ዘር ማጥፋት ወይስ ሰብዓዊ ፍጡር ላይ የተፈጸመ ወንጀል?
እስክንድር ነጋ፣ የህሊና እስረኛ፤ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ
ከሁሉ አስቀድሞ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሀጫሉ ግድያ በኋላ በኦሮሚያ ክልል ስለተከሰተው ሁኔታ ያወጣው ሪፖርት ምሥጋና ይገባዋል፡፡ የሚንቀሳቀስበትን አውድ ግምት ውስጥ እናስገባለት፡፡ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ በጐ እሴቶች ያሏት ሀገር መሆኗ የሚካድ ባይሆንም፣ በሰብዓዊ መብት አክባሪነታቸው ከሚወደሱ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ግን አልታደለችም፡፡ በፍጥነት የሚበቅልና የሚለመልም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ገና እንደ አዲስ ባህል የሚበቅልባት ሀገር ናት፡፡ በዚያ ላይ፣ ኮሚሽኑ መንግሥታዊ ተቋም ነው፡፡ መንግሥትና ገዢ ፓርቲ እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች በተጣበቁበት ሥርዓት መፈናፈኛ የለውም፡፡
ችግሩ በዚህ አያበቃም፡፡ ዕድሜ አንድ ትውልድን ለገደለው የሕወሓት የትምህርት ፖሊሲ (ነፍሳቸውን ይማረውና ፕሮፌሰር አሥራት የፖሊሲውን አስፈጻሚ “ዮዲት / ጉዲት” ብለዋት እንደነበር አስታወሳለሁ፤) ኮሚሽኑ እንደ ተቋም ብቁ የሆነ የሰው ኃይል ችግር አለበት፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ አናት ላይ ያሉት ኃላፊ ሳይቀሩ በሪፖርቶች የአርትኦት ሥራ ተጠምደው እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡
በኮምሽኑ አናት ላይ ስላሉት ሰው ካነሳሁ አይቀር፣ አንድ ሁለት ነገር ልበል፡፡ እንዲያው በጥቅሉ፣ “ከማውቃቸው ሰዎች መካከል፣ ይበልጥ እንዳውቃቸው ከተመኘኋቸው ሰዎች ተርታ ናቸው” ብዬ ልጀምር፡፡ እንደዚህ ብዬ የምናገርላቸው ሰዎች በጣም ትንሽ ናቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጠነኛ ርቀት ልታዘባቸው የቻልኩት፣ በ1998 ዓ.ም በማዕከላዊ እስር ቤት እኔም እሳቸውም ከቅንጅት አመራሮች ጋር ተከሰን በምርመራ ላይ ሳለን ነበር፡፡
ማዕከላዊ እንደገባሁ (የያዙኝ ፌዴራል ፖሊሶችና ደህንነቶች እኔንም ባለቤቴንም ከደበደቡ በኋላ) በተለይ “ሸራተን” በሚባለውና በመደዳ በጥርብ ድንጋይ በተሠሩ ቤቶች አንድ ክፍል ውስጥ ለብቻዬ ነበር የታሰርኩት፡፡ በሌሎቹ ክፍሎች ሦስትም አራትም፣ አንዳንዴም ከዚያ በላይ ሆነው ታስረዋል፡፡ በሮች በሙሉ ተዘግተው ነበር የሚውሉት፡፡ ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ በሮቹ ሁሉ ቀን ቀን ተከፍተው እስረኞች አብረው መዋል ሲጀምሩ፣ ከሌሎቹ ጋር ተቀላቅዬ አሁን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር የሆኑትን የዳንኤል በቀለን የዕለት ተዕለት ውሎ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡
በዚያን ጊዜ የአብዛኞቹ እስረኞች ፀባይ ጥሩ ነበር፡፡ ግን እንደዚያም ሆኖ፣ ዓመል ሆኖበት የሚያስቸግር አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ በርቀት አክብረናቸው በቅርበት ስናውቃቸው ያፈርንላቸው ሰዎች አጋጥመውናል፡፡ በዚያ ልክም አንዳንድ ላቅ ያለ ስብዕና ያላቸውንም አይተናል፡፡ ብዙዎቻችን ዳንኤል በቀለን በዚህኛው ምድብ ውስጥ አግኝተናቸዋል፡፡ ትንሽ ትልቅ ሳየሉ፣ ሁሉንም በትህትና ዝቅ ብለው አገልግለው አስደምመውናል፡፡ በተመሠረተባቸው ክስ የሀሰት ምስክሮች ሲቀርቡባቸው ደግሞ፣ የሚደነቅ የሙያ ብቃታቸውን አሳይተውናል (የሕግ ሙሁር ናቸው)፡፡ ይህን ሁሉ ደማምሬ፣ ኮሚሽኑ እስካሁን ከነበሩት መሪዎች የተሻለ መሪ አግኝቷል ለማለት አልቸገርም፡፡
ይህን ስል ግን፣ ፍጹም ናቸው ለማለት አይደለም፤ ፍጹም አምላክ ብቻ ነውና፡፡ ለምሳሌ፣ አሁን ያላቸውን ኃላፊነት ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ፣ ብዙዎቻችንን እስከዛሬ የሚከነክነንን ነገር ላንሳ፡፡
እኔና ዳንኤል ተካተንበት የነበረው ክስ፣ “የእነ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ፋይል” የሚል ስያሜ ነበረው፡፡ በዚህ ክስ ዳንኤልና እኔን ጨምሮ 39 ተከሳሾች በቅንጅት ከፍተኛ አመራር ሰጪነት ተመድበናል፡፡ ከእነዚህ መካከል ሰላሳ ሰባታችን፣ “ነጻ ዳኝነት አናገኝም” ብለን አንከራከርም ስንል፣ ዳንኤልና ሌላ አንድ ተከሳሽ ግን፣ “የፍትህ ሥርዓቱን መፈተሽ አለብን” ብለው ከብዙሃኑ ተለየተው ተከራክረዋል፡፡
ምንም እንኳን እኛ “አንከራከርም” ያልነው ቀደም ብሎ የፍትህ ሥርዓቱ በተደጋጋሚ ተፈትኖ በመውደቁ ቢሆንም፣ በዳንኤል ውሳኔ ቅር አልተሰኘንም፡፡ እንዲያውም፣ በተቃራኒው ደግፈናቸዋል፡፡ እሳቸው ተከራክረው የፍትህ ሥርዓቱን ቢያጋልጡ፣ እኛ “አንከራከርም” ያልነው በተጨባጭ ምክንያት እንደሆነ ማስረጃ ነበር የሚሆኑልን፡፡
ቢያንስ በመጀመሪያው ምዕራፍም በተግባር የሆነው ይሄው ነበር፡፡ ዳኛ ጠፍቶ እንጂ፣ ዳንኤል ተከራክረው ራሳቸውን ነፃ አውጥተዋል፡፡ በሀሰት የቀረቡባቸውን ምሥክሮች በመስቀለኛ ጥያቄዎች እርቃናቸውን ያስቀሩበትን ሂደት ታሪክ አንድ ቀን ያወጣዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ዳንኤል ምንም አደረጉ ምንም ግን፣ በአደባባይ የታየን እውነት ለመካድ ትንሽ ሀፍረት የማይሰማው ሥርዓት ስለነበር፣ ምንም ዓይነት የወንጀል ድርጊት ሳይረጋገጥባቸው “ጥፋተኛ” ተብለው የእስር ቅጣት (አራት ዓመት ይመስለኛል) ተወስኖባቸዋል፡፡
