ውስጠ ወይራው ያለመለወጥ ‹ለውጥ› (፪)
በክፍል አንድ መጣጥፌ ‹ለውጥ› እየተባለ የሚወራው ሀሰት መሆኑን አብራርቻለሁ፡፡ ‹ለውጥ› ተብየው ውስጠ ወይራ እንደሆነ እና ‹የለውጡ› መሪ ነኝ ባዩ አብይ አሕመድ ነብረው የወጡት ወያኔ የጣለውን እንቁላል እንደሆነ አብራርቻለሁ፡፡ በ‹ለውጥ› ሽፋን ‹ለውጥን› የመከላከል ቁልቁለቱ አያሌ ርዕዮተ ዓለማዊ፣ ሕገ መንግሥታዊ፣ ተቋማዊ እና ሥርዓታዊ መገለጫዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ሦስት መገለጫዎችን ቀንጭቤ እገልፃለሁ፡፡ አንደኛው የአዳፍኔነትና የአስቀጣይነት መንታ ስለት ሲሆን ይህንን ባለፈው ክፍል በዝርዝር አይተናል፡፡ በዛሬው ክፍል ደግሞ ሁለቱን ቀጥሎ እናያለን፡-
ለ/ የውርስ እዳ ደብዳቤውን ማን ይቅደደው?
የህወሀት ህገመንግሥት በጥቅሉ በተቃርኖ የተሞላ፣ ሃገሪቱን በመንታ ስለት የሚገዘግዝ፣ የሀገር ብተናን የጸነሰ ስታሊናዊ የትግል መሳሪያ ስለመሆኑ ነጋሪ አያሻውም፡፡ የተቃርኖው ዋና መሠረት የሚቀዳው ሕገመንግሥቱ ስታሊናዊ መአከላዊነትን ከፌደራሊዝም ጽንሰ ሀሳብ ጋር ለማዳቀል ከመሞከሩ ላይ ነው፡፡ ተረገጥ ወይ ተገንጠል በሚል መልኩ በአንድ በኩል የብሄረሰብ መብት ጠበቃነት ስም እስከመገንጠል የሚደርስ የተለጠጠ መብት ይሰጥና በሌላ በኩል ከመገንጠል በመለስ ያሉ ፍትሃዊ የብሄር መብቶችን ይደፈጥጣል፤ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ያሰፍርና በግልባጭ እኔ ልወቅላቹ የሚል ጠቅላይ ስርአት ይዘረጋል፤ በፌደራላዊ መዋቅር ስልጣንን የጎንዬሽ ያከፋፈለ መስሎ፤ እንዲሁም የመንግሥትን ሥልጣን በሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ መካከል የሥልጣን ክፍፍል መርህን የተከተለ መስሎ በግልባጭ ስልጣንን በአንድ ጠቅላይ ኃይል ስር የሚያከማች ስታሊናዊ የተዋረድ የእዝ ሰንሰለት/vertical delegation በማስፈን የተማከለ አስተዳደር ይጋብዛል፡፡ የሰብአዊ መብቶችን ዘርዝሮ ያሰፍርና በግልባጭ በዝርዝር ህጎች የሚታገዱበትን ስልት ይቀይሳል፣ ለመከበራቸውም ተቋማዊ ዋስትና አይሰጥም፤ መድበለ ፓርቲ ስርአት አሰፈንኩ ይልና በግልባጭ የአውራ ፓርቲ አገዛዝን ያሳልጣል፤ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር አላማ እንዳለው ይደነግግና በግልባጭ እስከመገንጠል መብት ይሰጣል፣ የሀገር ሉአላዊነትን እውቅና ይነሳል፡፡ ከላይ ለማሳያነት የተገለጹትን ህጸጾችንና መሰል ሰንኮፎችን መጸነሱን ስንመለከት ሀገሪቱ አሁን ለደረሰችበት በተቃርኖ የመሰቀዝ እና የፖለቲካ ቀውስ ዋና መሰረቱ የህወሃት ህገመንግሥት እና ሕገመንግሥቱ የተመሠረተበት የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት እንዲሁም ዘር ላይ የተመሠረተው የፌደራል አወቃቀር እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም፡፡
