቀር ሲገነዘብ ጦር እንማዘዛለን በማለት የሀሳብ ልዕልናን በቅፅፈት ወደ ጦርነት የሚቀይርን አካልን የለውጥ መሪ ነው የሚል ካለ፡፡
ለ27 ዓመት ሙሉ ጭቆና ስርዓትን ያዳበረ እና አሁንም በጭቆና ቀንበር ለመማቀቅ ራሱን ያዘጋጀ አካል መሆን አለበት፡፡ የዚህን መንግሥት ችግር በቀላሉ መዘርዘር አይቻልም አውሎ ያሳድራልና እንተወው ከመታሰርሽ በፊት ትግል ላይ በነበርሽበት ሰዓት የገጠመሽ ክስተት ካለ? ሁለተኛው ጥያቄዬ ነበር፡፡
ተቀጥሬ የምሠራው በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ለዘጠኝ ዓመት ያህል አገልግያለሁ እዚያ በምሠራበት ወቅት አንድ ለአምስት የሚባል ክንውን አለ፡፡ በዚህም መሠረት ማን የብልፅግና አባል ነው? ማን አይደለም ወይም ተቃዋሚ ነው የሚሉትን ጥያቄዎች በቀላሉ መመለስ የሚቻልበት የጥርነፋ ስልት ነው፡፡ በዚህ የጥርነፋ ስልት እኔ የተቃዋሚ አባል መሆኔ ታወቀ፡፡ ለዛውም ለመንግሥት የራስ ምታት ለሆነው ባልደራስ፡፡
ራስምታት ስልህ መንግሥት ባልደራስን ስለሚፈራው ነው፡፡ ምክንያቱም በጉልበት ካልሆነ በሃሳብ እና በፖለቲካ ገበያ ባልደራስን መቋቋም አይችልም፡፡ እያደረገ ያለውም ይህን ስለሆነ ወደ ዋናው ነጥቤ ስመለስ ከዛ በኋላ ሁልጊዜም ቢሆን እኔ ላይ ክትትል ማድረግ ጀመሩ፡፡ ሰብሰብ ብለን በተቀመጥንበት እኔን ለማሸማቀቅ ስለ እስክንድር መጥፎነት ማውራት፣ ስለ ባልደራስ አሉታዊ ነገር መናገር፡፡ በዚህ እንደማልበገርላቸው ሲረዱ ደግሞ በጥቅማጥቅም መጡብኝ፡፡ በደረጃ አንድገት፣ በስልጣን፣ በቤት ወዘተ ይህም አልሆነ አለ፡፡ በቁርጥ ከዚህ እንቅስቃሴ እንዳቆም ጥብቅ ትዛዝ ተሰጠኝ፡፡ ካልሆነ ግን የመንግሥት ስራዬን እንደምለቅ በግልፅ ቋንቋ ተነገረኝ፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በኮቴዬ ልክ በደህንነት ይከታተሉኝ ነበር፣ ሻይ ቡና ስንል በሰርቢስ እቤቴ ድረስ በመከተል፡፡ በGPS በመታገዝ ቤቴ ድረስ እየመጡ ለማፈን ሙከራ አድርገዋል፡፡ ስልኬን ጠልፈዋል፡፡ አሁንም እስር ቤት ውስጥ እያለሁ የእጅ ስልኬን ኢንተርኔትም ሆነ የስልክ ቁጥሩን እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ቀድሞ ሲል በስልኬ እየተደወለ ዛቻ እና ማስፈሪያ ይደርስብኝ ነበር፡፡ ፎቅ ላይ በመሆን ፎቶ ያነሱኛል፡፡ ብቻ ብዙ ነው፡፡
እስር ቤት እያለሽ እጅሽ ከተያዘበት እስካሁን ድረስ ያለው አያያዝሽ ምን ይመስላል?