በዚያ የፍትህ መድረክ ተቀምጠው ከነበሩት ሦስት ዳኛ ተብዬዎች (እነሱን “ዳኛ” ብዬ ለመጥራት ይከብደኛል) መካከል ሁለቱ በዚያ የሞራል ዝቅታ ላይ ለመገኘት የበቁት፣ ከውሳኔው በኋላ ተስፋ ያደረጉት ሽልማት ቢኖር ነው ብለን ለመገመት አልተቸገርንም፡፡ እንደ ገመትነውም፣ በሂደት የመሐል ዳኛ ተብዬው አንድ ደረጃ ከፍ ብለውም አይተናቸዋል፡፡ ሦስተኛው ዳኛ ተብዬ ግን፣ የሕወሓት አባል ነበሩና (የገዢው ፓርቲ እጩ ሆነው በምርጫ እስከመሳተፍ የደረሱ) ሽልማት ጠብቀው ነበር ለማለት ይከብዳል፡፡ “ግዴታዬ” የሚሉትን ነበር የተወጡት፡፡ ግን እሳቸውም አልቀናቸውም፡፡ ከውሳኔው በኋላ የህሊና ሰላም አላገኙም፡፡ ገና ሕይወት ከሥልጣን ሳይወርድ፣ ውቅያኖስ ተሻግረው የኢትዮጵያን ያህል ልታመቻቸው በማትችለው አሜሪካ አዲስ ሕይወት ጀምረዋል፡፡
እዚህ ድረስ የዳንኤል አካሄድ እንከን አልነበረውም፡፡ ሁላችንንም አስደስተዋል፡፡ ግን ብዙም ሳይቆዩ ያልጠበቅነውን ነገር አደረጉ፡፡ ቀደም ብዬ ጨረፍ እንዳደረኩት፣ ይሄን ጉዳይ የማነሳው አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተሰጣቸው ኃላፊነት አኳያ፣ እኛም እሳቸውም የሆነውን ነገር በአንክሮ አጢነን የምንማርበት ሊሆን ይገባል በሚል ነው፡፡ ፈረንጆች እንደሚሉት፣ ከታሪክ የማይማር ስህተቱን እየደጋገመ ይኖራል፡፡
እዚህ ጋር በማን መነፅር የተገለፀ ስህተት? ብለው የሚጠይቁ እንደሚኖሩ እገነዘባለሁ፡፡ በዘመናችን አንፃራዊነት ነግሶ፣ እውነትና ሀሰት፣ ትክክልና ስህተት ደብዝዘው፣ “አቋሜ ነው፤ እንደ አተያዬ ነው” በሚሉ ፈሊጦች ተሸፍነዋል፡፡ የጋራና የሚያስማሙ እሴቶች ጠፍተው በሞራል ባዶነት (moral vacum) እየተላኩ ይገኛሉ፡፡ እውነትና ውሸት፣ ትክክለኛና ስህተት ግን እንደተመልካቹ ወይም አንፃራዊ አይደሉም፡፡ ሁላችንንም የሚገዙ፣ በዘመናት ሂደት የማይለዋወጡ ናቸው፡፡ በዚህ መንፈስ ነው ከውሳኔው በኋላ ያለውን የዳንኤልን አካሄድ የምተቸው፡፡
ሕይወት በዳንኤል ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ካስበየነ በኋላ ሁለት ነገሮችን አደረገ፡፡ በአንድ በኩል፣ በዕድሜ ልክ እስራት የተወሰነባቸው የቅንጅት አመራሮች ከጥቂት ሳምንታት በፊት እንዳያረጉት (እኔና ባለቤቴን ጨምሮ ጥቂቶቻችን “ማስረጃ አልቀረበባቸውም” ተብለን ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ በነፃ ተለቀናል) ዳንኤልም በተመሳሳይ መንገድ ይቅርታ ጠይቀው ከእስር መውጣት እንዲችሉ በሩን ክፍት አደረገላቸው፡፡ በሌላ በኩል ግን፣ “የተበየነባቸው የእስር ዘመን አንሷል” ብሎ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለት፣ የይቅርታውን ዕድል የማይጠቀሙበት ከሆነ ረዥም የእስር ዘመን ሊጠብቃቸው የሚችልበትን ሁኔታ አመቻቸ፡፡
በዚህ ሁኔታ፣ በዳንኤል ፊት ሁለት አማራጮች ተደቀኑ፡፡ በመጀመሪያ፣ በአቋማቸው ፀንተው፣ “የፍትህ ሥርዓቱን በተግባር እፈትነዋለሁ” ያሉትን እስከመጨረሻው ገፍተውበት፣ የክርስቶስን ፈለግ ተከትለው በግፍ የተላለፉባቸውን እስር ተቀብለው ሥርዓቱን በኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በታሪክና በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ፊት እርቃኑን ማቆም ነበር፡፡