በመሆኑም የሀገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ መሠረታዊ ፈውስ ለመስጠት ሕገመንግሥቱ ከሚደነግገው ማሻሻያ ስርአት ውጪ በሆነ ዘዴ ሕዝባዊ ሕገመንግሥት ከመዘርጋት መጀመር አለበት፡፡ ሕገመንግሥታዊ “ማሻሻያ” ሲወሳ ከቃላት አጠቃቀም ጀምሮ መጤን ያለባቸው መሠረታዊ ተጠየቆች አሉ፤ እነሱም ሕገመንግሥቱ በምን ዘዴ፣ መቼ እና በምን ያህል መጠን ይሻሻል የሚሉት ጭብጦች ናቸው፡፡ በሕገመንግሥቱ ላይ ስርነቀል ንቅለተከላ መደረግ አለመደረጉ ላይ መሠረታዊ አንድምታ የሚያሳድሩ ጭብጦች ናቸው፡፡ በምን ዘዴ እና መቼ ይሻሻል ለሚሉት ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ በምን ያህል መጠን ይዘቱ ይቀየር የሚለውን የሚመልሱ ናቸው፡፡ 1ኛ በምን ዘዴ የሚለው በዋናነት ሕገመንግሥቱ እራሱ በዘረጋው የማሻሻያ ስርአት ወይስ ከሕገመንግሥቱ መአቀፍ ውጪ በሆነ መንገድ የሚለው ላይ ያጠነጥናል፤ ሕገመንግሥቱ እራሱ በዘረጋው ስርአት ለማሻሻል መሞከር ሕገመንግሥቱ መሠረታዊ መርዙን እንደያዘ ቁንጽል ማሻሻያ በማድረግ የማስቀጠል ውጤጥ ያስከትላል፡፡ ምክንያቱም በመሠረታዊነት የማሻሻል ፍላጎት ቢኖር እንኳ የማሻሻያ ስርአቱ የሚፈቅድ አይሆንም፡፡ ይህ ደግሞ ሕገመንግሥቱ ዘመን ተሸጋሪ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ፋይዳ የሚኖረው ለራሱ ለሕገመንግሥቱና ደራሲዎቹን ነው፡፡
በአንጻሩ የሀገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ የሚጠይቀው ደግሞ በሕዝብ ለሕዝብ ውይይት እና ድርድር የግለሰብ እና የቡድን መብትን አጣጥሞ የሚያስኬድ እና ወቅቱን የዋጀ አዲስ ማህበራዊ ውል ማሰርን ነው፡፡ በመሆኑም ሕገመንግሥቱ ከዘረጋው የማሻሻያ ስርአት ውጪ ሕገመንግሥታዊ ንቅለ ተከላ ማድረግ አልያም ጥንተ መሠረታችንን ያስጠበቀ አዲስ ማህበራዊ ውል መዋዋል ያስፈልጋል፡፡ 2ተኛ “ማሻሻያ” መቼ መከናወን አለበት፤ በዋናነት በሽግግር ወቅት ሁኖ፣ ከምርጫ በፊት ወይስ በኋላ በሚለው ጭብጥ ላይ የሚያጠነጥነው ነው፡፡ የዓለም አቀፍ ንጽጽራዊ ሕገመንግሥታዊ ሕግ/comparative constitutional law ተሞክሮ የሚያሳየው ስርነቀል ሕገመንግሥታዊ ንቅለተከላ ለማከናወን ትክክለኛው ወቅት በሽሽግግር ወቅት ሁኖ ከምርጫ በፊት መከናወን እንደሚገባው ነው፡፡ ከምርጫ በኋላ ስርነቀል ሕገመንግሥታዊ ንቅለተከላ ለማድረግ የሚቻልበት እድል እጅግ ጠባብ ነው፡፡ ምክንያቱም በዋናነት ከምርጫ በኋላ የሚደረግ ማሻሻያ ሕገመንግሥቱ የዘረጋውን ስርአት ተከትሎ ለማሻሻል ስለሚገደድ ነው፡፡ ሕገመንግሥቱ የዘረጋውን የማሻሻያ ስርአት ተከትሎ የሚደረግ ማሻሻል ደግሞ እንደተባለው መሠረታዊ ለውጥን አይጋብዝም፣ አይፈቅድምም፡፡
