ዐቃቤ ህግ ዛሬም ምስክሮቹን በችሎት ፊት ማቅረብ አልቻለም!

ከዛሬ ጀምሮ ዐቃቤ ህግ ምስክሮቹን ማሰማት እንዲጀምር የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በትላንትናው ዕለት ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም ዐቃቤ ህግ ምስክሮቹን ማቅረብ አልቻለም ። ምስክሮቻችንን በ15 እና 16 እናሰማለን እስከዚያ ድረስም ለምስክሮች ጥበቃ የሚያስፈልጉ ተግባራትን አከናውናለው በማለት ዐቃቤ ምስክሮቹን አለማቅረቡን ለፍ/ቤት ተናግሯል ።
ይሁን እንጂ የግፍ እስረኞች ጠበቆች ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን ምክንያት ውድቅ በማድረግ ። ምስክር አሰማሙ በአምስት ቀናት የተከፋፈለው ምስክሮች ብዙ ስለሆኑ እና በሁለትና በሶስት ቀናት ስለማያልቅ ነው ። ሆኖም ምስክር በሚያቀርብበት ቀን ለምስክሮች የማደርገውን ጥበቃ አልጨረስኩም ማለት የፍ/ቤት ትዕዛዝ አለማክበር ነው። ዐቃቤ ህግ ምስክር ማሰማት ፍላጎት እንደሌለው ጭምር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል ። የዐቃቤ ህግ ቀጠሮ አለማክበር እና የፍ/ቤት ትዕዛዝ አለመጠበቅ የተከሳሾች መሠረታዊ መብት የሚጥስ በመሆኑ ዐቃቤ ህግ ምስክር ማሰማት በፈለገ ጊዜ መዝገቡን የማንቀሳቀስ መብቱ ተጠብቆ ክሱ ተቋርጦ ደንበኞቻችን ከእስር ይፈቱ በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፤ ዐቃቤ ህግ ምስክሮቹን እሱ በፈለገው ጊዜ ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደም በተሰጠው ጊዜ መሰረት ከሐምሌ 14 እስከ 16 ባሉት ሶስት ቀናት ምስክሮቹን አቅርቦ እንዲያሰማ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል ።