ዐቃቤ ሕግ የእግድ ደብዳቤ ይዞ ቀረበ !
በድብቅ ካልሆነ ምስክሮችን አላቀርብም በማለት ፤ ዐቃቤ ሕግ የእግድ ደብዳቤ ይዞ ቀረበ !
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አስቀድሞ በሰጠው ቀጠሮ መሰረት ፤ በዛሬው እለት የካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ዐቃቤ ህግ ምስክሮችን አቅርቦ እንዲያስመሰክር ትዕዛዝ የተሰጠበት ቀን ነው ።
ይሁን እንጂ ዐቃቤ ህግ ከጠቅላይ ፍ/ቤት የእግድ ደብዳቤ በማቅረቡ ፤ ከፍተኛ ፍ/ቤት በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት በዛሬው እለት ዐቃቤ ህግ ምስክሮችን አላቀረበም ። ከዚህ ቀደም ምስክሮችን ከመጋረጃ ጀርባ በድብቅ ማቅረብ አለብኝ በማለት ዐቃቤ ህግ አቅርቦት የነበረውን ጥያቄ ፤ በዚሁ ፍ/ቤት ውድቅ የተደረገ ሲሆን ፣ በጉዳዩ ላይ ይግባኝ የተባለው ጠቅ/ፍርድ ቤት የከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔ በማጽናት ምስክሮች በግላጭ ይቀረቡ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል ።
ይሁን እንጂ ፤ በከፍተኛ ፍ/ቤት እንዲሁም በጠቅ/ፍቤት ውሳኔ የተሰጠበትን የምስክሮች አቀራረብ በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ሰበር ሰሚ ችሎት ዐቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቋል ።ሰበር ሰሚ የቀረበለትን ይግባኝ ተመልከቱ ፤ ጠቅላይ ፍ/ቤት ጉዳዩን ግራና ቀኝ አከራክሩ ይወስን በማለት ፤ መልሶ ወደ ጠቅላይ ፍ/ቤት መርቶታል።
ጠቅላይ ፍ/ቤት ከዚህ ቀደም ምስክሮች በግልጽ ችሎት ይቅረቡ በማለት የወሰነውን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው ፤ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የዐቃቤ ሕግ
ምስክሮች እንዳይሰሙ የእግድ ትዕዛዝ አውጥቷል ።
በዚህም መሰረት ፤ ዛሬ በከፍተኛ ፍ/ቤት ቀጠሮ ተሰጥቶት የነበረውን የዐቃቤ ህግ ግልጽ የምስክሮች አሰማም ሂደት
አልተካሄደም ። ይህም በመሆኑ የፊታችን የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጠቅላይ ፍ/ቤት እግድ ባወጣበት የምስክሮች አቀራረብ ላይ ቀጠሮ ተሰጥቷል ።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት ፤ እኛ በቀጠረንው መሰረት ችሎቱ እንዳይቀጥል እግድ መጥቶብናል ። የጠቅላይ ፍ/ቤት የእግድ ትዕዛዝ ውሳኔ ተከትለን ችሎቱ እንዲቀጥል ፤ ለመጋቢት 15 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተናቸዋል ብለዋል ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በከፍተኛ የኩላሊት ህመም እየተሰቃየ የሚገኘው አቶ ስንታየሁ ቸኮል ፤ ተገቢውን ህክምና ለማግኘት በተደጋጋሚ ለፍ/ቤት ያቀረበው አቤቱታ ምንም ምላሻ አለማግኘቱን አስመልክቶ፤ በዛሬው እለት በድጋሚ ለፍ/ቤት አቤቱታ አቅርቧል ።
ይሁን እንጂ ፍ/ቤቱ የማረሚያ ቤት አስተዳደር በቀረበው የህክምና ጥያቄ ላይ አስተያየት ይስጥበት በማለት ምላሽ ሰጥቷል ። በህመም ላይ የሚገኘው ስንታየሁ ቸኮሎ ” እኔ በከባድ ህመም እየተሰቃየሁ እንዴት ሆኖ ነው ማረሚያ ቤት በእኔ ህመም አስተያየት ይስጥበት የሚባለው ” በማለት ለፍ/ቤቱ ምላሽ ሰጥቷል ። ፍ/ቤቱ ግን ማረሚያ ቤት አስተያየት ይስጥበት በማለት፤ ጉዳዩ በቀጠሮ የሚታይ ሳይሆን በፍ/ቤት ቢሮ በደብዳቤ ልውውጥ እንዲሆን ትዕዛዝ ሰጥቷል ።