ከዚህ አኳያ የእነአቢቹ(ኦነጋውያን) ፍላጎት ሕዝባዊ መሻቱን እና ነባራዊ ሁኔታውን ያማከለ ነው ወይ? እነ አቢቹ ሕገመንግሥቱን እንደነበረ ማስቀጠል ወይስ ማሻሻል ነው የሚፈልጉት? ማሻሻል ቢፈልጉ እንኳ በምን ዘዴ፣ መቼ እና በምን ያህል መጠን የሚለው ጥያቄ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በትርክትም ሆነ በተግባር እንደተስተዋለው እነ አቢቹ ሕገመንግሥቱን ለአንድ ብሔር ብለው እንደማያሻሽሉት ነግረውናል፣ ምናልባት ቢያሻሽሉት እንኳ የኦነጋውያንን ሰልቃጭ አዠንዳዎች ለመጨማመር በታለመ፣ ሕገመንግሥቱ እራሱ በዘረጋው ስርአት ተመስርተው እና ከምርጫው በኋላ ነው፡፡ በዚህ አግባብ ደግሞ ስርነቀል ሕገመንግሥታዊ ንቅለ ተከላ አዋልዶ የሀገሪቱን ፖለቲካ መፈወስ አይቻልም፡፡ ሕገመንግሥቱን ከነመርዙ የማስቀጠል ቁማር ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በለውጥ ሽፋን ተረኛ ጨቋኝነትን የማዋለድ አዙሪት ነው፡፡ በመሆኑም በተለይ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው የትግል ትኩረቱ መሰባሰብ ያለበት እዚህ ቁልፍ አዠንዳ ላይ መሆን አለበት፡፡
ለመሆኑ እነአቢቹ(ኦነጋውያን) ለሕገመንግሥቱ የሚሳሱለት ለምንድነው? 1ኛ ሕገመንግሥቱ ተቀናቃኛችንን ስለሚጎዳ ብቻ እኛን ይጠቅመናል ከሚል ስሁት አመክንዮ/fallacy፤ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛውን ከጎዳ የግድ/Necessarily የዘውግ ብሄርተኝነትን ይደጉማል ከሚል ስሌት ይመነጫል፡፡ እንዲህ ያለ እሳቤ የሚመነጨው አጠቃላይ ሀገራዊ ስእል ከማጣት እና በራስ መሻት ሰማይ ስር ከመቀንበብ ነው፡፡ ኢትዮጵዊ ብሄርተኛው ንጉሳዊ ስርአትን የታገለው እንደ ሀገር ዘመኑን የዋጀ የተሻለ ስርአት ለማዋለድ ከማለም አይደለም ወይ፡፡ በዘውጌ ብሄርተኞች ስሌት አኳያ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው ንጉሣዊ ስርአቱን ጠጋግኖ ማስቀጠል በተገባው ነበር፡፡ ምክንያቱም ዘውገኞቹ ከንጉሣዊ ስርአቱ ጀምሮ ሲታገሉ የነበሩት የተሻለ ሀገራዊ ስርአት ለማዋለድ ሳይሆን እነሱ በጨቋኝነት የፈረጁትን ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛውን ማህበራዊ መሠረት አዳክሞ ተረኛ ጨቋኝ ለመሆን እንደነበር ከወቅታዊ የፖለቲካ አቋማቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵዊ ብሄርተኛው ከአብዮቱ ዘመን ጀምሮ በአልነጠረ የፖለቲካ አሰላለፍ ውስጥ እራሱን ከአራጆቹ ጋር ያዋለ የመስዋእት በግ ነበር ማለት ነው፡፡ ፖለቲካችን ከዚህ አዙሪት መውጣት አለበት፡፡ ሕገመንግሥቱ ንቅለተከላ የሚያስፈልገው በዋናነት በአጸዳደቅ ሂደቱም ሆነ በይዘቱ የቅቡልነት እጦት/legitimacy deficiency የተጋረጠበት፣ ዓለም አቀፍ የሕገመንግሥታዊነት መርህን ተከትሎ ያልጸደቀ፣ እና በይዘቱም ሀገራዊ ቃልኪዳን ከመሆን ይልቅ የአንድ ቡድን የፖለቲካ አላማ ማሳለጫ የትግል መሳሪያ በመሆኑ ነው፡፡ ሕገመንግሥቱ አማራን ወይም ኢትዮጵዊ ብሄርተኝነትን ስላገለለ ብቻ መቀየር