ክብር ለእነ ተመስገን ገብሬ
ጣልያኖች እየጠሩ ከሚወስዷቸዉ ሰዎች መካከል ሆኘ ተወሰድኩ። ከሰዉ መሀል ጠርተዉ ወስደዉ መረሸን ልማዳቸዉ ስለነበረ ወደ ሞት እየሄድን እንደሁ ታዉቆኛል። የተቆፈረ ጉድጓድ አፋፍ ስር ቁመናል። ከጀርባችን ደግሞ አናታችን ላይ አፋቸዉን አነጣጥረዉ የተደቀኑ መድፎች አሉ። እስከዛሬ ሰዎች ሲገደሉ አይቻለሁ። አሁን ተራው የእኔ ነው። ሞት ምን ይመስል ይሆን? መድፎች ተናገሩ፤ ተተኮሰ። ወደ ጉድጓዱ ወደቅን። መድፉ ብዙዎችን የገደለ ቢሆንም እኔ ግን አልተመታሁም። ሲጨላልም ከወደቅኩበት ጉድጓድ ወጥቼ አመለጥኩ” በዚህ ቅፅበት ከመረሸን የተረፈው አርበኛ፣ ደራሲ፣ ጋዜጠኛ እና ባለቅኔው ተመስገን ገብሬ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ፋሽስት ጣሊያን በአዲስ አበባ ላይ የፈፀመውን የግፍ ጭፍጨፋ በአይኑ አይቶ ፅፏል።
ሰላሳ ሺህ የአዲስ አበባ ኗሪዎችን ጭፍጨፋ ተመልክቶ ታሪክ ከማጋራቱም በላይ እስከ መጨረሻው ታግሎ ኢትዮጵያን ከጣሊያን ወረራ የታደገ አርበኛ ነው። ተመስገን ገብሬ፣ አብርሀ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶምን ጨምሮ ለሀገራች ሉዓላዊ ክብር ለታገሉ እና ለተሰው ጀግኖች አባቶቻችን ክብር ይገባቸዋል። የፕየሞንቴው መስፍን የጣሊያን መንግሥት አልጋ ወራሽ ባለቤት በመውለዷ በአዲስ አበባ ገነተ ልዑል ግቢ ውስጥ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ድግስ ተደግሷል። ሕዝቡም ተሰብስቧል። ግራዚያኒ ሰገነቱ ላይ ንግግር እያደረገ በነበረበት ሞገስ አስገዶም እና አብርሀ ደቦጭ አከታትለው የእጅ ቦምብ ወረወሩ። ከግራዚያኒ በተጨማሪ ሌሎች ሹማምንት ሁሉ ቆሰሉ። ለዚህም የተመስገን ሚና ከፍተኛ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። ከዚህ ቀጥሎ ኮንቴ በተባለው የጣሊያኖች አለቃ ትዕዛዝ ሕዝቡ ተጨፈጨፈ። የተመስገን ገብሬ ትግል፣ የአብርሀ ደቦጭና የሞገስ አስገዶም ጀግንነት የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት ነው። በአድዋ ድል ሽንፈትን ለተከናነበው ጣሊያን ዳግም ውርደት ሆኗል። ይህንን ታሪክ በመዘከር የሀገር ፍቅርን እና አንድነትን ከአባቶቻችን እንድንማር ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ያሳስባል።