ውስጠ ወይራው ያለመለወጥ ‘ለውጥ’ (በቃሉ ሰውመሆን (የሕግ ባለሙያ)
አቢቹ ሰብሮ የወጣው ወያኔ የጣለውን እቁላል ነው፤ በጥቅሉ ከ 1960 ዓ.ም ወዲህ እስካለንበት በተከሰተው እንዘጭ እቦጭ ውስጥ ኢትዮጵዊነትን ለከፍተኛ ኪሳራ የዳረገ እራስ በል እና እራስበሉን አስቀጣይ የሆነ ሽግግራዊ ክሽፈት አጋጥሞናል፤ አንደኛው የክሽፈት አንጓ የንጉሳዊ ስርአቱን አንጸባራቂ ውርሶች አዘምኖ ማሸጋገር ሲገባ ለአውዳሚ አቢዮት መዳረጋችን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የኢሕአዴግን አራሙቻ ስርአት የሚነቅል አብዮታዊ የስርአት ለውጥ ማዋለድ ሲገባን ጠጋግነን ማስቀጠላችን ነው:: ቅኝ እንደተገዛ ህዝብ ከኢትዮጵዊነት ጥነተ ውርስ እና ሀገር በቀል የእውቀት መሰረት ላይ ተነቅለን ተቅበዝባዥ እንድንሆን የዳረገን የፖለቲካ ታሪካችን አንዱ ዝንፈት ይህ ይመስለኛል:: አብዮት ለማይገባው አብዮት፤ ለሚገባው ደግሞ የአስቀጣይነት ሥራ ነው የተሠራው:: በተለይ የያኔው ትውልድ የኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ መልካም እሴቶቻችን እና ተቋማትን ተከላክሎ እና ዘመኑን እንዲዋጅ አድርጎ ማስቀጠል ሲገባው፤ ከጭቃ እሾህ ዘውገኞች ጋር አብሮ ተሰልፎ የኢትዮጵያዊነትን ጎን መሸንቆሩ ከታሪክ ተዋቅሽነት አያድነውም:: ከመሰረታችን ተነቅለን ስናበቃ ነቃዩን አስተሳሰብ ደግሞ ለማስቀጠል ከመዋተት ያለፈ ምን እራስበልነት አለ:: መንቀል እና ማስቀጠል ያለብንን ውርሰ መሰረት ካላወቅን ዘላቂ ስርዓት ማንበር ተስኖን ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት ለእዘጭ እቦጭ ተዳርገናል:: የስርዓት ለውጥ የሂደትም የግብም ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል:: ጅምሩን እና ሂደቱን ካለጎምነው ውጤቱ እዘጭ እቦጭ ይሆንና በለውጥ ሽፋን ተረኛ ጨቋኝ የማንበር አዙሪት ውስጥ መዳከርን ያስከትላል:: የሀገራችን ፖለቲካዊ ስነ ልቦና ትልቁ ጠባሳ ይህ ስለመሆኑ የሀሳቡ ተጋሪ ነኝ:: ለአምባገነኖች በአድር ባይነት አድፍጦ መገዛት፣ ገንፍሎ መንቀል እና መልሶ አምባገነን ማንበር፤ ለዚህ አዙሪት ዋናው መንስኤው ዘለቄታዊ ስርዓት ከማዋለድ በፊት የእርካብና መንበርን መሰላል የመጨበጥ ግለኝነት አስተሳሰብ ቀድሞ የመጋረጡ አባዜ ይመስለኛል::