አለበት የሚለው ሀሳብ ሕገመንግሥቱን የመቀየር መሠረታዊ ምክንያት የሚጠመዝዝ፣ ለመቀየር የሚደረገውን ትግል ማህበራዊ መሠረት የሚከፋፍል እና እዳውን ለአንድ ወገን ተጠቃሚነቱን ለሁሉም ለማላበስ የሚያደርግ ትርክት በመሆኑ መስተካከል አለበት፡፡ ሕገመንግሥቱ እንደ ሀገር የማያስቀጥለን፣ ሕዝባዊ ስርአትን የማይዘረጋ እስከሆነ ድረስ ሁላችንንም ይዞን መስመጡ አይቀርም፡፡ ስለሆነም የሕገመንግሥቱ መቀየር የኢትዮጵያውያን የሁላችን ትንሳኤ እንጂ የተወሰነ የፖለቲካ አሰላለፍ ጥቅም ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ እንዲያውም ሕገመንግሥቱ ያለአግባብ አሳብጦ የሚያፈነዳው በዋናነት ተረኛውን ኦነጋዊነት ነው፡፡ ፊኛ የሚፈነዳው ከመጠን በላይ በመነፋት አልያም ተሸንቁሮ በመተንፈስ ነው፡፡ የፖለቲካ ሴራም እንዲሁ ነው፡፡ ወይ አሳብጦ ወይ ሸንቆሮ ነው የሚያተረሽህ፡፡
2ተኛ የወያኔ ሕገመንግሥት በመሰልቀጥ ካልሆነም በመገንጠል የተቃኘውን የኦነጋውያን(የእነአቢቹን) ፖለቲካ ከግብ ለማድረስ ያስችላል ከሚል ስሌት የመነጨ ነው፤ በዋናነት የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጥንተ እርስት፣ የበራራ ስልጣኔ አሻራ ያረፈበትን እና የኢትዮጵዊነት አስኳል የሆነውን የሸዋ ክፍለ ሀገርን ጨምሮ የተለጠጠ ግዛት በኦሮሚያ ክልልነት ብቻ እውቅና የሰጠ ሕገመንግሥት ከመሆኑም በላይ የመገንጠል መብትን ችሮናል ከሚል ስሌት የሚመነጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በዘር እና ቋንቋ ላይ ብቻ ተመስርቶ ፌደራላዊ ስርአት አዋቅሮ የዘውግ መሬት መስፈር ከነባራዊ እውነታ ጋር መቃረን ነው፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የታሪክ ፍሰት ውስጥ የአንድ ንኡስ ማንነት ያልተቆራረጠ ዘላቂ ርስት እና ያልተዛነቀ ማንነት ኖሮ አያውቅም፡፡ ማንነታችንም ሆነ እርስታችን ሲዛነቅ እና ሲዋዋጥ የዘለቀ ነው፡፡ ሁላችንም በሁላችን ውስጥ አለን፡፡ በቀዳሚ ባለርስትነት/nativist view አመለካከት ከተቃኘን ኢትዮጵያን ጨምሮ የአለም ሀገራት በሙሉ እንደገና መዋቀር ሊኖርባቸው ነው፡፡ በቀዳሚ ርስትነት አመለካከት ከተመራን በኢትዮጵያ ሁኔታ ዋነኛ ተጎጂ የሚሆነው ኦነጋዊው ሰልቃጭነት ነው፡፡ ምክንያቱም እራሱ የሚያቀነቅነው ትርክት እራሱ የሰለቀጠውን ርስት እና ማንነት ሊያስተፋው ስለሚችል ነው፡፡ እንዳበጡ መገንጠል እንዳበጡ መሽሎክ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በእብጠቱ ልክ የመሽሎኪያው ቀዳዳው እየጠበበ ስለሚሄድ ነው፡፡ በጋራ ከበሰልንበት ቶፋ ወስጥ ንፍሮ ጨብጦ መውጣት አይቻልም፡፡ አንዱ መፍትሄ ከእውነታ ጠምዛዥ/distortive ከሆነው የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክ ላይ ከተመሠረተው የዘውጌ ፌደራሊዝም ተላቀን ነባራዊ ሁኔታውን (ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ታሪካዊ እና መልካምድራዊ ትስስርን፣ አስተዳደር አመቺነትን ወዘተ) ያገናዘበ አወቃቀር መቀየስ ነው፡፡