ማዕከላዊ እያለሁ ከቆጠራ በኋላ በመስኮት ለምስክርነት ያስጠኑኝ ነበር፡፡ አስጠንተውኛል የሚልም ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ቤተሰብ ሊጠይቀኝ ሲመጣ ይመልሱብኛል እዚህ ቃሊቲ እያለሁም ቢሆን ለዚህ ሰለባ ነኝ ከዚህ የጎላ ነገር
የለም፡፡ ማዕከላዊ እያለሽ የምርመራ ሂደትሽ ይዘት ምን ይመስላል ከምን አውድ ነበር የሚመረምሩሽ? ምርመራው እጅግ ያስቃል፡፡ ምርመራውን ከምነግርህ የክሱን ይዘት እና አውድ ብነግርህ ይቀላል፡፡ ምክንያቱም ምርመራውም ከክሱ ስለማይሻል፡፡ ምን መሰለህ የተከሰስኩት አንደኛ የሚኒሊክን ሀውልት እንዳይፈርስ ተከላክሰሻል፣ ሁለተኛ የአማራን እና የጋሞን ተወላጆችን አንድ በማድረግ አደራጅተሻል፣ ሶስተኛ የጦር ኃይሎችን ወጣቶች አደራጅተሽ በቄሮ ላይ ጥቃት አድረሰሻል የሚል ነው፡፡ እንግዲህ ተመልከት አላደረኩም እንጅ ባደርገው ጥፋቱን መከላከል ጥፋትን ማዳን ወንጀል የሚሆነበት ሀገር ሕዝብን አንድ ማደረግ፣ ሕዝብን ወደ አንድ ማዋሀድ፣ ልዮነትን ማጥበብ መተባበርን እና መደጋገፍን ማጎልበት እንደወንጀል ከተቆጠረ የኢትዮጵ ሕዝብ ይቅጣኝ፡፡ ጦር ኃይሎች ለተባለው እውነቱንም ሆነ ውሸቱን ድፍን የኢትዮጵ ሕዝብ ባይስተውም ዳኝነቱን ግን ለፈጣሪ እና ለእግዚአብሄር በታች ድርጊቱ ተፈፀመበት የተባለው የአካባቢው ሕዝብ ይፍረደኝ፡፡
አሁን እዚህ ድርጊት ውስጥ መግባትሽ እና ለዚህ ችግር ለመዳረግሽ ትፀፀቻለሽ?
አልፀፀትም፤ ምክንያቱም ምንም አይነት ወንጀልም ሆነ ጥፋት አልሠራሁም የታሠርኩበት ስሰርቅ፣ ንብረት ሳወድም፣ የሰው ነብስ ሳጠፋ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ሳጋጭ፣ የሰው ነፍስ ሳጠፋ አይደለም፡፡ እኔ የታሰርኩት ለምን የጭቁኖች ልሳን ሆንሽ ለምን ተጨቋኞችን አፅናናሽ ከባርነት ቀንበር እንዲላቀቁ ለምን አነቃሽ፣ ለመብት እንዲታገሉ ለምን ሰራሽና፣ ለግፈኞቹ እንደፈለግን እንዳንሆን ለምን እንቅፋት ሆንሽን ተብየ ነው፡፡ እና አልፀፀትም፡፡ እኔ የጀግና ልጅ ነኝ ጀግንነቴን ደግሞ የምገልፀው እንደነሱ ሰው በመግደል በማረድ ሀብት ንብረት በማውደምና በመዝረፍ አይደለም፡፡ ለጭቁኖች፣ ለተከፋ፣ ላዘኑ፣ የሰላም እጦት ለአንገበገባቸው ፈጥኖ ደራሽ በመሆን እንጅ፡፡ ተስፋቸው ተሟጦ በጨለማ ውስጥ ለሚዳክሩ የተስፋ ብርሃን በመሆን እንጂ፡፡ በመንፈሴም ሆነ በስነልቦናየ እንዲህ አይነት አኩሪ የሆነ መንፈስ ሠረፆ እንዴት እፀፀታለሁ፡፡ በፍፁም አልፀፀትም፡፡
ህዝቡ እንዲረዳሽ የምትፈልጊው ነገር ካለ?
የታሠርነው ለሕዝብ ደራሽ ናችሁ ተብለን ነው እና የፍትህ ሂደቱን የኢትዮጵ ሕዝብ አመዛዝኖ እንዲፈርደን እንፈልጋለን ፍትህን የምናገኘው ከፈጣሪ በታች በሕዝብ ነውና፡፡ ሌላ አሁን ሀገሪቱ ያለችበትን ምስቅልቅል ሁኔታ ሁሉም ሕዝብ ይገነዘባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህ ሁሉ ደግሞ ዋናው ተጠያቂ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ነው፡፡ ከዚህ ችግር ለመውጣት ደግሞ ወጣቱ ትውልድ በተረጋጋና በሠከነ መንገድ ጠንክሮ መሥራት አለበት፡፡ የዚህ ትውልድ ባላደራዎች ነን እና የጥንት አያት ቅድመአያቶቻችንና አባቶቻችን አንድነቷንና ክብሯን አስጠብቀው እንዳቆዩን በሀገር በመጤ ብሄርተኝነትና ዘረኝነት መንፈስ ልትበታትን ጫፍ ላይ የደረሰች ሀገር ወደነበረችበት የከፍታ ልዕልና መልሰን ለቀጣዩ ትውልድ እናስረክብ ዘንድ ያለምንም ብሄር እና ኃማኖት ልዩነት በመርህ እና በእውነት ላይ የተመሠረተውን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ታዛ ስር በመጠለል ይህን ዘረኛ እና ፅንፈኛ ጨቋኝ አገዛዝ ከስሩ ለመጣል ቆርጦ መታገል ካለበት ድል ለእውነተኛ ዲሞክራሲ!!!