ህዝባዊ ስርዓትን ጸነሰን ስናበቃ አገዛዝን እያዋለድን ቀጥለናል:: ከለውጥ ተብዬው ወዲህም እየሆነ ያለው ይሄው ነው:: በየትም በኩል ለውጥ ይከሰት መሰረታዊ የስርዓት ንቅለ-ተከላ ማስፈን የመጨረሻ ግብ መሆን ነበረበት:: “በለውጡ” ዋዜማ ህዝባዊ ትግሉ ፍሬ ሊያፈራ የሚችልበት መንታ የቢሆን ትንታኔዎች እንደ ጉም እየተነኑ ነው፤ በአንድ በኩል ህዝባዊ ትግሉ የመንግሥትን መዋቅር ከውጭ ወደ ውስጥ የሚያጸዳ የለውጥ ምዕራፍ ላይ ደርሶ ቢሆን ኖሮ አንድም ውርሰስንጥቁ አገርሽቶ የርስበርስ ሽኩቻ ሊከሰት ይችል ነበር፤ አልያም የደፈረሰው ጠርቶ ክሱት ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ የማዋለድ ዕድል ይፈጠር ነበር:: ሁለተኛ የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት ከሚጋራ የውስጥ ሀይል ጋር የተቀናጀ እና ከውስጥ ወደ ውጭ የሚፈነዳ አዝጋሚ ስር ነቀል የሽግግር ሂደት መጠንሰስ ነበር:: ይህም ለክሱት ሽግግር የሚከፈለውን ዋጋ ሊቀንሰው ይችላል:: ለለውጥ ተብዬውም ድጋፍ የተቸረው ከዚህ አኳያ ነበር:: የሆነው ግን ህዝባዊ ትግሉ የመንግስትን መዋቅር አጽድቶ ወደ ስርዓታዊ ሽግግር ከማምራቱ በፊት የህዝቡን መሰረታዊ የለውጥ መሻት የሚያዋልድ መስሎ የሚያጨነግፍ አስመሳይ የውስጥ ሀይል ነው የተከሰተው:: በመሆኑም ሀገራዊ መሻትን በቡድናዊ መሻት እና ተረኛ ጨቋኝ ለሚለውጥ ቁልቁለት ተዳርገናል:: የአስቀጣዩ ዳግማዊ ኢሕአዴግ ውስጠ ወይራ አላማው ከውርሰመሰረቱ በአውዳሚ አብዮት የተዳፈነውን የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ከፖለቲካዊ ውክልና እንደተነቀለ አንሳፎ ማስቀረት ሲሆን፤ በአንጻሩ ደግሞ በአብዮታዊ ለውጥ መነቀል የነበረበት ኢሕአዴጋዊ ውርሰ ጥፋት በለውጥ ሽፋን አለባብሶ ማስቀጠልን ያለመ ነው:: የለውጥ ተብዬው መዘውር መንትዮሻዊ ፍላጻ ያለው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን አዳፍኖ ማቆየት እና የዘውግ አረሙን ደግሞ አስቀጥሎ ምርቱን መሰበሰብ ነው::
በመሆኑም በተለይ ከኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው አኳያ በለውጥ መሻቱ እና በለውጥ ሽፋን እየተሰራ ባለው ተግባር መካከል መሰረታዊ መዛነፍ፣ ተቃርኖ እና መተላለፍ ተፈጥሯል:: በኢሕአዴግ ፍጻሜ ላይ የለውጥ መሻቱ እውን መሆን ሲገባው በአንጻሩ በለወጡ ኪሳራ ኢሕአዴግን ከነጥንተ ርእዮቱ የማዳን ሥራ እየተሠራ ነው:: “የለውጥ ሀይል” ተብዬው መሰረታዊ ጭንቀት ስር ነቀል ለውጥ ከመጣ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት አብዮታዊ ውድመት (በ1960) ከማስተናገዱ በፊት ወደነበረ ልዕልናው ያንሰራራል የሚል ነው:: ሁኔታው የሚከፋው ደግሞ ኢሕአዴግ ከተፈጥሯዊ እና ከሚገባው የፖለቲካ ሞቱ እንዲያንሰራራ እየተደረገ ያለው በአዲስ ርእዮት፣ ሕገ መንግሥታዊ እና መዋቅራዊ ለውጥ ሳይሆን የነበረውን ቡቱቶ ደርቶ በማስቀጠል ነው:: እየሆነ ያለው ድራፍት እንዳይጠጣ በሀኪም