ሐ/ የቁልቁለቱ ቁልቁለት፤ ህወሀትን ከህወሀት የማዳን ዘመቻ፤
በትግራይ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ውስጠ ወይራነት ምንያህል በውል ተገነዘብነው? እየሆነ ያለው እንደ ዳግማዊ ኢህአዴግ/ብልጽግና ሁሉ ህወሀትን የማስወገድ ሳይሆን ህወሀትን የማዳን ተግባር መሆኑ በይደር እየተገለጠ ነው፡፡ አንድ ድርጅት የሚሞተው ተቋማዊ መዋቅሩ ከመፍረሱ በተጨማሪ በዋናን መሠረታዊ ርእዮት አለማዊ፣ መዋቅራዊ እና ስርአታዊ ቁመናው ሲሻር፣ ወይም አስቀጣይ ሲያጣ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አቢቹ ቅድሚያ ኢህአዴግን የሚያፈርስ አስመስሎ ከሞት አፋፍ አድኖ ብልጽግና የሚል የዳቦ ስም በማውጣት ርእዬቱን አስቀጠለው፡፡ የለውጥ መሻቱ መአበል የኢህአዴግን ርእዮት ዓለም፣ ሕገመንግሥት፣ መዋቅር እና በጥቅሉ ስርአቱን ከመሠረቱ እንዳይቀይረው በለውጥ ሽፋን ለውጡን የማምከን ሥራ እየተሠራ ቀጥሏል፡፡ ህወሀትንም በሚመለከት እየሆነ ያለው ይሄው ነው፡፡ ለብልጽግና የስልጣን ተቀናቃኝ የሚሆኑ አንጃዎችን ከውስጡ አስወግዶ የድርጅቱን መርዘኛ እሳቤ በተተኪ አንጃ አሸጋሽጎ የማስቀጠል ውስጠ ወይራ ደባ ነው በሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው፡፡ አጋፋሪው ኃይል አሁንም እንደ ለውጡ መባቻ ሰሞን ጁንታ ጁንታ እያለ አቢቹን ሞሽሮታል፡፡ ጁንታ ምን አንድምታ እንዳለው ግን ቆም ብሎ የጠየቀ ጥቂት ነው፡፡ አቢቹ ጁንታ ሲል ህወሀትን በአጠቃላይ አፈቅረዋለው፣ ህወሀት ያነበረውን ርእዮት፣ ስርአት፣ ሕገመንግሥት እና መዋቅር ለማስቀጠል እችል ዘንድ ከድርጅቱ ውስጥ ጥቂት አንጃዎችን ማሸጋሸግ አለብኝ እያለ ነው፡፡ ጁንታ ማለት በአንድ ድርጅት ውስጥ ያለ አፈንጋጭ አንጃ እንደማለት ነው፡፡ ሕግ ማስከበር ዘመቻ የሚለው አገላለጽም ከህወሀት አንጃ መወገድ በኋላ ሊከወን የሚገባውን መሠረታዊ ፖለቲካዊ ውጤት የማዋለድን እድል አስቀድሞ የሚዘጋ ነው፡፡ ምክንያቱም ውጤቱ ከህጋዊነት አልፎ ፖለቲካዊ አንድምታ ካነበረ ወልቃይትን ጨምሮ ብዙ መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ ሊያገኙ ነው፡፡ ስለዚህ ወጣቱን ከማገድክ በኋላ ጉዳዩን የጁንታ እና የሕግ ጉዳይ ብቻ ታደርገዋለህ፡፡ ይሄ ከአቢቹ የሚጠበቅ ቀጣፊነት ነው፡፡