ሁለተኛ አማራጫቸው፣ የቀረበላቸውን ይቅርታ የመጠየቅ ዕድል ተቀብለው፣ በተደነገገው ሕግ መሠረት፣ “ወንጀለኛ ነኝ፣ ተጸጽቻለሁ፣ ይቅርታ ይደረግልኝ” ብለው ለይቅርታ ቦርድ አቤቱታ ማቅረብ ነበር፡፡
ዳንኤል፣ ሁለተኛውን አማራጭ ተቀብለው ይቅርታ ለመጠየቅ ብዙም አላመነቱም፡፡ እንደሰማነው ከሆነ፣ ለዚህ ሁለት ምክንያቶችን አቅርበዋል፡፡ አንደኛው፣ የፍርህ ሥርዓቱን የማጋለጥ ተግባራቸውን በስኬት በማጠናቀቃቸው፣ በቀጣይነት መታሠራቸው ትርጉም አልባ መሆኑን፣ ሁለኛው፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም በገዢው ፓርቲ እጅ እንደመሆኑ መጠን፣ በእሳቸውም ላይ እንደ ቅንጅት አመራሮች የዕድሜ ልክ እስራት መበየኑ አይቀሬ በመሆኑ፣ ከዚህ ከገጽ ሸክም ለመገላገል ያላቸው ብቸኛው አማራጭ ይቅርታውን መፈረም እንደሆነ ነበር፡፡
አንድ ጊዜ ከጀመሩት መንገድ አኳያ ግን፣ ዳንኤል መጨረሻ ላይ የወሰዱት አቋም ትክክል አልነበረም፡፡ “የፍትህ ሥርዓቱን ለመፈተሽ” ከተነሱ አይቀር፣ መንገዱን ጀምረው ግማሽ ላይ ማቋረጥ አልነበረባቸውም፡፡ መፈረማቸው የግድ ቢሆን እንኳን፣ ቢያንስ ይግባኙ እስኪያልቅ መጠበቅ ነበረባቸው፡፡ የይግባኙ ጫና ቶሎ ሰብሯቸዋል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ፣ አሁን ካላቸው ኃላፊነት አኳያ ሲመዘን አሳሳቢ ነው፡፡ በያዙት ቦታ ላይ ውጤታማ ለመሆን፣ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ዓይነት እስከ መጨረሻ የሚዘልቅ የሞራል ጥንካሬ የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ አውድ ነው የዳንኤልን የጀርባ ታሪክ ለማንሳት ያስገደደኝ፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ፣ በአንድ በኩል፣ የሪፖርቱን ድምዳሜ በመቃወም (ግድያዎቹ በሰብዓዊ ፍጡር ላየ የተፈጸሙ ወንጀሎችን እንጂ ዘር ማጥፋትን አያመለክቱም ያለው) በግፍ የተጨፈጨፉትን ንጹሃን ታሪክ በትክክለኛው ገጽታው ማስቀመጥ ሲሆን፣ በሌላ በኩል፣ ዳንኤል በቅንጅት ጊዜ የፈጸሙትን ስህተት እንዳይደግሙ ለመማፀን ነው፡፡ የሀገሪቱ ድምዳሜ ከኮሚሽነርነት ሹመታቸው ጋር የተቀበሉትን ጽዋ እስከ መጨረሻው ለመጨለጥ ማመንታታቸውን ያመላክታል፡፡
ከሀጫሉ ግድያ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልል ምንድን ነው የሆነው? ከሁሉ አስቀድሞ፣ ግጭት አልተፈጠረም፡፡ ግጭት ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ቡድኖች ወይም የማህበረሰብ ክፍሎች የሚፋለሙበት ክስተት ነው፡፡ ከሀጫሎ ግድያ በኋላ ግን፣ በኦሮሚያ ክልል ሁለት የተደራጁ ቡድኖች ወይም ሁለት የማህበረሰብ ክፍሎች አልተፋለሙም፡፡ አስቀድሞ ሲዘጋጅና ሲያቅድ የቆየ ቡድን ነበር ጥቃት የፈጸመው፡፡ በሩዋንዳም የሆነው እንደዚያ ነበር፡፡ ከሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ግድያ በኋላ፣ አስቀድሞ ሲያቅድና ሲዘጋጅ የቆየው የኢንተርሃሞይ ቡድን ጥቃት ነበር የፈጸመው፡፡ በሩዋንዳ ሁቱና ቱትሲ ጐራ ለይተው አልተፋለሙም፡፡ የተደራጀው ኢንተርሃሞይ ያልተደራጁትን ቱትሲዎችንና አጋሮቻቸው ብሎ የፈረጃቸውን ነበር ያጠቃው፡፡ በኦሮሚያ ክልልም ኦሮሞና ኦሮሞ ያልሆኑት ጐራ ለይተው አልተፋለሙም፡፡ የተደራጁ ቡድኖች ነፍጠኞችንና አጋሮቻቸው ብለው የፈረጇቸውን ነበር ያጠቁት፡፡
የመፍትሄው ግማሽ አካል ችግሩን በትክክል ከመረዳት ጋር የተቆራኜ ነው እንደሚባለው፣ በጥቃትና በግጭት መካከል ያለውን ልዩነት በአግባቡ መረዳት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ በሚደረገው ጥረት ላይ ወሳኝ ሚና አለው፡፡
አዎ፣ ገዢው ፓርቲ ቀደም ብሎ፣ ሰሞኑን ደግሞ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ እንደገለጹት፣ ከሀጫሎ ግድያ በኋላ በኦሮሚያ ክልል የሞቱትና የተጠቁት ሁሉ በብሔራቸው ብቻ ተለይተው አልነበረም፤ ኦሮሞዎችም ሰለባ ሆነዋል፡፡ የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ) የተፈጸመባት ሩዋንዳ የተገደሉትና የተጠቁት ሁሉ በማንነታቸው ሰለባ የሆኑት ቱትሲዎች ብቻ አልነበሩም፡፡ እንዲያውም፣ በሩዋንዳ ከተገደሉት መካከል ከ30 ከመቶ የማያንሱት “ለዘብተኛ ሁቱዎች” ተብለው የተፈረጁት የጨፍጫፊዎቹ ወገኖች ነበሩ፡፡ በዚህ ሳቢያ ግን፣ “በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ) አልተፈጸመም፤ ቱትሲ ብቻ ሳይሆን ሁቱም ሞቷል” አልተባለም፤ የጭፍጨፋ ምንነት ከዓላማው የሚቀዳ ነውና፡፡
በሩዋንዳ የጭፍጨፋው ዓላማ ምንድን ነበር? እስከ አንድ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ባጡበት በዚያ እልቂት፣ እስከ ሰባት መቶ ሺህዎቹ ቱትሲዎች፣ እስከ ሦስት መቶ ሺህዎቹ የሚቆጠሩት ደግሞ ሁቱዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁለት የማህበረሰብ ክፍሎች በሞት ቢተሳሰሩም፣ የሞቱበት ምክንያት ግን ለየቅል ነበር፡፡ ሁቱዎች የተገደሉት፣ “የቱትሲዎች አፍቃሪዎች ናችሁ” በመባል ሲሆን፣ የጭፍጨፋው ዓላማ ሁቱዎችን በሙሉ ማጥፋት አልነበረም፡፡ የተፈለጉት በከፊል ነበር፡፡ በአንጻሩ፣ ቱትሲዎች የተገደሉት፣ “የሁቱ ጠላቶች ናችሁ” ተብለው ሲሆን፣ የጨፍጫፊዎቹ ዓላማ ሁሉንም ቱትሲዎች ማጥፋት ነበር፡፡
ይህን የጨፍጫፊዎቹ ዓላማ መሠረት በማድረግም፣ በሩዋንዳ እልቂት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሁቱዎች ቢያልቁበትም፣ “በቱትሲዎች ላይ የተፈጸመ ዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ)” በመባል ይታወቃል፤ እንደ ወንጀልም እንደ ታሪክም፡፡
በኦሮሚያ ክልልም፣ “ነፍጠኞችና” ኦሮሞዎች በሞት ቢተሳሰሩም፣ የሞቱበት ምክንያት ግን ይለያያል፡፡ ኦሮሞዎች የተገደሉት፣ “የነፍጠኛ አፍቃሪዎች ናችሁ” ተብለው ነበር (በገዳዮቹ መነፅር፣ ኦሮሞ ሆኖ ኦርቶዶክስ መሆን፣ ወይም የገዢው ፓርቲ አባል መሆን፣ “ነፍጠኛ አፍቃሪ” በመባል ተፈርጀዋል፣ የጥቃት ሰለባም ሆነዋል)፡፡ የጨፍጫፊዎቹ ዓላማ ግን ኦሮሞዎችን ማጥፋት አልነበረም፡፡ በአንጻሩ፣ “ነፍጠኛው” “የኦሮሞ ጠላት ነው” ተብሎ ሲያንስ፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንዲጠፋ ነው የሚፈለገው፡፡ ለገዳዮቹ “ጥሩና መጥፎ ነፍጠኛ” የለም፡፡ ሁሉም “ነፍጠኛ” የማይፈለግና ከክልሉ መጥፋት ያለበት ነው፡፡