ለተከለከለ ሰው ቢራ እንደማጠጣት ያክል ነው:: ታማሚው ያንኑ እየተጋተ አዲስ መድሃኒት እንደተገኘለት ያክል ይቦርቃል:: በለውጥ ሽፋን ለውጥን የመከላከል ስልት፤ ወደፊት እያዩ ወደኋላ የመራመድ የአስመሳይነት፣ የአበያነት እና የልግመኛነት ቁልቁለት ውስጥ ነን:: ለውጡን እናግዝ እያለ ትውልድን የሚያደናግረው የፖለቲካ አደንጓሪ በኢሕአዴግ እና በዳግማዊ ኢሕአዴግ(ብልጽግና) መካከል መሰረታዊ የርዕዮት ልዩነት ስለመኖሩ ምን ማሳያ አለው? በአመዛኙ በሂደት ይለወጣል የሚል መከራከሪያ ሲያቀርቡ ይደመጣል:: ቀድሞውንም ጥያቄው ያለው ጥንስሱ ላይ ነው እንጂ በአንድ ጀምበር ሁሉ ይከሰት የሚል አይደለም:: ዳግማዊ ኢሕአዴግ ርዕዮቱን ሳይቀይር ዘዋሪውን ብቻ ቀይሮ የተረኝነት ሀዲድ ላይ አሳፍሮን ሳለ በሂደት የሚጠበቀው ለውጥ ከተረኛ አስቀጣይነት ሊዘል ይችላል ወይ? ፖለቲካችን የሚያስፈልገው እንቁላሉን ሰብሮ የሚወጣ የውረሰ ጥፋት አስቀጣይ ሳይሆን እንቁላሉን እራሱን የሚቀይር ስርዓታዊ ለውጥ ነው:: አቢቹ ሰብሮ የወጣው ወያኔ የጣለውን እቁላል መሆኑን አንዘንጋ:: ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛው በራሱ ጥንተ ውርስ እና ማህበራዊ መሰረት ላይ በተበባበረ ክንድ ለትግል መነሳት አለበት የምንለው:: የሆነው ሆኖ በለውጥ ሽፋን ለውጥን የመከላከል ቁልቁለቱ አያሌ ርዕዮት-አለማዊ፣ ተቋማዊ፣ ህገ መንግስታዊ እና ስርዓታዊ መገለጫዎች አሉት:: እነሆ በቅጭቡ፤ ሀ/ የአዳፍኔነት እና አስቀጣይነት መንታ ስለት፤ ውስጠ ወይራው ያለመለወጥ ‘ለውጥ’ በቃሉ ሰውመሆን (የሕግ ባለሙያ) 6 ቁጥር 04 ታህሳሥ 10 ቀን 2013 ዳሰሳ የሚዳፈነው ማን ነው? የሚቀጠለውስ? የሀገራችን ፖለቲካ በተውሶ ጥብቆ መቀንበብ ከጀመረበት የተማሪዎች አብዮት ጀምሮ በተለይም ከወያኔ መከሰት ወዲህ በመሰረታዊነት በሁለት የፖለቲካ አሰላለፍ ተቃርኖ ተሰቅዟል:: የተቃርኖው ስንጥቁ በዋናነት ከላይ ከተገለጸው የሽግግር ክሽፈት አንጓ፣ ከታሪክ አረዳድ እና የነባራዊ ሁኔታ ትንታኔ ተቃርኖ ይመነጫል:: ክሱት ብያኔውም የመደብ እና የዘውግ ጭቆና ትርክት በሚለው ይሸከፋል:: በጥቅሉ የስንጥቁ አንድ መከሰቻ ከኢትዮጵዊ ውርሰ-እሴት የሚቀዳው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት/civil nationalism ሲሆን ሌላኛው የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ላይ የተጠነሰሰው የዘውግ ብሄርተኛው/ ethnic nationalism ነው:: ወያኔ የተቀዳችበት ዥረት በቅኝ ገዢዎች ሀገር አፍራሽ ሴራ ተጣብቶ፣ በራስ በሉ ሌኒኒስታዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ታጅሎ በሻቢያ አውቆ አጥፊ ትርክት አጎንቁሎ አንቀጽ 39 ላይ የተቋተ የደም እዳ ነው:: በአመዛኙ የዘውግ ጭቆና ትርክት መሰረቱ የእውነታ ጥመት/ Distortion ነው፤ በነባራዊ ሁኔታ ትንታኔ እውነትን ሳይሆን የሚበጀውን ሀሰት ፈጥሮ፣ ለነበረው እውነት አዲስ ትርጉም ሰጥቶ ለፖለቲካ ፍጆታ የማብቃት ጥመት ነው:: ጥመት ደግሞ ከዜሮ ጀምሮ፣ በራሱ ዥረት ቀልብሶ የሚፈስ እና ሁሉን በራስ የመለወጥ ውርሰ ጥፋት ነው፤ የሻቢያ፣ የወያኔ እና የኦነጋውያን ርእዮት ውርሰ መሰረቱ፣ የፍሰት አቅታጫው እና መዳረሻው ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ እነደሚባለው ከዚሁ የሚቀዳ ነው::
ሀገሪቱ የቆመችበትን መሰረታዊ የህላዌ ምሰሶዎችን ለግዜያዊ የፖለቲካ ትሩፋት መሰዋት፣ ማጠልሸት፣ እንደ አዲስ መበየን፣ ከዜሮ መጀመር፣ በቅልብስ እሳቤ እና ቁልም አረዳድ የታጀለ ነው፤ የቁልቁለቱ መዳረሻ ራስ ጠልነት ነው:: የ“ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች” ምናባዊ ምስል ክሰታ፣ የተጨቋኝነት እና ቅኝ ተገዥነት ተረት፣ የአማራ ጨቋኝነት የጋራ ጠላት ምስል ክሰታ፣ እራስን በራስ… እስከመገንጠል፣ ወዘተ እውነታን እንደሚበጅ አጣሞ ለነበረው አዲስ ትርጉም መስጠት የፖለቲካ ትርፍ ማሳለጫ እና የትግል መሳሪያዎች ናቸው:: በሌኒኒስታዊ የዘውግ ጨቋኝ-ተጨቋኝ የፖለቲካ ትርክት ውስጥ ሁሉም ነገር የትግል መሳሪያ ነው:: እግዚያብሄርን ከመካድ ይነሳል፤ ታሪክ፣ ሀገር፣ ተቋማት(የሀይማኖትም ሆነ ማህበራዊ) ሰው፤ መሬት ሁሉ የፖለቲካ ትጥቅ ነው:: በትግሉ ውስጥ የሚከሰቱ ስብእናዎችም እራሳቸውን የጥቅሉ አለም ወይም የሀገር አንድ አካል አድርገው አይረዱም:: ይልቁኑ ሁሉም ነገር ለነሱ ሲል የሚኖር የሚመስላቸው ግላውያን/ narcist ሲሆኑ እራሳቸውን ብቻ እንደግብ ያያሉ:: በዚህ ቁልቁለት ወያኔ ስንጥቁን አስምሮ ሲያበቃ ከስንጥቁ አንዱን(የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክትን) በዋና መሳሪያነት ተጠቅሞ የሀገሪቱን ሁለንተና እንደ ነቀዝ በልቶ ለአስቀጣዩ አስረክቦታል:: አብላጫ ማህበራዊ ቅቡልነት እያለው ከፖለቲካ ውክልና ተገፍትሮ በተንሳፋፊነት ይልበላውን እያከከ የቀጠለው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው ነው::