ቀድሞውንም ቢሆን አቢቹ የህወሀት፣ የፖለቲካ ማደጎ፣ የልብ አፍቃሪ እና አስቀጣይ ነበር፡፡ በለውጡ ማግስት ለቃቅሞ ማሰር እየቻለ ህወሀት ትግራይ ከትሞ እንዲያገግም፣ መርዙን ለአዲስ ትውልድ እንዲያሰርጽ እድል ሰጠው፡፡ በዘረፉት እንዲጦሩ በመፍቀድ በሀገር የፍትህ ሚዛን ላይ ቀለደ፡፡ ሲቀጥል ወደገባበት ጦርነትም ቢሆን የህወሀት ሰይጣናዊ ተግባር ከእቅዱ ውጪ ስለሄደበት ነው እንጂ መዋጋት ፈልጎ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ህወሀት አልጨበጥ ብላው ነው እንጂ በአብሮነት የውርሰ ጥፋቱን መርዝ በማስቀጠል ለፍሬ ለማብቃት ይፈልግ ነበር፡፡ በመሆኑም እየተካሄደ ያለው ጦርነት መንታ ኪሳራ እያስከተለ ነው፡፡ አንድም በለውጡ መባቻ ሰሞን በቀላል መስዋእትነት የወያኔን አንጃ ለፍርድ አቅርቦ የዝርፊያ ተቋሞቹን መውረስ ሲገባ፣ ይህ ባለመሆኑ አሁን ለተገባበት ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ሀገሪቱን ዳርጓታል፡፡ ሁለተኛ ዘግይቶም ቢሆን ከባድ መስዋእትነት የተከፈለለት ዘመቻ ተገቢውን ሀገራዊ ፍሬ እንዳያፈራ እና ውጤቱ ሥልጣንን የማስጠበቅ፣ የጁንታ እና የሕግ ጉዳይ ብቻ እንዲሆን እየተሠራበት ነው፡፡ ይኸውም ህወሀትን ከህወሀት አድኖ ከእነ መርዘኛ እሳቤው አሸጋሽጎ ለማስቀጠል ከታለመው የአቢቹ ስረ-መሻት ይመነጫል፡፡
ለመሆኑ አቢቹ ለህወሀት በዚህን ያህል መጠን የሳሳለት ለምንድ ነው? 1ኛ የዘውግ ብሄርተኛውን የፖለቲካ አሰላለፍ የማስጠበቅ ውስጠ ወይራነት ነው፤ በህወሀት እና በነአቢቹ(በኦነጋውያን) ፖለቲካ ባጠቃላይ ከሥልጣን ተቀናቃኝነት ያለፈ አንዳች ልዩነት የለም፡፡ ሁሉም የሚቀዱት የኢትዮጵያዊነት ስሪትን ከሚጸየፍ የጥንተ ጠላት ተሰናሳይ ዥረት ነው፡፡ ይኸውም አውነትን አጣማሚ እና ሁሉን ለፖለቲካ መሣሪያነት ከሚሰዋ ሌኒኒስታዊ፣ ዘውጋዊ እና የጨቋኝ ተጨቋኝ ርእዮት ዓለም ነው፡፡ የአቢሲኒያን(ግዮናዊነት) ፖለቲካ አዳክሞ የማቆየት ፍላጎትን በውስጡ የጸነሰ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ህወሀት ከነመርዘኛ እሳቤው ከተወገደ የትግራይ እና የኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው ፖለቲካ በሕዝብ ለሕዝብ፣ በአዲስ ምእራፍ እና በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ዳግም በመሰባሰብ የፖለቲካ አሰላለፍ ለውጥ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ለዘውግ ብሄርተኛው በተለይም ለኦነጋዊ የፖለቲካ አሰላለፍ ቁልፍ ማምከኛ ኃይል የሚፈጥር ነው፡፡ አቢቹ ለህወሀት ያለው ስስት በአቢሲኒያውያን መካከል የተተከለውን የጸብ ግድግዳ ለማስቀጠል እና አልፎም የትግራይን ፖለቲካ የኦነጋውያን መጋቢ አድርጎ በማቆየት በሁለት መንታ ለማትረፍ የተሰላ ነው፤ አንድም ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛውን ለማዳከም ሲሆን ሁለተኛ ኦነጋውያንን ለማፋፋት ይረዳል ከሚል እሳቤ ነው፡፡ ለዚህ ነው የአማራ ልዩ ኃይል በትግራይ በሚካሄደው ዘመቻ ዋና ተጋፋጭ ነገር ግን ከውጤቱ እንዳያተርፍ እየተሴረ ያለው፡፡ ዘመቻው ሲጀመር ጀግናው የአማራ ልዩ ኃይል ሲል የነበረው አቢቹ ቆየት ብሎ ዘመቻው ጁንታን ለሕግ ከማቅረብ የዘለለ ህወሀትን በምልአት መደምሰስም ሆነ ወልቃይትን(በአብይ አጠራር ምእራብ ትግራይ) የማስመለስ አላማ እንደሌለው የነገረን፡፡ ይህ የሚያመለክተው በአቢሲኒያውያን ፖለቲካ መካከል በወያኔ የተተከለውን የጠብ ግድግዳ ለማስቀጠል ጸብ የሚጭር እና በአንጻሩ የትግራይን እና የኦነጋውያንን የዘውግ ፖለቲካ አሰላለፍ ከጸቡ አትርፎ እንዲጸና ከመሻት ይመነጫል፡፡ ስለሆነም ጥያቄው ያለው ህወሀት መወገዱ ላይ ሳይሆን በማን፣ እንዴት፣ በምን ያህል መጠን እና መቼ ይወገድ እና ከመወገዱ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው ምን ያተርፋል የሚለው ላይ ነው፡፡
በአቢሲኒያውያን መካከል የተተከለው የጸብ ግድግዳ በዋናነት የወልቃይት እና ራያ ጉዳይ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ በወልቃይት ላይ ለ27 አመት ሙሉ በወያኔ የተፈጸመው ሰቆቃ ወደር የማይገኝለት የዘር ማጥፋት እና ማጽዳት ተግባር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ወልቃይት ከጥንት ጀምሮ በጎንደር ክፍለሀገር ስር የነበረ መሆኑም በአያሌ ማስረጃዎች የተረጋገጠ እና በትግራይ ኤሊቶች ጭምር የተመሰከረ ነው፡፡ በወልቃይት ውስጥ አማራና ትግሬን ጨምሮ ሌሎች ማንነቶችም ለዘመናት ተዋህደው መኖራቸውንም ሆነ ለወደፊቱም አብሮነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሕዝብ አለመኖሩም እሙን ነው፡፡ ሰንኮፉ ያለው በወያኔ እኩያ ፖለቲካዊ ውሳኔ ወልቃይትን በጉልበት ከአንዱ ቆርሶ ለአንዱ መስጠት፣ የአማራውን ዘር አጥፍቶ የሌላውን በማስፈር የሕዝብ አሰፋፈር ቅየራ ውስጥ መገባቱ ላይ ነው፡፡ በመሆኑም የወልቃይት ጉዳይ ይደር የማይባል የማንነት እና የህልውና ትግል ሲሆን ግቡም የወልቃይትን ህብራዊነት ለማስመለስ እንጂ ወያኔ በሄደበት መንገድ ለመበቀል አይደለም፡፡ ሆኖም ግን በአቢቹ በኩል የሚኖረው ምላሽ አሉታዊ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ ምክንያቱም ወልቃይትን ሕዝብ ለሕዝብ መተማመን ላይ የተመሠረተ ፍትሀዊና ዘላቂ መፍትሔ ካገኘ በአቢሲኒያውያን መካከል የጠብ ግድግዳ የማስቀጠሉን የኦነጋውያን ስሌት ስለሚያከሽፍ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ የወልቃይት ጉዳይ የአማራውን ብሎም የኢትዮጵያዊ ብሄርተኛውን ፖለቲካ የአላማ መዛነፍ በማያስከትል መልኩ፤ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው የዘር ፌደራሊዝምን ከመቀልበስ ትግሉ ጋር በማይቃረን መልኩ፣ ብሎም በአቢሲኒያውያን መካከል የተተከለውን የጠብ ግድግዳ አፍርሶ በአብሮነት ለመቆም በሚያስችልና፣ ወሳኝ የፖለቲካ አሰላለፍ ለውጥ በሚያስከትል መልኩ መፍትሄ እንዲያገኝ መታገል ለኢትዮጵያ ፖለቲካ በጣም ወሳኝ አንድምታ ይኖረዋል፡፡