ስለዚህም፣ በሩዋንዳም በኦሮሚያ ክልልም የተጨፈጨፉትን “በማንነታቸውና በአመለካከታቸው” ብለን ለሁለት እንከፍላቸዋለን፡፡ ይህ እስከሆነ ድረስ፣ “በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ)፣ በኦሮሚያ ክልል በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የተፈጸመ ወንጀል (Crimes against humanity) ነበር” ብለን የተለያየ ድምዳሜ ላይ ልንደርስ የምንችልበት አመክንዮ ፈጽሞ ሊኖር አይችልም፡፡
እኔ ግን፣ በሩዋንዳ ካለቀው ሕዝብ ቁጥር አኳያ የኦሮሚያ ክልልን ስናነጻጽረው፤ ዝሆንና አይጥን ማነጻጸር ነው የሚሆነው፡፡ የሩዋንዳው እልቂት ግን፣ የአንድ ጊዜ ክስተት አልነበረም፡፡ ብዙ አሥርት ዓመታት የዘለቀ፣ በአስራዎቹ ጀምሮ ወደ መቶዎች፣ ከዚያም ወደ ሺህዎችና አሥር ሺህዎች፣ ብሎም ወደ መቶ ሺህዎች ያደገ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው አደጋውን በመሸፋፈን ችግሩ እንዳይባባስ ማድረግ ይቻላል በሚል እሳቤ ነበር፡፡ መሸፋፈኑ ግን መፍትሄ አላመጣም፡፡ በተቃሪኒው፣ ሕዝብ አስፈጅቷል፡፡ ይህ ስህተት በኢትዮጵያ መደገም የለበትም፡፡
በተጨማሪም፣ በሩዋንዳና በኦሮሚያ ክልል ያለቀውን ሕዝብ ቁጥር በሚመለከት፣ አንድ ድርጊት የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ) ለመባል የግድ ብዙ ሕዝብ ማለቅ የለበትም፡፡ ለምሳሌ፣ ከዓለም አቀፍ ሕግ በቀጥታ ቀድቶ፣ የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ዘር ማጥፋትን እንዲህ ያስቀምጠዋል፡-
አንቀጽ 269
ዘር ማጥፋት፤
ማንም ሰው፣ በሰላምም ሆነ በጦርነት ጊዜ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በጐሣ፣ በዘር፣ በዜግነት፣ በቀለም፣ በሃይማኖት፣ ወይም በፖለቲካ አንድ የሆነን ቡድን በመላ ወይም በከፊል ለማጥፋት በማሰብ፣ የጥፋቱን ድርጊት በማደራጀት፣ ትዕዛዝ፣ በመስጠት፣ ወይም ድርጊቱን በመፈጸም፣
ሀ. በማንኛቸውም ሁኔታ የማህበረሰቡን አባላት የገደለ፣ አካላዊ ወይም ህሊናዊ ጤንነት የጐዳ፣ ወይም የአካል ጉዳት ያደረሰ ወይም ያጠፋ እንደሆነ (ከ5 ዓመት እስከ ሞት ሊያስቀጣ ይችላል)፡፡
በሕጉ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፣ “…. የሆነን ቡድን በመላ ወይም በከፊል ለማጥፋት በማሰብ ……” የተፈጸመ ድርጊት የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ) የተፈጸመው በመቶ ሺህዎች ሲያልቁ አልነበረም፡፡ ቱትሲን ለማጥፋት ታስቦ ገና በአስራዎቹ የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ የዘር ማጥፋት ተፈጽሟል፡፡