ከዚህ አኳያ “የለውጥ ሀይል” ነኝ ባዩ አቢቹ(ኦነጋውያን) ተልእኮ እንዴት ይመዘናል? ላለፉት ሁለት አመታት በነባራዊ ሁኔታ ትንታኔ፣ በትርክት እና በተግባር እንደታየው እነ አቢቹ የጨቋኝ- ተጨቋኝ ትርክት ወራሾች እና አስቀጣዮች ለመሆናቸው በቂ ማሳያ አለ:: ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው እዚህ ላይ ብዥታ ውስጥ ገብቶ እራሱን ባያታልል መልካም ነው:: ማሳያውን ሁሉ መተንተን ለቀባሪው እንደ ማርዳት ነው:: የመደመር መጽሀፍ እስኳል መልክቱ የጨቋኝ ተጨቋኝ ርእዮት አስቀጣይነት ነው፣ የሽመልስ አብዲሳ ሰበርናቸው ትርክት እና አማራን እያጠፋነው ነው ድብቅ ንግግር፣ የአቢቹ የአስከሬን ዘር ቆጠራ እና ለአንድ ብሄር ብለን ህገመንግስት አናሻስልም ንግግር፣ ወዘተ ውስጠ ወይራ መልእክቱ የተዳፈነውን ኢትዮጵዊ ብሄርተኝነት አዳፍኖ ማቆየት እና መራሹን የዘውግ ፖለቲካ አረም ደግሞ አስቀጥሎ ምርቱን መሰበሰብ ነው:: የአዙሪቱን አንድምታ ከለውጥ ተብዬው አኳያ በዚህ መልክ ልቀንብበው፤
1ኛ እነ አቢቹ የፖለቲካ ውርሰ ስንጥቁን ለፖለቲካ ሚዛን ማስጠበቂያነት መጠቀማቸው አስቀጣይነት አንድ ማሳያ ነው፤ በስንትቁ ተቃርኖ የተሰቀዙትን አሰላለፎች እንደ ጽንፈኛ በመሳል እራሳቸውን በመሀል ሰፋሪ እና በለዘብተኛነት አቅርበው የቅቡልነት ማሳለጫ ቢያደርጉትም እራሳቸው በስንጥቁ አንድጫፍ የሚሰለፉ ናቸው::
2ተኛ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ቀና ለማለት ሲሞክር በጽንፈኝነት ፈርጆ የማደከም ልምምድ ያላቸው መሆኑ ሌላው የአዳፍኔነት ማሳያ ነው:: በመሰረቱ ልብ ማለት የሚገባው ኢትዬጵዊ ብሄርተኝነት የፖለቲካ ተቃርኖው ጥቅል አሰላለፍ ማሳያ እንጂ በራሱ ጽንፍ አይደለም:: ምሰሶው እንዴት ጽንፍ ይሆናል? አሜሪካዊነት ለአሜሪካውያን ጽንፍ ይሆናል ወይ? ከዚህ አኳያ እየተሰራ ያለው ሴራ ሆን ብሎ ሀሳዊ መንትዬሽ/ false dichotomy እና ሀሳዊ ንጽጽር/false equivalence በማስረጽ ምሰሶውን(ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን) ከመሀል የመገርሰስ፣ ገርስሰው ሲያበቁ መሀል መንገድ ላይ እንገናኝ በሚል ፈሊጥ ጭብጦውን ይዞ ወደምሰሶው የመንኳተት፣ ብሎም መሀሉን ለብቻ የመጠቅለል እና የመሰልቀጥ አደገኛ አካሄድ ይስተዋልበታል:: ሰዋዊው እስክንድር እና ዘውገኛው ጀዋር በጽንፍና ጽንፍ የሚፈረጁ ናቸው ወይ? የሰማይ መሳላል የሆነችው ሰንድቅ አላማችን እና የድርጅት አርማው የኦነግ ባድራ በጽንፍና ጽንፍ የሚፈረጁ ናቸው ወይ? OMN እና የድሮው ESAT ወይም ያሁኑ መረጃ ቲቪ በጽንፍና ጽንፍ የሚፈረጁ ናቸው ወይ? እውን የአማራ ራስን የመከላከል ተፈጥሯዊ ብሄርተኝነት እና እራስ ጠሉ የዘውግ ብሄርተኝነት የሚነጻጸ ናቸውን? ይህ ሁሉ የሀሳዊ መንትዬሽ/false dichotomy እና ሀሳዊ ንጽጽር/false equivalence ሰሊጡን ከኑጉ ጋር ቀላቅሎ የመውቀት የፖለቲካ ታክቲክ ማሳለጫ:: አሁን አሁንማ እስራት፣ ግድያን እና የአስክሬን ቆጠራን በራሱ በዚሁ መነጽር በብሄር ተዋጽኦ እና ከሁለቱም ጽንፍ የማዳረስ አሰራር እየተለመደ ነው:: ሁኔታው ቅኝ ብንገዛ ኖሮ ይሰራብን ከነበረው ባልተናነሰ የሀገራችንን እና ህብራዊ ማንነታችንን መሰረታዊ እሴቶች የማሳጣት ብሎም ለብቻ የመጠቅለል አደገኛ ውጤት ሊያስከትል የሚችል ነው::