2ተኛ የሽግግር ፍትህን አድበስብሶ ለአስቀጣይነት ፖለቲካ መሰዋት፤ ለውጡ ሊያሳካቸው ከሚገቡ አንኳር ትሩፋቶች አንዱ የሽግግር ፍትህን ማስፈን ነው፡፡ በተቃራኒው እየሆነ ያለው ግን የሀገሪቱን የፍትህ ሚዛን ያዛባ፣ ማልያ ቀያሪ ወንጀለኞችን ለዳግም ሹመት እና ዘረፋ እድል የሰጠ ከባድ የታሪክ ጠባሳ የሚያሳርፍ ተግባር ነው፡፡ የሽግግር ፍትህ አጠቃላይ ኢህአዴግን በሚመለከት የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶችን መውረስ/nationalize ማድረግን፣ ወንጀለኞችን በሚገባ አንጥሮ እንደየጥፋት መጠኑ በይቅርታ፣ ከሲቪል መብት መታገድ እና ለቅጣት መዳረግ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ነገር ግን በዳግማዊ ኢህአዴግ በኩል “በለውጥ” ሂደቱ የሽግግር ፍትህን ማንበር እራስን እንደማጥፋት ያለ ውጤት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡ አንደኛ ከላይ የተብራራውን የኦነጋውያን እና የወያኔ ተሰናሳይ የዘውግ ፖለቲካ አስቀጣይነት ከመዋቅር መንግሎ ሊያዳክመው እና ቅራኔ ውስጥ ሊከተው ይችላል ከሚል ስጋት የሚመነጭ ሲሆን፤ ሁለተኛ ተሸጋሻጊዎቹን(ተደማሪዎቹን) ኦህዴድ እና ብአዴንን በሽግግር ፍትህ ቁና ለመስፈር መሞከር ተደማሪዎች በለውጡ ላይ እምነት እንዳይኖራቸው ያደርጋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የብልጽግና እና የአቢቹ የእርካብ እና መንበር መሰላል መነቃቀል ይጀምራል፡፡ ስለዚህ መፍትሄው ህወሀትን ጨምሮ አጠቃላይ ኢህአዴግን በሽግግር ፍትህ ወንፊት ከማበጠር ነጻ የማድረግ እና አለባብሶ የማረስ አማራጭ ውስጥ መግባት ሆነ፡፡ ይህ ደግሞ አለባብሰው ቢያርሱ በአረም… የመመላለስ ቁልቁለት ውስጥ ዘፍቆናል፡፡
መቋጫ፤
አሁን ላለንበት አዘቅት የዳረገን ስርነቀል አብዮት በማይገባው ስርአት ላይ አብዮት ማድረጋችን እና በአንጻሩ ስርነቀል አብዮት የሚያስፈልገውን የወያኔ ስርአት አለባብሰን ለማስቀጠል መዋተታችን ነው፡፡ ከንጉሡ ስርአት ወርሰን ማስቀጠል የሚገባንን ቱባ፣ መሠረታዊ የኢትዮጵያዊነት ውሃልክ የሆኑ፣ እና የኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው እሴቶችን እና ተቋማትን አውድመን ስናበቃ፤ በአሁን ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን የሸረሸ እና ያዋረደ የወያኔ ስርአትን በአንጻሩ ስርነቀል ለውጥ እንዳይፈጸምበት በለውጥ ሽፋን ለውጥን የሚከላከል ስርአት ወደማንበሩ እየተንደረደርን ነው፡፡ መፍትሄው በፖለቲካ ሽግግራችን ውስጥ መንቀል እና ማስቀጠል ያለብንን አንኳር እሴት አንጥሮ ሲያበቁ በመልካም እሴቶቻችን ላይ የተመሠረተ ዘለቄታዊ ሕዝባዊ ስርአት ማዋለድ እና እራስን መሆን ነው፡፡
(በቃሉ ሰው መሆን፤ የሕግ ባለሙያ)
Email = [email protected]
(በቃሉ ሰው መሆን፤ የሕግ ባለሙያ)
Email = [email protected]
እሴቶቻችን ላይ የተመሠረተ ዘለቄታዊ ሕዝባዊ ስርአት ማዋለድ እና እራስን መሆን ነው፡፡