በኢትዮጵያ “የዘር ማጥፋት ተፈጽሟል፣ ወይም አደጋው አለ” ለማለት በመቶ ሺህዎች ማለቅ የለባቸውም፡፡ በኢትዮጵያ “ነፍጠኛ” የሚል መጠሪያ የወጣለትን የማህበረሰብ ክፍል በጠላትነት ፈርጀው ሊያጠፉት የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች አሉ፡፡ እነዚህ ቡድኖች ከአንድ በላይ በሆኑ ክልሎች ያሉ ቢሆንም፣ የስብት ማዕከላቸው በኦሮሚያ ክልል ያሉት ናቸው፡፡ ታላቅ ብሔራዊ አደጋ ደቅነውብናል፡፡ የጋረጡትን አደጋ መሸፋፈን በእሳት መጫወት ነው፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ያስቻለው መንግሥታዊ ተሳትፎ መኖሩ ነበር፡፡ በኢትዮጵያም ያንጃበበውን የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ) አደጋ በእጅጉ አሳሳቢ የሚያደርገው በመንግሥታዊ መዋቅር (በፌዴራልም በክልልም ደረጃ) የተደገፈ መሆኑ ነው፡፡ በእኔ ግምት፣ እነ ዳንኤል በኦሮሚያ ክልል የነበረውን የግድያ ዘመቻ ከዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ) ወደ ሰብዓዊ ፍጡር ላይ የተፈጸመ ወንጀል ዝቅ ያደረጉት የዚህን መንግሥታዊ ኃይል ቁጣ በመፍራት ነው፡፡ ችግሩና አደጋው አልታያቸውም ብዬ ለመገመት እቸገራለሁ፡፡ ካላቸው ኃላፊነት አኳያ፣ እነ ዳንኤል ከዚህ የፍርሃት ቆፈን በአፋጣኝ መላቀቅ ይገባቸዋል፡፡ በቅንጅት ጊዜ እንደታዘብነው፣ ከግማሽ መንገድ መመለስ የለባቸውም፡፡
በመጨረሻም፣ የተባበሩት መንግሥታት ጉዳይ አለ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት “የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ) አደጋዎች ሲከሰቱ የጎን ተመልካች አልሆንም” ብሎ ለዓለም ሕዝቦች በገባው ቃል መሠረት፣ አደጋዎቹ በኢትዮጵያ እየታዩ መሆናቸውን፣ ኒዮርክ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ (ባለፈው ዓመት) ተገኝቶ ያሳወቀው ቡድን አባል ነበርኩ፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ በቤንሻንጉል ብቻ እስከ መቶ ሺህ የሚጠጋ ሕዝብ ተፈናቅሏል፣ ኢትዮጵያም ዜጎቿ ተፈራርተው የሚኖሩባት ሀገር መሆኗ ተባብሷል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ትንፋሽ ያለው ነገር የለም፡፡ ለምን? ብለን መጠየቅ የግድ ይላል፡፡ እርግጥ፣ መፍትሔ ፍለጋ አልነበረም፡፡ ችግሩም መፍትሔውም እኛው ነን፡፡ ይህም ሆኖ፣ የተባበሩት መንግሥታት የዲፕሎማሲና የሞራል ሚና አለው፡፡ የምንኖረው ዓለም አንድ ትንሽ መንደር በሆነችበት ዘመን ነው፡፡ ይህን የተባበሩት መንግሥታት ሚና በሚመለከት በዝርዝር በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡
ድል ለዲሞክራሲ!
ጥር 17 ቀን 2013 ዓ.ም
ቃሊቲ ማረሚያ ቤት
አዲስ አበባ
እስክንድር ነጋ