3ኛ በጓያ አውድማ ላይ ጤፍ መውቃት ሌላው የአዳፍኔነት እና አስቀጣይነት ማሳያ ነው፤ እነአቢቹ(ኦነጋውያን) በትርክት ደረጃ የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ማቀንቀናቸው ከፖለቲካ ስልትነታ የማያልፍ፣ ግን ደግሞ ውስጠ ወይራ አንድምታ ያለው ነው፤ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት አብላጫ ማህበረሰባዊ ቅቡልነት ቢኖረውም ህገመንግስታዊ እና መዋቅራዊ መሰረት እንዳይቆናጠጥ በወያኔ እና በመሰሎቹ አውዳሚ ስራ ተሰርቶበትል:: ይህን ከማስቀጠል አኳያ በትርክት ደረጃ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ማዥጎድጎድ የፖለቲካ ማህበራዊ መሰረቱን በማሳከር በጋራ እንዳይቆም ከማድረግ ባለፈ በፖለቲካ መዋቅር ደረጃ ጠብ የሚል ውጤት እንዳማያስከትል እነአቢቹ ያውቁትል:: ምክንያቱም ስንኩል ማህበራዊ መሰረት ኖሮት ሳለ ህገመንግስታዊ እና መዋቅራዊ መሰረት ተቆናጦ ያለው በተጨባች የዘውግ ጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክ በመሆኑ ነው:: መሰረት የያዘውን የዘውግ ፖለቲካ ለማስቀጠል አንዱ ስልት መሆን ያለበት ደግሞ ኢትዮጵዊ ብሄርተኛው እውነተኛ እና መሰረታዊ ሽግግር የሚያስከትል ለውጥ እንዳያዋልድ በመከላከል ነው:: ይኸውም ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛውን በትርክት ሸንግሎ ወደሰገባው በመመለስ ማዳፈን ሲቻል ነው:: በለውጥ ሸፋን ለውጥን የመከላከል አዳፍኔነት እና እስቀጣይነት ይሉሀል እንዲህ ነው:: በተለይ የአቢቹን ፖለቲካዊ ትርክቶች መአከላዊ መልክት ለመረዳት አንዱ ዘዴ ትርክቱን ገልብጦ ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል:: እያሞገሰ ይቀብርሀል፣ የልብህን እየተናገረልህ በተግባር ያልነገረህን ሴራ ያጎናጽፍሀል:: የኦነጋውያን ዋና አላማ የተካደውን ኢትዮጵዊ ብሄርተኝነት አዳፍኖ ማቆየት እና መራሹን የዘውግ ፖለቲካ አረም ደግሞ አስቀጥሎ ምርቱን ለመሰብሰብ ይቻል ዘንድ በለውጥ ካባ ለውጥን በዘላቂነት መከላከል ነው:: ቀድሞውንም ለመቀልበስ የሚበቃ የለውጥ ፍላጎት እና ጅምር ስላልነበረ ባለንበት ሁኔታ የውድቀት አዙሪት ቀጠለ ነው እንጂ ለውጥ ተቀለበሰ ማለት አይቻልም::
ለ/ የውርስ እዳ ደብዳቤውን ማን ይቅደደው? (ክፍል ሁለት ይቀጥላል)